የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ሕብረት /ጋዴህ/

Wednesday, 09 December 2015 14:09

 

ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር

ለአቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ

አዲስ አበባ

ጉዳዩ፡- በጋሞ ሕዝብና በአካባቢው ላይ እየተፈፀመ ያለውን ሕገ-ወጥ ተግባር ይመለከታል፤

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ከዚህ በፊት በቁጥር ጋዴህ-19/923/04 በ26/04/2004 ዓ.ም እና በቁጥር ጋዴህ-21/996/06 በ03/01/2006 ዓ.ም ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በፃፍነው ደብዳቤ፣ ችግሩን ለመ/ቤቱ በተደጋጋሚ አሳውቀናል። ሆኖም እስከ ዛሬ ድረስ በሕዝቡና በአካባቢው ላይ እየተፈፀመ ያለው ግፍና በደል ተባብሶ ቀጥሏል እንጂ አንዳችም መፍትሄ አላገኘም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የጋሞ ብሔርን ሕልውና አደጋ ላይ ይጥላል፤ በብሔሩ መብት፣ ክብርና ማንነት ላይ አነጣጥሯል የተባለው “ማዶላ” በሚል ስያሜ በአቶ ቱፋ ታዳላ የተፃፈው የስድብ መጽሐፍ በተመለከተም በቁጥር ጋዴህ-23/1004/07፣ በ18/12/2007 ዓ.ም በፃፍነው ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ለደቡብ ክልል መስተዳድር ጽ/ቤት እና ለሌሎችም ለፌዴራልና ለደቡብ ክልል መንግስታዊ መ/ቤቶችና ተቋማት የህዝቡ ጥያቄ ምላሽና መፍትሄ እንዲያገኝ እንዲደረግ፣ መጽሐፉ በብሔሩ መብትና ሕልውና ላይ ተገቢ ያልሆነ ስድብንና ንቀት የሚያራምድ ስለሆነ እያደረ እየዋለ በሕዝቡ መካከል አደጋ ከመፍጠሩ በፊት አስቸኳይ መፍትሄ እርምጃ እንዲወሰድ በማለት ጠይቀናል። ይሄው ጥያቄም ቢሆን ሰሚ አላገኘም። እንዲሁም ይባስ ብሎ ለመብቱ፣ ለማንነቱና ለሕልውናው ሲል ጥያቄ ያነሳው ሕዝብ በጅምላ ሲታሰር፣ ሲገረፍ፣ ሲቀጣ፣ ከስራ ሲባረር፣ ሀብት ንብረቱን ሲቀማ፣ መምህራን፣ የመንግሰት ሠራተኞች፣ ነጋዴዎች፣ ገበሬው…. ወዘተ ወንጀለኛ፣ ፀረ-ሠላምና አሸባሪ በሚል ስም እየተለቀሙ ከፊሎቹ እስከ አዲስ አበባ ድረስ ተወስደው ሲታሰሩ፣ ከፊሎቹ የገቡበት ሳይታወቅ ቤተሰቦቻቸው ከአንድ ወር በላይ ለሆነ ጊዜ በፍለጋ ላይ ይገኛሉ። ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው ያለአግባብ ተሰድበናል፣ መጽሐፉ የብሔራችንን መብት ያንቋሽሻልና ይወገድ፣ የመጽሐፉ ፀሐፊ ለፍርድ ይቅረብ የሚል ጥያቄ በማንሳታቸው ምክንያት ነው።

ይህ የጅምላ ቅጣትና የአፈና ድርጊት እጅግ የተባባሰው ደግሞ የማዶላ መጽሐፍ ጉዳይ ከተነሳ ወዲህ ነው። በዚህ ምክንያት ሕዝቡ ተስፋ ቆርጧል። ወላጆች ስለልጆቻቸው በሰላም ወጥተው መመለስ ዋስትና አጥተዋል። በሰላም ውሎ ያመሸ ምሽቱ እስከሚነጋ ማን እንደሚታሰር፣ ማን እንደሚታፈስ ስለማያውቅ ቤቱን ትቶ በደጅና በጓሮ ተደብቆ የሚያድርበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህ ድርጊት ቀድሞውንም ቢሆን መጽሐፉን የፃፈው ግለሰቡ ብቻውን ሳይሆን በመንግስት መዋቅር ውስጥ ባሉና ከመንግስት ከፍተኛ ድጋፍ ከሚሰጣቸው ቡድኖች ጋር ተባብሮ ነው በማለት ሕዝቡ የሚያቀርበው አቤቱታ ትክክል መሆኑን የሚያሳይ ነው።

እጅግ የሚያሳዝነው በደቡብ ክልል ውስጥ ከሌላው ብሔር በተለየ የጋሞ ብሔር ሕዝብ መብቱ እየተረገጠ፣ ማንነቱ እየተናቀና እየተዋረደ፣ አንድነቱ እንዲበታተንና እንዲጠፋ ለማድረግ እየተሞከረና የብሔሩን ሕልውና ለማጥፋት የሚደረገው ዘመቻ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተባብሶ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት ሕዝቡም ሆነ ግለሰቦች ስለመብት መጠየቅ፣ መናገር፣ መፃፍ፣ መሰብሰብ፣ ሦስት-አራት ሰው (ወጣት) ሆነው አብሮ መታየትና መወያየት በፀረ-ሰላምነት፣ በወንጀል፣ በአሸባሪነት የሚያስከሰስ፣ እንዲሁም ያለጥያቄ ታፍነውና ታፍሰው እንዲታሰሩ የሚያደርግ መሆኑ ነው።

በዞኑ ውስጥ መናገርና መፃፍ፣ እርስ በርስ መገናኘትና መወያየት መሰብሰብ፣ ስለመብት መጠየቅ፣ አሸባሪነት ሆኗል። አሸባሪነትን መጠቀሚያ በማድረግ ህዝቡን እያሸበረ ያለው የዞኑ አመራር አምባገነናዊነት ተባብሶ ችግሩ ወደዚህ ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት መፍትሄ እንዲፈልግ በማለት ለደቡብ ክልል መስተዳደር ጽ/ቤት በተደጋጋሚ አሳውቀናል። የክልሉ መስተዳደር ችግሩን እያወቀ እንዳላወቀ ሆኖ በመሸፋፈንና በመደበቅ፣ ለአጥፊዎችና ለአምባገነኖች ሽፋንና ከለላ በመስጠት የሕዝቡ ሰቆቃና መከራ ወደዚህ ደረጃ እንዲደርስ አድርጓል። ዛሬም በችግሮች ላይ ተገቢውን እርምጃ ወስዶ መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ ችግሩን በመሸፋፈንና በመደበቅ ማቆየትን መርጧል።

ስለዚህ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በዞኑ ውስጥ ያለው ችግር ከዚህ የከፋ ደረጃ ላይ ሳይደርስ፣ በጋሞ ሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለው በደል ሕዝቡን ወደባሰ ችግርና ወደከፋ አደጋ ውስጥ ሳይከት በክቡርነትዎ ኃላፊነት የሕዝቡ ጥያቄዎች እንዲፈቱና ምላሽ እንዲያገኙ፣ በዞኑ የመልካም አስተዳደር እንቅፋትና ፀር የሆኑና የሕዝቡን መብት እየረገጡ ያሉ ክፍሎች ከኃላፊነት እንዲነሱ እንዲደረግና በዞኑ መልካም አስተዳደርና ሰላም እንዲሰፍን፣ ሕዝቡም የተረጋጋና ሰላማዊ ኑሮውን እንዲመራ እንዲደረግ በአክብሮት እንጠይቃለን።

ከአክብሮት ጋር

ፊርማና ማህተም አለው

ጀምበሬ ገ/መድህን

ም/ሊቀመንበር ¾ 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
647 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1045 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us