አቶ ካሳሁን ኃ/ማሪያም፤ ከትራንስፖርት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተርነት ተነሱ

Wednesday, 16 May 2018 13:20

ዜና ትንታኔ

 

አቶ ካሳሁን ኃ/ማሪያም፤

ከትራንስፖርት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተርነት ተነሱ

 

በትራንስፖርት ሚኒስቴር የትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር በመሆን ላለፉትሃያ ሁለት ዓመታት ያገለገሉት አቶ ካሳሁን ኃ/ማሪያም ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል፡፡

ሰኞ ዕለት በጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አሕመድ በተፃፈ ደብዳቤ ከኃላፊነት መነሳታቸው ታውቋል፡፡ በምትካቸው በትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት አቶ አብዲሳ ያደታ ዝቅ ተደርገው እንዲተኳቸው ተወስኗል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ እየወሰዱት ያለው የሪፎርም እርምጃ ተገቢነቱ ጥያቄ ውስጥ የሚወድቅ አይደለም፡፡ የጀመሩት ሪፎርም መሰረታዊ ለውጥ እንዲያመጣ እና አዲስ የሚሾሙ ሰዎች ከሕግ በታች መሆናቸውን ግንዛቤ የሚወስዱበት የአሿሿም ስርዓት እየተዘረጋ መሆኑን ለማስጨበት ሁለት መሰረታዊ ነገሮች መሟላት አለበት፡፡

አንደኛው፣ አዲስ የሚሾሙ ሰዎች ቀድሞ ከነበረው ኃላፊ ወይም ባለስልጣን በትምህርት ዝግጅት ከፍ ያሉና ለሚሾምበት ኃላፊነት ተዛማጅ የሙያ ባለቤት መሆናቸው መረጋገጥ አለበት፡፡ ሁለተኛ፤ ከኃላፊነት የሚነሱ ሰዎች በሰሯቸው ጥፋቶች ልክና መጠን በሕግ የሚጠየቁበት አሰራር መዘርጋት አለበት፡፡ ይህንን ማድረግ ሲቻል አዲስ ተሻሚዎች ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ከሕግ የበላይነት ማምለጥ እንደማይችሉ አውቀው እንዲገቡበት እድል ይፈጥራል፡፡ የሚወሰደው እርምጃም በሕግም በሕዝብ ፊት ቅቡል ይሆናል፡፡

እንደማሳያ ለማስቀመጥ፣ አቶ ካሳሁን ኃ/ማሪያም ይመሩት የነበረው የትራንስፖርት ባለስልጣን መስሪያቤት በየቀኑ በመኪና አደጋ ከሚቀጠፈው ዜጋ አንስቶ እስከ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ግብዓት እስከማቅረብ የነበረው አሉታዊ ሚና በቀላል የሚተመን አይደለም፡፡

በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዲመለከቱት የሚያስፈልገው ዋና ነጥብ በትራንስፖርቱ ዘርፍ በአንድም በሌላ መልኩ ከገዢው ፓርቲ ጋር ቁርኝት ያላቸው በትራንስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች እና በግል የትራንስፖርት ዘርፍ ተደራጅተው ያሉ ማሕበራት መካከል ያለው ያልተመጣጠነ የገበያ ውድድር ሊታረም የሚገባው ነው፡፡ ልማታዊ መንግስት የግሉ ዘርፍ መሰማራት በማይችልበት የሚሳተፍ የገበያ ስርዓት የሚከተል እንጂ፣ በግሉ ባለሃብት ሊሸፈን በሚችል ዘርፍ ተሻሚ የገበያ ስርዓት አይከተልም፡፡ በዚህ ዘርፍ ከገበያው ውድድር በባሰ የትራንስፖርት ባለስልጣን መስሪያቤት በገነገነ ኔትዎርክ በመያዙ የሚያስከትለው አሉታዊ ጉዳት በጊዜም በገንዘብም የሚተመን አይደለም፡፡

በአስረጂነት ለማሳየት በሰንደቅ ጋዜጣ በተደጋጋሚ ያሰፈርነውን የግሉ የትራንስፖርት ማሕበራት ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ የተፈጸመውን የአሰራርና ግድፈቶች በዚህ መልኩ ማቅረብ ተገቢ ነው የሚሆነው፡፡

የትራንስፖርት ማኅበራት ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ የገጠማቸው ተግዳሮቶች ምን ይመስላሉ?

 

1.የፍ/ብ/ሕግ ድንጋጌዎች ተጥሰው ህጋዊ ማኅበራት እንዲፈርሱ ተደርገዋል፣

በህግ አግባብ የተቋቋሙት ማኅበራት ህጉ በሚፈቅደው መሠረት ሊፈርሱ ይችላሉ። የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን መ/ቤት ግን የፍ/ብ/የሕግ ድንጋጌዎችን በመመሪያ በመሻርና ማኅበራት የሚፈርሱበት የህግ አግባብ በመጣስ ማኅበራትን አፍርሷል። ማሕበራት በሕግ የሚፈርሱበት አግባብ፣ በማኅበሩ የመመስረቻ ፅሁፍና የመተዳደሪያ ደንብ መሠረት (ፍ/ብ/ህ/ቁ454)፤ በማኅበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ውሣኔ (ፍ/ብ/ቁ460)፤ በፍርድ ቤት ውሣኔ (ፍ/ብ/ቁ461)፤ የማኅበሩ ዓላማና ክንውኑ ህገወጥ ወይም ለመልካም ፀባይ ተቃራኒ የሆነ እንደሆነ በአስተዳደር ውሣኔ (ፍ/ብ/ቁ462) ብቻ መሆኑ በፍ/ብ/ሕጉ በግልፅና በማያሻማ ሁኔታ ተደንግጎ እያለ፤ የባለሥልጣኑ መ/ቤት ግን ቁጥራቸው ከ80 በላይ የሆኑ በህግ አግባብ የተቋቋሙ ማኅበራት በአደረጃጀት ሰበብ እንዲፈርሱና ህልውናቸውን እንዲያጡ አድርጓል።

 

2.     የማኅበራት ሃብትና ንብረት እንዲመዘበርና እንዲባክን ተደርጓል፣

የባለሥልጣኑ መ/ቤት በህግ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት የማኅበራት ሃብትና ንብረት ተገቢ ጥበቃ እንዲደረግለት የሚያስችል የአፈፃፀም መመሪያ ማውጣትና መተግበር ሲገባው፣ በአንፃሩ ህጋዊ ሰውነትና ህልውና ያላቸውን ማኅበራት ከህግ አግባብ ውጭ እንዲፈርሱና ህልውናቸውን እንዲያጡ በማድረግ ሃብትና ንብረታቸው ለብክነትና ለምዝበራ እንዲጋለጥ አድርጓል።

ማኅበራት የአደረጃጀት ለውጥ ያድርጉ ቢባል እንኳን በቅድሚያ ሃብትና ንብረታቸው እንደዳይባክንና እንዳይመዘበር የሚያደርግ የአፈፃፀም እርምጃዎችን ማስቀደም ሲገባውና ሐብትና ንብረቱ የፍ/ብ/ሕጉ በሚያዘው መሠረት አዲስ ወደተደራጁት ማኅበራት እንዲተላለፍ ማድረግ ሲገባው፤ ሃብቱና ንብረቱ የደረሰበት እንዳይታወቅ በማድረግ ለተፈፀመው ጥፋት ሊጠየቅበት የሚገባ ጉዳይ ነው።

 

3.     የሎጅስቲክስ አስተባባሪ ባለመኖሩ በማኅበራት ላይ የሚደርስ ጉዳትን በተመለከተ፣

በሃገራችን የሎጅስቲክስ አስተባባሪ ማዕከል የለም። ይህም በመሆኑ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ግዙፍ ጭነቶች፣ ማዳበሪያ፣ የምግብ ስንዴ፣ የኮንስትራክሽን ብረቶች፣ ኮንቴነሮች….ወዘተ በጊዜ ሠሌዳ ተቀናብረው ወደብ እንዲደርሱ ስለማይደረግ፤ የትራንስፖርት አቅርቦቱ ከአቅም በላይ እንዲሆንና ወደብ ላይ ከፍተኛ ክምችት እንዲፈጠር ይደረጋል። በዚህ ጊዜ የትራንስፖርት ባለሥልጣን የትራንስፖርት ቅንጅቱን ለማስተባበር ሲል በትራንስፖርት ማኅበራት ላይ አላስፈላጊ ወከባና ጫና ይፈጥርባቸዋል፡፡ ይህም ሲባል ማኅበራት ካላቸው የጭነት ተሽከርካሪ ኃይል በላይ የጭነት ኮታ እየመደበና ማኅበራቱ ኮታውን ማንሳት በማይችሉበት ጊዜ ማኅበራቱን ከሥራና ከአገልግሎት እስከማገድ ይደርሳል።

ከዚህም በተጨማሪ የጭነት ተሸከርካሪዎችን ለመቆጣጠር በሚል ሰበብ ጋላፊና ደወሌ ላይ የመቆጣጠሪያ ኬላ በማቋቋም፤ የገቢና የወጪ ተሸከርካሪ ሹፌሮች ለኪራይ ሰብሳቢነት እንዲጋለጡ ዳርጓናል።

 

 

4.     የህገወጥ ማኅበራት እንቅስቃሴ ባለመቆጣጠር የሚፈፀሙ ህገወጥ ድርጊቶች፣

አዋጅ መሠረት የተደራጁ ብዙ ህጋዊ ማኅበራት እንዳሉ ሁሉ፤ ህጋዊ መስፈርቶችን ሳያሟሉ በየስርቻው የተቋቋሙ “የትራንስፖርት ማኅበራት” ተብዬዎች እንደ አሸን ፈልተዋል። እነዚህ “ማኅበራት” በህጋዊነት መስመር ስለማይመሩ በተለያዩ የድለላ የግንኙነት መስመሮች ጭነቶችን በከፍተኛ ዋጋ እየወሰዱና በህጋዊ ማኅበራት ውስጥ የተደራጁትን የጭነት ተሽከርካሪዎችን በደላላ እያግባቡ ዋጋ በመቀነስ ጭነቶችን ያጓጉዛሉ። በዚህም ከፍተኛ ጥቅም ያጋብሳሉ።

የትራንስፖርት ዋጋን የሚያንሩ እነዚህ ህገወጥ ማኅበራት መሆናቸው ሳይታወቅ ህጋዊ ትራንስፖርተሮች የማጓጓዣ ዋጋውን በማናር ይፈረጃሉ። የባለሥልጣኑ መ/ቤት እነዚህን ህገወጦች እንዲቆጣጠር በህጋዊ የትራንስፖርት ማኀበራት ለሚቀርብለት ማሳሰቢያ ጆሮ አይሰጥም።

 

 

5.የሞዴል የመተዳደሪያ ደንብ ትርጓሜ

በአዋጁ 468/1997 አንቀጽ 13 ስለማኅበራት መቋቋም በተደነገገው ቁጥር 5 ላይ፣ “ ባለሥልጣኑ የማኅበራት ሞዴል የመተዳደሪያ ደንብ ያወጣል” የሚል ሰፍሯል። ይህን የድንጋጌ አግባብ ከህግ አውጭው ፍላጎት ውጭ በመተርጎም፣ “ማኅበራት እንደጥንካሬያችን እና እንደተጨባጭ ሁኔታዎች የራሳችንን የመተዳደሪያ ደንብ እንዳናወጣ ገደብ አስቀምጠው፤ ሁሉም ማኀበራት በባለሥልጣኑ መ/ቤት በሚወጣ ሞዴል የመተዳደሪያ ደንብ አንድ ወጥ በሆነ መልኩ እንድንገዛ የሚያደርግ መመሪያ ቁጥር 1/2006 በጥቅምት 2006 ዓ/ም አውጥቷል።”

ይህም በመሆኑ የማኅበራትን የፈጠራ ችሎታና የውድድር መንፈስ የሚያቀጭጭ ከመሆኑም በላይ ሞዴል የመተዳደሪያ ደንቡ፣ ማኅበራት የሚተዳደሩበት የራሳቸው የመተዳደሪያ ደንብ እንዳይኖራቸው፤ ከሦስተኛ ወገን ጋር ያላቸውን ግንኙነት በራሳቸው ፍላጎት እንዳያራምዱ፤ ሃብትና ንብረት የማፍራት እንቅስቃሴያቸው በባለሥልጣኑ መ/ቤት ይሁንታ ብቻ እንዲፈፀም እና የውስጥ አደረጃጀታቸውና አመራራቸው በነፃነት እንዳያራምዱ ተግዳሮት እንደፈጠረባቸው አስታውቀዋል።

 

 

6.የትራንስፖርት ኦፕሬተር የደረጃ አሰጣጥ መሥፈርትና የሙያ ብቃት ማረጋገጫ የአፈፃፀም መመሪያ ቁጥር 1/ 2006 በማኅበራት ህልውናና እድገት ላይ ያስከተለው ችግር

የትራንስፖርት ባለሥልጣን በጥቅምት 2006 ዓ.ም “….የድንበር ተሻጋሪ የጭነት ትራንስፖርት ኦፕሬተር የደረጃ አሰጣጥ መሥፈርት የሙያ ብቃት ማረጋጫ የአፈፃፀም መመሪያ ቁጥር 1/2006 “በሚል ስያሜ አንድ መመሪያ አውጥቷል።ህ መመሪያ ዓላማ አድርጎ የተነሳው ድንበር ተሻጋሪ የጭነት ትራንስፖርት ዘርፍን ለማዘመን ነው ቢባልም በተግባራዊ የአፈፃፀም ውጤቱ ግን አዋጁን በመመሪያ በመሻር በርካታ ችግሮችን አስከትሏል።

በተግባር ከተከሰቱት ችግሮች መካከል፣ በደረጃ መሥፈርቱ መመሪያ መሠረት ተሸከርካሪዎች የተሰሩበት ዘመንና እድሜያቸውን በዋና መሥፈርትነት በመጠቀም ከ1 እስከ 10 ዓመት እድሜ ያላቸው በደረጃ 1፤ ከ10 እስከ 20 ዓመት እድሜ ያላቸው በደረጃ 2፤ ከ20 ዓመት በላይ እድሜ ያላቸው በደረጃ 3 እንዲደራጁ ከመደረጉም በላይ በእያንዳንዱ ደረጃ የእድሜ መሥፈርት የሚካተቱ ተሽከርካሪዎች እንደገና በመጫን አቅማቸው በመለየት ከ300 ኩ/ል በላይ የመጫን አቅም ያላቸው በ“ሀ” እንዲሁም እስክ 299.9 ኩ/ል የመጫን አቅም ያላቸው በ“ለ” እንዲመደቡ ይደረጋል።

ይህ አደረጃጀት፡- ተሽከርካሪዎቹ በደረጃው የእድሜ ጣሪያ ላይ ሲደርሱ ከነበሩበት ማኅበር ደረጃ ወደ ቀጣዩ የማኅበር ደረጃ እንዲሸጋገሩ ይገደዳሉ። ተሽከርካሪዎቹ በየጊዜው ከማኅበር ወደ ማኅበር እንዲፈናቀሉ በሚደረግበት ጊዜ የተሽከርካሪው ባለንብረት ለዓመታት በነበረበት ማኅበር የአባልነት ቆይታው ወቅት ለማኅበሩ ያስገኘው የገንዘብ፣ የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ የሃብትና የንብረት እሴቶችን ጥሎ እንዲሄድ ይገደዳል።

ሌላው፣ የማኅበራት ሃብትና ንብረት ባለቤትና ተቆጣጣሪ እንዳይኖረው፣ እንዲባክንና ለግል ጥቅም እንዲውል የሚያደርግ አሠራር ከመሆኑም በላይ የተሸከርካሪ ባለንብረቶች ገንዘብና አቅማቸውን አስተባብረው ወደ ላቀ ተቋማዊ የትራንስፖርት የእድገት ደረጃ አደረጃጀት ለመሸጋገር የሚዲርጉትን ጥረት የሚያመክን እጅግ ከፍተኛ ጎጂ የሆነ አሠራር ነው።

እንዲሁም ማኅበራት ይህ ለትራንስፖርት ዘርፉ እድገት ጎጂ የሆነውን የአደረጃጀት ሥርዓት ተጠንቶና ጉዳቱ ታውቆ አፋጣኝ የእርምትና የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ ለባለሥልጣኑ መ/ቤት ማሳሰቢያ ቢያቀርቡም የባለሥልጣኑ መ/ቤት ማሳሰቢያውን ካለመቀበሉም በላይ አማራጭ የማሻሻያና የማስተካከያ አደረጃጀት ለማቅረብ አልቻለም።

በመሆኑም ማኅበራት በአሁኑ ጊዜ ከተጋረጠባቸው የጥፋት መንገድ ለመላቀቅ የሚያስችላቸው በጋራና በአንድነት ተደራጅተው ህጋዊና ሠላማዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ አማራጭ አካሄዶችን ለመከተል ተገደዋል።

ከመነሻው መመሪያው በአዋጁ 468/1997 አንቀጽ 12 ተራ ቁጥር 2 “..በህዝብ የንግድ የመንገድ ማመላሻ ሥራ ላይ ሰዎችና ድርጅቶች በአዋጁ አንቀጽ 13 መሠረት የሚቋቋም ማኅበር አባል በመሆን ወይም የማኅበር አባል ሳይሆኑ ሥራቸውን በግል ሊያካሂዱ ይችላሉ..” የተሰኘውን ድንጋጌ ይሽራል። በመመሪያው መሠረት እያንዳንዱ የጭነት ተሽከርካሪ የማኅበር አባል የመሆን ግዴታ ተጥሎበታል።

በአዋጁ አንቀጽ 13 ተራ ቁጥር 4 “….በህዝብ የንግድ የመንገድ ማመላለሻ ሥራ ላይ የተሰማራ ማንኛውም ሰው ወይም ድርጅት በአንድ ጊዜ በአንድ የስምሪት መስመር   ውስጥ ከአንድ በላይ በሆኑ ማኅበራት ውስጥ አባል ሊሆን አይችልም….” የሚለው የአዋጅ ድንጋጌ በመመሪያ ተሸሮ ሁለትና ከዚያ በላይ የጭነት ተሽከርካሪ ባለንብረት የሆነ “ሰው“ በሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ድንበር ተሻጋሪ ማኅበራት ውስጥ እንዲደራጅ ተገዷል። በመሆኑም መመሪያው ባለንብረቱ የጭነት ተሽከርካሪዎቹን በአንድ ዕዝ ሥር ለመቆጣጠር ያለውን ህጋዊ ችሎታ ነፍጎታል።

ከላይ ለማሳያ አስቀመጥነው እንጂ፣ በአስር ሺ ተሽከርካሪ የሰው ሞት እንደሚሰላ የሚገነዘበው የትራንስፖርት ባለስልጣን በመኪና አደጋ የሚሞተውን የሰው መጠን በተዛባ ሁኔታ እንደሚያቀርብ ይታወቃል፡፡ ይኸውም፣ 750ሺ ተሽከርካሪ መኖሩ ቢነገርም፣ ከዚህ ውስጥ ምን ያሉ መኪና ምን ያህሉ ተሳቢ መሆኑ በግልፅ አይቀመጥም፡፡ ተሽከርካሪ ሲባል ሞተር ያለው ተንቀሳቃሽ ማለት ነው፡፡ ባለስልጣን መስሪያቤቱ ግን ተሽከርካሪ የሚቆጥረው ተሳቢውን ደምሮ ነው፡፡ ስለዚህም በአስር ሺ መኪና የሚለካው የሰው ሞት፣ ትክክለኛ አሃዙን አያሳይም፡፡

የተደረገው ለውጥ ከአናት መምጣቱ አንድ ነገር ሆኖ፣ በትራንስፖርት መስሪያቤት ያለውን የተበላሸ ኔተዎርክ መበጠስ ካልተቻለ ለውጥ መጠቀብ አይቻለም፡፡ ከዳሬክተሮቹ ጀምሮ መበወዝና ማስተካከል ቀጣይ ስራ መሆን አለበት፡፡

 

 

 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
3925 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 67 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us