አዳዲስ ዲያስፖራዎች ከነባሮቹ ጋር ተገናኝተው ልምድ የሚለዋወጡበት መድረክ ሊያገኙ ይገባል

Wednesday, 03 August 2016 14:35

አዳዲስ ዲያስፖራዎች ከነባሮቹ ጋር ተገናኝተው ልምድ የሚለዋወጡበት መድረክ ሊያገኙ ይገባል

ዶ/ር አረጋ ይርዳው፤ የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር

 

በውጪ ሀገር የሚኖሩ ወገኖች (የዲያስፖራ አባላት) ባሉበት ሀገር ሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ቤተሰቦቻቸው በየጊዜው የሚልኩት ገንዘብ (Remittance) እያደገ መጥቶ ባሳለፍነው የ2008 በጀት ዓመት ከአራት ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ መድረሱን መረጃዎች ያሳያሉ። ይህ ገንዘብ ሀገሪቱ በኤክስፖርት ከምታገኘው ዓመታዊ ገቢ በእጅጉ የላቀ ነው።

በተጨማሪም በውጪ ሀገር ይኖሩ የነበሩ በርካታ ኢትዮጵያዊን ወደሀገራቸው በመመለስ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ ተሰማርተው ለሀገራቸው ኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ ከማድረጋቸውም በላይ ለበርካታ ዜጎች አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ችለዋል። አንዳንድ የዲያስፖራ አባላት በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገር ያገኙትን የከፍተኛ ትምህርትና የካበተ የሥራ ልምድ ይዘው ወደሀገር ውስጥ በመመለስ በተሠማሩባቸው መስኮች ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወን ችለዋል፣ በማከናወን ላይም ይገኛሉ። ከእነዚህ ምሁራን አንዱ ዶ/ር አረጋ ይርዳው የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር ናቸው። ከ16 ዓመታት በፊት ከሚኖሩበት ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ወደትውልድ ሀገራቸው በመመለስ በሙያቸው ሀገራቸውን እያገለገሉ ይገኛሉ። ሰሞኑን በአማራ ክልል በባህርዳር ከተማ እየተከበረ ካለው ሁለተኛው የኢትዮጵያ የዲያስፖራ (Diaspora) ሣምንት ጋር በተያያዘ አስተያየታቸውን ጠይቀን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

ሰንደቅ፡- ከሚኖሩበት ሀገር ጠቅልለው በመመለስ ሀገራቸውን በማገልገል ላይ ከሚገኙ ባለሙያዎች አንዱ መሆንዎ ይታወቃል። የሰሞኑን የዲያስፖራ በዓል እንዴት አገኙት?

ዶ/ር አረጋ፡-ስለዲያስፖራ በዓል፣ ስለዲያስፖራ ተሳትፎ ጉዳይ መስማት የጀመርኩት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ነው። እኛ እንግዲህ ቀደም ብለን ስለመጣን ወይንም ዕድሜ ጠገብ ዲያስፖራ ስለሆንን ወይንም የዲያስፖራ ትርጉም ለየት ብሎ በመቀመጡ ምክንያት ሊሆን ይችላል በዚህ በዓል ላይ አልተጋበዝኩም፤ ምክንያቱን አላወኩትም። የውጪ ሀገር ፓስፖርት ኖሯቸው፣ የሌላ ሀገር ነዋሪ ሆነው፣ በተለያየ ምክንያት ለተለያየ አገልግሎት ወደሀገራቸው ከመጡ ሰዎች አንዱ ነኝ። ይህ መሆኑ በኢትዮጵያ የዲያስፖራ መመዘኛ ውስጥ ያስገባኝ ወይንም አያስገባኝ አላወኩም።

ሰንደቅ፡-“ዲያስፖራ” የሚለው ቃል አማርኛን እየተቀላቀለ መጥቷል። የቃሉ ትርጓሜ በውጪ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን የሚመለከት ነው ወይንስ ተጨማሪ ትርጉም ይኖረው ይሆን?

ዶ/ር አረጋ፡- ይህንን ጥያቄ በቀጥታ መመለስ ያለበት የተቋቋመው የዲያስፖራ ቢሮ ወይንም ማህበሩ ይመስለኛል። በእኔ አስተያየት ግን ዲያስፖራ የሚለው በተለያየ ምክንያት ወደተለያዩ ሀገራት የሄዱ ኢትዮጵያዊያንን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን የሚመለከት ስም ይመስለኛል። ባልሳሳት የቃሉ አመጣጥ በተለያዩ ሀገራት ተበትነው የነበሩ የአንድ ሀገር ሰዎችን ለመግለፅ የተሰጠ ስም ይመስለኛል።

ሰንደቅ፡- ዲያስፖራውን በተመለከተ በሚካሄዱ ሰሞነኛ ውይይቶች ላይ በመንግሥት አካላት በኩል ተደጋግሞ የሚነሳው ዲያስፖራው በሀገሩ በኢንቨስትመንት መስክ እንዲሰማራ የሚያግባባ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ግን በዲያስፖራው እጅ የተለያዩ ዕውቀቶች አሉ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲመጣ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችሉ አሉ። ከእነዚህ አንጻር መንግሥት የዲያስፖራውን ተሳትፎ ሰፋ አድርጎ ማየት የለበትም?

ዶ/ር አረጋ፡- ሰሞኑን የዲያስፖራውን በዓል አስመልክቶ በቴሌቪዥን የቀረበ ሪፖርት ተመልክቼ ነበር። ምክትል ጠ/ሚኒስትር አቶ ደመቀ ይመስሉኛል ገለጻ ሲያደርጉ አይቻለሁኝ። እንደገለጻው ከሆነ ዲያስፖራው በብዙ መስኮች እንዲሰማራ ተደርጓል፤ ይሄ ጥሩ ነገር ነው። አቅሙ ያላቸው ዲያስፖራዎች በኢንቨስትመንት መስክ መሳተፋቸው ትልቅ ነገር ነው። የገንዘብ አቅም የሌላቸው ግን የተለየ ክህሎትና ሥልጠና ያላቸው ሰዎች በዕውቀታቸው እንዲያገለግሉ መደረግ አለበት። አንዳንዶቹ ወደሀገራቸው ተመልሰው በተለያዩ ኩባንያዎች ውስጥ ተቀጥረው ሁሉ ሊሰሩ ይችላሉ። ለምሳሌ ዩኒቨርሲቲዎቻችን በቁጥር እየጨመሩ ነው። እነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች በጣም ብዙ የሰለጠኑ ባለሙያዎች ያስፈልጉዋቸዋል። እናም በተለያዩ ሀገሮች የሚገኙ የሰለጠኑ ኢትዮጵያዊያን ወደሀገራቸው መጥተው ቢያስተምሩ ለሀገራቸውና ለወገናቸው ትልቅ እገዛ ሊያደርጉ ይችላሉ ብዬ አምናለሁ። እንደእኔ ዓይነቱም ወደሀገሩ ገብቶ በማኔጅመነት፣ በሊደርሺፕ፣ በምህንድስና…. ያካበተውን ዕውቀትና ልምድ ቢያካፍል፣ በሥራ ላይ ቢያውል ትልቅ ጥቅም ይሰጣል። ሰሞኑን በቴሌቪዥን እንደተመለከትነው የዲያስፖራ አባላት የተለያዩ ፋብሪካዎችንና ልማቶችን ሲጎበኙ ነበር። እዚህ ሀገር ቀደም ሲል መጥተው በተለያዩ ሥራዎች ላይ የተሠማሩ፣ ትልልቅ ሥራዎች ያከናወኑና እያከናወኑ ያሉ ባለሀብት ዲያስፖራዎች መኖራቸው ይታወቃል። ከእነዚህ መካከል ሼክ ሙሐመድ አንዱ ናቸው። የሼክ ሙሐመድ ኩባንያዎች ቢጎበኙ ለዲያስፖራው ልምድ ማስተላለፍ ይቻል ነበር። ቀደም ብሎ ገብቶ በሥራ ላይ ያለው ዲያስፖራ ምን እየሰራ መሆኑ መታየቱ ትልቅ ጥቅም ይሰጣል። የሚነገረውንም ነገር በተጨባጭ ሊረዳ ይችላል፡፡ ለምን ይህ እንዳልተደረገ በግሌ አላውቅም። የዲያስፖራ ትርጓሜ የተለየ ሆኖ እንደሆነም አልገባኝም።

ሰንደቅ፡-ቀደም ብለው የገቡትን ዲያስፖራዎች መንግሥት በአግባቡ አልተጠቀመባቸውም እያሉኝ ነው?

ዶ/ር አረጋ፡- እውነቱን ለመናገር እንደዚያ ነው። ቀደም ብለው የመጡት እንዲሳተፉ ያልተደረጉት በደንብ ስላልታወቁ ነው? ስላልተመዘገቡ ነው? ተዘንግተው ነው? መረጃው የለኝም። የዲያስፖራ ማህበር ከመቋቋሙ በፊት ወደሀገራቸው ገብተው በተለያዩ ሥራዎች ላይ ያሉ ብዙ ዲያስፖራዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች መድረክ ቢያገኙ ተጨማሪ አቅም፣ ጉልበት መሆን ይችሉ ነበር። እንደአይ ኤም ኤፍ ፣ ወርልድ ባንክ ያሉ ተቋማት መረጃ ሲፈልጉ ወደእኛ ይመጣሉ። ብዙ ለሀገር የሚጠቅም ነገር እንነግራቸዋለን። አሁንም ቢሆን አዳዲሶቹ ዲያስፖራዎች ከነባሮቹ ጋር ተገናኝተው ሃሳብ እንዲለዋወጡ ማድረግ የበለጠ ጠቃሚ ነው ብዬ አስባለሁ።

ሰንደቅ፡-መንግሥት የዲያስፖራውን ተሳትፎ ለማሳደግ ጥረት እያደረገ ነው። ከዲያስፖራው ወገን ምንድነው የሚጠበቀው?

ዶ/ር አረጋ፡- የዲያስፖራውን ሁኔታ ለማወቅ በውጪ ሀገር የኖርክ ብትሆን ይመረጣል። በእኔ እምነት ሶስት ዓይነት ዲያስፖራዎች በውጪ ሀገር ይኖራሉ፤ አንዱና የመጀመሪያው ቀደም ብሎ ሄዶ ልጆቹን አስተምሮ፣ ቤተሰባዊ ኃላፊነቱን ተወጥቶ፣ የተወሰኑ እውቀቶች አካብቶ ወደመጨረሻ ጡረታ አካባቢ የደረሰ ወይንም በጡረታ ላይ ያለ ነገር ግን ሊያገለግል የሚችል ብዙ ሸክም የሌለበት ዲያስፖራ አለ። እንደነዚህ ዓይነቶቹ ወደ ሀገር እንዲመጡ ሁኔታዎች ቢመቻቹ፣ ቢበረታቱ ብዙ ጥቅም ይሰጣሉ። መጥተው ገንዘብ ካላቸው ኢንቨስትመንት ላይ ሊሰማሩ ይችላሉ፣ ባካበቱት ዕውቀት መምህራን፣ መሐንዲሶች፣ የህክምና ባለሙያዎች ወዘተ ሆነው እንደሙያቸው ሊሰሩ፣ ሊያገለግሉ ይችላሉ።

ሁለተኛው ዲያስፖራ ወደውጪ ሀገር ከሄደ በኃላ ትዳር (ቤተሰብ) መስርቶ ፣ ልጆች ወልዶ፣ የሚኖር ነው። ልጆቹን በማስተማር፣ ቤተሰብ በማስተዳደር ላይ የተወጠረ ነው። ማንኛውም ሰው ለልጆቹ ጥሩ ነገር መስጠት እንደሚፈልገው ሁሉ ቅድሚያ የሚሰጠው ለልጆቹና ለቤተሰቡ ነው። ይህ ዓይነቱ ዲያስፖራ ባለበት ሆኖ ሀገር ቤት ላሉ ቤተሰቦቹ የሚልከው ገንዘብ ለሀገር ይጠቅማል። እንዲህ ዓይነት ዲያስፖራዎች እዚያው ባሉበት ሆነው በሀገር ቤት ሐብት እንዲያፈሩ ማድረግ ይቻላል። ለምሳሌ መኖሪያ ቤት እንዲሰሩ ወይንም እንዲገዙ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ከተቻለ ተጠቃሚ መሆን ያስችላል።

ሶስተኛው ዓይነት ዲያስፖራ ወጣት ትኩስ ኃይል የሆነው ዲያስፖራ ነው። በሄደበት ሀገር ገና ለመቋቋም የሚታገል ነው። ይህም ለቤተሰቡ ወደሀገር የሚልከው ገንዘብ (ሬሚታንስ) ይጠቅማል።

በአጠቃላይ መንግሥት እነዚህም ወገኖች ለይቶ ማወቅ አለበት። እነሱን ለማወቅ እዚህ ቀደም ብሎ አራተኛ አድርጎ በመቁጠር በሚገባ ማሳተፍ ጥቅም አለው። ሕንድና ፓኪስታንን የመሳሰሉ ሀገራት በውጪ ሀገር ከሚገኙ ዜጎቻቸው ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ (ሬሚታንስ) ያገኛሉ። እነሱ የደረሱበት ለመድረስ ልንጥር ይገባል።

ሰንደቅ፡-ዲያስፖራውን ከመሳብ፣ ከማሳተፍ አኳያ የሚታዩ ጉድለቶች ምንድናቸው ይላሉ?

ዶ/ር አረጋ፡- የዲያስፖራ አባላት በባንክ በውጪ ምንዛሪ ገንዘባቸውን እንዲያስቀምጡ ሁኔታዎች መመቻቸታቸው ጥሩ እርምጃ ነው። መኖሪያ ቤት እንዲሰሩ ወይንም እንዲገዙ በመጠኑ እገዛ እየተደረገ መሆኑ በጥሩ ጎኑ የማያቸው ናቸው። በተጨማሪ ግን አንዳንድ ቢዝነሶች ላይ አክስዮን በመግዛት እንዲሳተፉ ቢደረግ ለዲያስፖራው ብቻ ሳይሆን እንደሀገርም ትልቅ ጥቅም ይሰጣል። ለምሳሌ በፋይናንስ ዘርፉ ባንኮችና ኢንሹራንሶች ላይ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ዲያስፖራዎች እንዲገቡ ሊፈቀድ ይገባል። ክቡር ጠ/ሚኒስትሩ በተገኙበት መድረክ ሁሉ ይህ ጥያቄ ተደጋግሞ ይነሳል፣ መልስ ግን አላገኘም። እዚህ ሀገር ዲያስፖራው መዋለ ንዋይህን አፍስስ ተብሏል። ሐብት አፍራ፣ ቤት ግዛ ተብሏል። ሁሉም ዲያስፖራ ሐብታም ነው ብሎ ማሰብ የተሳሳተ ነው። ነገርግን ያለችውን ትንሽ ገንዘብ አክስዮን እንዲገዛ በማድረግ ገንዘቡን ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ይቻላል። ራሱን የቻለ የዲያስፖራ ባንክ አክስዮን መስርቶ እንዲያቋቁምም መደገፍ ይቻላል። በእነሱ ላይ ትኩረቱ ያነሰ ይመስለኛል፡፡ የማይሆን ከሆነም ቁርጥ አድርጎ ለምን እንደማይሆን መንገር ያስፈልጋል።

ሰንደቅ፡-በመንግሥት በኩል ዲያስፖራው ወደሀገሩ ገብቶ እንዲሠራ ብዙ ጥረቶች እየተደረገ ነው፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሰለጠኑ ባለሙያዎች ጭምር በገፍ ወደውጪ ሀገር እየፈለሱ ነው። ይህንን እንዴት ማስታረቅ ይቻላል?

ዶ/ር አረጋ፡- ፍልሰት (Brain drain) በየዓመቱ ትንሽ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል አሰልጥነን የምናወጣ ቢሆን ኖሮ፣ መጠነኛ የተማሩ ሰዎች ኖረውን ላሉን ኩባንያዎች የሰለጠነ የሰው ኃይል ማቅረብ የማንችል ቢሆን ኖሮ ጉዳዩ ያስጨንቀን ነበር። አሁን በሀገራችን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ዩኒቨርሲቲዎች እየተስፋፉ ነው። ከእነዚህ ዩኒቨርሲዎች በየዓመቱ ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። በዚህ ምክንያት አንዳንዶች ሥራ ለማግኘትም ጭምር ውጪ ሀገር ሊሄዱ ይችላሉ። ለመሥራት የሚሄዱት ሰዎች እዚህ ሥራ እያለ የሄዱ ቢሆን ኖሮ ብሬን ድሬን ነው እንል ነበር። ወጣቶች እዚህ ተምረው ሥራ ካላገኙ ሌላ ሀገር ሄደው መሥራታቸው ነውር የለውም። እንዲያውም ጥቅሙ ከፍ ያለ ነው። እነዚህ ወገኖች ሰርተው ለቤተሰባቸው የውጪ ምንዛሪ ገንዘብ ሲልኩ ሀገርንም ይጠቅማል። ከዚህ አኳያ ሳየው የብሬን ድሬን ቲዎሪ ጊዜው ያለፈበት ይመስለኛል። እርግጥ ነው፣ ለሀገሪትዋ ሊጠቅም የሚችል ልዩ ዕውቀትና ልምድ ያላቸው፣ በሥልጠና ረገድ ደከም ያልንባቸው ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ወደውጪ ሀገር መሄዳቸው ይጎዳናል። በአጠቃላይ ግን ሰዎች ወደውጪ ሀገርም መሄድም ሆነ መምጣትም መቻል እንዳለባቸው መዘንጋት የለበትም።¾

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
809 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1051 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us