You are here:መነሻ ገፅ»ዜና

 

የተሻሻለውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ለማሻሻል በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ቀርቦ በጸደቀው አዋጅ መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ ምክርቤት አባል ያልሆኑት ኢንጅነር ታከለ ኡማ በንቲ በትላንትናው ዕለት በምክትል ከንቲባነት ተሾሙ።

አዲሱ ተሿሚ አቶ ታከለ ኡማ በትላንትናው ዕለት በተካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ ምክርቤት ልዩ ስብሰባ ላይ በምክትል ከንቲባነት የተሾሙ ሲሆን፤ ተሰናባቹን የቀድሞ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማን ኃላፊነት ሙሉ ለሙሉ ተክተው እንደሚሰሩ ታውቋል።

በዚህ ሹመት መሠረት በቀጣይ ዓመት ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ ኢንጂነር ታከለ የአዲስ አበባ ከተማን በምክትል ከንቲባ ይመራሉ። የተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅን ለማሻሻል ሰሞኑን በፓርላማ የጸደቀው አዋጅ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ከምክርቤቱ አባላት መካከል እንደሚመረጥ የደነገገ ሲሆን ምክትል ከንቲባው ግን ከምክርቤቱ አባላት ውስጥ ወይንም ከምክርቤቱ አባላት ውጭ ሊሾም እንደሚችል መደንገጉ ይታወሳል።

ኢንጂነር ታከለ ኡማ ከሹመቱ በኋላ በግል የማሕበራዊ ድረገፃቸው እንዳሰፈሩት፣ “ሀገራችን በተስፋና በአንድነት ጉዞ ላይ ባለችበት በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባን ማገልገል ክብርና መታደል ነው” ብለዋል።

አያይዘውም፣ አዲስ አበባ የሁሉም ክልሎች፣ ሃይማኖቶች እና በተለያዩ ማሕበራዊ መደቦች ውስጥ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ነች። እንዲሁም የተለያዩ ብሔሮች፣ እምነቶችና የኢኮኖሚ ብዝሃነት ያለባት ከተማ መሆኗን ገልጸዋል። የተለያዩ ችግሮች በከተማዋ ውስጥ እንደሚገኙም ከንቲባው አስታውሰው፤ ለከተማው ሕዝብ አብረን ከሰራን እንለውጠዋለን ሲሉ፤ ቃል ገብተዋል።

ቅርበት ካላቸው ወገኖች በተገኘ መረጃ መሠረት፤ አቶ ታከለ ኡማ የተወለዱት በምዕራብ ሸዋ አምቦ ከተማ ነው። የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአምቦ ከተማ ተከታትለዋል። በሲቪል ምህንድስና ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወስደዋል። የአዲስ አበባ ከንቲባ ከመሆናቸው በፊት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ እና የካቢኔ አባል በመሆን አገልግለዋል። ቀደም ባሉት ጊዜያት የሆለታ ከንቲባ እና የአምቦ መሬት አስተዳደር የቢሮ ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል።

በተጨማሪም የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክርቤት፤ የከተማዋ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ የነበሩትን ዶ/ር ኢንጂነር ሰለሞን ኪዳኔ እና የከተማዋ የኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ የነበሩትን ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስን በምክትል ከንቲባነት ማዕረግ ሾሟል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ እና አቶ አባተ ስጦታው በአምባሳደርነት መሾማቸው በመገናኛ ብዙሃን ሰሞኑን መነገሩ አይዘነጋም።¾

 

ኢትዮጵያና ኤርትራ አሁን ያሉበት ደረጃ እንዲደርሱ የውጭ መንግስታት የራሳቸውን ሚና የተጫወቱ መሆኑን ዘ ኢኮኖሚስት ከሰሞኑ ባስነበበው ዘገባ አመልክቷል። እንደዘገባው ከሆነ ሁለቱ ሀገራት መካከል በጠላትነት የመፈላለግ ዘመኑ አብቅቶ ወደ አዲስ ምዕራፍ እንዲገቡ አሜሪካ፣ ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኢሜሬት የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል።

እንደዘገባው ከሆነ በአፍሪካ ምድር ሰፊ የአሜሪካንን ፖለቲካ በማስረፁ ረገድ ሰፊ ሥራን የመስራት ልምድ ያላቸው ዶናልድ ያማማቶ ከአዲስ አበባ አስመራ በመመላለስ ሰፊ የማግባባት ሥራን ሰርተዋል። ዲፕሎማቱ ከአስርት ዓመታት በኋላ በዚሁ ጉዳይ የአስመራን ምድር ሲረግጡ የመጀመሪያቸው መሆኑን ያመለከተው ይኸው ዘገባ የአስመራ ጉዳያቸውንም በሚያዚያ ወር እንዳጠናቀቁ ለተመሳሳይ ተግባር በአዲስ አበባም ቆይታ ያደረጉ መሆኑን አስታውሷል። ዘገባው ይህም ሁኔታ አሜሪካ ከኤርትራ ጋር የተሻለ ግንኙነትን ለመፍጠር ፍላጎት ያላት መሆኑን ያሳያል በማለት አትቷል።

ይሁንና አስመራ በጉዳዩ ዙሪያ ብዙም ቀና ምላሽ የሰጠችበት ሁኔታ ባይኖርም በስተመጨረሻ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በሳዑዲ አረቢያ በነበራቸው ቆይታ ኤርትራ የሰላም ሀሳቡን እንድትቀበል የሳዑዲው ልዑል ሙሀመድ ቢን ሳልማን ፕሬዝዳንት ኢሳያስን እንዲያግባቡ የጠየቁ መሆኑን ዘገባው ያመለክታል። ከዚያ በኋላም ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ወደ ተባበሩት አረብ ኤሜሬት ከተጓዙ በኋላ ከተባበሩት አረብ ኤሜሬት ሙሀመድ ቢን ዘይድ ጋር ቆይታ ካደረጉ በኋላ መንግስት የሠላም ሀሳቡን የሚቀበል ከሆነ ሀገሪቱ በምላሹ በጥሬ ገንዘብና በኢንቨስትመንት ፍሰት መልኩ ወደ ኤርትራ ምድር ሰፊ ገንዘብ የምታፈስ መሆኗን ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ የገለፁላቸው መሆኑን ዘገባው ያትታል።¾

-    አሰብ ወደብን ለመጠቀም ዝግጅት ተጀምሯል

 

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ መሪዎች አስመራ እና አዲስ አበባ በየተራ ከጎበኙ በኋላ ባሉት ቀናት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ ፈጣን በሆነ መንገድ ለውጥ እያሳየ መሆኑን የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ20 ዓመታት በኋላ ይፋዊ የመንገደኞች ማጓጓዝ ሥራውን በዛሬው ዕለት ጀምሯል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ትላንት ለመገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዛሬው ዕለት 465 ተጓዦችን ይዞ ከ20 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አስመራ በረራውን ጀምሯል።

 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስቀድሞ በአስመራ የቲኬት ቢሮ ከፍቷል፤ ከኢትዮጵያ አስመራ በየቀኑ ቀጥታ በረራ እንደሚኖርም ታውቋል።

 

በተጨማሪም አየር መንገዱ 20 በመቶ የሚሆነውን የኤርትራ አየር መንገድ ድርሻ እንደሚኖረው ጠቅሰዋል።

 

የአሰብ ወደብን ለመጠቀም ዝግጅት እያደረገች እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታውቋል::

በተያያዘ ዜና በአስብ ወደብ መስመር የመንገድ ጥገና መጀመሩን እንዲሁም የኢትዮጵያ የባህርትራንዚት ቢሮ አሰብ ላይ ቢሮ መክፈቱ ተሰምቷል

በኢትዮጵያ በአሁን ጊዜ የተፈጠረው ሀገራዊ ሠላምና ህዝባዊ አንድነት ለንግዱ ዘርፍ የላቀ አስተዋፅኦ አለው ሲል ንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሀገራችን ዘላቂ ሠላም፣ የልማት ተጠቃሚነት እና ህዝባዊ አንድነቱን በማረጋገጥ ወደ ቀጣይ የልማት እንቅስቃሴ ለመዝመት የሚያስችል ሀገራዊ የሪፎርም ሥራዎች እየተሰሩ ነው። ከሀገሪቱ ህዝባዊ አንድነት በዘለለም ከጎረቤት ሀገራት ጋር ሠላም በመፍጠር ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንግሥት ከፍተኛ ስራ እየሰራ ይገኛል። ይህ ሀገራዊ ለውጥና ንቅናቄ በተለይ ለንግዱ ዘርፍ ያለው አስተዋፅኦ የላቀ ነው ያሉት በንግድ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ወንድሙ ፍላቴ ናቸው።

እንደ አቶ ወንድሙ ገለፃ፤ የሀገራችን ንግድ ከግብርና ባልተናነሰ የኢኮኖሚያችን የጀርባ አጥንት ነው። ዘርፉ የሚነቃቃውና የሚጠበቅበትን ሚና ተጫውቶ በሀገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ ለውጥ የሚያመጣው በሀገር ውስጥና ከጎረቤት ሀገራት ጋር የተረጋጋና ቀጣይነት ያለው ሠላም ሲኖር ነው። በሀገር ውስጥ ጤናማ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲኖርና የተለያዩ ምርቶችን ወደ ውጪ ልከን ለሀገራችን አስፈላጊ የሆነውን የውጪ ምንዛሪ ማግኘት እንድንችል አሁን የተጀመረው ሀገራዊ ንቅናቄና ለውጥ በጣም ወሳኝ ነው።

አቶ ወንድሙ አክለውም፤ ላለፉት ዓመታት የውጪ ንግድ አፈፃጸማችን ዝቅተኛ የሆነው ሀገሪቷ ውስጥ ከነበረው የሠላም እጦት፣ ከምርት አቅርቦት እጥረት፣ ከምርት ጥራት ችግር፣ ከውጪ ምንዛሪ አቅርቦት እጥረት ጋር በተያያዘ ምክንያት ነው ያሉ ሲሆን፤ የውጪ ምንዛሪ አቅርቦት እጥረትን ለማቃለል የሚያስችል እና በሀገር ውስጥም የተረጋጋና አዳጊ ገበያ እንዲሁም ለላኪዎቻችንና ለነጋዴዎቻችን በቂ የሆነ የውጪ ምንዛሪ ግኝት እንዲኖር መንግሥት የተለያዩ የማሻሻያ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል ብለዋል።

በመጨረሻም ንግድ ሚኒስቴር የተጣለበትን ሀገራዊ ተልዕኮ ለመወጣት የሚያስችለውን የሪፎርም ሥራዎች እየሰራ ነው ያሉት አቶ ወንድሙ፤ በተለይም አገልግሎት አሰጣጡን በማዘመንና በማቀላጠፍ የተገልጋዮችን እንግልት በማስቀረት ቀደም ሲል ይነሱ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እየሰራ ነው ብለዋል። ሲል የዘገበው በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ንግድ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው።

የገበያና ድርጅት ኢንስፔክሽንና ሪጉላቶሪ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ሙላት በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን በያዙ ማግስት በመስሪያ ቤቶች ቀልጣፋ፣ ግልጽ፣ ተደራሽ አገልግሎትና ዴሞክራሲያዊ አሰራር እንዲሰፍን የሰጡትን አቅጣጫ ተከትለን እየሰራን ነው ብለዋል። ንግድ ማኒስቴር በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠውን አቅጣጫ ለመተግበር የሚያስችል ፈጣን እቅድ አዘጋጅቶ ከመደበኛው እቅድ ጋር በማጣጣም እየሰራ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ አፈፃጸሙም በየ15 ቀኑ እየተገመገመ ክትትል እንደሚደረግበት ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ ንግድ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተገኘ ዘገባ ያስረዳል።¾    

 

የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች በመሠረታዊ ሠራተኛ ማሕበራቸው ላይ ተቃውሞ እያሰሙ ነው፡፡

 

ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ መሠረታዊ ሠራተኛች ማሕበር አባላት እንደገለጽት፤ ከመተዳደሪያ ደንባቸው ውጪ የማሕበሩ ሃላፊዎች እየተንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ምክር ቤቱ በአመት አራት ጊዜ እንደሚሰበሰብ ቢደነገግም፣ ከአንድ ጊዜ በላይ አልተሰበሰበም፡፡ ጠቅላላ ጉባኤ በአመት አንዴ እንደሚጠራ ቢደነገግም፣ ሶስት ዓመት ሙሉ አልተጠራም፡፡ ከሶስት ኦዲተሮች አንዱ ብቻውን ለሶስት አመታት እያገለገለ ይገኛል” ብለዋል፡፡

 

የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ መሠረታዊ ሠራተኛች ማሕበር ሊቀመበንበር አቶ አዲሴ ሃንዴቦ በስልክ አግኝተናቸው፣ ከተወሰነ ሰዓት በኋላ ደውሉ ብለውን የነበረ ሲሆን፤ ደግመን ስንደውልላቸው ምላሽ አልሰጡንም፡፡

ሠራተኞቹ ለኢንዱስትሪው ሠላም በማሰብ አቤቱታችንን በተደጋጋሚ በሠላማዊ መንገድ ብናቀርብም ሰሚ አጥተናል ሲሉ ለሰንደቅ ገልጸዋል፡፡

የጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ 100 ስኬታማ ቀናት በፎቶ

በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የኤርትራ መንግስት ተቃዋሚ ኃይሎች በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መንግስት የተደረሰው የሰላም ስምምነትን ተከትሎ ሕልውናቸው ስጋት ላይ መውደቁን ለዝግጅት ክፍላችን ገለጹ።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የኤርትራ መንግስት ተቃዋሚ ኃይሎች አመራር ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለጹት፤ “የኤርትራ መንግስትን የሽብር ፖለቲካ ኢኮኖሚን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በጋራ ስንመክት ከርመን፣ አሁን ላይ የኢትዮጵያ መንግስት በተናጠል የወሰደው የሰላም ስምምነት፣ የኢትዮጵያ መንግስትን ለሰብዓዊ መብት፣ ለዴሞክራሲ እና ለነፃነት ያለውን ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ነው። ቢያንስ የኢትዮጵያ መንግስት ነፍጥ ላነሱበት ኃይሎች ምህረት በማድረግ ወደ ሰላማዊ ትግል እንዲገቡ ሁኔታዎችን አመቻችቶ ሲፈቅድ፣ የኤርትራ ተቃዋሚ ኃይሎች እጣፈንታ ምን ሊሆን ይገባዋል ብሎ አልመከረም። አላማከረንም። የሰላም ስምምነቱን ጠልተን ሳይሆን ሁሉን አቀፍ የሰላም ስምምነት ተደርጎ ቢሆን ለሁለቱም ሕዝቦች ጠቀሜታዉ ከፍተኛ መሆኑ በመረዳት ያቀረብነው ቅሬታ ነው” ብለዋል።

በኤርትራ መንግስት ላይ ነፍጥ አንስተው እየታገሉ ያሉ ኃይሎች አያይዘውም፣ “የአስመራ መንግስት ከለላ የሰጣቸው የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች የቀረበላቸው የሰላም አማራጭ ጥሪ ሻዕቢያ ተቀብሎት በሰላም እየሸኛቸው ይገኛል። በአንፃሩ የኢትዮጵያ መንግስት እኛን በተመለከተ ምንም ዓይነት ውይይት ሳያደርግ ወይም የእራሳችን አማራጭ እንድንወስድ ሳያማክረን፣ ቢያንስ የግል ውሳኔያችን ለመጠቀም የሚያስችል የዝግጅት ጊዜ ሳይኖረን፤ ከኤርትራ መንግስት ጋር የሰላም ስምምነት ለማድረግ መወሰኑን ተከትሎ፣ ሕልውናችንን አደጋ ውስጥ ከቶታል” ብለዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ ያልፈለጉት አመራርም አያይዘው ለዝግጅት ክፍላችን ያላቸውን የስጋት ደረጃ እንደገለጹልን፤ “ከዚህ በፊት ሻዕቢያና ሕወሓት ደርግን አሸንፈው ኢትዮጵያን ሲቆጣጠሩ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የነበሩትን የጀበሃ አመራሮችና አባላትን ቤት ለቤት እያሳደደ የሻዕቢያ ቡድን የፈጸመውን ግድያ የሚታወስ ነው። ነገም በኢትዮጵያ ውስጥ የምንገኝ የሻዕቢያ መንግስት ተቃዋሚ ኃይሎች ሊደርስብን የሚችለውን ዕጣ-ፈንታ ማንም አያውቀም። ስለዚህም በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ተመሳሳይ ግድያ እንደማይፈጸምብን ዋስትናችን ምንድን ነው? ብላችሁ፤ ለኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄያችን አድርሱልን” ብለዋል።¾  

 

በይርጋ አበበ

ሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰሞኑን ሶስቱን ድርጅቶች ከሽብርተኝነት መዝገብ መሰረዙ የሚደነቅና ለተጀመረው ለውጥም ትልቅ ድርሻ እንዳለው አስታወቀ።

ፓርቲው ትናንት በጽ/ቤቱ “ሁላችን ለአንዳችን፣ አንዳችን ለሁላችን ስናስብ የማንወጣው፤ ተራራ የማንሻገረው ገደል አይኖርም” በሚል ርዕስ በሰጠው ጋዜጣው መግለጫ “የኦሮሞ ህዝብን ሰብዓዊና ዴሞክራሲዊ መብት ለማረጋገጥ ኦነግ እጅግ መራር ትግል ሲያካሂድ እንደቆየ ሰማያዊ ፓርቲ ይገነዘባል” ያለ ሲሆን “ምርጫ 1997ን ተከትሎ የአገዛዙ ሥርዓት የህዝብን ድምጽ በመቀማት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በእምቢተኝነት በመርገጥ ያሳየውን ጭፍን አምባገነን አገዛዝ፤ ከኢትዮጵያዊያን ጫንቃ ላይ ለማውረድ ሁሉን አቀፍ ትግል በማድረግ የህዝብን ድምጽና ዲሞክራሲያዊ መብት እናስመልሳለን በማለት አርበኞች ግንቦት 7 ተመስርቶ ላለፉት 10 ዓመታት ትግል ሲያካሂድ መቆየቱ ይታወቃል” ብሏል።

ሰማያዊ ፓርቲ በመግለጫው አክሎም ኦብነግ የሶማሌን ዜጎች መብታቸው እንዲከበር ከአብራኩ የወጡ ልጆቹ ዲሞክራሲን ለማስፈንና እንደሌሎች ወንድሞቹ በሃገራቸው እኩል ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ዋጋ ሲከፍሉ እንደቆዩ በገሀድ የሚታይ ሀቅ ነው ሲል ሶስቱም ድርጅቶች በሽብርተኝነት መፈረጃቸው አግባብ አልነበረም ብሏል።

ከዚህ ቀደምም ሶስቱ ድርጅቶች ከሽርተኝነት መዝገብ እንዲሰረዙ ሲጠይቅ መቆየቱን የገለጸው ሰማያዊ ፓርቲ፤ “ድርጅቶቹ የነጻነትና የዲሞክራሲ ታጋዮች መሆናቸውን በመገንዘብ ጥያቄዎቻቸውን በሰላማዊ መንገድ ለማስተናገድ የሚያስችል መድረክ ይፈጥር ሲል የነበረ በመሆኑ፤ ምክር ቤቱ አሁን ከጊዜ ቆይታና በዚህ ፍረጃ ምክንያት በርካታ ዜጎቻችን ከተሰቃዩ እና መሰዋዕት ከሆኑ በኋላ ፍረጃውን ወደማንሳት ውሳኔ በመምጣቱ ሰማያዊ ፓርቲ የሚያደንቅ ቢሆንም በዚህም ምክንያት ለተፈጠረው ቀውስ የታሪክ ተጠያቂዎች መኖራቸው ፓርቲያችን ያምናል” ሲል የሶስቱ ድርጅቶችን እንቅስቃሴ ገልጿል።

“ሰማያዊ ፓርቲ በተለይ በሕብረብሔራዊ አስተሳሰብና በሰላማዊ ትግል የሚታገሉ ድርጅቶች ጋር አብሮ ከመስራት ጀምሮ እስከ መዋሃድ የሚደርስ እርምጃ ለማከናወን ፈቃደኛ እንደሆነ ከዚህ ቀደም በስራ አስፈጻሚና በምክር ቤት ደረጃ በተሰጡ ተደጋጋሚ መግለጫዎች ላይ አቋሙን ግልጽ አድርጓል። አሁንም ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር አብሮ ከመስራት እስከ ውህደት ድረስ ለመስራት ፓርቲያችን ፈቃደኛ በመሆኑ የአርበኞች ግንቦት 7 ድርጅት አመራሮች ጋር በመገናኘት በሰሜን አሜሪካ የሚገኙት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር በአሜሪካ እየተወያዩ ነው” ብሏል።

የፓርቲው መግለጫ ስለ ሁለቱ ወገኖች የውይይት ጭብጥ ሲያስታውቅም “በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና ተቋማትን ነጻና ገለልተኛ ማድረግ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ህዝብ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከሚመራው መንግስት ጋር መነጋገር በሚቻልበት መንገድ ላይ እና የዜጎች ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን በእኩልነትና በተቋም ታግዞ ማስከበር የሚችል፣ የህዝብን አብሮ የመኖርና የመተማመን መንፈስ የሚያጎለብት እና ከጎረቤት አገራት ጋር በመተሳሰብ በጉርብትና መንፈስ ሊያኖረን የሚችል የዜጎች ተሳትፎ በነጻነት የሚያሳትፍ ህገ መንግስት ተዘጋጅቶ እውን በሚሆንበት ሁኔታ ላይ በዋነኝነት እንዲወያይ የሰማያዊ ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ወስኗል” ብሏል።

የሰማያዊ ፓርቲን እና የግንቦት ሰባትን አብሮ የመስራት ቅድመ ዝግጅቱን ያመቻቸው በሰሜን አሜሪካ የሚገኘው “ሸንጎ” መሆኑንም ፓርቲው አስታውቋል።

 

·        የማዕድን ዘርፍ ገቢ አሽቆልቁሏል

 

በ2010 በጀት ዓመት አስራ አንድ ወራት ከግብርና ከማኑፋክቸሪንግ እና ከማዕድን ምርቶች ዘርፍ በአጠቃላይ 4 ነጥብ 72 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 2 ነጥብ 58 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በበጀት ዓመቱ አስራ አንድ ወራት ከግብርና ምርቶች ዘርፍ በአፈፃፀም የተመዘገበው 1 ነጥብ 97 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነው። ይህ አፈፃፀም ከአምናው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወራት ከተገኘው 1 ነጥብ 96 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ጋር ሲነፃፀር በ7 ነጥብ 8 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በግብርና ምርቶች ዘርፍ ላይ ጭማሪ አሳይቷል።

በተመሳሳይ የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች ዘርፍ በአፈፃፀም የተመዘገበው 415 ነጥብ 93 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነው። ይህ አፈፃፀም ከአምናው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወራት ከተገኘው 362 ነጥብ 65 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ጋር ሲነፃፀር በ53 ነጥብ 28 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በማኑፋክቸሪንግ ምርቶች ዘርፍ ላይ ጭማሪ አሳይቷል።

የማዕድን ዘርፍ ዕቅድ አፈፃፀም ስንመለከት ደግሞ በአፈፃፀም የተመዘገበው 119 ነጥብ 03 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነው። ይህ አፈፃፀም ከአምናው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወራት ከተገኘው 190 ነጥብ 73 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ጋር ሲነፃፀር በ71 ነጥብ 69 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር (37 ነጥብ6 በመቶ) በዘርፉ ላይ ቅናሽ አሳይቷል።

በበጀት ዓመቱ አስራ አንድ ወራት የእቅዳቸውን ከ75 በመቶ በላይ ክንውን ያስመዘገቡ ምርቶች እንደቅደም ተከተላቸው የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ሻይ ቅጠል፣ ባህር ዛፍ፣ ጫት እና የቅባት እህሎች ናቸው። ከተያዘላቸው እቅድ ከ50 በመቶ እስከ 75 በመቶ ክንውን ያስመዘገቡ ምርቶች እንደቅደም ተከተላቸው ቡና፣ አበባ፣ ዱቄትና ምግቦች፣ ያለቀለት ቆዳ፣ የተፈጥሮ ሙጫና ዕጣን፣ ሥጋ፣ የተዘጋጀ የፍራፍሬ ውጤቶች፣ አትክልትና ፍራፍሬ እና የጥራጥሬ ሰብሎች ናቸው።

የግብርና ምርቶችን በተመለከተ በበጀት ዓመቱ የተመረተውን ምርት ወደ ገበያ እንዲወጣና የዘመኑ ምርት በተሻለ ጥራትና መጠን ለገበያ እንዲቀርብ፣ ኢፍትሀዊ የሆነ የግብይት ውድድር እንዳይኖር በማድረግ፣ ከክልሎችና ከግብየት ተዋንያን የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል መረባረብ እንደሚያስፈልግ የሚኒስቴሩ ሕዝብ ግንኙነት ክፍል የላከው ዜና ጠቁሟል።

የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች አፈፃፀምን ለማሻሻል በዋናነት ዝቅተኛ ደረጃ አፈፃፀም ያስመዘገቡትን ድርጅቶች የሚስተዋሉባቸውን ችግሮች ለማሻሻል ጥረት ማድረግና በአሁኑ ወቅት የዓለም ገበያ የሚጠይቀውን የተወዳዳሪነት መስፈርት ከሟሟላት አኳያ በመስራት የተቀባይ አገራትን ይሁንታ ማግኘት ይገባል።

የማዕድናት ምርቶች አፈፃፀምን በተመለከተ ወርቅን በተመለከተ በህገወጥ መንገድ የሚባክነውን ምርት ለማስቀረት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ሥራዎችን በቅንጅት መስራት፣ በዚህ ዘርፍ የተሰማሩትን ኩባንያዎችን ያሉባቸውን ችግሮች በመፍታት በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ እንዲገቡ በጋራ መረባረብ እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል።

በአጠቃላይ በተለይም በአሁኑ ወቅት ለኤክስፖርት አፈፃፀማቸው ቁልፍ ችግር ከሆኑት መካከል አንዱ የኮንትሮባንድ ንግድ፣ ኩባንያዎች/ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ያለመስራት፣ ምርትን በተሻለ ጥራት ያለማቅረብ በመሆኑ ይህንን ለማስወገድ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ርብርብ ማድረግ እና የገቢ ጉድለት በታየባቸው ምርቶች ላይ ትኩረት በመስጠት በቀጣይ ወር የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገብ ያስፈልጋል ብሏል።

Page 1 of 110

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us