ከህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ግብፅ እንቅፋት ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰች መሆኑ አነጋገረ

Wednesday, 11 October 2017 13:23

መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሆቴል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ብሔራዊ ም/ቤት ጽ/ቤት በ2010 እቅድና አተገባበር ዙሪያ ከአጋር አካላት ጋር ተሳትፎና ድጋፍ ከማጠናከር አንፃር የምክክር መድረክ አዘጋጅቶ ተወያይቷል።

በሚኒስትሮች ም/ቤት ደንብ ቁጥር 244/2003 ዓ.ም የተቋቋመ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ብሔራዊ ም/ቤት ጽ/ቤት፣ በተቀመጠለት ተልዕኮው መሰረት ምልዓተ ህዝቡ ለግድቡ ግንባታ የሚያደርገውን ሁለተናዊ ድጋፍና ተሳትፎ በማሳደግ ብሔራዊ መግባባቱን በማፋፋት እና በማጠናከር ከፍተኛ ሥራዎች እየሰራ መሆኑን የሥራ ክንውኖቹን በአሀዝ አስደግፎ አቅርቧል።


ኢትዮጵያ ለጀመረችው የሕዳሴ ጉዞ የህዳሴ መሰረት እና የሰላም ምንጭ እንደሚሆን በብዙዎች ዘንድ ተስፋ የተደረገበት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት መሆኑን ከተሳታፊዎች ተንፀባርቋል።


በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የፋይናንስ፣ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ፣ የአካባቢ ጥበቃና ተፋሰስ ልማት ድጋፍ በማጎልበትና የቁጠባ ባህል እንዲያድግ በማድረግ ታሪካዊ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ በማስቻል የሀገራችንን ገጽታ ግንባታና ብሔራዊ መግባባት መግባባትን ያሰፍናል ተብሎም ይጠበቃል።


በሥፍራው በመገኘት ከብሔራዊ ምክር ቤቱ ጽ/ቤት የቀረበውን የ2009 ዕቅድ አፈፃፀም እና በ2010 ቀጣይ እቅዶች ዙሪያ ከቀረቡት ሪፖርቶች በከፊል እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

 

 

ከዲያስፓራ ተሳትፎ እና ከፐብሊክ ዲፕሎማሲ አንፃር


ጽ/ቤቱ ከዲያስፖራ ተሳትፎ፣ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራን እና ዓለም ዓቀፍዊ ድጋፍ ከማጠናከር አንፃር የሰራቸውን ሲያስቀምጥ፣ ከፐብሊክ ዲፕሎማሲ አኳያ ወቅታዊ መረጃዎች ለህዝቡ ማድረስ፤ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አባላት ታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚኖረውን ፋይዳ በተከታታይ ከሚያሳየው ለውጥ ጋር መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም ማስተዋወቅ፤ ስለ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሂደቱ በተለያየ አግባብ መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም ግንዛቤ ማስፋት፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያና ጎረቤት ሀገሮች የሚኖረውን ጠቀሜታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስገንዘብ እና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲኖረው በደንብ የተደገፈ አሰራር ከውጭ ጉዳይ ሚ/ርና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን መስራቱን አስታውቀዋል።


በቀጣይ ጽ/ቤቱ በዚህ ዘርፍ ያለበትን ውስንነት ለመቅረፍ እሰራቸዋለሁ ብሎ ከዘረዘራቸው ሥራዎች በከፊል፣ ወደ ተፋሰሱ ሀገራት ለሚጓዝ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ስለ ህዝባዊ ተሳትፎ የተጠናከረ መረጃ በማደራጀት፣ መረጃውን ጥቅም ላይ እንዲውል ክትትልና ድጋፍ ማድረግ፤ ሀገር ውስጥ ላለው የውጭ ማህበረሰብ በተለይም ኤምባሲዎች፣ አህጉራዊ፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ግለሰቦችን በማሰባሰብ ግንዛቤ ለማሳደግ መድረክ ማመቻቸት፤ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የደረሰበት ደረጃ፣ የግድቡን ጉብኝት፣ ጽ/ቤቱ የሚያከናውናቸው ሁነቶችና ተግባራዊ የሚደርጋቸው ፕሮጀክቶች ወዘተ በመዘገብ ለህዝቡ እንዲደርስ ማድረግ፤ ከግድቡ ጋር የሚነሱ አፍራሽ አዝማሚዎችን በመረጃ በማጋለጥ ህዝቡ ትክክለኛ እውነታውን እንዲያውቅ ማድረግ ይገኙበታል።


አያይዞም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ከማጠናከርና የታላቁ ህዳሴ ግድብ የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ከማስረዳት አንፃር ቡድኑ ወደ ተመረጡ የተፋሰስ አገሮች አለመጓዙ በድክመት ሪፖርቱ አንስቶ፤ በቀጣይ በሀገር ውስጥ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ግንዛቤን ለተለያዩ ማህበረሰብ የማስፋት፣ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ በቀጣይ ወደ ተመረጡ የተፋሰስ አገሮች እንዲጓዝ የማመቻቸት ስራ እንደሚሰራ አስታውቋል።


ጽ/ቤቱ ከዲያስፖራና ከፐብሊክ ዲፕሎማሲ አንፃር ያለውን ስጋት ሳያስቀምጥ አላለፈም። ጽ/ቤቱ እንዳስቀመጠው፣ ከግብጽ እንዲሁም የግብጽ ተላላኪ ኃይሎች በተለያዩ ሚዲያዎች የሶሻል ሚዲያን ጨምሮ የግድቡን ግንባታ ለማደናቀፍ የሚያናፍሱት አፍራሽ አመለካከቶች ዋናው ተግዳሮቶቹ መሆኑን አስቀምጧል።


ጽ/ቤቱ ከዲያስፓራ ተሳትፎ አንፃር በአዎንታዊ ያስቀመጠው፣ ዲያስፖራው የተለያዩ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም አመለካከቶች ያሉበት ቢሆንም አብዛኛው በህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ በተለያየ መልኩ ድጋፋቸውን እየሰጡ መሆኑ ለጋራ መግባባቱ መጠናከር አዎንታዊ አስተዋጽኦ አድርጓል ብሏል። ይሁን እንጂ እንደጽ/ቤቱ አቀራረብ፣ የዲያስፖራው ተሳትፎ በቦንድ ግዢ የሚጠበቀውን ያህል እንዳልሆነ ከተሰበሰበው ገንዘብ መጠን ማየት ይቻላል ብሏል። በመሆኑም ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የየሀገራቱ የፋይናንስ ህግ መሰረት ባደረገ መልኩ የቦንድ ማሰባሰብ ስራውን የሚያጠናከርበት ሁኔታ ላይ በጋራ መስራት አሌ የሚባል አይደለም ብሏል። እንዲሁም የዲያስፖራ ቦንድ መረጃ አያያዝ እና አመላለስ ላይ እየታዩ ያሉ ችግሮች፣ በኢፌዲሪ ውጪ ጉዳይ ሚ/ር፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መ/ቤት መካከል ያለው የቅንጅት ማነስ መሆኑን አስታውቀዋል።


ጽ/ቤቱ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ያለውን አተያይ እንዳስቀመጠው፣ ሀገራችን በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ እያራመደችው ያለው የጋራ ተጠቃሚነት መርህ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ አዎንታዊ ምላሽ እየተሰጠው መሆኑ፣ በተለይ በሁሉም የተፋሰሱ ሃገራት አቋም እየሆነ መምጣቱ ሃገራችን በዲኘሎማሲው ዘርፍ ያስመዘገበችው ድል ተደርጎ እንደሚወሰድ ገልጿል።


ሆኖም ግን እንደጽ/ቤቱ ገለፃ፤ ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እይታ በተፃራሪ ግብጽና አንዳንድ በግብጽ ድጋፍ እየተሰጣቸው የሚገኙ አፍራሽ ሀይሎች የግድቡ ግንባታ ለማስተጓጎል የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ ተስተውሏል። በተጨማሪ የተፋሰሱ አገሮች የትብብር ማዕቀፉን ህጋዊ እውቅና በመስጠት ወደ ትግበራ እንዳይገቡ ግብጽ እንቅፋት ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰች እንደሆነ ለሕዝቡ ይፋ አድርጓል። በመሆኑም በግብጽ መንግስት እየተከናወነ ያለው አሉታዊ እንቅስቃሴ በዲፕሎማሲ ጥረታችን በዋናነት በፍትሀዊና የጋራ ተጠቃሚነት መርህ መሰረት መመከት ይገባል ሲል፤ ማሳሰቢያ ሰጥቷል። በተጨማሪ የአለምአቀፍ ሚዲያ ሞኒተሪንግ ስራ በማጠናከር ለአለምአቀፉ ማህበረሰብ ተደራሽ የሆኑ መረጃዎች በተለያዩ ቋንቋዎች የማዘጋጀትና የማሰራጨት፣ በተፋሰሱ ሃገራት ያሉ ህዝቦች አመለካከትትን በመቀየር ድጋፍ ለማግኘት እንደሚሰራ ጽ/ቤቱ ተናግሯል።

 

በጽ/ቤቱ ክትትልና ድጋፍ ስራዎቻችን ላይ ያሉ ውስንነቶች

 

ጽ/ቤቱ እንደገለጸው፣ ከእቅድ ዝግጅት አንፃር አንዳንድ ተግባራት ተጨባጭ፣ የሚለኩ አለመሆናቸው፤ እንዲሁም በእቅድ ውይይት ሁሉንም ባለድርሻ ማሳተፍ ላይ ውሱንነቶች መኖራቸው፤ በበጀት ዓመቱ የተማሪዎች የታቀደ ጉብኝትና የወ/ሪት ህዳሴ ኘሮጀክት ስራ በበጀትና የሰው ኃይልን ችግር አለመፈጸማቸው እንደ ችግር አንስቶታል።


እንዲሁም፣ የኘሮግራም ተሳታፊዎች፣ ባለድርሻዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችን አስቀድሞ እንዲዘጋጅ ከማድረግ፣ ከማሳሰብ ከመከታተል እና በእለቱ እንዲገኙ ጥሪ በተገቢው ማስተላለፍ ላይ ጉድለቶች አሉብኝ ብሏል።


ጽ/ቤቱ ከውስንነት ያለፉ ስጋቶች እንዳሉበትም ሳይናገር አላለፈም። ይኸውም፣ በገንዘብ ተቋማት የቦንድ ወለድ ለሚጠይቁ እና ጊዜው የደረሰ ቦንድ ለማስተናገድ በበቂ ሁኔታ ዝግጁ ሆነው ያለመገኘት፤ ከህብረተሰቡ የሚገኘው የቦንድ ግዢና ድጋፍ ቃል በተገባው መሰረት በወቅቱና በጊዜው ያለመሰብሰብ እና ባንኮችና ማይክሮ ፋይናንስ ቦንድ ሰርተፍኬት አልፎ አልፎ በወቅቱ ያለመስጠት፣ በዋናነት የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተጠቃሽ ነው ብሏል። እንዲሁም አማራጭ የሀብት ምንጮችን ለመጠቀም የሚያጋጥሙ የአሰራርና፣ የህግ ማዕቀፍ ችግሮች፣ ክልሎችም በዚህ ረገድ ያላቸው ተሳትፎ ቀዝቃዛ መሆኑ በተጨማሪ ስጋትነት አቅርቧል።


ጽ/ቤቱ የመንግስትና የግል ሰራተኞች በቦንድ ግዥ ያላቸው ተሳትፎ 4 ቢልዮን የደረሰ መሆኑን ገልፆ፤ በተለይ በአንዳንድ መስሪያ ቤቶች እስከ 6ኛ ዙር የደረሱበት ሁኔታ መኖሩን አንስቶ ይህን ተሞክሮ በባለሀብቱና አርሶና አርብቶ አደሩ ማስፋት ተገቢ መሆኑን አስምሮበታል። ይሁን እንጂ ሰፊ ህዝባዊ መሰረት ያላቸው አደረጃጀቶች ለአብነት በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ ማህበራትን አነሳስቶ የቁጠባ ባህል እንዲያሳድጉና ለግድቡ ግንባታ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የተደረገው ጥረት ዝቅተኛ መሆኑን አስቀምጧል።


አያይዞም፣ በአጠቃላይ በገጠርና ከተማ የሚገኘው ህዝብ በገንዘብ፣ በዕውቀት የሚያደርገው ድጋፍና ተሳትፎ ከጊዜ ጊዜ እየጨመረ ቢሆንም በተለይ በባለሀብቱ እንዲሁም የሲቪክ ማህበራትና ልዩ ልዩ አደረጃጀቶችን በሚገባ ማሳተፍ ላይ የሚቀር ሥራ መኖሩን፣ እንዲሁም የንግዱን ዘርፍ የሚመሩ ሚ/ር መስሪያ ቤቶች ክትትልና ድጋፍ በሚፈለገው መልኩ አለመሆን እንዲሁም ባለሀብቱ ከንግድ መቀዛቀዝ አንፃር ባለሀብቱን በቦንድ ያለው ተሳትፎ የተጠበቀውን አለመሆኑን ይፋ አድርገዋል።


በተጨማሪም በአንዳንድ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ሥራ አስፈጻሚ ጀምሮ በተገቢው ለእቅድ ግብአት በመስጠት፣ በተግባር ክትትልና ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም የሰው ሃይል መድቦ በወቅቱ እየተገናኙ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች የመስጠት ሂደት ወጣ ገባነት ያለውና በሚፈለገው ደረጃ አለመሆኑ አስታውቋል። ይህም እንደ ሌሎች መደበኛ ሥራዎች እኩል አለማየት ዋናው ችግር መሆኑ በተደረገው የመስክ ምልከታ ማረጋገጡን አስታውቋል።


የኢትዮ - ሶማሌና የጋምቤላ ህዳሴ ግድብ ማስተባባሪያ ጽ/ቤቶች በአሰራርና አደረጃጀት አለመጠናከሩ፣ ከፍተኛ የሎጀስቲክስ እና የሰው ኃይል እጥረት መኖሩ፤ ከባንኮች ጋር ያለው ግንኙነትና የኢንፎርሜሽን ልውውጥ ስርዓት መሻሻሎች ቢታዩም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የቦንድ ጉዳይ የሚከታተል ባለሙያ የማስቀመጥ ሥራ አለመጠናከሩ፤ ባለሀብቱ ቦንድ ለመግዛት ቃል የገባውን መፈጸም ላይ በሚፈለገው መልኩ አለመሆኑ ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው ሲል አክሏል። 

 


  የሕዳሴው ግድብ ክንውን አሃዞች

 • የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ60 በመቶ በላይ ተከናውኗል።

 

 • በ2009 ዓ.ም ከሕዝብ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ተሰብስቧል፤ በአጠቃላይ በ5 አመት ውስጥ 10 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ተሰብስቧል።

 

 • በ2009 ዓ.ም. በአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ሰፊ የአፈርና ውሃ ጥበቃ የተሰራ ሲሆን በጉልበት የተደረገ አስተዋፅዖ 23 ነጥብ 85 ቢሊዮን ብር የሚገመት ነው። ከ2005 ጀምሮ የተደረገው የጉልበት ተሳትፎ 79 ቢሊዮን ብር ይገመታል።

 

 • በ2009 ዓ.ም. ጽ/ቤት 39ሺ ሰዎች ግድቡን ጎብኝተዋል። በአጠቃላይ በ5 አመት ውስጥ 250ሺ ሰዎች ግድቡን ጎብኝተዋል።

 

 • የቦንድ ተሳትፎ 1 ቢሊዮን 273 ሚሊየን 439 ሺ 289 ብር ተሰብስቧል። 72 ነጥብ 28 በመቶ ብር ሊሰበሰብ ችሏል።

 

 • የመንግስትና የግል ሰራተኞች በ5 ዓመት ውስጥ በቦንድ ግዥ ያላቸው ተሳትፎ 4 ቢልዮን ብር ደርሷል።

 

 • ዲያስፖራው 42 ሚሊዮን 242ሺ 684 የአሜሪካን ዶላር በላይ ድጋፍ አድርጓል

 

 • ግድቡ የሀገሪቱ ቁጥባ 22 በመቶ በላይ እንዲያድግ አዎንታዊ ሚና ተጫውቷል።

 

 • ከ2008 እስከ 2009 ዓ.ም. የሕዳሴው ዋንጫ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በነበረው ቆይታ 607 ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዢ እና ልገሳ ተሰብስቧል።

 

 • የሕዳሴው ዋንጫ በደቡብ ክልል ብ/ብ/ ሕዝቦች በነበረው ቆይታ ከብር 968 ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዢና ልገሳ እንዲሁም በቁሳቁስ ልገሳ ማሰባሳብ ተችሏል።

 

 • ከቶምቦላ ሎተሪ 60 ሚሊዮን ብር ማሰባሰብ ተችሏል።

 

 • የባለሀብቱ ቦንድ ተሳትፎ በተመለከተ በድርጅት ከፍተኛው 500 ሚሊዮን ብር እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ 30 ሚሊየን ብር ተሳትፎ ተደርጓል። 

 


የ2009 ዓ.ም ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ አርአያነት ያለው የዜጎች ተሳትፎ

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

1. ወ/ሮ አሰለፈች ጸጋ በከሰልና ፌስታል በመሸጥ የምትተዳደር የሻሸመኔ ነዋሪ ስትሆን 57 ሺ/ሀምሳ ሰባት ሺ/ ብር ገንዘብ ቦንድ በመግዛት ተሳትፎ አድርጋለች።

 


2. ደቡበ ወሎ የምትገኝ ታዳጊ ህፃን የራሷን ዶሮ ለግድቡ ግንባታ በመለገስዋ ዶሮው በጨረታ ተሽጦ 17 ሺ ብር ማሰባሰብ ተችሏል።

 


3. በደቡበ ክልል ወላይታ ዞን የሚገኙ ጫማ ጠራጊዎች/ሊስትሮዎች ለአንድ ቀን ጫማ ጠርገው ያገኙትን ለህዳሴ ግድብ ቦንድ ግዥ አውለዋል።

 


4. በደቡበ ክልል የህግ ታራሚዎች እስከ ሞት ፍርድ የተበየነባቸው ከ2ሺ እስከ እስከ 60 ሺ ብር በግለሰብ ደረጃ ቦንድ በመግዛት ተሳትፎ አድርጓል።

 


5. በደቡበ ክልል አርባምንጭ ከተማ አንዲት ግለሰብ ገንዘብ የሌለኝ ቢሆንም ለሀገሪ ደሜን ልስጥ በማለት ባደረገችው ተሳትፎ ደሟ ለጨረታ ቀርቦ ተሳትፎ አድርጋለች። በመሆኑም ለታላቁ ህዳሴ ግድብ እየተደረገ ያለው ድጋፍና ተሳትፎ በገንዘብ፣ በእውቀትና ሙያ ብቻ ሳይሆን በደምም አሻራ ለማስቀመጥ አኩሪ ታሪክ እየተፈጸመ እነደሚገኝ አብነት ሆናለች።

 


6. አቶ አብርሃም በየየሚባሉና በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊ በልጆቻው ስም 3 ሚሊዮን ብር ቦንድ ገዝተዋል። በእስከ አሁኑም ዲያስፖራው ከ41 ሚሊየን ዶላር በላይ በቦንድ ተሳትፎ አድርጓል። 

 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
626 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

 • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

 • Aaddvrrt5.jpg
 • adverts4.jpg
 • Advertt1.jpg
 • Advertt2.jpg
 • Advrrtt.jpg
 • Advverttt.jpg
 • Advvrt1.jpg
 • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1021 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us