የልውጠ ህያው ቢቲ ጥጥ ከመመረቱ በፊት የተጠያቂነት ሥርዓት ሊዘረጋ እና በፈቃድ አሰጣጡ ላይ የህዝብ አስተያየት ሊሰበሰብ ይገባል

Wednesday, 13 June 2018 13:16

 

በሻምበል ገብረመድህን ቢረጋ

የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ጥበቃ ማህበር

ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ

ፀሐፊውን ለማግኘት - This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ; This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

እ.ኤ.አ. ከ197ዐዎቹ ጀምሮ በዘረመል ምህንድስና (Genetic Engineering) አማካይነት በተፈጥሮ ሥርዓት ሊገናኙ የማይችሉ፣ እጅግ በተለያዩ ዝርያዎች የሚገኙ ዘረመሎችን (Genes) ማቀናጀት ተችሏል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ያልተጤኑ አዳዲስ ባህርያት ሊከሰቱ እንደሚችሉ በመገመቱና ከነዚህ አዳዲስ ባህርያት መካከል አደገኛ የሚሆኑ ይኖራሉ ተብሎ ስለሚፈራ ከልውጠ ህያዋን (Genetically Modified Organisms) የሚሰሩ ምርቶች ጉዳይ ከአወዛጋቢ ዓለም አቀፍ አጀንዳዎች አንዱ ከሆነ ዓመታትን አስቆጥሯል

ስለዚህ በዘረመል ምህንድስና አማካይነት የሚገኙት ልውጠ ህያዋን ምርቶች፣ ሰብሎችና ሌሎች ውጤቶች ደህንነት (safety) ለማረጋገጥ የሚያስችል ዓለም አቀፍ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊነት ታምኖበት ከአሜሪካ በስተቀር ከሞላ ጎደል ዓለም ሁሉ የተቀበለው የካርታኼና ደህንነተ ህይወት ፕሮቶኮል እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ከግንቦት 2ዐዐዐ ጀምሮ የጸደቀ ሲሆን አገራችንም በአዋጅ ቁጥር 382/1995 በማፅደቋ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግሥት አንቀፅ 9 ንዑስ አንቀፅ 4 መሰረት የአገሪቱ ህግ አካል ሆኗል። ፕሮቶኮሉን በማፅደቅ ብቻ አስተማማኝ አገራዊ ደህንነተ ህይወት (biosafety) ሥርዓት ማረጋገጥ የማይቻል መሆኑን በመንግሥት በኩል ግንዛቤ በማግኘቱ ከጳጉሜ 4 ቀን 2ዐዐ1 ዓ/ም ጀምሮ እስከ ነሐሴ 7 ቀን 2ዐዐ7 ዓ/ም ድረስ ንቶ የነበረው የደህንነ ህይወት አዋጅ ቁጥር 655/2ዐዐ1 ታውጆ እንደነበር ይታወቃል።

የአዋጁ ዋና ዓላማ በሰውና በእንስሳት ጤና፣ በብዝሐ ህይወት፣ በአካባቢ፣ በማህበረሰቦችና በአጠቃላዩም በሀገር ላይ ከልውጠ ህያዋን ሊደርስ የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ማስቀረት ወይም ቢያንስ እስከ ኢምንታዊነት ደረጃ ድረስ ማሳነስ መሆኑን በአንቀፅ 4 ሥር ተመልክቷል። በመሆኑም የአዋጁ ዓላማ ከተሳካ ከሸማቾች መሰረታዊ መብቶች አንዱ የሆነውን የደህንነት መብት (The Right to safety) የሚያረጋግጥ በመሆኑ በአዋጁ ላይ ሸማቹ ህብረተሰቡ ግንዛቤ ግንዛቤ እንዲኖረው በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት ግንዛቤ ማስጨበጥና ሸማቾችን በመወከል በአገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች በመሳተፍ የበኩላችንን ገንቢ አስተዋፅኦ ስናበረክት ቆይተናል።

ይህ በዚህ እንዳለ አዋጁ ምርምርና ስርፀትን አያበረታታም፣ አገሪቱ ከጥበበ-ህይወት (biotechnology) ማግኘት የነበረባትን ጥቅም በተለይም ለምርምር ከተለያዩ ምንጮች ሊገኝ የሚችለውን የውጭ ምንዛሪ እንዳናገኝ እንቅፋት ሆኗል የሚሉ ወገኖች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከሚገኙ የልውጠ-ህያዋን ደጋፊ አግባቢዎችና (lobby group) እና ድንበር ዘለል ኩባንያዎች ጋር በመተባበር ባደረጉት እንቅስቃሴ ከነሐሴ 8 ቀን 2ዐዐ7 ጀምሮ የፀናው አዋጅ ቁጥር 896/2ዐዐ7 ይፋ ሆኗል።

አዋጁን ማሻሻል ካስፈለገ በቅድሚያ ነባሩ አዋጅ ተሞክሮ ተግዳሮቶች ተለይተው የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በተለይም የአርሶ አደሮችና ሸማቹ ማህበረሰብ ይሁንታ እንዲጠየቅ ያደረግነው ጥረት ወደጎን ተትቶ ለወትዋቾች በሚመች መልኩ በችኮላ እንዲሻሻል ተደርጓል። በተለይም በዓለም አቀፉ የካርታኼና ፕሮቶካል እና በማንኛውም አገር የደህንነተ - ህይወት ህግ ማዕቀፎች ዓላማዎች ውስጥ ተካትቶ የማያውቀውንና መካተት የሌለበትን “ዘመናዊ ጥበበ ህይወትን ጨምሮ ለብዝሐ ህይወት ጥበቃና ዘላቂ አጠቃቀም የሚያገለግል ቴክኖሎጂ ተደራሽነትንና በቴክኖሎጂ ዝውውር መጠቀምን ማሻሻል” የሚል ዓላማ እንዲካተት ተደርጓል። ከዚህም በተጨማሪ ለአምስት ዓመት የሚፀና ልዩ ፈቃድ ከሌሎች አገሮች ደህንነተ-ህይወት ህጎች በተለየ ሁኔታ በተሻላው አዋጅ ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል። በዚህም የተነሳ በጠንቅ ግምገማና አስተዳደር (Risk Assessment and management) ላይ የሚያተኩረው የደህነነተ ህይወት (biosafety) ጥላ እንዲያጠላበትና በአንፃሩ ምርምሩና ስርፀቱ የበለጠ ትኩረት እንዲሰጠው እየተደረገ ነው።

ይህንን የተሻሻለውን አዋጅ በመጠቀም ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልገውን ጥጥ አቅርቦት ለማሻሻል በሚል በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተለያዩ ስድስት ቦታዎች ልውጠ-ህያው ወይም ቢቲ ጥጥ በተከለለ ቦታ ሙከራ (Confined Field Trial) ሲደረግ ቆይቷል። የሙከራው ሂደትና ውጤት እስከምናውቀው ድረስ ለህዝብ ይፋ አልተደረገም። ሌላው ቀርቶ በራሳችን ጊዜ ለመከታተልና ለማጣራት እንድንችል ሙከራ የሚደረግባቸው ስድስት ቦታዎች እንዲገለፅልን በተደጋጋሚ ላቀረብነው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ባለማግኘታችን ምን እየተሰራ እንደነበረ ማወቅ አልቻልንም ነበር። ይሁን እንጂ ቢቲ ጥጡ ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት በተለይ ጥጥ ፍሬው ለምግብ ዘይት ግብአትና ለከብት መኖ ፋጉሎ ሊውል ስለሚችልና በዚህም የተነሳ በሰውና እንስሳት ጤና እንዲሁም በብዝሃ ህይወትና አካባቢ ላይ ሊደርስ የሚችለው ጉዳት ተገምግሞ እንዲለይና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ሊደርስ የሚችል ጉዳት አለመኖሩን ወይም ቢኖርም ወደእምንትነት ደረጃ ዝቅ ለማድረግ የሚወሰደውን እርምጃ በተለመለከተ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ማረጋገጫ እንዲሰጠን መወትወት አላቆምንም።

ይህበዚህእንዳለInternational Service for the Acquisition of Agri-Biotech Application: ISAAAበተሰኘዓለምአቀፍድርጅትድረገፅ (web site) http://www.isaaa.org/kc/cropbiotechupdate/article/default. asp?ID=16515 ሰኔ 29 ቀን 21ዐ ወይም ጁን 6 ቀን 2ዐ18Ethiopia Approves Environmental Release of Bt Cotton and Grants Special Permit for GM Maize በሚል ርዕስ ኢትዮዮጵያ JKCH1050 እና JKCH1947 የተሰኙ ሁለት ልውጠ ህያው ቢቲ ጥጥ ዝርያዎች እንዲመረቱና ልውጠ ህያው በቆሎ ምርምር እንዲካሄድበት የፈቀደች መሆኗን ይፋ አድርጓል። ከዚህም ሌላ ሪፖርተር ጋዜጣ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ቅዳሜ ሰኔ 2 ቀን 2ዐ1ዐ ወይም ጁን 9 ቀን 2ዐ18 እትምGMO cotton approved for plantations” በሚል ርዕስ የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚንስቴር የተባለውን ፈቃድ በትክክል የሰጠ መሆኑን የሚንስቴሩን ደህንነተ-ህይወት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ጉዲና ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።

ጥያቄአችን ለምን ፈቃድ ተሰጠ ሳይሆን ፈቃዱ ከመሰጠቱ በፊት መሟላት የሚገባቸው ቅድመ-ጥንቃቄ እርምጃዎችና ዝግጅቶች ስለመደረጋቸው ህብረተሰቡ ያወቀው ነገር ስለሌለ ይህ ለምን ሆነ? ነው። በኛ በኩል ሊደረጉ ከሚገባቸው ቅደመ-ጥንቃቄ ዝግጅቶችና እርምጃዎች አንዱ የጉዳት ተጠያቂነትና ካሣን በተመለከተ ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምትነት አስተዋፅኦ ያደረገችበትና ምሳሌ ሆና ለዓመታት እልህ አስጨራሽ ድርድር ሲደረግበት የቆየው Nagoya - Kuala Lumpur Supplementary Protocol on Liability and Redressመስከረም 22 ቀን 2ዐዐ3 ወይም ኦክቶበር 2 ቀን 2ዐ1ዐ ድርድሩ ተጠናቆ አገሮች ፈርመዋል። ኢትዮጵያ ይህንን ፕሮቶኮል ማፅደቅና የህጓ አካል ማድረግ በተለይ ከልውጠ ህያዋን በሰው እና እንስሳት ጤና ላይ የሚደርስ ጉዳት ሲኖር ተጠያቂነትን በማስፈንና ካሣ ለማስከፈል እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ስንወተውት የነበረ ቢሆንም ምንም ተጨባጭ እርምጃ ሳይወሰድ ከቆየ በኋላ እ.ኤ.አ. ማርች 5 ቀን 2ዐ18 ወይም የካቲት 28/2ዐ1ዐ ኢትዮጵያን ሳይጨምር የ41 አገሮችን ድጋፍ አግኝቶ ሥራ ላይ ውሏል። ይህንን ፕሮቶኮል የአገሪቱ ህግ ሳያደርጉ ማንኛውንም ዓይነት ልውጠ-ህያው ወደ አገር ውስጥ ማስገባትም ሆነ በአገር ውስጥ ማምረት ተቀባይነት የለውም የሚል ጠንካራ አቋም አለን።  

ከዚህም ሌላ የደህንነተ ህይወት አዋጅ ቁጥር 655/2ዐዐ1 ሙሉ ለሙሉ ውድቅ ያልተደረገ በመሆኑ በአዋጁ አንቀፅ 11 መሰረት የህዝብ ተሳትፎ ለማረጋገጥ ሲባል የጠንቅ ግምገማ እንደደረሰውና ከግንዛቤ የመነጨ ስምምነት ለማግኘት ማመልከቻ ሲቀርብ በህዝብ ማስታወቂያ አውታሮች በኩል ከአንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የህዝብ አስተያየት ተሰብስቦ እንደግብአት ተጠቅሞ መወሰን እንደሚገባ ተደንግጎ እያለ ይህ ስለመደረጉ ምንም የሰማነው ወይም የተጠየቅነው ነገር ስላልነበረ ተገቢ አይደለም እንላለን። ተጠይቀን ቢሆን ኖሮ ልውጠ ህያው ቢቲ ጥጥ ማምረት ጀምረው ብዙ ተጠቃሚ ሆነዋል የተባሉት ለምሳሌ ህንድ፣ ደቡብ አፊሪካ፣ ቡርክና ፋሶ እንዴት አርሶ አደሮቻቸውና ስነ ምህዳሮቻቸው እንዲሁም ከብቶቻቸው እንደተጎዱና በተለይ የቡርኪና ፋሶ መንግሥት ምንም ዓይነት የቢቲ ጥጥ እንዳይመረት የክልከላ ትዕዛዝ አስተላልፎ እንዳስቆመ ፈቃድ ጠያቂዎቹም ሆነ ሰጭ የመንግሥት አካላት በተጨባጭ የሚያውቁት ሐቅ ቢሆንም ተጨማሪ ተጨባጭ ማስረጃ ማቅረብና ማስረዳት እንችል ነበር።

ስለዚህ እስካሁን ድረስ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከተከሰቱትና አሁንም በመከሰት ላይ ከሚገኙት የተለያዩ ጠንቆች አንፃር ልውጠ ህያው ዘር ወይም ምርት ወይም የምርት ውጤት ወደአገር ውስጥ ከመግባቱ ወይም ከመመረቱ በፊት የጠንቅ ግምገማ ማድረግና ችግር ቢከሰት ተጠያቂነትን የሚወስድ አካል እንዲኖር የህግ ማዕቀፍ እንዲኖር ማድረግ፣ ሰፊው ማህበረሰብ በቂ ግንዛቤ ኖሮት በንቃት እንዲሳተፍ ማድረግ በተለይ ባሁኑ ወቅት መንግሥት ከሚከተለው የህዝብን ጥያቄ መሰረት አድርጎ ከመሥራት አንፃር ተገቢና ወቅታዊ በመሆኑጉዳዩ እንደገና እንዲታይ ይህንን ጋዜጣዊ መግለጫ ለማውጣት ተገደናል።

ለወደፊቱም ልውጠ ህያውን በተመለከተ ስለሚተላለፉ ውሳኔዎች ሁሉ አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮች፣ ሸማቾች፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ የምርምርና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የህግ አስፈፃሚ አካላት እና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት፣ የመንግሥትና የግል መገናኛ ብዙሃን ሁሉ የየበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
39 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 110 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us