የወልድያ ውበት የሀገር ኩራት ስታዲየምና የስፖርት ማዕከል

Wednesday, 28 December 2016 14:33

በኪነ ጥበባዊ ስራዎች የምትወደሰውና በእግር ኳሱ አይረሴ ተጫዋቾችን ያበረከተችው ወሎ አሁን ደግሞ በልዩነት የምትጠራበት ሌላ የሀገር መገለጫ አግኝታለች። በሰሜን ወሎ ወልዲያ ከተማ ልዩ ስሙ “መቻሬ ሜዳ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ግዙፍ ስታዲየምና የስፖርት ማዕከል ተገንብቷል።  የከተማዋ ሞገስ የህዝቧም ኩራት ሆኗል። የዚህ ፕሮጀክት እውን መሆን ደግሞ ለነዋሪዎቿ ደስታን የሚያጎናጽፍ ነው።

በእርግጥ ደስታና ኩራቱ ለወልድያና አካባቢው ነዋሪዎች ብቻ አይደለም። ደረጃቸውን በጠበቁ የስፖርት ሜዳዎች እጦት ለተቸገረው መላው የስፖርት አፍቃሪም ነው። ከጥቂት አመታት በፊት በደረቅ ሳር የተሸፈነውና ወጣ ገባ በሆነው በመቻሬ ሜዳ ለስታዲየም ግንባታ መሰረተ ድንጋይ ሲጣል እቅዱ የመሳካቱ ነገር አጠራጣሪ ነበር።

በወልድያና አካባቢው ህዝብ አስተባባሪነት ለመገንባት የታቀደው ስታዲየም መጀመሪያ ላይ መሰል ፕሮጀክቶች የገንዘብ ችግር ዋነኛ መሰናክሉ ነበር። ከህዝቡ የሚሰበሰበው መዋጮ ብቻ ግንባታውን ከዳር የሚያደርስ አልሆነም። የስታዲየሙ ግንባታ አስተባባሪዎችም ብዙ ብር ለማሰባሰብ በማቀድ በሸራተን አዲስ የገቢ ማሰባሰቢያ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆነ። በዝግጀቱ ላይ የክብር እንግዳ የነበሩት የክብር ዶ/ር ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ ለንግግር መድረክ ላይ ሲወጡ እንደወትሮው የበኩላቸውን የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ይገልጻሉ ተብሎ ተገመተ። ይህን ያህል ሚሊዮን ብር ይሰጣሉ ሲል ሁሉም ግምቱን መሰንዘር ጀመረ። እርሳቸውም ተናገሩ።

“ስታዲየሙን እኔ እሰራዋለሁ!”

ደማቅ ጭብጨባ ንግግራቸውን ተከትሎ ተሰማ።

በህዝቡ ለመገንባት ታስቦ የነበረው የወልዲያ ስታዲየም ሙሉ ፕሮጀክትን የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ተረክቦ መስራት ጀመረ። የስታዲየሙ ዲዛይንን እንደገና ከመከለስ ጀምሮ ስራው ተጀመረ። ከስታዲየሙ ጋርም የስፖርት ማዕከል መገንባት አስፈላጊ መሆኑ ታመነበት። ፕሮጀክቱ እንደአዲስ ለማለት በሚቻልበት ሁኔታ ተጠንቶና ተስተካክሎ ተዘጋጀ። በህዝቡ ጥያቄ መሰረትም “የሙሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ ስታዲየምና የስፖርት ማዕከል›› የሚል መጠሪያ እንዲኖረው ተደረገ። ባለቤትነቱ ግን የህዝቡ ይሁን

የሚድሮክ ቴክሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር ዶ/ር አረጋ ይርዳው በበላይነት ከሚመሯቸው 25 ኩባንያዎች መካከልም አስሩ በግንባታው ላይ የሚሳተፉበት ሆነ። ዶክተር አረጋም የፕሮጀክቱ የበላይ ኃላፊ ሆነው በቅርበት እየተከታተሉ ማስፈጸማቸውን ቀጠሉ።

የስታዲየሙና የስፖርት ማዕከሉ ግንባታ ከአራት አመት ተኩል ጊዜ በኋላ መጠናቀቁን አስመልክቶ ባለፈው ሳምንት በሸራተን አዲስ ሆቴል ለመገናኛ ብዙሀን በተዘጋጀው መግለጫ ላይ “ለደጉ ወገኔ…ለወልዲያ ህዝብ ይህ ያንስበታል” ሲሉም ዶክተር አረጋ በኩራት ተናገሩ። የፊታችን ጥር 6 ቀን 2009 ዓ.ም ተመርቆ ለህዝቡ በስጦታ ለማስረከብ ቀጠሮ መያዙንም አስታውቀዋል። ስለ ፕሮጀክቱ መሰረታዊ የሆኑ መረጃዎችንም በዝርዝር በማሳወቅ ለህዝብ ይድረስልን ብለዋል።

ሀገር በቀል የሀገር ሀብት

የሙሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ ስታዲየምና የስፖርት ማዕከል ግንባታ ሲካሔድ በሰው ኃይል ሙሉ በሙሉ የሀገር ልጆች የተሳተፉበት ነው። በቁሳቁስ ደግሞ 95 ከመቶ የሀገር ምርቶች ናቸው። በዚህም የተነሳ ስታዲሙና የስፖርት ማዕከሉን “ሀገር በቀል” ሲሉ ዶ/ር አረጋ ይርዳው ገልጸውታል።

በ17 ሔክታር ላይ ያረፈው ስታዲየም የፊፋን አለምአቀፋዊ ደረጃን ባሟላ ሁኔታ የተገነባ ነው። ጣሪያው ዙሪያ ገጠም ነው። ሙሉ በሙሉ ጣሪያው የለበሰ ስታዲየም በመሆን በሀገራችን የመጀመሪያ ያደርገዋል። ዙሪያውን 10 በሮች ሲኖሩት፤ ሰባቱ የአምቡላንስ መኪኖችን የሚያስገቡ ናቸው። 25 ሺ 155 የመቀመጫ ወንበሮችም አሉት። 200 የክብር መቀመጫ ቦታዎችም አሉት። ከውጭም ከ300 በላይ መኪኖችን ማቆም የሚያስችል ቦታ አለው።

ስታዲየሙ ምሽት ላይ ጨዋታዎችን ለማድረግም የሚያስችል ነው። የምሽቱን ጨለማ ገፍፈው የቀን ብርሀንን የሚያጎናጽፉ 156 ፓውዛዎች በዙሪያው ተገጥመውለታል።

ሜዳው እግር ኳስን በበጋም ሆነ በክረምት ለመጫወት የሚያስችል ነው። ዝናብ በዘነበ ቁጥር በተጫዋቾችም ሆነ በተመልካች ዘንድ የሚፈጠረው ስጋት በዚህ ስታዲየም አይኖርም። ሜዳው ላይ የቱንም ያህል ዝናብ ቢዘንብ እንኳ ኳስን ለመጫወት የሚያግድ አይሆንም። የመጫወቻ ሜዳው የለበሰው ሳር ከውጭ ሀገር የተዳቀለ ሲሆን፤ ዝናብ በሚዘንብ ወቅት ውሀው ወደ ውስጥ እንዲሰርግ የሚያስችል ነው። ከሳሩ አልፎ ወደ ውስጥ የሚሰርገው ውሀንም ውስጥ ለውስጥ የሚያጓጉዙና የሚያስወጡ ቱቦዎች አሉት።

ከሌሎች የሀገራችን ስታዲየሞች በተለየ ሁኔታ አራት ቡድኖችን በአንዴ ማስተናገድ ይችላል። በውስጡም አራት ቡድኖች የሚጠቀሙበት መልበሺያ ክፍሎች አሉት። በሌሎች የሀገራችን ስተዲየሞች ሁለት ቡድኖች ተጫውተው ቀጣይ ሁለት ቡድኖች የሚገቡ ከሆነ የመጀመሪያዎቹን ቡድኖች ክፍሎቹን እስኪለቁ ለመጠበቅ ይገደዳሉ። በወልዲያው ስታዲየም ግን ቡድኖች ሳይጠባበቁ መልበሻ ቤቶቹን በመጠቀም የመታጠቢያ አገልግሎትንም ማግኘት ይችላሉ። የእግር ኳስ ዳኞች፣ የህክምና ባለሞያዎችም መልበሻ ክፍል ተዘጋጅቶላቸዋል።

የስፖርት ጨዋታዎችን ለሚያስተላልፉ መገናኛ ብዙሀንም ስታዲየሙ ደረጃውን የጠበቀ ስፍራ አዘጋጅቷል። የሜዳ ውስጥ እንቅስቃሴዎችን በግልጽ ለማየት የሚያስችልና አላስፈላጊ ድምጾች ወደ ውስጥ እንዳይገቡ በሚያስችል ሁኔታ በመስታወት የተሸፈኑ ስምንት ክፍሎች አሉት።

ዘንድሮ በድጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የተቀላቀለው ወልዲያ ከነማ የእግር ኳስ ክለብ በሜዳው የሚያደርጋቸው ጨዋታዎችን በዚህ ስታዲየም የሚያካሒድ ይሆናል። ስታዲየሙ በርካታ ተመልካቾችን በምቾት የሚያስተናግድ ከመሆኑ አንጻር በስታዲየም ተገኝተው ድጋፍ የሚሰጡ የክለቡ ደጋፊዎች ቁጥርን ከፍ እንደሚያደርግ ይታመናል። ለአካባቢው የእግር ኳስ ስፖርት እድገትም ጉልህ ድርሻ ማበርከቱ አያጠራጥርም።

ከወልድያ ከነማ እግር ኳስ ክለብ ባሻገርም ስታዲየሙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አለምአቀፍ ጨዋታዎች ሲኖሩት እንግዳ ቡድኖችን ሊያስተናግድበት የሚችልም ነው። ኢትዮጵያ አህጉራዊ ውድድሮችን ለማስተናገድ ጥያቄ ብታቀርብና ብትወዳደር ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም አለኝ ብላ ብታስመዘግበው ተቀባይነት የምታገኝበትም አይነት ነው።

ከዚህ በተጨማሪም ስታዲየሙ ከእግር ኳስ በተጨማሪ ለአትሌቲክስ ስፖርትም አገልግሎት መስጠት ይችል ዘንድ ታስቦ የተሰራ ነው። ብዙዎቹ የሀገራችን ስታዲየሞች ደረጃውን የጠበቀ የመሮጫ ትራክ የላቸውም። ይህ በወልድያ ከተማ የተገነባው የሙሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ ስታዲየም ግን የመሮጫ ትራክንም ታሳቢ አድርጎ የተዘጋጀ ነው። ባለ ስምንት መስመር የመሮጫ ትራክ ተዘርግቶለታል።

ሁለገብ የስፖርት ማዕከሉ

በሙሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ ስታዲምና የስፖርት ማዕከል ከእግር ኳስ ጨዋታ በተጨማሪ ሌሎች ተወዳጅ ስፖርት አይነቶችም ቦታ አግኝተዋል። የኦሊምፒክ መመዘኛዎችን መሰረት አድርገው የተሰሩ የቅርጫት ኳስ፣ የእጅ ኳስ እና የሜዳ ቴኒስ መጫወቻዎች ተገንብተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የአለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የመዋኛ ገንዳ የተዘጋጀለት የዋና መዋኛም አለው።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም ስታዲየሙና ማዕከሉ ጋር በተያያዘ የእንግዶች ማረፊያ ህንጻም ተገንብቶለታል። ይህ የእንግዶች ማረፊያ ህንጻ 38 የማረፊያ ክፍሎች አሉት። ህንጻው የተገነባው ሕብረተሰቡ ለስታዲየም ግንባታ አሰባስቦ በነበረው 30 ሚሊዮን ብር ነው።

በወልድያ ከተማ የተገነባው  የሙሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲን ስታዲየምና የስፖርት ማዕከል ከስፖርታዊ ጥቅሙ ባሻገር ሌሎች መልካም ጥቅሞችንም የሚያጎናጽፍ ነው። የሀገር ውስጥና የውጭ ዜጎች ወደ ከተማዋ እንዲያመሩ የሚያደርግ አንደኛው የቱሪዝም መስህብና የገቢ ምንጭ ይሆናል።

 በሀገር ደረጃም ቢሆን ስታዲየሙና የስፖርት ማዕከሉ ለኢትዮጵያ መልካም ገጽታን የሚያጎናጽፍና ህዝቦቿን የሚያኮራ ነው።

ሌሎች የሀገራችን ክልሎችም ከወልድያ ብዙ ተሞክሮ መውሰድ ይኖርባቸዋል። በዚህ ረገድ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ስኬቱን ለሚጠይቁት ሁሉ ለማካፈል ፈቃደኛ መሆኑን ዶ/ር አረጋ ይርዳው ገልጸዋል። የሀገራችን ስታዲየሞችና የስፖርት ማዕከሎች ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ ሊገነቡ እንደሚገባም በአጽንኦት ተናግረዋል።

የሙሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ ስታዲየምና የስፖርት ማዕከል ብቻ ሳይሆን ሌሎች ልብ የሚማርኩ የወልዲያ መገለጫዎችም ከተማይቱ የጎብኝዎች መዳረሻ እንደምትሆን ዶ/ር አረጋ በልበ ሙሉነት ይመሰክራሉ።

ከአዲስ አበባ 520 ኪሎ ሜትር ላይ የምትገኘው የቆንጆዎች መፍለቂያ፣ የደጋግ ልቦች መገኛ፣ የተፈጥሮ አየሯና መልክዐ ምድሯ ውብና ተስማሚ የሆነው ወልድያን ማንም ሰው በህይወት ዘመኑ ሊጎበኛቸው ከሚገቡ አካባቢዎች አንዷ መሆኗን ይናገራሉ።

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
687 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1025 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us