ፖሊሲ የቴክኖሎጂ ፈጠራና ባለሙያዎቹ

Wednesday, 22 June 2016 12:17

 

ወሰንሰገድ መሸሻ በላቸው/ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. /

ከ1950እ.ኤ.አ.ጀምሮ ብሔራዊ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፖሊሲና ይህንኑ ፖሊሲ ሊያስፈፅሙ የሚችሉ መንግስታዊ አካላት በብዙ አገሮች ተፈጥረዋል።

በተለይም የተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት /UNESCO/ Çየሳይንስና ቴክኖሎጂ ፖሊሲÈ በሚል ርእስ በሰኔ 1970 ፓሪስ ውስጥ አዘጋጅቶት ከነበረው የአውሮፓና የሰሜን አሜሪካ አገሮች የሚንስትሮች ስብሰባ ወዲህ ብዙ አገሮች የራሳቸውን ብሔራዊ የሳይንስና ቴክኖሎጂ አቅም ለመገንባትና እድገታቸውን ለማፋጠን ፖሊሲ አውጥተዋል።

አዳዲስ እውቀቶችን የሚያመነጩ የኅብረተሰቡን ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ ቅድሚያ ትኩረት የሚያስፈልጋቸውን የሳይንስና ቴክኖሎጂ መርሃ ግብሮችና ፖሊሲው ከሚነድፋቸው ውስጥ የሳይንስና ቴክኖሎጂ አገልግሎቶች፣ የምርት መዋቅር ማሻሻል፣ ወሳኝ ወደሆኑት ክፍላተ ኢኮኖሚ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ከኅብረተሰቡ ተጨባጭ የተፈጥሮና ማኅበራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ለአገሪቱ ፍላጎት ማቅረብንና የመሳሰሉትን ባጠቃለለ መልኩ ነበር።

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፖሊሲ ሲወጣ 2 መሰረታዊ ችግሮች እንደሚያጋጥሙ ታሳቢ ሆኗል።

1ኛ. የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምር ውጤት ረዘም ያለ ጊዜ እሚወስድ መሆኑ ፖሊሲው ካለው ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ወደፊት የሚከናወኑትን ተግባራት በማካተት ሊገኝ የታሰበውን የሚያመለክት የኢኮኖሚና የሶሻል መዋቅር ሞዴል መያዝ።

2ኛ. ሁሉንም የሳይንስና ቴክኖሎጂ እንቅስቃሴዎች ለማቀድ ለምርምርና ሥርፀት የሚሆን ሠፊ መዋቅር፣ በጀት እንዲሁም የተጠናከረ ብሔራዊ የሳይንስ ኅብረተሰብ እንደሚያስፈልግ፣ በተጨማሪም ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለተሻለ ኑሮ ወሳኝ ቢሆንም አመች የሆነ የሶሻልና የኢኮኖሚ ሁኔታና እንዲሁም አስፈላጊ የሆነ የፖለቲካ ድጋፍ ከሌለ በስተቀር ፖለሲው ግቡን እንደማይመታ ማሰብ።

በደርግ ጊዜ ተረቅቆ ለመፅደቅ ቀርቦ የነበረው የፖሊሲ ረቂቅ ሰነድ ትኩረት ያደረገው ለተለያዩ ክፍላተ ኢኮኖሚ ግንባታ ተስማሚ ቴክኖሎጂን በማፍለቅ፣ ከውጭ መርጦ በማስገባት አገር በቀሉን ባሕላዊ ቴክኖሎጂ በአጭር ጊዜና በተመጣጣኝ ወጭ በማዳበር፣ በሰው ኃይል ሥልጠና፣ አቅርቦትና አጠቃቀም ረገድ የሀገሪቱን አንገብጋቢ ችግሮች ለመፍታት የሚያስችለውን አቅም ከመገንባቱ ላይ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በልዩ ልዩ ደረጃ የሚወጡትን የሀገሪቱን የልማት እቅዶች የሚደግፍ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፖሊሲ ለመንደፍና መመሪያዎችን ለማውጣት፣ የምርምር ቅድመ ተከተሎችን በመወሰን ምርምሮች በሀገሪቱ አንገብጋቢና መሠረታዊ ችግሮች ላይ ማተኮራቸውን ለማረጋገጥና በምርምርና ሥርፀት ተግባር ላይ ለተሰማሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ለመስጠትና ለማስተባበር እንዲቻል ማድረግን ይዞ የነበረ ሲሆን ለችግሮቹመንስኤ ከሆኑት ምክንያቶች አንዱ የሳይንስና ቴክኖሎጂ አቅም አናሳ በመሆኑ ይህንን አቅም ለማዳበር የሳይንስና ቴክኖሎጂ አቅጣጫን ለመቀየስ የሚረዳ ብሔራዊ ፖሊሲ ባይወጣም/ለማውጣት ትልቅ ጥረት ተደርጎ ነበር።

ሆኖም በኢህአዴግ ያልወጣውን የደርግ ፖሊሲን ተመርኩዞ በየካቲት 2004 የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሳይንስ፣ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ወጥቶ ቴክኖሎጂን ለማበረታታት መሰራቱ ይታወቃል።

በ26 ገፆች የተዘጋጀው ይህ ፖሊሲ ከራእዩ ከ2012-2015 በተያዘው እቅድ በ2015 ሀገራችን ውጤታማ የሆኑ የውጭ ቴክኖሎጂዎችን በፍጥነት የመማር፣ የማላመድ እና የመጠቀም አቅሟ ተገንብቶ ማየት መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ ገልፆታል።

በስትራተጂዎቹ ላይ ደግሞ ውጤታማ የሆኑ የውጭ ሀገራት ቴክኖሎጂዎችን በማስገባት ማምረቻ እና በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የማላመድና የመጠቀም አቅም እንዲፈጠር ማድረግ።

የውጭ ቴክኖሎጂዎችን ለማፈላለግ፣ ለመምረጥ፣ ለማስገባት፣ ለማላመድ፣ ለመጠቀምና፣ ለማስወገድ የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት የሚል ነው። የተሰመረባቸውን ያነፃፅሩ።

ሳይንስና ቴክኖሎጂን ለኢኮኖሚና ለማኅበራዊ ልማት ለማዋል፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂን ውጤት በአግባቡ ለመገንባትና ለመጠቀም እንዲሁም ምርታማነትን ከፍ ለማድረግ ብሔራዊ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፖሊሲ መኖር ወሳኝ መሆኑ መዘንጋት  የለበትም።

ብሔራዊ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፖሊሲ ማለት የአንድን ሐገር የምርት ኃይሎች በጥራትና በብዛት ለማሻሻል እንዲሁም የአገሪቱን የሶሻልና የኢኮኖሚ ደረጃን ለማሳደግ ወሳኝ የሆነውን የኅብረተሰቡን የሳይንስና ቴክኖሎጂ አቅም ለመገንባት፣ ለማደራጀት፣ አቅጣጫ ለማስያዝና በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስፈልጉ ሕጋዊና ተፈፃሚ የሆኑ ደንቦች፣ መመሪያዎች እና ዘዴዎችን በማዘጋጀት ሥራ ላይ ማዋል ነው።

ፈጠራ በእንግሊዝኛው INVENTION የሚል አቻ ስያሜ ይዞ በአማርኛ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው። የተፈጥሮ ሕግ በጥቅም ላይ እንዲውል የሚደረግበት የላቀና የመጠቀ ቴክኒካዊ ሃሳብ ነው።የዓለም አእምሮአዊ ድርጅት/WIPO/ ፈጠራን በቴክኖሎጂ መስክ ላለ አንድ የተወሰነ ችግር መፍትሄ የሚሰጥ የአንድ የፈጠራ ሠራተኛ ሃሳብ ነው ብሎ ይገልፀዋል።የዓለም አእምሮአዊ ንብረት ድርጅት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሥር ከሚገኙት 16 ድርጅቶች /SPECIALIZED AGENCIES/  መካከል አንዱ ነው።

አንድ ሐገር በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በባሕላዊ ዘርፎች የሚያደርገው ሁለገብ እንቅስቃሴ /ግስጋሴ/ በፈጠራ ሥራ መታገዝ ስላለበት፣ የበለፀጉት አገራት ከዛሬ መቶና ሁለት መቶ ዓመታት በፊት በስፋት ተጀምሮ በጥልቀት የቀጠለው የፈጠራ ሥራ መሆኑን ታሪክ የሚመሰክረውና እየታየ ያለ ሐቅ ሲሆን ታዳጊ ሐገሮችም ካሉበት የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ኋላ ቀርነት ለመውጣትና ከበለፀጉት ጥገኝነት ለመላቀቅ፣ የሕዝቦቻቸውን የኑሮ ደረጃ ከፍ ለማድረግ የፈጠራ እንቅስቃሴ በብሄራዊ ደረጃ መበረታታትና እንደ ዋና አቅጣጫ ሆኖ መታየት አለበት።

ቴክኖሎጂ የተለያዩ ጉዳዮችን እንዲያካትት ተደርጎ የተለያዩ ብያኔዎች ሲሰጠው ቆይቷል። ግብአቶችን/input/ ወደ ውጤቶች /output/ ለመለወጥ ስለሚያገለግሉ አካላዊ ሂደቶች ስብስብ፣ ስለግብአቶችና ውጤቶች ልዩ ይዘትና ባሕሪይ ምጥንነትንና እነዚህን ለማሸጋገርና ለመለወጥ የግድ እናሟላ ስለሚሉ ተያያዥና ድርጅታዊ ድርድሮሽ የሚገልፅ የእውቀት አካልናየማምረት ቴክኖሎጂ እውቀት አድርጎ ስለሚወሰድ ለብዙዎቻችን ሞዴልና ከፍተኛ አርአያችን የሆኑት ካፒቴን መኮንን ካብትሕ ይመር ብሩ፡-ሪሰርቸርስ፣ ኢንቬንተርስ ኤንድ ኢኖቬሽን አሶስየሽን- ኢትዮጵያን ለ5 ዓመታት በፕሬዚደንትነት ሲመሩ በነበሩበት ወቅት የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ የአሶስየሽኑ ኤዲቶሪያል ቴክኒክ ኮሚቴ ኃላፊ ሆኖ አብሯቸው የሰራና ካፒቴን የአመራር ዘመናቸውን በስኬት አጠናቀው ሲለቁ በተተካው ስራ አስፈፃሚ/ቦርድ/ ውስጥ በዋና ፀሃፊነት አሶስየሽኑን እየመራ በመሆኑም ለረጅም ጊዜ አብሮዋቸው በመስራቱየካፒቴን ጉዳዮች በሌሎች ብዙ ጋዜጦችም ሆነ መፅሔቶች በሚዲያም ስለሳቸው ብዙ የተባለ ቢሆንም በሌሎች ያልተገለፀ አዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራ በማቅረባቸውና በሐገራችን በኤልኒኖ ሳቢያ በተከሰተው ድርቅ ለወገን ለመድረስ በሚያስችል አደረጃጀት ታሪካዊ የሆነ ሥራ እየሰሩ በመሆናቸው በዛሬው ፅሁፌ ስለሳቸው በአጭሩ ላቀርብና ፖሊሲውን ለመቃጨት ወደድኩ።

ካፒቴን መኮንን በድርቁ ሊጎዱ የሚችሉትንእንስሳት ለመታደግ እስካሁን በሐገራችን ጥቅም ላይ ያልዋሉትን የስኳር ተረፈ ምርቶች ማለትም ባጋስ፣ ሞላሰስና የአገዳ ጫፍ ሊያደባልቁ የሚችሉ 6 የቁም ከብት መኖ ማደባለቂያ መሳሪያዎችና 1 የመኖ መከረታተፊያ መሳሪያ በመስራትበፌደራል አእምሮአዊ ንብረት ጽ/ቤት ያስመዘገቧቸውን ሁለት አይነት መሳሪያዎች በቅርቡ ጥቅም ላይ አውለዋል።

በተለይም ባጋስ ለስኳር ፋብሪካ በፈርነስነት የኃይል ምንጭነትና ለማገዶነት ይውል የነበረውን ከረጅም አመታት በፊት ጀምሮ ባደረጉት ጥናትና በደረሱበት ውጤት መሰረት ከደቡብ አፍሪካ ያለውን ተሞክሮና ያደረጉትን እንቅስቃሴ መነሻ በማድረግ በአሁኑ ሰዓት ለድርቁ ለእንስሳት መኖ ለማምረትና የተጎዱ እንስሳትን ለመታደግ ሥራ ላይ ለማዋል ድርጅት መስርተው በተግባር እየተንቀሳቀሱ ነው።ካፒቴን እስካሁን የሰሯቸው የቴክኖሎጂ የፈጠራ ውጤቶችና በምርምር ያመነጯቸው ሁሉ መሰረት ያደረጉት በአካባቢ ጥበቃ ላይ ከፍተኛ ትኩረት የሰጡ በመሆናቸው ከሌሎቹ ልዩ ያደርጋቸዋል። ሁለገብ መሆናቸውም ለዛሬው ፅሁፍ ዋቢ አድርገናቸዋል።

በየጊዜው እየተለዋወጠ ያለውን የኢትዮጵያን የአየር ንብረት ወቅታዊ ግንዛቤን የሚያሳይ የመልቲፕል ጀነራል ሰርኩሌሽን ሞዴሎች ውጤቶችን አጠቃለው የሚያቀርቡት በቅርቡ ካካሄዱት ጥናቶች መረዳት እንደሚቻለው ባለፈው መቶ ዓመት እንደአብላጫው የአፍሪካ ክፍል የኢትዮጵያ ሙቀትም እየጨመረ መምጣቱን፣ በቀጣዩ መቶ ዓመትም ሰው ሰራሽ የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮች ሙቀቱን ታይቶ በማይታወቅ መጠን እንዲጨምር እንደሚያደርጉት፣የአየር ንብረት ለውጥ ሞዴሎች የኢትዮጵያ ሙቀት በሁሉም ወቅቶች እ.ኤ.አ. በ2020ዎቹ  በ1 ነጥብ 40°ሴ. እና በ2 ነጥብ 9°ሴ. መካከል እንደሚጨምር አመልክተዋል። ይህ ሙቀት የሚያስጨንቁ የወበቅ ወቅቶችና ከፍተኛ የውሃ ትነት የበዙበት ይሆናልም ብለዋል።

አማካይ ዓመታዊ የዝናብ መጠኑ የመጨመር አዝማሚያ የሚኖረው ሲሆን በተለይም በጥቅምት፣ በኅዳርና በታኅሳስ ወራት እርጥበት እንደሚጨምር አብዝሃኞቹ ሞዴሎች ያሳያሉ።የማያቋርጥ ከባድ ዝናብ የሚጥልባቸው የዝናብ ወቅቶች አንደሚኖሩና ከፍተኛ ጎርፍን እንደሚያስከትል ጠቅሶ የድርቅና የጎርፍ ወቅቶችን አስከፊነት፣ ድግግሞሽና መጠን ለመተንበይ አስቸጋሪ መሆኑንም የጠቀሱት ሞዴሎች በምክንያትነት ያቀረቡት፣ እነዚህ ሁነቶች በኤልኒኖ ደቡባዊ መለዋወጥ እና በሕንድ ውቅያኖስ የባሕር ወለል የሙቀት መጠን የሚወሰኑ ስለሆኑ በሚያስተማምን ድፍረት ምንም ዓይነት ሞዴል ለማውጣት አስቸጋሪ ሆኖብናልበማለታቸው የማይታወቀውንናሳናስበው የሚመጣብንን መዓት ጠንቅቀው የተረዱት ካፒቴን መኮንን ግን ለእንስሳቱ መኖ ለማቅረብ 2 ዓይነት መሳሪያዎች ሰሩ። ዝናብን የማይፈልጉ ተረፈ ምርቶችን በማቀናበር ለድርቁ በአጋርነት ተሰለፉ።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ደህንነት አሁንም ለአየር ንብረት ተለዋዋጭነትና ከመጠን ላለፉ የአየር ባሕሪይ ክስተቶች የተጋለጡ ናቸው። በዝናብ ላይ የተመሰረተውና በዝናብ መጠን መዋዠቅ ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ ለጉዳት የሚጋለጠው ግብርና ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት 46 በመቶ ያህሉን በመያዝ እና 80 በመቶውን የሥራ እድልን በመፍጠር የአገሪቱ ኢኮኖሚ መሰረት መሆኑ ይታወቃል። ከአገሪቱ ሕዝብ 10 በመቶ የሚሆነው መደበኛ ዝናብ በሚጥልበት ዓመትም ችግር የተጠናወተው ሲሆን ቤተሰቦቹ በከፊል በምግብ እርዳታ ላይ የሚደገፉ ናቸው።በተለይ እንስሶቹ ለከፍተኛ አደጋና ለረሃብ ችግር የተጋለጡ ናቸው።

ድርቅ የግብርና ምርትን በከፍተኛ ደረጃ በማጓደል ተያያዥ የሆኑ የምርትእንቅስቃሴዎችንና ሥራ የማግኘት እድልን እየቀነሰ በገንዘብ ነክ ኢኮኖሚው ላይ ተደራራቢ ጉዳቶችን ያስከትላል። እንዲሁም ጎርፍ ብዙ ጊዜ በሰብልና በመሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት የሚያስከትል ሲሆን ስቃይንና ችግርን ያስከትላል። ለምሳሌ በአፋርና በአማራ ክልሎች በ2002 ዓ.ም. በብዙ ሽህ ሄክታር የሚገመት የሰብል እርሻ በጎርፍ ተጥለቅልቆ በአሰርት ሽዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ተፈናቅለው እንደነበር ሰነዶች ገልፀዋል።/ተፈናቃዮቹ ማገዶ እንጨት የተጠቀሙ ከሆነ የሚመነጠረውን ደን እናስብ።/ አሁንም በተመሳሳይ መልኩ ብዙ አካባቢዎች በጎርፍ እየተጥለቀለቁና የከፋ ጉዳት እየደረሰባቸው ነው። አሳዛኝነቱ የሚገዝፈው በድርቅ ተመትተው ለወራቶች ያህል የተጎዱት አካባቢዎች ወዲያውኑ በጎርፍ መጥለቅለቅ በድጋሚ የመጠቃታቸው ጉዳይ ነው። ይህ ዓይነት አገራዊ ችግር ደግሞ ዜጎችም እንዲረባረቡበት ግድ ይላል።

ኢትዮጵያ አሁን በመሬት ላይ ባለው ጫናና በመሬት መጎሳቆል ምክንያት ለፈጣን የአየር መከላት የተጋለጠች ናት።መንግስት በእያንዳንዱ ማሳና ጠፍ መሬት ላይ ጥበቃ ማቆም አይችልም። መጠበቅና መንከባከብ ያለበት ሁሉም ዜጋ ነው።ከተጎሳቆለው መሬት 79 በመቶ ያህሉ ከ16 በመቶ በላይ ተዳፋትነት ያለው ሲሆን 25 በመቶ ደግሞ ከ30 በመቶ በላይ ተዳፋትነት ያለው ነው። በዝናብ ወቅቶችና መጠን መዋዠቅ፣ በዝናብ ጊዜና ስርጭት ላይ በሚፈጠረው ለውጥ፣ በከፍተኛ ትነት፣ በድርቅና በጎርፍ በሚመጡ ጉዳቶች ምክንያት በምርት መጠን፣ በሰብል እርሻና በሰብል አመራረት ሥርአት እንዲሁም በተባይና በበሽታ ክስተት ድግግሞሽና ስርጭት ላይ ለውጥ ይኖራል።

የሙቀት መጨመር በዓመታዊ የእንስሳት ሀብት እድገት፣ በወተትና በበግ ፀጉር ምርትና በእንስሳት መራባት ላይ በሚያደርሰው ጉዳት ምክንያት በእንስሳት ውጤቶች ምርት ላይ ቀጥተኛ ተፅእኖ የሚደርስ ሲሆን በግጦሽ፣ በመኖ፣ በሳር መጠንና ጥራት እንዲሁም በበሽታና በተባይ መጨመር ምክንያት በተዘዋዋሪ መንገድ ጉዳት ስለሚደርስባቸው፣ አርብቶ አደር ማኅበረሰቦች በአየር ንብረት ለውጥ በተለይ ጉዳት ይደርስባቸዋል።

ከውሃ ሀይል የሚመነጭ የኤሌክትሪክ ኃይልም ቢሆን ለዝናብ መጠን፣ ለሙቀትና ለትነት መዋዠቅ የተጋለጠ ነው። ባለፉት የድርቅ ዓመታት የሀይል ምርት መቀነስ በኢኮኖሚው ላይ ከፍ ያለ ጉዳት አድርሷል። በ1995 ዓ.ም በድርቅ ምክንያት የኤሌክትሪክ ኃይል ሥርጭት ለአራት ወራት በሳምንት ለአንድ ቀን በወረፋ ይቋረጥ ስለነበር በአገር ውስጥ ምርት በተከታታይ እንዲቀንስ በማድረጉ በድኅነት ላይ ሌላ ተጨማሪ ጫና ሆኖ እንደነበርም አይረሳም።

በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ የ36.000 ሰዎች ሕይወት እንደጠፋ በጥናት መረጋገጡና እ.ኤ.አ.በ2030 ዓ.ም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ወደፊት የሚመጡት ከፍተኛ የጤና ችግሮች ወባ፣ ተቅማጥ፣የተመጣጠነ ምግብ ጉድለትና ከልብ ጋር የተያያዙ በሽታዎች እንደሚሆኑ ገልፀው ከኢትዮጵያ ሕዝብ 68 በመቶ በከፍተኛ ደረጃ የወባ ወረርሽኝ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች እንደሚኖር የዓለም የጤና ድርጅት የገለፀና እ.ኤ.አ በ2003 በተከሰተው ከፍተኛ ወረርሽኝ 2 ሚሊዮን ሰዎች በበሽታው እንደተያዙና 3.000 ሰዎች እንደሞቱ ጥናቱ አክሎ አብራርቷል።

የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ አደጋዎችን የሚያስከትል ቢሆንም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰጠው ምላሽ ደግሞ ለኢትዮጵያ ላቅ ያለ መልካም አጋጣሚ ይፈጥርላታል። በሰፊው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳ እንደ ኢትዮጵያያሉ ታዳጊ ሐገሮች ከማጣጣሚያና ከካርበን ፋይናንስ ተግባሮች ይጠቀማሉ። የካርበን ፋይናንስ ዓለም አቀፍ የካርበን ልቀትን ለሚቀንሱ ሥራዎች ማለትም ደኖችን ለመትከልና ንፁሕ ያልሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ለማስወገድ የሚሰጥ ክፍያ ሲሆን ለኢትዮጵያ የማይናቅ የገቢ ማግኛ ምንጭ ሊሆን ይችላል ተብሎለታል። ከካርበን ነፃ በሆነ የእድገት አቅጣጫ በመጓዝ ኢትዮጵያ በአመት 250 ሚሊዮን ቶን ካርበን ልታገል ትችላለች ተብሎ ተገምቷል። አሁን ባለው በቶን ከ10 -20የአሜሪካን ዶላር ዝቅተኛ የካርበን ዋጋ ሂሳብ እንኳን ለአገሪቱ በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር ያስገኝላታል ብለውም ያምናሉ።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የካርበን ማግለል አቅም አላት።ዜጎቿ ያለማቋረጥ ቢጨፈጭፉትም በደኖች የበለፀገችና ከፍተኛ የኃይል ታዳሽ ሀይል ምንጮች ማለትም ወራጅ ውሃ፣ ፀሐይ፣ ነፋስ እና የከርሰ ምድር ሙቀት ያላት ሐገር ናት። ከዚህ ሀብት ከፍተኛ ጠቀሜታ ለማግኘቱ አገሪቱ የረጅም ጊዜ እቅዷ ወደፊት ዝቅተኛ ካርበንን ከማመንጨት ጋር የሚስማማ መሆኑን ማረጋገጥ እንዳለባትና የካርበን ኢንቨስተሮችን የምትስብም መሆን እንዳለባት ተጠቁሟል።

ዓለም አቀፍ የካርበን ፋይናንስ በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ እያደገ የሚሄድ ሚና የሚኖረው ሲሆን ኢትዮጵያም ልትጠቀምበት ትችላለች። የወደፊቱን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል በከባቢ አየር ውስጥ ያለውን የካርበን መጠን መቀነስ ወይም በዕፅዋት፣ በዛፎችና በአፈር ተመጦ እንዲገል ማድረግን ዓላማው ያደረገው መንግስት ዋነኞቹ ጋዞች ካርበንዳይኦክሳየድ፣ ሚቴን፣ ናይትረስ ኦክሳይድ፣ ክሎሮፍሎሮካርቦንስ እና ሰልፈር ሄክሳፍሎራይድ ናቸው።

ረሐብ እንኳን ሰውን እፅዋትንም በራሳቸው ተሰደው ሌላ ቦታ እንዲበቅሉና አውሬ እንዲሆኑ እያደረገ ነው። ተክሎች የፀሐይ ብርኃንን ይፈልጋሉ። የፀሐይ ብርሃንንም በመጠቀም ካርቦሐይድሬትን መስራት የሚችሉ ናቸው። ለምነቱን ባጣ አፈር ላይ ከበቀሉ ግን እንደ ናይትሬትስ ያሉት አስፈላጊ ነገሮችን ማግኘት ስለሚቸገሩ እነዚህ የተራቡ ተክሎች አስፈላጊ የምግብ ምንጭ የሚሆኑላቸውን ነፍሳት እያነቁ በመመገብ ረሐባቸውን ስለሚያስወግዱ  እንደአውሬም ስለሚያደርጋቸው በተፈጥሮ ላይ ከፍተኛ መዛባትን ያስከትላሉ። እያንዳንዱ ፍጥረት አንዱ ላንዱ መኖር ግዱ ስለሆነ ይህ አለመሆኑ የከፋ ቀውስን ያመጣል። በምግብ ሰንሰለቱላይ መቋረጥን ይፈጥራል።

አንዳንዶቹ ነፍሳቶቹ ከገቡ በኋላ የሚዘጋ በር ስላላቸው ነፍሳቱን ለማጥመድ በራቸውን ብርግድ አድርገው በመክፈት አንዳንዶቹ ደግሞ የሚፈልጓቸውን ነፍሳት ለመሳብና ለመማረክ ካረፉበት በኋላ ሙጭጭ አድርጎ የሚይዝ ወጥመድ ስላላቸው አማልለው የገቡላቸውን ጭርግድ አድርገው ይመገቧቸዋል።እንግዲህ በዓለማችን እንድህ ዓይነት ሥጋ በል ነፍሳት ተመጋቢ ተክሎች እስከ 550 ይደርሳሉ።

የደን መሬት ወደ እርሻ ሲለወጥ የካርበን ዳይኦክሳይድ ልቀትን ያስከትላል። ከዚህ የሚወጣው ልቀት በ2002 ዓ.ም. ከነበረው የ25 ሚልዮን ሜትሪክ ቶን ልቀት በ2022 ዓ.ም ወደ 45 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ከፍ ይላል። ማገዶ እንዲሆንና ለሌላ ጥቅም እንዲያቆጠቁጥ ፋታ ሳይሰጠው በመመንጠሩም ደን ይቆረቁዛል፣ መሬቱም ይጎሳቆላል።በ2002 እና በ2022 መካከል ባሉት 20 ዓመታት ውስጥ  በእርሻነት እንዲያገለግል የ9 ሚሊዮን ሄክታር ስፋት ያለው ደን ይመነጠራል።በዚያ ወቅት ደግሞ የማገዶ እንጨት ፍላጎት 65 በመቶ ያድጋል።በዚህ ሳቢያም በየአመቱ 22 ሚሊዮን ቶን እንጨት ስለሚቆረጥበትና ደን በከፍተኛ ደረጃ ስለሚመናመን ካፒቴን መኮንን የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንጨትን በማገዶነት የማይጠቀሙ ሰዎችን በማፍራት የጋዝ ምድጃዎችን ሰርተው ጀባ ብለዋል።

በመንግስት ለግብርና ዘርፉ ከተመረጡት መካከል 3ቱን ብቻ ለይቶ ማየቱ የካፒቴን መኮንን ኤኮ - የሁሉነሽ ምድጃና የነጭ ጋዝ ምጣድ እንዲሁም አሁን የሰሯቸው የቁም ከብት መኖ ማቀናበሪያና መከረታተፊያ መሳሪያዎችን አስፈላጊነት መመዘን ያስችላል።

$11.  ማገዶ ቆጣቢ በሆኑና በአማራጭ ኃይል/በኤሌክትሪክ፣ በቡታጋዝ፣ በባዮጋዝ/ በሚሰሩ ምጣዶች መጋገርንና በምድጃዎች ምግብ ማብሰልን በማስፋፋት ማገዶን ማቃጠልንና የደን መመናመንን መቀነስ

$12.  በደኖችና ዛፍና ቁጥቋጦ ባለባቸው ቦታዎች የካርበን መገለልን ለመጨመር ደንን ማስፋፋትና የደን አያያዝን ማሻሻል የደንን ዘላቂ አያያዝ ያመጣል። ደኑም ሌሎች የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዘርፎች ከሚለቁት የበለጠ ሙቀት አማቂ ጋዝን ከከባቢ አየር ሊያገልል ይችላል።

$13.  በተጎሳቆለ የእርሻና የሳር ቦታ የሚካሄደውን ልቅ ግጦሽ መከልከል የአፈር ምርታማነትን ከማሻሻል በተጨማሪ በመሬት ውስጥና ከመሬቱ ላይ በሚፋፉ እፅዋት የሚገለለውን የካርበን መጠን ያሳድገዋል።

በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 44 ላይ ሁሉም ሰው በጤናማ አካባቢ የመኖርና በአካባቢ ሐብቶች የመጠቀም መሰረታዊ መብት አላቸው ብሎ በማያሻማ ሁኔታ ገልፆታል። የጎደለው ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍሉን መደላድል መፍጠር የሚችሉ ስውር የሆኑ እጀ ረጃጅሞች እጅ እንደረዘመ መቆየቱና ማጠር የሚችልበት ሁኔታ አለመመቻቸቱ ብቻ ነው።

የኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚ በየዓመቱ የ250 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀትን በአገር ውስጥ ማመንጨትን ያስቀራል። ከተግባራቱ ከ80 በመቶ የሚበልጡት የአንድ ቶን ልቀትን ለማስቀረት ከ15 የአሜሪካ ዶላር ያነሰ ወጪ ይፈልጋሉ። የአረንጓዴ ኢኮኖሚውን መንገድ መቀበል ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዓላማዎችን በማሟላት የገጠር ልማትን፣ ጤናን እና በባለ ከፍተኛ እሴት ሥራ የመቀጠር እድልን ያዳብራል።

በደን ዘርፍ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን በመተግበር 15 ነጥብ 7 ሚሊዮን የገጠርና 0 ነጥብ 3 ሚሊየን የከተማ ቤተሰቦች ተጠቃሚ በማድረግ 34 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቶን ካርበንዳይኦክሳይድን መቀነስ፣ የቡታጋዝ ምድጃዎች 0 ነጥብ 3 ሚሊዮን የከተማ ቤተሰቦች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ 0 ነጥብ 6 ሚሊዮን ቶን ካርበንዳይኦክሳይድ ልቀትን መቀነስ፣ የባዮ ጋዝ ምድጃዎች 1 ነጥብ 0 ሚሊዮን የገጠርና 0 ነጥብ 1 ሚሊዮን የከተማ ቤተሰቦች እንዲጠቀሙ በማድረግ 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቶን ካርበንዳይኦክሳይድ መጠን ልቀትን ለመቀነስ በመንግስት ታቅዷል።

ከዚህም ባሻገር በጥሩና ተስማሚ መኖ አቅርቦት የስጋ ምንጩን በ2002 ዓ.ም ወደ 30 በመቶ ከፍ በማድረግ የ20 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የካርበንዳይኦክሳይድ መጠንን ከሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀቱ መቀነስ ያስችላል ተብሎ ይታመናል። የማረስ ተግባርን በበሬዎች በማካሄድ ፋንታ 50 በመቶ በበሬዎች መሆኑ ቀርቶ ካፒቴን መኮንን እንደሰሩት ባሉ ማረሻዎች ማካሄዱ የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀትን በ10 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ይቀንሳል።

መንግስት በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ መሪነት ለመድብለ ሚንስትራዊው የአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ስልት ከፍተኛ ወጪ አድርጓል። ከ20 ዘርፋዊ መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ ከ50 የሚበልጡ ባለሙያዎች በ7 ኮሚቴዎች ተዋቅረው በሚንስትሮች ስራ አመራር ኮሚቴ እየተመሩ አራት ዘርፎችን ለአስቸኳይ ትግበራ በማዘጋጀት ሰፊ የሆነውን የውሃ የኃይል ምንጭን በጥቅም ላይ ማዋል፣ ኃይል ቆጣቢ ዘመናዊ ምድጃዎችን በሰፊው ለየቤተሰቡ ማቅረብ፣ የቤት እንስሳት የእሴት ሰንሰለት ስሉጥነትን ማሻሻል፣ እንደዚሁም ከደን ውድመትና በደን መጎሳቆል ሳቢያ የሚከተለውን የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት መቀነስ የሚሉት ናቸው።

እነዚህ ትግበራዎች እድገትን በአስቸኳይ የማስገኘት፣ የሙቀት አማፂ ጋዞች ልቀት የመቀነስ፣ እና ለሂደታቸው የአየር ንብረት ለውጥ ገንዘብን የመሳብ ከፍተኛ እድል ስላላቸው ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራባቸው ነው።

ከደን የሚወጣው የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት በሰዎች ተግባር ምክንያት የሚከሰት ነው። በ2002 ዓ.ም የወጣው ይህ ልቀት ወደ 55 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የካርበንዳይኦክሳይድ መጠን የሚጠጋ እንደነበረ የዘርፉ ሪፖርት በግልፅ አስፍሮታል። ይህ ልቀት የሚመነጨው ሰው ደኑን ለእርሻነት ሲመነጥረው ከደን ከሚወጣው ልቀት 50 በመቶ፣ እንደዚሁም እንጨትን ለማገዶ ሲቆርጥ 46 በመቶ እና እንጨቱን በሌላ ጥቅም ለማዋል ሲቆርጥ 4 በመቶ ነበር።

እናም ካፒቴን መኮንን በሰማይ በአየር ላይ ሆነው በአውሮፕላን አብራሪነታቸው ቁልቁል እያዩት በፍጥነት የሚመነጠረውን ደንና እየሳሳ የመጣው የእፅዋት ሽፋን ሊያስከትለው የሚችለውን አደጋ ጭምር በመገንዘባቸው የድርሻቸውን ለማበርከት ከጎጆ ኢንዱስትሪ ከፍ ባለ በኢንዱስትሪ ደረጃ የሚገመት ፋብሪካ መስርተዋል። የፋብሪካው የማምረቻ መሳሪያዎች ሙሉ በሙሉ በራሳቸው የተሰሩ እንጅ አንድም ማሽን/መሳሪያ ከውጭ አላስመጡም፣ ራሳቸው በራሳቸው እጅ ሰሯቸው እንጂ ከሌላ ቦታም አልገዟቸውም።

1ኛ. ኤኮ - የሁሉነሽ በነጭ ጋዝ የሚሰራ ምድጃ 2ኛ.በነጭ ጋዝ የሚሰራ ምጣድ 3ኛ.ለየት ያለ የማረሻ መሳሪያ4ኛ.የድንጋይ መቁረጫ፣ መጥረቢያና ቅርፅ ማውጫመሳሪያ 5ኛ.የመኖ መከረታተፊያ መሳሪያ እና የቁም ከብት መኖ ማደባለቂያ መሳሪያን የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለቤት ሆነው በሐገሪቱ የተከሰተውን ድርቅና ድርቁ የፈጠረውን የእንስሳት መኖ እጥረት ለመቅረፍ ከብዙ ዓመት በፊት በምርምር የደረሱበትን ባጋስ፣ ሞላሰስና የአገዳ ጫፍ በማደባለቅ ውሃና ዝናብ የማይጠይቀውን መኖ ለማምረት ደራሽ የተቀናጀ ግብርናና ሁለገብ የልማት ሥራ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር የሚባል ድርጅት ባሁኑ ሰዓት አቋቁመው በየስኳር ፋብሪካዎቹ አካባቢ መሳሪያዎቻቸውን እያባዙና እያስፋፉ በመትከል የእንስሳት መኖ ለማምረት እየሰሩ መሆኑን መረዳት ይቻላል።

እነዚህ ከላይ ከተዘረዘሩትና ቀደምት የሆነውንየካፒቴን መኮንን የቴክኖጂ የፈጠራ ስራቸውናእንቅስቃሴያቸው ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ያለውን ትስስርና የሐገሪቱን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ መሆኑን በግልፅ አይተናል።የጋዝ ምጣዶቹለሁለት ወይም ለሶስት ዓይነት አገልግሎቶች ታስበው መሆናቸውና ማንኛውም ቤተሰብ የተለያዩ ማብሰያዎችን የሚገዛበትን ገንዘብ እንዲያድን፣ በአነስተኛ ወጪ ብዙ መጠቀም፣በየትኛውም ስፍራ በቀላሉ መገልገልእንዲያስችሉት ታስበው የተሰሩሲሆኑ

ካፒቴን መኮንን የሰሯቸው በነጭ ጋዝ የሚሰሩ ረዘም ያለ የቁም ምጣድና አጠር ያለ ቁጭ ብለው ሊገለገሉበት የሚያስችሉና ባለ ብዙ አገልግሎት ሁለት ምጣድ በመሆናቸው እንጀራ መጋገር ብቻ ሳይሆን የብረት ምጣድ ተጥዶ አገልግሎት ሊሰጥ የሚችለውን ሥራም ይሰራሉ።

ትንሹ ወይም አጭሩ ምጣድ ትልቅ ድስት/ጎላ የሚባለውን ወይም በርሜል ጥዶ በድስቱ ሊሰራ የሚችለውን ለኃዘን ወይም ለደስታ የሚሆን ምግብ ለማዘጋጀትም የሚያስችል ነው።

እነዚህ የካፒቴን የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች ከሌሎቹ የሚለዩበት ሁኔታ ደግሞ ነዳጅ ቆጣቢዎች መሆናቸው፣ ርካሽ መሆናቸው፣ እንደልብ ማንቀሳቀስና በየትኛውም ቦታ አስቀምጦ ሊጠቀሙበት ማስቻሉ፣በብረት በመሰራታቸው በትንሹ ለ5 ዓመታት ማገልገላቸው፣ ወደ ምድጃው የሚገባው ነዳጅ 90 ከመቶ የሚሆነውን ወደ ኃይል መለወጡ፣ በጭስና በሽታ የሚጠፋው ነዳጅ 10 ከመቶ አካባቢ ብቻ በመሆኑ ከሌሎቹ ፈጥኖ ማብሰል የሚችልና ብዙ አለማስጠበቁ ልዩ እንደሚያደርገው መረዳት ተችሏል። ይህ ምድጃ አብዝሃኛውን ነዳጅ ወደኃይል ስለሚቀይርና እንደሌሎች ምድጃዎች ጭስና ሽታ ስለለው ለጤና፣ ለኢኮኖሚና በኢኮሎጂ የተሻለ ውጤት ያለው ነው። ኤኮ-የሁሉነሽ ስያሜውም ሃብታሙም ድሃውም የሚጠቀምበትና የሁሉም ሰው መሆኑን ለማመላከት እንደሆነ ተረድተናል።

ትልቁና አስፈላጊው ነገር ብዙ ሰዎች ባለ 3 ፌዝ ቆጣሪ ማግኘት መቸገራቸውና ብዙዎቹ ምጣዶች ደግሞ ባለ 3ፌዝ ስለሆኑ ከፍላጎት ጋር ባለመጣጣሙ በተራ ሶኬቶች መጋገር የሚችሉ ምጣዶችም፣ የኤሌክትተሪክ ኃይል የሚቆጥቡ የኤሌክትሪክ ምጣዶችም እየተሰሩ ቢሆንም ኃይልን ሙሉ ለሙሉ ከመቆጠብ አንፃርና ኤሌክትሪክ መስመር ባልተዘረጋባቸው አስቸጋሪና ዛፍን እየቆረጡ መጋገር ግዴታቸው የሆነባቸው ቦታዎች ሁሉ ሰዎች በጋዝ ምድጃዎቹ ሊጠቀሙበት ማስቻሉ አንድ እድገት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።

ከላይ እንዳየነው ፖሊሲዎቹ ከውጭ ሐገር የተኮረጁ ቴክኖሎጂዎችን ብቻ የሚገለብጥ ዜጋን በማፍራት እነዚህን በግልበጣ/በኩረጃ የተካኑ ዜጎችን የሚደግፍ የሚያበረታታና ያልኮረጀ የማይፈለግ መሆኑን አገራዊ ባሕልና የታላቅነት መገለጫ ተደርጎ እንደመርህ እንዲወሰድ በመንግስት ደረጃ በመሰራቱ ከአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች ጀምሮ እስከ ዩኒቨርስቲዎቻችን ፈተና መኮረጅ ደንብና መብት እንዲሁም የፖሊሲው አካል ሆኖ ተተረጎመ።በሥራ ፈጠራም ሆነ በምርምር፣ በቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራ ላይ አዲስ ነገር ይዘው የሚቀርቡ ሁሉ ፖሊሲው ስለማይደግፋቸውና አመራር ላይ የሚመደቡት አንዳንዶቹ ወሳኞቹ ስላልገባቸው /ሊገባቸው ስለማይፈልጉና ተኮርጀው በሌሎች ሐገራት ተሞክረው ያልተረጋገጡ ናቸው በሚልና ላወሳሰንም በደንቦቹም ስለማይደገፉ የፈጠራ ሰዎቹን ስሜትና ተነሳሽነት በሚጎዳ መልኩ አንቋሸውና አሳንሰው ያባርሯቸዋል። የቀረቡ ወረቀቶችን እንዳልባሌ ነገር ይወረውሯቸዋል።

በንግዱ ዓለም ሌላው የለፋበትንና የፈጠራውን ሰው ስራ ኮርጀው አስመስሎ በመስራት የራሳቸው አድርገው ትንሽ እንኳን ሳይቀይሩት መልሰው ያንኑ በመስራት የፈጠራ ባለቤቶቹን ከገበያው መድረክ በዝረራ ያስወግዷቸዋል። ብዙ ነጋዴዎች ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብና እንጣለው በሚል አድማዊ ሴራ የፈጠራ ሰዎችን ከገበያው ለዘለዓለሙ እንዳይመለሱ አድርገው ይጥሏቸዋል።

በተረጋገጠለትና በታወቀ ቴክኖሎጂ ያልተቃኘና ተገልብጦ በተሰራ መሳሪያ ያልተመረተ ምርት ሜድ ኢን አሜሪካ/ጣሊያን/እንግሊዝ/ፈረንሳይ የሚል በህገወጥ መንገድ ካልተለጠፈበት በስተቀር አገሬው የሀገሩን ምርቶች በሐገሩ ልጆች የተመረቱ ከሆኑ እንዳይገዛቸው አስገዳጅነት ፈጥሯል። እናም ሜድ ኢን--- የሚሉ ነገሮችን መለጠፍ፣ ማጭበርበርንና በሕገወጥ መንገድ መጓዝን ያስቀድማሉ።ምስሉ ብቻ ከምርቱ ጋር በመታየቱ ብዙ ብሮች/ዶላሮች የሚከፈለው ፈረንጅን በማስታወቂያ ላይ በማቅረብ ራሳቸው የሰሩትን ሳይቀር ፈረንጅ የሰራው ምርት እንደሆነ በማስመሰል ፈረንጅ አምላኪወገናቸውን ይቀልዱበታል።

ወላጆቻችን ቅድመ አያቶቻችንና የነሱ ቅድመአያቶች ጥበበኞችንና ባለሙያዎችን በዘመናቸው ባለጅ፣ ቀጥቃጭ፣ ፋቂ፣ ሸማኔ፣ ቡዳ እያሉ በመፈረጅ ከማኅበረሰቡ የተናቁና የተገለሉ ቢያደርጓቸውም እነዚህ ባለሙያዎች በሰሯቸው ቁሳቁስና የመገልገያ እቃዎች ግን በሽሚያ ነበር ሰዳቢና አንጓጣጮቹ ለባለቤትነት ይጣደፉ የነበረው። አሁን ዘመን ተቀይሮ ባለሙያዎችን ባለእጅነታቸው 70 በመቶ የቀለም ትምህርቱ 30 በመቶ ሆኖ ተማሪዎችን በብሔራዊ ደረጃ በሙያ ማሰልጠን ለሐገርም ለዜጎችም ወሳኝነቱን በማረጋገጥ በትምህርቱ ካሪኩለም ተቀርፆ የእድገት አቅጣጫ ተደረገ።

የበለፀጉት ሐገራት ችግሮቻቸውን ፈትተው አኗኗራቸውን ለማቅለል በሚረዱ ፈጠራዎች ላይ እየተራቀቁና ኑሮአቸውን እያቃለሉት ነው። ያልበለፀጉት ሐገራት እንደእኛ ሐገር የመሳሰሉት ገና ያልተቀረፉ እጅግ በጣም ብዙ ችግሮች አሏቸው።አብዝሃኞቹ ወገኖቻቸው በቀን አንድ ጊዜ መብላት ያልቻሉ ናቸው። የተቀሩት ደግሞ ቁርስ ምሳና እራታቸውን 5/11 በሚል ፈሊጥ የሚመገቡ ናቸው።

ያልበለፀጉት ድሃ ሐገራት መንግስታቶች ደግሞ የበለፀጉት ሐገራት ለኑሮአቸው ማቅለያ እየሰሩዋቸው ያሉትን ቴክኖሎጂዎች ቀድታችሁ በማምጣት የራሳችሁን ችግር ዘንጉት ይላሉ። በኋላ ቀር አስተራረስ በከብቶች ጫንቃ የሚያርስና በተበጣጠሰ ማሳ የሚኖሩ ሕዝቦችን የሚመሩ መሪዎች ለየግላቸው ኦክስጅን የሚሹት ባለፀጎችን ቴክኖሎጂ ቅዱ፣ አምጡ ገልብጣችሁ እዚህ አስፋፉ ይላሉ።

ለነገሩ አብዝሃኛው ዜጋቸው ንፁሕ ውሃ ሳያቀርቡለት በውሃ ወለድ በሽታ እየተሰቃየና እንደቅጠል እየረገፈ ተሿሚዎቹ ባልሰሩት መንገድ ላይ የሚሽከረከሩ በምርጥ አስፋልት ላይ ብቻ መነዳት ያለባቸውን፣ ባልሰሩትና ባልተዘጋጀ እርባና ቢስ መንገዶች በብዙ መቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዋጋ ያላቸው የቅንጦት መኪኖችን እየተጠቀሙ ይንፈላሰሳሉ።

በድርቁ ሳቢያ የሰው ሕይወት እንዳይረግፍ የተደረገው ጥረት ባይቋረጥ ኖሮ አስመስጋኝ ነበር። ደርግ በ1965ና በ1966 ዓ.ም ንጉሱን ለማስወገድ የተጠቀመበት መንገድ በመሆኑ፣ ኢህአዴግም ደርግን በ1976 የተከሰተውን ድርቅ በማጋነን መኮነኑና ለዓለም ሕዝብ ማሳጣቱ ኢህአዴግ ይህንን ጉዳይ በቀላሉ ሊያልፈው አለመቻሉን መገንዘብ ይቻላል። ዓለም አንድ መንደር በሆነችበት የመረጃው ፍጥነት በዘመነበትና ሁሉም በየኪሱ ባለው ሞባይል ከሁሉም አቅጣጫ በሚነጋገርበትና በሚወያይበት ዘመን ችግሮቹን መደበቁ አስቸጋሪ ቢሆንም ተቃዋሚዎቹም የማይምሩት ስለሆነም ይተጋበታል።

እንደ መንግስት የእንስሶቹ ማለቅ እንደሰብአዊ ጥሰት ስለማይታሰብ አላሰጋውም። አሁንም ከደጋዎቹ ከብቶች መንጋጋ የተለመደውን መኖ እየመነገገ ድርቅ ላጠቃቸው አካባቢ እንስሳት በማስመሰል እርምጃ በለለው መኖ ከደጋ እያጓጓዘ በየበርሃው እያዳረስኳቸው ነው ይላል።

ልቅ ግጦሽ ተከልክሎ ሰዎች ከብቶቻቸውን አስረው እንዲቀልቡ ታዘዋል፣ ተገደዋልም።  የደጋው ምርት የተለመደው መኖ ግን ብዙ የሚያስኬድ አይመስልም።የቢራ ፋብሪካዎች ተረፈ ምርት ፋጉሎም ወደ እንስሳት መኖነት መግባቱ ቢታወቅም የስኳር ተረፈ ምርቶቹም ቢጨመሩ በፍፁም በቂ አይሆኑም። በአፍሪካ አንደኛ በዓለም አስረኛ ነን ተብሎ ለአስታትስቲካዊ ጠቀሜታ የሚውሉት እንስሳቶቻችን መስጠት የሚገባቸውን ጥቅም እየሰጡም አደይደለም። መቼም የእንስሳት መኖም እንደቴክኖሎጂው ከውጭ ካልተቀዳ እዚህ የሚመረቱት አያስፈልጉንም አይባልም ብየ አምናለሁ።

የተስተካከለ ቢመስልም የእንስሳት መኖ ለማምረት የሚጠየቅ የሬጉላቶሪ እንቅስቃሴ የብቃት ማረጋገጫ ሰጪ ሰነድ እና ብቃት ማረጋገጫ ሰጪ ኤክስፐርቶች በጀርመኖች የተበየዱ መሳሪያዎች ካልሆኑ የእኛ ሐገር ቴክኖሎጂስቶች የሚሰሯቸውን መሳሪያዎች ለሚጠቀሙ ፈጠራዎች ብቃት ማረጋገጫ አንሰጥም ይሉ የነበሩት ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ፖሊሲው አንፃር ተመልክተውት ከሆነ ፖሊሲው በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚንስቴርና በሚመለከታቸው እየተከለሰ ነውና የግብርና/ የእንስሳትና አሳ ሃብት ሚንስቴር ሰነዱንም ኤክስፐርቶቹንም ሊያርሙና በደንብ ሊፈትሽ ግድ የሚለው ይመስለኛል።

ተቃዋሚዎቹም የሚደግፏቸውና የሚመርጡዋቸው ሰዎች/ሰብአዊዎቹ እንጂ እንስሳቱ ባለመሆናቸው ትኩረት ያልሰጧቸው እንስሳቱ፣ይደግፉኛል/ይመርጡኛል የሚሏቸው የሰዎች ህልውና መሆናቸውን ለሴኮንዶች ታህል አላጤኑትም፣ ፈፅሞም አያጤኑትም። ግዴታቸው እንደሆነም ጨርሶ ዘንግተውታል። ካፒቴን መኮንን ካብትህይመር ግን ለቦይለር ማሞቂያ ይቃጠል የነበረውን ባጋስ ለእንስሳት መኖ ማድረግ ቢጀምሩም፣ በሃገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ከዝናብ ጋር የማይገናኝ እየተቃጠለ ይባክን የነበረውን ምርት እንስሳትን በመቀለብ በተከሰተው ድርቅና የጎርፍ አደጋ ሳቢያጉዳት እንዳይደርስባቸው ማድረጋቸውን ሳላደንቅና ሳላመሰግን ማለፍ አይቻለኝም።

አደጋን ይዞ የመጣው ዝናብ ሰብልና ሰው እያጠፋ መሆኑን እያየ ያለው መንግስት በድርቁ ላይ የጀመረውን እንቅስቃሴ በፍጥነት ቀይሮ በጎርፍ መከላከል ተግባር ላይ ብቻ ሙሉ ለሙሉ ተጠምዶ እንኳን እንስሳትን ሰዎችንም ከጎርፍ አደጋ የማዳን ብቻ መርሁ አድርጎ በርብርብ እየሰራ መሆኑ የወረትና ያለእቅድ መንከላወስ እንዳለ አመላካች ሆኖ አግኝቸዋለሁ። በኤልኒኖ ሳቢያ ከፍተኛ አደጋ ያዘለ ድረቅና አውዳሚ ዝናብና ጎርፍ እንደሚከሰት ካሁን ቀደም በሌላው ፅሁፌ በዚሁ ጋዜጣ ላይ ያቀረብኩት የመንግስትን በዘርፉ የተደረገውን ጥናት መሰረት አድርጌ በመሆኑ መንግስት ይህ እንደሚመጣ ካወቀ ዓመታት እንዳለፉት ማመን አይቸግርም። መንግስት እንደሚከሰት የሚጠብቀው ችግር ነው ያጋጠመው። ሆኖም በሰሜን ሲተኮስ ሰራዊቱን በሙሉ ወደ ሰሜን በደቡብ ሲተኮስ ወደ ደቡብ ያለእቅድ ያለዝግጅትና ያለመረጃ አንዱን በር ከፍቶ ወደየተተኮሰበት እንደሚያጓጉዝ የጦር መሪ ድርቁ ሲያይል ወደድርቁ ጎርፍ ሲያይል ወደ ጎርፉ ፖለቲካው ሲመክን ወደ ፖለቲካው መባዘኑን ቆም አድርጎ ለሁለቱም ዘላቂ የሆነ መፍትሄ መሻት የወቅቱና መፃዒ የሐገራችን እጣና አጀንዳ መሆን ይገባዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
636 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1052 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us