ያላዋቂ ሳሚ ዓይነት

Wednesday, 09 December 2015 14:17

 

 

ከሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ጽ/ቤት

ኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

በሰንደቅ ጋዜጣ 11ኛ ዓመት ቁጥር 533 ረቡዕ ህዳር 15 ቀን 2008 ዓ.ም ዕትም “የኔ ሃሳብ” በሚለው ዓምድ ገፅ 20 ላይ ወልኬሳ የተባሉ ፀሐፊ ከሰባራ ባቡር አካባቢ “ፓርላማው አይሰበሰብም! ለምን?” በሚል ርዕስ የምክር ቤቱን መደበኛ ስብሰባ በተከታታይ ያለመካሄዱን አስመልክቶ ያቀረበው አስተያየት ከህግ፣ ከአሰራርና ከተጨባጭ ሁኔታ የተለየ ሆኖ በመገኘቱ አንባቢ ስለአምስተኛው አዲሱ ምክር ቤትና ስለሌሎች ተያያ¡ ጉዳዮች ትክክለኛው ግንዛቤ እንዲይዝ ይህ ፅሑፍ ቀርቧል።

ስለምክር ቤቱ ስብሰባና የስራ ዘመን

እነዚህ ጉዳዮች በህገ መንግስቱ አንቀፅ 58 ስር ተደንግገው ይገኛሉ። የምክር ቤቱ ስብሰባ የሚኖረው ምልዓተ ጉባኤ ሲሟላ እንደሆነ አንቀፅ 58(1) ንዑስ አንድ ያመለክታል። ይህ መርህ የምክር ቤቱ ጉባኤ ላይ ብቻ ሳይሆን ምክር ቤቱ በሚያቋቁማቸው ኮሚቴዎች ላይም ጭምር ይሰራል። የምክር ቤቱ የስራ ጊዜም ከመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ እስከ ሰኔ 30 እንደሆነ በዚሁ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ ሁለት እንደዚሁ ያሳያል።

ህገ መንግስቱ ምልዓተ ጉባኤ ሲሟላ ብቻ ስብሰባ እንደሚኖር ከመደንገግ ያለፈ ስለስብሰባዎች ዓይነትና በየዓመቱ ስለሚካሄዱ የስብሰባዎች መጠን የሚያነሳው ዝርዝር ነገር የለም። እነዚህ ዝርዘር ጉዳዮች በደንቦች እና በመመሪያዎች መፈታት የሚገባው ነው። ስለስብሰባዎች ዓይነት የሚደነግገው የምክር ቤቱ የአሰራርና የአባላት የስነ ምግባር ደንብ ቁጥር 6/2008 ነው።

በደንቡ አንቀፅ 13 የስብሰባ አይነቶች ተዘርዝረዋል።

አልተካሄዱም ተብሎ ቀን የተቆረጠለት የማክሰኞና የሐሙስ መደበኛ ስብሰባዎች የግድ በነዚህ ቀናት እንዲደረጉ ደንቡ አያስገድድም። አጀንዳ ካለ ስብሰባ ይኖራል፤ ከሌለ ደግሞ ስብሰባ አይኖርም። ይህን የደንቡ አንቀፅ 14 ንዑስ አንቀፅ 3 ሲደነግገው “መደበኛ ስብሰባ የማይካሄድ ከሆነ የምክር ቤቱ አባላት እንዲያውቁት ይደረጋል” በማለት ገልፆታል።

ምክር ቤቱ መስከረም 24 ቀን 2008 ዓ.ም ከተመሰረተ ወዲህ ማካሄድ ስለነበረባቸው ስብሰባዎች ብዛት የሚወስኑት እነዚህ የህግ አግባቦች ናቸው። ከዚህ በመነሳት ሶስት ነገሮችን ማመላከት ይቻላል።

1ኛ፡- እስከአሁን ድረስ አምስት መደበኛ ስብሰባዎች መካሄዳቸውን ነው። ስለዚህ የተካሔዱት መደበኛ ስብሰባዎችም ሆኑ ስብሰባ ሳይካሔድባቸው የቀሩት የስብሰባ ቀናትም በህጉ መሰረት የተስተናገዱ ናቸው። ስለዚህ የምክር ቤቱን ጉድለት የሚያሳይ ህጋዊ መነሻ የለም።

2ኛ፡- መደበኛ ስብሰባዎችን ማካሄድ አስፈላጊ ሆኖቢገኝ ኖሮ ጥቅምት 18 ቀን 2008 ዓ.ም ከተደረገው 4ኛው መደበኛ ስብሰባ ጀምሮ 8 መደበኛ ስብሰባዎችን ማካሄድ ይቻል ነበር። ያለመካሔዱም የህግ ወይም የአሰራር ክፍተትን የሚያሳይ አይደለም።

3ኛ፡- የስራ መደራረብ ወይም አፋጣኝ መፍትሔ የሚሻ ጉዳይ ምክር ቤቱን ቢያጋጥም ኖሮ በደንቡ አንቀፅ 16 መሰረት ልዩ ስብሰባዎችን በመጠቀም ከ5 ወይም ፀሐፊው እንዳመለከቱት ከ14 በላይም ስብሰባዎችን ማካሔድ ይቻል ነበር። ፀሐፊው የምክር ቤቱን የአሰራርና የአባላት የስነ ምግባር ደንብን በሚገባ ባለማወቃቸው እና ባለመገንዘባቸው አባላት ጓዝ ለማንሳት ከምስረታ በሗላ ወደ ክልል በፈቃድ የሚሄዱበትን ጊዜ ሁሉ በመደመር ቢያንስ አስራ አራት ስብሰባዎች ይካሄዱ ነበር ያሉት።

ፀሐፊው ይህንን ደንብ ባለመገንዘባቸው ምክር ቤቱን “በዓለማችን የማይሰበሰብ ፓርላማ” ወደ ሚል የተሳሳተ ድምዳሜ አድርሷቸዋል። የዚህ መከራከሪያና የተሳሳተ ድምዳሜ መነሻ ህገ መንግስቱንም ሆነ የምክር ቤቱን የአሰራርና የአባላት የስነ ምግባር ደንብን በአግባቡ ካለመገንዘብ የመነጨ በመሆኑ አንባቢያን በጋዜጣው የቀረበው የወልኬሳ አስተያየት የራሱ የግል ስሜት ብቻ እንደሆነና ምክር ቤቱን እንደማይመለከት ለመግለፅ እንፈልጋለን።

ከምክር ቤቱ ስብሰባ ጋር ተያይዞ ሌሎች ጉዳዮችንም መቃኘት ያስፈልጋል። የምክር ቤቱ የስራ ዘመን ለአምስት ዓመታት በመሆኑ ከመጀመሪያው ዓመት የተወሰነ ጊዜ ለዝግጅት ስራ መጠቀም ተገቢ ነው። በዚህ ወቅት የምክር ቤቱ አባላት በትምህርት ዝግጅታቸው፣ በፖለቲካዊ ብቃታቸው እና በስራ ልምዳቸው ምክር ቤታዊ ተልእኮን በአግባቡ መወጣት በሚችሉበት አኳኋን በየኮሚቴዎች  መደልደል አስፈላጊ ነው። ይህ ስራ ጥንቃቄ የሚጠይቅ በመሆኑ የራሱን ጊዜ መውሰዱ ግልፅ ነው።

በዚህ መሰረት ከተቋቋሙት ኮሚቴዎች አንዱ  የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች ናቸው። የነዚህ ቋሚ ኮሚቴዎች አመራርና አባላት ምድባ የተካሄደው በዚህ የጥቅምት ወር ነው። ይህ ስራ በመከናወኑ እነዚህ አስራ ስምንት ቋሚ ኮሚቴዎች የሚከታተሏቸውን አስፈፃሚ አካላት የ2008 በጀት ዓመት ዕቅድና የአንደኛ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት በማስቀረብ በግምገማ ስራ ላይ ተጠምደው ይገኛሉ። ይህም በቀጣዮቹ የምክር ቤቱ ጉባኤዎች ላይ የምክር ቤት አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሚኒስትሮች በሳል ጥያቄዎችን በጥያቄ ጊዜ እንዲያቀርቡ የራሱን የማይተካ ሚና ይጫወታል። በተጨማሪም ዝግጅቱ የቁጥጥርና ክትትል እንዲሁም የድጋፍ ስራውን የሚያጠናክር እንደሚሆን የሚታመንበት ነው።

የዝግጅቱ ስራ ሁለት ውይይቶችንም አስተናግዷል። አንዱ ከመገናኛ ብዙሃን እና ከሌሎች የዲሞክራሲ ተቋማት ጋር የተደረገው ውይይት ነው። ከመገናኛ ብዙሃን ጋር መወያየት ያስፈለገበት ምክንያት የምክር ቤቱን አሰራር የሚዲያ አካላት በሚገባ ተገንዝበው ስለምክር ቤቱ ስራ ትክክለኛ መረጃ ለህዝቡ እንዲያደርስ ለማስቻል ነው።

ሌላው ከብዙሃን ማህበራትና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር የተደረገው ውይይት ነው። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተሳትፎ ከሙያውና ከዕውቀት ዕገዛ ጋር የሚያያዝ ነው። የምክር ቤቱ የህግ አወጣጥም ሆነ የቁጥጥርና ክትትል ስራ በነዚህ ተቋማት መታገዝ በስራው ጥራት ላይ የራሱን የማይተካ በጎ ሚና ይጫወታል። ብዙሃን ማህበራት ደግሞ በተደራጀ ሁኔታ በምክር ቤቱ ስራዎች ውስጥ እንዲሳተፉ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው።

ከስብሰባ ጋር በተያያዘ ፀሐፊው በሰኔ ስለሚኖረው ጥድፊያም አንስተዋል። ረቂቅ አዋጅ በሚመረመርበት ጊዜ ረቂቅ አዋጁ በሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ፊት ከሃያ የስራ ቀናት በላይ መቆየት አይችልም። ከዚህ ውጭ አንድ ረቂቅ አዋጅ ተመርምሮ እስከሚፀድቅ ከሰላሳ የስራ ቀናት በላይ ፈጅቶ አያውቅም። ህዳርና ታህሳስ የተመራ ረቂቅ አዋጅ ቀርቶ ሚያዚያም የተመራ ረቂቅ አዋጅ ሰኔ ድረስ ሲዘልቅ ታይቶ አይታወቅም።

የአስፈፃሚ ሪፖርት የሚደመጥባቸው ጊዜያትም አስቀድሞ በዕቅድ ይመለሳል። በምክር ቤቱ በራሱ ምክንያት ጥድፊያ ውስጥ የገባበት ጊዜ የለም። ይህም ማለት ለጥድፊያ የሚሆን ውጫዊ ምክንያቶች የሉም ማለት አይደለም። ሪፖርት እንዲያቀርብ ቀጥሮ የተያዘለት አስፈፃሚ አንገብጋቢ ጉዳይ አጋጥሞት አፈ ጉባኤውን በማስፈቀድ ጊዜ እንዲቀየርለት ያደርጋል።  በአስገዳጅ ሁኔታዎች ጥድፊያ የሚፈጥሩ ስራዎች መቼም ቢሆን አይቀሩም። በተለያዩ ህጎችና በፍርድ ቤቶች አስገዳጅ ሁኔታዎች እውቅና ተሰጥቷቸው ስለሚስተናገዱ ምክር ቤቱስ ይህን ቢያደርግ ለምን የተለየ ነገር እንዳደረገ ይቆጠርበታል። ዋናው ነገር ምክንያታዊ ነው ወይስ አይደለም ብሎ ጉዳዩን በማስረጃ አስደግፎ ማቅረቡ ላይ ነው።

ስለምክር ቤቱ ዕቅድ

ምክር ቤቱ በዕቅድ ስለመመራቱም ፀሐፊው ስጋት እንዳላቸው በፅሑፋቸው ጠቁመዋል። ምክር ቤቱ በርካታ ሀገራዊ ዕቅዶችን የሚያስተናግድ ተቋም ነው። ባለፉት አምስት ዓመታት የምክር ቤቱ ስራዎች የተከናወኑት የአምስት ዓመታት ስትራቴጂክ ዕቅድ ተነድፎ ነው። የዚህ ዕቅድ አፈፃፀም ተገምግሞ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ተለይተዋል። መልካም ተሞክሮዎችም ተቀምረዋል። ይህም ለአሁኑ የምክር ቤት የስራ መነሻ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

የምክር ቤቱ የስትራቴጂክ ዕቅድ የተዘጋጀ ቢሆንም ከሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጋር ለማስተሳሰር ሲባል ይፋ አልተደረገም። ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በምክር ቤቱ ፀድቆ ወደስራ ሲገባ የምክር ቤቱም ስትራቴጂክ ዕቅድ ይፋ ስለሚደረግ ፀሐፊው ስጋት ሊገባቸው አይገባም።

የድርቁ ሁኔታ

ድርቁ ከተከሰተ በኋላ ነው የምክር ቤት አባላት ከምርጫ ክልላቸው ለምክር ቤት ምስረታ ወደአዲስ አበባ የመጡት። ድርቁ ከመስከረም 24 ቀን 2008 ዓ.ም በኋላ የተከሰተ አይደለም። በመሆኑም የምክር ቤት አባላት ሁኔታውን አብጠርጥረው ያዉቃታሉ።

 ፀሐፊው የሚለውን ስራ ለመስራት መቅደም ያለባቸው ስራዎች የተረሱ ይመስላሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን እየጎበኙ ህዝቡን እያነጋገሩ ይገኛሉ። ሚኒስትሮችም የሚሰጠውን ዕርዳታም ሆነ ከድርቁ ህብረተሰቡ ራሱን ለማዳን የሚያደርጋቸውን ጥረቶችንም ከጎን በመቆም እየደገፉ ይገኛሉ። የክልል ባለስልጣትም በዚሁ ስራ ላይ ተጠምደዋል። ከዚህ ጉብኝት የሚገኘው ግኝት ነው የምክር ቤቱንና የሌሎች አካላትን የስራ ድርሻ የሚወስነው።

ግኝቱን መሰረት ያደረገ ስምሪት ነው  ውጤት የሚያስመዘግበው። በግል የሚደረግ እንቅስቃሴ ውጤት አያመጣም። ምክር ቤቱ በድርቁ ወደተጠቁ አካባቢዎች ሲሄድ መስራት ያለበት የወሰነውን ጉዳይ አፈፃፀም መቆጣጠርና መከታተል ነው። በግል የሚሰራ ነገር አይኖርም። ስለዚህ አስፈፃሚው ከጉብኝቱ ሲመለስ ውይይት ፤ አስፈላጊ የሆነ ውሳኔና መልዕክት እንደሚኖር ይጠበቃል።

የቆዩ የምክር ቤት አባላት ሁኔታ

ሃያ ዓመታትን አሳልፈው ሃያ አንደኛውን ዓመት የያዙ የምክር ቤት አባላትን አስመልክቶ  ፀሐፊው አስተያየት ሲሰጡ አባላቱ  “ዓመታትን ከመቁጠር በቀር በአቅም ብስልትና በችሎታ የወጡበት ጊዜ የለም” ይላል። እነዚህ የምክር ቤት አባላት ለመረጧቸው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት መገለጫ እንደሆ የህገ መንግስቱ አንቀፅ 8 ንዑስ አንቀፅ 3 ያሳያል። በመሆኑም የማይሆናቸው መስለው ካገኟቸው በናንተ ላይ እምነታችንን አጥተናል በማለት ከቦታቸው የማንሳት መብትም አላቸው። እነሱ ምንም ባላሉበትና የይነሱልኝ ጥያቄ ለምርጫ ቦርድ ባላቀረቡበት ሁኔታ የሚያስታውሳቸው የለም ከሚል ከግል ስሜት ተነስቶ የአባላቱን ስም ማጥፋትና ለወከላቸው ህዝብም ክብር ያለመስጠት ህግና ደንብን መተላለፍ ነው።

ስለለምለምና ደረቅ ጣቢያ

በዚህ ጉዳይ የተከበሩ የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር በቂ ምላሽ የሰጡበት ጉዳይ ስለሆነ ብዙም ተጨማሪ ነገር ማለት አያስፈልግም። ዋናው ነገር በዚህ ጉዳይ ላይ ሁሉም የምክር ቤት አባላት እንደሚወዛገቡ ተደርጎ እንዳይወሰድ ጥንቃቄ ሊወሰድ እንደሚገባ አናስገነዝባለን።

አብዛኛው የምክር ቤት አባላት የህዝባቸውን ተጠቃሚነት መሰረት አድርገው ተልዕኮአቸውን እንደሚወጡ  ያለፉት ዘመናት ምክር ቤቶች ልምዶች ያሳያሉ። አሁን ያሉት የምክር ቤት አባላት የምክር ቤቱን ሸክሞች በራሳቸው ጉልበት፣ ጊዜ እና ገንዘብ መስዋዕትነትን በመክፈል ምክር ቤቱ አሁን ላለበት ደረጃ አድርሰዋል። አብዛኛው የአሁኑ የምክር ቤት አባላት  አመለካከትም ከቀድሞዎቹ የሚለይ አይደለም። ስለዚህ ይሄ አጀንዳ የምክር ቤቱ አጀንዳ ተደርጎ ሊራገብ አይገባም። ሊስተካከል የገባልም እንላለን።

ማጠቃለያ

ፀሐፊው ምክር ቤቱ የሚመራባቸውን ህጎችንም ሆነ  አሰራሮችን እንዲሁም ተጨባጭ ሁኔታዎችን በበቂ ሁኔታ ተረድተው አስተማሪ የሆነ ፅሑፍ ማቅረብ ሲገባቸው በቁንፅልና በግል ስሜት ላይ የተመሰረተ ሀሳባቸውን በማንፀባረቅ በምክር ቤቱ ስራ ላይ ጥላሸት በመቀባት ለአንባቢ የተለየ ምስል ለማሳየት መሞከራቸው ድርጊታቸውን ያላዋቂ ሳሚ እንዲሉ አስመስሏቸዋል። ስለዚህ ምክር ቤቱና የቆዩ የምክር ቤት አባላት ህግንና ተጨባጭ መረጃን መሰረት አድርገን በጠራ ዓይን መመልከት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ለፅሑፉ ይህን ምላሽ ለማቅረብ ተገደናል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
780 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1070 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us