ዓለም እንደቆዳ ተወጥራለች

Wednesday, 12 March 2014 12:57

እዮብ ሳለሞት

Kinghouse This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

መቼም እንደ አንድ ሃለፊነት እንደሚስማው ወጣት በዓለማችን ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ እየተከሰቱ ያሉትን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ቀውሶችን ተገንዝቦ ያሉትን ክፍተቶች ለሰፊው ህዝብ ማሳወቅ የሞራል ግዴታ ነው። በአንድ ፕላኔት ከመኖራችን ጋር ተያይዞ በአንድም በሌላ መልኩ ተፅእኖ ያሳድርብናል። በአሁኑ ወቅት ልብ ብለን ካስተዋልነው ዓለማችን እንደቆዳ እየተወጠረች ነው። በየትኛውም የዓለማችን ክፍል ህዝቦች በሰላም ወጥተው እንዳይኖሩ፣ ኑሮዎቸውን እንዳያሻሽሉ፣ ለዓለም የተሻለ ስራ እንዳያበረክቱ በተለያዩ ቀውሶች እየታመሱ ይገኛሉ። በአጠቃላይ የጥይት እሩምታ፣ የወላጆች ሰቀቀን፣ የህፃናት ዋይታ ሳይሰማ የማያድርበት ሁኔታ ላይ ደርሰናል። በየዜና ማሰራጫ አውታሮችም በኢራቅ፣ አፍጋኒስታን በሶማሊያ በመሳሰሉት ሀገራት በየቀኑ በአጥፍቶ ጠፊዎች በሚሰነዘሩ ጥቃቶች በርካታ ዜጎች እንደሚያልቁ እየሰማን፣ እያየን ነው። የችግሮቹ ምክንያቶች በርካታ ናቸው በዋነኝነት ግን ሀላፊነት የማይስማቸው መሪዎች ልዩነትን እንደሃጥያት የማየት ባህል፣ እንዲሁም ሀያላን ሀገራት በእርስ በእርስ ጦርነት ለማትረፍ በሚያደርጉት ጥረት መሆኑ በስፋት ይነገራል። በአንድ በኩል በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ሲቭል ማህበራት የሃይማኖት ተቋማት፣ የሰላም አስከባሪ ሃይል ወ.ዘ.ተ. እንዳሉ ሆነው በተቃራኒው የማያባሩ የእርስ-በእርስ ጦርነቶች፣ ስራ-አጥነት፣ ፍልሰት፣ ሽብርተኝነት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ የመጡበት ሁኔታ አለ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአውሮፓ ህብረት አፍሪካ ህብረት እንዲሁም መሰል ተቋማት እያሉ ዓለማችን እንዲህ ስትናጥ መዋልና ማደሩ የሆነ ክፍተት እንዳለ እያሳየ ነው።

የሶርያ ጉዳይ ይህን ያሳያል በሽር አላሳድ እንደዚያ ላለፉት 3 ዓመት በሶርያ ህዝብ ህይወት ላይ ሲቀልድ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአቋማን የውግዘት መግለጫ ከመስጠት ባለፈ በሶርያ ከተሞች በሆምስ በአፖሎ በየመንደሩ ፍርስራሽ ውስጥ ሆነው በስጋት ለሚባዝኑት ስለማዊ ዜጎች ጠብ ያለ ነገር የለም። ሩሲያ አሳድን በማስታጠቅ አሜሪካ ለተቃዋሚ ሃይሎች ወታደራዊ እርዳታ በመለገስ የህዝቡን የስቃይ ዘመን በማራዘም ወዳጅ በመምሰል የሚያደርጉት ድራማ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የተገነዘበበት ሁኔታ ነው ያለው። በሶሪያ ኪሳራ ከርሳቸውን ለመሞምላት የሚያደርጉት ፉክክር። በዓለማችን በአብዛኛው የሚፈጠሩት ግጭቶች ከጀርባ ሆነው ጫፍ እና ሌላ ጠርዝ በመያዝ ግጭቶችን የሚያጦዙት እነኚህ የቡድን 8 አባላት ሃገሮች በዋነኝነት አሜሪካ እና እሩሲያ ናቸው ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል። በቅርቡ ጥርስ አልባው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሶሪያን በተመለከተ ሁለቱንም ወገኖች በጄኔቫ ለማደራደር ሞክሮ ተስፋ ሰጪ ውጤት አልተገኘም። እነዚያ ሁለት ልበ ድፍን ሀገራት እያሉ መሃል ተሰንቅረው በአይዶሎጂ፣ በእርዳታ ስም አንዱን እያቀረቡ ሌላውን በመግፋት ገበጣ እየተጫወቱ እንዴት ሶሪያ ወደ ቀድሞ አቋሟ መመለስ ትችላለች?

ወደ ዩክሬን ስንመጣ ሀቁ ተመሳሳይ ነው። 76 ሰዎችን ህይወት የገበረው የኬቭ አመፅ መነሻው የዩክሬን ህዝብ የራሱን እድል በራሱ እንዳይወስን እድሉ ስለተነፈገው ብቻ ነው። ደግነቱ ከጥቅም ማስከበር አሽቅድድም ባሻገር መሰል ድርጊቶች ሲፈፀሙ የአውሮፓ ህብረት ሃገራት ችግሩ ሳይዛመት ለመቅረፍ የሚያደርጉት ርብርብ አስደናቂ ነው። ጀርመን፣ ሩሲያ፣ አሜሪካ፣ ፖላንድ ወ.ዘ.ተ. የልዑካን ቡድን በማቋቋም ሚኒስትሮቻቸውን በመላክ ጉዳዩን ለማርገብ እየታገሉ ነው። ወደእኛው ጉድ ስንመጣ ያሉት ቀውሶች ሳይፈቱ ተወዝፈዋል። በቅርቡ ቦኮ -ሐራም የተባለ የምዕራባውያንን አስተምህሮት የሚቃወም ፅንፈኛ ቡድን በናይጄሪያ መቶ ሰውን በማረድ መንደሮች ሲያቃጥል የአፍሪካ ህብረት ጉዳዩን ለማውገዝ እንኳን አቅም አላገኘም። የሃይማኖት ተቋማት ቢሆንስ ምነው ድምፃቸው ጠፋ? የአለም ዓቀፍ ተቋማት የአፍሪካ ማህበረሰባዊ ቀውሶችን እንደገቢ ማስገኛ ምንጭ መጠቀማቸው ቀርቶ የመፍተሔ አካል ቢሆኑ ? ችግሩ እነዚህ ተቋማት ከመነሻው የአፍሪካ እንዲሁም የሌላውን ክፍለ ሀገር ችግሮች ለመቅረፍ አይደለም፤ የተቋቋሙት። በተቃራኒው ጭር ሲል የማይወዱ በሚፈጠሩ ቀውሶች ትርፍ የሚያጋብሱ ነገረ ስራቸው ሁሉ ከአንገት በላይ የአዞ እንባ የሚያነቡ መሰሪዎች መሆናቸው በዓለማችን ላይ እየተፈጠሩ ያሉ በርካታ ውስብስብ ችግሮች ማሳያ ናቸው።

የደቡብ ሱዳን ጉዳይ ቢሆንስ ገና በጨቅላነት ጊዜያቸው ነፃነታቸውን በተቀዳጁ ማግስት እንዲህ ቅጥ አምባሩ የጠፋበት ሁኔታዎች ውስጥ መገኘታቸው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በአንድ ስራው ላይ እንደገለፀው ችግሩ ከወንበሩ ነው ያለው ትክክል ነው። በርካታ አመታት ለደቡብ ሱዳን ህዝብ ነፃነት እንታገላለን ብለው በርካታ መስዋዕትን ተከፍሎ የተገኘውን ድል በተገቢው ሁኔታ መጠበቅ፣ ህዝቡን መሰረተ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ አልቻሉም፣በምትኩ በህዝቡ ትግል ላይ ቀዝቃዛ ውሃ የደፋ ሆነው ቁጭ ብለዋል። የስልጣን ጥመኝነት ግለኝነት በልዩነት የማመን ችግሮች አፍጠው ወጥተዋል ኡጋንዳ ጦሯን በመላክ የሳልቫኪርን መንግስት በመርዳት ላይ ትገኛለች ሀገራችን ኢትዩጵያም ካላት ታሪካዊ ቁርኝት ጋር ተያይዞ ሁለቱንም ወገኖች ለመስማማት ደፋ ቀና እያለች ነው። ይህ በጎ ተግባር ነው። ሊያስመሰግን ይገባል። ይህው ሆደ ሰፊነት በሀገራችን ውስጥ ላሉት አንድ ሺህ አንድ ችግሮች ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ከፕሬስ ማህበረሰብ ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አብሮ በመስራት መቀጠል አለበት። ይኸው መከረኛ ዓባይ ጋር ተያይዞ ከግብፅ ጋር ያለውን አሰጣ-ገባ በዓለም አቀፍ ወቅታዊ አቋም እና አስተያየት ሳንዘናጋ ያለብን የቤት ስራዎች በተገቢው መንገድ መሰራት ወቅቱ የሚጠይቀው ፈተና ነው። በቅርቡ የግብፅ መከላከያ ሚኒስትር የጦር አዛዥ ፊልድ ማርሻል አብዲልፈታህ አልሲ ሩሲያ ተጉዘው ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በድንገት መገናኘታቸውና ጉብኝት ማድረጋቸውን እንዲሁም ግብጽ የ4 ቢሊዮን ዶላር ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ለመግዛት ማቀዷን እየሰማን ነው። ለጉዳዩ ለየት ያለ ትርጉም ተሰጥቶት የመከላከያ ተቋማችን፣ ዲፕሎማቶቻችን፣ ፓርቲዎች የራሳቸው ስራ እንዲሰሩ የሚገፋፋ መሆን አለበት። የሚያሳዝነው ነገር በሌላ ክፍለ-ዓለም በተለይም በአደጉት ሀገራት አንዱ ሀገር የህዝቡን ታሪክ የሚለውጥ፣ አካባቢውንም በኢኮኖሚ ሊያስተሳስር የሚያስችል ትልቅ ፕሮጀክት ሲነድፍ ምን እናግዝ፣የትኛውን ጎደሎ እንሙላ በማለት የባለሙያ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ሲሽቀዳደሙ ማየት ልብ የሚነካ የበሰለ ማህበረሰብ መገለጫ ውጤት ነው። በአፍሪካችን ነገሩ ለየት ያለና የሚያሳፍር ነው። አንዱ ጎረቤት ሌላውን ሰላም ለመንሳት፣ የተለያዩ ክፍተቶቸን ተጠቅሞ እንዴት እንደሚያምስ 24 ሰዓት ጊዜውን፣ ዕውቀቱን፣ ገንዘቡን፣ ለማተራመስ ሲመድብ ማየት እንግዳ ነገር አይደለም። ወይ አፍሪካ!!

ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
1744 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1041 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us