የዛሬው ትውልድ ከዓድዋ ምን ይማር?

Wednesday, 01 March 2017 12:35

 

ከአባ መላኩ

የዓድዋን ድል 121ኛ ዓመትን ለመዘከር ጥቂት ቀኖች ቀርተውናል። ስለ ዓድዋ ድል አንጸባራቂነትና ዘመን ተሻጋሪነት በርካታ የታሪክ ተመራማሪዎች የየራሳቸውን ምስክርነት ሰጥተዋል። ሁሉም የታሪክ ጸሃፊዎች የዓድዋ ድል የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን፣ ከዚያም አልፎ የመላ ጥቁር ህዝቦችን ታሪክ ቀያሪ ክስተት እንደሆነ ይስማማሉ። ኢትዮጵያ ኢትዮጵያዊያኖች ልዩነታቸውን አቻችለው አገራቸውን ሊወር የመጣውን ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀውን የአውሮፓ ሃይል በኋላቀር መሳሪያ መመከት መመከት ችለዋል። ለዓድዋ ድል መገኘት ዋንኛና ትልቁ ምክንያት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ልዩነታቸውን አቻችለው አንድነታቸውን አጠናክረው ወራሪውን የቀኝ ገዥ ሃይል መመከት በመቻላቸው ነው።


የዓድዋ ድል አውሮፓዊያን አፍሪካን የሚያዩበትን የተሳሳተ መነጽር እንዲለውጡት አስገድዷቸዋል። በአውሮፓዊያን ስለአፍሪካ ያላቸውን የንቀት አተያይ እንዲያጤኑት፣ ጥቁሮች ለመብቶቻቸው የሚሞቱ መሆናቸውን እንዲረዱት አድርጓቸዋል። አውሮፓዊያን አፍሪካን የሚወስዷት የኋላቀርና አቅም የሌላቸው ህዝቦች መኖሪያ አድርገው የነበረውን አስተሳሰብን ያስወገደው የዓድዋ ድል ነው። የዓድዋ ድልን የተመለከቱ የአለም ጥቁር ህዝቦች የፀረ-ቅኝ አገዛዝ ንቅናቄ እንዲያቀጣጥሉ ሞሯል ሆኗቸዋል። ወራሪውን ኃይል ጨምሮ በዘመኑ የነበሩ አውሮፓ ሃያላን መንግስታት በአፍሪካን ለመቀራመት የሚያደርጉትን ሩጫ እንደገና እንዲያጤኑት አስገድዷቸዋል። ለአብነት የኢትዮጵያን ነፃና ሉዓላዊ አገርነትን ሳይወዱ በግድ እንዲቀበሉ ሆነዋል። ከዓድዋ ድል ማግስት ምዕራባዊያኖች በአዲስ አባባ ኤምባሲያቸውን ከፍተው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ጀምረዋል።


የዓድዋ ድል ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን በአንድ ጥላ ማሰባሳብ የቻለ አለምን ያስደመመ ታላቅ ተጋድሎ ነው። የዓድዋ ድልን ልዩ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል በቀዳሚነት የሚነሳው ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በመካከላቸው ያሉትን በርካታ ልዩነቶቻቸውን ወደጎን በማድረግ የጋራ ጠላታቸው የሆነውን የውጭ ወራሪ ለመመከት መዝመታቸው ነው። ሁሉም የአፍሪካ አገሮች እዚህ ግባ በማይባል ትግል አገራቸውን ለአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች አሳልፈው ሲሰጡ ኢትዮጵያዊያኖች ግን በተጋድሎ የአገራቸውን ዳር ድንበር ማስከበር ችለዋል።


እንደ ዶናልድ ሌቪን ያሉ የታሪክ ተመራማሪዎች እንደሚሉት የአድዋ ድል ለኢትዮጵያ ህዝቦች የኋላ ታሪካቸው የትብብር ማሳያ ነው ሲሉ ጽፈዋል። አዎ ይህ አባባል ትልቅ መልዕክት ያለው ነው። የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ስንቅና ትጥቃቸውን ተሸክመው በእግራቸው ሺህ ኪሎሜትሮችር ተጉዘው የአውሮፓ ዘመናዊ መሳሪያን የታጠቀን ጦር ገጥመው ድል ማድረግ መቻላቸው ምን ያህል ጥልቅ የአገር ፍቅር እንዳላቸው የሚያሳይ ነው። የዓድዋ ድል የአያቶቻችንን የአገር ፍቅር ጽናት ያረጋግጣል፤ የዓድዋ ድል የአያቶቻችንን የመቻቻል ባህል ያሳያል፤ የዓድዋ ድል አያቶቻችን በመካከላቸው ያለውን ልዩነቶች እንዴት በአግገባብ እንደያዙት ያስተምራል፤ ባዕዳን በልዩነታቸው እንዳይጠቀም እንደተከላከሉ ያሳያል ፤ አዎ አዲሱ ትውልድ ከዓድዋ ድል በርካታ መልካም ነገሮችን ሊቀስም ይገባል።


በዓድዋ ጦርነት ወቅት የታየው የአንድነትና የትብብር መንፈስ ሁኔታ አለምን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊያን መሪዎችን ጭምር የሚያስገርም ነበር። ጥሪ የደረሰው የትኛውም ብሄር፣ ብሄረሰብና ህዝብ ለጦርነቱ ስኬት የሚችለውን ሁሉ አድርጓል። ሁሉም በአቅሙ ስንቅ ከማዘጋጀት እስከ ግንባር መሰለፍ ድረስ ተሳትፎ አድርጓል።


በቅኝ ግዛት ዘመን የአውሮፓ ወራሪ ኃይሎች አፍሪካን ለመቀራመት ይጠቀሙበት የነበረው ቀዳሚ ስትራቴጂ ከፋፍለህ ግዛው የሚባለውን ስትራቴጂ ነበር። ወራሪው የኢጣሊያ ሃይልም የኢትዮጵያ ህዝቦችን የትግል መንፈስ ለማዳከም ሲል የተለያዩ የመከፋፈያ ስልቶችን ለመጠቀም ቢሞክርም ህብረተሰቡ በአገሩ ሉዓላዊነት ላይ አንደራደርም በማለቱ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲው ሊሳካለት አልቻለም።


የአባቶቻችን የአንድነት የትግል መንፈስ ለአሁኑም ሆነ ለቀጣዩ ትውልድ ትልቅ ትምህርት ሊሰጥ የሚችል ነው። እንደእኔ እንደኔ ዛሬ ያ የአያቶቻችንና መንፈስ ያስፈልገናል። በቅርቡ እንደተመለከትነው አንዳንድ ወገኖች የግብጽና ኤርትራ መንግስታትን ድብቅ አጀንዳ ለማሳካት ሲሯሯጡ ተመልክተናል። እነዚህ አካላት አያቶቻችን ለአገራቸው አንድነት ሲሉ የከሰከሱትን አጥንት ያፈሰሱትን ደም እየረገጡ እንደሆነ ያስተዋሉት አይመስለኝም።


በቅኝ ግዛት ማስፋፋት ሩጫ ወቅት የአውሮፓ ወራሪ ሃይል በርካታ የአፍሪካ አገሮችን በቀላሉ ማንበርከክ ቢችሉም ኢትዮጵያ ግን ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀውን የጣሊያን ጦር አሳፍራ በመመለስ ለነጻነቷ አሻፈረኝ የሚሉ ህዝቦች መኖሪያ መሆኗን በተግባር አሳይታለች። ኢትዮጵያዊያን ልዩነታቸውን ማቻቻል የሚችሉ፣ ምንም ያህል የውስጥ ቅራኔ ቢኖራቸውም የጋራ ጠላት በመጣ ጊዜ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን አንድ መሆን የሚችሉ መሆናቸውን በአድዋ ድል በተግባራ አሳይተዋል።


ለጦርነት ስኬት ዘመናዊ መሳሪያ ብቻውን ፋይዳ እንደሌለው ይልቁንም የአላማ ጽናትና ፍቅር ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ በዓድዋ ጦርነት ኢትዮጵያዊያን ለአለም አረጋግጠዋል። ጣሊያኖች በወቅቱ ለራሳቸው ዘመናዊ መሳሪያና በቂ ዝግጅት በሰጡት ትልቅ ግምት እንዲሁም ኢትዮጵያዊያንን የተከፋፈሉና ኋላቀር መሳሪያ የታጠቁ ናቸው በሚል ስሌት ሳቢያ የአውሮፓው ግዙፍ ሰራዊት በኢትዮጵያ አገር ወዳድ አርሶ አደሮች ሽንፈትን ተከናንቧል። በዚህም ሳቢያ በቅኝ ገዠዎች ዘንድ ትልቅ መደናገርን ፈጥሯል።


ከላይ ለማንሳት እንደተሞከረው ለዓድዋ ድል ሰኬት የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች የነበራቸው ልዩነት ወደጎን በማድረግ በወራሪው ጠላት ላይ በጋራ መሰለፍ መቻላቸው ነው። አዎ ኢትዮጵያዊያን ሁሌም በውስጥ ጉዳያቸው ማንም ጣልቃ እንዲገባ እንዲሁም ማንም የውጭ ሃይል የአገራቸውን ህልውና እንዲደፍር አይፈቅዱም። ለዚህ በርካታ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል። በቅርቡ በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ወቅት የኤርትራው መንግስት ኢትዮጵያ ተከፋፍላለች፤ ከእንግዲህ ህዝቡ በአንድነት ሊቆም አይችልም በሚል የተሳሳተ እሳቤ ወረራ ፈጽሞ ነበር። ይሁንና ኢትዮጵያዊያን ምንም አይነት ልዩነት ቢኖራቸውም በአገር ጉዳይ ላይ አንድ ናቸው። ይህንንም በተግባር አሳይተዋል። የኤርትራ መንግስት ለዓመታት የገነባውን ሰራዊት በቀናት ምናልባትም በወራት ውስጥ ነበር የወራሪውን ሃይል አከርካሪ መስበር የቻሉት። ይህ ነው አንድነት፤ ይህ ነው ኢትዮጵያዊነት።


አያቶቻችን ባላቸው የአገር መውደድና የጀግንነት መንፈስ ወራሪውን የጣሊያን ጦር መመከት መቻላቸው አገራቸውን ከቅኝ ግዞት ታድገዋታል። እኛንም በራሳችን ስብዕና እንድንኮራ አድርገውናል። እኛም ድህነትን በመዋጋት የተሻለች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ማውረስ ይኖርብናል። በመሆኑም የዚህ ትውልድ ገድጅ መሆን ያለበት ድህነትን መዋጋት ነው። የድህነት ወጊያ ደም አይጠይቅም፤ አካል መጉደልንም አይጠይቅም፤ ከዚህ ትውልድ የሚፈለገው በተሰማራበት የስራ መስክ በታማኝነትና በቅንነት ህብረተሰብን ማገልገል ብቻ ነው።


የዓድዋ ድል ኢትዮጵያዊያኖች በቅኝ ግዛት ላይ የማያወላዳ አቋማቸውን ያስመሰከሩበት ትልቅ ገድል ነው። የዓድዋ ድል የፍትህ መጓደልን ሰዎች በጋራ መከላከል እንደሚችሉ የሳየ ታላቅ የዓለማችን ክስተት ነው። ምክንያቱም በዚያን ወቅት፣ እንደዚህ ያለ ታላቅ ህዝባዊ ተጋድሎ በየትኛውም የዓለም አገር ተደርጎ አይታወቅም።


ዓድዋ የመላው አፍሪካዊያን ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ህዝብ ከዚያም አልፎ የመላው ፍትህ የተጓደለበት ህዝብ ድል ነው። የአሁኑ ትውልድ ከዓድዋ ድል ሊቀስመው የሚገባ ዋናው ትምህርት በአገራዊ ጉዳይ ላይ ልዩነት ማድረግ እንደማይገባ ነው። የውስጥ ችግሮቻች እንዳሉ ሆነው ከውጭ የሚቃጣ ወረራንም ይሁን ከውስጥ የሚነሳን አገር የማፍረስ ዘመቻን በጋራ የመከላከል ኃላፊነትን ካለፉት ትውልዶች ልንማር ይገባል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
481 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1053 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us