የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) 3ኛ መደበኛ ጠ/ጉባዔ የአቋም መግለጫ

Wednesday, 14 October 2015 13:33

 

እኛ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) 3ኛ መደበኛ ጠ/ጉባዔ ተሳታፊዎች ዛሬ መስከረም 30 ቀን 2008 ዓ.ም ያካሄድነውን የአንድ ቀን ጉባዔ አጠናቀን ስንነሳ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ፤ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ አቋማችንን በመግለጽ የሚከተሉትን አስቀምጠናል።

1.  እንደሚታወቀው ሁሉ ላለፉት 25 ዓመታት በስልጣን ላይ የሚገኘው የኢህአዴግ መንግስት የመጀመሪያውን አምስት ዓመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አጠናቆ ሌላ ሁለተኛውን ለመቀጠል በመንደርደር ላይ ይገኛል። በተጠናቀቀውም ሆነ ሊጀመር ባለው እቅድ ውስጥ ኢኮኖሚው የላቀ የአንበሳውን ድርሻ መያዙ ሲታወቅ፤ እንደ ኦክስጅን (አየር) ለሰው ልጅ ህልውና እና ሁለንተናዊ እድገት በእጅጉ አስፈላጊና መሰረታዊ የሆኑ የዜጎች የግል ነፃነት ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች መረጋገጥ የሕግ የበላይነትና ትክክለኛ ዳኝነት ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ ጉዳዮችን ከሕገመንግስቱ ማዕቀፍ አኳያ በመጀመሪያውም ሆነ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ በቂ ወይም ምንም ትኩረት ያልተሰጠባቸው በመሆኑ የአምስቱ ዓመት እቅድም ሆነ ክንውኖቹ የህዝቦቻችንን ሌሎች መሰረታዊ ጥያቄዎችንና ፍላጎቶች የማያሟሉ በመሆናቸው በአጠቃላይ እቅዱ በዚህ መልኩ ሊከለስና ሊስተካከል ይገባል እንላለን።

2.  የኢህአዴግ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ አማራጮቻቸውን አንግበው ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ትግል የሚያካሂዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በሀገራዊ ህዝባዊ ጉዳዮች ተቀራርበው የሚሰሩበት ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ እንደሚመቻች በየጊዜው ቃል እየገቡ ቢሆንም፤ እስካሁን ገዢው ፓርቲም ሆነ መንግስት ከገጠር ንዑስ ቀበሌ እስከ ፌደራል ፓርላማ ያለውን ሁኔታዎች በሙሉ በብቸኝነት በሞኖፖል በመያዝና በመቆጣጠር ብቻቸውን ሊጋልቡና ሊያስጋልቡ ሀገራዊና ህዝባዊ አጀንዳዎች ዙሪያ ከተቃዋሚዎች ጋር አብሮ የመስራት ጉዳይ ቃልና ተግባር ሆድና ጀርባ የሆኑበት ሁኔታ ታርሞ የፖለቲካ የውይይት መድረክ በአስቸኳይ እንዲከፈት እንጠይቃለን።

3.  በኅብረተሰባችን ዘንድ የሚስተዋለው የእስካሁኑ የፖለቲካ ጥላቻና ቁርሾ ቂምና በቀል በብሔራዊ መግባባት የማይቋጭ ከሆነ፤ ሀገራችን የስጋት ቀጠና ከመሆንዋ የተነሳ ተጋላጭነቷም ተጠናክሮ ለውስጣዊ ውስብስብ ችግሮች እና ለውጫዊ ጣልቃ ገብነቶች ተጋልጣ በአጠቃላይ ሀገራችንና ህዝባችን ወደ ከፋ ሁኔታ ከመሻገራቸው በፊት ኢህአዴግ ለብሔራዊ መግባባት አጀንዳ ራሱን በቅንነትና በቁርጠኝነት አዘጋጅቶ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሁኔታዎችን በአስቸኳይ እንዲያመቻች በአፅንኦት እንጠይቃለን፤ ዛሬም ነገም ለብሔራዊ መግባባት ለስኬቱ አምርረን እንታገላለን። በሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት በእድሜ ጠገብነቱ የሚታወቀው የብሔራዊ መግባባት አጀንዳ በኢህአዴግ ከተጣለበት ግዞት ነፃ ወጥቶና ነፍስ ዘርቶ በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች የጋራ ትብብርና ጥረት ተልዕኮው እስኪሰምርና አስኳሉ ፍሬ እስኪያፈራ ድረስ ዛሬም ነገም ድምፃችንን ከፍ አድርገን እንጮሃለን። ህዝቡም በጋራም ሆነ በተናጠል ድምፁን ከዳር እስከ ዳር እንዲያስተጋባ እንጠይቃለን።

4.  በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ የሀገራችን ህዝቦች ላይ እያፈራረቀ የሚደርሰውንና እያደረሰም የሚገኘውን አሳሳቢና አስጨናቂ የድርቅና የረሃብ ክስተት ለመከላከልም ሆነ ለመቆጣጠር የኢህአዴግ መንግስት እንቅስቃሴ ሠርገኛ መጣ፣ ጎመን ቀንጥሱ ዓይነት ከተጠበቀውና ከተገመተው በታች ሆኖ የመገኘቱ ጉዳይ በእጅጉ አሳሳቢ ከመሆኑ አኳያ የባሰና የከፋ የረሀብ የጭንቅ ወቅት ከመፋጠኑ በፊት ሁሉም መንገዶች ወደ ረሃብ ግንባር ሊያቀኑ ይገባል እንላለን።

5.  በጠቅላላና አአካባቢያዊ ምርጫዎች ዋዜማና ማግስት በሀገራችን ተፎካካሪ ፓርቲዎች መንደር የሚጋጋሉ የትብብር ጥምረት ቅንጅትና የውህደት እንቅስቃሴዎች ትኩሳታቸው በቀናትና በሳምንታት እጅግ ቢበዛም በጥቂት ወራት ደብዛቸው እየጠፋ ይባስ ብሎ ከድጡ ወደ ማጡ እየተንሸራተተ ለበለጠ የእርስ በርስ መጠላለፍና መጎሻሸም ጥላሸት መቀባባትና መጠፋፋት ብሎም… “ውሻ በቀደደ” …. አይነት ውጫዊ አካል ወይም ክፍል በጠባቡ ቀዳዳ ገብቶ በገሃድ ከማተራመሱ ባሻገር ራስ-ወዳድነታችንና ከንቱ ዝና መሻታችንን አካባቢያዊነታችን፣ ድብቅ የስልጣን ጉጉታችንና ጥማታችንን ተደማምሮ የቆምንለትን ትልቅ ህዝባዊ ዓላማችንን እየጨፈለቅንና እያስጨፈለቅን በምንገኝበት በአሁኑ ወቅት ከዚህ አይነቱ ድንግዝግዝ የፖለቲካ ቁማር ተላቀን በቅንነትና ግልጽነት በዴሞክራሲያዊ መርህ ደረጃ ተቀራርበን ሰላማዊ ትግሉን አፋፍመን ለማስቀጠል የተዘጋጀን የፖለቲካ ፓርቲዎች ብንኖር ፓርቲያችን በመልካም ምሳሌነትና በቁርጠኝነት የተቃዋሚዎችን የሰላማዊ ትግል ትብብር ከማረጋገጥ ረገድ እስካሁን የተጀመሩ አንዳንድ የትብብር ሙከራዎችን ለማሳካት የበኩሉን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።

6.  የሀገራችን የአፍሪካ ቀንድ ጂኦ ፖለቲካዊ ጉዳዮች እና ሁኔታዎች አሳሳቢነታቸው ሊካድ የማይችል ሐቅ በመሆኑ መንግስት ከጎረቤት ሀገሮች በተለይም ከኤርትራ ጋር ያለው ፍጥጫ ከጫፍ ደርሶ ጦር አማዝዞ በዜጎቻችን ህይወት በአካልና ንብረት ሜጋ ፕሮጀክታችንንና እንዲሁም አንድነታችን ላይ አደጋ ወይም ኪሳራ እንዳያስከትል /ከውጭ ወራሪ ራስን መከላከለ እንደተጠበቀ ሆኖ/ ከአስመራ መንግስትና በኤርትራ በረሃ አሉ ከተባሉ ተቀናቃኞች ጋር ጊዜውን የጠበቀና ያወቀ ዴሞክራሲያዊ ውይይት እንዲካሄድ አጥብቀን እንጠይቃለን። ሀገራችን ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት ልታመጣ የምትችለው የአፍሪካ ቀንድ እና አካባቢዋ አህጉራዊና የዓለም ሠላምና ዴሞክራሲ የጋራ ብልፅግናና ዕድገት ለዜጎች ነፃነትና የሰብአዊ መብት መረጋገጥ ከፍተኛውንና ታሪካዊ ዓለም አቀፋዊና አካባቢያዊ ድርሻችንን ስንወጣ መሆኑን የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) በፅኑ ያምናል።

የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) 3ኛ መደበኛ ጉባዔ

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

መስከረም 30 ቀን 2008 ዓ.ም

አዲስ አበባ¾    

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
611 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1028 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us