ሚድሮክ የወርቅ ማዕድን ኩባንያ በመተከል ወርቅ ሊያመርት ነው

Wednesday, 08 February 2017 14:19

ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኃ/የተ/ የግል ማህበር በቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መተከል ዞን በቡለን ወረዳ ጎንጎ በተባለ አካባቢ የከፍተኛ ደረጃ የወርቅ ማዕድን ለማምረት የሚያስችለውን ስምምነት ከማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ጋር ተፈራረመ፡፡ 

ስምምነቱን ጥር 22 ቀን 2009 ዓ.ም የፈረሙት አቶ ሞቱማ መቃሳ የማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ሚኒስትር እና ዶ/ር አረጋ ይርዳው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር እና የሚድሮክ ወርቅ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡

የውሉ ስምምነት ፊርማው ከተፈረመበት ቀን ጀምሮ ለ15/ለአሥራ አምስት/ ዓመታት የሚፀና ሆኖ የፈቃድ ዘመኑም ሲጠናቀቅ በባለፈቃዱ ጥያቄ መሠረት በእያንዳንዱ የፈቃድ ዕድሳት ጊዜ ከ10 /ከአስር/ ዓመታት ላልበለጠ ጊዜ ሊታደስ ይችላል፡፡

የፈቃዱ የቆዳ ስፋትም 27 ነጥብ 2 ካሬ ኪሎ ሜትር ሲሆን ኩባንያው ከዚህ በፊት ለምርመራ ሥራ ከ310 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያደረገ መሆኑንም በፊርማ ሥነሥርዓቱ ላይ ተገልፆአል፡፡ ኩባንያው በሙሉ ኃይሉ ወደ ሥራ ሲገባ ለ600 ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡

የአካባቢ ጥበቃን በተመለከተ የሠራተኞቹን፣ የአካባቢ ጥበቃና ነዋሪዎች ጤንነትና ደህንነት በማይጎዳ በተፈጥሮ ላይ ብክለት በማያስከትል መልኩ የምርት ስራውን የሚያከናውን ሲሆን ሥራውን ሲያቋርጥ በተፈጥሮ አካባቢ ላይ በሰው ህይወትና ንብረት እንዲሁም ዕፅዋት ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ማናቸውም ቅሪቶችና ግንባታዎችን ያስወግዳል፡፡ምርቱ ለስራው ተፈፃሚነት ባላቸው ህጎች መሰረት ያከናውናል፡፡

መንግሥት ለወርቅ ማምረቱ ውል ተፈጻሚነት በቅድሚያ በአካባቢው የሚገነውን የመሠረተ ልማት አውታሮች በተለይም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እና የመንገድ ግንባታ ማሟላት እንዳለበት ሁለቱ ወገኖች ተስማምተዋል፡፡

 

ስለሚድሮክ ማዕድን ልማት ጥቂት ነጥቦች

በኦሮሚያ ክልል በአዶ ሻኪሶ ወረዳ ለገንደንቢ አካባቢ በሻኪሶ ከተማ የሚገኘው የለገደንቢ ወርቅ ማዕድን በግል ይዞታ ኩባንያ ሆኖ ከመቋቋሙ በፊት የመንግሥት የልማት ድርጅት አካል ነበር፡፡ መንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዛወር ባወጣው ፖሊሲ መሠረት ለገደንቢ ወርቅ ማዕድን ኢንተርፕራይዝም በቀድሞው የኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ አማካኝነት ለግል ባለሀብቶች ለጨረታ ቀረበ፡፡ ለዚህም ጨረታ የተሳታፊዎችን ቁጥር ለማብዛት ሲባል ማስታወቂያው ለአንድ ጊዜ በላይ እንዲወጣ ተደርጎ እንደነበር ይታወቃል፡፡

ከወጣው የጨረታ ማስታወቂያ አኳያም የወርቅ ማዕድኑን ለመግዛት በጨረታው ውድድር የተሳተፉት 13 ያህል ኩባንያዎች ነበሩ፡፡ በወቅቱ ሚድሮክን ወክሎ በጨረታው እንዲሳተፍ የተደረገው ሀብትነቱ የሚድሮክ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሊቀመንበር ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ የሆነው ብሔራዊ ማዕድን ኮርፖሬሽን (National Mining Corporation) በሞግዚትነት ነበር፡፡ ከዚሁ ኮርፖሬሽን በስተቀር ሌሎች ኩባንያዎች ሁሉም የውጭ ሀገር ኩባንያዎች የነበሩ ሲሆን በጨረታው የማጣራት ሂትም መጨረሻ ላይ የደረሱት ኩባንያዎች ብሔራዊ ማዕድን ኮርፖሬሽን JCI Company እና Canyon Resources Corporation ብቻ ነበሩ፡፡

ጨረታው የተከፈተው ሚያዝያ 8 ቀን 1989 ዓ.ም (እ.ኤ.አ. 1997) ሲሆን በውድድሩም የተሻለ ከፍተኛ ዋጋ ያቀረበውና የጨረታው አሸናፊ ሆኖ የተገኘው ከሚድሮክ በኩል ስለመሆኑ ውሳኔው ለብሔራዊ ማዕድን ኮርፖሬሽን የተገለፀው ሰኔ 4 ቀን 1989 ዓ.ም (እ.ኤ.አ 1997) ነው፡፡ በመሆኑም የለገደንቢ ወርቅ ማዕድን ሕጋዊ ሽያጭ ውል በሚድሮክና በፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ መካከል እ.ኤ.አ. በጁን 1997 ተፈርሟል፡፡

ቀጥሎም የወርቅ ማምረት (Mining) እና ፍለጋ (Exploration) ሥራውን ማከናወን የሚያስችል ስምምነት ከቀድሞው ማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር እ.ኤ.አ. ማርች 29/1998 ተፈርሟል፡፡ ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኩባንያን በለገደንቢ የወርቅ ማምረቱን (Mining) እና የወርቅ ፍለጋ (Exploration) ሥራ ማካሄድ ያስቻለው ይኸው ስምምነት ነው፡፡ በስምምነቱ መሠረት ኩባንያው በዚሁ ለገደንቢ በሚባለው ሥፍራ ወርቅ ለማምረት 8 ነጥብ 4 ካሬ ኪሎ ሜትር (Sq.km) እንዲሁም ለወርቅ ፍለጋ ሥራ ደግሞ 80 ነጥብ 1 ካሬ ኪሎ ሜትር (Sq.km) ለመጠቀም የሚያስችለው ፈቃድ አለው፡፡

የወርቅ ማምረቱ ሥራ ፈቃድ በጠቅላላ 20 ዓመታት ፀንቶ የሚቆይ ሲሆን፤ ስምምነቱ ለኩባንያው ተጨማሪ የ10 ዓመታት ፈቃድ ማግኘት የሚያስችለው ነው፡፡

በወርቅ ፍለጋ ረገድም ኩባንያው በማዕድን አዋጁ መሠረት በየጊዜው የሚታደሱ ፈቃዶችን ተግባራዊ በማድረግ የሚሰራ ሲሆን በተደረገው ከፍተኛ የወርቅ ፍለጋ ሥራ ኩባንያው ሁለተኛውን የወርቅ ማምረት ፈቃድ አግኝቷል፡፡ ይህም ሁለተኛ የማምረት ፈቃድ በሳካሮ የማምረት ፈቃድ ያስገኘ ሲሆን፤ የምርት ተግባሩ እ.ኤ.አ በ2009 ተጀምሯል፡፡ ፈቃዱም የ20 ዓመት ውል ያለው ነው፡፡

ኩባንያው በሥራው እያደገ ስለመምጣቱ ሌላው መገለጫ ከለገደንቢና ሳካሮ የማዕድን ማምረቻ ሌላ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ በተመለከተ ዞን የማዕድን ፍለጋ (Exploration) በብር 310 ሚሊዮን ወጪ ለ10 ዓመታት እንዲካሄድ በማድረግ ኩባንያው የፕሮጀክቱን አዋጭነት ማረጋገጡ ነው፡፡ ከዚሁ አንጻርም የከፍተኛ ማዕድን ማምረት (large scale mining) ፈቃድ ስምምነት ከማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ጋር ሰሞኑን ፈጽሟል፡፡ በዚህም ስምምነት መሠረት መተከል የኩባንያው ሶስተኛው የወርቅ ማዕድን ማምረቻ ተቋም ሆኗል፡፡     

ሚድሮክ ጂኢኦ እና ኤክስፕሎረሽን አገልግሎት ኃ/የተ/የግ/ማህበር ዘመኑ በሚፈቅደው ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና ብቃት ባላቸው የሰለጠኑ ባለሙያዎች በመታገዝ ከማዕድን ልማት ጋር በተያያዘ በዋንኛነት የአፈር ምርመራና የቁፋሮ ሥራ የሚያከናውን ሀገር በቀል ብቸኛ ኩባንያ ነው፡፡ ኩባንያው የማዕድን ፍለጋና ምርመራ እንዲሁም የቁፋሮ (ኤክስፕሎረሽን) ሥራዎችን ለሚድሮክ ወርቅ ኩባንያ ብቻ ሳይሆን አገልግሎቱን ለሚፈልጉ የተለያዩ ኩባንያዎችም በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡

ሚድሮክ ወርቅ ኩባንያ እና ሚድሮክ ጂኢኦ እና ኤክስፕሎረሽን ኃ/የተ/የግል ማህበር ከማዕድን ልማት ጋር በተያያዘ በሚያከናውኑዋቸው ፕሮጀክቶች የአካባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሌሎች ፕሮጀክቶችን በመገንባት ለሀገራዊ ልማት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ ኩባንያዎቹ የማዕድን ልማት በሚያከናውኑባቸው አካባቢዎች የትምህርት ተቋማትን፣ የገጠር መንገዶችን፣ የንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦቶችንና መሰል የልማት ተግባራት በመሳተፍ ሕዝባዊ ወገንተኝነታቸውን በተግባር አስመስክረዋል፡፡

በተጨማሪም በወርቅ ሽያጭ ገቢ ብቻ ሳይሆን በሮያሊቲ ፣ በገቢ ታክስ እና በሠራተኞች ደመወዝ ገቢ ግብር በማስገባት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት አዎንታዊ ሚናቸውን እየተወጡ ነው፡፡

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
735 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1056 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us