“የስታዲየም ፕሮጀክቱ ካሳደገንና ካስተማረን ሕዝብ ጋር ይበልጥ የሚያስተሳስረን ነው”

Wednesday, 11 January 2017 14:27

“የስታዲየም ፕሮጀክቱ ካሳደገንና ካስተማረን ሕዝብ ጋር ይበልጥ የሚያስተሳስረን ነው”

ዶ/ር አረጋ ይርዳው፤ የፕሮጀክቱ ዋና መሪ

 

በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን ወልድያ ከተማ የተገነባው “ሙሐመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲ ስታዲየምና የስፖርት ማዕከል” ቅዳሜ ጥር 6 ቀን 2009 ዓ.ም በወልድያ ከተማ ከፍተኛ የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናት፣ የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የወልድያ ከተማ ሕዝብ፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ይከናወናል። ይህ በዓይነቱም ሆነ በጥራቱ ለሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን ስታዲየም ግንባታ ሒደት ጋር በተያያዘ ከዶ/ር አረጋ ይርዳው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር እና የፕሮጀክቱ ዋና መሪ ጋር ያደረግነው አጭር ቃለምልልስ ከዚህ በታች ተስተናግዷል። መልካም ንባብ።

 

ሰንደቅ፡- በወልድያ ከተማ ያሳለፉትን የልጅነት ጊዜ እንዴት ያስታውሱታል?

ዶ/ር አረጋ፡- የተወለድኩት ጎንደር ነው። ወልድያ የሄድኩት በ1949 ዓ.ም ነው። ጊዜውን የማስታውሰው ልዑል መኮንን የሞቱበት ዓመት በመሆኑ ጭምር ነው። ወልድያ እንደመጣሁ የገባሁት ሶስተኛ ክፍል ነው። ጎንደር የቤተክህነት ትምህርት ስማር ነበር። በወልድያ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴን ያጠናቀቅሁት በአራት ዓመት ነው። ከሶስት እስከ ስምንተኛ ክፍል በነበረኝ የትምህርት ቆይታ ጎበዝ ተማሪ ስለነበርኩኝ በአንድ ዓመት ሁለት ክፍል እየዘለልኩኝ ያለፍኩባቸው ዓመቶች እንደነበሩ አስታውሳለሁ። የተማርኩት በወልድያ ከተማ በሚገኘው የእቴጌ ጣይቱ ብጡል የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት ነበር፤ ት/ቤቱ በወቅቱ በከተማዋ ብቸኛ ነበር። በወቅቱ እርሻ፣ ስፖርት፣ እጅ ሥራ ፣ሥዕል የመሳሰሉ ትምህርቶችን ሁሉ እንማር ነበር። በወቅቱ በሁሉም ትምህርት አንደኛ ለመሆን ጥረት አደርግ ነበር። ስለዚህ በጣም የምደሰትበት የትምህርት ወቅት አሳልፌለሁ። የክፍል ጓደኞቼ ላይ የነበረው የትምህርት ፍላጎት የተለየ ነበር። ሰኔ ወር ላይ ከአንደኛ አስከ ሶስተኛ ደረጃ ለሚያገኙ ጎበዝ ተማሪዎች ከትምህርት ሚኒስቴር የሚሰጥ ልዩ ሠርተፊኬት እንደነበር አስታውሳለሁ። ሽልማቱ የወላጆች ስብሰባ ተጠርቶ እከሌ አንደኛ፣ እከሌ ሁለተኛ፣ እከሌ ሶስተኛ ወጥቷል ተብሎ ይነገራል። ይሄን አስታውሳለሁ። ሌላው የ7ኛ ክፍል፣ የ8ኛ ክፍል ቡድን እየተባለ እግር ኳስ ጨዋታ እናደርግ ነበረ። የእጅ ሥራ እና ሥዕል ትምህርቶች የተለየ ፍላጎት ነበረኝ። ይህ መሠረቴ ነው፤ ወደመሐንዲስነት የወሰደኝ ብዬ አስባለሁ። በወቅቱ በት/ቤቱ ውስጥ ት/ቤቱ የተሟላ የተግባረዕድ ቁሳቁሶች እንደነበሩ አስታውሳለሁ። ፕሮጀክት ተሰጥቶን ለመጀመሪያ ጊዜ ጃንጥላ መስራቴንም አልዘነጋውም። ቆንጆ የኬሚስትሪና የፊዚክስ ላብራቶሪ ነበረን። ሌላ ትዝ የሚለኝ በ1952 ዓ.ም ይመስለኛል፤ 8ኛ ክፍል ስንፈተን ተፈታኞች በምዝገባ ቁጥራቸው የፈተና ውጤት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ሲወጣ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር። ስለዚህ ማለፍና መውደቅ የሚታወቀው በጋዜጣ ነው ተብሎ ጋዜጣ ለማግኘት የምናደርገው ጥረት አስታውሳለሁ። በመጨረሻም ተገኝቶ ቁጥሩን አይቼ ማለፌን ሳውቅ የተሰማኝን ከፍተኛ ደስታ አልረሳውም። ተማሪ እያለን ብዙዎቻችን ቁምጣ ሱሪ ነበር የምናደርገው፣ በወቅቱ ሸራ ጫማም እንጫማ ነበር።

አባቴ ልብስ ነበር የሚሰፉት። እኔም በወቅቱ የስፌት ሙያ ተምሬ በትርፍ ጊዜዬ ልብስ እሰፋ ነበር። ማክሰኞ ትልቅ ገበያ ስለነበር ልብስ ተቀዶበት የሚመጣ ሰው ካለ እሱን አስተካክዬ ሳንቲም ለማግኘት የምሞክረውን አስታውሳለሁ። ወጣት እንደመሆኔም የመጀመሪያ የፍቅር ጊዜ ያሳለፍኩት በወልድያ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት የተከለከለ ቢሆንም ውስጥ ለውስጥ ደብዳቤ መፃፃፍ፣ የመሳሰለውን እንደዕድሜ እኩዮቻችን እናደርግ ነበር።

 

 

ሰንደቅ፡- የወልድያ ስታዲየም ግንባታ ገንዘብ ማሰባሰብ ፕሮግራም በሸራተን ሆቴል ሲካሄድ ሼክ ሙሐመድ የተወሰነ ድጋፍ ያደርጋሉ ተብሎ ሲጠበቅ ሙሉ በሙሉ እሰራዋለሁ በማለት ቃል ገቡ። ለእርስዎም ይህንኑ እንዲያስፈጽሙ  አደራ  ሰጡ፤ በወቅቱ ምን ተሰማዎት?

ዶ/ር አረጋ፡- ለግንባታው ገንዘብየማሰባሰብ ፕሮግራም ሲጀመር የአዲስአበባ ኮሚቴ ሊቀመንበር እኔ ነበርኩኝ። ባህርዳር ሌላ ኮምቴ ነበር፤ ወልድያም እንዲሁ። የስታዲየሙን ግንባታ ዕቅድ መጀመሪያ ያሰቡት የወልድያ ከተማ አስተዳደር (ዞኑ) ይመስለኛል። ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ ተሰባስበን ገንዘብ አሰባሳቢ ኮሚቴ አቋቋምን። እውነቱን ለመናገር ሰዎችን አሳምኖ ገንዘብ ለማግኘት ብዙ ለፋን። እዚህ አካባቢ ምናልባትም ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ያሰባሰብንም አይመስለኝም። ወልድያ ያለው ደግሞ ወደ 28 እና 29 ሚሊዮን ብር አወጡ። ሲጠቃለል የተሰባሰበው ወደ 30 ሚሊዮን ብር ገደማ ነው። የገንዘብ መዋጮ ለመሰብሰብ በአዲስ አበባ መቻሬ ሜዳ ብዙ ጊዜ እንሰበስብ ነበር። የሚሰጠው ገንዘብ ስንመለከተው መቼ ነው ሚሊየን የሚሆነው የሚለው ያስጨንቀን ነበር። ገንዘቡ ስታዲየሙን ባይገነባም ቢያንስ ቢያንስ የተወሰነ ቀዳዳ ይሸፍንልናል የሚል ስሜት በብዙዎቻችን ዘንድ ነበር። ከሕዝቡ የተሰበሰበው ብር አሁን መጨረሻ ላይ የእንግዳ ማረፊያ ህንፃ ሊሰራልን ችሏል።

ለስታዲየሙ ግንባታ ገንዘብ የማሰባሰብ ሃሳብ በመጣበት ወቅት ስለጉዳዩ  ከሼክ ሙሐመድ ጋር ስንገናኝ እናወራ ነበር። በወልድያ ስታዲየም የመገንባት ሃሳብ እንዳለ አሳወኩት። እኔና እሱ ስለዚህ ጉዳይ ብዙ ተወያይተናል። በዚህ ምክንያት በሸራተን ሆቴል ገንዘብ የማሰባሰብ ፕሮግራም ሲካሄድ ለእኔና ለእሱ አዲስ ነገር አይደለም። በሸራተን ቃል የገባውን ጉዳይም ቢሆን አስቀድሜ የዚያ ዓይነት ስሜት እንዳለው አውቅ ስለነበር ለእኔ ውሳኔው አዲስ ነገር አልነበረም። በሌላ በኩል የወልድያ ነዋሪዎች ባገኙኝ አጋጣሚዎች ሁሉ የስታዲየሙ ግንባታ ሼክ ሙሐመድ ቢያግዙን፣ ብትነግርልን የሚል ጥያቄዎችን ያቀርቡልኝ ነበር። ስለዚህ እንደዚህ ዓይነቶቹን ስሜቶች ለእሱ አንፀባርቄያለሁ። ስለዚህ ነገሩን አስቀድሞ አውቆት ነው የገባው። የስታዲየሙ ግንባታ ወጪ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚፈጅ ሲታወቅና የምናሰባስባት ገንዘብ ትንሽ መሆኗ ሲታወቅ እኛ ብንሠራው ይሻላል በሚል ሼህ ሙሐመድ ቃል ገባ። ይህንንም ተከትሎ ኃላፊነቱን ለእኔ መስጠቱ አዲስ ነገር አይደለም። አንደኛ የምህንድስና ባለሙያ ነኝ። ሁለተኛ እንደምሰራው ያውቃል። ሦስተኛ ስለወልድያ ያለንን የጋራ ስሜት በሚገባ ይገነዘባል። ፕሮጀክቱ ካሳደገንና ካስተማረን ሕዝብ ጋር ይበልጥ የሚያስተሳስረን እንደሆነ ሁለታችንም እናውቃለን። ቀደም ብለን ተወያይተንበት ስለነበር ኃላፊነቱ ሲሰጠኝ ለእኔ ያልተጠበቀ ዱብዕዳ አልነበረም። ኃላፊነቱን በደስታ ተቀብዬ ወዲያውኑ ወደሥራ ገባሁኝ።

 ይህ ሲደረግ ደግሞ በሌላ በኩል ሌላ የቤት ሥራ አከናውን ነበረ። ቀደም ብዬ ስታዲየሙን ሼህ ሙሐመድ የሚሰራልን ቢሆን ምንታደርጋላችሁ በሚል ሕዝቡን አነጋግር ነበር። ያነጋገርኩዋቸው የሕብረተሰቡ አካላት በሙሉ ስታዲየም በስሙ እንዲሰየም እንደሚያደርጉ ቃል ገብተውልኛል።

 

ሰንደቅ፡- ወደሥራው ስትገቡ በኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ ቀደም በዚህ ደረጃ ያለ ስታዲየም ግንባታ ልምድ አልነበረም። ይህ ሁኔታ አላስቸገራችሁም?

ዶ/ር አረጋ፡- የስታዲየም ግንባታ የተወሳሰበ ሥራ አይደለም። ቀላል ሥራ (ስትራክቸር) ነው። ዝም ብለህ ብታስበው የደረጃ ብዛት ነው። እስከዚህ የተወሳሰበ አይደለም። ስታዲየም ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ተሠርቷል ብዬ አምናለሁ። 50 ዓመት ገደማ ይሁነው እንጂ የአዲስ አበባ ስታዲየም አለ። አበበ ቢቂላም ጥሩ ስታዲየም ነው። ሌላው ቀርቶ ጎንደር ልጅ ሆኜ ስታዲየሙን አስታውሳለሁ። ባህርዳር ቆንጆ ስታዲየም ተሠርቷል። መቀሌም ተጀምሯል። ስለዚህ ስታዲየም የመሥራት፣ ዲዛይን የማድረግ ዕውቀት አለን።

የወልድያ ስታዲየም ግንባታ ስንገባ ቀደም ሲል ተሠርቶ የነበረውን ዲዛይን ተጨማሪ ነገሮችን ስለሚያስፈልጉት መሻሻል ነበረበት። የሚያስፈልግ ነገሮች ተጨመሩ። መጀመሪያ 200 ሚሊየን ብር ገደማ የሚፈጅ ዲዛይን ነበር። ስለዚህ የዲዛይን ልምዱ አለ ብዬ አምናለሁ። ከዚያ ወደሥራ ሲገባና አንዳንዶቹ ነገሮች አዲስ ሲሆኑብን ለምሳሌ እንደጣሪያ ክዳን ስንሰራ ልኬቶቹን እርግጠኛ ለመሆን ጭምር አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እየሄድን በባለሙያዎች እንዲያዩዋቸው እናደርግ ነበር። ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ዕውቀቱ አለ። እርግጥ ነው፤አዳዲሶቹ ስታዲየሞች ለየት ያለ ስትራክቸር አላቸው፣ ማቴሪያሎቹ ለየት ያሉ ናቸው። በአሁን ሰዓት ቦሌ መድሐኒዓለም አካባቢ በመሠራት ላይ ያለው ስታዲየም ከዚህ አንጻር ሊጠቀስ ይችላል። ብዙዎቹ ነገሮች ውጪ ተሠርተው መጥተው እዚህ ይገጣጠማሉ ብዬ እገምታለሁ።

ሰንደቅ፡- ሌላው በዚህ ግንባታ ያገኛችሁት ትልቅ ልምድ አለ፣ ወደፊት ሁዳን ጨምሮ ያገኛችሁትን ዕውቀት ለማሸጋገር ምን አስባችኋል?

ዶ/ር አረጋ፡- እኔ ፕሮጀክቱን ስጀምር በቅድሚያ ያደረኩት ነገር ቢኖር ፕሮጀክቱን ራሴ መምራት ጀመርኩኝ። ሌላው ከቴክኖሎጂ ግሩፑ 25 ኩባንያዎች 10 ኩባንያዎች እንዲሳተፉ አደረኩኝ። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ በዲዛይንና በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚንቀሳቀሰው ሁዳ ሪል ስቴት ነው። እሱን ዋና አደረግንና ለሌሎቹ ሰብ ኮንትራት እንዲወስዱ አደረግነው። መጀመሪያ የነበረውን ንድፍ በመውሰድ ዲዛይኑ ሦስት ጊዜ ያህል እንዲሻሻል አድርገናል። የዲዛይን ልምድ ያገኘንበት ነው። ወጣት መሐንዲሶች ናቸው። ስታዲየም ሠርተው አያውቁም፣ ዲዛይንም አድርገው አያውቁም። አንዴ ከገባንበት በኋላ ሥራውን ወሰዱ። ከዚያ ቀጥሎ የሚያስፈልጉ አንዳንድ ቁሳቁሶች ታይልስ፣ ብረታ ብረት፣ የእንጨት ሥራዎች በሙሉ በቴክኖሎጂ ግሩፑ ኩባንያዎች የተሰሩ ናቸው። የጣራ ክዳኑን ኮስፒ ነው የሠራው። እሱን ለመሥራት ከውጪ ሀገር ፕሌቶች እያመጣን፣ እየቆረጥን እየበየድን፣ ካልኩሌት እያደረግን የሠራነው ነው።

ይህ ፕሮጀክት ልዩ የሚያደርገው ነገር የሼህ ሙሐመድ ድርጅቶች - የሙያ ክህሎት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። ስታዲየሙን ሠርቶ ማስረከቡ አንድ ጥቅም ነው። በተጨማሪም ዕውቀቱ ቤታችን እንዲቀር አድርገናል። ወጣት መሐንዲሶችን ቀጥረናል። ይህን ያደረግነው እንዲማሩና እንዲያድጉ ጭምር ነው። መዓት የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች ከወልድያ ወስደን አሰልጥነናል። ከልምድ አኳያ እነኚህ ልጆች ስታዲየም ቀርቶ ሌላም ለመሥራት ዕውቀቱ አላቸው። ይኸኛው ኦርጋኒክ ዓይነት ስታዲየም ነው፤ በኢትዮጵያዊያን የተሠራ ነው። ከውጪ እርዳታ አግኝተናል ወይ ከተባለ አዎን በሚያስፈልገን ብቻ መጠነኛ ድጋፍ አግኝተናል። መብራት መግዛት ነበረብን። ገዝተን ራሳችን ተከልን። ማስተካከሉ (አጀስትመንቱ) ለውጪ ባለሙያዎች ሰጠን። ምክንያቱም መብራቶቹ እንደ አዲስ አበባ ስታዲየም አራት ቦታ የተተከሉ ሳይሆኑ ትሪብዩን ላይ ሁሉ የተገጠሙ ናቸው። ጨረሮቹ ዓይን እንዳይወጉ በዘርፉ ባለሙያዎች መስተካከል ነበረባቸው። የመሮጫ ትራክ ማቴሪያል ያስመጣነው ከቻይና ነው። የመሮጫ ትራኩ እንዴት ተደርጎ እንደሚነጠፍ የውጭ ባለሙያዎቹ እግረመንገድ እንዲያሳዩን አድርገናል።

ከወልድያ ግንባታ ባሻገር ተመሳሳይ ኮንትራቶች አዲስ አበባ አካባቢ ስናገኝ ለመስራት ሁለት ቦታ ሞከርን። ነገርግን አልተሳካም። መንግስት ወደፊት እንደዚህ ዓይነት ኮንትራት በሚኖረው ጊዜ በተለየ መንገድ የሚያይበት መንገድ ቢኖር ጥሩ ሊሆን ይችላል።

ሰንደቅ፡- በመጨረሻም ስታዲየሙ ተጠናቅቆ፣ ለሕዝብ ልታስረክቡ በገባችሁት ቃል መሠረት ወልድያ መገኘታችሁ ምን ስሜት ይሰጥዎታል?

ዶ/ር አረጋ፡- ከሙያ አኳያ እኔ መሐንዲስነቴን እወዳለሁኝ። እንደምታውቀው ከአውሮፕላን ቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ በአሜሪካን ሀገር ለረዥም ዓመታት ሰርቻለሁ። አንድን ፕሮጀክት ፕላን አድርጎ፣ ዲዛይን ሠርቶ፣ አምርቶ፣ ሙከራ አካሂዶ ሥራ ላይ ማዋል የብዙ ዓመት ሥራዬ ነው። ወደ ሀገሬ ከመጣሁ በኋላ ደግሞ ከበድ ባለ መልኩ ሥራዎችን እየመራሁኝ፣ አብሬ እየሠራሁኝ፣ እዚህ ደረጃ ማድረሳችን እንደመሐንዲስነቴ አርክቶኛል። ሌላው የማኔጅመንት አቅሜንም ፈትኜበታለሁ ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም የምንሠራው ዲዛይን ብቻ አልነበረም። ሌሎችንም ሥራዎች ጎን ለጎን አብረን እንሠራ ነበር። እጅግ በጣም ያረካኝ ብዬ የማስበው ግን ወጣት መሐንዲሶች ዕድሉ ተሰጥቷቸው እንዲሳሳቱ፣ ትክክል እንዲሰሩ፣ እንዲያርሙ፣ እንዲደፍሩ፣ በራሳቸው የመተማመን ብቃታቸው እንዲያድግ፣ በቲዎሪ ያገኙትን ዕውቀት በተግባር እንዲሞክሩት ማድረጋችን፣ መጨረሻ ላይ ውጤት ላይ ደርሰው ሲደሰቱ ማየቴ ትልቁ እርካታዬ ነው።

ሼህ ሙሐመድ በተከታታይ ላደግንባትን ከተማ አንድ ነገር ሳላደርግ እያለ ይቆጭ ነበር። ይህንን ስል ወልድያ ላይ በሌሎች ጉዳዮች ሼህ ሙሐመድ ድጋፍ አላደረገም፣ አልሠራም ማለቴ አይደለም፣ ብዙ የሠራቸው ነገሮች አሉ። መንገድ ሠርቷል፣ ለማዘጋጃ ቤቶች የሚጠቅሙ ተሽከርካሪዎችን ረድቷል፣ የባንክ ቅርንጫፍ እንዲከፈትና ሌሎችም በርካታ ነገሮች አድርጓል። ነገር ግን እንዲህ ተለቅ ያለና ትርጉሙ ከፍ ያለ የሕዝብ ፕሮጀክትን በመሥራት ያ- የሚፈልገውን ነገር ለሚፈልገው ሕዝብ፣ ቦታው ላይ ሄዶ መፈጸም መቻሉ በግሌ ትልቅ እርካታና ደስታ ሰጥቶኛል።

ወልዲያ በእኔ ልቦና ውስጥ ልዩ ቦታ አላት። የተማርኩበት፣ ያደኩበት፣ የተከበርኩበት፣ ቤተሰብ ያፈራሁበት አካባቢ ነው። ዕውቀትን፣ ማንነቴን የፈተንኩበት አካባቢ ነው። ስለዚህ ከሕዝቡ ጋር ኃይለኛ ትስስር አለኝ። እኔም በሼህ ሙሐመድ አማካይነት ሕዝቡ ጎን የመቆም ዕድል አግኝቼ፣ ይህንን ፕሮጀክት ተግባራዊ ማድረጌ ትልቁ እርካታዬ ነው። ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ አንድ ላይ የሚሠራ ግሩፕ ነው። አንድ ላይ እየሄዱ ይህንን በመሥራት በኩባንያዎች መካከል የፈጠረው ኅብረትና ትስስር ቀላል የሚባል አይደለም። አሁንም ሠራተኛው ለምረቃው ዝግጅት ፍፁም በባለቤትነት ስሜት ፕሮጀክቱ የእኛ ነው የሊቀመንበራችን ነው ብለው ማሰባቸው በጣም አስደስቶኛል።¾      

Last modified on Wednesday, 11 January 2017 15:00
ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
635 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1063 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us