“ባወቅነው ልክ [በሙሰኞች ላይ] እርምጃ እየወሰድን ነው”

Wednesday, 11 January 2017 14:36

“ባወቅነው ልክ [በሙሰኞች ላይ] እርምጃ እየወሰድን ነው”

ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ

 

ጠ/ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ጥር 1 ቀን 2009 ዓ.ም በጽ/ቤታቸው ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል። ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የመጡ ጋዜጠኞች የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ ጥያቄዎቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን፤ ዝግጅት ክፍላችንም ከእነዚህ ጥያቄዎች መካከል በመንግሥት ጥልቅ የተሀድሶ ንቅናቄ ጋር በተያያዘ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ጋር በተያያዘ ለተነሱ ጥያቄዎች ጠ/ሚኒስትሩ የሰጡትን ምላሾች ከዚህ በታች አቅርበናል።

 

 

ከጥልቅ ተሀድሶው ጋር በተያያዘ የከፍተኛ አመራሩ ተጠያቂነት ጉዳይ፣

በማንኛውም መንግሥት የአመራር ሥርዓቱ ወሳኝ ነው። በሒደት የካፒታሊስት ሥርዓት እንደምንገነባ ሁሉ፣ ሥርዓቱና የሚያጋጥሙት አደጋዎች ምንድናቸው የሚለውን ለይተናል። ከሚያጋጥሙ አደጋዎች አንዱ ሥራውን የሚመራው አካል ቀስ በቀስ የራሱን ኑሮ፣ ሕይወት የማሻሻል፣ የግል ብልፅግናውን የመፈለግ፣ የቆመለትን ዓላማ እየሸረሸረ መሄድ፣ በአመለካከት ደረጃ፣ በሒደትም በተግባር የሚገለፅ ችግር እንደሚያጋጥም ይታወቃል። ስለዚህ ይሄ ነገር ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን ከበርካታ ዓመታት በፊትም ኢህአዴግ በተሃድሶ እንቅስቃሴ ይሄንን መሠረታዊ የኢህአዴግ መርህ የሚሸረሽሩ እርምጃዎችን ማስተካከል ይገባናል በሚል ስንሠራ ነበር ቆተናል።

የአሁን የ15 ዓመቱን የተሀድሶ እንቅስቃሴ በምናከብርበት ጊዜ ያመጣናቸው በርካታ ለውጦች አሉ። ይሄ ሀገር ከጥልቅ ድህነት እንዲወጣ፣ በዓለም ኅብረተሰብ ዘንድ እያደገ ያለ ኅብረተሰብ ሆኖ እንዲመዘገብ ያደረጉ አፈፃፀሞች አሉ። እነዚህ በገሀድ የሚታዩ፣ ለማንም የማይደበቁ ናቸው። ይሄንን በምንፈፅምበት ጊዜ ግን ፈተናዎችም ነበሩ። ከፈተናዎቹና ተግዳሮቶቹ ዋናውና በውል ለይተን የጠቀስነው የመንግሥትን ሥልጣን የምናይበት መንገድ አንዱ ነው። ይሄ የመንግሥትን ሥልጣን የምናይበት ሁኔታ በምንፈትሽበት ጊዜ በሌብነት (በሙስና) መልክ የሚገለፅ አስተሳሰብና አሠራር አለ። ከዚያ ባሻገር ግን የያዘውን ሥልጣን ለሕዝብ አገልግሎት ማዋል ሲገባው፣ ሌት ተቀን ተረባርቦ ውጤት ማምጣት ሲገባው፣ ኑሮውን፣ ቤተሰቡን፣ ሕይወቱን በመምራትና ባይሰርቅ እንኳን ቅንጡ የሆነ ኑሮ (ሌግዥሪየስ) ኑሮ ለመኖር የመሞከር ችግር ታይቷል። ከዚህ ጀምሮ እስከ ስርቆት ድረስ የሚዘልቅ የተለያየ ደረጃ ያለው ጉዳይ አለ።

እጅግ አብዛኛውን ሰው እያጠቃ ያለው አመለካከት ለሥራው ከመትጋት፣ ሌት ተቀን ከመረባረብ ይልቅ መዝናናትን የመምረጥ ጉዳይ፣ ሕዝብን በአግባቡ ያለማስተናገድ ጉዳይ፣ እንደማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ 11፡30 ጠብቆ የመውጣት ወይም ከሥራ ሰዓት ውጪ አርፍዶ መሥራት ያለመፈለግ፣ የተለያዩ ጉዞዎችን ማብዛት፣ የተለያዩ ውጤት የማያመጡ ጉዳዮች ማብዛት፣ ሥልጣንን ለኅብረተሰብ ለውጥ እንጠቀማለን ብሎ ለወሰነ ፓርቲ የማይገቡ ድርጊቶች ናቸው። እንግዲህ ሰዎች በሚቀየሩበት ጊዜ ይህንን መስፈርት ከታች ጀምሮ ያሟላ ሰው ብቻ ነው ለዚህ የሕዝብ አገልግሎት ሊሰለፍ የሚገባው ተብሎ ይወሰዳል።

ስለዚህ አንዳንዱ ተሿሚ ከራሱ የአቅም ማነስ ጋር (የተሰጠውን ሥራ በብቃት ለመወጣት ዕውቀትም፣ ክህሎትም በተለይም የአመለካከት ያለመያዝ ነው) በጠቅላላው ሥርነቀል በሆነ መንገድ ማየት ይገባናል በሚል የታየ ጉዳይ ነው። ስለዚህ ሰዎች በሚነሱበት ጊዜ ከእነዚህ በአንዱ ተገምግመው ነው ማለት ነው። ስለሆነም ከአቅም ማነስ ችግር ጋር ተገምግሞ የሚነሳ ሰው ካለ በአቅሙ የሚመደብበት ሁኔታ መኖር አለበት። ስለዚህ ዝቅ ብሎ በአቅሙ የሚመደብበት ሁኔታ ታይቷል። በተመሳሳይ መንገድ ሌሎች አካባቢዎች ላይ የተመደበ ሰው ካለ በተመሳሳይ መታየት አለበት። ነገር ግን ግልፅ ሊሆን የሚገባው በምንም መልኩ በስርቆት፣ በሌብነት፣ በሙስና ማስረጃ እያለ ሊቀር የሚችል ሰው አይኖርም። አንዳንድ ጊዜ ጥርጣሬዎች ይኖራሉ። አንድን ሰው ተጠያቂ ማድረግ የሚቻለው በሁለት መንገድ ነው። አንዱ አስተዳደራዊ በሆነ መንገድ ከሥልጣን ይነሳል። ከሥልጣን ከተነሳ በኋላ በቂ ማስረጃ ካለህ እንዲጠየቅ ታደርጋለህ። በቂ ማስረጃ ከሌለ ደግሞ ወደ ሕግ አቅርበህ ልታሸንፍ ስለማትችል ትርጉም የለውም ማለት ነው። ሙስና በጣም ውስብስብ የሆነ ነው። በተገኘው ማስረጃ ልክ ተጠያቂ እያደረግን መጥተናል። ነገር ግን በዚህ ያበቃል ማለት አይደለም። ሙስና ውስብስብነቱ ታውቆ አሁን ከሥልጣን ላይ የወጡ ወይንም በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ካሉ በጥናት ላይ እየተመሠረተ መሄድ መቻል አለበት። እንደሥርዓት በተሃድሶው እንቅስቃሴ እናካሂዳለን ያልነው ሕዝቡ በፀረሙስና ትግሉ በስፋትና በጥልቀት የሚሳተፍበትን ሁኔታ ማመቻቸት ማስረጃዎችን ለማግኘት በጣም ወሳኝ ነው። በብዙ ሀገሮች እንደተለመደው የሙስና ወንጀል ውስብስብነት ታሳቢ ያደረጉ፣ ሕዝብ ማስረጃ የሚሰጥበትን አደረጃጀቶችን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል። ከዚህ አኳያ መንግሥት የወሰነው የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ማዕከል አቋቁሞ ሕዝቡ በየጊዜው መረጃዎችን፣ ማስረጃዎችን የሚሰጥበትን ሁኔታ የማመቻቸት፣ ሁለተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሐብትና ንብረት ምዝገባ ይፋ የሚሆንበት ሁኔታ ማመቻቸት ያጠቃልላል።

የመንግሥት ባለሥልጣናት ሐብት ይፋ ሲሆን ከዚህ የተለየ ተጨማሪ ሐብት አለው። በራሱ ብቻ ሳይሆን በዘመዶቹ፣ በወዳጆቹ የተያዘ ሐብት አለ የሚል ካለ እንዲጠቁም ነው። ከዚያም አልፎ የፀረሙስና ትግል ተቋማት አሉ። በቅርቡ በተጠናከረ መልኩ ያቋቋምነው የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አለ። በሥራ ላይ ያለው የሥነምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን አለ። እንደዚሁም የፖሊስ ኮሚሽናችንን ከዚህ በፊት ከነበረው አደረጃጀት ለየት አድርገን በአሜሪካን ሀገር እንደሚታወቀው ኤፍ ቢ አይ ዓይነት የምርመራ ቢሮ አቋቁመናል። ተቋሙ በሰው ኃየልም በማቴሪያልም ተጠናክሮ ጥቆማዎች ለመቀበል የሚያስችል ነው።

አሁን በመጣው የመረጃ ቴክኖሎጂ በኩልም ሕዝቡ ጥቆማ የሚያቀርብበት ሁኔታ ይመቻቻል። ዋናው ጉዳይ ግልፅነትን የማስፈን ጉዳይ ወሣኝ ነው። ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የተቋማዊ ግንባታ ሥራ ተጀምሯል። የተደበቁ ነገሮችም ካሉ ፈልፍሎ በማውጣት የፀረሙስና ትግሉን ማጠናከር ይቻላል። ዞሮ ዞሮ ይሄን ውስብስብ ወንጀል በሕዝብ ተሳትፎ ላይ የተመሠረተ መከላከልን አድርጎ መሄድ ጉዳይ ነው። ይሄ ለእኛ ዋንኛውን ጉዳይ አይተካም። ዋንኛው ጉዳይ ሰው አስቀድሞ በአመለካከት ሙስናን የሚጠየፍ ኅብረተሰብ በመፍጠር ዙሪያ ነው ማተኮር ያለብን። ከዚህ አኳያ በተሀድሶ ጊዜ ዋነኛ ድል ተብሎ ሊወሰድ የሚገባው የሚታማ ነገር ካለ ወደመድረክ እንዲወጣ ይረዳል።

ይሄ የሚሰጠን ዕድል በአመለካከት ዙሪያ ሰዎች እንዲገነቡ ያደርጋል። ሙስና የማይታለፍ መሆኑ ግንዛቤ ላይ ይወድቃል። ሁሉም ሰው ራሱን የሚጠብቅበት፣ ራሱን የሚገዛበት ሁኔታ ያመቻቻል። ሰው ራሱን የማይገዛ፣ በአመለካከቱ ራሱን የማይመራ ከሆነ ምንም ብታደርገው መስረቁን አይተውም። ሙስና የአመለካከት መሸርሸር ውጤት ነው። ሙስና ሕዝብን ከማገልገል ይልቅ ራስን የማገልገል አመለካከት የበላይነት ይዞ የሚታይበት ነው። ከዚህ አኳያ በመንግሥትም ሆነ በድርጅታችን ውስጥ ያስቀመጥነው አመለካከት የመገንባት ጉዳይ አንዱ ነው።

እናም ሁሉም ከፍተኛ አመራር ንፁህ ነው ሊባል አይችልም። ንፅህና የሚለካው በተግባራዊ እንቅስቃሴና እንዲሁም ኅብረተሰቡ የሚያቀርባቸውን መረጃዎች መሠረት አድርጎ ነው። ሙስናና ብልሹ አሰራር ለማስወገድ መቼም ጊዜ ቢሆን እረፍት የማይሰጥ ትግልን ይጠይቃል።

የመልካም አስተዳደር ጉዳይ፣

የመልካም አስተዳደር ችግር በዋነኛነት የአመለካከት ችግር ነው ብያለሁ። ስለዚህ በዚህ ደረጃ ከፍተኛ አመራሩ የአመለካከት ችግር አለ ብሎ አምኖ ተቀብሏል። ባገኘነው መረጃና ማስረጃ ልክ ሰዎች ተጠያቂ ሆነዋል። የትኛው ማስረጃ ኖሮ ነው እርምጃ ያልወሰድነው፣ ይነገረን እያልኩኝ ነው። ይሄ ማስረጃ እያለ አላሰራችሁም የሚል ከሆነ ይፈትነን። እርምጃ የሚወሰደው በተጨባጭ ማስረጃ ላይ ተመስርቶ ነው። ሙስና ውስጥ የሚዘፈቅ ሰው፣ ለሰው ነግሮ አይሰርቅም። ከሰረቀ ውስብስብ አድርጎ፣ ደብቆ ነው። ይሄ ሊገለጥ የሚችለው ኅብረተሰባዊ እንቅስቃሴ ሲኖር ብቻ ነው። ከዚህ ተነስተን ባወቅነው ልክ እርምጃ እየወሰድን ነው። አሁንም እንቀጥላለን።¾ 

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
511 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us