“ወጣቱ በሠላማዊ መንገድ ሥልጣንን መንጠቅ አለበት”

Wednesday, 22 November 2017 12:25

ወጣቱ በሠላማዊ መንገድ ሥልጣንን መንጠቅ አለበት

ሜጀር ጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖት

 

በይርጋ አበበ

 

የህወሓት ታጋይና በኋላም የአየር ኃይል አዛዥ የነበሩት ሜጀር ጄኔራል አበበ ተ/ሃይማኖት ከአየር ኃይል አዛዥነታቸውና ከህወሓት/ኢህአዴግ አባልነታቸው ራሳቸውን ካገለሉ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ሆነው ቆይተዋል። በኋላም በጡረታ ተገልለዋል። ኢህአዴግ ሥልጣን መልቀቅ የነበረበት በ1987  ዓ.ም ነበር። ሆኖም ሁልጊዜም እኔ አውቅልሃለሁ በሚለው አመሉ እሥካሁን ሥልጣን ላይ ቆይቷል ሲሉ ይናገራሉ። በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ሰፋ ያለ ቃለምልልስ አድርገዋል። ይህንንም ቃለምልልስ ለአንባቢያን በሚመች መልኩ አዘጋጅተን አቅርበነዋል።

 

ሰንደቅውይይታችንን በወቅታዊ ጉዳይ እንጀምር። አገራችን የምትገኝበት ፖለቲካዊ ሁኔታ እንዴት ያዩታል?

ጄኔራል አበበ- ጠቅለል አድርገን ስናይ ሁለት ነገሮችን እናገኛለን። የመጀመሪያው ወቅታዊ ጉዳይ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ መሠረታዊ የሕገ-መንግሥት ጉዳይ አለ። ሕገ-መንግሥት በእኔ አመለካከት የኢትዮጵያን የሰላም፣ የዴሞክራሲ እና የልማት ጉዞ የቀየሰ ሕገ-መንግሥት ነው። ለኢትዮጵያም የሚበጃት አሁን ያለው ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ነው። ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ ችግር የለበትም። ችግር ያለበት በፖለቲካው የመንግሥት ሥርዓቱ ነው። ይህ ችግር ደግሞ መሠረታዊ የዴሞክራሲ ችግር ነው። የዴሞክራሲ ችግር ባይኖርበት ኖሮ አሁን ያለው ፖለቲካዊ ቀውስ አይታይም ነበር።

በነገራችን ላይ የፖለቲካ ቀውስ የሌለበት አገር ያለ አይመስለኝም። በአውሮፓም ሆነ በአሜሪካ አለ። ልዩነቱ እነሱ ያለው የቀውሱ ደረጃ እና ቀውሱ የሚፈታበት መንገድ ነው። በእነሱ የችግር መፍቻ ተቋሞች አሉ። እኛ ግን እንደዚህ አይነት መሠረታዊ የሕዝብ ጥያቄዎች በሚነሱበት ጊዜ መልስ ሊሰጡ የሚችሉ ተቋሞች የሉንም።

ሰንደቅቀውስ መፍቻ ተቋማት የሚሏቸው የዴሞክራሲ ተቋሞች የሚባሉትን ነው፤ የሲቪክ ማኅበራትን?

ጄኔራል አበበ- ሲቪክ ማኅበራትም፣ ፓርቲዎችም፣ ሕግ አውጭውም፣ ሕግ አስፈፃሚውም ሆነ ሕግ ተርጓሚውም እነዚህ በሙሉ እየሰሩ አይደሉም። ስለዚህ የሕዝቡን ፍላጎት ለመመለስ የሚያስችል ሁኔታ የለም። የሕዝብን ጥያቄ በሰላም መፍታት ስላልተቻለ ነው ሕዝቡ ወደ ኃይል እየሄደ ያለው። በመሆኑም አሁን ያለው ፀረ-ዴሞክራሲ አያያዝ ካልተፈታ ወደ ትልቅ ችግር ነው የምናመራው። ነገር ግን ይህን ወቅታዊ ቀውስ ወደተሻለ ደረጃ መቀየር የሚቻልበት ዕድል አለ ብዬ አስባለሁ።

ከዚህ በፊትም ኢትዮጵያ ውስጥ ቀውሶች ነበሩ። ነገር ግን አሁን ያለውን ቀውስ የፌዴራል ሲስተሙ የፈጠረው እንደሆነ ሲናገሩ እሰማለሁ። በደርግ ጊዜ ሁሉ ጦርነት ሲካሄድ የፌዴራል ሥርዓት ስለነበረ አይደለም፤ ሁሉ ሕዝብ ያለቀው። አሁን ያለው ችግር የተፈጠረው በፌዴራል ሥርዓቱ ሲስተም ሳይሆን የግለሰብና የቡድን መብት ባለመከበሩ ነው።

ሰንደቅየፌዴራል ሥርዓቱ የአንድነታችን መሠረት ነው ተብሎ በተደጋጋሚ ቢነገርም፤ ቋንቋን መሠረት ያደረገው የአገሪቱ የፌዴራል ሥርዓት ግን በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚነሱ ግጭቶችን የብሔር መልክ እያላበሳቸው ይገኛል። ለዚህ ደግሞ ችግሩ የፌዴራል ሥርዓቱ ሥረ-መሠረት ያደረገው ዘውግን በመሆኑ ነው ይባላል። እውን የቀደመው ሀሳብዎ ለዚህ መልስ አለው?

ጄኔራል አበበ- በእርግጥ የከፋ ጦርነት የነበረው በደርግ እና በኃይለሥላሴ ዘመን ነው። ጦርነቱ የተከናወነውም ብሔሮችና ብሔረሰቦች ተደራጅተው የሚያካሂዱት ነበር። ለምሳሌ በትግራይ ህወሓት እንዲሁም በኦሮሚያ ኦነግ ያውም እስከመገንጠል የሚሄድ ጦርነት ነበር። አሁን የሚሆነውን ሥንመለከት ግን ዴሞክራሲ በመጥፋቱ የተፈጠረ መሆኑን ነው። ምክንያቱም ማስተንፈሻ የሚሆነው ዴሞክራሲ በመጥፋቱ ሕዝቡ ወደ አላስፈላጊ መንገድ እንዲሄድ ያደርገዋል። ይህዘርንማዕከል ያደረገ ጥቃት አድሃሪ ነው። በጣም መጥፎ ነው።

ግን ይህ ነገር እንዴት መጣ? የሚለው ጥያቄ ሲነሳ፤ ለምሳሌ በኦሮሚያ የነበረውን ግጭት ብናነሳ፤ ሕዝቡ ያነሳውን ጥያቄ የክልሉ ገዥ ፓርቲ ኦህዴድ በሰላማዊ መንገድ መፍታት አልቻለም። ስለዚህ በዚህ መሀል መንገዱ የተሳሳተ ይሆናል። ሰላማዊ በሚሆንበት ጊዜ እና ጥያቄዎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ በሚፈቱበት ጊዜ የትምክህት እና ጠባብነት አመለካከቶች ቦታ አይኖራቸውም። ነገር ግን ተቃራኒው በሚሆንበትና በነፃነት መነጋገር በማይችልበት ጊዜ ወደ አንድ ጫፍ ይሄዳል። ይህ ደግሞ በጣም መጥፎ ነው።

ጥያቄው ይህ ለምን ሆነ? ብለን ሥንጠይቅ ዴሞክራሲ እንዲኖር የሚጠይቀው ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት፤ ዴሞክራሲ ሳይኖር ሲቀር የሚፈጠር መሆኑን ነው። ምክንያቱም ዴሞክራሲ ከሌለ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ፌዴራላዊ ይሁን ወይም ሌላ የከፋ ጦርነት እና ግጭት ይፈጠራል። በደርግ ጊዜ የነበረውን ማየት ይቻላል። በደርግ ጊዜ ሕገ-መንግሥቱም ሆነ ፖለቲካው ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ነበር። አሁን ግን ሕገ-መንግሥቱ ዴሞክራሲያዊ ሲሆን፤ ፖለቲካው ደግሞ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ነው። ስለዚህ ህዝቡ ጥያቄ ያቀርባል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ከሁሉም ፅንፍ ያለው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ውይይት መካሄድ ነበረበት። ግን ደግሞ ማካሄድ አልተቻለም እንጂ ቢካሄድ ኖሮ መፍትሄ ይመጣል። ይህ በማይሆንበት ጊዜ ግን አጋጣሚውን ፅንፈኛው ኃይል ይጠቀምበትና የብሔር መልክ ያላብሱታል።

ሰንደቅእርስዎ በሚሉት የፌዴራል ሥርዓቱ ችግር የለበትም ብለን እንስማማ። ሕገ-መንግሥቱንም ችግር የለበትም ብለን እንቀበል። ነገር ግን የፌዴራል ሥርዓቱንም ሆነ ችግር የለበትም የሚሉትን ሕገ-መንግሥት የመሠረተው የፖለቲካ ሥርዓት ዴሞክራሲን ሰጥቶ ለመቀበል ተፈጥሯዊ ባህሪ አለው?

ጄኔራል አበበ- ይህ የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ (Context) ነው። እኛ ያደግንበት ፊውዳል ሥርዓት ነው። ልጅ በነፃነት ከወላጆቹ ጋር መነጋገር በማይቻልበት ሁኔታ ተቀርጾ ያሳደገን ሥርዓት ነው። ለዴሞክራሲ መታገል አለብኝ እያልክም ቢሆን ብዙ እንቅፋቶች ያጋጥሙሃል። በአንድ በኩል በመሪዎች በኩል መሳፍንታዊ አስተሳሰብ አሁንም አለ። በሌላ በኩል ቅድም ያልኩት የተቋማት አለመኖር መሪዎች መስፍናዊ አስተሳሰብ ቢኖራቸው እንኳን የመሪዎችን መጥፎ ባህሪ መግታት ይችሉ ነበር። ለምሳሌ በአሜሪካ ዶናልድ ትራምፕ መጥፎ ባህሪ ቢኖራቸውም ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ስላሉ የትራምፕን ባህሪ መግታት ይችላሉ። ወደ እኛ አገር ስታመጣው እነዛ ተቋማት የሉንም። ይህ ደግሞ በአጭር ጊዜ የምትገነባው አይደለም። የረጅም ጊዜ ሥራ ነው። ይህ በመሆኑም አሁን ወደዛ ለመሄድ ሽግግር ላይ ነን ማለት ይቻላል። ያም ሆኖ ለስልጣናቸው ብቻ የሚያስቡ መጥፎ ሰዎችም አሉበት። ነገር ግን ያደግንበት ማኅበረሰብ እና የደሞክራሲ ተቋማት አለመኖር እነዛን መጥፎ ሰዎች ይገቱ ነበር። አሁን ችግሩ ምን መሰለህ? በሚነሱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሰፋፊ ውይይት አናደርግም። ለምሳሌየትግራይ የበላይነት አለየሚል ነገር አለ። መኖሩም ሆነ አለመኖሩ እኮ በግልፅ ውይይት አይደረግበትም። በድብቅ አለ ይባላል። ነገር ግን የትግራይ የበላይነት መኖሩም ሆነ አለመኖሩ በግልፅ በቴሌቪዥን (ለምሳሌ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን) ግልፅና ዴሞክራሲያዊ ውይይት ቢካሄድበት እውነታው ታውቆ ይታረም ነበር። ነገር ግን ይህ አልተካሄደም። ስለዚህ ሁሉም ኋላ ቀር የሆኑ አስተሳሰቦች ዴሞክራሲያዊ ከባቢ በሚኖርበት ብዙ ጊዜ በኢህአዴግ ጠባብነት እና ትምክህት የሚሉ ነገሮች መልስ ያገኛሉ። ነገር ግን በመጀመሪያ የኢህአዴግ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቡጠላትብሎ መፈረጁ ነው። ጠባብነትና ትምክህት ግን አርሶአደሩም ጋር አለ፣ ላብአደሩም፣ ባለሀብቱም ውስጥ አለ። ከራሱ ከኢህአዴግ ውስጥም አለ። ለዛ ነው ኢህአዴግጠላትሲል እኔ የምጠላው።

ሰንደቅሰውን በአስተሳሰቡ ጠባብና ትምክህት ብሎ በጠላትነት መፈረጅ በራሱ የጠባብነትና የትምክህተኝነት ባህሪ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል?

ጄኔራል አበበ-  ይህ ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት ነው። በጣም ያሳስታል። ምክንያቱም ኅብረተሰቡ ውስጥ ብዙ የማይመቹ አስተሳሰቦች አሉ። እነዚህ አስተሳሰቦች ሲመጡጠላትብለህ ከፈረጅከው ያለህን ጉልበት በሙሉ ተጠቅመህ ትዋጋለህ ማለት ነው። አሁን ግን እሱ አይደለም መሆን ያለበት። አንተ ያላመንክበትን ሁሉጠላትካልከው ጠቅላላ የዴሞክራሲ-የለም ማለት ነው። እሱ ደግሞ ትልቅ ችግር ነው። አሁን ካለንበት ቀውስ ለመውጣት መደረግ ያለበት ሕገ-መንግሥቱን መተግባር ነው። ዓለም ላይ ያሉ መብቶችን ሁሉ ያካተተውን ሕገ-መንግሥት ተግባራዊ አድርገን መወያየት ባለመቻላችን ነው አሁን የገባንበት ቀውስ የተፈጠረው። ሕገ-መንግሥቱን መሠረት አድርገን ተወያይተን ወደ መፍትሄ ካልመጣን ግን የበለጠ አደገኛ ነው የሚሆነው።

ሰንደቅ- ሕገ መንግሥቱ ይከበር ወይም ተግባራዊ ይደረግ ሥንል በውስጡ ያሉት መብቶች ሳይሸራረፉ ይጠበቁ ማለታችን ነው። ከሕገ መንግሥቱ መብቶች አንዱ የመደራጀት ነፃነት ነው። በዚህ አንቀፅ መሠረት   የተደራጁ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አማራጭ ሃሳባቸውን ለህዝብ እንዳያቀርቡ ሰላማዊ ሰልፍ መጥራትን ጀምሮ ሌሎች መብቶች ተጋፈናል። በተለይ  ለአሥር ወር በዘለቀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይህ የመብት ጥሰት ተደርጎብናል  ሲሉ ይናገራሉ። በዚህ መልኩ የተፈለገው ለውጥ መምጣት ይችላል?  

ጄኔራል አበበ- አይመጣም። ግን ምንድን ነው ከአዋጁ በፊትም እኮ ያው የመብት ጥሰት ነበረ። በእርግጥ አዋጁ በወቅቱ የነበረውን ችግር ለመፍታት አስፈላጊ ነበር። ፀረ-ዴሞክራሲያዊ የሆኑ አካሄዶች የነበሩት ግን ከአዋጁ በፊትም ነበር፤ በተለይ 1997 . በኋላ። 1997 . የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ማድረግ እንደሚችል ኢህአዴግ አየ። ከዛ ሁሉም የመንግሥት ተልዕኮ አስፈፃሚዎች (Missionaries) በሙሉ የሕዝብን መብቶች ለመንጠቅ ነው የተጠቀሙበት።

ሰንደቅ1997 ምርጫ በኋላ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ያጠባሉ የተባሉ አዋጆች (የፕሬስ ሕግ፣ የፀረ ሽብር አዋጅ፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አዋጅና የምርጫ ስነምግባር ሕግ) ወጥተዋል ሲሉ ሞጋቾች ያቀርባሉ። በዚህ ሁሉ የኢህአዴግ አመራሮች የጋራ ውሳኔ ሰጭነት ቀርቶ አቶ መለስ ሙሉ በሙሉ በሚያስብል መልኩ ወደፊት የቀረቡበት ጊዜ ነበርም የሚሉ አሉ። ወቅቱን የዴሞክራሲ ብርሃን   የጠፋበት የጨለማ ዓመታት ተብሎ ሊጠራ ይችላል?

ጄኔራል አበበ-  የጨለማ ዘመንየሚለው ተብራርቶ ካልቀረበ አስቸጋሪ ነው። ግን 1997 . አንድ የዴሞክራሲ ብልጭታ ነበር። ክስተቱ አገራችን ወደፊት የምትሄድበት ዕድል ነበር። ነገር ግን ያን ዕድል አጣነው። ዕድል ያመለጠን በኢህአዴግ ብቻ አልነበረም። ተቃዋሚዎችም ዝግጁ አልነበሩም። በእርግጥ ዋናው ተዋናይ ኢህአዴግ ነው። ያን ዕድል በማጣታችን ደግሞ ፀረ-ዴሞክራሲያዊነቱ እየባሰበት መጥቷል። በዚህ መልኩ ከሆነ እየተነጋገርን ያለነው 1997 ክስተት አንድ ትልቅ የብርሃን ብልጭታ ነበር። ግን ያን አጣነው። ነገር ግን ያን አጋጣሚ ከተማርንበት አሁንም ሌላ ዕድል አለን ብዬ አስባለሁ። ህዝቡ በሰላም የጠየቀውን ጥያቄ መመለስ የሚችል ስልጣን በጉልበት መጠየቅ ጀምሯል። ስለዚህ ኢህአዴግ እንዳለፉት ጊዜያት ሕዝቡን እንደፈለገ ማድረግ አይችልም። ቀጣዩ ምርጫም ተስፋ የምናይበት ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ምክንያቱም ኢህአዴግ እንደፈለገው ኮሮጆ የሚሰርቅበት አጋጣሚ ይኖራል ብዬ አልጠብቅም። ስለዚህ ከተጠቀምንበት ቀጣዩ ምርጫ ሌላ የብርሃን ብልጭታ የምናይበት ይሆናል።

ሰንደቅቀጣዩ ምርጫ ሊካሄድ ሁለት ዓመታት ብቻ ናቸው የሚቀረው። አሁን አገሪቱ ውስጥ የፖለቲካው አየር መፋዘዝ ይታይበታል እየተባለም ይነገራል። በዚህ ፖለቲካ አየር ቀጣዩን ምርጫ የዴሞክራሲብልጭታያመጣል ብለን ተስፋ ማድረግ አንችላለን?

ጄኔራል አበበ- አሁን መመዘኛው እሱ አይደለም። መመዘኛው 2008 . ጀምሮ ሕዝቡ ምን እያደረገ ነው የሚለው ነው። 2008 . ጀምሮ እስካሁን ሕዝቡአልገዛምእያለ ነው። ይህ ደግሞ ለዴሞክራሲ መሠረታዊ ጥያቄ ነው። እኔም ተስፋ የማደርገው በዚህ ነው። ኢህአዴግ ይፈልጋል፣ አይፈልግም አይደለም ጥያቄው። አሁን ያለው ሁኔታ ከኢህአዴግ ቁጥጥር ውጭ ስለሆነ ማድረግ ያለበት ብቸኛ አማራጭ የሕዝብን ፍላጎት መስማትና ከእሱ ጋር መሄድ ነው። ይህን ማድረግ ካልቻለ ሕዝቡ እንደማይገዛለት ያውቀዋል፣ አይቶታልም።

ብዙ ሰው የሚመለከተው አሁን የተፈጠረውን የሕዝቡን አልገዛም ባይነት መጥፎ ጎኑን ብቻ ነው። እሱም የብሔር ግጭት የሚመስለውን ብቻ ነው። ነገር ግን ይህ ዘርን ለይቶ ማጥቃቱ ታርሞ የሕዝቡ አልገዛም ባይነት መጀመሩ ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል። አልገዛም የሚል ሕዝብ ማምጣት አስቸጋሪ ቢሆንም፤ ሕዝቡ ራሱ ያመጣው በመሆኑ ኢህአዴግ ሌላ አማራጭ የለውም። ወይ ስልጣኑን መተው፤ አለዚያ ሕዝቡ የሚለውን መስማት ይገባዋል።

ሰንደቅ- በተቃዋሚ ኃይሉ በኩል ያለውን በተመለከተስ?

ጄኔራል አበበ- የረባ ተቃዋሚ እኮ የለም። በእርግጥ የረባ ተቃዋሚ እንዳይኖር አንዱና ዋናው ምክንያት ኢህአዴግ ነው። ኢህአዴግ ይታወቃል፣ ጨቋኝ በመሆኑ ብዙ ነገር አበላሽቷል። በዚህም አሥቸጋሪ ፖለቲካ ፈጥሯል። ከዚህ በተጓዳኝ ግን ራሳቸው ተቃዋሚዎችም የራሳቸው ድክመት አለባቸው። ጠንካራ ተቃዋሚ ሁልጊዜ የሚታገለው በአሥቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ሆኖ እንጂ አልጋ በአልጋ በሆነ ሁኔታ ብቻ አይደለም። በራሳቸው መተማመን የላቸውም። ለዚህም ነው ብዙዎችን ተቃዋሚዎችተቃዋሚዎችአይደሉም የምለው። የተወሰኑ ጠንካራ ተቃዋሚዎች መኖራቸውን ግን አልክድም። እነሱም ቢሆኑም ግን በውስጣቸው ዴሞክራሲያዊ ባህሪ የላቸውም። አይተማመኑም። ምንም እንኳን ኢህአዴግ ገንዘብና ስልጣን ስላለው የፈለገውን ማድረግ ቢችልም፤ ሁልጊዜኢህአዴግ ነው የሚከፋፍለንማለት ከመጀመሪያውም አልነበሩም ማለት ነው። አሁን የተፈጠረውን የሕዝብ ሁኔታ እንኳን መጠቀም አልቻሉም።

በኦሮሚያ እና በአማራ ከተፈጠረው የሕዝብ ተቃውሞ ባልተናነሰ እንዲያውም በባሰ መልኩ በትግራይ ያለው ሕዝብ ወደ አመፅ አልሄደም እንጂ ህወሓትን ከመጥላት አኳያ ሥናየው የበለጠ እንደሆነ ነው። ግን ይህን የሚጠቀምበት ተቃዋሚ የለም። ስለዚህ እንደዚህ ያለ የተመቻቸ ሁኔታ ተቃዋሚዎች ተፈጥሮላቸው ነበር፤ አልተጠቀሙበትም እንጂ። በእርግጥ መንግሥት እየጨቆናቸው ለመሆኑ ጥያቄ የለኝም ግልፅ ነው። ግን ትግል ነው እስካሉ ድረስ ይህን የሕዝብ መነሳሳት መጠቀም ነበረባቸው። በአጠቃላይ በተቃዋሚዎችም ሆነ በኢህአዴግ በኩል ስታየው ፖለቲካችን ውስጥ ያለው ችግር ያመጣው መሆኑን ነው። በመሠረቱ ፖለቲካችን ችግር አለበት።

ሰንደቅበአገሪቱ ከሚንቀሳቀሱ ሰላማዊ ፓርቲዎች አንዱ ኦፌኮ ነው። ይህ ፓርቲ ከሊቀመንበሩ  ር መረራ ጉዲና ጀምሮ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበሩ፣ ዋና ፀሐፊውና ሌሎች አመራሮቹ ታሥረውበታል። ፓርቲው   የመሪዎቹን እሥር ምክንያት የፖለቲካ አመለካከት እንደሆነ ነው የሚገልፀው።በዚህ ሁኔታ ነው ያለሁትየሚለውን ፓርቲ የትግል እንቅስቃሴ መተቸት ተገቢ ነው?

ጄኔራል አበበ- የፖለቲካ መሪዎች መታሰር በትግሉ ላይ ተፅዕኖ የለውም ማለቴ አይደለም። ግን አንድ ወይም ሁለት አመራር ታሰሩ ብሎ ትግል ማቆም ከመጀመሪያውም ድርጅቶቹ አልነበሩም ማለት ነው። እንደነገርኩህ መንግሥት ጨቋኝ (Impressive) ነው። ግን በዚህ ጨቋኝ ሥርዓት ውስጥ ሆነህም መታገል እስከመረጥክ ድረስ ልታደርግ የምትችለው የተፈጠረልህን የሕዝብ ድጋፍ ተጠቅመህ መታገል ነው። ኦፌኮ ያልከው ፓርቲ እኮ ኦሮሚያ ውስጥ ሁሉ ሕዝብ በመንግሥት ላይ አልገዛም ብሎ ተነስቶለታል። ሕዝቡ እኮ አምጿል፤ እንዲያውም አንዳንድ ቦታማ ጠብመንጃ እስከማንሳትም ደርሷል። ስለዚህ ፓርቲው ጠንካራ ከሆነ ምንም እንኳን መሪዎቹ መታሰራቸው ቢጎዳቸውም ይህን እድል በሚገባ መጠቀም አለባቸው። በእርግጥ በዚህ መሀል ብዙ ወጣት ምሁራን በመታየታቸው እነዛን ወጣቶች በማቀፍ መሥራት ይቻላል። ዴሞክራሲያዊ የሆነውን ሕገ-መንግሥት መሠረት አድርገን ሕዝቡ ውስጥ ከሰራን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማሸነፍ እንችላለን። በደርግ ጊዜ ይህ አይቻልም ነበር። ምክንያቱም ሕገ-መንግሥቱ በራሱ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ነበር።

አሁን ምንድነው መሰለህ? ይህ የእኛ ትውልድ ያበቃለት የሞተ ትውልድ ነው። ላለመሞት ይንገዳገዳል እንጂ የሞተ ትውልድ ነው። አሁን ከላይ ያሉት ህወሓት ውስጥ ያሉት አመራሮች ለምሳሌ ላለመሞት ይንገዳገዳሉ እንጂ  የሞተ ትውልድ ነው። ሰው ሲሞት ከመሞቱ በፊት ይንፈራገጣል አይደል? በዛ ትውልድ አመራር እየሆነ ያለውም ነው። ስለዚህ በአገራችን እየሆነ ያለውን በተመለከትን ጊዜ ሊያድናት የማችለው ወጣቱ ብቻ ነው። ግን ደግሞ ወጣቱ አልተደራጀም። ሽማግሌውም አልቻለም፤ ወጣቱም አልተደራጀም በዚህ መሀል ፖለቲካዊ ቀውስ አለ።

ስለዚህ በተለይ ወጣቱ ምሁር በደንብ መዘጋጀትና መደራጀት አለበት። በተወሰነ ደረጃም ኦሮሚያ ውስጥ የሚታየው እሱ ነው። አሁን የኦሮሚያ ፕሬዝደንት አቶ ለማ የሚናገረው ነገር ወደ ተግባር ሲቀየር ምን ሊሆን እንደሚችል በኋላ የሚታይ ቢሆንም  ምርጥ ምርጥ የሆኑ ሃሳቦች ያቀርባል። ፕሬዝደንት ለማ የሚያቀርበውን የመሰለ ሃሳብ እኮ ሌሎቹ አያቀርቡም። ሌሎቹ እኮ በራሳቸው ግምገማ፤ በራሳቸው ጥልቅ ተሃድሶ በሚሉት ወንጀለኛ አስተሳሰብ ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ገብተው ነው የወጡት።

የአቶ ለማ አስተሳሰብ በተግባር ስናየው ሌላ ሊሆንም ይችላል ወይም ደግሞ ጥሩ ሊሆን ይችላል። መለካት የምንችለው በአሁኑ አቋሙ ስለሆነ ወጣቱ ትውልድ ይህችን አገር ይምራት ለምለው ሃሳቤ እሱ ምልክት ነው።

ሰንደቅከወራት በፊት በትግርኛ ከሚታተም መፅሔት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ወጣቱ ምሁር ካረጀው አመራር ላይ በስልት ስልጣኑን መረከብ አለበት ብለው ነበር። በዚህ ሀሳብዎ ላይ የሚነሱ አስተያየቶች አሉ። ሃሳብዎ ሥርዓቱ ታድሶ እንዲቀጥል ነው? በሌላ በኩል ደግሞ በስልት ስልጣኑን መንጠቅ ሲባል እንዴት ነው የሚነጥቀው?

ጄኔራል አበበ- ጥያቄው እኮ የትኛው ነው የሚታደሰው? የሚለው ነው። በነገራችን ላይ ተሃድሶ የሚለውን ነገር ኢህአዴግ አጨማልቆታል፤ አልወደውም። እኔ የምለው ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ እንዲጠናከር ነው። የሚያጠናክረው ደግሞ የዴሞክራሲያዊ ትውልድ ነው። የእኛ 60ዎቹ ትውልድ የፊውዳል አሥተሳሰብ እና ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ይዞ በመሃል እየጠፋ ያለ ትውልድ ነው። አሁን ያለው ትውልድ ግን ቢያንሥ ስለዴሞክራሲ ገና ከመጀመሪያ ደረጃ ጀምሮ ተምሯል። ስለ ሕገ-መንግሥት ያውቃል፤ የአሜሪካን ምርጫ ያያል፤ የሌሎች አገራትንም ያያል። በእኛ አገርም ቢሆን ችግር ቢኖርበትም እንኳን ምርጫ ያያል። ችግር ቢኖርበትም እዚሁ አገርም ጋዜጦች አሉ። ቴሌቪዥን ያያል። በዚህ መልኩ ነው ያደገው። በእኛ ጊዜ ግን ይህ ሁሉ አልነበረም። እኔ ራሴ ከመቀሌ ከመጣሁ በኋላ ነው ቴሌቪዥን ያየሁት።

ይህ ትውልድ ግን ገና ሲያድግ ሳይፈልገው ነው ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ እየገባበት ያደገው። ይህ ትውልድ ገና ስላልተደራጀ ችግር አለበት።  ለመደራጀት ትንሽ ጊዜ ያስፈልገዋል።

ይህ ሥርዓት ይታደሳል፣ አይታደስም? የሚለውን ለማየት የሚታደስ እንኳን ቢሆን ሊታደስ የሚችለው በወጣቱ ትውልድ እንጂ አሁን ባሉት ኋላ ቀር ሽማግሌዎች አይደለም። ይህ ችግር ከህወሓት ብቻ ሳይሆን ከብአዴንም ያለ ነው። በአንፃራዊነት ደኢህዴን እና ኦህዴድ ትንሽ ይሻላሉ። እዛም እዚህም ቢሆን የሚታደሰውና ይህችን አገር የሚያድነው ወጣቱ ትውልድ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ስልጣንመንጠቅሲችል ነው። ስልጣን ላይ ያለ ሰው ስልጣኑን አይሰጥም። ስለዚህ ወጣቱ ስልጣኑን መንጠቅ ነው ያለበት። ካልሆነ ግን በልመና አይሰጠውም።

አሁን ባለው ሁኔታ ወጣቱ ስልጣኑን ከሽማግሌዎች ላይ በሰላማዊ መንገድ መንጠቅ የሚችልበት ምቹ ሁኔታ አለ። ምንም እንኳ ወደተሳሳተ መንገድ ሊያመራ የሚችል የሕዝብ አመፅ ቢኖርም፤ ሕዝብ አልገዛም ማለት በመጀመሩ ይህን እድል መጠቀም ይችላል። በእርግጥ እንደነገርኩህ በአንዳንድ አካባቢዎች የሕዝቡ አመፅ ከጎኑ ያሉ ሌሎች ኢትዮጵያውያንን እየጎዳ ነው። ይህ ክስተት አካሄዱ ሥህተት ቢሆንም፤ በአጠቃላይ ሲታይ ግን ሕዝቡ ጠያቂ እየሆነ መሆኑን ያሳያል።

ሰንደቅሥልጣን ላይ ያለው ነባር አመራር ዴሞክራሲያዊ አይደሉም እያሉንነ ው። ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ የሌለው አመራር ዴሞክራት የሆነ ተተኪ ወጣት ሊያፈራ ይችላል ብሎ መውሰድ ይቻላል?

ጄኔራል አበበ- ምን መሰለህ በእቅድ አይደለም፤ በአጋጣሚ (Default) ነው። ደጋግሜ እንደነገርኩህ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ሕገ-መንግሥት አለ። በሕገ-መንግስቱ መሠረትም ፓርቲዎች ሲቋቋሙ ታያለህ። ወጣቱ ከመጀመሪያ ደረጃ /ቤት ጀምሮ በሲቪክስና የሥነምግባር (ሥነዜጋ) ትምህርት ስለ ዴሞክራሲ፣ መብት እና ፖለቲካ ተምሯል። ከዛ ባይማር እኮ በዕለት ተዕለት ህይወቱ የሚታየው አስተምሮታል። 1997 . ምርጫ አንድ ትልቅ አስተማሪ ነው። ምንም እንኳ ትንሽም ቢሆን ሰንደቅን ጨምሮ ሪፖርተር፣ አዲስ አድማስ ጋዜጦች አሉ። ከእነዚያ እያነበበ ወጣቱ ይማራል። ለዚህ ነው በእቅድ (Design) አይደለም በዲፎልት ነው የምልህ። በዲዛይን ቢሆንማ አይወድቅም። ኢህአዴግ ሳያስበው የሠራቸው ብዙ መልካም ሥራዎች አሉ። ለምሳሌ ጥራታቸው ላይ ችግር ቢኖርበትም ዩኒቨርስቲዎች ተስፋፍተዋል። የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ /ቤቶችም በየቀበሌውና ወረዳው ተከፍተዋል። ሌሎች መሠረተ ልማቶችም እንዲሁ። እሱ (ኢህአዴግ) በሄደበት መንገድ የማይሄድ ደሞክራቲክ ትውልድ እየተፈጠረ ነው።

ሁልጊዜ አንድ አመራር ወይም መንግሥት ሲያረጅ የሰራውን ጥሩ ሥራ እያበላሸ ይሄዳል። ለምሳሌ ድህነትን በመቅረፍ አኳያ ኢህአዴግ ጥሩ ነገር ሰርቷል። ይህ ግን ከሕዝቡ ጋር ካልሄደ መቃብሩ ነው የሚሆነው። ምክንያቱም ኢህአዴግ ቢፈልግም ባይፈልግም ዴሞክራቲክ ማኅበረሰብ እየተፈጠረ ነው። ኢህአዴግ ከዚህ ለውጥ ጋር መራመድ አቃተው። ይህ ደግሞ ተፈጥሯዊ ነው። በእኔ አመለካከት ኢህአዴግ እስከ 1987 . ብቻ ነበር አገርን የማስተዳደር ኃላፊነቱን የተወጣው። ከዛ በኋላ ማድረግ የነበረበትእኔ አልችለውም የሚችሉት የተማሩት ወጣቶቹ ናቸው፣ ቀስ በቀስ ስልጣኑን ያዙማለት ነበረበት። ግን ድንቁርናም ተጨምሮበት እኔ ሁልጊዜ እችለዋለሁ የሚል ነገር መጣ። ያም ሆነ ይህ ግን አሁን ኢህአዴግ ፈለገም፣ አልፈለገም ይህችን አገር ወደፊት መምራት የሚችል ምሁር አለ። ፈለገም፣ አልፈለገም ኅብረተሰቡ አልገዛም ማለቱን ሊረዳ ይገባል።¾    

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
759 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1059 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us