የደቡብ ሱዳን ትርምስና የጋምቤላው ፍጅት በኢትዮጵያ

Wednesday, 04 May 2016 12:52

 

ወሰንሰገድ መሸሻ በላቸው/ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

ካለፈው የቀጠለ

በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የያዙት ጀነራል ኦማር አልበሽር ከ24 ዓመት የስልጣን ዘመናቸው በፍፁማዊ አምባገነንነት ፈላጭ ቆራጭ ሆነው ሱዳንን ገዝተዋታል። ሆን ብለው ዜጎቻቸውን በመከፋፈል እርስበርስ አፋጅተዋቸዋል። ዓለም እየሄደበት ያለውን መስመር መከተል ግድ ስለሆነባቸውም ከ24 ዓመት የስልጣን ጉዞ በኋላ የተበላ እቁብ የተባለለትን ምርጫ አካሂደው አሸናፊ ተብለው በግልበጣ ያገኙትን የስልጣን ወንበር በምርጫ ስም ይዘው እየተጓዙ ነው።

ከ1983 ዓ.ም እስከ 2005 ድረስ የተካሄደው ረጅሙ ውጊያ አሁንም በሱዳን መሬት በደቡቡ ክፍል ይጦዛል፣ ይበርዳል። 6 ቢሊየን በርሚል የሚገመት የነዳጅ ክምችት ያለበት የደቡብ ሱዳን ግዛት ተጠቃሚ ያለመሆኑን ከሚያሳየው መረጃ አንፃር ሲታይ ይህንን የነዳጅ ክምችት የሰሜን ሱዳን አስተዳደር በቀጥታ በነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦዎች በማስተላለፍ በቀይ ባሕር ላይ በተመሰረተው ፖርት ሱዳን በኩል ለውጭ ገበያ እያቀረበ ይጠቀምበታል።

የደቡብ ሱዳን ነፃ አውጪ ግንባር የአልበሽር መንግስት ከደቡብ መሬት እየቀዳ የሚያግዘው የነዳጅ ሀብታችንን ለሰሜን ሱዳናውያን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ብቻ እያዋለው ስለሆነ ተገቢ አይደለም የሚል ክስ ሲያቀርቡ ኖረዋል፣ ለዚህ ጥያቄያቸው ምላሽ ለማግኘት መራራ ትግል አካሂደው በትግላቸው ለህዝበ ውሳኔ በቅተው ከሰሜን ሱዳን ተገንጥለው መንግስት መስርተው እንደሀገር የቆሙ ቢሆንም የደቡብ ሱዳን መንግስት ለሁለት ተከፍለው እርስበርሳቸው እየተፋጁ ነው።

ለሱዳናውያን ነዳጅ ብቸኛው የኢኮኖሚ ዋልታ ነው። ሁለቱም አካላት ነዳጅ የኢኮኖሚያቸው ዋልታ መሆኑን ይገነዘባሉ። በሁለቱም ድንበር አዋሳኝ የሆነችው የአቤይ ግዛት ደግሞ ከሁሉም አካባቢዎች ከፍተኛ የነዳጅ ክምችት ያለበትና በርካታ የውሃ ሀብት ባለቤት በመሆኗም ለሁለቱም ወገኖች እጅግ አስፈላጊያቸው የሆነ ግዛት ነው። ይህ ግዛት ደግሞ በሁለቱ መንግስታት ጥያቄ የኢትዮጵያ ሰራዊት በሰላም አስከባሪነት እንዲጠብቅ ተደርጓል።

የሱዳን መንግስት ከደቡብ ሱዳን ነፃ አውጭ ሰራዊት ጋር በሚፋለምበት ወቅት አብዝሃኞቹ የዳርፉር አፍሮ አረቦች ዳር ሆነው ውጤቱን ጠባቂዎች ነበሩ። እነዚህ የዳርፉር አፍሮ አረቦች በ1990ዎቹ አካባቢ የመሬት ጥያቄ ከማንሳት ያለፈ ብዙ እንቅስቃሴ ያልነበራቸው ጃንጃዊድ በሚል መጠሪያ የሚታወቁ ዘላን ከብት አርቢዎች ኢቢን ኦመር ሰኢድ ከሚባል አማፂ ቡድን ጋር በመቀላቀል ሰፊ የግጦሽ መሬት ያለበት በደቡብ ዳርፉር በመንቀሳቀስ አረብ ያልሆኑትን ገበሬዎች መሬት ለመንጠቅ ጥቃት መሰንዘር ጀመሩ። ታጣቂዎቹ አረብ ያልሆኑት ገበሬዎችም የተከፈተባቸውን ጥቃት በመፍራት እየለቀቁ በመሸሻቸው የደቡብ ሱዳን አማፂ ቡድን እነዚህን አረባዊ ሱዳኖች አጥቅቶ መልሶ አረብ ያልሆኑት ሱዳናውያኖችን መሬት ከተቆጣጠረ በኋላ ከ1999 ጀምሮ ማእከላዊውን የካርቱም መንግስት ማጥቃት ጀመረ።

በደቡብ ሱዳን ነፃ አውጭ ከፍተኛ ጥቃት የተሰነዘረበት የካርቱም መንግስት የአረባዊ የሆኑትን ጃንጃዊዶችን እስካፍንጫቸው በማስታጠቅና በከፍተኛ ደረጃ በማደራጀት በደቡብ ሱዳን አማፅያን ላይ የተጣመረ ጥቃት ከፈተ።

አረብ የሆኑት ጃንጃዊዶች ከካርቱም መንግስት ባገኙት ድጋፍ ታግዘው የደቡብ ሱዳን አማፂያንን የሚደግፉትንና አረብ ያልሆኑትን የከፈር፣ የዛግሀዋ፣ የማሳላይቲ ጎሳዎች የሆኑትን የደቡብ ዳርፉር ገበሬዎች እንደገና መቷቸው። በአልበሽር የታጠቁትንና የሚደገፉትን ጃንጃዊዶች መቋቋም አልቻሉም።

ጃንጃዊዶች በሙስሂላል መሪነት የደቡብ ሱዳን አማፂያንን ማጥቃት ትተው የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም ብሎ የደቡብ ሱዳን ህዝብ በአማፂያኑ ላይ እምነት ለማሳጣት የነዚህ ጎሳዎች አባላት ባልሆኑት በሌሎቹ የደቡብ ሱዳን ጎሳዎች ላይ በማነጣጠር የትግሉን አቅጣጫ ቀየሩት።

የደቡብ ሱዳን አማፂያን የደቡብ ሱዳን የነፃነት ንቅናቄ በሚባል ታሪካዊ ስም ተቀናጅተው ለረጅም አመታት የዘለቀውን ጦርነት በማቆም ለመጀመሪያ ጊዜ ግንባር ፈጥረው ደቡብ ሱዳናውያንን የሚወክልና የሚደራደር ድርጅት መሆን ቻለ። በነዳጅ በበለፀገችው በአቤይ ግዛት ከደቡብና ከሰሜን የሚጎርፉ ታጣቂዎችን የሚደግፉ የጎሳ መሪዎች በሰሜን ዘላኖቹና የደቡቡ ወገን በሆኑት የዲንቃ ጎሳዎች መካከል የሚፈፀመው ግጭት ከ100 ሰዎች በላይ ቀጥፏል።

ከ2007-2010 ብቻ በእርሻ፣ በባዮፊዩል፣ በሰብሎችና በቱሪዝም በነፃአውጭው ባለስልጣናት ከ26 ነጥብ 400 ስኩየር ኪሎሜትር /2 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር/ የሚበልጥ መሬት ለቻይናና በመካከለኛው ምስራቅና በምእራባውያን ኢንቨስተሮች የተሰጠ ሲሆን አላአይን ዋይልድ ላይፍ የተባለ የአረብ ኢምሬት ኩባንያ ለብሔራዊ ፓርክ ብሎ ያጠረው 22 ነጥብ 800 ስኩየር ኪሎሜትር ነው። የአሜሪካው ናይል ትሬዲንግ  ኩባንያ ደግሞ ከዋና ከተማዋ ከጁባ ወጣ ብሎ 6.000 ስኩየር ኪሎሜትር ሜትር ይዞ ለባዮ ፊዩል የሚሆኑ ሰብሎችን እያለማ ነው። /በእርስበርስ ግጭት አብዝሃኛው ሕዝብ ከመጠለያ ሳይወጣ ከየቀየው ተፈናቅሎ ጠመንጃ የነገበው ሁሉ ማረፊያና መድረሻው ሳይታወቅ/ የፍልስጥኤም ሀማስ ሸማቂዎች መሳሪያ ወደግዛታቸው የሚያሸጋግሩበትና የሚያራግፉበት እንደሆነ እስራኤል የምታስጠነቅቅበት ሱዳን ከግብፅ በሚያዋስናት የቀይ ባሕር ጠረፍ በሚገኝ ወደቧ በደረሰ የአውሮፕላን የአየር ጥቃትና በ2009 በኮንቦይ ይጓጓዙ በነበሩ መኪኖችም ላይ ጥቃት ደርሶ እንደነበር ይታወሳል።

በደቡብ ምእራብ የሱዳን ግዛት በዳርፉር በነዳጅ የበለፀገችው የአባያ ግዛት በኮርዶፋን ግዛት በሚገኝ የኑማ ተራራማ ቀበሌና በኮርዶፋን ግዛት ከሪፈረንደሙ ቀደም ብሎ በተካሄደው የክልል አስተዳዳሪዎች ምርጫ የሚወዳደሩ እጩዎች አብዝሃኛውን ደጋፊ ይፎክሩ የነበሩት አህመድ አሮን እና አብዱልአዚዝ አልሂሊ የተባሉ ጎሳ መሪዎች ነበሩ። አልሀሊ ዳርፉር ከደቡብ ሱዳን ጋር እንድትጠቃለል የሚፈልጉ ሲሆኑ አህመድ አሮን ግን ዳርፉር ነፃነቷን አውጃ ራሷን የምታስተዳድርበት አማራጭ ካልቀረበ ድምፀ ውሳኔው አይሞከርም ብለው በተለያየ አቅጣጫ ተሰላለፉ።

በኮርዶፋ አህመድ አሮን አሸናፊ መሆናቸው በመገለፁ የደቡብ ሱዳን ነፃ አውጪ ግንባር ዋና ፀኃፊ ጀነራል ፓጋን አሙም ተቃውመው የካርቱም መንግስት ደቡብ ሱዳንን ለመከፋፈል የጠነሰሰው ሴራ እንደሆነና ምርጫው መጭበርበሩን በወቅቱ ይገልፁ ነበር።

ከደቡብ ሱዳን ወይም ከሰሜን ሱዳን አንደኛውን ወገን መርጠው እራሳቸውን በአንደኛው ሃገር መመደብ ይጠበቅባቸው እንደነበር በመታመኑ ከደቡቡ መገንጠል በኋላም በየትኛውም ወገን ስላልሆኑም ከሁለቱ አንዱን እንዲመርጡ የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚሽን ቢደራጅም ክልሉን የሚያስተዳድሩ የጎሳ መሪዎች ክልሏ እራስን በራስ የማስተዳደር ነፃነቷን አግኝታ ሶስተኛዋ የሱዳን ሀገር ሆና እንድትንቀሳቀስ የሚፈልጉ መሆናቸውን በመግለፅ ባስነሱት ተቃውሞ ከደቡብ ሱዳንና ከሰሜን ሱዳን መንግስታት ታጣቂዎች ጋር በተካሄደ ግጭት 800 ንፁሃን ህይወት የቀጠፈና 356 ቤቶች በእሳት እንዲጋይ ተደርጓል።

የአልበሽር ጦር በነዳጅ የበለፀገቸውን አባያ ግዛት የሰሜን ሱዳን አካል ናት በማለት እ.ኤ.አ. ግንቦት 21/ 2012 በታንክ የታገዘ  ወረራ በማድረጋቸው የተመድ ዋና ፀኃፊ ባንኪሙን አውግዘው ጉዳዩን የሚያጣራ ፀጥታው ምክር ቤት ልኡካንን በሁለቱም የሱዳን መንግስታት ልከው ሳልቫኬርንና አልበሽርን በማነጋገር የካርቱም የአልበሽር ጦር ባስቸኳይ ለቆ እንዲወጣ አስጠንቅቀዋል። ለዚህም የሰጡት ምክንያት የደቡብ ሱዳን ነፃ አውጭ ግምባር የዲንቃ ጎሳዎችን እንደመጀመሪያ ዜጋ የአረብ ዝርያ ያላቸውን የሚዜሪያ ዘላኖች እንደሁለተኛ ዜጋ በመቁጠር እያሰቃያቸው ነው የሚል ነው። ይሁን እንጅ የነዳጅ ሃብቷ/ማጣሪያው በሰሜን ሱዳን ነው/ ለመወረር እንዳበቃት ይታወቃል። 40.000 ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። የምእራባውያን ዲፕሎማቶችና የአፍሪካ መሪዎች በአቤይ ግዛት በሰላም አስከባሪነት ኢትዮጵያን የመረጡበት መነሻውም የካርቱም አቤይ ግዛትን በመውረሩና ግዛቴን አለቅም በማለቱና ተመድ ልቀቅ ብሎ በመወሰኑ ነበር። ሁለቱ ሃገሮች ሲወጡ የሚተካ ኢትዮጵያ በ300 ጥምር ቡድን 4200 ወታደሮችን አሰማራች።

ከ10 ግዛቶቹ በ9ኙ ከ300 የሚበልጡ ግጭቶችን ባስተናገደችው ደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ህይወት የጠፋው በአቤይ ግዛትና በኮርዶፋ ነው። ደቡብ ሱዳን በየቀኑ 350.000 በርሚል ታወጣለች፣ ሰሜን ሱዳን 115.000 በርሜል ታመነጫለች የደቡብ ሱዳን ነዳጅም በቧንቧ በሰሜኑ ግዛት ስለሚያልፍና በሰሜን ሱዳን ውስጥ ስለሚጣራ መደራደሪያዋ ያደረገችው ካርቱም ናት።የደቡብ ሱዳን ህዝብ በሕዝበ ውሳኔ ራስን በራስ ማስተዳደር ከጀመረ በጥቂት ቀናት ውስጥ  በየካቲት 9እና 10 በደቡብ ሱዳንና በታጠቁ የጎሳ ቡድኖች መካከል በተከፈተ ውጊያ 105 መሞታቸውንና 50 ሰራዊት፣ ለ39 ታጣቂዎችና ሌሎቹ ንፁሃን ሰዎች  ሞት ተጠያቂዎቹ ኤኬ 47 የታጠቁ  የአመፅ ቡድኖች መሆናቸውን የደቡብ ሱዳን ሰራዊት ቃል አቀባይ ፊሊፕ አውገር ሲገልፁ የቀድሞው የደቡብ ሱዳን ጦር አዛዥ የነበሩት ጎርጊ አቶር በተቃራኒው በደስታ የሰከሩት የደቡብ ሱዳን ወታደሮች መሆናቸውን ይገልፃሉ። በፋንጅ ግዛት በነዳጅ ፍለጋ የፈረንሳዩ ቶታል ኩባንያ ተሰማርቶ ስለነበር በነዳጅ የበለፀገችውን ግዛታችንን ሀብት ለመዝረፍ የደቡብ ሱዳን ወታደሮች ያደረጉት ግጭት ነው ብለውም ይወነጅላሉ።

የድኅረ ቅኝ አገዛዝ ሱዳን ፖለቲካዊ መስመር ከአንድ ብሄራዊ አይዲዮሎጅ የራቀ በጎሳ፣ በቀለምና በኃይማኖት የተካረረ በጠመንጃ የተደገፈ የትግል ጎራ ሆኖ ለብዙ አመታት ኖሯል። የሰዲቅ አልማህዲን መንግስት የገለበጠው ወታደራዊው ጁንታ ከጀርባው አክራሪ የእስልምና አመለካከት ባላቸው ዶ/ር ሐሰን አልቱራቢ /በ1999 ጀምረው ከሱዳን መንግስት አፈንግጠው ወጥተዋል/ ኮሎኔል ኦማር አልበሽርን ከፊት አድርገው ተሰየሙ። እስልምናን የመንግስት ፖሊሲና መርህ ሆነ። አብላጫ ቁጥር ያለው የደቡብና የምእራብ ሱዳን ህዝብ ክርስቲያን የሆነና አገር በቀል ልማዳዊ ሃይማኖቶችን የሚከተል መሆኑ እየታወቀ የሸሪአ ሕግ በመትከል ግጭቱ የተባባሰ ቢሆንም አልቱራቢ ከዚህ ሁሉ ጀርባ የነበሩ ሰው ናቸው። (ይቀጥላል)

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
580 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 985 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us