ሽፈራው ሽጉጤ በገዛ ፈቃዳቸው ለቀቁ ወይንስ ተሰናበቱ?

Wednesday, 27 June 2018 13:00

-    ሲራጅ ፈጌሳ ከኃላፊነታቸው ለቀቁ

 

የደኢህአዴን ሊቀመንበር የኢህአዴግ የሥራ አስፈጻሚ ኮምቴ አባል እና ከ60 ቀናት በፊት (መጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም) ለገዥው ፓርቲ ሊቀመንበርነት እና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ዕጩ ተወዳዳሪ የነበሩት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በድንገት በገዛ ፈቃዳቸው ከሥልጣናቸው የመልቀቅ ዜና ትኩስ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ ምንም እንኳን እንደቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በራሴ ፈቃድ ለቅቄያለሁ ቢሉም መልቀቂያቸው ከሰሞኑ ደም አፋሳሽ ግጭትና ቀውስ ጋር በቀጥታ የተገናኛ የመሆኑ ጉዳይ ጸሐይ የሞቀው ሐቅ ሆኗል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ ግጭቶቹን ተከትሎ በደቡብ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ሕዝብን ቀርበው ካነጋገሩ በኃላ አመራሩ ከሥልጣን እንዲለቅ በይፋ ጥያቄ መሰል ማሳሰቢያ ሰጥተው ወደአዲስ አበባ መመለሳቸው አመራሩ ከላይ እስከታች እንዲታመስ ምክንያት እንደሆነ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ይናገራሉ፡፡ የጠ/ሚኒስትሩ ማሳሰቢያ ውስጠ ወይራ ቢሆንም ‘ከግጭቱ ጀርባ የእናንተ እጅ አለበት’ የሚል ግልጽ መልዕክትን የያዘ ነው የሚሉ ወገኖች በርካቶች ናቸው፡፡ ይህን ተከትሎ እነሽፈራው ሽጉጤ በማህበራዊ ሚዲያው ሳይቀር ከፍተኛ ትችትና ስድብ ለማስተናገድ ተገደዋል፡፡ በተለይም እሳቸው እና ምክትላቸው አቶ ሲራጅ ፈጌሳ በፌዴራል ሥልጣን ላይ አዲስ አበባ ተቀምጠው የፓርቲ ኃላፊነታቸውን በሪሞት ኮንትሮል እየመሩ ነው፣ ግጭቱም የተባባሰው ወሳኝ አካል በቅርብ ባለመኖሩ ነው በሚል መረር ያሉ ትችቶች ሲዘንብባቸው ከርሟል፡፡ የውስጥና የውጭ ውጥረቱም አይሎ ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ እስከመወሰን አድርሷቸዋል፡፡

አቶ ሽፈራውም ከኃላፊነታቸው ለመልቀቃቸው በዋነኛነት ሶስት ነጥቦችን አስቀምጠዋል፡፡ አንዱ ለአዲስ አመራር ቦታ ለመልቀቅ፣ በደቡብ ክልል ከተከሰተው ችግር ጋር ተያይዞ የመፍትሔው አካል ለመሆን እና በፌዴራል ደረጃ ሆነው በክልል ወውስጥ ሥራቸውን ለማከናወን አስቸጋሪ ስለሆነባቸው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፤ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከኃላፊነት እንዲነሱ በደኢህዴን ውስጥ የአንበሳ ሚና እንደነበራቸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ያረጋገጡት ነው፡፡ እሳቸው ከተነሱ በኃላ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ተሸቀዳድመው የሊቀመንበርነቱን ቦታ ለመያዝ የሞት ሽረት ትግል አድርገዋል፡፡ አካሄዳቸው ያላማራቸው ጓዶቻቸው ጋር ከፍ ያለ አለመግባባት ተከስቶ እንደነበር ምንጮቹ ይጠቁማሉ። በወቅቱ አቶ ሽፈራው፤ አቶ ሬድዋን ሁሴን ለደኢህአዴን ሊቀመንበርነት በዕጩነት መቅረብ በመቃወም ምክንያቱን ለማስረዳት የሄዱበት ርቀት ትዝብት ላይ ጭምር የጣላቸው እንደነበር ምንጮቻችን ያስታውሱታል፡፡

ይህም ሆኖ አቶ ሽፈራው ወደ ሊቀመንበርነት ሲመጡ ቀላል የማይባል የደኢህዴን አመራር አባላት ደስተኛ አልነበሩም። ይህም ቅሬታ በኢህአዴግ ምክር ቤት ሊቀመንበርነት ምርጫ ላይ ቀላል የማይባሉ የደኢህዴን አባላት አቶ ሽፈራውን በመምረጥ ፈንታ ዶ/ር አብይን በመምረጥ ኩርፊያና ቅሬታቸውን አወራርደዋል።

በኢህአዴግ ምክር ቤት የሊቀመንበርነት ሥልጣን ለመቆናጠጥ እልህ አስጨራሽ ትግል ካደረጉትና አሁን ላለው ጠ/ሚኒስትር መመረጥን አጥብቀው ከታቃወሙት አንዱ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ነበሩ፡፡ እናም በዚህም ምክንያት ግንኙነታቸው ሻክሮ መቆየቱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች አስታውሰዋል፡፡

ይህም ሆኖ የእሳቸው መልቀቅና በወ/ሮ ሙፍሪሂት ካሚል መተካት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በተለይም በሲዳማ እና በወላይታ ሕዝቦች መካከል የሚታዩ አለመግባባቶች ዘላቂ መፍትሔ ያመጣ ይሆን የሚለው በሒደት የሚታይ ነው፡፡

በተያያዘ ዜና ትላንት ማምሻውን ለሕትመት እየገባን በነበረበት ሰዓት በደረሰን ዜና መሠረት የደኢህአዴን ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ከኃላፊነታቸው ተነስተው በአቶ ሚልየን ማቴዎስ መተካታቸው ተሰምቷል፡፡ አቶ ሲራጅ የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ በዶ/ር አብይ ካብኔ የትራንስፖርት ሚኒስትር ሆነው መመደባቸው የሚታወስ ነው፡፡

በተጨማሪም ሜጀር ጀኔራል ደግፌ በዲ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮምሽነር ሆነው የተሾሙ ሲሆን ረዳት ኮምሽነር ሐሰን ነጋሽ እና አቶ ዘልዓለም መንግሥቱ ምክትል ኮምሽነር በመሆን ተሹመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ምክትል ኮምሽነር ግርማ ካሳ ከቅዳሜው የሰልፍ የቦምብ ፍንዳታ የሽብር ወንጀል ጋር ተጠርጥረው ለእስር መዳረጋቸው አይዘነጋም፡፡a

ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
425 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1043 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us