የኢትዮጵያ የጸረ ሽብር ህግ ሲገመገም

Wednesday, 12 March 2014 12:51

ዝራው አሻግሬ (LLB)
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  
             
       በአለማችን ላይ በሀገራት በአንድ ድምጽ የተወገዘ ተግባር ሽብርተኝነት ነው። የሽብርተኝነት ቀጥተኛ ትርጉም ለመስጠት አስቸጋሪ ነው። የአሜሪካን ተጨባጭ  ሁኔታ እንኳን ብናይ የአሜሪካ የተለያዩ ህግ አስፈጻሚዎች አንድ አይነት የሽብር  ትርጉም  ላይ  መድረስ  አቅቷቸዋል።  ምክንያቱም በአንዱ ወገን ሽብርተኛ የተባለው  በሌላው ወገን የነፃነት ታጋይ  ስለሆነ። ስለ ኢትዮጵያ የሽብር ህግ ከመዳሰሳችን  በፊት የሽብርተኝነትን ዓለማቀፋዊ ትርጉሞች በጥቂቱ እንይ። ሽብርተኝነት በዓለም  አቀፍ ደረጃ  አያሌ ትርጉም ተሰጥቶታል፤  የተወሰኑትን እንይ፡-
     -  ሽብርተኝነት ፀረ-መንግስት ሆኖ የተወሰኑ ሰዎችን ወይም ቡድንን ወይም  አጠቃላይ  የህብረተሰቡ  አህምሮ  ላይ  ሽብር ለመፍጠር  በማስላት  ወይም በማሰብ የሚፈፀም ማንኛውም የወንጀል  ድርጊት ነው።
ሌጉ ኦፍ ኔሽን, እ.አ.አ 1937.
     - ለማህበራዊና ፖለቲካዊ ጥቅም  ለማትረፍ፤ መንግስትንና  ህዝብን  ወይም የተወሰነ  ክፍልን  ለማስፈራራት፤ በሰዎችና  ንብረት  ላይ የሚወሰድ ህገወጥ የኃይል  እርምጃ  ሽብርተኝነት  ይባላል።
የፌዴራል ቢሮ ኦፍ ኢንቨስትጌሽን (FBI) (የአሜሪካ የፌዴራል የምርመራ ቢሮ)
     - ሽብርተኝነት ምንም ዓይነት መነሾ ይኑረው ለግለሰቦች ወይም ለተደራጁ  ወንጀሎች አጀንዳ ተግባራዊነት ህብረተሰቡ ላይ ጉዳት በማድረስ፤ ህይወታቸውን፣ ነፃነታቸውን፣ ወይም ደህንነታቸውን አደጋ ላይ መጣል፤ ፍርሃት  ለማስፈንና ሲሸበሩ ለማየት መፈለግ፤ ወይም አካባቢን በማወክ ወይም የግለሰብ ሆነ የህዝብን መሰረተ ልማት ወይም ንብረት መያዝ ወይም መቆጣጠር መፈለግ፤ ወይም ብሔራዊ  የማህድን   ሀብትን  አደጋ ላይ ለመጣል  በመፈለግ የሚደረግ ማንኛውም አይነት የማስፈራራት  ወይም  የኃይል  ተግባር  ነው።      
የዓረብ አገራት የሀገር ውስጥና የፍትህ ሚኒስትሮች ምክር ቤት፤ 1998  እ.ኤ.አ.
     -   በአጠቃላይ ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊ  ወይም  ርዕተዮዓለማዊ  ግብን  ለማሳካት  በመንግስት  ወይም   በህብረተሰቡ ላይ  ፍርዓት  ለማስረጽ ወይም  ለማሰፈራራት   በስሌት  የሚወሰድ   ህገወጥ የኃይል   እርምጃ   ወይም   ህግ ወጥ የኃይል   ተግባር   ለመፈጸም   ማስፈራራት ሽብርተኝነት ይባላል።


ዩ ኤስ  ዲፓርትመንት   ኦፍ ዲፌንስ
-  ሽብርተኝነት ተፈጽሟል የሚባለው የፖለቲካ ዓላማን ለማሳካት በሚወሰደው የኃይል  ተግባር  ንጹሃን ኢላማ  ሲሆኑ ነው።
ዎልተር ላኩኤር  ፕሮፌሰር /የታሪክ  ተመራማሪ/የፖለቲካ  ተንታኝ     ብዙዎች ብዙ ጊዜ እንደ ዘመናዊና  ዲሞክራሲያዊ ህግ  ምንጭነት የሚጠቅሷት አሜሪካ  በህጓ ላይ ስለ ሽብርተኝነትና  ከሽብርተኝነት ጋር በበተያያዥነት የሚነሱ ድርጊቶችን   የህግ  መለያ ቁጥር  22 ምዕራፍ 38 አንቀጥጽ 2656 ኤፍ(ዲ) /U.S. Code Title 22, Ch.38, Para. 2656f (d)/ ላይ ትርጉም በሚል የተገለጸውን   ዝርዝር ትረጉሞች ብናይ ከሀገራችን የሽብር ህግ ጋር ለማነጻጸር ስለሚጠቅመን የሚመለከተውን እንመልከት።
    የአሜሪካ  አጠቃላይ ህዝብ የሚተዳደርበት የህግ መጽሐፍ ሽብርተኝነትን  የሚደነግገው አገሮች  በየዓመቱ  ሽብርኝነት   አስመልክተው  ሪፖርት የሚያደርጉትን  መነሻ   በማድረግ የዩናይት ስቴት   ኮንግረስ ሴክረተሪ  በየዓመቱ  እንደ  መስፈርት  በመውሰድ የሚያቀርበውን የሽብርተኝነትን   ትርጉም  መሰረት  በማድረግ  ነው።
የአሜሪካ ህግ ሽብርተኝነትን   በአንቀጽ 2656f (d)/ ሲተረጉመው፡-
1/ “ዓለም ዓቀፍ ሽብርተኝነት” ማለት ቃሉ እንደሚያመለክተው ዜግነታቸው ወይም አገራቸው ከአንድ በላይ የሆኑ ሰዎች የተሳተፉበት የሽብር ተግባር ነው።
2/ “ሽብርተኝነት” የሚለው ቃል የሚያመለክተው፤ ፖለቲካዊ መነሻ ያለው ቀድሞ የታስበበትና መሳሪያ ያልያዙ ሰዎች ላይ በተወሰኑ ብሔርተኛ ቡድን አሊያም ሚስጥራዊ ወኪሎች አማካኝነት የሚወሰድ ህገወጥ የኃይል ተግባር ነው።
3/ “የሽብር  ቡድን” ማለት  ማኛውም ቡድን  ወይም  ማንኛውም  ትርጉም  ያለው ንኡስ  ቡድን ያለው  ሆኖ  ዓለማቀፋዊ  የሽብር  ተግባር  የሚሠራ  ማለት  ነው።
4/  “ግዛት”  ወይም  “የሀገር ግዛት”  ማለት   የሀገሪቷ  የመሬት አካል፣  የውሃ  አካልና  የሰማይ  ክልል  ነው።
5/ ”መጠለያ“  ወይም  “የሽብርተኞች መጠለያ”  ማለት   በአንድ  አገር  ግዛት ያለ  ቦታ
ሀ. ሽብረተኞች ወይም  የሸብርተኛ  ድርጅት
1.  የሽብር ተግባር የሚያከናውኑበት ማለትም ሥልጠና፣ የገንዘብ  ማሰባሰብ ሥራ የሚሰሩበት፣ ገንዘብ የማስተዳደር ሥራና  አባሎች  ምልመላ የሚያካሂዱበት፣ ወይም
2.  የማስተላለፍ ሥራ የሚሰሩበት ቦታ
ለ.  በግልፅ ፍቃዱን የሰጠ፣  ሁኔታውን የሚያውቅ፣ ዝም ብሎ የተወ፣ ያባበለ፣  ግዛቱን  ሲጠቀሙ  ችላ ያለ  መንግስት እንዲሁም  ከዚህ በታች  በተገለጹት  ቁጥሮች  መሰረት  ኃላፊነቱን ያልተወጣ፡-
1.  በክፍል 240(j)(1)(a)
2.   በዚህ ርዕስ በክፍል 2371(a)
3.  በዚህ ክፍል 2780(d)
  በማለት  በህጉ ላይ  አስፍሯል። የኛ ሀገር የጸረ ሽብር ህግስ ምን ይላል። 


የኢትዮጵያ የጸረ ሽብርተኝነት ህግ


     ከሽብር ጋር የተያያዘው ስለ ሽብር የሚያወራው የኢትዮጵያ ህግ  የኢትዮጵያ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 ዓ.ም   በመባል ይታወቃል።  በዚህ  አዋጅ ላይ በርካታ ሰዎች የዜጎችን ነጻነት የሚጋፋና ከሌሎች  አገሮች የሽብር  ህግ በተለየ መልኩ የተቀረጸ  እንዲሁም ከሽብርተኘነት ፅንሰ  ሀሳብ ወይም  ማቋቋሚያ  ወጣ  ያለ ነው በማለት ቅሬታ ያሰማሉ።  እስቲ ሽብርተኝነት  ምን  ትርጉም ዓለው  በኢትዮጵያ  ህግ፣  ከዓለም  አቅፍ ህግ፣ ከመደበኛው የወንጀል ህግና  ሥነሥርዓትና መሰል ህጎች  በምን ይለያል? በተለየ ለጥንቃቄ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፣ ከሽብረተኘነት ፅንሰ ሀሳብ ወጣ ያሉ ናቸው የሚባሉትንና ክርክር የተነሱባቸውን የህግ አንቀጾችን በተወሰነ  በማሳየት እንገምግም።  ከትርጓሜው  እንጀምር፡-


አንቀጽ 2- ትርጓሜ


1. “ንብረት” ማለት  ማንናውም ግዙፍነት ያለው ወይም ተንቀሳቃሽ፣ ወይም የማይንቀሳቀስ ሀብት  ሲሆን፤ የባንክ  ሂሳብን የመሰሉ የዚሁ  ንብረት ወይም ሀብት  ባለሃብትነት ወይም ጥቅምን   የሚያስረዱ   ሰነዶችንና  ደብተሮችን ያካትታል።
 2. “ ከሽብርተኝነት  ድርጊት የተገኘ ”  ንብረት   ማለት   ገንዘብን  ጨምሮ በማንም ሥም  ይዞታ  ወይም   ቁጥጥር   ሥር  ቢገኝም   ከሽብርተኝነት   ድርጊት   በመነጨ  ንብረት   አማካኝነት  የተገኝ  ወይም  የተፈራ   ማናቸውም   ንብረት  ነው።
3. “የሽብርተኛ ንብረት” ማለት ከሽብርተኝነት ድርጊት የተገኘ ንብረት፣ የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም  የዋለ፣  እየዋለ ያለ ወይም  የሚውል  ንብረት ነው።           
4. “ሽብርተኛ ድርጅት” ማለት ፡-
 ሀ. የሽብርተኝነት ድርጊትን  የመፈጸም ዓላማ ያለው ወይም  የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም ያቀደ፣ የተዘጋጀ፣ የፈጸመ፣ ያስፈጸመ ወይም  ያቀደ፣  እንዲፈጸም በማናቸውም ሁኔታ የረዳ ወይም  ያነሳሳ ከሁለት  ያላነሱ አባላትን  የያዘ ቡድን፣ ማህበር ወይም ድርጅት፣ ወይም
ለ. በዚህ  አዋጅ  መሠረት በሽብርተኝነት  የተሰየመ ነው፤
5. “እገታ ወይም ጠለፋ” ማለት ሰውን በመያዝ ወይም በቁጥጥር ስር በማድረግ የያዘውን ሰው እንደሚገድል፣ ከባድ ጉዳት እንደሚያደርስበት ወይም እንደማይለቀው መዛት ነው።
6.  “ማነሳሳት”  ማለት   ድርጊቱ ባይሞከርም  ሌላውን  ሰው በሞጎትጎት፣ ተስፋ  በመስጠት፣ በገንዘብ፣ በስጦታ፣ በማስፈራራት  ወይም በማናቸውም  ሌላ  ዘዴ የሽብርተኝነት   ድርጊት  እንዲፈጸም  ማግባባት  ነው
7.  “የህዝብ   አገልግሎት” ማለት ለህዝብ አገልግሎት ለመስጠት የተደራጁ የኤሌክትሮኒክ፣ የኢንፎርሜሽን፣ ኮሚኒኬሽን፣ የትራንስፖርት፣ የፋይናንስ፣ የህዝብ አገልጋሎት መስጫ፣ የመሰረት ልማት ወይም እነዚህን የመሰሉ ተቋማት ወይም ሥርዓቶች  ነው፤
8. “ዲጂታል  ማስረጃ” ማለት  በዲጂታል  ቅርጽ   የተቀመጠ ወይም የተላለፈ የማስረጃነት ዋጋ  ሆኖ  በማናቸውም ማስተላለፊያ ላይ በኮምፒተር፣  በኮምፒውተር  ውሰጥ   ወይም   በሌላ   በተመሳሳይ መሳሪያ የተቀረጸ ወይም  የተቀመጠ  በሰው ፣ በኮምፒውተር ወይም  በተመሳሳይ  መሳሪያ መነበብ ወይም  መረዳት የሚችል መረጃ ሲሆን  በመግለጫ፣ በህትመት ወይም  በሌላ መንገድ የሚወጣ የዚህኑ መረጃ ውጤት ይጨምራል፤
ከላይ  በተገለጸው የፀረ-ሽብሩ  ህግ የትርጉም  አንቀጽ  ላይ  አብዛኛው ከሌሎች ህጎች  ብዙም የተለየ  ነገር ስሌለለው አስተያየት መስጠት ጠቃሚ ስላልሆነ፤ የሽብር  ህግ አነጋጋሪ ከሆኑት ሀረጎች መካከል  የሆነውን  “ሽብርተኛ  ድርጅት” የሚለው አንቀጽ ለዲሞክራሲያዊ  ህግ ተምሳሌት ናት የምትባለው  አሜሪካን  አንጻር የኛን   ሥናይ የትርጉም  ልዩነት   ስለሚታይ  ልዩነቱን  ማሳየት  ተገቢ  ነው።
      የአሜሪካን  ህግ “ሽብርተኛ  ድርጅት” የሚለውን ሲተረጉም ከላይ  እንደሚታየው የተወሰነ ቡድን ወይም ስብስብ  በአለም ዓቀፍ ደረጃ  የሽብርተኝነት ተግባር የሚፈጽም  ማለት ነው።  ይህ ማለት ሽብርተኛ  ለመባል  በአሜሪካን ህግ  አንደኛው  መስፈርት ዓለማቀፍ የሽብር ተግባር(ከአንድ አገር በላይ ወይም ቢያንስ ቢያንስ የሁለት አገሮች ዜግነት ያላቸው  አባላቶች ባሉት ቡድን የሚሰራ ሽብር ተግባር ማለት  ነው)  መሥራት። ወደ እኛ ሀገር  ህግ ስንመጣ  ሽብርተኝነት ከሁለት ያላነሱ  አባላት ያለው ቡድን ወይም ማህበር፣ድርጅት ወይም በአዋጁ  መሰረት በሽብርተኝነት የተሰየመና የሽብር  ተግባር ላይ በተለያየ መልኩ የተሳተፈ ማለት  ነው። በዚህ  ህግ ላይ የአሜሪካኑ አይነት የሽብር  ተግባር ተፈጸመ ወይም ሽብርተኛ  ድርጅት  ነው  ለማለት ከአንድ  በላይ  አገር ላይ የሽብር  ተግባር  መፈጸም አይጠበቅም ማለት  ነው። በሌላ አነጋገር እኛ  አገር  አዚሁ  ሀገር ውሰጥ ሌላ  ተጨማሪ አገር ለይ የሽብር  ተግባር  መፈጸም  ሳያስፈልግ  በህጉ የሽብር ተግባር ተብሎ የተጠቀሰውን ድርጊት  ከፈጸምን ወዲያውኑ የሽብርተኛ ቡድን የሚል ስያሜ ይሰጠናል  ማለት  ነው።
     ዋነኛውና በብዙ አገሮች ከላይ  እንዳሳየሁት የተለያየ  ትርጉም እንደተሰጠው ብዙዎችን የሚያከራክረው ሽብርተኛ ወይም የሽብር  ድርጊት የሚለው  ትርጉም  ከዓለም አቀፍ የሽብርተኝነት  ትርጉም  አንፃር የኛው  ሀገር የቱጋ  እንደሆነ እንየው።  የእኛ  ሀገር  ህግ  እንደ ሌሎች ሀገራት ሽብርተኝነት  ብሎ አይደለም  ትረጉም የሚሰጠው  ይልቁንስ  የሽብር  ድርጊቶች  በማለት  እነጂ።   በኛ  ሀገር የሽብር  ድረጊቶች   ምንምን ናቸው።

 
አነቀጽ-3  የሽብርኝነት   ድርጊቶች
     ማንኛውም ሰው ወይም ቡድን የፖለቲካ፣ የሃይማኖታዊ ወይም የአይዶሎጂ ዓላማን ለማራመድ በማሰብ በመንግሰት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር፣ ህብረተሰቡን ወይም የህብረተሰቡን ክፍል ለማስፈራት ወይም  የሃገሪቱን መሰረታዊ ፖለቲካዊ፣ ህገመንግስተዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ማህበራዊ ተቋማትን ለማናጋት ወይም ለማፍረስ፡-
1/ ሰውን የገደለ ወይም በአካሉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ፤
2/ የህብረተሰቡን ወይም የህብረተሰቡን ክፍል ደህንነት ወይም ጤና ለከፍተኛ አደጋ ያጋለጠ እንደሆነ፤
3/ እገታ ወይም ጠለፋ የፈጸመ እንደሆነ፤
4/ በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ፤
5/ በተፈጥሮ ሀብት፣ በአካባቢ፣ በታሪካዊ ወይም የባህል ቅረጽ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ፤
6/ ማናቸውንም የህዝብ አገልግሎት ለከፍተኛ አደጋ ያጋለጠ፣ የያዘ በቁጥጥር ሥር ያደረገ፣ ያቋረጠ ወይም  ያበላሸ እንደሆነ፤ ወይም   
7/ በዚህ አንቀጽ 1/ እስከ 6/ ከተመለከቱት ድርጊቶች መካከል ማንኛቸውንም ለመፈፀም የዛተ እንደሆነ፤ ከ15 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ በሚደርስ ጽኑ እስራት ወይም በሞት ይቀጣል።
በእኛ ሀገር ማንኛውም ሰው ወይም ቡድን 1.የፖለቲካ 2.የሃይማኖት 3.አይዶሎጂ ዓላማን ለማራመድ በማሰብ መንግስትን ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር፣ ህብረተሰቡን ለማስፈራራት ወይም የሀገሪቱ ተቋማትን (ፖለቲካዊ፣ ህገመንግስታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ማህበራዊ ናቸው፤) ለማናጋት ወይም ለማፍረስ ከተራ ቁ.1-7  የተገለጹት ድርጊቶች የፈጸመ ሽብርተኛ ነው ወይም የሽብር ድርጊት ፈፅሟል  ይባላል። እንግዲህ  የኢትዮጵያ ፀረ-ሽብር ህግ ሽብርተኝነትን እነደዚህ  ይግለጽ እንጂ  መላው የአሜሪካ ህዝብ የሚገዛበት የህግ  መጽሀፍ  ከላይ  እነደሚታየው  ሽብርተኝነት ፖለቲካዊ መነሾ ኖሮት መሳሪያ ባልያዙ የህብረተሰቡ ክፍሎች ላይ የሃይል እርምጃ መውሰድ በሚል ገልጾታል። ይህ ከኢትዮጵያ ህግ የሚለይበት ማሰፈራራት፣ሃማኖታዊ ርዕዮተዓለማዊ የሚሉ ጉዳዮች የሽብርን ተግባር የሚያቋቁሙ መስፈርቶች አይደሉም። በተጨማሪም ፀረ መንግስት የኃይል  ተግባሮችም እንደ ሽብር ተግባር አልተወሰዱም።  
ከላይ በተገለጹት የሌሎች ሀገራት የሽብር ትርጉም ላይ ማስፈራራት  እንደ  ሽብር ተግባር የሚወሰድ መሆኑና ማስፈራራት  እንደ  ሽብር ተግባር የሚወሰደው በቃል ማሰፈራራት በመደረጉ ብቻ ሳይሆን ከኃይል እርምጃ ጋር ተያይዞ ሲመጣ መሆኑን በአብዛኛው የሚያስረዱ ሲሆን በኢትዮጵያ ህግ ማስፈራራት አልፎም ተርፎ ዛቻ  ከጀርባው ፖለቲካዊ ፣ሃይሞኖታዊና ርዕዮተዓለማዊ ዓላማ ካለው  የማስፈራራቱ  ድርጊት በተግባር የተፈተሸም  ባይሆን በቃል መናገር ብቻ ሽብርተኛ የሚል ስም ያሰጣል። በተጨማሪ ጉዳዩን ለየት  የሚያደርገው አንድ ግለሰብም  ቢሆን(ማንኛውም  ሰው፤ አንቀጽ-3 የመግቢያ አንቀጽን ይመልከቱ) የተገለጸውን ዓላማን ፖለቲካዊ፣ሃይማኖታዊ ወይም ርዕዮተዓለማዊ ፍላጎትን ለማሳካት በሚል ቢዝት ሽብርተኛ ተብሎ ከመወንጀል  አይድንም። ለምሳሌ  አቶ መ የአንድ ሃይማኖት ተከታይ ሆኖ በቡድን በመሆን ወይም በግሉ ሃይማኖቱን ምክንያት አድርጎ አንድ  ሰውን  የራሱ አይነት እምነት ያለው ሊሆን  ወይም  ላይሆን ይችላል እገልሃለው፣ አጋይሃለው ወይም አግትሃለው ብሎ የዛተ  እንደሆነ ከ15  ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይም ሞት ሊቀጣ የማይችልበት  ሁኔታ  የለም። (የፀረ ሽብር አዋጅ  ቁጥር  652/2001 ህግ  አንቀጽ 3/7)
    የኢትዮጵያ ፀረ ሽብር  ህግ  ከላይ  እንደምናየው ከአሜሪካኑ የመከላከያ  ዲፓርትመንት ትርጉም እና የዓረብ ሀገራት የአገር ውስጥና የፍትህ ሚነስትሮች ምክር ቤት ትርጉም ተቀነጫጭቦ  የተወሰደ ይመስላል።  ይሁንና አሜሪካን መላ አገሪቱ ህዝብ የሚተዳደርበት ፣የሌግ  ኦፍ  ኔሽን እ.ኤ.አ 1937 ትርጉምና ከሌሎች ሀገራት የሽብር ህግ ትርጉም  አኳያ  ሲመዘን ዛቻን እንደ ሽብርተኝነት  ተግባር  መውሰድ እንደ ጫፍ  የወጣ ህግ ያስቆጥረዋል።
    የፀረ-ሽብር  ህጉን እንደሚቃወሙ ሰዎች ወይም  ቡድኖች  አገላለጽ ይህ ህግ  ጫፍ የወጣና በመደበኛው የወንጀል  ህግ ሊገዛ የሚችለውን  ሁሉ በሽብር ተግባር  ፈርጆታል  በማለት  ከሚጠቅሱት  የወን ጀል  ህግ  መከካል ይህው መዛት ወይም  ዛቻ አንዱ ነው። የ1997 የወንጀል ህግ  ህግ  ዛቻን  እንዴት ይገልጸዋል እስቲ  እነደወረደ   እንየው፡-


አንቀጽ 580 ዛቻ
    ማንም ሰው በሌላ ሰው ላይ ድንጋጤ ወይም ፍርሃትን በሚቀሰቅስ ሁኔታ ከባድ ወይም ጉዳት የሚያደርስበት መሆኑን በመግለጽ ያስፈራራው እንደሆነ፤ የግል አቤቱታ ሲቀርብበት ከ500 ብር በማይበልጥ መቀጮ ወይም ከስድስት ወር በማይበልጥ ቀላል  እስራት  ይቀጣል።
የ1997ቱ የወንጀል ህግ እንደሚታየው አንድ ሰው ከዛተ ያውም የተዛተበት ሰው ብቻ ካመለከተ (ዓቃቢ ህግ ወይም ሌላ ሰው ተክቶ ሊገባ አይችልም)የ500 ብር መቀጫ ወይም ከስድስት ወር የማይበልጥ እስራት  ነው የሚያስከትለው።
ሌላው በፀረ  ሽብር ህጉ ከላይ በገለጽናቸው የተለያዩ ተቋማትና  እንዲሁም  አገሮች  ላይ እምብዛም ባልተገለጸ  መልኩ ወይም  ባልተለመደ  ሁኔታ  የሆነ ችግር ተፈጠረ በማለት የሀሰት  ወሬ  ማውራት  እስከ 10 ዓመት  የሚያስቀጣ ተግባር  ነው።  አንቀጹን  እንየው።


አንቀጽ-11
ሀሰት የሽብርተኝነት ድርጊት ስለማስፈራራት
     ማንኛውም ሰው ሀሰተኛ መሆኑን እያወቀ ወይም እያመነ የሽብረተኝነት ድርጊት እንደተፈጸመ ወይም እየተፈጸመ እንደሆነ ወይም እንደሚፈጸም በማንኛቸውም መንገድ ለሌላ ሰው ሆን ብሎ የገለፀ እንደሆነ ከ3ወር እስከ 10 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ይቀጣል።                
     በሀሰት የሽብርተኝነት ድርጊት ስለማስፈራራት በሚል ደረጃውን ከፍ ለማድረግ ተሞከረ እንጂ በቀላል ቋንቋ ስንገልጸው የሀሰት ወሬ ማውራት እንደ ማለት ነው። ይህው ህግ በዚህው መንፈስ በ1997 የወ/ህግ አንቀጽ 485 ላይ በወሬ ህዝብን  ማሸበር  በሚል   ተደንግጎ  ይገኛል። 


አንቀጽ 485 በወሬ  ህዝብን  ማሸበር
1.  ማንም ሰው ፡-
ሀ/ ለህዝብ  ደህንነት  ወይም  ለግለሰቦች  ህይወት፣ጤና ወይም ንብረት  አስጊ የሆነ አደጋ  በተለይም የወረራ፣ የሰው ግድያ፣ የእሳት ቃጠሎ ፣የጥፋት  ወይም   የዘረፋ  አደጋ እንደሚደርስ በማስፈራራት፤  ወይም
ለ/ ስለነዚሁ ሁኔታዎች  ወይም በአጠቃላይ ስለሚደርስ  ሁከት  ወይም በቅርብ ስለሚደርስ ጥፋት  ወይም   የተፈጥሮ አደጋ  የሀሰት  ወሬ በመንዛት፤  አስቦ ህዝብን  ያሸበረ  እንደሆነ፤
ከ 3 ዓመት  በማይበልጥ  ቀላል  እስራት  ወይም  በመቀጮ  ይቀጣል።
2. ከፍተኛ  ቅጣቶችን  የሚወስኑ አግባብ ያላቸው  ድንጋጌዎች   እንደተጠበቁ ሆነው ሁኔታዎቹ በጣም  ከባድ የሆነ  ብጥብጥን ወይም ምስቅልቅል ሊያመጡ  የሚችሉ ወይም ያመጡ  እንደሆነ  ፤ቅጣቱ ከሦስት ዓመት የማይበልጥ  ጽኑ እስራት ይሆናል።                                         


አንቀጽ-486  የሀሰት ወሬዎችን  በማውራት ህዝብን  ማነሳሳት
     ማንም ሰው  በአገር  ደህንነት  ላይ ከሚፈጸሙት  ወንጀሎች ውጭ   በሆነ አካኃን አንቀጽ  240፣  257/ሠ/፣    እና  261/1 ፡-
 ሀ/  በመንግስት፣ በሕዝብ ባለሥልጣኖች ወይም በሥራቸው ላይ የሐሰት ወሬዎችን፣ ጥርጣሬዎችን ፣  ጥርጣሬዎችን፣ ወይም የሐሰት ሐሜታዎች የሚፈጠር ወይም የሚነዛ ሰው፤ ከዚህም የተነሳ የህዝብን አስተሳሰብ  ያናወጠ፣ የቀሰቀሰ ፣ ወይም  ለማናወጥ  የሚችል  እንደሆነ ፤ወይም
 ለ/ በማናቸውም ዓይነት ማሳጣት ወይም ሌላ ዘዴ ጥርጣሬን  ያስፋፋ፣ ጥላቻን  ያነሳሳ  ወይም የኃይል  ድርጊት  ወይም  የፖለቲካ ፣የዘር ወይም የኃይማኖት  ሁከት  የቀሰቀሰ እንደሆነ፤ በቀላል  እሥራት ወይም በመቀጮ፣ ወይም ወንጀሉ ከባድ በሆነ ጊዜ  ከሦስት  ዓመት  በማይበልጥ ፅኑ እስራት ይቀጣል።     
 የፀረ ሽብር ህጉ እነቀጽ -11  እና የ1997 የወንጀል  ህግ አንቀጽ-485  እና 486  እምብዛም  የትርጉም  ለውጥ አይታይባቸውም እንዲሁም የ1997ቱ በማውራት ማሸበርን በዝርዝር በተገቢው ሁኔታ ገልጾታል። ቅጣት  ለማክበድና ከፀረ ሽብር  ህጉ  ጋር በአንድ ጠቅልሎ ለማውጣት ካልተፈለገ  በስተቀር እዚህ  ጋር የ1997 የወ/ህግ በወሬ  ለማሸብር  የወንጀል  ድርጊት  በቂ አንቀጽ  ነው።  
     ከህትመት ሚዲያው ጋር የተያያዙና ሌሎች አነጋጋሪ የሽብር ህጉ አንቀጾችን በሚቀጥለው ጊዜ  እንገመግማቸዋለን።  ይቀጥላል…..

ይምረጡ
(11 ሰዎች መርጠዋል)
3230 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1031 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us