ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በማዕድን ኢንጂነሪንግ ዘርፍ በዲግሪ መርሃግብር ተማሪዎችን ያስመርቃል

Wednesday, 29 June 2016 12:31

 

በሚድሮክ ወርቅ ኩባንያ ስፖንሰርነት ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ከ2004 የትምህርት ዘመን ጀምሮ ተቀብሎ ሲያስተምራቸው የነበሩትን የማዕድን ኢንጂነሪንግ ተማሪዎች ከአንድ ወር በኋላ እንደሚያስመርቅ አስታወቀ።

 

ተማሪዎቹ በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በማዕድን ኢንጂነሪንግ ዘርፍ መሰልጠናቸው ታውቋል። በሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ዋና መ/ቤት ከትላንት በስቲያ በተሰጠው መግለጫ ላይ የተገኙት ዶ/ር ጥበበ ታፈሰ የዩኒቨርሲቲው የማዕድን ምህንድስና ትምህርት ክፍል ኃላፊ በሰጡት ማብራሪያ በዶ/ር አረጋ ይርዳው ውሳኔ መሠረት በ2004 ዓ.ም በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የማዕድን ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል ተከፍቶ ተማሪዎችን በመቀበል በባችለር ኦፍ ሳይንስ ዲግሪ ሲያሰለጥን መቆየቱን፣ ተማሪዎቹ ከንድፈሃሳብ ትምህርት ባሻገር በለገደንቢ ወርቅ ማዕድን ሥፍራ በመገኘት የተግባር ልምምድና ስልጠና መውሰዳቸው አስረድተዋል።

 

ዶ/ር ጥበብ በዚሁ ማብራሪያቸው ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ያሰለጠናቸው የማዕድን መሐንዲሶች በዩኒቨርሲቲው በቆዩባቸው አምስት ዓመታት የሚፈለግባቸውን የቲዎሪ፣ ልምድና ሙያውን በሚገባ ለማወቅና ለማስረጽ በጣም አስፈላጊና ወሳኝ የሆነውን በማዕድን ድርጅት ውስጥ ማከናወን ያለባቸውን ሥልጠና አጠናቀዋል። ምሩቃኖቹ በማዕድን ምሕንድስና እና በማዕድናት ማበልፀግ ሥራዎች ላይ ለመሰማራት ብቻ የሰለጠኑና ትምህርታዊ ብቃት ያላቸው ብቻ ሳይሆኑ በማዕድናት ፕሮጀክት ዝግጅትና ጥናት፣ በማዕድናት ጥናትና ልማት፣ በማዕድናትና ውኃ ቁፋሮ፣ በዋሻ ቁፋሮ፣ በማዕድናት አስተዳደር፣ ፈቃድና ቁጥጥር፣ በኢንቫይሮንመንት፣ የሙያ ደኅንነትና ጤና፣ በማስተማር፣ ወ.ዘ.ተ. ሥራዎች ላይም ለመሰማራት እንዲችሉ ተገቢው ትምህርትና ሥልጠና እንዲሁም ልምምድ የማድረግ ዕድል የተሰጣቸው በመሆናቸው በቂ ችሎታ አላቸው ብለዋል።

 

አያይዘውም የዘንድሮ ተመራቂዎች በጠቅላላው 25 ያህል ሲሆኑ 22 ያህሉ ወጪያቸው በሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኩባንያ ሙሉ በሙሉ መሸፈኑን ተነግሯል። ከዕጩ ተመራቂዎቹ መካከል ስድስት ያህሉ ሴቶች ናቸው ተብሏል።

 

ዶ/ር አረጋ ይርዳው የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰርና የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት በበኩላቸው ተማሪዎቹ ለአምስት ዓመታት በሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ስኮላርሺፕ እንደተሰጣቸውና ሲገቡም ከምረቃ በኋላ ሊያገለግሉ መስማማታቸውን አስታውቀዋል።

 

ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ ማስተማር ከጀመረ በኋላ አክሱም ዩኒቨርሰቲ እና የአዲስአበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሰቲዎች በዘርፉ ስልጠና መስጠት መጀመራቸውን ዶ/ር አረጋ አስታውሰዋል።

 

ኢንዱስትሪ እና የትምህርት ተቋማት የማስተሳሰር ጉዳይ ብዙ ጊዜ የሚነሳ እንደሆነ ያስታወሱት ዶ/ር አረጋ የማዕድን ሚኒስቴር ከካሪኩለም ቀረጻ ጀምሮ፣ ሚድሮክ ወርቅ ኩባንያ ስፖንሰርሽፕ በመስጠት፣ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በማስተማር ትስስር የመፍጠርን ሥራ በተግባር ማሳየት ችለዋል፤ ውጤትም አግኝተንበታል» ብለዋል።

 

ከ300 ሚሊየን ብር በላይ የወጣበት የመተከል ማዕድን ፍለጋ ሥራ ተጠናቆ የማዕድን ፈቃድ ጥያቄ መቅረቡንና በቅርቡ ፈቃዱ ሲገኝ ወደዚሁ ሥራ አዲስ ተመራቂዎች እንዲሰማሩ እንደሚደረግ ዶ/ር አረጋ አረጋግጠዋል።

 

ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ተቀዳሚ ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ብርሃኑ ሲሳይ በካሪኩለም ዝግጅት ሂደት በአሜሪካ፣ በደቡብ አፍሪካና በመሳሰሉት አገራት የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ልምድና ተሞክሮ ታይቶ በጥንቃቄ መቀረፁን አስታውሰዋል። አያይዘውም ወደስልጠናው የሚገቡ ተማሪዎች በዋንኛነት የትምህርት ሚኒስቴርን የቅበላ መስፈርት ያሟሉ መሆናቸውን እንደሚረጋገጥ አስረድተዋል።

 

በመግለጫው ላይ የሚድሮክ ወርቅ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አለማየሁ ታከለም ተገኝተዋል።

 

የዘርፉን የኋላ ታሪክ አስመልክቶ በዶ/ር ጥበበ የቀረበ ማብራሪያ

በኢትዮጵያ ማዕድናት ለበርካታ ዓመታት የተመረቱ እና ጥቅም ላይ የዋሉ ቢሆንም ትኩረት ይሰጣቸው የነበሩት ወርቅና የግንባታ (construction) ማዕድናት ነበሩ። እነዚህ ማዕድናት በባህል አምራቾች ይመረቱ የነበረ ሲሆን ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያደርጉት አስተዋፅዖም በጣም አናሳ ነበር።

 

የማዕድናት ዘርፍ በርካታ ተግዳሮቶች እና የሚመለከታቸውን ሁሉ ግንዛቤ በስፋት ያላገኘ ነው። ሆኖም ከቅርብ አሥር ዓመታት ወዲህ ማዕድናት የሚያመርቱ ድርጅቶች የተቋቋሙ ሲሆን የማዕድናቱም ምርት ለኤኮኖሚያችን የሚያደርጉት አስተዋፅዖ እያደገ መጥቷል። ዕድገቱም እንደሚቀጥል፤ በተለይም ማዕድናት በገቢና በውጪ ምንዛሪ አፍሪነት እንዲሁም በኢንዱስትሪያላይዜሽን ዕድገት ተገቢ አስተዋፅዖና የማይናቅ ሚና እንደሚጫወቱ ይጠበቃል፤ ይታመናልም።

 

በሌላ በኩል ለማዕድናቱ ልማት ወሳኝነት ካላቸው ዋነኛው በጂኦሎጂ፣ ማዕድን ምሕንድስናና በማዕድን ማበልፀግ ሙያ የሰለጠነና የዳበረ ክህሎትና ብቃት ያለው የሰው ኃብት ነው። የዚህ ኃብት በተገቢው መጠን አለመኖር ከኢንቨስትመንት እጥረት ጋር ተዳምሮ የማዕድናቱን ዕድገትና ሊያስገኙ የሚችሉትን ኤኮኖሚያዊና ማኅበረ-ሰብዓዊ አስተዋፅዖ ያቀጨጨውና በተገቢው ፍጥነት እንዳይሔድ የገታው ሆኗል።

 

ምንም እንኳን አገራችን ከፍላጎት አንጻር በጣም አናሳ ቢሆኑም በርካታ በአገር ውስጥና በውጪ አገራት የሰለጠኑ ጂኦሎጂስቶች ያሏት ቢሆንም በማዕድን ምሕንድስናና በማዕድናት ማበልፀግ ሙያ የሰለጠኑ ባለሙያዎችም ሆኑ ቴክኒሺያኖች አሉ ለማለት አያስደፍርም። በተለይ የእነዚህ ሙያዎች ሥልጠና በአገራችን አለመሰጠትና የእስከዛሬዎቹ በሙሉ ከውጪ ሰልጥነው የመጡ፣ የአዳዲስ ምሩቃን መምጣትም ከበርካታ ዓመታት በፊት መቋረጡ፣ ያሉት አናሳ ቁጥር ያላቸው ባለሙያዎች ቀደም ሲል በተቋቋሙ ድርጅቶች መያዝ የማዕድናት ምርትና ማበልፀግ ሥራዎች በውጪ ባለሙያዎች ላይ እንዲደገፉ እያስገደደ መጥቷል። ይህ ሁኔታ ደግሞ የማዕድናቱን የሥራ ፈጣሪነት ሚና ከማዳከሙም በተጨማሪ ለውጪ ባለሙያዎችና ሥራ ተቋራጮች በደመወዝና በመሣሠሉት መልክ በሚደረጉ ክፍያዎች ወደ ውጪ የሚያስወጣና የአገራችንን ጥቅም የሚጎዳ መሆኑን ያብራራል።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
788 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1050 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us