ከ1983 ጀምሮ በዩኒቨርስቲ ግጭት እና አመፅ ታጅቦ የኖረው የኢህአዴግ መንግስት ስህተቶች

Wednesday, 21 May 2014 13:06

ከእንዳልክ አለባቸው

የዩኒቨርስቲ ማህበረሰብ ስሙም እንደሚያመለክተው አለማቀፋዊ ሰብእና መላበሻ የእውቀት ማእከልና የሰው ልጅን ስልጡን፣ ስለታምና ችግር ቆራጭ፣ መፍትሔ አመንጪ፣ ሀይል አድርጎ የመስሪያ ፋብሪካ ነው። ተማሪ በዩኒቨርስቲ ውስጥ ትክክለኛ አህጉራዊ ሀገራዊ አለማቀፋዊ ማህበረሰብ እና ግለሰባዊ ጉዳዩችን አንጥሮ በማውጣትና በማወቅ ነገሮችን ጠልቆ ይማራል ይመረምራል። ትክክለኛውንም ጉዳይ ተላብሶ ያንፀባርቃል።

ይህ የዩኒቨርስቲ ሁለንተናዊ መገለጫ ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር ስናስተያየው አዎን ዩኒርሲቲዎችን የእውቀት ማእከሎቻችን ብቻ ሳይሆኑ የለውጥ መነሻ ማእከሎቻችንም እንደነበሩ በነበሩበት ሁኔታዎች በደምብ ማስታወስ ይቻላል።

በኢትዮጵያ ማህበረሰብ ውስጥ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በ 1992 በተደረገ አንድ ጥናት በትምህርት ገበታ ላይ ካለው የተማረ የሰው ሀይል 1በመቶ ያህሉ ብቻ ለዩኒቨርስቲ የሚበቃ አካል እንደሆነ ሲነገር ይህ 1በመቶ ደግሞ ያልተማረውን ህዝብ ጨምሮ በውክልና ደረጃ ከአካባቢው 10 ሺህ ያላነሱ ሰዎችን የሚወክል አካል ሆኖ ይኖር ነበር። ይህ ከ1983 አመት በኋላ በተስፋፋው የትምህርት ዘርፍ የመጣው ለውጥ ከ 3በመቶ ያላነሰ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ይህም የሆነበት ምክንያት የህዝብ ቁጥር ማሻቀብ እና የሀገሪቱ የትምህርት ስትራቴጂካዊ አቅጣጫ የእድገቱን ያህል የትምህርት ቤት እና የተማረ ቁጥሩ በዚያው መጠን እኩል በማሻቀቡ ምክንያት በ1ኛ ደረጃና በሁለተኛ ደረጃ ያለው የተማሪ ቁጥር ዩኒቨርሲቲ ከሚገባው ተማሪ አንፃር ቁጥር አሁንም የትየሌሌ በመሆኑ የመጣውን ለውጥ በዚያው እንዲቆይ አድርጎታል።

የተማሪው ቁጥር መጨመሩ እና ት/ት አቅርቦት እንዲሁም የትምህርት ጥራት ጉዳይ የተማሪውን ስብእናም ጭምር በርካታ ምስቅልቅልን የፈጠረው የት/ት ፓሊሲው ችግርን ለዚህ ለአሁኑ ርዕስ ለጊዜው እንተወዉና ከ1983 ወዲህ በነበረው የዩኒቨርስቲዎች የለውጥ ጥያቄን መንግስታዊ ምላሽ በትንሹ ለማየት እንሞክር።

የኢህአዴግ መንግስት ግንቦት 20/1983 ዓ.ም አዲስ አበባን ሲቆጣጠርና ተከትሎም በነበረው ሁኔታ ቅድሚያ ተቃውሞ የገጠመው ከሁሉም አካል ይልቅ የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ ግምባር ቀደም ነው። ይህም በሪፊረንደም እና የኤርትራን የመገንጠል ጥያቄ በመቃወም ቀድሞ ወደ አደባባይ የወጣው የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነበር። የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በተለይም ከ1984 እና 85 ድረስ በነበረው ሁኔታ በደርግ ጊዜ ኢህአዴግን ለመውጋት የዘመቱ ተመላሽ ተማሪዎች የቆሰቆሱት ተግባር ተደርጎ በመውሰድ መንግስት መረር ያለ አፀፋ ቢወስድም የተማሪዎቹ ጥያቄ ግን የኤርትራ ሪፍረንደም ትክክለኛውን አቅጣጫ አልያዘም የሚል ነበር። በዚህም ተማሪዎች የህዝብ ልጅነታቸውን እና የሚማረውም ለሀገር ለመታገል እንጂ ማንም እንዳሻው የሚፈነጭባት ሀገርን ለመቀበል እንዳልሆነ ለማሳወቅ አደባባይ ወጥቶ ታዋውሞውን አሰምቷል። “አትነሳም ወይ አትነሳም ወይ ይሄ ባንዲራ የአንተ አይደለም ወይ” የሚለውን የተለመደውን መፈክር ይዞ በግቢው ውስጥ በተለያዩ አቅጣጫዎች ሲዟዟር የነበረው ተማሪ አጠቃላይ ጥያቄው በኤርትራ የተካሄደው የሪፍረደም አሰጣጥ ሁኔታን አግባብ አለመሆን በአግባቡ የተቃወመ ጠንካራ ጥያቄ ነበር።

በዚህም የመንግስት ምላሽ እጅግ ጭካኔ የተሞላና በህዝብ ልጅ ላይ ሊፈፀም የማይገባው አስከፊ እርምጃ በመውሰድ ዛሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ ሁለተኛ በር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የደም አበላ ያላበሳ ዘግናኝ ተግባር ተማሪው ላይ ፈፅሞ ለረጅም ጊዜ በዛ በር ተማሪዎች እንዳይወጡ እንዳይገቡ እስከመዘጋት የደረሰ ክስተት የፈፀመ ነው። ኢህአዴግ ሲወድቅ ያ ቦታ ኀውልት ሳይቆምበት የሚቀር አይመስለኝም።

ከዚህ በኋላ ኢህአዴግ የዩኒቨርስቲውን ተማሪ በተለያዩ የብሄር አመለካከቶች ጠንከሮ በመያዝ የከፋፈላቸው ስለሆነ 1990ዓ.ም አመተምህረት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኦሮሞ ተማሪዎች የሰዲስ አባባን ዋና ከተማነት አስመልክቶ ባነሱት ጥያቄ በርካታ ተማሪዎችን አፍሶ ወደ እስር ቤት በማጎርና በመደብደብ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ዳግም በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ጣልቃ እንዳይገቡ፣ አርፈው ትምህርታችሁን እነዲማሩ የማድረጊያ እርምጃ ወሰደ።በማስከተለም መነሻውን ከመምህራኑ ጋር በማያያዝ በተለይ መምህራን ከአካዳሚ ስራቸው ውጪ አንድም የሀገራዊ ጉዳይ ተማሪዎቻቸው ፊት ለማውራት እንዳይችሉ ደምብና መመሪያ አውጥቶ ያን ያላከበረ መምህር ከስራው እንዲለቅ እስከ ማስደረግ እርምጃ ወሰደ። በወቅቱም መምህራን መንግስት ከአካዳሚክ ነፃነት ውስጥ እጁን ጣልቃ እያስገባ መሆኑን በመቃወማቸው በርካታ መምህራን ከስራ ገበታቸው ተባረሩ፤ ገሚሱም በገዛ ፍቃዱ ለቆ ወደ ግል ኮሌጅ አመራ።

በ1993ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከዚህ ቀደም በተነሱ ችግሮች ምክንያት በግቢው ውስጥ ፓሊስ በመግባቱና በርካታ የአካዳሚ መብቶች የተጣሱበት ዩኒቨርስቲ በመሆኑ ከኢትዮጵያ ሰብአዊ ኮሚሽን ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ ዩኒቨርስቲው አጠቃላይ ሁኔታ አሳፋሪ ደረጃ ላይ መሆንን አስመልክቶ 10 ጥያቄዎች ዩኒቨርሲቲው ተማሪ ጥያቄዎች ህብረት አነሳ። ተማሪዎች ህብረቱ በዚያ ወቅት ተቋቁሞ ገና ስራ የጀመረ ቢሆንም ከተማሪው ክፍል የሚነሱበትን ጥያቄዎች መመለስ ቢሳነው። ተማሪዎች በስነፅሁፍ መልኩ ሀሳባቸውን በባህል መአከል እያቀረቡ የተማሪውን ትኩረትና ግፊት እንዲጨምር በማድረግ የተማሪዎችም ህብረት አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ጥያቄውን በይፋ አቀረበ።

በወቅቱ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብትን በተመለከተ ተማሪው በራሱ አነሳሽነት ሊወያይ ሲገባው ኢስመጉ በብሄራዊ ሎተሪ አዳራሽ ውስጥ በተካሄደ ስብሰባ "እንደ ቀድሞዎቹ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የህዝባችሁን ችግር መናገር ባትችሉ እንኳ የራሳችሁ ችግር ለመናገር ሞክሩ" በሚለው የኢስመጉ አወያዩች እራሱን ለመፈተሸ የበቃው የተማሪዎች ህብረት ዩኒቨርሲቲው የትምህርት መስጫ ማእከል ሳይሆን በፓሊስ የፊጥኝ ተይዞ እየተማረ ያለ የእስር ቤት መታጎሪያ ቦታ መሆኑን ተረድቶ ጥያቄውን ለዩኒቨርስቲው አካዳሚ ፕሬዝዳንት አቅረበ። ተማሪውም የህብረቱ ጥያቄ አፋጣኝ መልስ ስላልተሰጠው በፕሬዝዳንቱ ቢሮ ፊት በመሰብሰብ ትምህርት እናቆማለን፣ ምግብም አምበላም ጥያቄዎችን ከዩኒቨርስቲው በላይ ስለሆነ የመንግስት አካል ያናግረን የሚል ጥያቄ ይዞ አደባባይ ዋለ።

በራሱ ጥያቄ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ መንግስት ፊት የቀረበው የዩኒቨርስቲው ተማሪ የተመለሰለት መልስ ከግቢው ውስጥ ካለ ፓሊሰ በተጨማሪ ሌላ ፈጥኖ ደራሽ ፓሊስ ቆመጥና በትር አከርካሪው እስኪሰበር መደብደብና አልፎም በዱላው ምክንያት አመጹ ተባብሶ ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በመቀጠሉ በጥይት እሩምታ ለማስቆም ተሞከረ። በወቅቱም በአመፅ ላይ ተሳትፈዋል ወይም ቀስቅሰዋል የተባሉ ወጣቶች ከየተበተኑበት ተለቃቅመው እስር ቤት ገቡ ገሚሱም ሀገር ጥለው በኬንያና በጅቡቲ ተሰደዱ። ትምህርት ለአንድ አመት ያህል ተቋርጦ የግቢውን ፓሊስ ተቀይሯል ያለው መንግስት ምልምል አዲስ ወታደሮች በማስገባት የራሱን ፓለቲካዊ ድራማ ተጫውቶ ተሻገሮታል።

ከ1985ዓ.ም እንዲሁም የኦሮሞ ተማሪዎች በግቢው ውስጥ የኦነግ አመለካከትን ያራምዳሉ በሚል መነሻ የተወሰኑ ተማሪዎችን የማደሪያ ክፍላቸው ድረስ ሄዶ በማፈስና በማሰር ተማሪውም የታሰሩ ተማሪዎች ካልተፈቱ አንማርም የሚል አቋም በመያዛቸው በዚህም ጥያቄ ላይ የተሳተፉ ተማሪዎችን ለመበተን በሚል ወደግቢው የገባው አድማ በታኝ ወታደር በማስገባት ብጥብጥ ተነሳ። በዚህም በርካታ የኦሮሞ ተወላጅ ተማሪዎች ታፍሰው ለእስር ሲዳረጉ የተወሰኑት ተፈቱ። የተወሰኑት ቢዚያው የት እንደገቡ ሳይታወቅ ቀረ። በፍርድ ቤት ይታያል የተባሉ ተማሪዎችም እንደነበሩ በወቅቱ ቢሰማም ምን እንደተፈረደም የሚታወቅ ነገር የለም፤ ይሄን ቤት ይቋጠረው።

በ1997ዓ.ም መንግስት ዲሞክራት ሆኛለሁ ብሎ በለበሰው የማስመሰል ጭምብል ተጠቅሞ ለምርጫ የቀረቡትን ፓርቲዎች ድምፅ መልሶ በመቀማት አሸንፊያለው የሚል አቋም ያራመደው የኢህአዴግ መንግስት ይህ ተግባሩን ተቃውመው አደባባይ የወጡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በአደባባይ እንዲደበደቡ በሁለት በር አሰርጎ ያስገባቸው ስልጡን አድማ በታኞች ድጋሚ ዩኒቨርሲቲውን ወረሩ። በመላው ሀገሪቱ ያሉ ዩኒቨርስቲዎችም በደም አበላ ታጠቡ። በርካቶች ከወዳጅ ዘመድ በሌሉበት ቦታ የህዝብ ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደ ቤታቸው ተመለሱ። ይህ ትርምስ በዩኒቨርስቲ ተጀምሮ በዋና ዋና ከተሞች በርካታ ህዝባዊ አመፅን የቀሰቀሰ የኢትዮጵያ ፓለቲካ ውስጥ ትልቅ ህዝባዊ ንቅናቄ የተካሄደበት ወቅት ነበር።

ሆኖም ደም አልባሽ አፀፋዎችን በህዝብም በዩኒቨርስቲዎች ላይ መውሰድ የለመደው የኢህአዴግ መንግስት ከእንግዲህ ከዩኒቨርሲቲ ምንም አይነት ብጥብጥ እንዳይነሳ የማድረጊያ ስትራቴጂ ነድፎ ዩኒቨርስቲዎችን ከነ አካዳሚክ ነፃነታቸው ጨፍልቆ በእጁ መዳፍ ውስጥ የማስገባት ስራን ሰራ። የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች ከእንግዲህ የኢህአዴግ ካድሬዎች መፈንጫ እንጂ ዳግም በመብት ጥያቄ አንግበው መንግስትን የሚነቀንቁ አካላት ሊሆኑ አይችሉም በሚል አቋም እራሱን ወደ ቀድሞው አምባገነናዊ ማንነቱ በመለወጥ ተማሪውን አፉን አስያዘው።

ከ1997 ወዲህ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ሆኑ ሌላው የፓለቲካ ንቅናቄ በ1997 ከታየው ህዝባዊ አመፅ በመነሳት ነገሮች በአስከፊ ሁኔታ እንዲሄድ አደረገ። የ2002ቱን ምርጫ 100 በመቶ አሸነፍኩ በሚል ስም የሰለቸው ህዝብና የዩኒቨርስቲ ተማሪም ይሁንልህ ከማለት የዘለለ አንድም አቋም ማሳየት አልቻለም። ምክንያቱም ለሚነሱት ህዝባዊ ጥያቄዎች የሚሰጠው አፀፋዊ መልስ ምን እንደሆነና በስም ደረጃ በመንግስት አመራሮች አልለይ ያለው ዲሞክራሲ የቋንቋ ውበት እንጂ ተግባር እንዳልሆነ ታይቷል።

ነገር ግን ተማሪው በተለያየ ሁኔታ ከዚህ በላይ በጠቀስኳቸው ብዛት እና ንቅናቄ ባይሆንም በየጊዜው በሚወሰዱ እርምጃዎች ዙሪያ የራሱን አቋም እያራመደ ሄዷል። ይህም አቋም እንደ ቀድሞዎቹ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በሀገራዊ ጉዳይ ከምንም በላይ የማይደራደር አካል ከመሆኑም በላይ በያገባኛል ስሜት ተነቃንቆ አቋም የሚይዝ አካል መሆኑን አልካደም። ምንም እንኳ የኢህአዴግ በ 1 ለ 5 የአደረጃጀት ስንሰለት ሳይቀር ለመታሰር ቢገደድም ሰው ስጋው እንጂ ህሊናው የማይታሰር አካል መሆኑን የአስመሰከረባቸው አጋጣሚዎች በርካቶች ናቸው። በተለያዩ አደረጃጀቶችና ጠርናፊዎ የተያዘው ተማሪው እራሱን ለኢህአዴግ የሚያስገዛ ኢህአዴግ ፍፁም እንደሆነ አድርጎ እንዲያምንና ኢህአዲግ የአዲሱ ትውልድ አባት አድርጎ እራሱን ያቀረበ በመሆኑ ከ1997 በኋላ እስከ 2006 ዓ.ም ድረስ እረፍት ሊያገኝ ችሏል።

በዘንድሮው 2006 እንግዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ የማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ የተነሳው የተማሪው ጥያቄ ከመደወላቡ ዩኒቨርስቲ ወደ ሌላው ዩኒቨርስቲ እየቀጠለ የሄደ ትልቅ ጉዳይን ያነገበ፣ ተማሪም በተመሳሳይ በመንግስት አፀፋው ያው ከጀርባ ያለውን የተቀጣ የፈሪ ብትር መዘዘ። የህዝብን ልጅ አሳር ከማሳየት ያለፈ መልስ አለመኖሩ ነው ክፋቱ። በዚህ የተማሪዎች ጥያቄ ከ 34 በላይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እንደ ሞቱ የሚነገር ሲሆን መንግስት አሁንም ለሚነሱ ጥያቄዎች መልሱ ዱላ ነው ባይ ነው።

በዚህ የአዲስ አበባ የማስተር ፕላን ጥያቄም ጀርባ ኢህአዴግ ህዝቡን ከፋፍለህ ግዛ በሚለው ስትራቴጂው መጀመሪያ የሸረበው ሴራ ለተለያዩ የልማት ስራዎች እንቅፋት ሲሆንበት አንዱን ከሌላው በመንጠቅና በመጠቅለል የገዛ ጥቅሙን እንጂ የህዝብን ትክክለኛ ስሜት የተረዳ ስራ የማይሰራ መንግስት መሆኑን በይፋ ያሳየበት ነው።

ሁሌም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄርሰቦች ለኢህአዴግ መንግስት የማስመሰል እቃቃዊ ቲያትር እንጂ በአግባቡ በእውቀት እና ጥናትን መሰረት ባደረገ ስራን ስለማያራምድ ዛሬ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ሲፈልግ ከአዲስ አበባ ተነስቶ አዳማ ይገባል፤ ሲፈልግ ከአዳማ ተነስቶ ደግሞ አዲስ አበባ ይገባል። ሲፈልግ ከጋምቤላ እስከ መተማ የሱዳን ድረስ መሬት ይሸጣል። በአጎራባች ክልሎች የሚፈጠረው አለመግባባትም በየጊዜው ችግር ፈጣሪ እና በችግሩም የሚነሳው ጥያቄ መልሱ ዱላ ይሆንበታል። ሲያስፈልግ የኦሮሚያ አጎራባች ከተሞች አዲስ አበባ ይሆኑበታል። ሲያስኘው የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የሶማሌ ክልል ይሆንበታል። ምንጊዜም ችግር ፈጣሪን የአሰራር ስርአት መከተል ተመልሶም ለችግሩ አግባብነት ያለው መልስ ከመስጠት ይልቅ አደጋ መፍጠር ልምዱ ነው።

መንግስት ምንግዜም ትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሰረተ ስራ አለመስራት እና የሚነሳበትን ተቃውሞ በተለይም የዩኒቨርስቲው ምሁር የሚያነሳውን ጥያቄ ለመመለስ የሚቀናው ዱላው እንጂ ሌላ ምኑም አለመሆኑ አሳፋሪ ነው።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
1335 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us