ለወዳጄ አብድራህማን በመረጃ ዘመን ማስረጃ አልባ ጽሑፍ፣

Wednesday, 23 April 2014 12:02

ታምራት ታረቀኝ

ብዙ የተነገረለት የመኢአድ አንድነት ውህደት ከሽፎ አመራሮቹ ከውህደት ወደ መዘላለፍና መወነጃጀል ማምራታቸውን ከሰንደቅ ጋዜጣ አንብቤ ያሰፈርኩትን ጽሁፍ መነሻ አድርጎ ወዳጄ አብደራህማን አህመዲን ሚያዚያ 8/2006 ዓም ለሰንደቅ ጋዜጣ የላከው ጽሁፍ በኢንተርኔትም ተሰራጭቶ ጋዜጣው ለንባብ ከመድረሱ አስቀድሞ ፌስ ቡክ ላይ አነበብኩት፣ ብዕሩ ንዴቱን ያሳብቃልና ምኑ እንዳናደደው ግራ ገብቶኝ የራሴን ጽሁፍ መልሼ አነበብኩት። ነገር ግን ወዳጄን ሊያናድደው ይችል ይሆናል የምለው አንድም ቃል አላገኘሁም።

ከወራት በፊት በፊስ ቡክ ተገናኘንና ከፕሮፌሰሩ ጋር ስለ ጀመርኩትን ሙግት ምን አስተያየት አለህ ሲለኝ ብዙዎቹን ጽሑፎቹን እንዳላነበብኳቸው ነገርኩትና ፕ/ር መስፍንንና አቶ ተመስገን ዘውዴን የሚመለከቱ ስድስት ያህል ጽሁፎች በኢሚይል ላከልኝ። ከፊሎቹ ተቆራርጠው ቢደርሱኝም አንብቤ ከሰጠሁት አስተያየት አንዱ ጽሁፎቹ ጥላቻ የሚታይባቸው መሆናቸውን ነው። “እንደ ተናደድህ ብዕር አታንሳ” የሚለውንም አባባል ላስታውሰው ሞክሬ ነበር። (አንተ እያልሁ የምገልጸው ከነበርን ቅርበት አንጻር መሆኑ ይታወቅልኝ)

ወዳጄ እርሱ እንዳሳነሰው ሳይሆን ግንኙነታችን ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1998 ዓ.ም ይዘልቃል። የተለያየነው እኔ ወደ እስር ቤት እርሱ ወደ ፓርላማ በመሄዳችን ነው። ይህን ያህል ትውውቅ እያለን እኔን ለመግለጽ «በቅርብ እናውቀዋለን የሚሉ እንደነገሩኝ ከሆነ መቶ አለቃ ታምራት ..ብሎ» በዘጠኝ ዓመት ትውቃችን ያላወቀውን አዲስ የእኔን ማንነት አግኝቶ ነው ስለ እኔ የገለጸበትን ክፍል የጀመረው። አይደለሁም እንጂ ብሆን ኖሮ አላፍርበትም። ግን ለምን አስፈለገ?

ወዳጄ በእውነት ሳይሆን በስሜት በማስረጃ ሳይሆን በነገሩኝ፤ በአስተውሎት ሳይሆን በንዴት መጻፉ አሳፈረኝም አሳዘነኝም።እናም በዚህ መልክ ለቀረበ ጽሁፍ ምላሽ መስጠት አስፈላጊ ባይሆንም አንባቢውን በማክበርና የተነሳውን ጉዳይ ከሁለት አቅጣጫ ተረድቶ የራሱ ድምዳሜ ላይ እንዲደርስ ለመረዳት ይህችን ጽሁፍ አዘጋጀሁ።በአሉባልታ ሳይሆን በማስረጃ ለማቅረብ ስሞክር እንደ ወዳጄ ጉዳይ በቀጥታ የማይመለከታቸውን ሰዎች ስም በመጥራት ርጥቡ ሬሳ ደረቅ አስነሳ ይሉ ነገር ውስጥ እንዳልገባ ለመጠንቀቅ ሞክሬአለሁ።

1ኛ ነገር ለማጣፋጥ እውነትን ከውሸት መቀየጥ፣

መቼም የቱንም ያህል ንዴት ቢያይል የቱንም ያህል ጥላቻ ማስተዋልን ቢጋርድ በአደባባይ በተፈጸመና በግልጽ ብዙ ሰው ባየውና በሚያውቀው ነገር ላይ ውሸት ጨምሮ ቃላት አሳምሮ በመናገርም ሆነ በመጻፍ ውሸትን እውነት ማድረግ የሚቻል አይመስለኝም። ወደጄ መዐህድ፣ አማራጭ ኃይሎች፤ ኢዳግ፤ ኢዴፓ፣ ቅንጅት፤ አንድነት፤ መርህ ይከበር እያለ እንደ ፌንጣ ከፓርቲ ወደ ፓርቲ ሲዘል ቆይቶ አሁን ሰማያዊ የረጋ ይመስላል ይለኛል።

ከዚህ ገለጻው መጀመሪያ የሚወጣው ውሸቱ ነው፣ ምክንያቱም የአማራጭ ኃይሎች እና የኢዳግ አባል አልነበርኩምና። ሁለተኛው የማስተዋል ጉድለት/ግርዶሽ ነው። ወዳጄ የምክር ቤት አባል የነበረበትን ኢዴፓ የመሰረትነው የያኔው ወጣቶች ከመዐህድ በቀኝ አዝማች ነቅዐ ጥበብ በቀለ ካቢኔ የተባረርን እንጂ ከአማራጭ የወጣን አልነበርንም። እንደውም ለኢዴፓ መመስረት አንዱ ምክንያት አማራጭ አዳራሹን ከመፍቀድ ባለፈ እኛን በፖለቲካው ውስጥ ተሳታፊ ለመሆን በሚያስችለን መልኩ ሊያስተናግደን አለመቻሉ ነው።

ኢዳግ ከኢዴፓ ጋር ተዋህዶ የከሰመ ፓርቲ ነው (በዚህ አጋጣሚ ከራስ በላይ ለሀገር አሳቢ ለሆኑትና ውህደቱን በማሳካት ኢዴፓን ላጠናከሩት የኢዳግ አመራሮችና አባላት ያለኝን ክብርና እድናቆት ልገለጽ።) ውህደቱ ሲፈጸም አቶ አብደረህማን የኢዴፓ ብሔራዊ ምክር ቤት አባል ነበርና ይህን ለማስረዳት ሌላ ማስረጃ ማቅረብ አይጠበቅብኝም። ታዲያ እኔ የሁለቱም ፓርቲዎች የኢዴፓም የኢዳግምአባል የሆንኩት እንዴት ነው።

ሌላው የማስተዋል ጉድለት ኢዴፓም ቅንጅትም እንደ ፌንጣ መዝለሌ የተገለጸበት ነው። ኢዴፓ የቅንጅት አባል መሆኑን የማያውቅ ያለ አይመስለኝም፤ ስለሆነም እኔ የኢዴፓ አባል እንደ መሆኔ የቅንጅት አባልነትን ያገኘሁት በዚህ መንገድ እንጂ አንደ ፌንጣ በመዝለል አይደለም። መርህ ይከበር ደግሞ ፓርቲ አይደለም፣

“በተጣደፈ ውህደት ቅንጅትን በአፍ ጢሙ መድፋቱን ዘነጋውና የሚለው ወዳጄ በዚህ ሳያቆም እነርሱ ራሳቸው ያልተጠና ውህደት በመፈጸም ሕዝብ መስዋዕትነት የከፈለበትን የትግል ውጤት የትም በትነዋልና በማለት በቅንጅት ጉዳይ እኛን ተከሳሽ ተወቃሽ ያደረገናል።

እዚህ ገለጻ ውስጥ አንድ እውነት ሁለት ውሸት ይገኛል። አንባቢንም ያልዋጀ የድፍረት አቀራረብ ነው። ቅንጅት በአፍ ጢሙም ይባል በጀርባው እንዳይሆን እንዳይሆን መሆኑ እውነት ነው። እኔና ዶ/ር ኃይሉ የቅንጅት ምክር ቤት አባል ስለነበርን ብቻ አቶ አብደራህማንም እንደ ቃሊቲው ችሎት በጅምላ ካልፈረደብን በስተቀር በተገለጸው ደረጃ የሚያስከስሰንም ሆነ የሚያስወቅሰን ነገር አልፈጸምንም። በጣም የሚያስገረመውና አንባቢን ምንም እንደማያውቅ የሚያደርገው ያልተጠና፣ በተጣደፈ ሁኔታ የተፈጸመ ያለው ውህደት በእኛ የተፈጸመ አደርጎ መግለጹ ነው። ለመሆኑ ከውህደት በፊት እኔ የጥምሩ ቅንጅት ምክር ቤት አባል እንዳልነበርኩ አቶ አብደረህማን አንዴት ማስታወስ ተሳነው። ታዲያ የምክር ቤት አባል ያልሆነ ሰው እንዴት ሆኖ ነው በተገለጸው መልክ ያለጥናት ውህደት በጥድፊያ ፈጻሚ ተብሎ ተወቃሽና ተከሳሽ የሚሆነው።

2ኛ በመረጃ ዘመን ማስረጃ አልባ ጽሁፍ፣

እኔን የገረመኝ አቶ ዘካርያስን ለማድነቅም ለመዝለፍም ቃላት የማይመርጥ ሲል ነው ይልና የእኔን ተዛላፊነት ለማወቅ የሚሻ በ1999 ዓም የጻፍኩትን መጽሐፍ እንዲመለከት ይጋብዛል። እኔ ስለ አቶ ዘካርያስ ስገልጽ የቅርቡን ሰንደቅ ላይ የወጣ ጽሁፍ መነሻ አድርጌ ወደ ኋላ ሄጄም አዲስ አድማስ ጋዜጣን ቀኑንና ዘካርያስ የጻፈውን ጠቅሼ እንዲሁም በአንድነት ግቢ ያነበበውን ግጥም በማስረጃት አቅርቤ ነው። አቶ አብድራህማን ሾላ በደፈናው መጽፉን አንብቡ ከማለት ለርሱ ስድብ ወይንም ዘለፋ ሆኖ የታየውን አንድ ሁለት ቃላት መግሐጽ ቢችል ምንኛ መልካም ነበር። ማስረጃ የሌለው ነገር ደግሞ አሉባልታ ነው። መጽሀፉ እንደ ወጣ ሰሞን ስለ መጽሐፉ የዘገበውና እኔንም ቃለ ምልልስ ያደረገልኝ ይሄው ሰንደቅ ጋዜጣ በወቅቱ የነበሩ አዘጋጆች የምትሉት ካለ በማለት ከጠየቁዋቸው ሰዎች አንዱ አቶ አብዱራህማን ነበር። ታዲያ ያኔ ተጠይቆ እንኳን መልስ ለመስጠት ያልፈለገው ከመጽሐፉ የሚያወጣለት ህጸጽ ባለመኖሩ እንጂ ለስድብ መልስ አይሰጥም በሚል አልነበረም። የወዳጄ ንዴትና በእኔ ላይ ጥላቻ ያደረበት ምክንያት የገባኝ እዚህ ጋር ደርስ ነው። በመጽሐፉ ውስጥ በስም ከተገለጹት ሰዎች አንዱ ወዳጄ ነውና።

ለእንጨቱ ሁሉ መቆንቆኑን ማን አስተማረውና የምትለው አባባል ደግሞ አለቦታዋ ነው የገባቸው። ምክንያት መጀመሪያ ነገር ወዳጄ የእኔን ተሳዳቢነት በማስረጃ አላየም። ብሆን ደግሞ ከእኔ ተምረው ተሳዳቢ የሆኑ ሰዎችን አንድ ሁለት ብሎ ማሳየት ነበረበት።

3ኛ ዘጠኝ ዓመት ረዥም ሆኖ የነበረው ሊረሳ፣

ውህደቱ ደረጃ በደረጃ ይሁን ሲባል አሁኑኑ መፈጸም አለበት ብለው ክችች ማለታቸውን በማለት ለመፍረሱም ምክንያቱ ይሄው እንደሆነ አድርጎ በመግለጽ ዘጠኝ ዓመት ረዥም ሆኖ ሁሉን የሚያስረሳ ይመስል ወዳጄ ያልነበር ነገር ጽፏል። ብዙ ማስረጃዎችን በማቅረብ እውነታው ይህ እንዳልሆነ ማሳየት እችላለሁ ግን ገጽ እፈጃለሁ። ስለሆነም ጥቂት ማስረጃዎችን ላቅርብ። ደግሞም እኮ የማስረጃ ብዛቱ ሳይሆን ተአማኒነቱ ነው። ውህደቱ በጥድፈያ ይፈጸም የምል አልነበርኩም፡፤ ማስረጃ በአቶ ቸኮል ይመራ የነበረው የእጩ ምልመላና ምደባ ኮሚቴ ውስጥ ተመድቤ በቅንጅት ስም አንድም እጩ ሳንመዘግብ የዕጩዎች ማስመዝገቢያ ግዜ ነጎደ። እለቱን አላስታውስም፣ የጥምረቱ ቅንጅት ምክር ቤት መሰብሰቡን ሰማሁና ሄድኩ። ስብሰባው አልቆ ሲበተኑ ልደቱን ስለ እጩዎች ጉዳይ ተነጋገራችሁ ወይ ስለው አልተነጋገርንም አጀንዳችን የውህደት ጉዳይ ነበር አለኝ። በጣም ተናድጄ አንድም እጩ ሳይዘጋጅ ግዜው እያለፈ ቀስ ብሎ በሚደርስ ጉዳይ ትነጋገራላችሁ። ለመሆኑ በውህደት ጉዳይ እንድትነጋገሩ ለኢዴፓ ሰዎች ማን ውክልና ሰጣችሁ በማለት ብዙ ተናገርኩት። እርሱም በርጋታ አዳምጦኝ የተለመደውን አንተ ደግሞ ብሎ ጥሎኝ ሄደ። ከዛ ያገኘኋቸውን አመራሮች ሁሉ ምንድንነው የምትሰሩት ስላቸው እኛ እኮ እየተሰራ ነው በቅርብ ቀን ያልቃል ተብሎ ሪፖርት ተደርጎልን ነው አሉኝ። አኔም ፓርቲዎች ዝርዝር እንዳላቀረቡ በቅንጅት ስም የተመዘገበ አንድም እጩ አለመኖሩን ነገርኳቸው።

የኢዴፓና የመኢአድ የውህደት አመቻች ኮሚቴ አባል ነበርኩና፣ በማይረባ ምክንያት ከጫፍ የደረሰ ውህደት ሲፈርስ አይቻለሁና የውህደቱ ጥድፊያ አሳስቦኝ ምን እየሰራችሁ ነው በማለት ፕ/ር መስፍንንና ዶ/ር ብርሀኑን ለየብቻ በተለያየ ቀን ሳነጋግራቸው በተለይ የሁለቱ ፓርቲዎች መጓተት በዛ ስራ ሊያሰራን አልቻለም፣ በእጩዎች ምደባ ግዜ ደግሞ ይበልጥ ሊከፋ እንደሚችል ይገመታል። ስለዚህ አስቀድመን ውህደቱን መፈጸም ብንችል ይሄን ችግር እናስወግዳለን ብለን ነው አሉኝ። እኔም ሁለቱ ፓርቲዎች ውስጥ (መኢአድና ኢዴፓ) ችግር አለ። ይህን ችግር ሳትፈቱ ውህደት ማሰብ የማይሆን ነው። እናንተ አሁን የገባችሁት የደፈረሰ ባህር ውስጥ ነው። ያላችሁ እድል ወይ ውሃውን ማጥራት ወይ አብራችሁ እየተንቦራጨቃችሁ ይበልጥ ማደፍረስ ስላቸው ፕ/ር መስፍን ምን የደፈረሰ የጨቀየ እንጂ ነበር ያሉኝ። ከዚህ በኋላ ነው ቅራኔን ለማስወገድ ተብሎ ለንግግር ፕሮግራም ተይዞ ደብረ ዘይት የተኬደው። እዛ እልባት ላይ ሳይደርስ ቀርቶ ንግግሩ አዲስ አበባ ላይ ቀጥሎ ነበር አውቃለሁ መጨረሻው ባያምርም።

ከዛም በኋላ በየቦታው የሚሰማው አላምር ሲል ሰኔ 10/1997 ዓ.ም ስሜን ሳልገልጽ «በውህደት የሚፈጠረው ፓርቲ እንከን የለሽ እንዲሆን እንሻለን» በሚል ርእስ ሁለት ገጽ ጽሁፍ አዘጋጅቼ በምክር ቤቱ ጸሐፊ በአቶ ገብረክርስቶስ በኩል ሰብሰባ ሲቀመጡ ለምክር ቤት አባላት እንዲደርስ አደረግሁ። የዚህ ጽሁፍ መደምደሚያ «በአጠቃላይ ቅንጅት ወደ ውህደት ሲሸጋገር ማየት የምንሻው የጠራ አሰራር፤ የጠነከረ አመራር፤ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን መርሁ አድርጎ የሚራመድ፤ ሕዝብን የሚያከብርና በሕዝብ የሚወደድ ፓርቲ ሆኖ እንዲወጣ ነው፣ ‹የእነ ቶሎቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ› ይሉት አይነት እንዳይሆን አደራ እንላለን፤ ‹አንከን የለሽ› ውህደት እንዲፈጠር እንሻለን፤ እግዚብሄር አምላክ ለዚህ ያብቃን» ነበር የሚለው። (አስፈላጊ ከሆነ ሙሉውን ጽሁፍ ለዝግጅት ክፍሉ መላክ እችላለሁ።) እናስ ወዳጄ!

ለውህደቱ መፍረስ ምክንያቱ በጥድፊያ መፈጸሙ እንደሆነ ተደርጎ የተገለጸውም ቢሆን ትክክል አይደለም። ዋናው ምክንያት ከራስ በላይ አለማሰብ ነው። ለዚህ ደግሞ በወቅቱ በየጋዜጣው ትሰጡዋቸው የነበሩ ቃለ ምልልሶችን መለስ ብሎ ማየት በቂ ነው። ወዳጄ በጦቢያ ጋዜጣ ከ50 ዓመት በላይ ያሉ ሰዎች በፖለቲካው ውስጥ አያስፈልጉም በማለት የገለጸው ይህንኑ ያሳያል። አንድ ላክል።

ቀኑ ዓ.ም ቦታው ቦሌ ቅንጅት ቢሮ ከሰዓት በኋላ ልደቱ ማህተም አላደርግም ያለበትን ምክንያት ሲያስረዳ አቶ አብዱራህማን እዛው ነበር በኋላ ስብሰባውን ሳይጨርስ አፍጥር ደረሰብኝ ብሎ ቢሄድም ልደቱ የተናገረውን ሰምቷል፣ ኢህአዴግ ቅንጅትንና አቶ ኃይሉን በሀገር ክህደትና በዘር ማጥፋት ወንጀል ሊከስ እንደሆነ መረጃ አለኝ፣ ሰርተፍኬታችንን መልሰን አንድ ላይ ሆነን ከሚያገኘንና ከምንመቻች ለየብቻ ሆነን ብናሳልፈው ይመረጣል ነበር ያለው። ይህን በየጋዜጦችም ተናግሮታል። ወዳጄ ይህን የሚክድ ከሆነ ይንገረኝ ጋዜጦቹን ባላገኝ ቪዲዮውን እሰጠዋለሁ።

ሌላው ምክንያትም ቢሆን በቅንጅት ውስጥ ኢዴፓ ተገቢ ቦታውንአላገኘም ዴሞክራሲያዊ አሰራር የለም የሚል እንጂ ቅንጅትን ለውህደት የሚያበቁ ቀሪ ስራዎች አሉ የሚል አልነበረም። እነዚህ ሊያሳምኑ ቀርቶ በቅጡ እንኳን የሚያዳምጣቸው ሲጠፋ ነው ውህደቱ ታች ድረስ ሳይወርድ ማህተም አናደርግም የሚል ሰበብ የመጣው።

4ኛ ልደቱ ላይ መንጠልጠል ለምን።

አቶ አብደረህማን ምክንያቱ ባይገባኝም (የፍቅር እንዳልሆነ ግን አውቃለሁ) በብዙ ጹሁፎቹ በልደቱ መንጠልጠል ወይንም ታኮ ማደረግ ይታይበታል። ለመጻጻፋችን ምክንያት በሆነው ጉዳይ ልደቱን ቀጥተኛ ተነሽ የሚያደርገው ምክንያት አልነበረም። ያለ ቦታው አንስቶ እኔም ስሙን እንዳነሳው አደረገኝ እንጂ።

«ውህደቱ ደረጃ በደረጃ መፈጸም አለበት የሚሉትን እነ ልደቱን ክፉኛ የታገሉት ዶ/ር ኃይሉ…»«የቅንጅት ውህደት ደረጃ በደረጃ እንዲከናወን እነ ልደቱ ሀሳብ ሲያነሱ እነ ታምራት ደግሞ..»፣ እነ ተብለው በደፈና የተገለጹት ከልደቱ በስተጀርባ ያሉት እነማን ናቸው? አቶ አብደረህማንን ይጨምራል? ከሆነ ባለጉዳዩ ራሱን መግለጽ ሲገባው በልደቱ ጀርባ መሸጎጥ ለምን አስፈለገ? እነ ልደቱ ከማለት እኛ ብሎ ለመግለጽ የሚፈራ ወይም የሚፈለግ ነገር ይኖር ይሆን?

5ኛ--የጥላቻ ግርዶሽ ኋላን አያሳይም፣

አቋምንም መርህንም መቀየር ይቻላል፣ ይህ የሚሆነው ግን እንዲቀየር ያስገደደውን በቂ ምክንያት አንድ ሁለት ብሎ ዘርዝሮ በማቅረብ እንጂ እንዲሁ በዘፈቀደ ከመሬት ተነስቶ መሆን የለበትም፣ የሚለው ጥሩ አባባል ነው። ነገር ግን ትናንትም ዛሬም የእነ ቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ ይሉት አይነት ትብብርም እንበለው ውህደት መኖር እንደሌለበት እምነቴ ነውና የአቋምም ይባል የመርህ ለውጥ አላደረኩም። ለውጥ አድርገሀል ከተባለ ትናንት ፓርቲዎች ህብረት እንዲፈጥሩ ሲቻልም ተዋህደው አንድ እንዲሆኑ መስራት ያስፈልጋል የሚል እምነት ነበረኝ። ከዳር ቆሜ ሳይሆን በአካል ተሳታፊ ሆኜ እንዳረጋገጥኩት የፓርቲዎቹ ቁመና ሆነ የመሪዎቹ ስብእና ለዚህ የሚያበቃ ባለመሆኑ 22 ኣመት በከንቱ ታልፏልና ተባበሩ ከማለት ጠንክሩ ማለት ይሻላል የሚል እምነት ይዣለሁ። ይህንንም በተደጋጋሚ በተለያዩ ጋዜጦች ጽፌአለሁ። ሌላው ቢቀር ወዳጄ በሚያዘወትረው በዚሁ ሰንደቅ ጋዜጣ የሐምሌ 2005 ዓ.ም ዕትም ላይ፣                  «ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚቀርበው ወቅታዊ ጥያቄ ተባበሩ ሳይሆን ጠንክሩ ቢሆን»በሚል ርዕስ ያሰፈርኩትን ጽሁፍ ወዳጄ ቢያስታውስ ቢያንስ ካልተገባ ወቀሳ ይቆጠብ ነበር። ጽሑፉ የሚያበቃው እንዲህ በማለት ነበር፣«ባለፉት 21 ዓመታት በየምርጫዎቹ ዋዜማ የተፈጠሩ ከአማራጭ ኃይሎች ምክር ቤት እስከ መድረክ ያየናቸው መተባበሮች ጠንክረው ሊወጡ የሚችሉትን እያዳከሙ፣ በግዜ ከፖለቲካው መድረክ ሊገለሉ የሚገባቸውን እድሜ ከማራዘም በስተቀር ይሄ ነው ተብሎ የሚጠቀስ ተግባር አከናውነዋል የሚል ካለ መነጋገር እንችላለን። (ይህኛው ቅንጅትን አይመለከትም)

የመጨረሻው መጨረሻ እንዳይሆን በሚያሰጋው ምርጫ 2007 ዋዜማ ላይ ሆነን 21 ዓመት ሙሉ ጮኸን ምላሽ ያላገኘውንና እየተሞከረ ለውጤት ያልበቃውን መተባበር መጠየቅ ለውጥ ከመሻት ጉጉት የሚነሳ ጥያቄ ሊባል አይችልም። ለሁሉም ልክ አለው፣ ስለሆነም የወቅቱ ጥያቄ ጠንከሩ መሆን አለበት። ጠንክሩ ማለቱ ብቻውን ደግሞ የሚፈለገውን ለውጥ አያመጣምና ለመጠንከር ደፋ ቀና የሚሉትን አይቶና ለይቶ መረዳት ያስፈልጋል።»

     እናስ ወዳጄ ይህን ካነበብክም በኋላ አቋምና መርህ የለሽ ትለኝ ይሆን? በዚህ ረገድ ማናችን እንደምንታማ የዛኔው የጋራ ወዳጆቻችን ይመሰከራሉና አሳ ጎርጓሪ ባትሆን መልካምነው።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1296 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1018 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us