You are here:መነሻ ገፅ»ወቅታዊ
ወቅታዊ

ወቅታዊ (186)

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የአማራና ቅማንት ሕዝቦች ተቀላቅለው በሚኖሩባቸው 12 ቀበሌዎች ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት ጀመረ። በዚህ መሠረት ቦርዱ የሕዝበ ውሳኔው መስከረም 7 ቀን 2010 ዓ.ም እንዲካሄድ በማቀድ የአፈጻጸም የጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ይፋ አድርጓል፡፡


ቦርዱ የአማራና ቅማንት ሕዝቦች ተቀላቅለው የሚኖሩባቸው 12 ቀበሌዎች ሕዝበ ውሳኔ እንዲያካሂድ በፌዴሬሽን ምክር ቤት በቀረበለት ጥያቄ መሠረት በማድረግ ቅድመ ዝግጅቶች መጀመሩን በቅርቡ በአምባሳደርነት የተሾሙት የቦርዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና መግጳቸውን ከቦርዱ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።


ባሳለፍነው ወር የቦርዱ ፅ/ቤቱ የቴክኒክ ጉዳዮችን ለመመርመር አንድ ቡድን ወደ ቦታው በመላክ የቅድመ ዝግጅት ዳሰሳ ጥናት ማካሄዱንና ስንት ምርጫ ጣቢያዎች ማቋቋም እንዳለበትና ስንት የምርጫ አስፈፃሚዎችና የሕዝብ ታዛቢዎች ማሰማራት እንዳለበት  መለየቱን ቦርዱ አሳውቋል።


የአሁኑ ስብሰባም በሕዝበ ውሳኔ አፈፃፀም የጊዜ ሰሌዳ/ ረቂቅ ላይ ለመመካከርና የአማራና ቅማንት ሕዝቦች ተቀላቅለው በሚኖርባቸው 12 ቀበሌዎች በሚካሄደው ሕዝበ ውሳኔ የአፈፃፀም ማብራሪያ ላይ  ከክልሉ መስተዳድር አካላት እና በክልሉ የተዋቀሩ የሁለቱ ሕዝቦች የጥምር ኮሚቴ አባላት ጋር ጥልቅ ውይይት ተካሂዷል። 


የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክርቤት አፈ ጉባዔ አቶ ይርሳው ታምሬ በአካባቢው የነበሩትን ጥያቄዎች አብዛኛዎቹ ከሕዝብ ጋር በመወያየት፣ በመግባባት እና በመተማመን የተፈቱ መሆናቸውን በማስታወስ ሕዝበ ውሳኔ የሚካሄድባቸው 12 ቀበሌዎች ግን በሕዝብ ውሳኔ መፍትሄ እንዲያገኙ በሁለቱ ወገኖች ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ መቅረቡን አስታውሰው፤ ምርጫ ቦርዱ በነዚህ አካባቢዎች ለሚያካሂደው ሕዝበ ውሳኔ አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ እንደሚደረግና ሕዝበ ውሳኔው ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እምነት እንዳላቸው ተናግሯል። በመቀጠልም የሁለቱ ህዝቦች በሠላም አብሮ የመኖር ታሪካቸውን የሚያጠነክርና የሚያጎለብት ሕዝበ ውሳኔ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጿል።


በሁለቱ ህዝቦች ለዘመናት የዘለቀውን ተቻችሎና ተግባብቶ አብሮ የመኖር ግንኙነትና ዝምድና የሚጠናከርበት፣ ችግሮች ተወግደው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማታቸው የሚጎለብትበት፣ የሕዝቦቹ ዘላቂ ሠላምና ብልፅግና የሚረጋገጥበት ሕዝበ ውሳኔ እንዲሆን የበኩላቸውን እንደሚወጡ የመድረኩ ተሳታፊዎች አረጋግጧል።


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ መንግሥት አንቀጽ 102 እና በተሻሻለው የኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ አዋጅ ቁጥር 532/1999 ዓ.ም. መሠረት የተቋቋመ ተቋም እንደሆነና፤ ቦርዱ ግዙፍ ሕዝባዊና ሕገ-መንግሥታዊ ኃላፊነት ተሸክሞ ወደ ሥራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ በየአምስት ዓመቱ በተከታታይ የሚካሄዱ ምርጫዎችን የጠቅላላ ምርጫ አምስት ጊዜ፣ የአካባቢ ምርጫ አምስት ጊዜ እንዲሁም በተለያዩ ደረጃ የምርጫ ዓይነቶች ማለትም የማሟያ ምርጫ፣ ድጋሜ ምርጫ እና ሕዝበ-ውሳኔዎችን ነፃ፣ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እንዲሁም በሕዝብ ዘንድ ተዓማኒ ሆነው እንዲጠናቀቁ በማድረግ በርካታ ልምድ ያካበተ ተቋም ነው።


ሕዝበ ውሳኔ ማለት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት ሲወሰን የህዝብ ፍላጎትን ለመለካት እና የሕዝብን ውሳኔ ለማወቅ ድምፅ የሚሰጥበት ሥርዓት ነው። በዚሁ መሠረት ቦርዱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ የሕዝበ ውሳኔ ምርጫዎችን በብቃት በማካሄድ የህዝቦችን የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤትነትን አረጋግጧል። ለአብነት ለመጥቀስ የቤጊ ሕዝበ ውሳኔ፣ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ አዋሳኝ ቀበሌዎች፣ እንዲሁም በኦሮሚያ እና በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች አዋሳኝ በሆኑት ቀበሌዎች ላይ የተካሄዱ ሕዝበ ውሳኔዎች ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መጠናቀቃቸውን ይታወሳል፡፡


የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የአማራና የቅማንት ሕዝቦች ተቀላቅለው በሚኖርባቸው 12 ቀበሌዎች ለሚካሄደው ሕዝበ ውሳኔ አፈፃፀም ያጸደቀው የጊዜ ሰሌዳ እነሆ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

የአማራና የቅማንት ሕዝቦች ተቀላቅለው በሚኖሩባቸው 12 ቀበሌዎች ለሚካሄደው ሕዝበ ውሳኔ አፈፃፀም የጊዜ ሰሌዳ

ነሐሴ 2009 ዓ.ም

ተ.ቁ

ክንውን

ቀን

1

በህዝበ ውሳኔው የጊዜ ሰሌዳ እና የህዝብ ውሳኔ ማስፈጸሚያ ማብራሪያ ላይ ውይይት የሚደረግበት፤

ነሐሴ 10 ቀን 2009 ዓ.ም

2

ለህዝበ ውሳኔው አስፈፃሚዎች ስልጠና የሚሰጥበት፤

ነሐሴ 24 እና 25 ቀን 2009 ዓ.ም

3

ለህዝበ ውሳኔው የህዝብ ታዛቢዎች ምርጫ የሚካሄድበት፤

ነሐሴ 28 ቀን 2009 ዓ.ም

4

ስለህዝበ ውሳኔው የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ለህዝቡ ገለፃ የሚሰጥበት፤

ነሐሴ 28 ቀን 2009 ዓ.ም

5

ለህዝበ ውሳኔው ድምፅ ሰጪዎች ምዝገባ የሚከናወንበት፤

ነሐሴ 29 ቀን 2009 ዓ.ም እስከ መስከረም 3 ቀን 2010 ዓ.ም

6

የህዝበ ውሳኔው የመራጮች መዝገብ ለህዝብ ክፍት ሆኖ የሚቆይበት፤

ከመስከረም 4 እና 5 ቀን 2010 ዓ.ም

7

የህዝበ ውሳኔው ቅሬታ በየደረጃው የሚቀርብበት እና ውሳኔ የሚሰጥበት፤

ነሐሴ 29 ቀን 2009 ዓ.ም እስከ መስከረም 12 ቀን 2010 ዓ.ም

8

የህዝበ ውሳኔው የድምፅ መስጫ ዕለት፤

መስከረም 7 ቀን 2010 ዓ.ም ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12፡00 ሰዓት

9

ድምፅ አሰጣጡ እንደተጠናቀቀ የህዝበ ውሳኔ ድምጽ ቆጠራ የሚጀመርበት፤

መስከረም 7 ቀን 2010 ዓ.ም ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ

10

የህዝበ ውሳኔው የድምፅ ቆጠራ በድምፅ መስጫ ጣቢያው በይፋ የሚገለፅበት፤

መስከረም 8 ቀን 2010 ዓ.ም

11

የህዝበ ውሳኔው የድምጽ ቆጠራ ውጤት ተጠናቅሮ ለፌደሬሽን ምክር ቤት የሚላክበት፡፡

መስከረም 15 ቀን 2010 ዓ.ም

 

 

የቅማንት ማህበረሰብ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ስለመወሰኑ፣


የአማራ ክልል ምክር ቤት መጋቢት 3 ቀን 2007 ዓ.ም ባካሄደው ጉባዔ የቅማንት ማህበረሰብ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ውሳኔ ማሳለፉ አይዘነጋም፡፡ ይህንን ውሳኔ ተከትሎም በሰሜን ጎንደር ዞን የቅማንት ማህበረሰብ የራስ ገዝ አስተዳደር 42 ቀበሌዎችን እንዲያቅፍ ተደርጎአል፡፡ በቀጣይም ከሕዝቡ ጋር በተደረጉ ውይይቶች 12 ቀበሌዎች ወደራስገዙ እንዲካተቱ መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ደግሞ የአማራና የቅማንት ሕዝቦች ተቀላቅለው በሚኖሩባቸው 12 ቀበሌዎች ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወስኖአል፡፡


የቅማንት ማህበረሰብ በሰሜን ጎንደር ዞን በተወሰኑ ወረዳዎች የሚገኝ እና ራሱን በራሱ ለማስተዳደር ጥያቄ ሲያነሳ የቆየ ሕዝብ ነው፡፡

 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮምሽን

የቅማንት ግጭትን አስመልክቶ ምን አለ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮምሽን ሰኔ 3 ቀን 2008 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ባቀረበው ሪፖርት የቅማንት ብሄረሰብ የማንነት ጥያቄ ተከትሎ ስለደረሰው ግጭት እንዲህ ብሏል፡፡

በሰሜን ጎንደር ዞን የቅማንት ብሄረሰብ የማንነት ጥያቄ ማቅረቡ ሕገመንግስታዊ እንደነበር የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮምሽን ሪፖርት ይጠቅሳል። ይህ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በክልሉ መንግስት እንዲሁም በፌዴራሉ የፌዴሬሽን ም/ቤት በኩል የተወሰዱት እርምጃዎች ግን ደካማ መሆን ለግጭቱ መፈጠር አይነተኛ ምክንያት መሆኑን አመላክቷል። እንዲሁም አጥኚ ቡድን ተቋቁሞ ጥያቄው የጥቂት ቋንቋውን ተናጋሪ ግለሰቦች አድርጎ ለማሳየት መሞከሩ ትክክል እንዳልነበር፣ ሕገመንግስቱ ቋንቋን መሠረት ቢያደርግም ቋንቋውን አንድም ሰው ተናገረው ወይም ከዚያ በላይ ሕገመንግሥቱ ያስቀመጠው ነገር እንደሌለ ተመላክቷል።

 

ግጭቱ ከተፈጠረ በኃላ ከሰሜን ጎንደር ዞን የተሠማራው ልዩ ኃይል በተለይ በአይከልና በማወራ ቀበሌዎች በወሰደው እርምጃ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሞትና የመቁሰል አደጋ እንዲከሰት ማድረጉ ተመጣጣኝና ህጋዊ ምክንያት የሌለው ነበር ብሎታል።

 

በኮምሽኑ ሪፖርት መሠረት ከቅማንት የማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ በተከሰተ ግጭት በአጠቃላይ 97 ሰዎች ሲሞቱ 86 ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላልና ከባድ የመቁሰል አደጋ ደርሷል።

 

ኮምሽኑ በሪፖርቱ ላይ ባቀረበው ምክረሃሳብ የህዝቡ ጥያቄ አግባብ ባለው ሕግ መሠረት እንዲፈታ፣ ችግሩን በማባባስ ረገድ ሚና የነበራቸው አካላት ጉዳያቸው ተጣርቶ ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቋል። ሕገመንግሥቱ ለሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች እኩል ቦታ የሚሰጥ ቢሆንም ከዚህ በፊት የተለያዩ በደሎች ለደረሰባቸው ብሄረሰቦች ልዩ ጥበቃና ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ በሚያዘው መሠረት የአማራ ክልል ልዩ ድጋፋ ባለማድረጉ የቅማንት ማህበረሰብን ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል ማለቱ አይዘነጋም።¾

የመንግስት የፋይናንስ ድርጅቶች ማለትም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እና ኢትዮጵያ መድን ድርጅት በ2009 በጀት ዓመት ያስመዘገቡት ጠቅላላ ሀብት ወደ ብር 523 ነጥብ 01 ቢሊዮን ማደጉ ተሰማ። ከዚህ ጠቅላላ ሐብት ውስጥ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብር 465 ነጥብ 8 ቢሊዮን በማስመዝገብ ከፍተኛ ድርሻ መያዙም ዶ/ር ስንታየሁ ወ/ሚካኤል የምንግሥት ፋይናንስ ድርጅቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሰሞኑን አስታወቁ።

ሶስቱም የፋይናንስ ድርጅቶች ያስመዘገቡት ጠቅላላ ሐብት እ.ኤ.አ. እስከ ሰኔ 30/2017 ወደ ብር 523 ነጥብ 01 ቢሊዮን ያሻቀበ ሲሆን ከእቅዱ ብር 517 ነጥብ 07 ቢሊዮን ባር ሲነፃፀር የ101 ነጥብ 15 በመቶ አፈፃፀም አሳይቷል። ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ብር 440 ነጥብ 37 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር የ82 ነጥብ 64 ቢሊዮን ወይም የ18 ነጥብ 77 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

ከዚሁ ሐብት ውስጥ በጥሬ ገንዘብ የሚገኘው ብር 59 ነጥብ 75 ቢሊዮን ሲሆን እስከ ሪፖርት ዘመኑ በብድር መልክና በኢንቨስትመንት መልኩ ከጠቅላላ ሐብት ውስጥ ያላቸው የድርሻ መጠን እንደቅደም ተከተላቸው ብር 183 ነጥብ 51 ቢሊዮን እና ብር 269 ነጥብ 76 ቢሊዮን ነው።

እንዲሁም የመንግስት የፋይናንስ ድርጅቶች ያስመዘገቡት ጠቅላላ ዕዳ ብር 490 ነጥብ 12 ቢሊዮን ያሻቀበ ሲሆን ከእቅዱ ብር 487 ነጥብ 91 ቢሊየን  ጋር ሲነፃፀር የ100 ነጥብ 45 በመቶ አፈፃፀም አስመዝግቧል። ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ብር 415 ነጥብ 5 ቢሊዮን  ጋር ሲነፃፀር የ74 ነጥብ 62 ቢሊዮን  ወይም የ17 ነጥብ 96 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

የሶስቱ የፋይናንስ ድርጅቶች ካፒታል ሪዘርቩን ጨምሮ ብር 32 ነጥብ 9 ቢሊዮን ያሻቀበ ሲሆን ከእቅዱ ብር 29 ነጥብ 16 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር የ112 ነጥብ 76 በመቶ አፈፃፀም አስመዝግቧል። ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ብር 24 ነጥብ 9 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር የ8 ቢሊዮን ወይም የ32 ነጥብ 13 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

 

1.  የሶስቱ የመንግስት የፋይናንስ ድርጅቶች እ.ኤ.አ. ሰኔ 30/2017 ላይ በተናጠል ያላቸው ጥቅል የሐብት፣ ዕዳና ካፒታል እንደሚከተለው ቀርቧል፣

 

v    ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

·   የባንኩ ጠቅላላ የሀብት ክምችት ብር 465 ነጥብ 8 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ይህም ከእቅዱ ብር 452 ነጥብ 31 ቢሊዮን አንጻር ሲታይ 102 ነጥብ 97 በመቶ አፈፃፀም ማስመዝገብ መቻሉን ያሳያል። ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ብር 384 ነጥብ 62 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር የ81 ነጥብ 18 ቢሊዮን ወይም የ21 ነጥብ 1 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። ለዚህም የደንበኞች ብድርና ቅድሚያ ክፍያ እና ከብሔራዊ ባንክ ተቀማጭ ዋናውን ድርሻ ወስደዋል። ባንኩ ከሁለቱ የመንግስት ፋይናንስ ተቋም ጠቅላላ ሀብት ጋር ሲነፃፀር 89 ነጥብ 05 በመቶ የሚሆነውን ሀብት የያዘ ሲሆን የሌሎቹ 10 ነጥብ 95 በመቶ ይሸፍናል።

· የባንኩ ጠቅላላ ዕዳ ብር 441 ነጥብ 85 ቢሊዮን ሲሆን ይህም ከእቅዱ ብር 433 ነጠብ 86 ቢሊዮን 101 ነጥብ 84 በመቶ መሆኑን ያሳያል። ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ብር 368 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ሲነፃፀር 73 ነጥብ 35 ቢሊዮን ወይም 19.9 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

·         የባንኩ ካፒታል ሪዘርቩን ጨምሮ ብር 23 ነጥብ 91 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ይህም ከታቀደው ብር 18 ነጥብ 45 ቢሊዮን 129 ነጥብ 61 በመቶ ማስመዝገብ መቻሉን ያሳያል። ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ብር 16 ነጥብ 14 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር የ7 ነጥብ 77 ቢሊዮን ወይም የ48 ነጥብ 14 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። ባንኩ ከሐብት እዳና ካፒታል አንጻር እቅድ ክንውኑ ሲታይ ጥሩ አፈፃፀም እንዳስመዘገበ መረዳት ይቻላል።

 

 

v    ኢትዮጵያ ልማት ባንክ

·      ባንኩ ጠቅላላ ያስመዘገበው ጠቅላላ ሀብት ብር 53 ነጥብ 12 ቢሊዮን ሲሆን ይህም ከእቅዱ ብር 60 ነጥብ 67 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር 87 ነጥብ 56 በመቶ ማከናወኑን ያሳያል። ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ብር 52 ነጥብ 25 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር የ0 ነጥብ 87 ቢሊዮን ወይም የ1 ነጥብ 7 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

·    የባንኩ ጠቅላላ ዕዳ ብር 45 ነጥብ 2 ቢሊዮን ሲሆን ይህም ከእቅዱ ከነበረው ብር 50 ነጥብ 93 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር 88 ነጥብ 76 በመቶ አፈፃፀም አሳይቷል። ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ብር 44 ነጥብ 34 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር የ0 ነጥብ 86 ቢሊዮን ወይም የ1 ነጥብ 94 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

· የባንኩ ካፒታል ብር 7 ነጥብ 92 ቢሊዮን ሲሆን  ይህም ከታቀደው ብር 9.74 ቢሊን 81 ነጥብ 31 በመቶ አስመዝግቧል። ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ብር 7 ነጥብ 92 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር ምንም ዓይነት ጭማሪ አያሳይም።

 

v    የኢትዮጵያ መድን ድርጅት

·         የድርጅቱ ሀብት ጠቅላላ ብር 4 ነጥብ 12 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ከእቅድ ተይዞ ከነበረው ብር 4 ነጥብ 1 ቢሊለን አንፃር ሲታይ 100 ነጥብ 68 በመቶ ብልጫ አስመዝግቧል። ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ብር 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር የ0.62 ሚሊዮን ወይም የ17 ነጥብ 71 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

·  በዚሁ ወቅት የድርጅቱ ጠቅላላ ዕዳብር 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን በእቅድ ከተያዘው ብር 3 ነጥብ 12 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር በብር 98 ነጥብ 42 ከመቶ አፈፃፀም ያሳያል። ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ብር 2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር 0 ነጥብ 4 ቢሊዮን ወይም 14 ነጥብ 81 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

·     የድርጅቱ ካፒታል ሪዘርቩን ጨምሮ ብር 1 ነጥብ 05 ቢሊዮን የደረሰ ሆን ይህም በእቅድ ከተያዘው ብር 0. 97 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር 107 ነጥብ 9 በመቶ አፈፃፀም ያሳያል። ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ብር 827 ነጥብ 49 ሚሊዮን ጋር ሲነፃፀር የ220 ሚሊዮን ወይም የ26 ነጥብ 51 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

 

2.     የመንግስት የፋይናንስ ድርጅቶች የትርፍ አቋም እ.ኤ.አ. ሰኔ 30/ 2017

ሶስቱም የፋይናንስ ድርጅቶች በትርፋማነት የተመዘገበው ውጤት ብር 15 ነጥብ 64 ቢሊዮን ሲሆን ከእቅዱ ብር 14 ነጥብ 55 ቢሊየን ጋር ሲነፃፀር 107 ነጥብ 49 በመቶ አፈፃፀም አሳይቷል። ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ብር 14 ነጥብ 8 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር የ0 ነጥብ 84 ቢሊዮን ወይም የ5 ነጥብ 7 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

 

v    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ብር 12 ነጥብ 96 ቢሊዮን ትርፍ አቅዶ 14 ነጥብ 62 ቢሊዮን ትርፍ አስመዝግቧል። ይህም የእቅዱን 112 ነጥብ 75 በመቶ ማከናወኑን ያሳያል። ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ብር 13 ነጥብ 9 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር የ0 ነጥብ 72 ቢሊዮን ወይም የ5 ነጥብ 2 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። ባንኩ ከሁለቱ የመንግስት ፋይናንስ ተቋማት ጠቅላላ ትርፍ ጋር ሲነፃፀር 95 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ የያዘ ሲሆን የሌሎቹ 5 በመቶ ይሸፍናል።

 

v  የኢትዮጵያ ልማት ባንክ

ብር 934 ነጥብ 34 ሚሊዮን ትርፍ አቅዶ 323 ነጥብ 85 ሚሊዮን ትርፍ አስመዝግቧል። ይህም 34 ነጥብ 66 በመቶ ማከናወኑን ያመለክታል። ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ብር 425 ነጥብ 45 ሚሊዮን ጋር ሲነፃፀር የ101 ነጥብ 63 ሚሊዮን ወይም የ23 ነጥብ 9 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።

 

v  የኢትዮጵያ መድን ድርጅት

ድርጅቱ ብር 651 ነጥብ 73 ሚሊዮን ትርፍ አቅዶ 698 ነጥብ 58 ሚሊዮን ትርፍ አስመዝግቧል። ይህም 107 ነጥብ 19 በመቶ ማከናወኑን ያመለክታል። ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ብር 486 ነጥብ 17 ሚሊዮን ጋር ሲነፃፀር የ212 ነጥብ 41 ሚሊዮን ወይም የ43 ነጥብ 7 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። ለክንውኑ መጨመር ዋንኛ ምክንያት በመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከመንግስት ተቋማት ይሰበሰባል ተብሎ በእቅድ የተያዘው ገንዘብ ወደ አራተኛው ሩብ ዓመት በመሰብሰቡ ነው።

 

3.      የብድር ሥራ እንቅስቃሴ

የመንግስት የፋይናንስ ድርጅቶች ወደ ኢኮኖሚው ያሰራጩት የብድር መጠን የብድር ቦንድ ኩፖን ጨምሮ ብር 99 ነጥብ 9 ቢሊዮን ነው። ይህም ከእቅዱ ብር 123 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ሲነፃፀር 80 ነጥብ 62 በመቶ መመዝገቡን ያሳያል።

 

v    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ብድር ስርጭት በሚመለከት ብር 94 ነጥብ 5 ቢሊን ያሰራጨ ሲሆን ይህም በእቅዱ ከተያዘው ብር 109 ነጥብ 8 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር 86 ነጥብ 07 በመቶ ማከናወኑን ያሳያል። በብድር በማሰባሰብ ስራ ባንኩ ብር 50 ነጥብ 3 ቢሊዮን ሊሰበስብ አቅዶ ብር 53 ነጥብ 9 ቢሊዮን በመሰብሰብ 107 ነጥብ 18 በመቶ ማከናወኑን ያሳያል። በብድር ክምችትም አንፃር በቦንድ የተሰጠውን ጨምሮ ካቀደው ብር 370 ነጥብ 12 ቢሊዮን ብር 419 ነጥብ 4 በማስመዝገብ ካቀደው 113 ነጥብ 31 በመቶ ማከናወኑን ያሳያል።

የተበላሸ ብድር ከጠቅላላው ብድርና ቅድሚያ ክፍያ አንጻር በመቶኛ ሲሰላም ከእቅዱ 2 ነጥብ 8 በመቶ አከናውኗል።

 

v    የኢትዮጵያ ልማት ባንክ

ባንኩ ብር 14 ነጥብ 08 ቢሊዮን ለማበደር አቅዶ ብር 5 ነጥብ 38 ቢሊለን ብድር የሰጠ ሲሆን የእቅዱን 37 ነጥብ 18 በመቶ አከናውኗል። ባንኩ በወቅቱ ሊሰበስበው ካቀደው ብድር ቦንድን ጨምሮ ብር 6 ነጥብ 0 ቢሊዮን ውስጥ ብር 4 ነጥብ 56 ቢሊዮን አከናውኗል። ይህም የእቅዱን 76 በመቶ ማስመዝገቡን ያሳያል። በብድር ክምችትም አንፃር በቦንድ የተሰጠውን ጨምሮ ካቀደው ብር 42 ነጥብ 46 ቢሊዮን ብር 33 ነጥብ 83 ቢሊዮን በመሰብሰብ 79 ነጥብ 65 በመቶ ማስመዝገብ ችሏል። የተበላሸ ብድር ከጠቅላላው ብድርና ቅድሚያ ክፍያ አንፃር በመቶኛ ሲሰላም በእቅድ ከተያዘው 9 ነጥብ 16 በመቶ 24 ነጥብ 98 በመቶ ለማስመዝገብ ችሏል።

 

4.      የቁጠባ ሥራ እንቅስቃሴ

የመንግስት የፋይናንስ ድርጅቶች አጠቃላይ የቁጠባ ሂሳብ ክምችት እ.ኤ.አ. ሰኔ 30/2017 ላይ በተንቀሳቃሽ ሂሳብ የተቀመጠ የመንግስት ተንቀሳቃሽ ሂሳብን 163 ነጥብ 46 ቢሊዮን፣ በቁጠባ ሂሳብ የተቀመጠ 189 ነጥብ 06 ቢሊዮን እና በጊዜ ገደብ 13 ነጥብ 41 ቢሊዮን የተቀመጠ ብር በድምሩ ብር 365 ነጥብ 63 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ይህም ከታቀደው ብር 345 ነጥብ 13 ቢሊዮን የ106 ነጥብ 03 በመቶ ድርሻ ይዟል። ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው 277 ነጥብ 73 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር የ31 ነጥብ 76 በመቶ ብልጫ ተመዝግቧል።

 

5.      የውጭ ምንዛሪ ግኝት

የውጭ ምንዛሪ ግኝት በተመለከተ አገሪቱ ከምታመርተው ለውጪ ንግድ የሚሆን ምርት ሽያጭና በሐዋሳ ከሚገኝ ገቢ ሁለቱ የመንግስት ባንኮች እስከ እ.ኤ.አ. ሰኔ 30/2017 ላይ በነበረው ምንዛሪ መሰረት በድምሩ USD 4 ነጥብ 54 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አስገኝተዋል። ከእቅዱ USD 5 ነጥብ 65 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር የ80 ነጥብ 04 በመቶ አፈፃፀም ተመዝግቧል። ከባፈው ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው USD 4 ነጥብ 72 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር በ0 ነጥብ 22 ቅናሽ ተመዝግቧል። ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የታየው ቅናሽ የ Official Transfer, Service Receipt  እና FCY purchase ከታቀደው አንጻር ክንውናቸው አናሳ በመሆኑ ነው። ከዚሁ የውጪ ምንዛሪ ግኝት ውስጥ፤ የኢትዮጵያንግድባንክ 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ USD 0 ነጥብ 04 ቢሊዮን ዶላር አስገኝተዋል።

 

6.      የአረቦን አሰባሰብና ካሳ ክፍያ

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ጠቅላላ የተሰበሰበ የአርቦን ገቢ ብር 2 ነጥብ 72 ቢሊን የደረሰ ሲሆን ይህም ከታቀደው 2 ነጥብ 75 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር 98 ነጥብ 74 በመቶ አፈፃፀም አስመዝግቧል። በአንፃሩ ድርጅቱ ብር 1 ነጥብ 34 ቢሊዮን በካሳና በኮሚሽን መልክ ወጪ አድርጓል። ይህም ከእቅዱ ብር 998 ነጥብ 5 ሚሊዮን በብር 134 ነጥብ 75 በመቶ አፈፃፀም አስመዝግቧል።

 

የመንግሥትን አሠራርን በግልጽነትና በተጠያቂነት ላይ የተመሠረተ ለማድረግ ከሚቻልባቸው መንገዶች አንዱ ሀብትን ማሳወቅና ማስመዝገብ ነው። ሀብት ማስመዝገብ ሙስናና ብልሹ አሠራርን ለመከላከልና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉትን ተሞክሮዎች መሠረት በማድረግ የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 668/2002 ወጥቶ በሥራ ላይ እንዲውል ተደርጓል። በአዋጁ መሠረትም  የመንግሥት ባለሥልጣናትና ተሿሚዎች ሀብታቸውን የማስመዝገብ ግዴታ ተጥሎባቸዋል። በዚህም መሠረት የፌዴራል የሥነምግባርና የጸረ ሙስና ኮምሽን ባለፉት ዓመታት በሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሀብት መዝግቦ የያዘ ሲሆን በአዋጁ መሠረት ለሕዝብ ይፋ አለማድረጉ ግን እስከአሁንም አነጋጋሪነቱ እንደቀጠለ ነው።

ሀብት የምንለው ምንን ያካትታል?

ሀብት የምንለው በእንግሊዝኛው (asset) የሚባለውን ግንዛቤ ነው። በኢትዮጵያ የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ አዋጅ መሠረት ሀብት ስንል በይዞታነት የሚገኝ ማንኛውም የማይንቀሳቀስና የሚንቀሳቀስ ግዙፍነት ያለው ወይም ግዙፍነት የሌለውን እንዲሁም የመሬት ይዞታንና ዕዳን ይጨምራል።

 

 

በተለመደው አጠራር ሀብት/ንብረት የሚገለፀው በገንዘብ፣ በቤት፣ በመኪና እና በመሳሰሉት ሲሆን የሕግ ባለሙያዎች ንብረት የሚለውን አገላለፅ ለሁለት ከፍለው ይመለከቱታል። ይኸውም የሚንቀሳቀስ እና የማይንቀሳቀስ /ቋሚ/ በማለት ነው።

 

 

የሚንቀሳቀሱ /ተንቀሳቃሽ/ ንብረቶች በተፈጥሯቸው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ፀባያቸውን ሳይለቁ መንቀሳቀስ የሚችሉ ናቸው። የሚንቀሳቀሱ ንብረቶች እንደገና ግዙፍነት ያላቸውና የሌላቸው በመባል በሁለት ተከፍለው ይታያሉ። ግዙፍነት ያላቸው የሚባሉት የሚታዩ፣ የሚዳሰሱ እና የሚጨበጡ ንብረቶች ሲሆኑ ግዙፍነት የሌላቸው የሚባሉት በተቃራኒው ለመታየትና ለመዳሰስ የማይችሉ ለምሳሌ የአዕምሮ ንብረቶችና የመሳሰሉትን ያጠቃለለ ነው።

 

 

የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች በባህሪያቸው መንቀሳቀስ የማይችሉና ቢንቀሳቀሱም እንኳን የመጀመሪያ ፀባያቸውን በማጣት /በመፍረስ ወይም በመበላሸት/ ሊንቀሳቀሱ የሚችሉ ናቸው። መሬትና ቤቶችን በምሳሌነት ማቅረብ ይቻላል።

 

 

የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ሦስት አጠቃላይ ጥቅሞች አሉት

የመጀመሪያውና ዋንኛው ሙስናን አስቀድሞ የመከላከል (Preventive functions) ሲሆን የሙስና ወንጀልን ምርመራ ማቀላጠፍ (investigative function) እንዲሁም የሕዝብ አመኔታን መፍጠርና ማጠናከር ናቸው።

 

 

በነዚህ ዙሪያ ሊታዩ የሚችሉ በርካታና ዝርዝር ጥቅሞችም ሊጠቀሱ ይችላሉ። ለምሳሌ፡- የህዝብ ተመራጮች፣ በመንግስት የተመደቡ ኃለፊዎች፣ ተሿሚዎችና ሠራተኞች ሀብት አስቀድሞ በመመዝገቡ ምክንያት ግለሰቦቹ በሚገጥማቸው የጥቅም ግጭት ወቅት ትክክለኛ ውሳኔ እንዲኖራቸው ያግዛል። ለምሳሌ ስጦታና ተመሳሳይነት ያላቸው የገንዘብ ጥቅሞች መቀበልን አስመልክቶ ዜጎች ትኩረት ለሰጧቸው ህዝባዊና መንግሥታዊ ኃላፊዎችና ሠራተኞችን ሀብትና ንብረት በግልፅ በማወቃቸው በህዝባዊና መንግስታዊ አስተዳደሩ ላይ እምነት ያዳብራሉ።

 

 

ዜጎች ትኩረት በሚሰጧቸው ህዝባዊና መንግሥታዊ ኃላፊዎችና ሠራተኞች የሀብትና የንብረት ይዞታ ላይ ሊነሳ የማችለውን ከመረጃ የራቀ ሀሜትን ይቀንሳል።

 

ሙስናን ለመከላከልና ለመዋጋት በሚደረገው ርብርብ የማስረጃ ማሰባሰቡን ሂደት ቀላል ለማድረግ ያግዛል።

 

 

የሀብት ምዝገባ መረጃን ይፋ ማድረግ ለምን?

ከኮምሽኑ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያስረዱት የሀብትን ማስመዝገብ ሥራ፣  ለሕዝብ ከማሳወቅ ጋር ተቆራኝቶ ካልተተገበረ ለመልካም አስተዳደር እውን መሆን የሚኖረው ፋይዳ ዝቅተኛ ነው። ሀብት ተመዝግቦ መረጃው ለሕዝብ ክፍት የሚሆንበት ሁኔታ ከሌለ የሚጠበቀው ግልፅነት በሚፈልገው ደረጃ ካለመፈጠሩም በላይ ተጠያቂነት የሚተገበርበትን መንገድ ያጠበዋል። በዚህም ምክንያት ሕዝብ በመረጣቸው ተመራጮች፤ መንግሥት ኃላፊዎችና ሠራተኞች ላይ የሚኖረውን ቅሬታና ጥርጣሬ እንዲያድግ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። እርግጥ ነው፤ ምዝገባ ብቻውን ሙስናና ብልሹ አሠራሮች እንዲቀረፉ  አያግዝም።

 

 

ልምዳቸውን ለመመልከት ከቻልንባቸው የላቲን አሜሪካ ሀገራት እንደምንረዳው በርካታ ሀገራት በተለያየ አግባብ የሀብት ምዝገባ ፋይሎችን ይፋ ያደርጋሉ። ለምሳሌ በሀማስ የተጨመቀ (summarized) የሀብት ማሳወቂያ ምዝገባዎች በጋዜጣ እንዲወጡ ሲደረግ፤ በኢኳዶር ደግሞ ሁሉም የሀብት ማሳወቅ ምዝገባዎች ሕዝብ እንዲያውቃቸው ወይም በሕጋዊ አካል እንዲረጋገጡ ይደረጋል።

 

 

በተጨማሪም በአርጀንቲና ከሚዲያ አካላት በስተቀር ሌሎች የተመዝጋቢ ግለሰቦችን የተመዘገበ ሐብት መረጃ ለማግኘት ከፈለጉ በጹሁፍ ጥያቄው ለሚመለከተው ክፍል ቀርቦ ሊሰጥ ይችላል። በፔሩ ደግሞ ደመወዝን ጨምሮ የመንግሥት ኃላፊዎችን ሐብት ሕዝብ የማወቅ መብት እንዳለው በሕገ መንግስታቸው ተደንግጓል።

 

 

በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካም የዚህ ምዝገባ ዝርዝር ለስድስት ዓመታት ለሕዝብ ክፍት ከመሆኑም በላይ የምዝገባው ሪፖርት በድረ-ገፅ ተጭኖ ይገኛል።

 

 

በአውሮፓ ሀገራትም የተመዘገበው ሀብትና ንብረት መረጃ ህዝብ እንዲያውቀው ይደረጋል።

 

 

በደቡብ አፍሪካ ከተመዘገበው ዝርዝር ሐብትና ንብረት ውስጥ ከተወሰኑት በስተቀር (የደመወዝ መጠን፣ መኖሪያ አድራሻ፣ በቤተሰብ አባላት ስም ከተመዘገበ ሐብትና ንብረት) ሌላው ለሕዝብ ይፋ ይደረጋል።

 

 

በኤስያና ፓስፊክ የተመዘገበን ሐብትና ንብረት ለህዝብ የማሳወቅ ሁኔታም ከህንድ በስተቀር በተጠቀሱት ሁሉም ሀገራት በይፋ ለሕዝብ ክፍት ነው። በህንድ ግን አስመዝጋቢው ኃላፊ ወይም ሠራተኛ ሀብቱንና ንብረቱን የሚያሳውቀው በታሸገ ፖስታ በማቅረብ ሲሆን፤ ፖስታው መከፈት የሚችለው በፍርድ ቤቶች ነው።

 

ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ በሀብት ማሳወቅና ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 668/2002 መሠረት የምዝገባው መረጃው ለሕዝብ በቀላሉ ተደራሽ ሊሆን በሚችል መልክ የተዘጋጀ አለመሆኑ የኮምሽኑ ቁርጠኝነት ላይ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን እያስነሳበት ይገኛል። መረጃው በይፋ ባለመገለጹ ምክንያትም ባለሥልጣናትና ተሿሚዎች በገቢያቸው ልክ እየኖሩ ስለመሆኑ፣ ትክክለኛ ሀብታቸውን ስለማስመዝገባቸው ሕዝብ እንዳያውቅና አውቆም ተጨማሪ መረጃ እንዳይሰጥ አግዷል።

 

በአሁኑ ወቅት በተለይ በማህበራዊ ድረገጾች እገሌ ከገቢው በላይ ሀብት አፍርቷል፣ በሙስና ተዘፍቋል እየተባሉ የሚነገሩ ነገሮች አሉ። እነዚህ በአሉባልታ መልክ የሚነገሩ፣ ነገርግን ሲደጋገሙ በመንግሥትና በህዝብ መካከል ያለውን አመኔታ ለጎዱ የሚችሉ መረጃዎች ማጥራት የሚቻለው የሀብት ምዝገባ መረጃውን በወቅቱ ይፋ ማድረግ ቢቻል ነበር። ይህ አለመሆኑ ከገቢያቸው በላይ ሀብት የሚያፈሩ፣ ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ይዘው የሚገኙ ግለሰቦች ወይንም ሹማምንት እንዲበራከቱ የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል ተብሎ ይገመታል።¾

ውጤታማ የሥራ መሪዎች በፒራሚዱ ውስጥ ሆነው ወደላይ፣ ወደታች፣ ወደጎን የመሄድ አቅሙ ያላቸው ናቸው

ዶ/ር አረጋ ይርዳው

የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር

 

የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር (ሲኢኦ) ቢሮ የዛሬ 17 ዓመት (በ1992 ዓ.ም) ሲመሰረት አምስት ኩባንያዎችን በመያዝ ነበር። የኩባንያዎቹ ቁጥር በ17 ዓመታት ወደ 25 አድጓል። ሲጀመር 4 ሺ 136 የነበረው የሠራተኞች ቁጥር ዛሬ ላይ 9 ሺ 395 (የትረስት 2000 ኮንትራት ሠራተኞችን አያካትትም) የደረሰ ሲሆን ዓመታዊ የሽያጭ መጠኑም ከ492 ሺ ብር ወደ ብር 6 ቢሊየን ዕድገት ተመዝግቦበታል። የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች አነሳስና ዕድገት የዳሰሰ ቆይታ ከቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር ዶ/ር አረጋ ይርዳው ጋር  አድርገናል። መልካም ንባብ።

ሰንደቅ፡- የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሲኢኦ ቢሮ ከተመሠረተ 17 ዓመት ሞልቶታል፣ ሒደቱን እንዴት ያስታውሱታል?

ዶ/ር አረጋ፡- ከ17 ዓመታት በፊት ሼህ ሙሐመድ ያስቡት የነበረው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ድርጅቶች በአንድ ላይ ሆነው የሚመሩበት መንገድ እንዲፈጠር ነበር። አሜሪካ እያለሁ ኃላፊነት ሲሰጠኝ ጥናት አድርጌ ከሼህ ሙሐመድ ጋር ዋሽንግተን ተገናኝተን ፍኖተ ካርታ (ሮድማፕ) ሠራን። ይኸን ለመሥራት አስቀድሜ ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ ለ70 ቀናት ያህል በዚያን ጊዜ የነበሩትን ኩባንያዎቹን ሳጠና ቆይቼ ተመልሻለሁ። በእነዚህ ቀናት ከየኩባንያዎቹ ሥራ አስኪያጆች፣ ከአንዳንድ የመንግሥት አካላት ጋር ያለውን ሁኔታ አጥንቼ ነው ሮድማፑን የሠራሁት። ከጥናቱ በኋላ በሮድማፑ መሠረት ሥራው ይጀመር ሲባል እዚህ አዲስ አበባ ቫቲካን አካባቢ ወደሚገኘው የሚድሮክ ቢሮ መጣሁ። እዚያ ለአምስት ወራት ያህል ሥራው እንዴት መጀመር እንዳለበት ሳጠናና ስዘጋጅ ቆይቻለሁ። በመጀመሪያ ላይ ወደቴክኖሎጂ ግሩፑ የመጡት አምስት ኩባንያዎች ነበሩ። እነሱም ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን፣ በወቅቱ ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን በፕራይቬታይዜሽን ተገዝቶ አመራሩን ፈረንጆች የያዙበት ሁኔታ ነበር። ኤልፎራ ኩባንያ - በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ድርጅቶች ነበሩት። ወደ ስምንት የተለያዩ መንግሥት እጅ የነበሩ ድርጅቶች ስለነበሩ በአንድ አሰባስቦ ኤልፎራ ተብሎ የተደራጀ ነው። ሦስተኛው ሁዳ ሪል እስቴት ነው። ሁዳ፤ ናኒ  እና ሎሊ  የሚባሉ ህንጻዎች መሠረት ተጥሎ መቻሬ የሚባል ግቢ ውስጥ ደግሞ የፕሮጀክት ጽ/ቤት ሠርቶ የሚሠራ ነበር። አራተኛው በወቅቱ ድል ቀለም የሚባለው ፋብሪካ ነው። አሁን ኤም ቢ አይ ተብሏል። ፋብሪካው ያኔ በገርጂ አካባቢ ጽ/ቤት ከፍቶ ሥራውን ለማስፋፋት እያሰበ ነበር። የመጨረሻው ኮምቦልቻ የሚገኘው የብረታ ብረት ፋብሪካ ነው። እነዚህ ነበሩ፤ በወቅቱ የተረከብናቸው። እያንዳንዱ ኩባንያ ቀደም ብዬ በመጣሁ ጊዜ ለጥናት ቃለመጠይቅ አድርጌ ስለነበር (መረጃ) ነበረኝ ። ስለዚህ በኋላ ስመጣ አዲስ አልሆነብኝም። ወደሥራ ከተገባ በኋላ እያንዳንዱ ኩባንያ የነበረውን መዋቅር መመልከት፣ አካባቢውን መመልከት፣ ሰውን መመልከት፣ ምርቱን መመልከት እና ይህን በሙሉ በአዲስ መዋቅር፣ በአዲስ ፖሊሲና አሠራር እንዲገቡ ማድረግ ይገባ ነበር። ሁሉም ድርጅቶች ላይ የነበሩ አመራሮችን እየሰበሰቡ ስለሂዩማን ሪሶርስ ፖሊሲ፣ ስለፋይናንስ ፖሊሲ መነጋገርና መተግበር ነበረብን። ይህንንም ራሳችን አዘጋጀን። እነዚህን ፖሊሲዎችን የማስረዳትና የማስጨበጥ ሥራዎች ማከናወን ነበረብን። እነዚህ አምስቱ ኩባንያዎች ላይ የነበረን ድካም ከፍ ያለ ነበር። የነበረኝ ፍልስፍና ኩባንያዎቹ ያላቸውን ሠራተኞችን፣ ዋና ሥራ አስኪያጆች ባሉበት መጠቀምና አሠራራቸውን መለወጥ ስለነበር ፈታኝ ነበር።  ስለሆነም ሰዎቹ ባሉበት አዲሱ አሠራር እንዲገባቸው፣ እንዲላመዱት አድርጎ ለውጥ እንዲመጣ የማድረግ አቅጣጫ ነው የተከተልነው። ምክንያቱም በቦታው ያገለገለንና ሥራውን የለመደን ሰው አንስተህ በሌላ በመተካት ብቻ ውጤት አይገኝም። የመምራት ዘዴ ወይም ሲስተም እንደወንዝ ነው። ይህንን የሚፈስ ወንዝ በትክክለኛ መንገድ እንዲስተካከል ማድረግ ተገቢ ነው። ከዚያ በወንዙ የሚዋኙትን ሰዎች ማሰልጠንና በውሃ ውስጥ ሳይሰጥሙ ወንዙ ወደሚፈስበት አቅጣጫ አብረው እንዲዋኙ ማድረግ ይገባል። ወደጎን የሚዋኙ ካሉም ማስተካከያ እየፈጠሩ በትክክለኛው አቅጣጫ እንዲዋኙ ማድረግ ያስፈልጋል።

 

ሌላው የሠራተኛውን ጥቅማጥቅም ሥርዓት የማስያዝ ጉዳይ ነው። ሠራተኛ ተኮር አሠራር መዘርጋት ያስፈልግ ነበር። ለምሳሌ ፕሮቪደንት ፈንድ እንዲኖር ማድረግ፣ የዕረፍት ቀናት፣ የዓመታዊ የደመወዝና ጥቅማጥቅም ዕድገት ጉዳይ፣ የቦነስ ልዩ ጉርሻ ጉዳይ፣ የሕክምና ጉዳይ መስመር እንዲይዝ ማድረግ ነው። ቀጥሎም ያሉትን እያንዳንዱን ጥቅማ ጥቅሞች ሁሉም ሠራተኛ በሚገባ እንዲያውቅ ማድረግ ነው። እያንዳንዱ ኩባንያ የራሱ ራዕይ፣ ተልዕኮና እሴቶች እንዲኖረው ማድረግ ነው። ይኼን በማድረግ ሁሉም ኩባንያዎች አንድ ላይ ቡድናዊ ስሜት እንዲፈጥሩ የሚያስችል ሥራዎችን አከናውነናል።

 

በዚህ ሒደት “ኢትዮጵያናይዜሽን” የሚል ፍልስፍና ውስጥ ገባን። ኢትዮጵያናይዜሽን ማለት የውጭ ዜጎች የሚሠሩትን ሥራ ኢትዮጵያውያን እንዲሠሩ ማበረታታትን የሚመለከት ነው። ቀለም ፋብሪካ ላይ የውጭ ሰዎች ነበሩ፣ በኢትዮጵያዊያን እንዲተኩ አደረግን። ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ላይ ከ30 በላይ የሚሆኑ የውጭ ዜጐች ነበሩ። እነዚያን በኢትዮጵያውያን እንዲተኩ አድርገናል። መጀመሪያ ላይ የነበረው ምዕራፍ ከፍተኛውና አንድ መሠረት የመጣያ ሂደት ነበር። የሥራ ባህል የመፍጠርና የመከተል ጉዳይ ስለነበር ትንሽ አስቸጋሪና ከበድ ያለ ነበር። ውጭ ሀገር የተገኘን ዕውቀት ክህሎት ይዞ መጥቶ እዚህ ኮፒ ለማድረግ መሞከር ሳይሆን የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ ተመልክተህ፣ እንዴት አድርጌ ላጣጥመው፣ ላዋህደው በማለት ለነባራዊው ሁኔታ አመች ስልት መፍጠር ያስፈልጋል። በአሜሪካን የለመድከውን አሠራር እንዳለ አመጣለሁ ብትል እዚህ ያለ ሰው እንደ አሜሪካኖች ሆኖ አይጠብቅህም። ጥበቡ የነበረንን፣ የምናውቃትን ዕውቀት በሀገር ውስጥ ካገኘነው ጋር አጣጥሞ ሥራ ላይ ማዋል ነው። ይህን በሚገባ የሠራንበት ስለሆነ እጅግ የጠቀመን ፍልስፍና ነው። ለዚህም ነው፣ መመሪያዎችንና ፖሊሲዎችን የሚሠራልን ሰው ያልቀጠርነው። ሁሉንም በራስ አቅም እኛው ለመወጣት ሞክረናል። እሱ ጠቅሞናል። በዚህም ምክንያት ራሳችን ከሠራተኛውና አመራሩ ጋር ያወጣነው ሥርዓት በሥራ ስንተረጉመው ችግር አላመጣብንም።

 

ሰንደቅ፡- ጅምሩ ላይ ፈተናዎቹ ምን ነበሩ?

ዶ/ር አረጋ፡- የመጀመሪያ ፈተና አንዳንዶቹ ድርጅቶች በፕራይቬታይዜሽን ሂደት የመጡ ስለሆነ የራሳቸው ችግር ነበራቸው። ከዚህ ችግርም መውጣት ነበረባቸው። ይህ ሒደት የዓመታት ጊዜን ወስዷል። ሌላው ወደዚህ ሀገር የመጣሁት በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የመጨረሻ ወቅት ነበር። ኤልፎራ ኩባንያ ብዙ ኮንትራት አግኝቶ ለመንግሥት ይሠራ ነበር። ከጦርነቱ በኋላ ይሄ ኮንትራት ሲሰረዝ ከሥራው ጋር ተያይዞ በብዛት ተቀጥሮ ይሠራ የነበረው የኤልፎራ ሠራተኛ መቀነስ ነበረበት። ይህም ራሱን የቻለ አስቸጋሪ ሁኔታ ነበረው። ምክንያቱም ሰው መቀነስ በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ። በተለይ በፕራይቬታይዜሽን የተገዙት ሚድሮክ ወርቅ እና ኤልፎራ በውስጣቸው ዘመናዊ መሣሪያ የሌላቸው፣ ግን ብዙ የሰው ኃይል የያዙ ስለነበረ፣ ይህንን ዘመናዊ ማድረግ አስፈላጊ ነበር። ዘመናዊ ለማድረግ በምንሞክርበት ጊዜ በተለይ ኤልፎራ ላይ የፕራይቬታይዜሽን ሂደት አለመጠናቀቅ ብዙ ውጣ ውረድ ነበረበት። ስለዚህ በሒደት ሁለቱንም እያጣጣምን ለመጓዝ ሞክረናል። በአንድ በኩል የፕራይቬታይዜሽኑ ጉዳይ ፍጻሜ ለማድረስ በሌላ በኩል ደግሞ ኩባንያዎች ሥራ ላይ እንዲሆኑና ሠራተኛው እንዳይበተን፣ እንዲቆይ አድርገናል። 

 

ከዚያ በኋላ ሌሎች ኩባንያዎች መጨመር የጀመሩት በሁለት መልክ ነው። አንዱ የምንሠራው ሥራ ፍላጎት የፈጠራቸው ናቸው። ሆም ዲፖ ኩባንያ፣ የኮስፒ እና የኤም ቢ አይ ምርቶች ለመሸጥ የተቋቋመ ነው። ሌላው ትረስት የሚባለው የጥበቃ አገልግሎት የሚሰጥ ኩባንያ እንዲሁ ፍላጎት የፈጠረው ነው። ድርድቶቹ መጠበቅ ያለባቸው በራሳቸው በኩባንያዎቹ የጥበቃ አባላት ሳይሆን የጥበቃን ሥራ በሚያከናውን ሌላ ኩባንያ መሆን አለበት በሚል ፍልስፍና ያደረግነው ነው። እኛን ተከትለው ከተማ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ከ50 ያላነሱ የሴኩሪቲ ኩባንያዎች በመፈጠራቸው ደስተኞች ነን። ሌላው ፍላጎት አስገድዶን የፈጠርነው ዩናይትድ አውቶ ሜንቴናንስ ኩባንያ ነው። ይህን ያደረግንበት በየቦታው የተበታተኑ የመኪና ጋራዦች በመኖራቸው ከወጭና እና ከጥራት አኳያ ችግር ነበረ። በተጨማሪም ኩባንያዎቻችን የየራሳቸው ጋራዦች በማደራጀት ለመጠቀም ይሞክሩ ነበር። ለምሳሌ ሚድሮክ ወርቅ የራሱ ጋራዥ ነበረው። ኤልፎራም የራሱ ነበረው። እነዚህን አጥፈን አንድ ኩባንያ በማቋቋም ለሁሉም የቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች ተሽከርካሪዎች አገልግሎት እንዲሰጥ ዩናይትድ አውቶ ሜንቴናንስን አቋቋምን። የጋራ አገልግሎት የሚባል ፍልስፍና በመጠቀም ሌላ ለውጥ ጨመርን። ስለሆነም እያንዳንዱ ድርጅቶች የራሱ ኦዲተር፣ የራሱ የሕግ አገልግሎት እንዲኖረው በማድረግ ፈንታ እነዚህን አገልግሎቶች የሚሰጡ ሰዎች በአንድ ቦታ እንዲሆኑና ሁሉንም ኩባንያዎች እንዲያገለግሉ በማድረጋችን ይበልጥ ተጠቃሚ ሆነናል።

 

ከዚያ ቀጥለን ያደረግነው ነገር አዳዲስ ህብረት ፈጣሪ የሆኑ ጠቃሚ ባህሎችን መፍጠር ነበር። ለምሳሌ የደንበኞች ቀን፣ የሠራተኞች ቀን፣ የቤተሰብ ቀን እንዲኖር አደረግን። በተጨማሪም ሠራተኛውን ስለፖሊሲ፣ ስለአመራር ወዘተ እራሳችን የማስተማር ሥራ ውስጥ ገባን። ሠራተኛውን ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እስከ 12ኛ ክፍል መማር ከፈለገ፣ ከዚያም በላይ መማር ከፈለገ በያለበት በሚገኙ የትምህርት ተቋማት እንዲማር የሚያስችል መመሪያ አወጣን። ስለዚህ ሠራተኛው የመማር ዕድል መኖሩን አወቀ። እነዚህ ለጋራ ጥቅም የሚውሉ ሥርዓቶችን እንዲስፋፉ አደረግን። ከዚያ በኋላ ሌሎች ኩባንያዎች ወደኛ መቀላቀል ጀመሩ። በቅድሚያ ከሌላ ግሩፕ መጥተው የተቀላቀሉን ዋንዛ እና አዲስ ጋዝ ናቸው። እነዚህ ሁለት ድርጅቶች የኪሳራ ችግር ገጥሟቸው መዘጋት ደረጃ ላይ በደረሱበት ጊዜ ሼህ ሙሐመድ ከሚዘጉ እንደገና እንዲያንሰራሩ እናድርጋቸው ብለው ወደእኛ እንዲቀላቀሉ ሆኑ። ኩባንያዎቹ በፕራይቬታይዜሽን የተገኙ ነበሩ። እነሱም ወደዘረጋነው አሠራር ሲስተም እንዲገቡና እንዲንሰራሩ አደረግን።

 

የአንድ ኩባንያ የመዋቅር መሠረቶች ናቸው የምንላቸው በዋናነት በግራ በኩል አገልግሎት ሰጪ በቀኝ በኩል ኦፕሬሽን የሚባሉት ክፍሎች ናቸው። አገልግሎት ሰጪ የምንላቸው ሂዩማን ሪሶርስ አገልግሎት፣ ማቴሪያልስ ማኔጅመንት አገልግሎት፣ የፋይናንስ አገልግሎት ብለን የምንጠራቸው ናቸው። አገልግሎት ብለን የምንጠራበት ዋነኛ ምክንያት እነዚህ ዘርፎች ለኦፕሬሽኑ አገልግሎት ሰጪዎች በመሆናቸው ነው።

 

በሌላ በኩል ያለው ኦፕሬሽን ነው። ኦፕሬሽን የሚያመርተው ክፍል ነው። ይሄ አሠራር (ስትራክቸር) በሁሉም ኩባንያዎች ላይ ተዘርግቷል። ይህ አሠራር አንዱ ጥቅሙ አንድ ኩባንያ ላይ ጠንከር ያለ የፋይናንስ ሰው ወይም ሌላ ባለሙያ ብታገኝ ወደሌላ ደከም ወዳለ በማዘዋወር ጭምር ለማሰማራት፣ የተሻለ ዕድል ለመስጠት የሚያስችል ነው። ሕጋዊ በሆነ መንገድ ሠራተኛው ካለበት አንድ ኩባንያ ሥራውን ለቅቆ ወደ ሌላ ኩባንያ እንዲቀጠርና የተሻለ ልምድና አሠራሩን እንዲያጠናክርና እንዲሻሻል ዕድል ይሰጣል።

 

እንደ ትራንስ ኔሽን ያሉ ኩባንያዎች የተመሠረቱት የሚጠቀሙበት መሣሪያ በእጃችን አስቀድሞ ስለነበረ የተፈጠሩ ናቸው። ቀደም ሲል ጀምሮ ሼህ ሙሐመድ አውሮፕላኖች ነበሩዋቸው። እነዚህ አውሮፕላኖች ብዙ ጊዜ ሥራ ፈትተው የሚቆሙበት ሁኔታ ነበር። ለእሳቸው አገልግሎት ከመስጠት ውጪ ለቢዝነስ አገልግሎት አይሰጡም ነበር። በዚህ ሒደት ግን ለአውሮፕላኖቹ ጥገና፣ የመለዋወጫና ተያያዥ ወጪዎች ከሼህ ሙሐመድ ኪስ ይወጣል። ይሄ ከሚሆን አይሮፕላኖቹን ተጠቅመን ራሱን የሚያስተዳድር ኩባንያ ሆኖ እንዲቋቋም አድርገናል።

 

ሬይንቦ የመኪና ኪራይና የቱሪዝም አገልግሎት የሚሰጠው ድርጅታችን ደግሞ ቀደም ሲል ለአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ተብለው በሼህ ሙሐመድ የተገዙ መኪኖች ለመንግሥት ካገለገሉ በኋላ ሲመለሱ ሥራ ላይ መዋል ስለነበረባቸው የተቋቋመ ነው።

 

ሠላም የነርሶች ማሰልጠኛ ኮሌጅ በተመሳሳይ ሁናቴ የተገኘ ነው። መጀመሪያ ኮሌጁ ተቋቁሞ ከሠራ በኋላ ለአራት ዓመታት ተዘግቶ ነበር። ከተዘጋ በኋላ አስተማሪዎቹ አሉ፣ ሐብቱም አለ። ተማሪዎች ግን አልነበሩም፤ ለምንድነው ቁጭ የሚለው ብለን ወደ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ እንዲቀላቀል አደረግነው።

 

በዚህ መልኩ የኩባንያዎችን ቁጥር እያደገ በአሁኑ ሰዓት ቁጥራቸው 25 ደርሷል።

 

ሰንደቅ፡- ቀደም ሲል ጀምሮ መጠሪያ ስማችሁ ላይ “ቴክኖሎጂ” የሚል ቃል አለ። ይህ ቃል እንዴት ሊመረጥ ቻለ?

ዶ/ር አረጋ፡- መጀመሪያ ሥራ ስንጀምር እኔና ሼህ ሙሑመድ በአንድ ጉዳይ ለንደን ላይ ነበርን፤ በአጋጣሚም ስለራዕያችን እናወራ ነበር። እንዴት አድርገን ነው፤ ኩባንያዎቹን የምንመራው፣ የምናስተዳድረው እያልን ስንነጋገር በዚያን ጊዜ የነበረው አካሄድ ምርት ማምረት ወይም ማንፋክቸሪንግ ላይ የተሠማሩትን ኩባንያዎች አንድ ላይ ማድረጉ ይሻላል። እነዚህ ቴክኒካል ነገር አላቸው። ከፋይናንስ፣ ከኢንሹራንስ፣ ከግዢ ጋር ከተሠማሩት ጋር ሲነጻጸሩ እነዚህ ምርት ተኮር የሆኑ ኩባንያዎች የተለዩ ናቸው ብለን አሰብን። ሚድሮክ ወርቅ፣ ኮስፒ፣ ኤልፎራ፣ ሁዳ፣ ኤም ቢ አይ፣… የሚያመርቱ ኩባንያዎች ናቸው። እነዚህ ቴክኒክ ላይ የሚያተኩሩ ኩባንያዎች ይዘን የቴክኖሎጂ ግሩፕ እንበላቸው የሚል ሃሳብ የመጣው ከሼህ ሙሐመድ ነው። በወቅቱ ሃሳቡን ሼህ ሙሐመድ ወረቀት ላይ በብዕር እንደፃፉት አስታውሳለሁ። በዚህ መልክ ነው፤ ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ የሚለው ስያሜ የመጣው።

 

ሰንደቅ፡- በአሁን ሰዓት በቴክኖሎጂ ግሩፑ ውስጥ አምራች ያልሆኑ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም አሉ?

ዶ/ር አረጋ፡- አዎን! ስያሜው አንዴ ከወጣ በኋላ በዚያው ቀረ፤ ልንለውጠው አልቻልንም። በየጊዜው ፍላጎቶቻችን ተከትለን አዳዲስ ኩባንያዎችን ፈጥረናል። ለምሳሌ ኩዊንስ ኩባንያ የኤልፎራን ምርት በችርቻሮ ለኅብረተሰቡ ለማቅረብ ታቅዶ የተቋቋመ ነው። ሆም ዴፖም እንዲሁ ነው። እነዚህ ሽያጭ ላይ የሚሰሩ እንጂ ቴክኒክ ነክ ተቋማት ወይም አምራች አለመሆናቸው ይታወቃል። ሒደት ያመጣቸው ናቸው። ስሙም በዛው እንደተጀመረ ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ በመባል መታወቁን ቀጥሏል።

 

ሰንደቅ፡- እንደሚታወቀው 25 ኩባንያዎችን አይደለም አንድ ቤተሰብ ማስተዳደርና መምራት ከባድ ነው። እነዚህን ኩባንያዎች ለማስተዳደር፣ ለመምራት ያስቻልዎ የአመራር ጥበብ ምንድነው?

ዶ/ር አረጋ፡- መጀመሪያ ኩባንያን አንድ ላይ አድርጎ መምራት የሚለው የሆልዲንግ ኩባንያ ልምድ በምዕራቡ ዓለም የተለመደና ረጅም ጊዜ ሲሰራበት የኖረ ነው። አንድ ኩባንያ ሆልዲንግ ኩባንያ አቋም ይዞ ብዙ ድርጅቶችን በውስጡ አካቶ፣ ከላይ የቦርድ አመራር ኖሮት ይሰራል። ለምሳሌ አውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ ኩባንያ እንዲሁ ከውጭ ሆነን ስናየው አውሮፕላን ብቻ የሚያመርት ይመስለናል። ነገር ግን በሥሩ ከአውሮፕላን ሥራ ውጭ የተለያዩ ዘርፎች ላይ የተሠማሩ ኩባንያዎች ስብስብ ነው። አማዞን የሚባል ኩባንያ አለ። በየጊዜው ሲገዛ ታየዋለህ። በሥሩ ብዙ ኩባንያዎች ስላሉ ወይንም ሆልዲንግ ኩባንያ በመሆኑ ነው። እኔ ወደ ሀገሬ ስመለስ ከ17 ዓመት በፊት የሆልዲንግ ኩባንያ አሠራር በኢትዮጵያ ውስጥ በሕግ የተፈቀደና ግልጽ የሆነ ጉዳይ አልነበረም። ስለዚህ ያለው ጥበብ እያንዳንዱ የቴክኖሎጂ አባል ኩባንያ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ራሱን ችሎ ማቋቋም ብቻ ነው። ብዙ ሰዎች የማይገባቸው አንድ ላይ ስላደረግናቸው ከአንዱ ወደ አንዱ ሰዎችን እንደልባችን የምንወስድ፣ ገንዘብ ከአንዱ ወደ ሌላው የምንወስድ ይመስላቸዋል። እንደዚህ አናደርግም፤ ይህ ዓይነቱ አሠራርም ሕጋዊ አይደለም።

የአመራር ጥበብ ምንድነው ካልክ የሲኢኦ ቢሮ እንዲኖር ማድረጋችን ነው። የሲኢኦ ቢሮ ከእነዚህ ኩባንያዎች ጋር የሊደርሺፕ ኮንትራት ገብቶ የሚሠራ፤  ሚድሮክ ሲኢኦ የአመራር አገልግሎት ሰጭ ኃ.የተ.የግል ኩባንያ የሚባል አቋቋምን። ይህም ከ25 ኩባንያዎች አንዱና በማኔጅመንትና በሊደርሺፕ አገልግሎት ከተሰማራው ድርጅት ውሰጥ የሲኢኦ ቢሮ ይገኛል። ሌሎች 24 ኩባንያዎች ከሲኢኦ ቢሮ ከሚገኝበት ኩባንያ ጋር የአመራር አገልግሎት ለማግኘት ኮንትራት ገብተዋል። ለእነዚህ አገልግሎት እያንዳንዱ ኩባንያ ይከፍላል። በዚያ አማካይነት የጋራ የሆነውን የሊደርሺፕ አገልግሎት እንሰጣቸዋለን። በዚህ መልኩ ነው እየሠራን ያለነው። በሀገራችን የሆልዲንግ ኩባንያ ሕግ ሥራ ላይ ሲውል ባለቤቱ አንድ እስከሆነ ድረስ በአንድ መሰብሰብ ይቻላል። ስለዚህ እስካሁን በጥበብ ነው የመራነው። ስለሆነም ቀደም ሲል አምስት ኩባንያዎች ላይ የነበረውን አቅም እያሳደጉ ለ25ቱም ማዳረስ ችለናል። 26ኛ ኩባንያ ይመጣል ቢባል በቅድሚያ ኩባንያውን እናጠናለን። ምን ዓይነት ስትራክቸር እንዳለው እንመለከታለን፣ ያለንን ፖሊሲዎችና መሣሪያዎች የአዲሱን ኩባንያ ሎጎ በመሥራትና በመለጠፍ፣ ሥራ ማስጀመር ነው። ከዚያ የፋይናንስና፣ የማርኬቲንግ፣ የምርትን ወዘተ ሁኔታዎች መመልከት ነው። ይሄ ከሆነ በኋላ ለሠራተኛው፣ ለአመራሩ ሥልጠና መስጠት ነው። ከዚያ ቀጥለን ሠራተኞች የራሳቸውን ማኅበር እንዲያቋቋሙ፣ የተቋቋሙ ካሉም እንዲጠናከሩ እናበረታታለን። ሠራተኛው የሚያገኘው ጥቅም ምን እንደሆነ፣ ከእሱ ምን እንደሚጠበቅበት በየጊዜው እናስረዳለን። በየዓመቱ በጋራ የምናደርገው የኩባንያዎች የሥራ አፈፃፀም ግምገማ ተካፋይ እንዲሆን ይደረጋል። አዲስ የመጣው ኩባንያ ሌሎች ኩባንያዎች አፈፃፀማቸውን ሲያቀርቡ ያያል። እሱም በዚያው መሠረት ያቀርባል። ጥበቡ ይህ ነው። ሠራተኛው በምንሠራው ሥራ ሁሉ ያገባኛል፣ የእኔነው ብሎ እንዲያምን ማድረግ ነው። በሁሉም ኩባንያዎች ውስጣዊ መደጋገፍ እንዲኖር ማድረግ ነው። አንዱ ኩባንያ ለሌላው ኩባንያ ደንበኛ ነው። ይሄ ማለት አንድ ኩባንያ የሚሸጥ ዕቃ ይኖረዋል። ሌላኛው ኩባንያ ያንን ዕቃ መግዛት ቢፈልግ፣ ሌሎች ተመሳሳይ ከግሩፑ ውጭ ካሉ ኩባንያዎች ጋር በዋጋ ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ ግዢው ይፈፀማል እንጂ አባል ነኝ ብሎ ዋጋ እንደፈለገ አይጭንም ወይም አይቀንስም። ሊገዛ የተፈለገው ዕቃ እዚሁ ካለ አንደኛው ኩባንያ ውጭ ሄዶ የሚገዛበት ምክንያት የለም። ግዥና መሸጡ እዚሁ በግሩፑ ይከናወናል።

 

ሰንደቅ፡- በአጠቃላይ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ያበረከቱትን አስተዋፅኦ እንዴት ይገልፁታል?

ዶ/ር አረጋ፡- የኢኮኖሚ አስተዋፅኦ በምንድነው የምትለካው? ለእኔ ሀገር የሚጀምረው ከቤተሰብ ነው። የቤተሰብ ገቢ ከፍና ዝቅ ማለቱ የሀገርን ኢኮኖሚ ይለካል ብዬ አስባለሁ። ብዙ ጊዜ ሀገሪቱ አድጋለች ሲባል ሰዎች ለመቀበል ይቸገራሉ። ቤቴ፣ ኑሮዬ መቼ ተሻሻለና ነው ሀገሪትዋ አደገች የሚሉት ይልና ለመቀበል ይቸገራል። በሀገር ደረጃ ያለው ዕድገት የኢኮኖሚ መለኪያ አለው። ዓለም የሚጠቀምበትን መለኪያ ተጠቅመህ ሀገሪትዋ በዚህ ያህል መቶኛ አድጋለች ማለት ይቻላል። በተመሳሳይ ሁኔታ ዕድገቱ በነፍስ ወከፍ ይመጣል። በነፍሰወከፍ ሲባል ቤተሰብ ውስጥ ይገባል ማለት ነው። አንድ ቤተሰብ ባለፈው ዓመት ያገኝ ከነበረው ገቢው የተሻለ ከሆነ መሻሻል አለ ማለት ነው። ሠራተኛው የደመወዝ ጭማሪ፣ ዕድገት አግኝቶ ከሆነ ኩባንያው ተሻሽሏል፣ አድጓል ማለት ነው። ሠራተኛው ባለበት ቁጭ ብሎ ከሆነ፣ የሚሠራበትም ኩባንያ አልተነቃነቀም ማለት ነው። የተያያዘ ነገር ነው። እኛ ዕድገትን የምንለካው ኩባንያው ሰዎች መቅጠር ችሏል ወይ? ደመወዝ ካለፈው ዓመት ለሠራተኛ ተጨምሮለታል ወይ በማለት ነው። በነገራችን ላይ በኩባንያዎቻችን የደመወዝ ጭማሪ በየዓመቱ የሚደረገው በሠራተኛ የሥራ ውጤት መሠረት ነው። አንድ ጊዜ ተቋርጦ አያውቅም። የሥራ ውጤት መገምገም ፍልስፍናችን ብር መጨመር ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን ሠራተኛውን በክህሎት ማደግንም ያገናዘበ ነው። ኩባንያው ደመወዝ መጨመር ባይችል፣ ዘንድሮ የምሰጠው ገንዘብ የለኝም ቢል እንኳን የሠራተኛው የሥራ ውጤት ግምገማ “አፕሬይዛል” አይቋረጥም። ስለዚህ ለሠራተኛው የምንሰጠው የደመወዝ ጭማሪ ለሁለት የተከፈለ ነው። ሠራተኛው የሥራ አፈፃፀሙ ይመዘንና ኤ፣ ቢ፣ ሲ ወይም ዲ ደረጃዎች ውስጥ አንዱን ያገኛል። ያ ኩባንያ ዘንድሮ ጥሩ ገቢ አግኝቶ ከሆነ ‘ኤ’ ማግኘት ስንት መቶኛ ጭማሪ ያስገኛል፣ ቢ፣ ሲ፣ዲ ማግኘትስ ምን ያህል ነው የሚለው ማኔጅመንቱ ይወስናል።

 

የሚሰጠው የገንዘብ የደመወዝ ጭማሪውም ሁለት ዓይነት መልክ አለው። የማኔጅመንት አባል የሆነ እና ያልሆነ እኩል ጭማሪ አያገኙም። ምክንያቱም ማኔጅመንቱ ደህና ደመወዝ ስላለው ከማኔጅመንቱ ‘ኤ’ ያገኘው ሰባት ፐርሰንት ጭማሪ ቢያገኝ በተመሳሳይ ሁኔታ ‘ኤ’ ያገኘው የማኔጅመንት አባል ያልሆነ ሠራተኛ ምናልባት አሥር በመቶ እንዲያገኝ ሊደረግ ይችላል። ይህም ዝቅተኛ ደመወዝ ያላቸውን ለመርዳት ይጠቅማል።

 

የመስከረም ወር የት/ቤት መከፈት ጋር በተያያዘ ብዙ ወላጆች ወጪ እንደሚበዛባቸው ይታወቃል። በዚህ ጊዜ ኩባንያዎቻችን የአንድ ወር ደመወዝ ለሠራተኛው ቦነስ ሳይሆን የዓውደ ዓመት መዋያ ጉርሻ በባለሃብቱ መልካም ፈቃድ የሚሠጥ ነው። ይህም ተገቢውን የታክስ ህግ ባከበረ መልኩ የሚፈጸም ነው።

 

ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ለሠራተኞቻችን እንሰጣለን። ወንድ ልጅ ሆኖ እንኳን ሚስቱ ብትወልድ እረፍት እንሰጣለን። ለሴት ልጅ እንዲሁ። ሕፃናት መዋያ ለሴት እናት ሠራተኞቻችን አቋቁመናል። እነዚህ ነገሮች ቀጥታ በገንዘብ የማትተረጉማቸው ለሠራተኞች የሚሰጡ ማበረታቻዎች ናቸው። ሠራተኛው ተረጋግቶ፣ ደስ ብሎት እንዲሠራ ይረዳሉ።

 

ደጋግሜ እንደምለው፣ ወንበሩ፣ ጠረጴዛው፣ ተሽከርካሪው፣ ቁሳቁሱ ወዘተ… ሀርድዌር ነው። ሶፍትዌሩ ሰው ነው። ማኔጅመንት ማለት እነዚህን ሁለቱን ሀብቶች (ሪሶርስስ) ነው አንድ ላይ አጣምሮ ውጤት እንዲያመጡ የሚያደርግ ነው። በሁለቱ መካከል ያለው ማያያዣው ማኔጅመንት ነው። የማኔጅመንት ጥበብ እነዚህ ሁለቱ ነገሮች እንዲጣመሩ ያደርጋል። ይሄን ፍልስፍና ስንሰብከው፣ ስናስተምር ነው የኖርነው። ሃርድዌርና ሶፍትዌር ያለው ኮምፒውተር ያለ ኤሌክትሪክ እንደማይሠራ ሁሉ ቁሳቁስና ሰው ያለበት ኩባንያ ያለ ማኔጅመንት ሊሠራ አይችልም።

 

ማኔጅመንት ውስጥ ሰዎች መጠንቀቅ ያለባቸው አንድ ነገር አለ። መጀመር ቀላል ነው። አስጀምረህ፣ ፖሊሲ አውጥተህ፣ እንዴት እንደሚጀመር ተነጋግረህ፣ ሰዎች ቀጥረህ በሉ ሥራችህን ቀጥሉ ማለት ቀላል ነው። በጣም የሚያስቸግረው ያ ሥራ ተሠራ ወይ ብለህ ሒደቱን መከታተል ላይ ማተኮሩ ነው። ሥራ እንደአቀበት ነው። ወደላይ ስትሄድ ሊያዳግትህ ይችላል፣ በርትተህ ከተጓዝክ አቀበቱ ታሸንፋለህ። ጉራማይሌ የሆነ ዕውቀት፣ ጉራማይማሌ አስተሳሰብ ያለበት ኩባንያን ስትመራ  የአንተ የአመራር ሥራ ከፒራሚዱ ጫፍ ላይ መሆን ብቻ ሳይሆን ወደታች ጭምር እየወረድክ፣ እንደገና ወደላይ እየወጣህ መሥራት እንጂ አለቃ ወንበር ላይ ቁጭ ብለህ ልምራ ብትል አስቸጋሪ ይሆናል። እንደዚያ ልናደርግ የምንችልበት ደረጃ ላይ በሀገር ደረጃ ገና አልደረስንም። አሜሪካ ብትሄድ በየደረጃው እውቀት አለ። ሁሉም የሚሠራውን ያውቃል። ስለዚህ ሥራአስኪያጁ ወደታች መውረድ ላይኖርበት ይችላል። በሲኢኦ ደረጃ ያሉ ሰዎች ጭራሹን በቢሮ መኖራቸውም የማይታይበት ሁኔታ አለ። እዚህ ሀገር እንደዚያ ላድርግ ብትል ከላይ ተንሳፈህ ልትቀር ትችላለህ። ከላይ ወደታች ፣ከታች ወደላይ እንደ አስፈላጊነቱ መሥራት ያስፈልጋል። ይህ «Detail Minded» በሆነ መልክ የመሥራት ሂደት የማኔጅመንት ቲዎሪ ላይ ጣልቃ ገብነት ሆና ስለምትታይ ለቲዎሪ አቀንቃኞች አትመችም። ብዙ ሰዎች ይህ ሰው ሲኢኦ ነው? ጄኔራል ማኔጀር ነው? ለምንድነው ታዲያ ታች ወርዶ በማይገባው ቦታ ይሠራል በማለት ሊተቹ ይችላሉ። ያልተነካ ግልግል ያውቃል ነውና የሚሉትን መተው ነው።

 

ሰንደቅ፡- ማን እንደፈጠረው ባይታወቅም በእኛ ሀገር ማኔጀር ማለት ብዙ ጊዜ ከሠራተኛው ራሱን ነጠል አድርጎ ቢሮ ውስጥ የሚቀመጥና አመራር የሚሰጥ ተደርጎ የሚታይበት አሠራርና ልማድ አለ፣ እርስዎ ደግሞ በተቃራኒው ሠራተኞችዎን በየኮሪደሩ ሲያገኙ፣ ሲያናግሩ ይታያሉ፣ እስቲ ስለዚህ የፍልስፍና ተቃርኖ ቢያስረዱን?

ዶ/ር አረጋ፡- መጀመሪያ ማኔጀር ስትሆን የኩባንያውን የዕለት  ተዕለት ሥራ በመመሪያ መሠረት መሥራት ነው። ይህ ደግሞ የራሱ የሆነ የሥራ መዘርዘር (ዲስክሪፕሽን) አለው። ዳይሬክተርም የራሱ አለው። ጀኔራል ማኔጀሩም በሥራ መዘርዝሩ መሠረት መሥራት የሚገባው አለ። በዚህ መሠረት መሥራት ከፈለክ ታች የሚሠራው ሥራ ያለ አንተ ጣልቃ ገብነት ራሱን ችሎ የሚሄድ መሆን መቻል አለበት። ኦፕሬሽን ላይ ያለ ሰው በሚገባ እየሠራ ከሆነ የእኔ ጣልቃ ገብነት አያስፈልግም፤ የምጨምረው ነገር የለኝምና። ጥቃቅን ጉዳዮች ላይ የምገባበት ምክንያት የለኝም። ነገር ግን በመንግስት ደረጃም ቢሆን ጠ/ሚኒስትሩ ከተቻለ ታች ወርደው ሰዎች ማናገራቸው አዲስ ነገር አይደለም። ይህን ሲያደርጉ እንመለከታለን። ትንሽዬ ምሳሌ ልስጥህ። ኤምቢአይ የቀለም ፋብሪካችን በቅርቡ የቃጠሎ አደጋ ደረሰበት። በዚህ ምክንያት ምርቱ ቆመ። እኔ ሲኢኦ ነኝ፣ እዚሁ ቁጭ ብዬ የሚያስፈልገውን ነገር ንገሩኝ፤ የምትፈልጉትን አፀድቃለሁ ማለት እችላለሁ። ግን ያደረኩት ምንድነው፤ ከረባቴን አወለኩ፤ ቱታዬን ለበስኩ። በየቦታው ያሉትን ባለሙያዎቻችንን ሰበሰብኩ። ቡድን አቋቋምኩ። በአሥር ቀናት ውስጥ በቃጠሎ ጉዳት የደረሰበትን ጠግነን ወደሥራ ማስገባት ቻልን። ይህ ክስተት ዝቅ ብሎ የመሥራትን ውጤታማነት በተግባር ያሳየ ይመስለኛል። በዚያ መልክ ሥራው ባይቀናጅ ኖሮ የወራት ጊዜን በወሰደ ነበር።

ወደታች ወርደህ የሠራተኛውን ሁኔታ ማየት ሳትችል፣ ችግሩን ሳትካፈል ብትቀር አለቃችን’ኮ የእኛን ሥራ የት ያውቃል ሊልህ ይችላል። ይሄ ወደታች ወርዶ ማየት፣ መደገፍ፣ መመሪያ መስጠት፣ የተበላሹ ነገሮች ካሉ እንዲስተካከሉ ማድረግ፣ ጥሩውን ነገር ማበረታታት ለእኔ ጣልቃ ገብነት አይደለም። ፒራሚዱ ጫፍ ላይ ያሉ ሰዎች ፒራሚዱ ውስጥ ወደታች ወደ ላይ የሚወጡበት የሚወርዱበት፣ መሰላል ያስፈልጋቸዋል። የማያስፈልግ ከሆነ፣ መውጣትና መውረድ አያስፈልጋቸውም። የሚያስፈልግ ከሆነ ግን መውረድ ብቻ ሳይሆን አብረህ መሥራትም አለብህ። የቡድን ሥራ የሚባለው ለእኔ ይኸ ነው።

 

አንዳንድ ጊዜ ለማንም ሳልነግር ድንገት ተነስቼ አንዱን ኩባንያ እጎበኛለሁ። ይህ ዓይነት ጉብኝቴ ኩባንያዎቹ ያሉበትን ደረጃ እንድፈትሽ ያግዘኛል። የአሠራር ስታንዳርድ እንዳይወርድ ይረዳኛል። ዝም ብትል ግን ወርዶ፣ አሽቆልቁሉ ሊሆን ይችላል። ኢትዮጵያ ውስጥ ውጤታማ ይሆናሉ ብዬ የማስባቸው ሥራ መሪዎች በተቻላቸው መጠን በፒራሚዱ ውስጥ ሆነው ወደላይ፣ ወደታች፣ ወደጎን የመሄዱ አቅሙ ያላቸው ናቸው። ምክንያቱም ያለው ተጨባጭ ሁኔተ ይህን ዓይነት ሊደርሺፕ የሚፈልግበት ጊዜ በመሆኑ ነው። አርሶአደሮችን ተመልከት። ካላንደራቸው ከተፈጥሮ (ዝናብ፣ፀሐይ) ጋር የተያያዘ ነው። የሚሠሩትን ያውቃሉ፣ መቼ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ያውቃሉ፣ መቼ እንደሚያርሱ፣ መቼ እንደሚኮተኩቱ፣ መቼ ምርቱን እንደሚሰበስቡ፣ መቼ እንደሚወቁና ወደጎተራ እንደሚያስገቡ፣ መቼ ለገበያ እንደሚያወጡ፣ ሁሉንም ያውቃሉ። አርሶአደሮቹ የራሳቸው የሥራ ባህል አላቸው። ይኸ ባህል ወደፋብሪካ፣ ወደከተማ መምጣት አለበት። ሙስና፣ ተገቢ ያልሆነ ቢሮክራሲ የሚኖረው ይህ ዓይነት አሠራር ስላልመጣ ነው። እንደአርሶ አደሩ ሥራን በጊዜውና በትክክል መተግበር ባለመቻሉ ነው። ሥራን በጊዜው ጀምሮ በታቀደለት ጊዜ መፈጸምን ከአርሶ አደሩ መማር ያስፈልጋል። በተጨማሪ ከመርካቶም ብዙ ቁምነገር መማር ይቻላል።

 

ሰንደቅ፡-በ17 ዓመት ቆይታዎ ረክተዋል? ያስብኩትን አሳክቻለሁ ብለው ያምናሉ?

ዶ/ር አረጋ፡- በአብዛኛው ረክቻለሁ። በየዓመቱ የሚደረግ የደመወዝ ጭማሪ ለሁሉም ሠራተኛ አለ። በየዓመቱ ለራሴ የሥራ አፈፃፀም የምሰጠው “ቢ” ወይንም “ሲ ፕላስ” ነው። ምክንያቱም የማስበውና ያሳካሁት ነገር አልጣጣም ስለሚለኝ ነው። ረክቻለሁ የምላቸው ነገሮች አሉ። በተለይ ኩባንያዎቻችን ሰው ተኮር በመሆናቸው ብዙ ሰዎች የሥራ ዕድል በመከፈቱ፣ ሠራተኞቻችንም እፎይ ብለው፣ ተረጋግተው፣ ለሊቀመንበራችን ለሼህ ሙሐመድ በየሄዱበት ረጅም ዕድሜና ጤና እየተመኙ ሲሠሩ ማየት በጣም የምረካበት ትልቅ ነገር ነው። በተጨማሪም ከ90 በመቶ በላይ የሆኑ  ሠራተኞቻችን በፎቶግራፍ ሣይሆን በአካል ያውቁኛል ብዬ አምናለሁ። ይሄ ግንኙነቴ ያረካኛል። ሌላው ሰዎች ያላቸውን ችሎታቸውን አሟጠው ለሥራ እንዲያውሉ፣ ይሄ እኮ የእኔ ጉዳይ አይደለም ብለው እንዳይዘናጉ፣ የተማርኩት ይህንን አይደለም የሚል ባህርይን እንዲተው፣ ቻሌንጅ አደርጋለሁ። አንዳንድ ጊዜ በቁጣም ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ አንድ አካውንታት ከሂሳብ በስተቀር አላውቅም ማለት የለበትም። የመጀመሪያ ዲግሪ የተሰጠህ ብዙ ነገር ለመሥራት እንጂ የአካውንታት ትምህርት ስላለህ ሌላ ሥራ አትሠራም ማለት አይደለም። የሰው ልጅ ብዙ ችሎታ አለው ብዬ አስባለሁኝ። በዚህ አስተሳሰብ ሰዎችን በተለያየ ቦታ ላይ ችሎታቸውን እንዲያወጡና እንዲጠቀሙበት በማድረጌ በጣም ያረካኛል። እኔ የተማርኩት ሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ነው፣ ስፔስ ኢንጅነሪንግ ነው፣ ማኔጅመንት ነው፤ ግን ሲኢኦ ቢሮን፣ ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኩባንያን፣ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲን በተለይ እመራለሁ፣ በየኩባንዎቹ ሄጄ ስለስጋ፣ ስለእንቁላል፣ ስለቆርቆሮ ስናገር እገኛለሁ። እኔ ይህን ማድረግ ከቻልኩ ሌሎችም ይችላሉ። ሰዎች ችሎታቸውን መገደብ የለባቸውም። ራሳቸውን ቻሌንጅ ማድረግ አለባቸው ብዬ አምናለሁ።

 

 

በትዕዛዝ ጠዋት ስትገባ ፈርመህ ግባ፣ ስትወጣ ፈርመህ ውጣ በማለት ሠራተኛን ማስተዳደር ሳይሆን ሲነጋ ሠራተኛው መ/ቤቴ መሄድ አለብኝ ብሎ በፍቅር እንዲመጣ የማድረግ ሁናቴ መፍጠር ያስፈልጋል። ሠራተኞቼ ለሥራና ለኩባንያዎቻቸው ያላቸው ፍቅር እጅግ አርክቶኛል።

 

 

ሌላው ብዙ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶችን ወደአመራር ቦታ አውጥቻለሁ ብዬ አስባለሁ። አሁን ብዙ ዋና ሥራአስኪያጆች ወጣቶች ናቸው። ይሄን ማድረግ መቻሌ ያረካኛል። ቴክኖሎጂ ግሩፕ እንደስታዲየም ዓይነት ትልቅ ፕሮጀክት ወስዶ የቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች ተባብረው መሥራትና ውጤታማ እንዲሆን ማድረጋቸው በምሣሌነቱ ቆንጆ ነው ብዬ አምናለሁ። አርክቶኛልም። በኢትዮጵያናይዜሺያን ፕሮግራሜ ኢትዮጵያውያን ፈረንጆችን ተክተው መሥራት በመቻላቸው ደስተኛ ነኝ።

 

ሌላው የቴክኖሎጂ ግሩፑ ጨዋነት፣ የሀገር ሕግ ማክበር ባህል ላይ ያለን ትኩረት በሰፊው እየታወቀ መሄዱ በጣም ደስ ይለኛል።

 

 

በመጨረሻም ለአለቃዬ በመጠኑም ቢሆን የቴክኖሎጂ ግሩፕ መሀል እሴት ጨምሯል ብዬ ስለማምን  ደስ ይለኛል። ሰዎችን መርዳት ማለት ቤተሰብን መርዳት ነው፣ ቤተሰብ መርዳት ማለት ሀገርን መርዳት ነው። በዚህ ረገድ ጥሩ ሥራ ሠርተናል ብዬ አምናለሁ።

 

ሰንደቅ፡-የጎደለ ነገር ምን አለ? በሥራ አፈፃፀም ወደ “ኤ” የማያስገባዎ ነገር ምን ተገኘ?

ዶ/ር አረጋ፡- የመጀመሪያ ነገር የነበረኝ ራዕይ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ማሳካት አለመቻሌ ነው። መጀመሪያ የነበረኝ ራዕይ የሼህ ሙሐመድ በኢትዮጵያ የሚገኙ ኩባንያዎች በጠቅላላ አንድ አመራር ኖሯቸው፣ ከመንግስት ቀጥሎ በጣም ግዙፍ ሆነው ማየት ነበር። አሁን ያለው የተለያዩ ኩባንያዎች አደረጃጀት መጥፎ ነው ማለቴ አይደለም። አሁን ያለው አሠራርም ሌላኛው አማራጭ መሆኑን እገነዘባለሁ። ነገር ግን አንድ ጠንካራ የሆነ ግሩፕ ተፈጥሮ፣ ጥንካሬው በአስተማማኝ መሠረት ላይ እንዲቀመጥ፣ የሼህ ሙሐመድ ራዕይና ሌጋሲ ለአሁን ብቻ ሣይሆን ለቀጣይ ትውልዶች እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ። ለምሳሌ ከአንድ ሰው ዕድሜ በላይ በሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የተመሠረተውን ቦይንግ ኩባንያን ውሰድ። መሥራቹ ሚስተር ቦይንግ ካረፉ ብዙ ዓመታት አልፈዋል። አሁንም ግን ገናና እና ስመጥር ኩባንያ ሆኖ ቀጥሏል። በዚሁ መልክ የሼህ ሙሐመድ ሌጋሲ የዛሬ 100 እና 200 ዓመታትም የሚዘልቅ እንዲሆን ከማድረግ አኳያ ብዙ አልሠራንም ብዬ አምናለሁ።

 

ከዚህ ውጪ በጣም ደስተኛ ነኝ። በሥራ ብቻ ሣይሆን በሌሎች ማኅበራዊ ተሳትፎዎች በመንግስት አካባቢ፣ በሃይማኖት አካባቢ፣ ወዘተ የምችለውን ሁሉ ማድረግ በመቻሌ ውጤታማ አድርጎኛል ብዬ አስባለሁኝ።

 

ወደፊትም ገና እንሠራለን፣ እናድጋለን፣ ለሀገራችንም ኢኮኖሚ ዕድገት የተሻለ ነገር እናደርጋለን በሚል አሁንም የአቅማችንን እያበረከትን እንገኛለን። ይህም ሆኖ ላደርግ የምችለውንና ያለኝን ችሎታ ከሠራሁትና አሁን ከምሠራው ጋር ሳነጻጽረው ብዙ ይቀረኛል። ስለዚህም ‘ኤ’ የማገኝበትን ጊዜ እናፍቃለሁ።¾

 

ከመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል

ቤተክርስቲያን ማለት ስሙ እንደሚያመለክተው የክርስቲያን ቤት የሕዝበ ክርስቲያን መሰብሰቢያ የምዕመናን አንድነት ወይም ኅብረት ማለት እንደሆነ ከአጠራሩ የምንረዳው ሐቅ እንደሆነ ለማንም የተሠወረ አይደለም።

ከጥንት ሲያያዝ በመጣው ትውፊት መሠረት ካህኑ በክህነቱ ቀዳሽ፣ ምእመኑም በምእመንነቱ ለቅዳሴ ለውዳሴ አስፈላጊ የሆኑትን ንዋየ ቅድሳት እንደባለቤት ሁኖ እያሟላ ቤተ ክርስቲያን ስትገለገል ቆይታለች፤ አሁንም እየተገለገለች ትገኛለች፤ ለወደፊቱም እንደዚሁ።

ወደ ከተማችን አዲስ አበባ ስንመጣም ካህኑ ራሱን የሚረዳበት የገቢ ምንጭ ስለሌለው ምእመኑ የባለቤትነት  መብቱን እንደያዘ በተቻለ መጠን አሥራት በኩራቱን እያወጣ የቤተ ክርስቲያኗ አገልጋዮች ቀጥሮ እሱ እንደባለቤት ሆኖ ቤተ ክርስቲያኒቱን እያገለገለ ይገኛል።

ታድያ ከስሙ እንደምንረዳው ቤተ ክርስቲያን የሕዝብ እንጂ ልዩ ባለይዞታ /ባለቤት/ እንደሌላት እየታወቀ አንዳንድ ጸሐፍያን ነን ባዮች በተለያዩ ድረገጾች የልብ ወለድ መነባንብ ማለትም በዓለ ወልድ የማን ነው? ካቴድራሉስ? በማለት ሕዝብን ሲያደናግሩ ይስተዋላሉ።

ይሁንና ከሙዳዩ ምጽዋት የሚገኘው ገቢ የአገልጋዩን ደመወዝ ሊሸፍን ባለመቻሉ ሌላ የገቢ ምንጭ ማፈላለግ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። ከዚህ በመነሳትም የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጽ/ቤት ባለችው ከደርግ አፍ የተረፈች ይዞታ ላይ ቆርጦ ለት/ቤትና ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚውልና የሚከራይ ሁለገብ አዳራሽ ሠርቶ ከኪራይ በሚኘው ገቢ ከ 3ዐዐ በላይ ሠራተኞችን የሚያስተዳድርና እንዲሁም ካቴድራሉ አገር አቀፍ እንደመሆኑ መጠን የሀገር መሪዎችና ታዋቂ ግለቦች በሞት ሲለዩ የሚቀበሩበት በመሆኑ እና የሕዝብ ብዛት በጨመረ ቁጥርም የቀብር ቦታ ስለሚጠብ ለሕዝቡና ለሠራተኛው ጥቅም ሲባል ረጅም ዕድሜ ያላቸውን ቀብሮች (ዓጽም) ወደ ሌላ ቦታ በማሰባሰብ ፉካዎችን ገንብቶ በገቢው ሠራተኛውን የሚደጉም መሆኑ ይታወቃል።

ከቀብሩ የወጣው አጽምም በአዲስ መልክ ባሠራው ሙዝየም ሥር ባለው ቦታ እና ፉካ በክብር ተቀምጦ ይገኛል። ከነዚህም መካከል የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ዓጽም ተጠቃሽ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በበዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ አርፈው ከሚገኙት ታዋቂ ግለሰቦች መቃብር የተነሳ ቦታው በመጣበቡና በመጨናነቁ ምክንያት በበዓል ጊዜ ግቢው በሐውልትና በብረት አጥር ብዛት ስለተጨናነቀ ምዕመናን እንደልብ የአምልኮ ሥርዓታቸውን መግለፅ ከማይችሉበት ደረጃ ተደርሶ ነበር። ታቦተ ሕጉ ወጥቶ በሚዞርበት እና በሚከበርበት ወቅት ሐውልቱና የብረት አጥሩ አላንቀሳቀስ በማለቱ አጽሙ እንዳለ ሆኖ የብረት አጥሩና ሐውልቱ ተነሥቶ በቀብሩ ላይ መጠለያ እንዲሠራበት እና የእያንዳንዱ ፎቶ እና ታሪክ ዓጽሙ ካለበት ፊት ለፊት እንዲጻፍ ወይም እንዲለጠፍ ተደርጎ ሕዝቡ ለጸሎትና ለማስቀደሻ እንዲገለገልበት ለማድረግ ከሕዝብ ጋር በመመካከር እና የሕዝቡን ይሁንታ በመቀበል ሥራ የተጀመረ መሆኑ ግልፅ ነው። ቢሆንም አንዳንድ ግለሰቦች ይህን ከፍተት በመጠቀም የካቴድራሉን መልካም ገጽታ ጥላሽት ለመቀባትና ለማጥቆር እንዲሁም መልካም ዝናውን ለማደፍረስና ስም ለማጥፋት በብዙ ሲደከሙ ይታያሉ። ማጠንጠኛቸውም በበዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን ዙርያና አጥር ግቢ ከተነሣው እና በመነሳት ላይ ባለው በመቶዎች የሚቆጠር ቀብር እና ሐውልት መካከል እነሱ የሚያውቋቸውንና ለቢዝነሳቸው ማወፈርያ ዋጋ ያወጡልናል ያሏቸውን ግለቦች ስም እየጠሩ የካቴድራሉን አስተዳደር እና ሠራተኛውን ሲያብጠለጥሉ ይገኛሉ።

በእነርሱ እምነት እነርሱ የሚያውቋቸውን እና በየመጣጥፋቸው ሁሉ ስማቸውን የሚጠሯቸው  ብቻ እንጂ ሌላው ከቀብሩ የተነሳው ሰው ለሀገሩም ሆነ ለወገኑ ሥራ የሠራ አይመስላቸውም። ይሁንና ሐቁ ጠፍቷቸው ሳይሆን ለእነሱ ካልመሰላቸው ሥራ መሥራትም ሆነ ታሪክ መሥራት ስለማይዋጥላቸው ነው። ቤተ ክርስቲያን የሕዝብ ሀብት እንደመሆኗ መጠን ካቴድራሉ የሕዝቡን ችግር አይቶና ተመልክቶ ቦታውን ለሕዝብ አገልግሎት በሚመች መልኩ ለማስተካከል ሲባል የሚመለከታቸውን የቀብሩ ቤተሰቦች ዘመኑ ባፈራቸው መገናኛ ብዙሃን ተጠርተው ስለጉዳዩ ውይይት በማድረግ ሐሳባቸውን እንዲገልፁ መደረጉና በጉዳዩ ላይ ስምምነታቸውን ከገለፁ በኋላ የአጽም ማንሳቱ መርሐ ግብር እንዲከናወን መደረጉ ጥፋቱ እና ስህተቱ የት ላይ ነው?

ጉዳዩ ወዲህ ነው። ሕዝብና ሕዝብ ሲያጋጭና ሲያተራመስ እጃቸው የሚሞላላቸው የሕዝብ እና የቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪ ነን ባዮች፤ ምእመናኑ በካቴድራሉ ልማት እና ለቤተ ክርስቲያኑ የሚደረገውን እንቅስቃሴ አይቶና ተገንዝቦ የአጽም ማንሳቱን ሥራ ደግፎ መርሐ ግብሩ በሠላም እንዲከናወን ፈቃደኛ ከመሆኑም ባሻገር ለሚደረገው የካቴድራሉ ልማትና የማስፋፊያ መርሐ ግብር ልዩ ልዩ አስተዋጽኦ በማድረጉ አልተደሰቱም። በዚህም ምክንያት የካቴድራሉ ሕግና ሥርዓትን የተከተለ አሠራር ውስጣቸውን ስላቃጠላቸውና ስለከነከናቸው በሕልምም ሆነ በገሀድ የሚመኙትና የሚፈልጉት የሕዝብ ትርምስ ባለመከሰቱ አዛኝ እና ተቆርቋሪ በመምሰል ለቢዝነሳቸው ማሳኪያ እና ማበልፀጊያ ሲሉ የሙታኑ ቤተሰቦች እንዲቀርቡ ወይንም እንዲመጡ አዋጅ መነገር አልተሰራበትም እያሉ የቤተ ክርስቲያን ቀኖና አዋቂ ለመምሰል እያማሰኑ ነው።

ስለቀኝ ጌታ ዮፍታሔ አጽም ፍልሰት ጉዳይ፣

የበዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊና ዕድሜ ጠገብ እንደመሆኑ መጠን ጫካ ስለዋጠውና ማንኛውም የበዓለ ወልድ ተስፈኛ የኔቢጤ ሁሉ እንደመጸዳጃ ቤት የሚጠቀምበት ሁኔታ እያየለ በመምጣቱ ችግሩን መቅረፍ የግድ ብሏል። ችግሩን ለመቅረፍም ዕድሜ ጠገብ የሆኑ አጽሞችን ማፍለስ ወይንም ባሉበት ሐውልታቸው እንዲነሳ ማድረግ ተገቢነቱ ታመነበት። ከነዚህ መካነመቃብሮች መካከል አንዱ የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ መቃብር ሲሆን ከዛሬ 8 ዓመት በፊት ዓጽሙን በክብር አንስቶ አዲስ ባሠራው ሙዝየም ውስጥ በክብር አሳርፎት ነበር። አሁን ቤተሰቦቻቸው ከ8 ዓመታት ቆይታ በኋላ በክብር ከተቀመጠበት ሙዝየም አንስተው ሲወስዱ የካቴድራሉን ካህናትና አስተዳደር እያነሱ ማራገብና የስም ማጥፋት ዘመቻ መክፈት ለፖለቲካ ፍጆታ የሚያገለግል መስሏቸው ካልሆነ በቀር እነቆርጦ ቀጥል የሚጽፉት መነባንብ የታሪክም ሆነ የእምነት መሠረት ያለው አይደለም።

ሲጀመር የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ዓጽም ከነበረበት ቦታ በክብር ተነሥቶ ለ8 ዓመታት ያህል ሙዝየም ቤት ሥር በክብር ተቀምጦ ነበር እንጂ እነራስ ገዝ እንደሚሉት አልባሌ ቦታ ላይ አልነበረም፣ አልተቀመጠም። የካቴድራሉ ካህናትም አባቶቻቸውንና የሀገር ባለውለታዎችን ጠንቅቀው የሚያውቁና የሚያከበሩ በመሆናቸው ዓጽማቸውን ለ8 ዓመታት ያህል በክብር በሙዝየም ውስጥ እንዲቀመጥ ማድረጋቸው ሊያስመሰግናቸው እንጂ ሊያስወቅሳቸው አይገባም ነበር።

በመሆኑም ካቴድራሉ የአባቶችንና የሀገር ባለውለታዎችን ክብር አሳምሮ የሚገነዘብ ስለሆነ መምህር ሳይኖራቸውና ከመምህራን ሥር ቁጭ ብለው ሳይማሩ መምህር ነን ከሚሉ የደጀ ሰላም ቀበኞች የሚወሰደው ግንዛቤ እና ትምህርት አይኖርም።

የመልአከ ብርሃን አድማሱ ዓጽመ ፍልሰት በተመለከተ፣

እነቆርጦ ቀጥል እንደሚሉት ወደ የመን ወይም ወደሮም እንዲሄዱ ሳይሆን በዓጽማቸው ላይ ተጭኖ  የነበረውን የድንጋይ ክምር እና የብረት አጥር ብቻ ተነሥቶ ዓጽሙ ያለበት ቦታ ለሕዝበ ክርስቲያኑ መጸለያ እና ማስቀደሻ እንዲሆን ከማመቻቸት በቀር አስከሬኑ አልተነሳም፤ ከቦታውም አልወጣም፤ ዓጽሙም በነበረበት ቦታ ላይ እንደ ተቀመጠ ይገኛል።

ከዚህ ጽሑፍ ላይ ጎልቶ የሚታየው ነጥብ አጥንትንና ጉልጥምትን በተመለከተ እና እንዲሁም የጎጥና የተራራዎች ጉዳይ የሚመለከት ነው። ይህም የሚያሳየው ካጥንታቸውና ከጉልጥምታቸው ውስጥ የተዋሐደው ጠባብ አመለካከት የሚያንፀባርቅ እንጂ የካቴድራሉን ስህተት አያመለክትም። ምክንያቱም ካቴድራሉ እነርሱ እንደሚሉት የቀብሩን ምንነት በመለየት ሳይሆን በበዓለ ወልድ ውስጥ ቦታውን አጣቦ የሚገኘውን ቀብር ሁሉ ዓፅሙን /አስከሬኑን/ ሳይነካ እንዳለ ከመሬት በመተው ከቅጥር ግቢ ውስጥ ከሚገኙ መቃብራት ላይ የነበረውን የብረት አጥር እና የዕብነ በረድ ክምር ብቻ እንዲነሳ ሲያደረግ ከ6ዐ በላይ ቁጥር ያለው ቀብር ሲሆን የሰው እኩልነትና አንድነት የማይዋጥላቸው በሕዝብ ስም የሚነግዱ የቢዝነስ እና የእምነት ኮንትሮባንዲስቶች ከግቢው ከተነሱት አያሌ የሀገርና የቤተ ክርስቲያኗ ባለውለታዎች መካከል ስለአንድና ሁለት ሰዎች ቀብር ብቻ ሲጮሁ ስለሚደመጡ ነው።

ይህም ከምን የተነሳ እንደሆነ የሕዝበ ክርስቲያኑ አስተዋይ አእምሮና ትክክለኛ ሚዛን የሚስተው አይሆንም። በእውነት ስለ ታሪክ እና ስለ ሕዝብ የሚቆረቆሩ ቢሆን ኖሮ ለምን ስለነ ቀኛዝማች መንገሻ እና ሌሎች ታዋቂ የሀገር ባለውለታዎች አይጽፉም ነበር። ዳሩ ግን የእነሱ ተልዕኮ አንድና አንድ ብቻ በመሆኑ የሞኝ ልቅሶ ሆነና ስለ ሀገር፣ስለ ሥነ ጥበብ፣ ስለ ታሪክ ወዘተ የተቆረቆሩ እና የተጨነቁ በመምሰል ቢዝነሳቸውን በምን መልኩ እንደሚያካብቱ በማሰብና በማሰላሰል ብቻ የሕዝቡን ቀልብ ለመሳብ የሚያደርጉት የብልጣብልጥነት ዘዴና ስልት ለመጠቀም ታስቦ የሚቀርብ ልብ ወለድ ነው።

አሁን በተያዘው ጉዳይ ርዕሳችን አይደለም እንጂ የእኛው የአራት ኪሎ ሐራዎች ሊቅ የጸጋ ዘአብና የእግዚእ ኃረያ ልጅ ስለሆኑት አቡነ ተክለ ሃይማኖት የልደት ቦታም ሊያስተምሩን እየዳዳቸው ነው። ይሁን እና የሕዝበ ክርስቲያኑ ተስፋ ስለ ጻድቁ ጸሎትና ምልጃ በተመለከተ እንጂ ስለሀገራቸው የሚገደው ነገር ስለሌለ ይህ ጉዳይ አያከራክረንም። የሚያስገርመው ግን እያስመሰሉ መናገር የአዋቂነት ምልክት የሚመስላቸው ቆርጦ ቀጥሎች ምንም እንኳ የቤተ ክህነት ተወካዮች በፍለጋው የተሳተፉ ቢሆኑም የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ አጽም ከተቀበረበት ሲወጣ ፈላጊና አፈላላጊ የነበሩት የሥጋ ዘመዶቻቸው ጭምር መሆናቸው እየታወቀ እንዳልነበሩ ተደርጎ የተፃፈው የማጣቀሻ ጽሑፍ ምናልባት የየዋሆችን እና ከ 2ሺ ዓ.ም ወዲህ ለተወለዱ ሕፃናት ማታለያ ካልሆነ በቀር በወቅቱ ለነበርነው እና ሁኔታውን በቅርብ ሁነው ሲከታተሉ ለነበሩ ግን ከትዝብት በቀር የሚያተርፈው ቁም ነገር አይኖርም።

ሲጠቃለልም ቤተ ክርስቲያን የሕዝቡ የሥርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ እንደ መሆኗ መጠን ለሕዝቡ አገልግሎት ምቹ ለማድረግ እንጂ የግሉን ቤት የሠራበት አካል የለም። በመሆኑም በዓለ ወልድ የማን ነው? የሚያሰኝ ተግባር አልተፈጸመበትም፤ መልሱም የሕዝቡ ሊሆን ይገባል። ሊቀ ሥልጣናቱም ቢሆኑ ቀብሩ እንዲነሳ ሲሉ ሕዝቡን ያነጋገሩት ለሕዝብ አገልግሎት የሚውል የሕዝብ መጠለያ ለማሠራት እንጂ ተልባ ሊዘሩበት አልነበረም።

አስተያየት ጸሐፊዎችም ቢሆኑ ስለ ቤተ ክርስቲያኗ ሥርዓት እና ታሪክ ተቆርቁረው ሳይሆን ሕዝቡ ከካቴድራሉ አስተዳደር ጋር ለምን ተስማምቶ ዓጽሙ እንዲነሳ ፈቀደ ለምንስ ትርምስ አልተፈጠረም በማለት የባሕር ማዶ ተስፈኞች የሚዘምሩትን መዝሙር ለማድመቅ እንጂ ስለ መልአከ ብርሃን አድማሱ ቀብር በመቆርቆር የሚቀርብ ተቃውሞ አይደለም። ስለሆነም እንኳን ክህነት እምነት ሳይኖራቸው በመምሰል በቤተ ክርስቲያን አባቶች እና በቤተ ክህነት ሠራተኞች ላይ ዓይናቸውን ተክለው ባለማቋረጥ አተኩረው የሚመለከቱ የብፁዓን አባቶች ቀንደኛ ጠላቶች እስከመቼ ድረስ የዘለፋ ብዕራቸውን ቀስረው በቤተ ክርስቲያን ላይ እንዳሾሉ ይኖራሉ የሚለውን ጥያቄ የሁሉም የቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪ ሊሆን ይገባል። ምንም እንኳ የቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት የሚፈቀደው ባይሆንም እንደነዚህ ያሉትን በቤተ ክርስቲያንና በመሪዎቿ ላይ ለሚነግዱ ኢሎፍላውያን ግን የቤተ ክርስቲያኗ ምሁራን ብዕራቸውን ሊያነሱ ይገባል እንላለን።

“ስለ አባታችን የተሰጠው ማብራሪያ የተሳሳተ ነው”

 

ሳምንታዊው የሰንደቅ ጋዜጣ ረቡዕ ሐምሌ 5 ቀን 2009 ዓ.ም ባወጣው ጽሑፍ “በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ አጽሞች እንዲፈልሱ የተደረገው የመቃብር ሥፍራው ሞልቶ በመጨናነቁ ነው” በሚል ርዕስ በመጀመሪያ ገጹ አጠር ያለ ማብራሪያ ሰጥቷል። ማብራሪያቸውን የሰጡት ሊቀ ሥልጣናት አባ ገብረ ሥላሴ በላይ የቅድስት ሥላሴ ካቴድራልና የበዓለ ወልድ አስተዳዳሪ መሆናቸውን ገልጿል።


ዘገባው ስለመላከ ብርሃ አድማሱ አጽም መፍለስ ጉዳይ ሲያወሳ እንዲህ ይላል።


“የመላከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬን አጽም ለማንሳት ወንድማቸው መጥተው የነበረ ሲሆን በአቅም ማነስ ምክንያት ማንሳት እንደማይችሉ በመግለጣቸው ካቴድራሉ ሀውልቱን በማንሳት አጽሙ ባለበት እንዲቆይና ስምና ታሪካቸው በግድግዳ ላይ እንዲጻፍ ወስኖ ነበር ብለዋል። ሆኖም በአሁኑ ወቅት የልጃቸው ባል የሆነ ግለሰብ በመምጣቱ ሌላ ቦታ ሰጥተን አጽሙ ለማፍለስና ለማሳረፍ እየተዘጋጀን ነው ብለዋል” በማለት አጠቃሎታል።


ይህ ቃል የእርስዎ የክቡር ሊቀ ሥልጣናት አባ ገብረ ሥላሴ ቃል መሆኑ ነው።

 

ክቡር አባታችን
ይህ ቃል በእውነት የእርስዎ ከሆነ፣ ከድፍረት አይቆጠርብኝና ፍፁም ስህተት መሆኑን ላረጋግጥልዎ እወዳለሁ። ከመልአከ ብርሃን አድማሱ ቤተሰቦች በዚህ ሁኔታ ከእርስዎ ዘንድ የቀረበ የለም። መልአከ ብርሃን አድማሱ ወንድምም፣ የልጅ ባልም የላቸውም።


በሕይወት ያለን ልጆቻቸው፡-
- ወ/ሮ በላይነሽ አድማሱ
- ኮ/ሸዋዬ አድማሱ
- አቶ ምህርካ አድማሱ
ስንሆን የቀሩት ልጆቻቸው፣ በሞት ቢለዩም የልጅ ልጆች አሉ። ሌላ በቤተሰብነት የምናውቀው የለም።


ምናልባት እርስዎ የጠቀሱአቸው ሰዎች የመልአከ ብርሃን ሀውልት ፈርሶ፣ ፎቶ ግራፋቸው ሜዳ ላይ ወድቆ በማየታቸው ተቆርቋሪ በመሆን እርስዎን ለማነጋገር የፈጠሩት ዘዴ ሊሆን የሚችል ይመስለኛል።

 

ክቡር አባታችን
ስለ መልአከ ብርሃን አድማሱ አጽም ፍልሰት ልጆቻቸው የወሰድነውን እርምጃ እርስዎ ቢረሱትም ዘርዝሬ ልግለጠው። ቀኑን በትክክል ባላስታውሰውም በዚህ ዓመት በታህሳስ ወር ላይ ይመስለኛል፤ ካቴድራሉ በባዕለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን ቅጽር ግቢ ውስጥ ያሉ የሙታን መቃብሮች እንደሚነሱ ማስታወቂያ ሲያወጣ፣ ቁጥር አንድ የመልአከ ብርሃን አድማሱ ስም ነበር።


ማስታወቂያው ስለሁኔታው ለመወያየት ቀን ወስኖ የቤተሰብ ጥሪ ያቀረበ ቢሆንም እኛ ማስታወቂያውን ዘግይተን በማየታችን በስብሰባው አልተገኘንም።


ከስብሰባው ቀን በኋላ እኔ በግል ወደ ኮሚቴው ጽ/ቤት ሄጄ አንድ ሰው የኮሚቴው አባል የሆኑ ይመስሉኛል አግኝቼ ጉዳዩን በዝርዝር ገለጡልኝ።


ያሉኝን ቃል በቃል ባላስታውሰውም የካቴድራሉ ሀውልቶች እንዲነሱ የተወሰነበት ምክንያት የባዕለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን ግቢ በመጥበቡ ምክንያት ምዕመናን መጠጊያና ማረፊያ አጥተው ስለተቸገሩ ሀውልቶች ፈርሰው ዙሪያውን ማረፊያና መጠለያ ለመሥራት ነው። ስለ ሙታኑ ቅሬተ አጽም አያያዝ ካቴድራሉ ለቤተሰብ አማራጭ ሰጥቷል። ይኸውም፡-


1. የፈለገ አጽሙን አውጥቶ ወደ ፈለገበት እንዲወስድ፣
2. ብር 23 ሺ በመክፈል አጽሙን በፉካ ማስቀመጥ፣
3. አጽሙ ሲወጣ ሀውልቱ ፈርሶ መቃብሩ ሊሾ ተደርጎ በግድግዳ ላይ የሟች ፎቶና ስም እንዲጻፍ የሚሉ ናቸው።


በእለቱ ስብሰባ የተገኙ ቤተሰቦች አብዛኛዎቹ በምርጫው ተስማምተዋል። ሆኖም ብዙ ሰው ስላልተገኘ ሌላ ስብሰባ ይደረጋል አሉኝ። ከዚያም እኔ የማን ቤተሰብ መሆኔን ጠይቀው ስልኬን መዝግበው ተለያየን።


ከዚህ በኋላ ሁኔታውን ስንከታተል የሀውልቶች መፍረስ እንደማይቀር ተረዳን። እኛም አባታችን ሕይወታቸውን በሙሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እምነት ላይ በልዩ ልዩ መልኩ ከተነሱ መናፍቃን ጋር ባደረጉት ተጋድሎ ቤተ ክህነት የተለየ መታሰቢያ ማድረግ ሲገባት እንዴት ቤተሰብ ያሰራላቸው ሀውልት ይፈርሳል ብለን ቅሬታችንን ለሚመለከታቸው ለማቅረብ ጥረት ማድረግ ጀመርን።


በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳለን ታናሽ ወንድሜ በሆነ አጋጣሚ ብፁዕ አቡነ ማትያስ በካናዳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስን ያገኛቸዋል። እሱም በአጋጣሚው ተጠቅሞ የአባታችን ሀውልት ሊፈርስ መሆኑን ይገልጥላቸዋል። እሳቸውም በሁኔታው አዝነው እርስዎን በስልክ ካነጋገሩ በኋላ ብፁዕ አባታችን ለሊቀ ሥልጣናት ገልጬላቸው እርስዎ ጠይቀውኝ እንዴት አይሆንም እላለሁ። ልጆቻቸው ማመልከቻ ጽፈው ይምጡ ብለዋልና ጽፋችሁ ሂዱ በማለት ለወንድሜ ነገሩት።


ወንድሜም ይህንኑ ለእኔ ገልጦልኝ ሳንውል ሳናድር፣ በስምዎ ማመልከቻ ጽፈን ከቢሮዎ ድረስ መጥተን በእጅዎ ሰጠንዎ። የማመልከቻው ፍሬ ነገር የአባታችንን ማንነት በመጠኑ የሚገልጥና ሀውልቱ ባለበት ይቆይልን የሚል ነበር።
እርስዎም ማመልከቻችንን ተቀብለው ካነበቡት በኋላ እኛን ምንም ሳያነጋግሩን፣ በማመልከቻውም ላይ ምልክት ሳያደርጉ አንድ ቢሮ ቁጥር ጠቅሰው ወስደን እንድንሰጥ ማመልከቻችንን መለሱልን።


ወደተገለጠልን ቢሮ ስንሄድ በቢሮው ውስጥ አራት ሰዎች አግኝተን ማመልከቻችንን ሰጠን። በጽሁፍ ካሰፈርነው በተጨማሪ ስለአባታችን ማንነት ለኮሚቴው በሰፊው ለማስረዳት ሞከርን። ክርክር ነበር ማለትም ይቻላል። ሆኖም ኮሚቴው “የሀውልቱ መፍረስ የማይቀር ነው። ባለፈው ጊዜ ከተነገራችሁ ምርጫ ውጭ ምንም ማድረግ አይቻልም። ለእናንተ አንድ ተጨማሪ ምርጫ እንሰጣችኋለን። ይኸውም የምትችሉ ከሆነ ከካቴድራሉ ውስጥ ቦታ ሰጥተናችሁ አጽማቸውን አውጥታችሁ መቅበር ትችላላችሀ” ሲሉ ውሳኔአቸውን ገለጡልን፣ እኛም ከዚህ ኮሚቴ በላይ አቤት የሚባልበት እንዳለ ስንጠይቅ ወሳኞቹ እኛው ነን አሉን። የበኩላችንን ቅሬታ ገልጠንላቸው ተለያየን።

 

ክቡር አባታችን
ከካቴድራሉ ጋር እኛ ልጆቻቸው የነበረን ግንኙነት እስከዚህ የደረሰ መሆኑ እየታወቀ እንደሌለን ሆኖ መነገሩ ምንዋ አባታችን አሰኝቶናል።


ወደ ፍሬ ነገሩ ልመለስ። ኮሚቴው ከእኛ በላይ ወሳኝ የለም ብሎ ቢያሰናብተንም፤ ይህን ጉዳዩ ለብፁዕ ፓትርያርኩ ማሳወቅ አለብን ብለን አጠር ያለ ማመልከቻ አዘጋጅተን ለብፁዕነታቸው ያደርስልናል ብለን ላሰብነው ሰው ሰጥተን ውጤቱን መጠባበቅ ጀመርን። ሆኖም የሰጠነው ሰው የውሃ ሽታ ሆነብን። አቤቱታችንም በዚሁ ቆመ።


አባታችን ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ሐምሌ 24 ቀን 1962 ዓ.ም ነው። ጸሎተ ፍትሐቱና የቀብራቸው ሥነ ሥርዓት በወቅቱ በነበሩት ፓትርያርክ በብፀዕ አቡነ ቴዎፍሎስ አመራር ሰጭነት ነበር የተፈጸመው። የመቃብሩንም ቦታ ራሳቸው አቡነ ቴዎፍሎስ ነበሩ የመረጡት፤ ቀብራቸው ሲፈጸም ጰጳሳቱ ሳይቀሩ እንባቸውን እያፈሰሱ ነበር የተሰናበቷቸው።


ለአባታችን መጻሕፍቶቻቸው ቋሚ መታሰቢያዎቻቸው ቢሆኑም አስክሬናቸው የት እንደደረሰ ለማሳወቅ ቤተሰብ ሀውልት አሰርቶ፣ መልካቸው እየታዬ፣ ማንነታቸው እየተነበበ እስከ አሁን ቆይቷል።


ጊዜ የማያመጣው ነገረ የለምና አሁን ሀውልታቸው ይፍረስ፣ አጽማቸው ይፍለስ ተባለ። ከላይ እንደጠቀስነው ካቴድራሉ ከሰጠን አራት አማራጮች አንዱን መምረጥ ግዴታ ሆነ። እንደምኞታችን ለ47 ዓመታት ተከብሮ የኖረው አጽማቸው፣ ሲረገጥ ከምናይ፣ ሌላ ቦታ ወስደን በክብር ብናሳርፈው ደስ ባለን ነበር። ሆኖም አቅማችን ስለማይፈቅድ አጽማቸው ሳይወጣ ሊሾ እንዲደረግ በሚል ምርጫ እህትና ወንድሜን ወክዬ ከሌሎች ላለመለየት በ17/9/09 ዓ.ም ካቴድራሉ ባዘጋጀው ውል ላይ ፈረምኩ። ሀውልታቸውም ወዲያው ፈረሰ።


ይህን ጽሑፍ የሚያነብ ለምን እርዳታ አልጠየቃችሁም ሊል ይችላል። በእርግጥም ይህን ችግር ለሕዝብ ብንገልጽ በመቶ ሳይሆን በሺህ የሚቆጠር ወገኖቻችን ሊረዱን እንደሚችሉ አንጠራጠርም። ሆኖም ሕዝብ ላለማስቸገር ብለን ተውነው። አሁን ሀውልቱ ፈርሶ ፎቶግራፋቸው ወድቆ ያዩ ሰዎች በተቆርቋሪነት እየተነሱ እኛን “ይህ እንዲሆን ለምን ፈቀዳችሁ?” እያሉ እየወቀሱን ነው። በተለያዩ መልኩም የሀውልታቸው መፍረስ መወያያ እየሆነ ነው።

ክብር አባታችን ሊቀ ሥልጣናት አባ ገብረ ሥላሴ


ለሰንደቅ ጋዜጣ ሌላ ቦታ ሰጥተን አጽሙን ለማፍለስ እየተዘጋጀን ነው ያሉት እርግጥ ሆኖ በካቴድራሉ አስተባባሪነት የሚፈጸም ከሆነ ልጆቻቸው ደስተኞች ነን። ፈቃደኝነታችንንም እህትና ወንድሜን ወክዬ በዚህ ጽሑፍ አረጋግጣለሁ።


ልጃቸው
ኮ/ሸዋዬ አድማሱ

 

 

የባህርዳር ከተማ ትልቅ የውበት ምንጭ እንደሆነ የሚነገርለት የጣና ሐይቅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመጤ አረም መወረር አስደንጋጭና አሳሳቢ መሆኑ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በመነገር ላይ ይገኛል። አረሙን መስፋፋት ተከትሎ በሐይቁ ላይ ከተከሰቱና ይከሰታሉ ከሚባሉ ችግሮች መካከል የዓሳ ምርትን መቀነሱ፣ ውሃ በሞተር ለመሳብ አዳጋች መሆኑ፣ በቀጣይም የውሃ ትራንስፖርት አገልግሎትን ሊያስተጓጉል ይችላል ተብሎ መገመቱ ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ።


ጣና ሐይቅ የሚገኘውና የሚካለለው በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር፣ በደቡብ ጎንደር እና በምዕራብ ጎጃም አስተዳደር ዞኖች በዘጠኝ ወረዳዎች የሚያካልለው የጣና ሐይቅ በ1ሺ785 ሜትር ከባህር ወለል በላይ ከፍታና 3ሺ156 ስኩዌር ካሬ ሜትር የሚደርስ ስፋት አለው።


የሐይቁ ስርዓተ ምህዳር በርካታ የውሀ ዕፅዋቶችና እንስሳቶች በውስጡ የያዘ፣ በዙሪያው የተፈጥሮ ደኖች የቡና ተክል፣ የደንገልና የሳር ዝርያዎች ያሉበት ነው። ሐይቁ ከ300 በላይ የአዕዋፍትና እስከ 28 የሚደርሱ የዓሳ ዝርያዎች የሚገኙበት ሲሆን ለበርካታ የብዝሃ ህይወት ክምችትና ታሪካዊ ቅርሶች መገኛምሥፍራ ነው።


ጣና ሐይቅ ለአካባቢው ማህበረሰብና ለሀገሪቱ ለባህር ትራንስፖርት፣ ለዓሳ ልማት፣ ለመስኖ ልማት፣ ለሀይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ፣ ለአሽዋ ማምረቻ፣ ለቱሪዝም አገልግሎት ይሰጣል። በተጨማሪም ለቱሪስቱ መስህብ የሆኑ አቢያተ-ክርስቲያናትና ገዳማትን በውስጡ መያዙ፣ ለአካባቢው ማህበረሰብ ለአማራጭ የገቢ ምንጭ ማሰገኘቱ ከሚሰጣቸው ጥቅሞች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።


 በአካባቢው ባሉ ታሪካዊ ስፍራዎችና  ገዳማት አማካኝነት የዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻ የሆነው ይኸው ሐይቅ ገባር ወንዞቹን ጨምሮ ለሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ፣ ለመስኖ እርሻ፣ ለዓሳ ሃብት ልማትና መጓጓዣ በማገልገል ላይ ይገኛል።
ጣና ሐይቅ ከባህርዳር እስከ ጎርጎራ የሚደርስ የባህር ትራንስፖርት ያለው ሲሆን ለአካባቢው ማህበረሰብና ለቱሪስቶች ሰፊ አገልግሎት ለመስጠት ወደ 12 ወደቦች፣ የጀልባና የመርከብ መናፈሻ ቦታዎች ይገኙበታል። 

ስለመጤ አረሙ ጉዳይ
የጣና ሐይቅ ባለፉት ዓመታት ከግብርና ልማትና ከከተሞች መስፋፋት ጋር በተያያዘ የተለያዩ ችግሮች ተጋርጠውበታል። በሐይቁ ውስጥ የሚገኙ ነባር ዕፅዋቶች መመናመን፣ የዓሳና የአዕዋፍ መራቢያ ቦታ በደለል መሞላት፣ በበጋ ወራት የወንዞች መድረቅ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ጣና ሐይቅ የሚገባውን የውሃ መጠን እየቀነሰው ይገኛል።


የክልሉ መንግስት በጥቅምት ወር 2004 ዓ.ም ባካሄደው ጥናት የዎተር ሐይሰንት መጤ አረም ወይም በአካባቢው አጠራር “እምቦጭ” ወይም “አፈሻፈሸ” አረም በጣና ሐይቅ ላይ መከሰቱን አረጋግጦአል። ይህን ተከትሎ ባለፉት አምስት ዓመታት በውሀው ላይ በዓይን የሚታዩ አሉታዊ ተፅኖዎች ተከስተዋል። ከተከሰቱት ችግሮች መካከል የዓሳ ሀብትን ለማምረት የዓሳ መረብ መጣል አለመቻል፤ የሐይቁ ውሃ ጥራት መጓደል፤ የማሳ እርሻ እርጥበት ማጣት፤ በሞተር ዉሃ መሳብ አለመቻል በዋናነት ይጠቀሳሉ። ዎተር ሀይሰንት የተባለው ይኸው የአረም ዝርያ በውሀ ላይ በመንሳፈፍ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ፣ በፍጥነት በመራባት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰፊ የውሀ አካላትን መሸፈን የሚችል  ቋሚ ዕፅዋት ነው። አረሙ በክልሉ ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ ከአሁን በፊት ታይቶ ስለማይታወቅና የአረሙ መገኛ ወይም መፈጠሪያ በሌላ ሀገር በመሆኑ መጤ ከሚባሉት የአረም ዕፅዋት ዝርያዎች ይመደባል።


ይህ መጤ የአረም ዝርያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተው በደቡብ አሜሪካ አገራት ሲሆን በተከታታይ በሰሜን አሜሪካ፤ በአውስትራሊያ፤ በአፍሪካ፤ በኒውዝላንድ እና በህንድ አገር በስፋት የሚገኝ አደገኛ አረም መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

 

የአረሙ ስርጭትና ያለበት ሁኔታ፤


 መጤ አረሙ በአካባቢው የሚገኘውን ሐይቅና ሌሎች የውሃ አካላትን፤ ውሃ አዘል መሬቶችን በፍጥነት የመውረርና አካባቢውን በአጭር ጊዜ ውስጥ በስፋት የመሸፈን አቅም ያለው ነው።
መጤ አረሙ በሰሜኑ የጣና ሐይቅ ዳርቻ ከርብ ወንዝ እስከ ጎርጎራ በከፍተኛ ደረጃ ተስፋፍቶ የሚገኝ ሲሆን ስርጭቱ በሁለት መስተዳድር ዞኖች (ደቡብ ጎንደርና ሰሜን ጎንደር) በሶስት ወረዳዎች (ሊቦ ከምከም፤ ጎንደር ዙሪያና ደንቢያ) በስምንት ቀበሌዎች (ማለትም ካብ፤ አግድ ቅርኝ፤ ሞፈርሃ፤ ጣና ወይና፤ አቦ ጣና ወይና፤ አድስጌ ድንጌ፤ አቸራ)  ይገኛል። ከነዚህ ቦታዎች በከፍተኛ ደረጃ ተስፋፍቶ የሚገኘው በሁለቱ ወረዳዎች ጎንደር ዙሪያና ደንቢያ፤ በአራት ቀበሌዎች ሞፈርሃ፣ ዳንጉሬ፤ አቦጣና፣ አቸራ፣መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።


የአረሙ ባህርይ በውሃና በእርጥበት መሬት ላይ ስሮች በመንሳፈፍ በዘርና ያለዘር /በአገዳው ቅጠል/ በፍጥነት በመራባት ተወዳዳሪ ያልተገኘለት አደገኛ (invasive) አረም ነው።


አረሙ ከየትና እንዴት ወደኢትዮጵያ እንደገባ በግልጽ የሚታወቅ መረጃ ባይኖርም ለመጀመሪያ ጊዜ በአማራ ክልል በእርሻ ማሳዎች ላይ መታየት የጀመረው በ2003 ዓ.ም እንደነበር ቀስ በቀስ እየተስፋፋ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኃላ ወደ ጣና ሐይቅና ውሃ አዘል መሬቶች በፍጥነት መስፋፋት መጀመሩ ታውቋል።


የአረሙ ባህርይና ዓይነትን በተመለከተ ከአማራ ክልል የአካባቢ ጥበቃ መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ ያገኘነው መረጃ እንደሚከተለው ይዘረዝረዋል። ቅጠሉ ሰፋፊና (ከ10 እስከ 20 ሴ.ሜ ስፋት ያለው) ከውሀው ላይ መንሳፈፍ የሚችል፣ ዕፅዋቱ ረጃጅም ስፖንጅ የሆነ አገዳ ያሉት፣ በሁለት ሳምንት እጥፍ ሆኖ የመራባት አቅምና ፈጣን ዕድገት ያለው፣ ዘሩ ለ30 ዓመታት የመቆየትና የመራባት አቅም ያለው፣ በስሩ፤ በአገዳውና በዘሩ መራባት የሚችል፣ የዕፅዋቱ ዕድገት ከውሀው ወለል እስከ አንድ ሜትር ከፍታ በላይና ወደ ውሃው ውስጥ እስከ ሁለት ሜትር ጥልቀት ማደግ የሚችል፣ የዕፅዋቱ ስር ጥቁር ቀለም ያለው፣    አበባው ወይን ጠጅ ውብና የሰውን ልጅ መሳብ የሚችል፣ አንድ አረም በሕይወት ዘመኑ እስከ 6 ሺ ሄክታር የውሃ አካልና ውሃ አዘል መሬቶችን መሸፈን የሚችል፣ በአንድ ካሬ ሜትር እስከ 50 ኪ.ግ. የመመዘን ክብደት ያለው ነው።

አረሙ የሚያስከትለው ጉዳት፤


 አረሙ በወረርሽኝ መልክ በአጭር ጊዜ ውስጥ የመራባት አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑ በመጤ አረሙ የተሸፈነ አካባቢ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስርዓተ ምህዳሩ በመናጋት ለተፈጥሮና ለሰው ልጅ የሚሰጠው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ሊቀንስ ወይም ሙሉ በሙሉ ሊቆም እንደሚችል መረጃው ይጠቁማል። ከሚያስከትላቸው ጉዳቶች ውስጥ የጸሀይ ብርሃን ወደ ውሀው እንዳይገባ የሚከለክል መሆኑ በዋንኛነት ይጠቀሳል። በመሆኑም በውሀ ውስጥ ያሉ ዕፅዋቶችን፣ የዓሳ ጫጩቶች ብርሃንና አየር በመከልከል በዕድገታቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያደርሳል። የውሃ ማፋሳሻዎችን በመዝጋት ወደ ሐይቁ የሚገባውን የውሀ መጠን በመቀነስ በውሀ ግድቦች፤ በሀይድሮ ኤሌክትሪክና የመጠጥ ውሃ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያደርሳል።መጤ አረሙ የውሀውን አካል በመሸፈንና ባለው ስነህይወታዊ ፈጣን ዕድገት ከሚወስደው ውሀ በተጨማሪ ለወባና ለብላህርዝያ መራቢያ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። የውሀው አካል በአረም መሸፈኑ ምክንያት በውሃ ላይ እየተካሄደ ያለው የትራንስፖርት አገልግሎቱ እንዲቆም ያደርጋል። ለዓሳ አመራረትም ተጽእኖ ያደርሳል። የአካባቢው የውሃ አዘል መሬትን በመጤ አረሙ በመሸፈን በእንስሳት ግጦሽ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያስከትል ይችላል። አረሙ ዕድገቱን ጨርሶ በሚሞትበት ጊዜ ወደ ሐይቁ በመስጠምና በመበስበስ በውስጡ ያለ ከፍተኛ ንጥረ ነገርና መርዛማ ኬሚካሎችን ወደ ውሃው አካላት በመልቀቅ ውሃውን ለብክለት ይዳርጋል።


አንዳንድ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት “ዎተር ሀይሰንት የተባለው መጤ አረም ተንቀሳቃሸ ነው፤ቆመህበት ልትሄድበት ትችላለህ። የቅጠሉ ቁራጭ በጀልባ ወይም በሰው ወደሌላ ወንዝ ከሄደ በቀላሉ ራሱን ማባዛት አይቸግረውም። ሁለት ሜትር ጥልቀት አለው። ሥሩ ለመንሳፈፍ እንዲያመቸው ኳስ፣ ኳስ የሚያካክሉ ቅጠሎች ያፈራል” ይላሉ።


ከአረሙ ጋር በተያያዘም የጣና በለስ ሃይድሮ ፓወር ሥጋት እንደተጋረጠበት የተናገሩት አቶ መልሳቸው አረሙ ወደተርባይኑ ከገባ ከጥቅም ውጪ ሊያደርገው እንደሚችል በመጥቀስ ጉዳዩን ለኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሸን በማሳወቅ በነሱም በኩል መፍትሔ እንዲፈለግ ግንኙነት መጀመሩን ይፋ አድርገዋል።


አረሙ ጎርጎራ አካባቢ የታየው ለሌላ ጥናት በሄዱ ባለሙያዎች እንደነበር አስታውሰው በአሁኑ ወቅት አረሙ 90 ኪሎሜትር ተጉዞ ጣና ላይ በሰፊው መታየቱ አስደንጋጭ ክስተት እንደነበር አልሸሸጉም።


ምን መፍትሔ አለ?


በ2004 ዓ.ም ከክልሉ በኩል በጀት ተመድቦ አረሙ ያለበትን ደረጃ ለማወቅ የሚያስችል መሰረታዊ መረጃ የማሰባሰብ ሥራ፣ የሕዝብ ንቅናቄን ለመፍጠር የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ተከናውኖአል። በተደጋጋሚ በጀልባ በመታገዝ አረሙን በሰው ጉልበት የመንቀል ሥራ ተከናውኖ የመስፋፋት ዕድሉን ለመቀነስ ቢሞከርም የታሰበውን ያህል ለውጥ ማምጣት አልተቻለም።

 

እናም ምን ይሻላል?


በዋንኛነት የፌዴራልና የክልሉ መንግሥት በቀጣይም መንግሥታዊ ያልሆኑ ሀገራዊና ዓለምአቀፋዊ ድርጅቶች እንዲሁም ሰፊው የአማራ ክልል ሕዝብ ጣና ሐይቅን ከጥፋት የመታደግ ኃላፊነት አለባቸው። ችግሩን ለመቆጣጠር ሌሎች ሀገሮች ልምድ በመቀመር በፍጥነት እንዲተገበር አስፈላጊውን እርምጃ ሊወስዱ እና እንዲወሰድ የተቻላቸውን ግፊት ሊያደርጉ ይገባል።

ፕሬዚደንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሁለተኛ አመት የስራ ዘመን በንግግር መክፈታቸው የሚታወስ ነው። ፕሬዚዳንት በዚሁ ንግግራቸው በ2009 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራባቸውን ተግባራት ወይንም ዕቅዶች ለሕዝብ ይፋ አድርገዋል። ከእነዚህ ዕቅዶች መካከል ሕገመንግሥታዊ ማሻሻያ እስከማድረግ እርምጃን ይጠይቃል የተባለውን የምርጫ ሕግ የማሻሻል ጉዳይ በፕሬዚደንቱ መነሳቱ የብዙዎችን ትኩረት የሳበ ዓቢይ ርዕሰ ጉዳይ ነበር። ፕሬዚደንቱ እንዲህ ነበር ያሉት «ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ይበልጥ ለማጎልበትና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል በሚደረግ ድርድር የምርጫ ህጉን የማሻሻል ስራ ይከናወናል»


በሌላ በኩል በኦሮሚያና በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች በተቀሰቀሱ ሁከቶች የሰው ሕይወትና የንብረት መውደም ማጋጠሙን ፕሬዚደንቱ ዶ/ር ሙላቱ አስታውሰው ችግሩን ለመፍታት የተሟላ የመፍትሄ ሃሳብ በማዘጋጀትና ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ አማራጭ የሌለው መሆኑን አስቀምጠዋል።


በተጨማሪም በሕገመንግሥቱ ተደንግጎ ነገርግን ለዓመታት ተግባራዊ መሆን ሳይችል የቀረው የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም የሚመለከት አዋጅ በዚህ ዓመት እንደሚወጣም አጽንኦት ሰጥተው ለህዝብ ይፋ አድርገዋል። ሌሎች በርካታ ጉዳዮች በፕሬዚደንቱ ተዳስሰዋል።


እናም የበጀት ዓመቱ ሊጠናቀቅ የቀናት ዕድሜ በቀረው በዚህ ሰዓት ከፕሬዚደንቱ ካደረጉት የመንግሥት አመታዊ ዕቅዶች ምን ያህሉ ተፈጽመዋል ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይሆናል። ኦሮሚያ በአዲስአበባ ላይ ያላትን ጥቅም በሚመለከት የተቀጠውን ሕገምንግሥታዊ ድንጋጌ መሠረት አድርጎ ላለፉት ዓመቴት ሲቀርብ የነበረ ጥያቄ መልስ ያስገኛል የተባለ ረቂቅ ሕግ በሚኒስትሮች ም/ቤት ጸድቆ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ቀርቧል፡፡ አዋጁ በያዝነው በጀት ዓመት የመጽደቁ ነገር አጠራጣሪ ይሁን እንጂ በዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ በአዎንታ መውሰድ የሚቻል ነው፡፡


ሌላው የምርጫ ሕጉ የማሻሻል ጉዳይ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በጀመረው ድርድር ከቀረቡት አጀንዳዎች መካከል ሕገመንግሥቱ እንዲሻሻል የሚጠይቀው በኢህአዴግ በኩል ተቀባይነት ማጣቱ የምርጫ ሕጉን የማሻሻል ጉዳይ ከወዲሁ ጥላ አጥልቶበታል፡፡ የፕሬዚደንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም በሁለቱ ም/ቤቶች መክፈቻ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር በርከላታ ጉዳዮችን ዳስሰዋል፡፡ ምን ያህሉ ተተግብሯል የሚለውን ለመለካት እንዲረዳ ንግግራቸውን በድጋሚ አቅርበነዋል።

*** *** ***

የተከበራችሁ መላ የአገራችን ህዝቦች፣


ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶችና ክቡራትና ክቡራን፤


ከሁሉ በማስቀደም ሁለቱ ምክር ቤቶች በ5ኛው የስራ ዘመናችሁ፣ ሁለተኛውን ዓመት ለምትጀምሩበት ለዛሬው ቀን በመብቃታችን የተሰማኝን ልባዊ ደስታ በራሴና በኢፌዴሪ መንግስት ስም ለማቅረብ እወዳለሁ። በዚህም አጋጣሚ በአገራችን ልዩ ልዩ አካባቢዎች በተካሄዱ ግጭቶች በህይወትም ሆነ በአካል ለተጐዱ ወገኖቻችን፣ እንዲሁም በቅርቡ በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልል የኢሬቻ ባህላዊ ስነ-ስርዓትን ለማክበር ከተሰበሰቡ ወገኖቻችን መካከል ፀረ ሰላም ኃይሎች በፈጠሩት ግርግር ህይወታቸው ላለፈ ወገኖችና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለመላው የኦሮሞና የአገራችን ህዝቦች የተሰማኝን ጥልቅ ሃዘን በራሴና በመንግስት ስም ለመግለፅ እወዳለሁ።

የተከበራችሁ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት፣


የተከበራችሁ መላ የአገራችን ህዝቦች፤


በፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ስርዓታችን ወሳኝ ሚና የሚጫወቱትን ሁለቱን ምክር ቤቶች በምንከፍትበት በዛሬው እለት፣ በብዙ መሰረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መምከር እንደሚገባን ከማንም የተሰወረ አይደለም። ያሳለፍነው ዓመት አገራችን ኢትዮጵያ በብዙ መስኮች ወደፊት የተራመደችበት እንደሆነው ሁሉ ልዩ ልዩ ሁኔታዎች የተከሰቱበትም ነበር። በመሆኑም መልካም ጅምሮችን አጠናክረን ለማስቀጠል፣ ችግሮቻችንን ደግሞ መላ የአገራችንን ህዝቦች በሚያረካ ደረጃ ለመቅረፍ ይቻል ዘንድ እነዚህን ሁኔታዎች አንስተን በዝርዝር ልንመክርባቸው ይገባናል።


አገራችን ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በፈጣን የለውጥ ሂደት ወደፊት ስትራመድ ቆይታለች። ለማንም ግልፅ እንደሚሆነው ለውጡ ከገጠር እስከ ከተማ፣ በሁሉም የህይወት መስክ የተካሄደ ከመሆኑም በላይ ያልዳሰሰው የህብረተሰብ ክፍልም የለም። ለውጡ በዚህ ብቻ ሳይወሰን በህብረተሰባችን ውስጥ መሰረተ ሰፊ የለውጥና የተጠቃሚነት ጥያቄዎች ለመቀስቀስ ምክንያት ሆኗል። ከሰራናቸው መልካምና ውጤታማ ተግባራትም ሆነ ከታዩ ድክመቶችና ከተከሰቱ ተጨባጭ ችግሮች በመነሳት፣ ቀጣዩ ሂደት ይበልጥ ፍሬያማና የህዝባችንን መብትና ተጠቃሚነት ይበልጥ የሚያረጋግጥ፣ የአገራችንን ሰላምና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የሚያጠናክር እንዲሆን አድርጐ መቃኘት እጅግ አስፈላጊ ሆኖ የሚገኝበት ወቅት ላይ ደርሰናል። በመሆኑም ባሳለፍነው ዓመት ካሳካናቸው ውጤቶችም ሆነ ካጋጠሙን ችግሮች በመነሳት ጉዳዮን በዝርዝር መመልከትና ቀጣዮቹን አቅጣጫዎች በትክክል መተለምና በላቀ ርብርብ ተግባራዊ ማድረግ ተገቢ ይሆናል።


ባሳለፍነው ዓመት አገራችንን ከገጠሟት ችግሮች መካከል አንዱና ትልቁ ሰፊ መልክዓ ምድርን የሸፈነው የድርቅ አደጋ ነበር። ድርቁ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታየውን የተፈጥሮ መዛባት ተከትሎ የተከሰተ ሲሆን በአስከፊነቱም ባለፉት 50 ዓመታት ከታዩ ድርቆች ሁሉ የሚስተካከለው አልነበረም። በዚህ የተነሳ በብዙ ሚሊየኖች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችና ቤተሰቦቻቸው ለረሃብ አደጋ የሚጋለጡበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። የድርቁ አስከፊነት በእንስሳት ሀብታችንም ላይ ከባድ የመኖና የውሃ እጥረት ችግር እንዲያጋጥም በማድረጉ የገጠሩ ህብረተሰባችን ህይወት አደጋ ላይ ወድቆ ነበር።


ችግሩ ከተከሰተበት ወቅት ጀምሮ ይህ አደጋ መከሰቱን የተገነዘበው የኢፌዴሪ መንግስት፣ ከመቸውም ጊዜ በተሻለ ደረጃ በራሳችን አገራዊ አቅም በመተማመን ልንፈታው እንደምንችልና እንደሚገባን በመተማመን ተንቀሳቅሷል። በተወሰነ ደረጃ ችግሩ ከአገራችን አቅም በላይ ሆኖ ቢገኝ በወገኖቻችን ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለማስወገድ ይቻል ዘንድ በወቅቱ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ከማሳወቅ ሳይቆጠብ፣ ችግሩን በወሳኝነት በራሳችን አቅም ለመፍታት ተንቀሳቅሷል። በዚህ መሰረት አደጋውን ለመቋቋም የሚያስችለን በጀት በመመደብ፣ በአንድ በኩል ከአገር ውስጥ ትርፍ አምራች አካባቢዎች እህል በመግዛት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በድርቅ ለተጠቁ ወገኖቻችን የሚሆን ቀለብ ለማቅረብ የሚያስችል ከዓለም ገበያ የእህል ግዥ አካሂዷል።


የተገዛው እህል ከማንኛውም ሸቀጥና ምርት ቀድሞ እንዲጓጓዝና ለተረጅዎቹ እንዲደርስ ማድረግም ተችሏል። በውጤቱም ከድርቁ ጋር የተያያዘ ማንኛውም አይነት ሰብዓዊ ቀውስና ጉዳትን ለማስወገድ ችሏል። ከዚህ የተሳካ እንቅስቃሴ ጐን ለጐን ለእንስሳት መኖና ውሃ ለማቅረብ የተሳካ እንቅስቃሴ አካሂዷል። መንግስት በራሳችን አገራዊ አቅም በመተማመን ችግሩን ለመፍታት ያደረገው ይህ እንቅስቃሴ ዓለም አቀፍ ለጋሽ አገሮች በተለመደ የትብብር መንፈስ ከሰጡት እርዳታ ጋር ተዳምሮ የድርቁ አደጋ በዜጐች ላይ ይህ ነው የሚባል ጉዳት ሳያደርስ እንድናልፍ አስችሏል። በዚህ አጋጣሚ ይህን በመሰለው የተፈጥሮ አደጋ ወቅት ከጎናችን ሳይለይ የእርዳታ እጁን በመዘርጋት የምናውቀው ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ፣ ዘንድሮም ላደረገልን ቀና ትብብር በራሴና በኢፌዴሪ መንግስት ስም ላመሰግን እወዳለሁ።


ባለፈው ሩብ ምእተ ዓመት ያጋጠሙንን የድርቅ አደጋዎች ከመቋቋም አኳያ ተመሳሳይ ጉዳትን ስናስወግድ መቆየታችን ከመላ የአገራችን ህዝቦች የተሰወረ አይደለም። በመሆኑም ይህን የመሰለ ውጤት ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘ ነው ሊባል አይችልም። ይህም ሆኖ የዘንድሮውን ውጤት ከዚህ ቀደም ከነበሩት ድርቅን የመከላከል እንቅስቃሴዎች የሚለየው በወሳኝነት በራሳችን አገራዊ አቅም በመተማመን የፈታነው መሆኑ ነው። ልዩነቱ አገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት 25 ዓመታት ባስመዘገበችው የኢኮኖሚ እድገትና በፈጠረችው አገራዊ የመቋቋም አቅም፣ በድርቅ የመጠቃት አደጋ በሚያጋጥምበት ጊዜ ከማንም እርዳታ ሳንጠብቅ ችግሩን በራሳችን አቅም ለመፍታት እንደምንችል የተረጋገጠበት መሆኑ ነው።


ይህ የመላ የአገራችን ህዝቦች የትግልና ልማታዊ ርብርብ ውጤት በመሆኑ መላ ኢትዮጵያዊያን በዚህ ታላቅ አገራዊ ድል ልባዊ ኩራት ሊሰማን ይገባል ብየ አምናለሁ። በገጠር የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራዎች በተከናወኑባቸው አካባቢዎች የከርሰ ምድር ውሃ ይዞታችን እንደበለፀገና በተጨባጭ ለክፉ ቀን ስንቅ ሆኖ እንዳገለገለን ተረጋግጧል። በተጨማሪም ባለፈው ዓመት በዝናብ እጥረት ያጋጠመን የምርት ቅናሽ በሌላ ጊዜ ከሚያጋጥመን ያነሰ እንደነበርም ታይቷል። በድርቅ በተጠቃንበት ዓመት ከመኸር ግብርና የተገኘው 26.7 ሚሊዮን ቶን የግብርና ምርት ከዚያ በፊት ከነበረው በመጠኑ የተሻለ መሆኑ ሲታይ የግብርና ልማት አቅጣጫችን ምን ያህል ትክክለኛ እንደሆነም አረጋግጧል። በመሆኑም በዚሁ አጋጣሚ በዚህ መስክ የጀመርነውን መልካም ስራ ከመቸውም ጊዜ በላይ አጠናክረን ልንገፋበት እንደሚገባን ለማስገንዘብ እወዳለሁ።


በዘንድሮው ክረምት በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች የተመጣጠነና ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ በማግኘታችን፣ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ካለፈውም በጣም የተሻለ ምርት ለማግኘት በሚችሉበት ደረጃ ተንቀሳቅሰዋል። ተጨባጭ ውጤቱ ወደፊት የሚገመገም መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ከእንግዲህ ሊያጋጥም የሚችል ማንኛውም ዓይነት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ጉዳት እንዳያደርስ ተጠንቅቀን እስከተረባረብን ድረስ የ2008/09 የግብርና ምርታችን ከፍተኛ ጭማሪ የሚገኝበትና የህዝባችንን ተጠቃሚነት ይበልጥ የሚያጐለብት እንደሚሆን ይጠበቃል።

 

የተከበራችሁ የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት፣


የተከበራችሁ መላ የአገራችን ህዝቦች፣


ባሳለፍነው ዓመት ያጋጠመንን የድርቅ አደጋ ለመቋቋም ከፍተኛ ጥረት እያደረግን በነበረበት ወቅት፣ የተከሰተው ሌላው አገራዊ ችግር፣ በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች ሁከትና ግጭት መቀስቀሱና አንፃራዊ የፖለቲካ አለመረጋጋት መታየቱ ነበር። ለሁላችንም ግልፅ እንደሚሆነው በልዩ ልዩ የአገራችን ክፍሎች፣ በተለይ ደግሞ ወጣቶች የተሳተፉባቸው ሁከቶችና ግጭቶች ተቀስቅሰዋል። በእነዚህ ግጭቶች ሳቢያ በአሳዛኝ ደረጃ የወጣቶችና ሌሎች ዜጐች፣ እንዲሁም የፀጥታ አስከባሪ ሃይሎቻችን ህይወት ተቀጥፏል።


ቀላል የማይባል ንብረትም ወድሟል። በተጨማሪም የዜጐች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ተስተጓጉሏል። በዚህ የተነሳ ደፋ ቀና ብለው ሰርተው ኑሮአቸውን ለማሸነፍ የሚንቀሳቀሱ ዜጐች ለፈተናዎች ተዳርገዋል። ይህን የመሰለው ችግር በየአካባቢው እንዲቀሰቀስ ምክንያት የሆኑ ወቅታዊ ችግሮች እንደነበሩ ባይካድም፣ ከተከሰተበት ሁኔታና ከደረሰው የህይወትና የንብረት ጉዳት በመነሳት መሰረታዊ ምክንያቶቹን በውል ማስቀመጥ ይገባል። እነዚህን ለመፍታት የሚያስችል የተሟላ የመፍትሔ ሃሳብ በማዘጋጀት መላውን ህብረተሰብ በሚያሳትፍ አግባብ ተግባራዊ ማድረግ ወሳኝ ሆኖም ተገኝቷል።


ለማንም ግልፅ እንደሚሆነው ባሳለፍነው ዓመት በተከሰቱት ግጭቶች ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ የነበሩት የአገራችን ወጣቶች ነበሩ። ይህ እውነታ ወጣቶቻችን የሚገኙበትን ሁኔታ በትክክል መገንዘብና ለችግራቸውና ለጥያቄያቸው የሚመጥን መሰረታዊ መፍትሔ ማቅረብ አጣዳፊ ሆኖ ይገኛል።


አገራችን ኢትዮጵያ በህዝብ ብዛት ከአፍሪካ በ2ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ወደ መቶ ሚሊዮን ከሚጠጋው ህዝቧ ውስጥ ደግሞ ከግማሽ የማያንሰው በወጣት የእድሜ ክልል የሚገኝ ነው። ስለሆነም በህብረተሰባችን ውስጥ የሚካሄድ ማንኛውም የለውጥ እንቅስቃሴ ተወደደም ተጠላም ወጣት ተኮር መሆኑ የግድ መሆኑ አይቀርም። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አብዛኛው የአገራችን ህዝብ በገጠር የሚገኝ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወጣቱም በዋነኛነት ተከማችቶ የቆየውና ዛሬም የሚገኘው በዚሁ የገጠሩ ክፍላችን ነው።


ይህ የወጣት ኃይል ለረጅም ጊዜ በገጠር ተወስኖ ከቆየ በኋላ በተወሰኑ መሰረታዊ ምክንያቶች ከገጠር ወደ ከተሞች በመፍለስ ላይ ይገኛል። አብዛኛው የገጠር ወጣት መሬት አልባ በመሆኑ ከገጠሩ ጋር ተጣብቆ የሚቆይበት ጠንካራ ምክንያት የለውም። በዚህ ላይ የግብርና ምርታማነት እየጨመረ መሄዱን ተከትሎ፣ በመፈጠር ላይ ያለው ትርፍ ጉልበት ገጠርን እየለቀቀ ወደ ከተሞች እንዲንቀሳቀስ ግድ የሚልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በተጨማሪም ወጣቱ በአገራችን የተስፋፋው የትምህርት እድል ተጠቃሚ ሆኖ ከቆየ በኋላ የወላጆቹን ልማዳዊ የግብርና ስራ ሊቀጥልበት የማይፈልግ እየሆነ በመምጣቱ የገጠሩ ወጣት ቀስ በቀስ ወደ ከተሞች በተለይ ደግሞ ወደገጠር ከተሞች እየጐረፈ መከማቸት ጀምሯል።


ይህ ወጣት ገጠሩን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ የለቀቀ ቢሆንም፣ በከተሞቻችን አስተማማኝ የስራና የገቢ ሁኔታ ገና ያልተፈጠረለት ነው። በተከማቸባቸው ከተሞች ሁሉ በአመዛኙ ከእለት ስራ ያለፈ ቋሚ የስራና የገቢ እድል የሌለው በመሆኑ ህይወቱ አስተማማኝ መሰረት ያልያዘ ነው። ሁኔታዎች ዘንበል ያሉ ቀን ለከፋ አደጋ እጋለጣለሁ ብሎ እርግጠኛነት በማጣት ውስጥ የሚገኝ ወጣት ነው። ይህን የመሰለው ወጣት በትንንሽ የገጠር ከተሞች ብቻ ሳይሆን፣ በትልልቅ ከተሞችም ጭምር የሚገኝ በመሆኑ መንግስት ከመቸውም ጊዜ የተለየ ወጣት ተኮር ርብርብ ካላደረገ በስተቀር፣ አገራችን በቅርቡ ለተከሰተው ዓይነት ፖለቲካዊ ችግር በተደጋጋሚ መጋለጧ እንደማይቀር መገንዘብ ይገባል።


መንግስት የወጣቱን ችግር ለማቃለል ባለፉት ዓመታት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደተንቀሳቀሰ ይታወቃል። በተለይ ደግሞ ከ3ኛው አገራዊ ምርጫ በኋላ የወጣቶች የልማትና ተጠቃሚነት ፓኬጅ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ተቀርፆ በተካሄደው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ብዙ የአገራችን ወጣቶች ተጠቃሚ መሆን እንደጀመሩም ይታመናል። ይህም ሆኖ ከዚህ ቀደም የተዘጋጀው መፍትሄም ሆነ በዚሀ ላይ በመመሰረት የተከናወነው ስራ እጅግ እየሰፋ ከመጣው የወጣት ቁጥርና ፍላጐት ጋር የሚመጣጠን እንዳልሆነ ታይቷል። ከዚህ በተጨማሪ ለወጣቶች ታስበው የተቀረፁ የልማትና ተጠቃሚነት ኘሮግራሞች በመንግስት በኩል በሚታዩ የተለያዩ ድክመቶች፣ በተለይ ደግሞ በአድልአዊ እና ብልሹ አሰራሮች ምክንያት ሲደነቃቀፉ የወጣቱ ትውልድ ቅሬታ እንደሚባባስ ታይቷል። በመሆኑም ባሳለፍነው ዓመት የተከሰቱት ችግሮች በመሰረቱ ከኢኮኖሚ ፍላጐትና ተጠቃሚነት ጋር የተያያዙ በመሆናቸው እነዚህን ችግሮች ራሱን ወጣቱን ትውልድ በቀጥታና ዴሞክራሲያዊ አኳኋን በሚያሳትፍ አቅጣጫ መፍታት ጊዜ የማይሰጥ ተደርጐ ሊወሰድ ይገባዋል።


ባሳለፍነው ዓመት የተከሰተው የፖለቲካ አለመረጋጋት ከተጠቃሚነት አኳያ ያመጣው ችግር የአገራችንን ወጣቶች ብቻ የሚመለከት አልነበረም። በአገራችን ፈጣን ብቻ ሳይሆን መላውን ህዝብ በየደረጃው ተጠቃሚ የማድረግ ግብ ይዘን በምንገነባው ኢኮኖሚ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ጥቅም በፍትሃዊነት የማስከበር ጉዳይ ሁሌም ቢሆን በተጨባጭ እየተለካና ይህንኑ በፍትሃዊነት እያሳካን በመሄድ ላይ መሆናችን እየተረጋገጠ ሊሄድ የሚገባ ጉዳይ ነው። በዚህ ረገድ ቁጥራቸው ሰፊ የሆኑትና በደመወዝ የሚተዳደሩ ወገኖች ከሚያጋጥማቸው የኑሮ ውድነትና የቤተሰብ ኃላፊነት ጋር በተጣጣመ ደረጃ መጠቀም መጀመራቸውን ማረጋገጥ አማራጭ የሌለው ሆኗል።
መንግስት በዚህ ረገድ ያነገበውን የፍትሃዊ ተጠቃሚነት አላማ ለማሳካት በማለም ባለፉት በርካታ ዓመታት ድህነትን ለመቀነስ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መቆየቱና ከጠቅላላ አገራዊ ባጀታችን ውስጥ እጅግ አብዛኛው ድሃ ተኮርና የዜጐችን የማምረት አቅም በመገንባት ላይ ያነጣጠረ እንዲሆን ማድረጉ ተገቢ ቢሆንም በዚህ ረገድ በተለይ ካስመዘገብነው እድገታችን ጋር በሚመጥን ደረጃ መጠቀም ያልጀመሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ችግር ለማቃለል በተለየ ትኩረት መንቀሳቀስ አንገብጋቢ ሆኖ ይገኛል።


ባሳለፍነው አመት መፍትሄ የሚሹ ሆነው ከታዩት ችግሮች ሌላው በከተሞች አቅራቢያ በሚገኙ ገጠሮች የሚከሰት የአርሶ አደርና የአርብቶ አደር ወገኖቻችን መፈናቀል ጉዳይ ነው። አገራችን ታዳጊ እንደ መሆኗ ከተሞቻችን በልዩ ልዩ ምክንያቶች ወርድና ቁመታቸው እየጨመረ እንደመጣና ወደፊትም ይህ ሁኔታ እየሰፋ እንደሚሄድ ለመገመት አያስቸግርም። በተመሳሳይ መልኩ በገጠር ሰፋፊና ዘመናዊ እርሻዎችን እንዲሁም ትልልቅ የሃይል ማመንጫና የመስኖ ግድቦችን የመስራት ፍላጎታችንም የገጠር መሬትን ከመጠቀም ውጭ ሊሳካ የማይችል ነው። በመሆኑም ዘመናዊ እርሻዎችና ትልልቅ ግድቦች መስፋፋታቸው ቀጣይ በመሆኑ ይህን ከአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ መብትና ጥቅም ጋር በተጣጠመ አኳኋን መፈፀም አማራጭ የሌለው ሆኖ ይገኛል።


አርሶ አደሩ የተቻለውን ያህል መሬቱን ከፍተኛ ጥቅም ሊያገኝ በሚችልበት ሁኔታ እንዲያለማው ከማድረግ ጀምሮ ለላቀ አገራዊ ጥቅም በሚፈለግበት ጊዜ ደግሞ ይህንኑ ከአርሶ አደሩና ከአርብቶ አደሩ ዘላቂ፣ ቀጣይና ታዳጊ ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ ልንፈፅመው የሚገባን ሆኖ ይገኛል። ሃቁ ይህ ቢሆንም በከተሞች አቅራቢያ የሚካሄደውም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የአርሶ አደርና አርብቶ አደር መፈናቀል ከተመጣጣኝ ካሳና የማቋቋም እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ጉድለቶች የሚታዩበት እንደሆነ ለመገንዘብ ተችሏል። በዚህ የተነሳ በተለይ ለከተሞች በቀረቡ አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮቻችን ለልዩ ልዩ ቅሬታዎች ሲጋለጡ ቆይተዋል። በመሆኑም በያዝነው አመት ይህን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል አቅጣጫ ይዘን በመረባረብ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ለማስፋት ትኩረት መስጠት ይገባል።


ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በልማታዊ መንገድ በችሎታና በጥረት ተወዳድረው ለመጠቀም የሚሹ ያሉትን ያህል ካላግባብ የመጠቀም አዝማሚያ የተጠናወታቸው ጥቂት ማህበራዊ ኃይሎች ለአገራዊ እድገት ካበረከቱት አስተዋፅኦ በላይ ሲጠቀሙ የሚታይ በመሆኑ በመነሳት የፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ጉዳይ በጥብቅ መፈተሽና ማስተካከል አስፈላጊ ሆኖ ይገኛል። እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች አገራችን በከፈተችው እድል ከመጠቀም ወደኋላ የማይሉ ቢሆኑም የመንግስትን ህግ አክብሮ በመንቀሳቀስም ሆነ የግብር ግዴታቸውን በመወጣት ደረጃ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንደማይወጡ ይታወቃል።


በመሆኑም በኮንትሮባንድና በማጭበርበር እንዲሁም የጉምሩክ ማስተላለፍ ቀዳዳዎችን እና ትስስሮችን በመጠቀም ለአገራዊ እድገት ካበረከቱት አስተዋፅኦ በላይ የሚጠቀሙ ክፍሎች የሚራመዱበትን ህገ ወጥ ተጠቃሚነት በመከላከልና በመቆጣጠር ከዚህም አልፎ የግብር መክፈልና ህግ የማክበር ግዴታቸውን እንዲወጡ በማድረግ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጉዳይ የማያጠራጥር ተፈፃሚነት እንዲኖረው ማድረግ ይገባል። ከዚሁ ባልተናነሰ ደረጃ ከከተማ መሬት እና በአንዳንድ ቆላማ አካባቢዎች ከገጠር መሬት ጋር ተያይዞ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችና አላአግባብ የመጠቀም ዝንባሌዎችን ለማስተካከል ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል።


በዚህ አጋጣሚ በቅርቡ በአንዳንድ የአገራችን ክልሎች ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በኃይል ለመናድ ሲካሄዱ የቆዩ አፍራሽ እንቅስቃሴዎችን መሰረታዊ ባህርይና እንድምታ በትክክል መገንዘብ ተገቢ ሆኖ ይገኛል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በህብረተሳባችን ዘንድ በተለይ ደግሞ በወጣቶቻችን በኩል የተነሱ ፍትሃዊ ጥያቄዎችን ተገን በማድረግ አንዳንድ አፍራሽ ኃይሎች ቅሬታን ወደሁከትና አውዳሚ እንቅስቃሴ ለመቀየር ተረባርበዋል። አገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት ከኖረችበት ማሽቆልቆል ወጥታ በእድገት ጎዳና መገስገስ በጀመረችበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት በትንሳኤ ላይ መሆናችንን የማይቀበሉ አገሮችና የኒዮ ሊበራል አጀንዳቸውን ሊጭኑብን የተዘጋጁ ኃይሎች፣ ወደትርምስ እንድንገባ አቅደው፣ አገራችንን ለማተራመስ በስፋት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ይፋ ሆኗል።


በተለይ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የማንንም እጅ ሳንጠብቅ በመላ የአገራችን ህዝቦች ተሳትፎና በአገራዊ አቅማችን በመተማመን መገንባት መጀመራችን ያስቆጣቸው አገሮች፣ ረዘም ላሉ ዓመታት ውስጥ ውስጡን ሲዘጋጁ ከርመው በአሁኑ ጊዜ ፅንፈኛ የዳያስፖራ ኃይሎች ከቀሰቀሱት ነውጥ ጋር በመመጋገብ አገራችንን ለማተራመስ በቀጥታ እየተረባረቡ ይገኛሉ። በቀላሉ ሊያነሳሱዋቸው የሚችሉ ወጣቶችን የጥፋት ሃሳቦች፣ እንዲሁም ክብሪትና ነዳጅ እያስታጠቁ ለአገራችን ቁልፍ ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦ ያላቸውን ፋብሪካዎች፣ የአበባ እርሻዎችና ሌሎች ተቋማት በማጋየት ከፍተኛ ውድመት አስከትለዋል። የግለሰቦችን ቤቶችና ሌሎች ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረቶች አውድመዋል።


ይህን ድርጊት መንግስት ለቴክኖሎጅ ሽግግርና አገራዊ ልማትን ለማፋጠን በማሰብ ያስፋፋውን ዘመናዊ የመገናኛ መሰረተ ልማት ለክፋትና ውድመት በመጠቀም ያስተባበሩት ደግሞ አገራችን በአሸባሪነት የሰየመቻቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ናቸው። የኦነግና ግንቦት ሰባት መሪዎች ከግብፅ መንግስት ተቋማት ጋር እጅና ጓንት በመሆን ባቀናበሩት የጥፋት እንቅስቃሴ በርካታ አገራዊና የውጭ ባለሃብቶችና ሰራተኞቻቸውን ለአደጋ ያጋለጠ የታሰበበት ከፍተኛ ውድመት ፈፅመዋል። ይህ ከአገራችን ወጣቶች ፍትሃዊ ጥያቄዎች ጋር አንዳችም ተዛምዶ የለውም።


ከፅንፈኛ ዳያስፖራዎች ጀምሮ በአባይ ወንዛችን ላይ የተጠቃሚነት መብታችንን ለማረጋገጥ የጀመርነውን እንቅስቃሴ ለማኮላሸት የሚንቀሳቀሱት እነዚህ ወገኖች፣ በቅርቡ ታላቁን የእሬቻ በዓል ከማወክ ጀምሮ በልዩ ልዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ያካሄዱት ውድመትና ቃጠሎ በማንኛውም ሚዛን ፍትሃዊነት የሌለው ነው። በመሆኑም መንግስት ይህን የመሰለው አፍራሽና ከባድ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ታዝሎ የመጣ ፀረ-ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ እንዲመከትና ወንጀለኞቹም በጥብቅ በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ያደርጋል። በቃጠሎ የወደሙ ንብረቶች በተለይ ደግሞ የምርት ተቋማት አገራችንና ህዝቦቿ ከውጭ የልማት አጋሮቻችን ጋር በመተባበር በአፋጣኝ መልሰው እንዲገነቡና ለላቀ ምርታማነት እንዲበቁ ጠንካራ ርብርብ ይደረጋል። በመሆኑም መላ የአገራችን ህዝቦች ኢትዮጵያን እንደፈራረሱት የሰሜን አፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ለማተራመስ የሚደረገውን ይህን አፍራሽና አሳፋሪ ሙከራ መንግስትና ህዝብ በጀመሩት መንገድ በጋራ ይፋለሙታል።

 

የተከበራችሁ የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት፣


የተከበራችሁ መላ የአገራችን ህዝቦች፣


2ኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተግባራዊ ማድረግ በጀመርንበት ዓመት የተከሰቱት ችግሮች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንድምታ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታችንን በማዳበር ልንፈታቸው የሚገባ ልዩ ልዩ ፖለቲካዊ ጉዳዮችም እንዳሉም አመላክተውናል። በዚህ ረገድ ቀዳሚው ጉዳይ በአገራችን የብሔር ብሔረሰቦችን መብት መሰረት አድርገው የሚነሱ የማንነት ጥያቄዎችን በህገ-መንግስታችን በጥብቅ በመመራት መፍታት እንዳለብን ሊሰመርበት የሚገባ መሆኑ ነው። ለማንም ግልፅ እንደሚሆነው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን የተዋቀረው ኢትዮጵያ የብዙ ህዝቦች አገር የመሆኗን እውነታ ያለማቅማማት በመቀበል ነው።


አገራችን ኢትዮጵያ የአንድ ቋንቋ፣ ወይም ባህል አገር ሳትሆን የብዙ ቋንቋዎች፣ ሌሎች የማንነት መገለጫዎች ባለቤት የሆኑ ብዙ ህዝቦች እናት የሆነች አገር ነች። ቀደም ሲል በአገራችን ይህን እውነታ በመካድ ብሔር ብሔረሰቦቻችን ካላግባብ የተያዙበት መንገድ ለግጭትና የእርስ በርእስ ለዘመናት ጦርነት መንስዔ እንደነበር በመገንዘብ አዲሱ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ብዝሃነትን በማወቅና በመቀበል እንዲሁም በአግባቡ በማስተዳደር ላይ እንዲመሰረት ተደርጓል። ይህም በመሆኑ አገራችን ለ25 ዓመታት የዘለቀ አስተማማኝ ሰላም ተጐናፅፋ ቆይታለች።


ላለፉት 25 ዓመታት የተገነባው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ከሞላ ጐደል የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ በተግባር የመለሰ ቢሆንም፣ በተወሰነ ደረጃ መሰረተ ሃሳቡ ተግባራዊ ያልተደረገባቸው ማህበረሰቦች ደግሞ እንደነበሩ ታይቷል። በዚህ የተነሳ ዘግይተው ጥያቄ የሚያቀርቡ ራሳቸውን የቻሉ ማህበረሰቦች የተከሰቱ ሲሆን፣ የነዚህ ህዝቦች ጥያቄ በዴሞክራሲያዊው ህገ መንግስታችን ማዕቀፍ ሊስተናገድ የሚችልና የሚገባው ሆኖ ይገኛል። ይሁንና ይህን የመሰለው ፍትሃዊ ጥያቄ በወቅቱ ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኝ ባለመደረጉ በአንዳንድ አካባቢዎች ለግጭት መንስኤ መሆን ጀምሯል። ይህም ሆኖ ግጭቱ የተቀሰቀሰው አንዳንድ ወገኖች እንደሚያስቡት ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአታችን ለግጭት መንስዔ ስለሆነ፣ ወይም ደግሞ በማንነት ዙሪያ የሚነሱ አዳዲስ ጥያቄዎችን በብቃት ለማስተናገድ የሚቸገር በመሆኑ አይደለም።


ፌዴራላዊ ስርአታችን በመሰረታዊ ባህሪው የማህበረሰቦችን ማንነት ማክበር በመሆኑ ችግር ፈች እንጅ ችግር ፈጣሪ ወይም አባባሽ አይደለም። ይህ ሩቅ ሳንሄድ አዲሱ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአት፣ አገራችን በዘመናዊ ታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ሩብ ምዕተ ዓመት የሞላው ረዥም የሰላም ዘመን እንድትኖር፣ ህዝቦቿ ለሃያ አምስት ዓመታት በሰላም፣ በፍቅርና በመካባበር እንዲኖሩ ያስቻለን በመሆኑ የሚረጋገጥ ነው። ስለሆነም ችግሩ በተጨባጭ የተነሳው ከስርአቱ ባህሪ ሳይሆን፣ ማህበረሰቦች የሚያነሱትን የማንነት ይከበርልን ጥያቄ ከህገ-መንግስታዊው ድንጋጌ በመነሳትና ይህንኑ በጥብቅ በማክበር መመለስ ሲገባ ከዚሁ ተቃራኒ በሆነ አያያዝ በአንዳንድ አካባቢዎች በመፈፀሙ ነው።


ከዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አኳያ ሌላው ትኩረት የሚሻ ሆኖ የተገኘው ራሱን ዴሞክራሲያችንን ከእድገታችን ጋር በተገናዘበ ሁኔታ ተግባራዊ የማድረግ ጉዳይ ነው። አገራችን ባፀደቀችውና በምትመራበት ህገ-መንግስት ዴሞክራሲያዊ የአስተዳደር ስርዓትን መርጣለች። የመረጥነው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለአንዴና ለሁልጊዜ ረግቶ የሚቀመጥ ሳይሆን ከአገሪቱ የእድገት ደረጃ ጋር ተገናዝቦ ሁሌም ቢሆን በታዳጊነት መገንባትና እየዳበረ መጓዝ ያለበት ነው። ከዚህ በመነሳት በአገራችን ብዝሃነት ያሉዋቸው ማህበረሰቦች እንደሚገኙና እነዚህም የየራሳቸው ልዩ ልዩ ፍላጐቶች ያሏቸው መሆኑን በመገንዘብ የተለያዩ ጥቅሞችን በማቻቻልና በማጣጣም ልትመራ የሚገባት እንደሆነ ታምኖበት በዚሁ ቅኝት ስትራመድ ቆይታለች። ከሁሉ በፊት በጥቅሞች መካከል የሚከሰቱ ልዩነቶች ሁሉ በዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ መንገድ እንዲገለፁ ማድረግ፣ አገራችን በተረጋጋ መንገድ ለመቀጠል እንድትችል የሚያደርጋት ቁልፍ እንደሆነ ታምኖበት ፍላጐቶች በነፃነት እንዲገለፁ ሲደረግም ቆይቷል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ከመልካም አስተዳደር ችግርና ከመሳሰሉት ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ ቅሬታዎችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ከማስተናገድ አኳያ በመንግስትም ሆነ በህብረተሰብ ደረጃ ክፍተቶች እንዳሉ ተስተውሏል። በመንግስት በኩል ለህዝብ ቅሬታ መከሰት ምክንያት የሆኑ ችግሮችን በፍጥነት ካለማረም ጀምሮ ህዝብ የተሰማውን ቅሬታ በዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ መልክ ይገልፅ ዘንድ በበቂ ሁኔታ ያለማስተናገድ ችግር ታይቷል። በአንዳንድ የህብረተሰባችን ክፍሎች በኩል ደግሞ ህገ-መንግስታዊ ስርዓታችን ማንኛውንም ጥያቄ ሆነ የህዝብን ፍላጐት በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ለማራመድ የሚያስችል ብቁ የመታገያ ማዕቀፍ እንዳጎናፀፈን በውል ባለመገንዘብ በጥቂቱም ቢሆን ከህገ መንግስታዊ ስርአቱ ውጭ በሚታዩ ሁከቶች በመሳተፍ መልክ የሚታዩ ስህተቶች ተስተውለዋል። አልፎ አልፎ በተለይ ደግሞ በወጣቶቻችን ዘንድ ህግ በመጣስ መንግስትና ህዝብን ለማጋጨት የሚሹ አፍራሽ ፀረ- ሰላም ሃይሎችን በየዋህነት በመከተል የተሳሳቱ የትግል ስልቶች የመጠቀም አዝማሚያ ታይቷል። በዚህ ረገድ ፍላጐትን በሰላማዊ ሰልፍ አማካይነት ከመግለፅ መብት ጋር ተያይዘው የተከሰቱ ችግሮችን ማስታወስ ይቻላል። እነዚህ ችግሮች በመንግስትም ሆነ በህብረተሰብ ደረጃ ዴሞክራሲያችንን በማበልፀግ ተጨማሪ እርምጃዎች መራመድ እንዳለብን የሚያመላክቱ ሆነዋል።


ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችንን ከማበልፀግ አኳያ ሌላው ትኩረት የሚሻው ጉዳይ በአገራችን የፍላጐት ብዝሀነት እንዳለ ተገንዝቦ እነዚህን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመግለፅ የሚቻልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ከማድረግ አኳያ የምክር ቤቶቻችንን ተዋፅኦ የማጐልበት ጉዳይ ነው። እንደሚታወቀው አገራችን በምትከተለው የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ስርዓት በመመራት ባለፉት ሀያ አምስት ዓመታት በድምሩ ለአስር ጊዜ አገራዊ፣ ክልላዊና ከባቢያዊ ምርጫዎች ተካሂደዋል። በእነዚህ ምርጫዎች የብዙ ፓርቲዎች ተሳትፎ የነበረ ሲሆን፣ በተለይ ባለፉት ሁለት ምርጫዎች እንደተከሰተው በምክር ቤቶቻችን የገዥው ፓርቲ ሙሉ የበላይነት ያለበት ሁኔታ ተስተውሏል። ይህ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በተካሄደ ምርጫ የህዝብ ድምፅ ያስገኘው ውጤት እንደሆነ ባያጠያይቅም፣ ተቃዋሚዎችን የመረጡ የህብረተሰብ ድምፆች በመኖራቸውና በአብላጫ ድምፅ ወንበር የማግኘት የምርጫ ሥርዓታችን መሠረት በአገራችን ወሳኙ የስልጣን አካል በሆነው ምክር ቤት የማይወከሉ ድምፆች እንዲኖሩ አድርጓል። በመሆኑም ከገዥው ፓርቲ በተለዩ ፓርቲዎች የሚወከል ጥቅምና ፍላጐት ያላቸው ማህበረሰቦችን የሚወክሉ ፓርቲዎች በምክር ቤቶቻችን ውስጥ የመሳተፍ እድል ሳያገኙ ቀርተዋል። ስለሆነም ይህን የመሰለው ሁኔታ ስርዓታችን ተረጋግቶ እንዲቀጥል ከማድረግ አኳያ የራሱ አሉታዊ ተፅእኖ የሚያስከትል በመሆኑ፣ በተቻለ መጠን ከቀጣዩ ምርጫ በፊት ዴሞክራሲያዊ መድረኮችን በማስፋትና በቀጣዩ ምርጫም በህግ ማእቀፍ በተደገፈ አኳኋን የህዝብ ምክር ቤቶች የተለያዩ ድምፆች የሚሰማባቸውና የሚፎካከሩባቸው መድረኮች እንዲሆኑ በማድረግ ማስተካከል ያስፈልጋል።


የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታችን ለፓርቲዎች ተሳትፎ ከሚሰጠው ትኩረት ባልተናነሰ ደረጃ፣ በከፍተኛ ትምህርትና በልዩ ልዩ የስራ ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ምሁራንን ጨምሮ በተለያዩ የሲቪክ ማህበረሰብ አደረጃጀቶች ውስጥ የሚታቀፉ ዜጎችን በቀጥታ በማሳተፍ ጠቃሚ ሃሳቦቻቸውን ሁሉ ለአገር ግንባታ ማዋል ይጠይቃል። በዚህ ረገድ ልዩ ልዩ መድረኮችን በመክፈት የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ለማረጋገጥ የተለያዩ ጅምር ጥረቶች እንዳሉ ባያጠያይቅም እስካሁን የተደረጉት ጥረቶች በቂ እንዳልሆኑ ለመገንዘብ አያስቸግርም። በተከፈቱት መድረኮች የሚቀርቡ አስተያየቶችን በውል አዳምጦ ጠቃሚዎቹን ያለማቅማማት በመውሰድ፣ የተሳሳቱና ጐጅ አስተያየቶችን ደግሞ በአመክንዮና ጭብጦች ታግዞ በማስተካከል፣ የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎና አስተዋፅኦ ወደሚገባው ደረጃ ማድረስ አስፈላጊ ሆኖ የሚገኘው ከዚህ የተነሳ ነው።


በአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን በታዳጊ አኳኋን ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ ትኩረት የሚሻ እንደሆነ የተረጋገጠው ሌላው ጉዳይ በስነ ምግባርና ስነ ዜጋ እሴቶች የታነፀ ትውልድ የመፍጠር ጉዳይ ነው። በየትኛውም ዓለም ዜጐች መብትና ግዴታቸውን በውል ተገንዝበው፣ ከእያንዳንዳቸው የሚጠበቀውን ኃላፊነት እየተወጡ፣ በመብቶቻቸው ላይ ደግሞ የማይደራደሩ ሆነው እስከተገነቡ ድረስ አገሮች በእድገት ጐዳና እንደሚራመዱ ይታወቃል። የላቀ የዜግነት እንቅስቃሴም መልካም አስተዳደርን ለማስፈንም ጭምር ወሳኝ ጉዳይ ነው። በእኛም አገር ከዚህ የተለየ ሊሆን አይችልም። ዜጐች በአገር ግንባታ ሂደት ንቁ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትምህርትና ክህሎትን ማስፋፋት አማራጭ የሌለው ቢሆንም፣ ከዚሁ በማይነጠል መልኩ በስነ ምግባርና ስነ ዜጋ እሴቶች የታነፀ ትውልድ የመፍጠር ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ሆኖ ይገኛል።

 

የተከበራችሁ የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት፣


የተከበራችሁ መላ የአገራችን ህዝቦች፣


ከወቅታዊ የአገራችን ሁኔታ በመነሳት እነዚህን የመሳሰሉ ጉዳዮች አጣዳፊ መፍትሔ የሚሹ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ዛሬም እንደ ትላንቱ አገራችንን በታለመው ፈጣን የእድገት አቅጣጫ ለማስቀጠልና የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማጐልበት ሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ተግባራዊ የማድረግ ጉዳይ ልዩ ትኩረት የሚሻ ሆኖ ይገኛል። በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዳችን የተሳካ አፈፃፀም በመበረታታት የነደፍነው ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ወደ ተግባር ከተሸጋገረ አንድ ዓመት አስቆጥሯል። በዚህ መሰረት ባሳለፍነው ዓመት በሁሉም መስኮች እቅዳችንን ተግባራዊ ለማድረግ የተንቀሳቀስን ቢሆንም አፈፃፀማችን በልዩ ልዩ ተግዳሮቶች ተፅዕኖ ስር ለማለፍ የተገደደ እንደነበር ከመላ የአገራችን ህዝቦች የተሰወረ አይደለም። ድርቁና ከሞላ ጐደል አብዛኛውን የዓመቱን ክፍል የሸፈኑ የሰላምና መረጋጋት ችግሮች በአፈፃፀማችን ላይ ራሳቸውን የቻሉ ተፅእኖዎች ያሳደሩ ነበሩ።


ምንም እንኳ በትልልቆቹ ኘሮጀክቶቻችን አፈፃፀምና የተሻለ ዝናብ ከመገኘቱ ጋር ተያይዞ በታየው የተሻለ የግብርና ምርታማነት እና በኢንዱስትሪ መስክ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች በመከናወናቸው ኢኮኖሚያችን አሁንም በፈጣን እድገት ጐዳና መቀጠሉ የተረጋገጠ ቢሆንም፣ አገራችን ከፈጠረችው መልካም መነሻና ካላት ድልብ አቅም በመነሳት ለላቀ ውጤት ተግተን መስራት የሚገባን ወቅት ላይ እንገኛለን። ባሳለፍነው ዓመት ያጋጠሙ ችግሮች በአፈፃፀማችን ላይ ያሳደሩትን ተፅዕኖ በመቋቋም ሳንወሰን በዚህ ምክንያት የተፈጠረውን ክፍተት በሚያካክስ ደረጃ ለውጥ ለማምጣት መረባረብ ያስፈልጋል።


ከዚህ በመነሳት በያዝነው ዓመት የግብርና ኘሮግራማችን በተለምዶ ጥሩ እድገት ሲያሳዩ የቆዩትን የግብርና መስኮች ለላቀ ውጤታማነት ለማብቃት እንቀሳቀሳለን። ከግብርና ዘርፉ ውስጥ በቀላሉ ከፍተኛ መሻሻል ልናሳይ የምንችለው አሁንም በተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤና በዚሁ ተደግፎ የመስኖ ስራችንን በማስፋፋት በሰብል ምርት እድገት በማምጣት በመሆኑ እነዚህን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ አልመን መንቀሳቀስ ይኖርብናል።


የተፈጥሮ ሃብት ልማት አገራችን ያላትን እምቅ የግብርና አቅም አሟጠን እንድንጠቀምበት የሚያስችለን ዋናው መግቢያ በመሆኑ አካባቢውን ተግቶ የመለወጥ ባህል ማዳበር በጀመረው አርሶ አደርና አርብቶ አደሮቻችን እንዲሁም በየገጠሩ ወጥተው ወርደው ህዝብን በሚያስተምሩ ሙያተኞቻችን በመተማመን የመሬታችንን ለምነትና የውሃ ሃብታችንን ለማበልፀግ መረባረብ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው ይደረጋል። በምንገኝበት የእድገት ደረጃ የሰብል ምርት የህልውናችን መሰረት በመሆኑና በዚህ መስክ የምናስመዘግበው እድገት ሁሉ በገጠርም ሆነ በከተማ የህዝባችንን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ቁልፍ ተፈላጊነት ያለው እንደሆነ በመገንዘብ ይህን ለማልማት መላ አቅማችንን እናረባርባለን።


እነዚህ እንደተጠበቁ ሆነው የአገራችንን አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ከፍተኛ ዋጋ ወደሚያስገኙ ምርቶች ለማሸጋገር ተፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ የማሟላት ጉዳይ በእቅዱ መሰረት ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝ ይደረጋል። ከፍተኛ ዋጋ ከሚያስገኙ የግብርና ምርቶች መካከል በአነስተኛው አርሶ አደር ማሳ የሚለሙ እንደቡና የቅባት እህሎች፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች፣ ደኖችና የእንስሳት ሃብታችን ልማት ዋናዎቹ ሲሆኑ በዚህ ረገድ የአገራችን ያላትን ድልብ አቅም በአፋጣኝና በብቁ ዝግጅት ወደማልማት እንሸጋገራለን።


ከዚህ በመነሳት የግብርና ልማታችን በአንድ በኩል በቀላሉ ከፍተኛ የእሴት ጭማሪ ልናመጣባቸው በሚገባን መስኮች መረባረብን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የቀጣዩ የግብርና ዘርፍ እድገት አምጭ መስኮችን ለይቶ በበቂ ቅድመ ዝግጅት ወደማልማት መሸጋገርን በታሳቢነት የሚወስድ እንዲሆን ይደረጋል። በገጠር ከግብርና ልማታችን ጋር በማያያዝ ሊመጣ ከሚገባው እድገት ዋናው ተጠቃሚ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ መሆናቸውን ከማረጋገጥ በተጨማሪ የእነዚህ ወገኖች የመሬት ተጠቃሚነት ዋስትና ይበልጥ አስተማማኝ እንዲሆን ከማድረግ ጀምሮ ለምርታቸው ተገቢውን ዋጋ አግኝተው ተጠቃሚነታቸው እንዲሰፋ የማድረግ ጉዳይ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል።


በተለይ ደግሞ አይቀሬ ከሆነው የከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ የገጠር መሬትን ለላቀ ጥቅም ለማዋል የሚደረግ እንቅስቃሴ የአርሶ አደሩንና የአርብቶ አደሩን መሰረታዊና ታዳጊ ጥቅሞች አሳልፎ በማይሰጥ መንገድ እንደሚፈፀም ይረጋገጣል። በዚህ ረገድ ክፍተት ያለባቸውን ነባር ህጎችን የማስተካከል፣ በአፈፃፀም የሚታዩ ስህተቶችን ታግሎ የማረም፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም አዳዲስ የህግ ማዕቀፎችን የማዘጋጀትና ከሁሉ በላይ ደግሞ ከመሬታቸው ለልማት ሲባል የሚነሱ አርሶ አደሮችንና አርብቶ አደሮችን በሚያሳትፍ አኳኋን እንዲፈፀም ይደረጋል።


አገራችንን በግብርናው ዘርፍ ለማሳደግ የሚካሄደው ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ወደ ኢንዱስትሪ መር ልማት ለመሸጋገር ዝግጅት የምናደርግበት እንደሆነ ይታወቃል። በዚህ መሰረት ከወዲሁ ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ኘሮጀክቶች ተቀርፀው ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል አንዱ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ሲሆን፣ በዚህ ረገድ በዋና ዋና ማዕከላት ላይ የሚገነቡ ትልልቅ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ በመካሄድ ላይ ነው። በሌላ በኩል የግብርና ምርቶቻችንን ባለቀለት መልኩ ለማዘጋጀት የሚያግዙ ኢንዱስትሪያዊ ተቋማት የሚስፋፉባቸው በርካታ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት በመካሄድ ላይ ነው። እነዚህን ፓርኮች በአግባቡና በትክክል በመምራትና በማስተዳደር በተለይ ደግሞ የአገራችን ባለሀብቶች አቅም መገንቢያ ሆነው እንዲያገለግሉ በማድረግ ጭምር እሴት ከመፍጠር ፋይዳቸው ባሻገር የግሎባላይዜሽንን ማእከል ለማቋቋም የሚያስችሉን መወዳደሪያ አቅሞች የምንፈጥርባቸው እንደሚሆኑ ይታመናል።


ከዚህ በመነሳት በኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ፖሊሲያችን መሠረት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት በተጠናከረ አኳኋን የሚከናወን ይሆናል። አገራዊ ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን ውስጥ በበቂው እንዲሳተፉ ከማድረግ በማይተናነስ አኳኋን፣ በእነዚህ መስኮች የሚሰማሩ የውጭ ባለሃብቶችም ለአገራዊ ልማት ስትራትጅያችን ተፈፃሚነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ የሚያበረክቱበትን ሁኔታ ማረጋገጥ ያስፈልጋል። በተለይ ደግሞ ፓርኮቹ እጅግ የምንጓጓለትን የቴክኖሎጅ ሽግግር ለማስፈፀም ቁልፍ አስቻይ መድረኮች መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባናል።

 

የተከበራችሁ የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት፣


የተከበራችሁ መላ የአገራችን ህዝቦች፣


ባሳለፍነው ዓመት ከተከሰተው የወጣቶች ጥያቄ ጋር በማያያዝ አስፈላጊነቱ እጅግ ጐልቶ የመጣው የልማት አውድማ በገጠር የኢንዱስትሪ ልማትን የማስፋፋት ጉዳይ ነው። ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ልማትን ለማስፋፋት የትላልቅ ፓርኮች መስፋፋት ጠቃሚና አስፈላጊ ቢሆንም፣ በገጠር የሚገኘውን ሰፊ የወጣት ሃይል አቅም ለመጠቀምም ሆነ በቀላሉ ኢንዱስትሪያዊ ግብዓት አድርገን ልንጠቀምበት የምንችለውን ሰፊ የተፈጥሮ ሃብት ከማልማት አኳያ የገጠር አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪን የሚያክል የለም። የገጠር አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ በኮንስትራክሽንና በአግሮ ኘሮሰሲንግ መስኮች ከፍተኛ እሴት የመጨመር ፋይዳ ያለው እንደሆነ በፍጥነት እያደጉ ካሉ አገሮች ታሪክ በመነሳት ለመገንዘብ ይቻላል። በተለይ ደግሞ የገጠር አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪን የአገራችን ወጣቶች በሰፊው የስራና የሃብት ፈጠራ እድልነት እንዲጠቀሙበት ለማድረግ በርግጥም ዘርፉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትርጉም ያለው እድገትና የህዝብ ተጠቃሚነት ልናረጋግጥ የምንችልበት ነው። በመሆኑም በአገራችን ኢንዱስትሪያዊ ልማትን በማፋጠን ልናመጣው የምንፈልገውን ሽግግር አስተማማኝ ለማድረግ እንችል ዘንድ ለገጠር የአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ልማት የተለየ ትኩረት እንዲሰጠው ይደረጋል። ይህንን ለማድረግም ክልሎች መለስተኛ ከተሞችንና የገጠር ማዕከላትን መሠረት አድርገው ሰፊ እንቅስቃሴ በተቀናጀ ሁኔታ እንዲያከናውኑ ይጠበቃል። የፌዴራል መንግሥትም ሁለንተናዊ የማስፋፀሚያ ድጋፎችን በማድረግ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት በቅንጅት መሥራት ይጠበቅበታል።


ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዳችን በመሰረተ ልማት አውታሮች ግንባታ ልዩ ትኩረት መስጠቱ ይታወሳል። ይህን መነሻ በማድረግ አገልግሎቱን ለማስፋፋት ከሜጋ ኘሮጀክቶች ጀምሮ ከባቢያዊ ፋይዳ እስካላቸው አነስተኛ ልዩ ልዩ የመሰረተ ልማት ኘሮጀክቶች ታቅደው ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛሉ። ከዚህ አንፃር ሲታይ አገራችን የእድገት ደረጃ ላይ ከሚገኝ ከየትኛውም ለተመሳሳይ አገር በላቀ ደረጃ የመሰረተ ልማት ግንባታ በማከናወን ላይ ትገኛለች። በአገራችን በመካሄድ ላይ ያለው የመሰረተ ልማት ግንባታ በተለይ ትልልቆቹ ኘሮጀክቶች ከፍተኛ የገንዘብ ወጭ የሚጠይቁና እስኪጠናቀቁ ድረስም ረዥም ጊዜ የሚወስዱ ናቸው። በዚህ ዙሪያ መንግስት ለእድገታችን አማራጭ የሌላቸውን እንደታላቁ የህዳሴ ግድብና የባቡር ልማት እንዲሁም የመሳሰሉ ኘሮጀክቶች በላቀ ቁርጠኝነት የሚቀጥልባቸው ይሆናል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ያለንን ውሱን አገራዊ ፋይናንስ በሰፊ ኢንዱስትሪያዊና የዘመናዊ ግብርና ሴክተር ላይ የተሰማራ አገራዊ ባለሃብት በተለይ ደግሞ ወጣት ባለሃብት ለመፍጠር በሚያስችለን አቅጣጫ ማሰማራት ይገባናል። እንዲሁም በመሰረተ ልማት ስራዎቻችንና እሴት የመጨመር ቀጥተኛ ፋይዳ ባላቸው ሴክተሮች መካከል የሚኖረውን የኢንቨስትመንት ፋይናንስ ስምሪት ሚዛን እያስተካከሉ መሄድ ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል። ከዚህ በማይተናነስ መልኩ በመንግስት ኘሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ የሚታየውን መጓተትና ብክነት ለመቆጣጠር ከመቸውም ጊዜ የተለየ ትኩረት እንዲሰጥ ይደረጋል። የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ስራ ተቋራጮች ጥራት ያለው ስራ ማከናወናቸውን ከማረጋገጥ ጀምሮ በኮንትራት አስተዳደር ዙሪያ ከውስጥም ከውጭም የሚታዩ ብልሽቶችን በህግ ተጠያቂነት ጭምር በማስተካከል በኘሮጀክቶች ዙሪያ የሚታየውን ጉድለት ለመቆጣጠር እና ለማስተካከል ትኩረት ይሰጣል።

የተከበራችሁ የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት፣


የተከበራችሁ መላ የአገራችን ህዝቦች፣


ከፍ ሲል ከተዘረዘሩት የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ማሳያ ጉዳዮች በመነሳት በያዝነው ዓመት ለየት ያለ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ስራዎችን በአጭሩ ማመላከት ተገቢ ይሆናል። በዚህ ረገድ ከሁሉ በፊት ትኩረት የሚሰጠው የወጣቶችን ችግር ለመቅረፍ ይሆናል። የአገራችን ወጣቶች የወደፊቷ ኢትዮጵያ ገንቢዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ዛሬ በምንገኝበት ወቅት የራሳቸው ፍትሃዊ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ፍላጐትና ጥያቄዎች ያሏቸው በመሆኑ እነዚህን በአግባቡ የመመለስ ጉዳይ ቀዳሚ ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል። ከወጣቶች ጥያቄዎች መካከል ሁሉንም ችግሮቻቸውን አስተሳስሮ የመፍታት እድል የሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ ጉዳይ በመሆኑ ከያዝነው ዓመት ጀምሮ ወጣቶች የስራና የሃብት ፈጠራ እድላቸው በተጨባጭ እውን እንዲሆንና እየሰፋም እንዲሄድ ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል። ይህ ጥረት ይሳካ ዘንድ የፋይናንስ አቅርቦትን ማስፋት፣ አዳዲስ የኘሮጀክት ሃሳቦችን ማመንጨትና አሳታፊ የአፈፃፀም ስርዓት መገንባትን የግድ ይላል።


በዚህ መሰረት መንግስት በያዝነው ዓመት በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶችን ለኢኮኖሚያዊ ልማት ተጠቃሚነት የማብቃት ዓላማ ያለውና ለዚህ ዓላማ ብቻ የሚውል የወጣቶች ተንቀሳቃሽ ፈንድ በማቋቋም ስራውን ይጀምራል። ለዚህም ሲባል ለፈንዱ ማቋቋሚያ የአሥር ቢሊዮን ብር ተመድቧል። የፈንዱን አስተዳደርና አጠቃቀም በተመለከተ በሚወጣው የህግ ማዕቀፍ መሠረት የወጣቶችን ተሳትፎና ቁጥጥር በሚያረጋግጥ ተዘዋዋሪ አኳኋን ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል። ለወጣቶች የስራ መነሻ ይሆን ዘንድ ከተመደበው ፈንድ ጐን ለጐን የስራ ፈጠራው የሚያተኩርባቸው መስኮች የተለዬ በመሆኑ ከወጣቶች ጋር ተመክሮባቸው መግባባት ላይ እንዲደረስባቸው ይደረጋል። መንግስት የወጣቶች ፈንድ አጠቃቀምና የኘሮጀክቶች ትግበራ መሰረተ ሃሳቦችን ከሚመለከታቸው የአመራር አካላትና ከወጣቶች ጋር በመመካከርና ተፈላጊውን የአቅም ግንባታ ድጋፍ በመስጠት የሚያስፈፅም ሲሆን፣ የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተቀየሰው ኘሮግራም በየጊዜው እየተገመገመ አስፈላጊው የማስተካከያ እርምጃ የሚወሰድበት እንዲሆን ይደረጋል።


የፐብሊክ ሰርቪሱን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ከዚህ ቀደም ለሀገራችን መምህራን እና የፍትህ አካላት ዳኞችን ጨምሮ አቅም የፈቀደውን ያህል ማሻሻያ ለማድረግ ጥረት መደረጉ ይታወቃል። የአገራችን ፐብሊክ ሰርቪስ ከእድገታችን ጋር ተመጋጋቢ በሆነ ደረጃ ተጠቃሚ እየሆነ እንዲሄድ ለማድረግ በየወቅቱ የዋጋ ግሽበትን ታሳቢ ያደረገ የደመወዝ ማስተካከያ እየተደረገ መምጣቱም ግልጽ ነው። በዘንድሮ ዓመትም የሥራ ደረጃ ማስተካከያና ለእኩል ሥራ እኩል ክፍያ መርህን የተከተለ የሪፎርም ሥራ ጥናትና የሙከራ ትግበራ እስከ ዓመቱ አጋማሽ በማጠናቀቅ አቅም የፈቀደውን ማስተካከያ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል። በተመሳሳይ መልኩ የመከላከያና የፖሊስ ሠራዊት አካላትን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ ከማስቀጠል ጐን ለጐን የኑሮ ውድነትን ታሳቢ ያደረገ የደሞዝ ማስተካከያ የሚደረግ ይሆናል።


ከፍ ሲል ከተገለፁት የህዝብን ተጠቃሚነት በተለይ ደግሞ በልዩ ሁኔታ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች መብትና ጥቅም ከማስከበር በተጨማሪ የአገራችንን ዴሞክራሲ ለማጐልበት የተለየ እንቅስቃሴ ይደረጋል። ከዚህ አኳያ ቀዳሚው ስራ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል በሚደረግ ድርድር የምርጫ ህጋችንን የማሻሻል ጉዳይ አንዱ ይሆናል። አገራችን የምትመራበት የምርጫ ህግ በብዙ አገሮች እንዳለ የሚሰራበት ቢሆንም፣ ከእኛ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ድምፅ ሊሰማ የሚችልበትን አስተማማኝ ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ ከመገኘቱ ጋር የህግ ማሻሻያ ይደረጋል። ስለሆነም የምርጫ ህጋችን የአብላጫ ድምፅና የተመጣጣኝ ውክልና ስርዓቶችን በትክክለኛ ሚዛን ያጣመረና የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ድምፅ የሚሰማባቸው ምክር ቤቶች እንዲኖሩን ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ እንዲስተካከል ይደረጋል። ይህም በፓርቲዎች መካከል በሚካሄድ የሰጥቶ መቀበል መርህ የሚገዛና አገራዊ ጥቅማችንን ማዕከል ባደረገ ግልፅነትን የተላበሰ የድርድር ሂደት የሚፈፀም ይሆናል።


ከዚህ ጎን ለጎን ዴሞክራሲያችንን ከማስፋት አኳያ በሁሉም ደረጃዎች የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ትርጉም ያለውና ውጤታማ ተሳትፎ የሚያደርጉበት ስርዓት እንዲዘረጋ ይደረጋል። በዚህ ረገድ ከከፍተኛ ጀምሮ እስከዝቅተኛው እርከን ድረስ የሚገኙ የመንግስት ኃላፊዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚኖራቸው ተሳትፏዊ መስተጋብር ህግና ስርዓት እንዲበጅለትና ተጠያቂነትን በሚያረጋግጥ አግባብ እንዲፈፀም ይደረጋል። መንግስት በዚህ ረገድ ያለው አፈፃፀም በቀጣይነት ለባለድርሻ አካላት እየቀረበ የሚገመገምበትና ተፈላጊ የማስተካከያ እርምጃዎች የሚወሰዱበት ስርዓት በስራ ላይ እንዲውል ይደረጋል።


ህገ-መንግሥታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን በሚደነግገው መሰረት ከማንነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ተገቢ ጥያቄዎች በዚህ በጀት ዓመት ውስጥ የተሟላ እልባት እንዲሰጣቸው ይደረጋል። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የአስፈፃሚውን አካል ሥራዎች ውጤታማ ለማድረግ የሚያከናውናቸውን የቁጥጥር ሥራ መልካም ጅምሮች የበለጠ ከማጐልበት በተጨማሪ የተያያዝነውን የዕድገትና ትራንፎርሜሽን ጉዞ ለማሳካት የሚያግዙ አዋጆችን እንደሚያወጣ ይጠበቃል። ከዚህ አኳያ በዘንድሮ ዓመት የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለመደንገግ የሚወጣውን አዋጅ ጨምሮ ሌሎች በርካታ አዋጆች የሚወጡ ይሆናል።

 

የተከበራችሁ የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት፣


የተከበራችሁ መላ የአገራችን ህዝቦች፣


መንግስት በነደፈው መሰረታዊ የለውጥ አቅጣጫ እየተመራ ላለፈው ሩብ ምእተ ዓመት አገራችንን ከማሽቆልቆል ጉዞ አውጥቶ በእድገት ጐዳና እንዳረማመዳት ከመላ ህዝባችን የተሰወረ አይደለም። በተለይ ደግሞ ባለፉት አሰራ አምስት ዓመታት በዓለም ፈጣን የሚባለውን እድገት በማስመዝገብ ስንጓዝ መቆየታችን አያከራክርም። ከዚህ መሰረታዊ ስኬት በመነሳት መላ የአገራችን ህዝብች በሁሉም መስክ የተጀማመሩ መልካም ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ልባዊ ፍላጐት እንዳላቸው መንግስት በጥብቅ ይገነዘባል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አገራችንን ወደ ፊት ባራመድንባቸው በእነዚህ ዓመታት፣ ቀስ በቀስ እያደጉ የመጡ በርካታ ችግሮች እንዳጋጠሙን ይታወቃል። እነዚህ ችግሮች በአንድ በኩል ከፍ ሲል እንደተገለፀው ከእድገታችን ጋር ተያይዘው የመጡ ናቸው።


በሌላ በኩል ደግሞ በየደረጃው በሚገኙ የመንግስት አመራር አካላት ዘንድ በሚታዩ ድክመቶች፣ በተለይ ደግሞ በምግባረ ብልሹነት ምክንያት የተፈጠሩ ችግሮች በወቅቱና በአስተማማኝ ሁኔታ ባለመፈታታቸው የተከሰቱ ናቸው። የመልካም አስተዳደር ችግሮችም ሆነ የህዝባችንን ተጠቃሚነት በተገቢው ደረጃ ያለማረጋገጥ ድክመት በዋነኛነት የምግባረ ብልሹነት ውጤቶች ናቸው። ምግባረ ብልሹነት ደግሞ በመንግስት የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የተቀመጡ ሰዎች የተረከቡትን ህዝባዊ አደራ ለህብረሰባዊ ለውጥ ማምጫ በትጋት የሚሠሩበትን መሣሪያ ማድረግን እየዘነጉ ስልጣንን የኑሮአቸው መሠረት የማድረግ አተያይና በዚህም ላይ የተመሰረተ ተጨባጭ ስህተት ከመፈፀማቸው ጋር ተያይዞ የተከሰተ ውጤት ነው። ይህ መታየት በጀመረበት ጊዜ ሁሉ የእድገታችን ፍጥነት መቀነሱም ሆነ የህዝብ ተጠቃሚነት ለአደጋ መጋለጡ አይቀርም።


መላ የአገራችን ህዝቦች በየአካባቢው ሲመለከተው የቆየውን በስልጣን ካላግባብ የመጠቀም ዝንባሌ እና የህዝብ አገልጋይነት መጓደል መነሻ በማድረግ ቅሬታቸውንና የሚታያቸውን የመፍትሄ ሃሳብ እያቀረቡ ሲታገሉ ቆይተዋል። እነሆ ይህን የህዝብ ትግል መነሻ በማድረግና ጉዳዩን ከልብ በመቀበል መንግስት ባሳለፍነው ዓመት መጨረሻ ራሱን ከዚህ ዝንባሌ ለማፅዳት ቁርጠኛ እንቅስቃሴ ማካሄድ ጀምሯል። በዚህ እንቅስቃሴ ቀደም ሲል የተጀመረውን አገራዊ ህዳሴ ከመቀዛቀዝ አውጥቶ ወደ ቀጣይ የለውጥ ሂደት ለማሸጋገር አንዱ ቁልፍ እርምጃ መንግስታዊ ስልጣንን ወደ ግል ኑሮ ማሻሻያ ለማሸጋገር የሚደረገውን ይህን ዝንባሌና ጥረት ማስቆምና መንግስት በርግጥም የህዝብና የአገር መገልገያ መሳሪያ መሆኑን ማረጋገጥ ነው። ለህዝቡም ብቁና ፍትሃዊ አገልግሎት መስጠት እንዲቻል ማድረግ ነው።


ከዚህ በመነሳት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስራውን በሚጀምርበት ከፊታችን ባለው ወር ውስጥ የፌዴራል መንግስትን የአመራር ሥርዓት በአዲስ መልክና ቅኝት ለማዋቀር ተግባራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ይደረጋል። የፌዴራሉ አካል የሆኑ ክልል መንግሥታትም ተመሳሳይ ቅኝት እንደሚከተሉ ይጠበቃል። በዚህ መሰረት የመንግስት ስልጣንን ካላግባብ የመጠቀም ዝንባሌን የሚገታና ከእንግዲህ በውጤት አልባነት የመንግስት ስልጣን ላይ ተቀምጦ መቆየት የማይቻል መሆኑን የሚያረጋግጥ አዲስ የመንግስት ምክር ቤት የማደራጀት እንቅስቃሴ ይካሄዳል። በዚህ እንቅስቃሴ የተቻለውን ያክል ብቃትና ቅንነት ያላቸውን ግለሰቦች በኃላፊነት ላይ በማስቀመጥ የመንግስት የስራ አፈፃፀም በውጤትና በውጤት ብቻ የሚመራ እንዲሆን ማድረግ ይጀመራል። ይህን ተከትሎ ውጤት ያላመጣ ማንኛውም ሰው በማንኛውም ሽፋን በመንግስት ስልጣን ላይ እንደማይቀጥል የሚያረጋግጥ ቋሚ የአሰራር ስርዓት ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል።

 

የተከበራችሁ የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት፣


የተከበራችሁ መላ የአገራችን ህዝቦች፣


ለማንም ግልፅ እንደሚሆነው አገራችን የምትገኝበት የእድገት ደረጃ ከጥልቅ ድህነት ለመውጣት የሚደረግ መፍጨርጨር ያለበት እና በየጊዜው ዉስብስብ ሁኔታዎች የሚከሰቱበት መሆኑ የማያጠያይቅ ቢሆንም ላለፉት 25 ዓመታት እንደተመለከትነው በሁሉም መስፈርቶች ወደፊት ስንራመድ ቆይተናል። በኢኮኖሚና ማህበራዊ፣ በዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር እንዲሁም በውስጣዊ ሰላምና አለም አቀፍ ግንኙነት መስክ ረጅም ርቀት ተጉዘናል። በመሆኑም በዚህ መድረክ ከተከሰቱት አጠቃላይ ሁኔታዎች በመነሳት በመላ የአገራችን ህዝቦች ትግልና ጥረት የተመዘገቡ ድሎችን በማስጠበቅ፣ መልካም ጅምሮችን ዳር በማድረስና የህዝባችንን ተጠቃሚነት በማስፋት ማሳካት ይገባናል። በሌላ በኩል ደግሞ እድገታችን የወለዳቸው አዳዲስ ተግዳሮቶችን ጨምሮ ከራሳችን የአመራር ድክመት የፈለቁና በአገራችን ፊት የተደቀኑ ችግሮች ደግሞ አስተማማኝ መፍትሔ የሚሹ ሆነው የሚገኙ ናቸው።


እነዚህን ተግዳሮቶች በፈርጅ በፈርጃቸው እየፈቱ መልካሙን ጅምር አጠናክሮ ለማስቀጠል፣ በሁሉም መስክ ሚዛኑ የተጠበቀና ህገ መንግስታዊ ስርዓታችንን በተከተለ አኳኋን የሚካሄድ ትግልን ማጠናከር የግድ ይላል። ሰላማችንን ለማወክ የሚሹ የውስጥና የውጭ ፀረ-ሰላምና አሸባሪ ሃይሎችን በአስተማማኝ ሁኔታ እየመከትን ነገር ግን ደግሞ ተግዳሮቶችና ችግሮችን በአስተማማኝ ደረጃ ለመፍታት የሚያስችል በህገ-መንግስታዊ መርሆዎቻችን በመመራትና በዚሁም በመገዛት የሚካሄደውን ትግል ማጠናከር ይገባናል። አገራችን በጠንካራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ መሰረት ላይ በተገነባችበት በዚህ ወቅት ህገ-መንግስታዊ ስርዓታችንን አስተማማኝ የለውጥ መሳሪያ አድርገን እስከተጠቀምንበት ድረስ በርግጥም ረጅም በማይባል ጊዜ ያሰብነውን ግብ ማሳካት እንደምንችል እምነቴ የፀና ነው።


አመሰግናለሁ

 

የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለው ልዩ ጥቅም በሚመለከት በ1987 ዓ.ም የፀደቀው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የተከበረ ቢሆንም፤ ባለፉት 22 ዓመታት ይህን ሕገመንግሥታዊ መብት ሊተገብር የሚችል ዝርዝር ሕግ ባለመውጣቱ ተግባራዊ ሳይሆን ቆይቷል። ይህም ሆኖ ሕጉ እጅግ ዘግይቶም ቢሆን በትናንትናው ዕለት በሚኒስትሮች ም/ቤት ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተላልፏል። አጠቃላይ የአዋጁን ይዘት የሚዳስሰው መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል።

*** *** ***

 

የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሰፊ ውይይት ካካሄዱበት በኋላ በተወካዮቻቸው አማካይነት ያፀደቁት ህገ-መንግሥት የሁሉንም ሕዝቦች መብቶችና ጥቅምች የሚያስጠብቅ ነው።


ህገ-መንግሥቱም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የቃል-ኪዳን ሰነድ ሲሆን ዓላማውም በሕዝቦች መፈቃቀድና ፍላጎት እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለማጎልበት እንዲቻል በጋራ ያፈሯቸው እሴቶችና ሃብቶች እንዲሁም ትስስሮች እንዳሏቸው በማመን- በታሪካቸው ሂደት ውስጥ ያጎለበቷቸውን የጋራ ጉዳዮች ይበልጥ ለማበልፀግና የተዛቡ ግንኙነቶችንም በማረም አንድ ጠንካራ የጋራ ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ እና የጋራ ፖለቲካዊ ማህበረሰብ ለመገንባትና ለማጠናከር የታለመ ነው።


ይህንን በማድረግም በሀገራችን ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሠፍንና ፈጣንና ህዝቡ በየደረጀው ተጠቃሚ የሚሆንበትን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ለማፋጠን በራሳቸው ፈቃድና በፍላጎታቸው የመረጡት መሆኑን በፅኑ የሚያምኑበት ነው።


የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን ልዩ ጥቅም በህገ-መንግሥቱ እንዲሰፍር ያደረጉት የኦሮሞን ሕዝብ ጨምሮ መላው የሀገራችን ሕዝቦች ናቸው። የመረጡት የፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የፌደራል መንግሥትና የክልሎች መንግስታት እንደሚኖሩ የሚደነግግ በመሆኑ የፌዴራል መንግሥቱ መቀመጫ የሆነች ከተማ መመረጥ ስለነበረበትም የኦሮሞ ሕዝብም ሆነ መላው የሀገራችን ህዝባች በኦሮሚያ ክልል እምብርት ላይ ያለችውን አዲስ አበባ ከተማን የፌዴራሉ መንግሥት መቀመጫ አድርጎ መርጧታል። ይህም በህገ መንግሥቱ እንዲሰፍር አድርገዋል።


ይህንን ውሣኔያቸውን መሠረት በማድረግም በህገ-መንግቱ አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀስ 5 ላይ የሚከተለውን አስፍረዋል፡-

 

“የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሐል የምትገኝ በመሆኗ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል። ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል” በማለት ደንግጓል።


ይህንን የአዲስ አበባን ነዋሪ ሕዝብ ጨምሮ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በጋራ የቃል-ኪዳን ሠነዳቸው ያሰፈሩትን ጉዳይ በዝርዝር ሕግ መመለስ የሚያስፈልግ በመሆኑ የሕገ-መንግሥቱን መንፈስ ተከትሎ ዝርዝሩ እንዲሠራ ተደርጓል። ዝርዝሩን ለመሥራት ግብዓት እንዲሆን በክልሉ ገዥ ፓርቲ ኦህዴድና በኦሮሚያ ክልል፣ በአዲስ አበባ አስተዳደርና በፌዴራል ደረጃ ከተለያዩ አካላት ጋር ውይይቶች ሲካሄዱ ቆይተው በመጨረሻ በኢህአዴግ ሥራ-አስፈጻሚ ደረጃ በዝርዝር ታይቶ የመንግሥት ህጋዊ ተቋማት መክረውባቸው ህግ-ሆኖ እንዲወጣ ስምምነት ላይ ተደርሷል።


በዚህም መሠረት የኢፌዲሪ የሚኒስትሮች ም/ቤት በረቂቅ አዋጁ ላይ በመወያየት የሚከተሉትን ጉዳዮች ተመልክቶ የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት መክሮበት ሕግ ሆኖ እንዲወጣ በትናንትናው ዕለት አስተላልፏል።


ህገ-መንግሥቱ በአንቀጽ 49 ንኡስ አንቀጽ 5 ያስቀመጣቸውን ጉዳዮች


1ኛ/ ከአገልግሎት አቅርቦት ልዩ ጥቅም አኳያ፣


2ኛ/ ከተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምና የአካባቢ ጥበቃ ጋር የተያያዘ ልዩ ጥቅሞች አኳያ፣


3ኛ/ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሐል የምትገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳሰሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ማዕከል በማድረግ የኦሮሚያ ክልል ያለው ልዩ ጥቅምን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ አንቀጾች እንዲቀረፁና እንዲካተቱ ተደርጓል።


የህገ-መንግሥቱ ዋና መነሻም አንድ ጠንካራ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት በምናደርገው ጥረት የፌዴራል መንግሥቱ መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል እምብርት ላይ የምትገኝ ከኒዮርክና ጄኔቫ ቀጥላ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሦስተኛ ማዕከል የሆነች፣ የአፍሪካውያን የፖለቲካና ዲፕለማሲ መዲና የሆነች መሆኗንም ታሣቢ በማድረግና እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሐሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በራሳቸው ፈቃድና በፍላጎታቸው የመሠረቱት የፌዴራል ስርዓት ውስጥ የፌዴራል መንግሥቱ መቀመጫና ሕገ-መንግሥቱ ከመጽደቁ በፊት በሽግግር ወቅትም የክልል 4 ዋና መዲና እንዲሁም ህገ-መንግሥቱ ከፀደቀም በኋላ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ ሆና እየገለገለች ያለች ናት።


ከዚህም ተነስቶ አዲስ አበባ እነዚህን የዓለምአቀፍ፣ የአህጉራዊ እንዲሁም የሀገራዊ ከዚያም አልፎ በፌዴራል ሥርዓታችን መሠረት የኦሮሚያ ክልልን ልዩ ጥቅም አካቶ የያዙ ሃላፊነቶችን መወጣት ያለባት ከተማ እንድትሆን ያደርጋታል። የኦሮሚያ ክልል ልዩ ጥቅም እንዲጠበቅ የሚወጣው ህግም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪያዎችን መብቶችና ጠቅሞች በምንም መልኩ የማይሸራርፍ ይልቁንም የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለው ልዩ ጥቅም በመጠበቁ ምክንያት የአዲስ አበባ አስተዳደር ሕዝብና የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ ትስስርና መስተጋብር ይበልጥ ህጋዊ መሥመር ይዞ እንዲጠናከር የሚያደርግና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብት ይሆናል። የከተማዋና የክልሉ የመንግሥት አካላትና ነዋሪ ሕዝቦችም ዘላቂ ያለው ሰላም እንዲሰፍን ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እና መልካም አስተዳደር እንዲጎለብት እንዲሁም ፈጣንና ሕዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበት ልማት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያስችላል።

 

የአገልግሎት አቅርቦት ጉዳዮችን በተመለከተ፣


በማህበራዊ አገልግሎቶች ልዩ ጥቅም ማለትም ከትምህርት አኳያ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ የአርሦአደሩ ልጆችን እንዲሁም አዲስ አበባ ወይም ፊንፊኔ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ በመሆኗ ምክንያት ልጆቻቸው በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ማስተማር ለሚፈልጉ ዜጎች የከተማ አስተዳደሩ በአፋን ኦሮሞ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ማደራጀት እንዳለበት አስቀምጧል። ከዚህ በተጓዳኝ የአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ላይ ያለው የኦሮሚያ ክልል ነዋሪ አብዛኛውን አገልግሎቱን በተለይም የሆስፒታል አገልግሎቶችን ከከተማዋ የሚያገኝ በመሆኑ በኦሮሚያ እምብርት ላይ የተቆረቆረች ይህች ከተማ ይህንን አገልግሎት ለመስጠት በእቅዷ ውስጥ ማካተት ይኖርባታል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ የአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ የፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን እንዲሆን ተደርጓል።


ከማህበራዊ አገልግሎቶች የሚመደበው ሌላው የባሕል፣ የቋንቋና የሥነጥበብ አገልግሎቶች ሲሆን ከዚህ አኳያም የማህበራዊም ሆነ የኢኮኖሚ አገልግሎቶች ለማቅረብ እንዲቻል ልዩ ጥቅሙን ለማስጠበቅ በዚህ አዋጅ መሠረት አገልግሎት ተጠቃሚ ለሆኑት የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች በቋንቋቸው አገልግሎቱ እንዲቀርብ ከአማርኛ በተጓዳኝ አፋን ኦሮሞ በከተማ አስተዳደሩ የሥራ ቋንቋ ሆኖ የሚያገልግል ይሆናል።


በመግቢያ ላይ ለማመላከት እንደተሞከረው የአዲስ አበባ ከተማ ዓለምአቀፍና አህጉራዊ እንዲሁም ሀገራዊና የከተማ ነዋሪዎቹን ለማገልገል ከምታደርገው ጥረት ባሻገር የኦሮሞ ሕዝብ ማንነት የሚያንፀባርቁ አሻራዎች በከተማዋ ውስጥ በቋሚነት እንዲኖር ከክልሉ ሕዝብ ጋር በተያያዙ ታሪካዊ ክስተቶች ስም መታሰቢያዎች አንዲኖሩ አመቺ የሆኑ እንደ አደባባዮች፣ ጎዳናዎች፣ ሰፈሮች እና የመሳሰሉት ቦታዎች አንደአስፈላጊነቱ በቀድሞ የኦሮሞ ስማቸው እንዲጠሩ ማድረግ ያስፈልጋል። በተጨማሪም የከተማዋ አስተዳደር የኦሮሞ ሕዝብ ባሕልና ታሪክ የሚያንፀባርቁ የባሕልና ታሪክ ማዕከላት፣ ቲያትርና ኪነጥበባትና የመዝናኛ ማእከላት የሚነገቡበትንና የሚተዋወቁበትን ሁኔታዎች የሚያመቻች ይሆናል።


ከኦሮሚያ ክልል ጋር በተያያዘም የከተማዋ ስያሜ ፊንፊኔ ተብሎ ስትቆረቆር በነበረው ስያሜዋ የሚጠራ መሆኑ ይታወቃል። በዓለም አቀፍ፣ በአህጉራዊና በሀገር ደረጃ በፌዴራል መንግሥቱና በአዲስ አበባ አስተዳደር አዲስ አበባ ተብሎ የሚጠራ መሆኑም ግልጽ ነው። ይህም ሕገ-መንግሥታዊ መሠረት ያለው ነው። በሁለቱም እርከኖች ያለው የከተማዋ መጠሪያ ባለበት እንዲቀጥል ማድረጉ ተገቢና ይኼው እንደተጠበቀ ሆኖ የሁለቱም የከተማዋ መጠሪያዎች “ፊንፊኔ” እና “አዲስ አበባ” በሕግ ፊት እኩል እውቅና እንዳላቸው ማስቀመጡ ተገቢ ይሆናል። መሠረታዊ ነገሩን የሚቀይር ባይሆንም የስሞቹን አጠቃቀም ዝርዝር በደንብ መወሰን ያስፈልጋል በሚልም ተቀምጧል።


ለ/ በኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ስለሚኖረው ኢኮኖሚያዊ አገለግሎት ልዩ ጥቅምን በተመለከተ ሲዘረዘር ከመሬት አቅርቦት፣ ከውሃ አገልግሎት አቅርቦት፣ ከፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻዎች የማስወገድ አገለግሎት፣ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ የሥራ እድል አቅርቦት፣ በመንግሥት ወጪ ከሚገቡ የኮንደሚኒየም ቤቶች አቅርቦት እንዲሁም ከገበያ ማእከላት አቅርቦትና አርሶ አደሩ ለልማት ተነሺ ሲሆን በቂ ካሣ የማግኘትና በዘላቂነት የማቋቋም አገልግሎቶችን ያካተተ እንዲሆን ተደርጓል።


እዚህ ላይ ብዥታ ሊኖር የማይገባው ነገር ቢኖር እነዚህ አገልግሎቶች በሚቀርቡበት ጊዜ የኦሮሚያ ክልል አዲስ አበባ ከተማ ከሌሎች ክልሎች በተለየ ሁኔታ ሊጠበቅለት የሚገባው ልዩ ጥቅምን ለማመላከት እንጂ በአዲስ አበባ ነዋሪ ዜጎች ላይ በብሔር ልዩነት ምክንያት የተለየ ጥቅም ለማቅረብ እንዳይደለ ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል። በብሔር ልዩነት ምክንያት በግለሰብ ባለሀብቶች፣ መንግሥት ሠራተኞች ወይም በማናቸውም ዜጎች መካከል ልዩነት አይኖርም።


የመሬት አቅርቦቱም ለክልሉ ለተለያዩ መንግሥታዊ ሥራዎች እና ሕዝባዊ አገልግሎቶች የሚውሉ ሕንጻዎች የሚሠሩበትን መሬት ከሊዝ ነጻ እንዲያገኙ ለተቋማቱ ብቻ የተፈቀደ መሆኑ ግንዛቤ መያዝ ያለበት ይሆናል።


የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመጠጥ ውሃ የሚያገኘው በአብዛኛው በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከሚገኙ የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር መገኛዎች በመሆኑ ከዚህ አኳያ ጉድጓዱ የሚቆፈርበት፣ ግድብ የሚለማበት ወይም የውሃ መስመሩ አቋርጠው የሚያልፍባቸው የክልሉ ከተሞች እና ቀበሌዎች በአስተዳደር ወጪ የመጠጥ ዉሃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚደረግ በሕጉ ተቀምጧል።


የትራንስፖርት አገልግሎትን በተመለከተ የተቀናጀ የትራንስፖርት ስምሪት ኖሮ የሕዝቡን ትስስር ለማጠናከር የአውቶቡስ፣ የታክሲ እንዲሁም የባቡር አገልግሎት መሠረተ-ልማትና አገልግሎቶች ስምሪት የተቀናጀና በዙሪያው ያሉ ከተሞችንም ያማከለ እንዲሆን ለማድረግ በአዋጁ ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል።


በአዲስ አበባ ጋር በተያያዘ በዙሪያ ያሉ ወጣቶች በተቀናጀ ሁኔታ የሥራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሌሎች በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉት አካባቢዎች አዲስ አበባ የሚሠራቸው ሥራዎች ለዙሪያ ወጣቶች የሥራ እድል እንዲያመቻች በእውቀትና በእቅድ የተመሠረተ ሥራ መሠራት ያለበት ይሆናል።


የአዲስ አበባ ከተማ በኦሮሚያ ክልል እምብርት ላይ ያለች በመሆኑ በዙሪያዋ በግብርና ሥራ የሚተዳደሩ አርሶአደሮች ይገኛሉ። እነዚህ አርሶ አደሮች ለአዲስ አበባ ከተማ የምግብ እህል በማቅረብ የከተማዋን ሕዝብ ኑሮ ደግፎ የያዙ ናቸው። አርሶ አደሮችም በቀጥታ ከምርቶቻቸው ተጠቂሚ እንዲሆን የመሐል ደላሎችን አስወግደው በቀጥታ ከሸማቹ ጋር በግብይት ሰንሰለት እንዲተሳሰሩ የከተማ አስተዳደሩ ምርቶቻቸውን የሚሸጡባቸውን የገበያ ቦታ በማዘጋጀት በራሱ ወጭ የግብይት ማእከላትን አቋቁሞ ለአርሶ አደሮቹና ማህበሮቻቸው እንዲያቀርብ እንዲደረግ በአዋጁ የተቀመጠ ጉዳይ ነው።


የከተማ አስተዳደሩ ከባንኮች ጋር በመተባበር የማህበራዊ ቤቶች የሆኑትን የኮንደሚኒየም ቤቶች አስገንብቶ ከነዚህ ውስጥ በከተማው ላሉ የመንግሥት ሠራተኞትና ሴቶች በኮታ በእጣ ወስጥ ገብተው እንዲወዳደሩ የደርጋል። በተመሳሳይ መልኩ ለኦሮሚያ ክልል መንግሥት ሠራተኛ ሆነው በከተማው ውስጥ ለሚኖሩትም ተመሳሳይ እድል እንዲሰጥ በአዋጁ ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል።


በከተማው ውስጥ ለበርካታ ጊዜያት የኖረው የኦሮሞ አርሶአደር ቁጥሩ ቀላል ባልሆነ ሁኔታ በልማት ምክንያት ተነሺ ነበር። አሁንም ለልማቱ ተፈላጊ እስከሆነ ድረስ በማሳመን ይህንኑ መፈፀም የሚገባን ይሆናል። ዋናው ቁም ነገር ይህ ተነሺ አርሶአደር ቢያንስ ቢያንስ ከቀድሞ ኑሮ የተሻለ ሁኔታ ሊፈጠርለት ይገባል። በልማቱ ማስፋፋት ምክንያት ተጎጂ ሊሆን በጭራሽ አይገባም። በዚህ መሠረት ለወደፊቱ በቂ ካሣና በዘላቂነት የሚቋቋምበት ሁኔታ እንዲመቻችለት፣ ከዚህ በፊት የተሠራውም ሥራ ተፈትሾ ጉድለቶች እንዲስተካከሉ፣ እነዚህን ሥራዎች የሚያስተባብር የሚመራና የሚያስፈጽም ጽ/ቤት እንዲደራጅ በአዋጁ እንዲካተት ተደርጓል።


የኦሮሚያ ክልል በከተማው ስለሚኖረው የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምና የአካባቢ ጥበቃ ልዩ ጥቅም፣


ከከተማው መሠረተ-ልማት አቅርቦት፣ ከመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ከደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ጋር የተያያዘ በተፈጥሮ ሃብት ላይና በአየርና ውሃ ላይ የሚደርስ ብክለት እንዳይኖር የሚያደርግና ይህንን መብት የማስጠበቅ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሊሠጠው እንደሚገባ ታመኖበታል። ከዚህ አኳያ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ያሉ ከተሞችና ቀበሌዎች ከከተማው ከሚወጡ ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻዎች ከሚደርሱ የአካባቢ ብክለትና ጉዳት የመጠበቅ መብት እንዳላቸው፣


ከአዲስ አበባ ከተማ በሚወጡ ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻዎች ከሚደርሱ የአካባቢ ብክለትና ጉዳት የክልሉን ከተሞችና ቀበሌዎች ለመጠበቅ የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ እንዲካሄድ እንደሚደረግ፣ ቆሻሻን መልሶ የመጠቀም ሥርዓት እንደሚዘረጋ፣


በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ያሉ ከተሞችና ቀበሌዎች ደህንነቱ ሳይጠበቅና ቁጥጥር ሳይደረግበት ከተቀመጠው ደረጃ በላይ ወደ ክልሉ በተጣሉ ወይም በፈሰሱ ቆሻሻዎች ምክንያት በሰው፣ በእንስሳትና በተፈጥሮ አካባቢ ላይ ለደረሰው ጉዳት በሕግ አግባብ ከአስተዳደሩ ካሳ የማግኘት መብት እንደሚኖራቸው፡


ለአዲስ አበባ ከተማ ልማት የግንባታ ማእድናት ማግኛ ሥፈራዎች የአየር ብክለት እንዳያስከትሉ እና ለደን ልማት ወይም ለሌሎች ልማቶች መዋል እንዲችሉ እንዲያገግሙ አንደሚደረጉ፣


ለአዲስ አበባ ከተማ የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ ማከሚያና ማስወገጃ ቦታዎች እንዲሁም መልሶ መጠቀሚያ ስፈራዎች አስተዳደሩና ክልሉ በጋራ ባጠኗቸወ ቦታዎችና ሳይንሳዊ መስፈርቶችን ባሟሉ ሁኔታዎች እንዲተዳደሩ አንደሚደረጉ በአዋጁ በዝርዝር እንዲካተት ተደርጓል።

 

ተቋም ስለማደራጀት


በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 14 በአስተዳደሩ ውስጥ በልማት ምክንያት የሚፈናቀሉ የኦሮሞ ብሔር አርሶ አደሮች ዘላቂ መቋቋሚያ የሚሆን ካሣ የማግኘት መብታቸውን ለማስከበር እና ከዚህ በፊት በልማት ምክንያት የተፈናቀሉ እና በቂ ካሣ ያላገኙ የኦሮሞ ብሔር አርሶ አደሮች በጥናት ላይ የተመሠረት የማስተካከያ ሥራ ለመስራት ከሚቋቋመው ጽ/ቤት በተጨማሪ አዋጅ ውስጥ የተጠቀሱትንና ሌሎች የጋራ ጉዳዮችን ክልሉ አና አስተዳደሩ የሚወያዩበትና የሚወስኑበት ተጠሪነቱ ለፌዴራል መንግሥት የሆነ ከአስተደደሩና ከክልሉ ምክር ቤት የተውጣጣ የጋራ ምክር ቤት እንደሚቋቋም ተመለክቷል።


የምክር ቤቱ ዋና ዓላማውም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49/5/ መሠረት የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦተ፣ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ፣ እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማ በኦሮሚያ ከልል መሐል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ በዚህ አዋጅ የተዘረዘሩትን ልዩ ጥቅሞች በተጨባጭ ተግባራዊ እንዲሆን መከታተል፣ መገምገምና ለአፈጻጸሙ ቅልጥፍና ድጋፍ ማድረግ ይሆናል።


የምክር ቤቱን አባላት በተመለከተ ከአስተዳደሩ ምክር ቤትና ከክልሉ ምክር ቤት በእኩል ቁጥር የሚወከሉ እንደሚሆን፤ ዝርዝር የምክር ቤቱ አወቃቀር፣ ተግባርና ሀላፊነት፣ የሥራ ዘመን፣ የስብሰባ ሥነ ሥርዓት የአባላት ሥነ ምግባር እና በጀት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣ ደንብ እንደሚወሰን ተመልክቷል።


ማጠቃለያ


በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ /5/ የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሐል የምትገኝ በመሆኗ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል። ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል በማለት ይደነግጋል። የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ በሥራ ላይ ለማዋል እና የኦሮሚያ ክልልን ልዩ ጥቅም ለማስጠበቅ ዝርዝር ሕግ ለማውጣት ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተው ይህ ረቂቅ አዋጅ ሊዘጋጅ ተችሏል። በረቂቅ አዋጁ ዝግጅት ሂደት ውስጥ የኦሮሚያ ክልል ገዥ ፓርቲ ኦህዴድ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የመንግሥት ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ተሳትፈውበታል። በአዋጁ የመጽደቅ ሂደትም በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሣተፉበት ይሆናል።


ዋናው ጉዳይ ይህ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ መላው የአገራችን ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተስማምተው ያፀደቁት ድንጋጌ ነው። በመሆኑም መላውን የሐገራችንን ሕዝቦች ተጠቃሚ የሚያደርግና የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችን የበለጠ ጥልቀት እንዲኖረውና ሕዝቦች በመከባበርና በመፈቃቀድ ለሐገራችን ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሁም መልካም አስተዳደር ለማስፈንና ፈጣንና ሕዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበትን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ለማረጋገጥ ይረዳናል። ይህን ልዩ ጥቅም በዝርዝር አዋጁ ማውጣቱ የማንንም ሕዝብ እንዲሁም የአዲስ አበባን ነዋሪዎች መብትና ጥቅም በማይጋፋ መንገድ በህገ መንግሥቱም የተቀመጠ በመሆኑ ይኸው በዝርዝሩ ሕጉም በጥንቃቄ የተሠራ ነው። ጉዳዩ ከሁሉም ሕዝቦች ጥቅም አኳያ ተዘርዝሮ የተዘጋጀ ነው። 

“በኦዲት ግኝቱ ላይ ተጠያቂነትን ለማስፈን

ፓርላማው ተግቶ ይሰራል”

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፅ/ቤት

የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

ሰንደቅ ጋዜጣ ግንቦት 30 ቀን 2009 ዓ.ም በረቡዕ ዕትሙ ወቅታዊ በሚል ዓምድ ስር በገፅ 3 ላይ ‘የፌዴራል ዋና ኦዲተር ሪፖርቶችና የፓርላማው ዝምታ’ በሚል ርዕስ አንድ ፅሑፍ በጋዜጣው ሪፖርተር ለንባብ አብቅቷል። የፅሁፉ ማጠንጠኛ የመንግስትን የፋይናንስ ሕግና ደንብ የተላልፉ ተቋማትን ፓርላማው ተጠያቂ ለማድረግ በዋናው ኦዲተር በተነሱ ጉዳዮች ላይ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ  ዝምታን መርጧል የሚል ነው፡፡

የፅሁፉ መነሻ ግንቦት 22 ቀን 2009 ዓ.ም በምክር ቤቱ 35 መደበኛ ስብሰባ ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ያቀረበው የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶች የ2008 በጀት ዓመት ሂሳብና ክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ነው፤ ስለ ጉዳዩ አንባቢ ትክክለኛውን ግንዛቤ እንዲይዝ ማድረግ ተገቢና አስፈላጊ በመሆኑ፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፅ/ቤት የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሸን ዳይሬክቶሬት ከህግና አሰራር አንፃር ምላሽ ለመስጠት ይህን ፅሁፍ አሰናድቷል፡፡

 

የህግ ማዕቀፍ

ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤትን እንደገና ለማቋቋም በወጣው የአዋጅ ቁጥር 982/2008 መሰርት በመንግስት መዋቅር ውስጥ በሚገኙ ልዩ ልዩ መስሪያ ቤቶች ላይ ኦዲት ያደርጋል። የኦዲት ግኝት ለምክር ቤቱ ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል፤የዚህ ዋነኛ አላማም በመንግስት ፋይናንስ አሰራር ላይ ተጠያቂነት፣ ግልፅነትንና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ሲሆን፤ የኦዲት ሪፖርት መቅረብ በመንግስት ፋይናንስ አሰራር የገንዘብ አጠቃቀምና ንብረት አያያዝ ምን አንደሚመስል  ከማስገንዘብ ባሻገር ክፍተቶች ካሉ በቀጣይ ሊወሰዱ ሰለሚችሉ እርምቶች መፍትሄ ለማበጀት አስፈላጊነቱ አጠያያቂ አይሆንም፡፡ በህገ መንግስቱ ድንጋጌ መሰረት የመንግስት ተቋማት የኦዲት ግኝት ለሕዝብ ግልፅ እንዲሆን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን  እንዲዘግቡት ተደርጎ ለህዝብ ተደራሽ ይሆናል፡፡

ቀጣይ ተግባር የሚሆነው ጥፋተኞችን ተጠያቂ ማድረግ ነው፡፡ ተጠያቂነትን ለማምጣት የተቀመጡ የህግ ማዕቀፎች አሉ፡፡ አንዱ የፌዴራል ዋና ኦዲተርን ስልጣንና ተግባር የሚደነግገው የአዋጁ አንቀፅ 5 ንዑስ አንቀፅ 6 ነው፡፡ የዋና ኦዲተሩ የምርመራ ውጤት ወንጀል መፈፀሙን የሚያሳይ ሆኖ ሲገኝ ለሚመለከተው አካል ወዲያውኑ እንዲያሳውቅ ድንጋጌው ያስገድዳል፡፡ የሚመለከተው አካል የሚባሉትም በአዋጁ አንቀፅ 20 ንዑስ አንቀፅ 2 መሰረት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የጠቅላይ አቃቤ ህግና የኦዲት ተደራጊው መስሪያ ቤት ወይም ድርጅት የበላይ ኃላፊዎች ናቸው፡፡ ዋናው ኦዲተር ይህን የህግ ማዕቀፍ የተመለከተ ሪፖርት ለምክር ቤቱ አላቀረበም፡፡ ዋና ኦዲተሩ በዕለቱ ለምክር ቤቱ ያቀረቡት መደበኛ ሪፖርታቸውን ነው። ሪፖርቱ መደበኛ በመሆኑ ህጉ ያስቀመጠውን አቅጣጫ ተከትሎ መስራትን ይጠይቃል፡፡ ሌላኛው የህግ ማዕቀፍ አንቀፅ 17 ንዑስ አንቀፅ 3 ነው፡፡ ይህ ንዑስ አንቀፅ ተመርማሪ መስሪያ ቤቶች በፌዴራል ዋና ኦዲተር በተላኩ ሪፖርቶች በተገለፁ ግኝቶች ላይ ተገቢውን የእርምት እርምጃ እንዲወስዱ በተሰጡ የማሻሻያ ሃሳቦችና አስተያየቶች መሰረት ከ15 ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ እርምጃ እንዲወስዱ ግዴታ ይጥልባቸዋል፡፡

አንዱ ተጠያቂነት ማለት በተሰጠው አስተያየት መሰረት ጉዳዮችን ማስተካከል ማለት ነው፡፡ ይህም የሚመለከተው ተመርማሪ መስሪያ ቤቶችን ይሆናል፡፡ አንቀፅ 17 ንዑስ አንቀፅ 4 ደግሞ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚያቀርበው ሪፖርት ውስጥ ድክመት የታየባቸው ኃላፊዎች በታዩት ድክመቶች ላይ አስፈላጊውን የማስተካከያ እርምጃ ወስደው ይህንኑ ለምክር ቤቱና ለፌዴራል ዋና ኦዲተር እንዲያሳውቁ ግዴታ ይጥልባቸዋል፡፡

ዋናው ኦዲተር ሪፖርታቸውን ምክር ቤቱ ያቀረቡት በ35ኛ መደበኛ ስብሰባው  ግንቦት 22 ቀን 2009 ዓ.ም መሆኑ ይታወሳል። ተመርማሪ መስሪያ ቤቶች ማስተካከያ እርምጃ እንዲወስዱ በህጉ የተሰጣቸው 15 የስራ ቀናት ናቸው፤ ይህም እስከ ሰኔ 13 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ የየመስሪያ ቤቶቹ ኃላፊዎች የተወሰደውን እርምጃ ማሳወቅ ይጀምራሉ፡፡ ይህም ቢሆን በቂ ምክንያት ካለ ጊዜው ሊራዘም እንደሚችል የአዋጁ አንቀፅ 21 ንዑስ አንቀፅ 1/መ ይደነግጋል፡፡

አሰራሩ እንደዚህ በግልፅ ተቀምጦ ሳለ ገና ሰኔ 13 ቀን 2009 ዓ.ም ሳይደርስ ጋዜጣው በግንቦት 30 ቀን 2009 ዓ.ም እትሙ፤ ስለ “ፓርላማው ዝምታ” ማንሳት ተገቢ ያልሆነ፤ ሳይደወል ቅዱስ የሚሉት ነው፡፡ ተመርማሪ መስሪያ ቤቶች ህጉ ያስቀመጠላቸው ጊዜ ገደብ መች ተጠናቀቀ? ሌሎች ሂደቶች መኖራቸውንም መረዳት ያስፈልጋል።የጋዜጣው ሪፖርተር ትችት ለመሰንዘር የቸኮሉ ናቸው፤ህጉንና የምክር ቤቱን አሰራር የሚያውቁት አይመስለንም፡፡

ፓርላማው በቀደሙት ዓመታት የኦዲት ግኝት ተፈፃሚ እንዲሆኑ ያደረገውን ጥረት በተወሰነ ደረጃ ማየት ይቻላል፤

 

የ2005 በጀት ዓመት

የፌዴራል ዋናው ኦዲተር መ/ቤት የ2004 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት መሥሪያ ቤቶች የሂሳብና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ሚያዚያ 22 ቀን 2005 ዓ.ም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል። ኦዲቱ የ124 የፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶችን በማካተቱ የዋናው ኦዲተርን ኦዲት ማድረግ ሽፋን ወደ 96.12 በመቶ እንዳሳደገው በሪፖርቱ ተመላክቷል።

የዚህ ኦዲት ሪፖርት ግኝቶች ምንድ ናቸው? በአሁኑ ግኝት ከተመለከቱ ችግሮች ጋር ተመሳሳይነት ስላለው ዳግም ማንሳቱ አስፈላጊ አይደለም። የፌዴራል ዋናው ኦዲተር ለችግሮች ምን መፍትሔ ጠቁሟል? ጉድለቱ ተጣርቶ እንዲስተካከል፣ ያልተወራረዱ ሂሳቦች በፋይናንስ ደንብና መመሪያ መሠረት እንዲወራረዱ፣ ያልተሰበሰቡ ገቢዎች እንዲሰበሰቡ፣ ግዥ የመንግስትን ግዥ ደንብና መመሪያ ተከትሎ እንዲፈፀም፣ ያለአግባብ የተከፈለ ገንዘብ ለመንግስት ካዝና ተመላሽ እንዲሆን እና ሌሎች ተመሳሳይ ማሳሰቢያዎችም  ተሰጥተው ነበር።

ግኝቱንና ማሳሰቢያውን የተከታተሉ የምክር ቤት አባላት ምላሽ፤ በአጭሩ “በደንብና መመሪያ የማይሠሩትን አካላት እስከ መቼ እንታገሳቸዋለን?’’ የሚል ይገኝበታል። ሪፖርቱ በቀረበበት ዕለት ከምክር ቤት አባላት የተነሱ ጥያቄዎችንና አሰተያየቶችን በዚህ ፅሁፍ በስፋት ማቅረብ አመቺ ባይሆንም፤ በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ የመንግስት ወጪ አሰተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበው አስተያየት ምክር ቤቱን ስለሚወክል በአጭሩ  ማቅረብ ይቻላል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተርን ከመደገፍ አንፃር ምክር ቤቱ ማድረግ ከሚገባቸው ተግባራት አንዱ ‘… በተለይ ሂሳብ በማይዘጉና ለኦዲት ተባባሪ ለማይሆኑ ኦዲት ተደራጊ መ/ቤቶች ኃላፊነትን ካለመወጣት ባሻገር ህግም እየተጣሰ ስለሆነ፤ ምክር ቤቱ በዝምታ ማለፍ ስለሌለበት በቀረበው ሪፖርት መሠረት ርምጃ ሊወስድ…’ እንደሚገባ የሚያሳስበው ነው። ሌላው ‘... በቋሚ ኮሚቴዎች ተለይተው የሚቀርቡ የህግ ጥሰትና የሀብት ብክነት የከፋ ችግር አለባቸው በተባሉ አስፈፃሚ መ/ቤቶች ላይ ምክር ቤቱ ከሚመለከታቸው ጋር ተነጋግሮ ተገቢ ውሳኔ እንዲያገኙ ካላደረገ የምክር ቤቱ የቁጥጥርና ክትትል ስራ ውጤታማ ሊሆን ስለማይችልና የኦዲት ስራንም ዋጋ ስለሚያሳጣ ሪፖርቱ ተገቢውን ውሳኔ ያግኝ...’ የሚለው አስተያየት ሁለተኛው ነበር። ሶስተኛው አስተያየት ደግሞ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች ሚከታተሏቸው  አስፈፃሚ ተቋማት በሪፖርቱ መሠረት የማሰተካከያ እርምጃ ስለመውሰዳቸው ማረጋገጥና መከታተል እንደሚገባቸው የሚያሳስብ ነው።

የማስተካከያ እርምጃዎች ስለሚወሰዱበት ሁኔታ የሚገልፅ መግለጫ በቀድሞ የገንዘብና ኤኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ፊርማ ለምክር ቤቱ ቀርቧል። ይህን መግለጫ ምክር ቤቱ በአራተኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ የአንደኛ መደበኛ ስብሰባው አጀንዳ አድርጎ በስፋት ተወያይቶበታል።

 መግለጫው ምን ምን ነጥቦችን በውስጡ ይዟል? ለወደ ፊቱ መወሰድ ስላለበት የማስተካከያ እርምጃ ሪፖርት የሚያቀርብ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሪፖርት ማቅረቡን መግለጫው ያመለክታል። ለኦዲት ግኝቱ የህግና የሥርዓት ክፍተቶች የሌሉ ስለመሆናቸውና ክፍተቱም የአፈፃፀም ችግሮች ስለመሆናቸው ይገልፃል። በሶስተኛ ደረጃ  የኦዲት ተደራጊ ባለበጀት መ/ቤቶችን እና የገንዘብና ኤኮኖሚ ልማት ሚኒስቴርን ችግሮች ይዘረዝራል። የሚኒስቴሩ ችግሮች ረጅም ዓመታትን ያስቆጠሩ፤ሊሰበሰቡ ባልቻሉ ሂሳቦች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ የተደረገው እንቅስቃሴ አጥጋቢ ያለመሆኑንና በከፍተኛ ትምህርት አዋጅና በመንግስት የፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ መካከል ያለውን የግንዛቤ ችግር ለማስተካከል ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በቂ እንቅስቃሴ አለመደረጉ ነው የሚገልፀው። የመጨረሻው የመፍትሔ ሀሳብና የተወሰዱ እርምጃዎችን የሚያመለክት ነው።

የመፍትሔ አስተያየቶቹና የተወሰዱት እርምጃዎች ምንድናቸው? በመፍትሔዎቹ በኩል ሕጎቹን በሚመለከት የግንዛቤ ማስጨበጫና አጫጭር ሥልጠናዎችን ለዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች እንዲሁም ለማሰልጠኛ ተቋማት መስጠት፣ ግልፀኝነትን መፍጠርና ደንብና መመሪያ እንዲዘጋጅና ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ እንደመፍትሔ ተወስዷል። እነዚህ ተግባራት የሚፈፀሙበት የጊዜ ሠሌዳም በመግለጫው  ሰፍሯል።

ተመርማሪ መ/ቤቶች የማሰተካከያ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችላቸውን መርሐ ግብር አዘጋጅተው እንዲያቀርቡ ማድረግና በዚሁ መሠረት ክትትል ማድረግ ሌላው የመፍትሔ አስተያየት ነው። ሌላው አስተያየት የውስጥ ኦዲት እንዲጠናከር ለመንግስት የውሳኔ ሃሳብ ማቅረብ የሚል ነው። እንደዚሁም ረጅም ጊዜ የቆዩ ሂሳቦችን ለመለየት ጠንካራ የሥራ ክፍል በአስቸኳይ መመስረት እና ስለውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብ ለአፈፃፀሙ መመሪያ ማስተላለፍ የሚሉ የመፍትሔ ሃሳቦች የሚሉት ናቸው።

እስከአሁን ስለተወሰዱ እርምጃዎች አራት ነጥቦች የተቀመጡ ሲሆን አንዱ እርምጃ ተመርማሪ መ/ቤቶች በድርጊት መርሐ ግብሩ መሠረት ግኝቱን ስለመፈፀማቸው የሚከታተል አንድ ቡድን መቋቋሙ ነው። ሌላው ሥልጠናና ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በ2006 በጀት ዓመት ዕቅድ መካተታቸውና ለመንግስት የሚቀርበውን የውሳኔ ሃሳብ የሚያዘጋጁ ሶስት የቴክኒክ ኮሚቴዎች መቋቋማቸው ከተወሰዱት እርምጃዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ  ናቸው።

በዚህ መግለጫ ላይስ የምክር ቤት አባላት ምን ምን አስተያየቶችን አቀረቡ? እንዴትስ ሊያስፈፅሙት አሰቡ? የህግና የሥርዓት ክፍተት ስለመኖሩ ከምክር ቤቱ አባላት አስተያየት ተሰንዝሯል። የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 650/2001 ከመንግስት የፋይናንስ አስተዳደር አዋጅና ደንብ ጋር ለአፈፃፀም ግልፅ አለመደረጉ፣ ደንብና መመሪያ ያልወጣለት መሆኑ ሚ/ር መ/ቤቱ  እንደ ችግር  ከወሰደ፤ ይህም የሕግ ክፍተት መኖሩን ማስቀመጥ እንደሚያስችልና በደንብና መመሪያ የሚሞሉ ክፍተቶች እያሉ  ክፈተቶቹን በግንዛቤ በመፍጠሪያ መድረኮች ለመፍታት የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጡ ትክክል እንዳልሆነ  ያመለከተ አስተያየት ቀርቧል።

የሚያስከስሱ ጉዳዮች እያሉ መግለጫውን አጠቃልሎ ማቅረቡ ትክክል እንዳልሆነ አስተያየት የቀረበ ሲሆን፤ ችግሩን ከአፈፃፀም ጋር ብቻ ማያያዙ ተጠያቂነትን ስለሚያሳጣና የሕግ ጥሰት በሕግ ስለሚያስቀጣ መግለጫው ይህንንም መያዝ እንደነበረበት አስተያየት ተሰጥቷል።

የሚኒስቴሩን መግለጫ በንባብ ያቀረቡት የተከበሩ አፈ-ጉባኤ አባዱላ ገመዳ በበኩላቸው መግለጫው የኦዲት ግኝቱ የሚስተካከልባቸውን መፍትሔዎች እና የአፈፃፀም ጊዜ ሰሌዳ ጭምር በማስቀመጡ ትልቅ ትርጉም ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል። ሕግ የጣሱትን ከተጠያቂነት የሚከለክል አንዳችም ነገር በሪፖርቱ እንዳልተጠቀሰ ከማመልከታቸው ባሻገር በፋይናንስ ሕጋችንም ለክፉ የሚሰጥ ክፍተት እንደሌለ በአስተያየታቸው ጠቁመዋል።

በመግለጫው ላይ የተደረገው ውይይት ሲጠቃለል የመግለጫውን ተፈፃሚነት በዋናነት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲከታተሉ ሲመራላቸው፤ ሌሎች ቋሚ ኮሚቴዎችም የሚከታተሏቸውን መ/ቤቶች የመግለጫውን አፈፃፀም በሥራ አፈፃፀም ሪፖርታቸው አካተው እንዲያቀርቡና ክትትል እንዲያደርጉ ምክር ቤቱ አስምሮበታል። ይህ ጥረት ምን ውጤት አስገኘ? ጥረቱ የህግ ማሻሻያ እንዲደረግ የራሱን አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ የፋይናስ አስተዳደር አዋጁ ሲወጣ የዩኒቨርሲቲዎች የውስጥ ገቢ አሰባሰብና አጠቃቀም በህግ የታገዘ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ የውስጥ ኦዲት እንዲጠናከር፤ የውስጥ ኦዲተሮች ተጠሪነት ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር እንዲሆንም ይህ አዋጅ ደንግጓል፡፡ ይህ የሚያሳየው የህግ ክፍተቶችን በመሙላት ችግሮችን እንዲፈታ ምክር ቤቱ የሄደበትን ርቀት ነው፡፡

በቁጥጥርና ክትትል በኩል ከምንግዜውም በላይ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከዋናው ኦዲተር ጋር በመሆን ተመርማሪ መስሪያ ቤቶች ስለወሰዱት የማስተካከያ እርምጃ የህዝበ አስተያየት መስጫ መድረክ በማዘጋጀት ሪፖርት እንዲያቀርቡ እያደረገ ይገኛል፡፡ ከአንዳንድ ሃላፊዎች ጋር እልህ አስጨራሽ ትግል የተስተናገደበት መድረክ ተስተውሏል፡፡ እያንዳንዱ ቋሚ ኮሚቴም አስፈፃሚ ተቋምን ሲገመግም የኦዲት ግኝት ሪፖርትን በመያዝ ነው፤ ይህ ከክትትልና ቁጥጥር አንፃር ትልቅ እምርታ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በእርግጥ የአገሪቱ የፋይናንስ ችግር ከኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት የሚመነጭ በመሆኑ ስርነቀል ለውጥ ለማምጣት የፓርላማ ትግል ብቻ በቂ አይሆንም፤ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ቁርጠኛ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርላማውን እንደሚተባበሩ የ2009 በጀት ዓመት የመንፈቅ ዓመት ሪፖርታቸውን ሲያቀርቡ፤ በችግሩ አሳሳቢነት ላይ ጥያቄዎች ተነስተው በኦዲት ግኝት ላይ ተመስርቶ እርምጃ የማይወስዱ ኃላፊዎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ለምክር ቤቱ ቃል መግባታቸው ይታወሳል፡፡ይህ ተፈፃሚ እንዲሆን ምክር ቤቱም የበኩሉን ይጥራል፡፡

ለመቋጨት የኦዲት ግኝት ተፈፃሚነት ላይ የፓርላማ ዝምታ አይኖርም፤ ኖሮም አያውቅም። ህገ መንግስታዊ ተልዕኮ ያለው ተቋም በመሆኑ ሪፖርት አድምጦ ከንፈር የሚመጥ (Lip Service) አይደለም፤ ተግባር ከንግግር ይበልጣል እንደሚባለው ምክር ቤቱ በሕዝብ ወገንተኝነት ስሜት የአገሪቱን የፋይናንስ ህግ ጠብቀው በማይሰሩ ኃላፊዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፤ እደረገም ነው፡፡ ይህ ሲባል ግን በቂ ስራ ተሰርቷል ለማለት አይደለም፤እንደ ምክር ቤትም ሆነ እንደ መንግስት የሚቀሩ ስራዎች መኖራቸው ይታመናል፤ ሆኖም በጥቅሉ ፓርላማው ምንም እንዳልሰራ አስመስሎ ከመፃፍ ይልቅ ሚዛናዊ ሆኖ ጥንካሬዎችንም ማንሳት ቢችሉ ተገቢና ጠቃሚ ተግባር ነው፤ በእርግጥ የጋዜጠኝነት ሙያ አንዱ መርህ ሚዛናዊነት ያለው ዘገባ ማቅረብ ስለሆነ፤ ጋዜጣውም ሆነ የጋዜጣው ሪፖርተር የምክር ቤቱን ዘገባ ለህዝብ ተደራሽ ሲያደርጉ ሚዛናዊነትን ቢላበሱ መልካም ነው እንላለን።¾

Page 1 of 14

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us