ራሱ ባወጣው ሕገመንግሥት የማይገዛ መንግስት ለዜጎች በሕይወት መኖርም ሆነ ለሰብአዊ መብት መከበር ደንታ አይኖረውም

Thursday, 28 September 2017 14:49

 

ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት (መድረክ)

የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

ከዛሬ 26 ዓመት በፊት የአምባገነኑ የደርግ መንግስት ሲገረሰስ የኢትዮጵያ ሕዝብ የነበረው ተስፋና ምኞት ወደፊት አገራችንን ዘላቂ ሠላምና ሕገመንግስታዊ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንደሚሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት እንደሚገኝ፣ ሕዝቡ በነፃ ፍላጎቱ የህግ የበላይነት እና በራሱ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ፌዴራላዊ መንግስት በማቋቋም፣ የግለሰብና የቡድን መብቶችን እና የብሔር ብሔረሰቦችን እኩልነት በማረጋገጥ አንድነቱ የተጠበቀ ኢትዮጵያን በጋራ ለማየት ነበር።

ዛሬ አገሪቷ በምትተዳደረው ሕገ መንግስት አንቀጽ 32/1 መሠረት “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ ሀገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጪ ዜጋ በመረጠው የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከሀገር የመውጣት ነፃነት አለው”። ሕገመንግስታዊ ድንጋጌውን ለማስከበር ባለመቻሉ እንሆ ዜጎች ከአንዱ ክልል ወጥተው በሌላው ወይም በጎረቤት ክልል ውስጥ ለግድያ እና ለመፈናቀል ይዳረጋሉ።

ይህንን እንድናነሳ ያስገደደን ሰሞኑን እንደታየው በምሥራቁ አገራችን ክፍል፣ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልላዊ መንግስታት መካከል በድንበር ጥያቄ ምክንያት በተነሣው ግጭት ዜጎች ለሞት፣ ከነበሩበት ቀዬ፣ ከቤት ንብረታቸው የመፈናቀል አሰቃቂ በደል ብቻ ሳይሆን የወደፊት አብሮነትን ተፈታታኝ ችግር ገጥሞናል። ማንነታቸው የማይታወቁ፣ የተደራጁና የታጠቁ ልዩ ኃይሎች ከቦታ ወደ ቦታ እየተዘዋወሩ ሕዝቡን እየገደሉ የሚያፈናቅሉ ኃይሎች መኖራቸው በሁለቱ መስተዳደር ኃላፊዎች ተገልጿል። ይህ ታጣቂ ኃይል ከማን ትዕዛዝ እንደሚቀበል በውል የሚታወቅ ነገር ባይኖርም ሁለቱም ክልሎች አንዱ በሌላው ላይ ከማሳበብ በስተቀር የእነኝህ ኃይሎች አዛዥ ማን እንደሆነ በግልጽ ያስታወቁት ነገር የለም። ይሁን እንጂ እነዚህ ልዩ ኃይል ተብየዎች እና ለዜጎች ሰብአዊ ህልውና ደንታ የሌላቸው በፌዴራል መንግስት ዕውቅና በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል መስተዳደር አደራጅቶ እና አሰልጥኖ እንዳሰማራቸው የአደባባይ ሚስጢር ነው።

መንግሥት የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነትና ግዴታ እንዳለበት ይታወቃል፤ ይሁን እንጂ በዚህ በድንበር ጥያቄ ሰበብ ለዘመናት አብረው የኖሩ ክፉና ደጉን ያዩ ሕዝቦች “አንተ የዚህ ክልል ዜጋ አይደለህም ውጣ ወደ ክልልህ ሂድ” የሚባልበት ጉዳይ ሊኖር አይገባም። ሕገ መንግሥቱን አክብሮ የሚያስከብር መንግሥት እንዲህ ዓይነት ነገር ሲፈጸም የዜጎችን መብትና የአከባቢው ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት ያለምንም ጥርጥር የኢህአዴግ መንግሥትና ክልል መስተዳድሮች ነበር። ይህ ሣይሆን ቀርቶ ግን በድንበር ጥያቄ ምክንያት የተነሣ በሁሉም አገራችን ክፍሎች ለማለት በሚቻልበት ሁኔታ ግጭቶች እየተበራከቱ ነው፣ የብዙ ሰዎች ሕይወት በከንቱ አልፏል፣ ሕዝቦች በከፍተኛ ደረጃ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ይኖሩ የነበሩ 55,000 የኦሮሞ ተወላጆች ተፈናቅለው አሁን በምሥራቅ ሐረርጌ ተጠልለው የወገንን ዕርዳታ ፈላጊ እንደሆኑ ከደረሱን መረጃዎች ለማወቅ ተችሏል። ግጭቱ የሱማሌ ክልል ከኦሮሚያ ክልል ጋር በሚያዋስነው ከምሥራቅ ሐረርጌ እስከ ደቡብ ክፍል ሞያሌ ድረሰ ተስፋፍቶ በዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ ይገኛል።

ወደኋላ መለስ ብለን ብንመለከት ባለፈው 2009 ዓ.ም ዘመን አገራችን የተለያዩ አስከፊ ክስተቶችን አስተናግዳለች። የሕዝብ ብሶት ከገደብ አልፎ አደባባይ የወጣበትና የደረሰበትን ችግር ሠላማዊ በሆነ ሁኔታ መንግሥትን የጠየቀው ሕዝብ ተተኩሶበታል። ኢህአዴግ በ2007 ዓ.ም በተደረገው ሀገር አቀፍ ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝብ መቶ በመቶ መርጦኛል በማለት የሀገሪቷን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበሮቹን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ ባለበት ወቅት ሕዝብ በዴሞክራሲ አለመኖር፣ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ሙስና በመንሰራፋቱ፣ ለሰብአዊ መብት መረጋገጥና በነፃነት መኖር፣ የሥርኣት ለውጥ ጥያቄ አንስቶ እንዲፈታለት ጠይቋል።

የኢህአዴግ መንግሥት ሕዝብ ያቀረባቸውን የመብት ጥያቄዎች ተገቢ መሆናቸው ተቀብሎ ምላሽ ባለመስጠቱ የተነሣ ለደረሰው ጉዳት መንግሥት የሚያምንና ኃላፊነቱንም እንደሚወስድ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይፋ አድርገው ይቅርታ ጠይቀዋል። ሕዝቡም ኢህአዴግ ቆራጥ ሆኗል፣ የሕዝብን ጥያቄ ካለምንም ማመንታት በራሱ ወስኖ የቀረቡትን ብሶቶች ያስተካክላል፣ ዴሞክራሲያዊ አሠራርን ይከተላል ብሎ ይጠብቅ ነበር። ይሁን እንጂ ከሕዝብ ለቀረበለት ጥያቄ ወዲያውኑ አፋጣኝ መልስ የሚሰጥ መስሎ ራሴን በጥልቅ ተሀድሶ አድርጌያለሁ በማለት ራሱን እንደገና አደራጅቶ የካቢኔ ሹም ሽር ከላይ እስከ ታች ቀበሌ ድረስ አድርጎ ሕዝቡ የጠየቀውን መልስ እሰጣለሁ በማለት ቀድሞ ይዞት በነበረው ሁኔታ ቀጥሏል። ኢህአዴግ የአቋም ለውጥ ለማድረግ ባለመቻሉና ከሕዝብ ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ባለመቻሉ የሕዝብ ቅሬታ ቀጥሎ በአገሪቷ ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች ህዝባዊ ተቃውሞ አስከትሏል።

እንዲያውም ተፈጥሮ ያስከተላቸው ችግሮች ሳይጨመሩ የሕዝብን ብሶት ከሚያባብሱ እርምጃዎች አንዳንዶቹ መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ላይ ታላቁ  የኦሮሞ ባህልና ኃይማኖታዊ የእሬቻ በዓል አከባበር ላይ የብዙ ወገኖች ህይወት ዘግናኝ አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ ጠፍቷል።

የሕዝብ ቅሬታ ተባብሶ ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ ሆነ በማለትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት ከ20,000 በላይ ዜጎች እስር ቤት የታጎሩበትና ለ10 ወራት ያህል ከሕገ መንግስቱ ድንጋጌ ውጪ የዜጎች መብት በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተገደበበት ጊዜ ነበር።

በአነስተኛ ግብር ከፋዮች ላይ የመክፈል አቅምን ያላገናዘበና ትኩረት ተሰጥቶት ከከፋዩ ህብረተሰብ ጋር በቂ ጥናትና ምክክር ሳይደረግበት የተወሰነው ግብር ቅሬታን ፈጥሯል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩም ጥናቱ 40በመቶ ግድፈት ያለበት መሆኑን ገልጸውታል።

በየጊዜው የፍጆታ ዕቃዎችና የሸቀጣ ሸቀጥ መግዣ የዋጋ እየናረ በመምጣቱ ዋጋ ግሽበት ሊጨምር ችሏል። ይህም በሸምቶ አደሩ ኅብረተሰብ ላይ ቀላል የማይባል ችግር እንደፈጠረ ይታወቃል።

የ2009 ዓ.ም ዘመን በዚህ ሁኔታ ቢታለፍም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ በአዋሳኝ ድንበሮች አከባቢ በተነሣው ግጭት ሁሉም የአገራችን ክፍሎት በዜጎች ላይ የሚደርሰው ሞት፣ ስደት፣ ከቤት ንብረት መፈናቀል በርክቷል።

አሁን በተያዘው አዲሱ 2010 ዓመት መግቢያ ቀደም ብሎ ተጀምሮ የነበረው ግጭት አሁንም እየተካሄደ ነው። መስከረም 2 ቀን 2010 ዓ.ም አወዳይ ከተማ የ12 ኢትዮጵያዊያን ሱማሌዎች እና የ6 ኦሮሞዎች ሕይወት አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ በተደራጁና በታጠቁ ኃይሎች ግድያ ተፈጽሞባቸዋል። ኢትዮጵያ ሱማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መስተዳደር የ12ቱ ሟቾች ቀብር ሥነ ሥርዓት በተፈጸመበት ጊዜ ወዲያውኑ በክልሉ የ7 ቀናት ብሔራዊ ሃዘን እንዲሆን አውጀዋል። በግፍ ለተገደሉት ዜጎች የሐዘን ቀን ለምን ታወጀ ሳይሆን ሀዘኑንም ሆነ ደስታውን ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ባማከለ መልኩ መሆን ነበረበት። በደቡቡ የአገራችን ክፍል በኦሮሚያና በሲዳማ ብሔረሰቦች መካከል  ተመሳሳይ ግጭት ተነስቶ መጠነኛ ጉዳት ደርሷል። በጉጂ ኦሮሞና በቡርጂ ብሔረሰብ መካከል የተካሄደው ግጭት ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። መስከረም 2 ቀን 2010 ዓ.ም በተቀሰቀሰው ግጭት ከቡርጂ የአንድ ታዳጊ ሕፃን ጨምሮ 3 ሰዎች ሲሞቱ 5 ሰዎች ደግሞ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል። ብዙ የእህል ክምር በዚሁ ሰበብ ሊቃጠል ችሏል። ከመስከረም 1 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በገላና አባያና በቡሌ ሆራ ወረዳ በሚኖሩ የጉጂ ኦሮሞ እና በአማሮ ወረዳ ውስጥ በሚኖሩ የኮሬ ብሔረሰብ መካከል በተከሰተው ግጭት በኮሬ በኩል የሰባት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ የ14 ሰዎች ደግሞ በጽኑ ቆስለዋል። በጉጂ በኩል ደግሞ የ8 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ በርካቶች ቆስለዋል።  በዚሁ ግጭት እስከ 40,000 የሚደርስ ሕዝብ ከነበረበት ቤት ንብረቱ ተፈናቅሏል።

መስከረም 7 ቀን 2010 ዓ.ም በባሌ ዞን አዳራጋ ወረዳ ቢዩ ቀበሌ 16 ሰዎች በተደራጁና በታጠቁ ልዩ ኃይሎች ግድያ ሲፈጸምባቸው 4 ሰዎች ቆስለው ጊኒር ሆስፒታል በመታከም ላይ እንደሆኑ ታውቋል።

በዚህ በባሌ ዞን ከአንገቶና ሌንሳዎ ወረዳዎች በእነዚህ ማንነታቸው በውል በማይታወቁ ታጣቂዎች በተነሣው ግጭት 1700 የሚደርሱ አባወራዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። እነዚህ ከነቤተሰባቸው ጭምር ወደ 5000 የሚደርሱ ሰዎች የመፈናቀል ዕጣ እና ሌሎች ችግሮች የድሃ ዜጎቻችን ሕይወት ወደ አዘቅት ከመወርወሩም በላይ ሠላምን ያደፈርሳል።  

ይህ ከድንበር ጥያቄ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ለወደፊት በሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ ግጭት አይከሰትም የሚል እምነት የለንም። በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መካከል የወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄ ጉዳይ ብዙ ጊዜ ሁለቱ ክልሎችን ሲያወዛግብ እንደቆየ ይታወቃል። ይሁን እንጂ የሁለቱ ርዕሳነ መስተዳድሮች ስምምነት ተደርጓል ተብሎ በመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ተገልጿል። ስምምነቱ የሕዝብ ፈቃደኝነት ጭምር ከሆነ ዘላቂ ሠላም የመፍጠሩ ጉዳይ ከተሳካ የመድረክ ምኞቱ መሆኑን በአጽንኦት ይገልጻል።

በየአካባቢው የሚከሰቱ ግጭቶች ላይ ላዩን ሲታይ ሕዝቦች በድንበር ጥያቄ ምክንያት የሚነሣ ነው ተብሎ ቢቀርብም እውነታው ግን ሕዝቡ ለዘመናት አብሮ የኖረ፣ ክፉና ደጉን የሚራ ሕዝብ እንጂ በዕለት ሁኔታ ተነሳስቶ በድንበር አሳቦ እስከመጠፋፋት እና ለከፋ አደጋ እንደማይደርስ እናውቃለን። ገዢው ፓርቲና መንግሥት የአስተዳደር መዋቅሩ ከላይ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ጎጥ ድረስ ዘርግቶ ሕዝቡን 1 ለ 5 የስለላ መረቡን ዘርግቶ ባለበት ሁኔታ ከመንግሥት እውቅና ውጭ የሚፈጸም አንዳችም ክፉም ሆነ በጎ ነገር እንደማይኖር እርግጠኞች ነን።

በሁሉም አገሪቷ ክልሎች የገዢው ፓርቲና መንግስት ካቢኔዎችና ካድሬዎች አማካይነት ችግሮቹ እንዲባባሱ እንደሚያደርጉት እንገምታለን። ይህም የሕዝባችን የወደፊት አብሮነት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ፍላጎት ያላቸው ወገኖች ጣልቃ በመግባት ሁኔታዎችን ወደ ሕዝቦች ዕልቂት እንዳያመራና የበለጠ እንዲባባስ የሚፈልጉ አካላት ያሉ መሆኑን ይጠቁማል። ለመሆኑ ለዘመናት በሠላም አብሮ የኖረው ሕዝብ አሁን ተነሥቶ በድንበር ግጭት ምክንያት ለዚህ ከፍተኛ ዕልቂትና መፈናቀል እንዴት ሊደርስ ቻለ? ለሚለው ጥያቄ ሀገሪቷን የሚያስተዳድረው ፓርቲና መንግሥት ራሱ ባወጣው ሕገ መንግሥት የማይገዛ መንግሥት መሆኑን አስምረንበት እንናገራለን። ይኼውም ሕዝብ ቀደም ሲል ያነሳቸው፣ የዴሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ የመብትና የስርዓት ለውጥ ጥያቄዎችን ላለመመለስና የሕዝቡን ሠላማዊ ትግል አቅጣጫ ለማስቀየር የታቀደ ዘዴ ሆኖ አግኝተናል።

ዜጎች ሉአላዊ ሀገርና መንግሥት በጋራ የሚመሰርቱት በግል የሚደርስባቸውን ጥቃት መንግሥት እንዲከላከልላቸው፣ የጋራ ኃይል ለመፍጠር፣ መሠረተ ልማትን እንዲሠራላቸው፣ ደህንነታቸውና ፀጥታን እንዲያስከብርላቸው ወዘተ… ብለው ነው። ነገር ግን የኢህአዴግ መንግሥት የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ አገልግሎቶች ማስፋፋት፣ የመሠረተ ልማት ውጥኖች ሁሉ በራሱ ችሮታ ያደረገ እያስመሰለ በየጊዜው በሚቆጣጠረው የብዙኃን መገናኛ መሣሪያ ሕዝብን  ለማሞኘት ይሞክራል። የሕዝብ መንግሥት የገዛ ሕዝቡን ያከብራል፣ ይታዘዛል፣ የሕዝቡ ተቀጣሪ ነው፣ አምባገነን መንግሥት ሕዝብን ይንቃሉ፣ የሚከሰቱ ችግሮችን በኃይል ለመፍታት ያምናሉ፣ ሁሉን ነገር ከሥልጣኑ አንፃር ለማየት ይጥራሉ።

ኢህአዴግ በባሕርዩ በህዝቦች ስቃይ የራሱን የስልጣን ዘመን ለማራዘም ሲል የማይጠቀማቸው ስልት የለም። መድረክ፤ ኢህአዴግ አዘወትሮ የሚጠቀምባቸዉን ስልቶች ጠንቅቆ ያውቃል። አሁን በየቦታው ዳር ድንበርን በማካለል ስልት ሕዝቦችን በካድሬዎች አማካይነት እያጋጨ፣ እያለያየ ለጊዜ ማራዘሚያ የሚጠቀምበት ስልት ነው። ስለዚህ ሁሉም ዜጎች ይህንን ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው ችግሮቻቸውን ከሌላ ጣልቃ ገብነት ውጪ ራሳቸው ተቀራርበው ሊያጋጩዋቸው በሚችሉት ጉዳዮች ላይ በመግባባት ተወያይተው መፍታት እንደሚችሉ ለማስገንዘብ እንወዳለን። ለዚህም አፋጣኝ ጥሪ እናደርጋለን።

አምባገነኖች ሕዝብን ለመከፋፈል ቢሞክሩ እንኳን የአንዱ ብሔር ሕልውና ለሌላው ብሔር ህልውና አስፈላጊ ነው። በኢህአዴግ ጠባብ ፍላጎት የፌዴራል ስርዓቱ በዴሞክራሲያዊ አሰራር ባለመታጀቡም የፌዴራል ስርዓቱ አደረጃጀት ለግጭቶቹ መንስኤ ተደርጎም ሊወሰድ አይገባም።

መድረክ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በአገሪቷ ውስጥ እየተፈጠረ ያለው ፈርጀ ብዙ ችግሮች ኢህአዴግ በያዘው ሁኔታ መቀጠሉ አደጋ ያለው መሆኑን ከማስገንዘብ የቦዘነበት ጊዜ የለም። እነዚህ ችግሮች የሚፈቱበትን መንገድ ለማሳየት የዴሞክራሲ ምህዳሩ እንዲሰፋ፣ ኢህአዴግ ላወጣው ሕገመንግሥት ተገዢ እንዲሆን፣ ዜጎች በአገራቸው ጉዳይ ውስጥ ወሣኝ መሆናቸው ታውቆ በተለይም የአገራችን ጉዳይ ይገባናል የሚሉ ፓርቲዎች በክብ ጠረጰዛ ተቀራርበው ሠላማዊ በሆነ ሁኔታ ችግሮችን መፍታት እንዲችሉ ገለልተኛ በሆኑ ወገኖች ማዕከልነትና በታዛቢዎች አማካይነት የጋራ ድርድር ለማድረግ መድረክ ምንጊዜም ዝግጁ ሆኖ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።

በአጠቃላይ የጠቀስናቸው ችግሮች የኢህአዴግ መንግስት መዋቅሩን ከላይ እስከ ታች ድረስ ዘርግቶ በሚያስተዳድረው ሕዝብ ላይ የተፈጸሙ ጉዳዮች ስለሆኑ ተጠያቂው ራሱ መንግሥት ነው፣ ስለዚህ፡-     

1.በአገሪቷ ውስጥ በድንበር ጥያቄ ምክንያት እና በሕዝቦች መካከል በተከሰቱ ግጭቶች ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች ቤተሰቦች መቋቋሚያ እንዲከፈላቸው።

2.በመንግሥት አስተዳደር ድክመት ምክንያት የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ ባለመቻሉ እንዲያውም የየአካባቢው ካድሬዎችና ካቢኔዎች አባባሽነት ምክንያት ለተፈጠረው የዜጎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀል ተጠያቂዎች ስለሆኑ መንግሥት በአስቸኳይ ተፈናቃዮቹ ወደነበሩበት ቀዬአቸው ተመልሰው የቀድሞ ሰላማዊ ኑሮአቸውን እንዲቀጥሉ እንዲያደርግ አጥብቀን እንጠይቃለን።

3.የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት በጋራም ሆነ በተናጠል የአካባቢውን ፀጥታ፣ ሠላም የማስከበርና የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነትና ሕገመንግስታዊ ግዴታ አለባቸው። በመሆኑም ማንነታቸው ያልታወቀ ታጣቂ ኃይሎች በቡድን ተደራጅተው ምንም ትጥቅና የመከላከል ኃይል በሌላው ሕዝብ ላይ ዘምተው ይህን የከፋና ዘግናኝና አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ የንፁሐን ዜጎች ህይወት ሲጠፋና ከነበሩበት ቀዬአቸው እንዲፈናቀሉ ሲደረግ ባለሥልጣኖቹ አስቀድመው አያውቁም ማለት አይቻልም። የከፋ ጉዳት ከመድረሱ በፊት እርምጃ መውሰድ ሲገባቸው ይህንኑ ባለማድረጋቸው ለጠፋው የዜጎች ሕይወትና ለደረሰው ውድመት በሕግ እንዲጠየቁ እናሳስባለን።

4.ይህን ኃላፊነት የጎደለውን ሰይጣናዊ ድርጊት ለዘመናት አብሮ ተከባብሮ በሠላም በመኖር ላይ ባለው ሕዝብ መካከል ግጭቶች እንዲባባሱ፣ የዜጎች ሕይወት እንዲጠፋ፣ ንብረት እንዲወድም፣ ሕዝብ እንዲፈናቀል ያደረጉ፣ ለዚህ በቀጥታ አመራር የሰጡ፣ የፈጸሙ፣ የተባበሩ ከፌዴራል መንግሥት ጀምሮ እስከ ታችኛው ቀበሌ አመራር ድረስ እጃቸው ያለበት፣ በመንግሥታዊ መዋቅር ውስጥ ያሉ ሁሉ ለጠፋው የሰው ሕይወትና ለደረሰው ውድመት ተጠያቂዎች ናቸው። ስለዚህ ጥፋቱን ገለልተኛ የሆነ አካል አጣርቶ ጥፋተኞች በሕግ እንዲጠየቁ እንዲደረግ እናሳስባለን።

በመጨረሻ ሕዝባችን ለወደፊቱ በዚህ ሰይጣናዊ ድርጊት የተነሳ በወገኖቻችን ላይ ለተፈጸመው የሞት አደጋ ጥልቅ የሆነ ሀዘናችንን እየገለጽን እንደዚህ ዓይነት የጥቃት እርምጃዎች እንዳይጋለጥ አብሮነትን የሚሸረሽሩ ወቅቱን እየጠበቀ የሚከሰተውን ግጭት ሕዝቡ አንድነቱን አጠናክሮ ነቅቶ በመጠበቅ ስርዓት በተሞላበት እና ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ አንድነቱን አጠናክሮ አስፈላጊውን የዕርምት እርምጃ እንዲወስድ መድረክ አበክሮ ያሳስባል።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2010 ዓ.ም

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
183 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1069 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us