እህልና አረም

Wednesday, 29 July 2015 17:50

በዳንኤል ክብረት (www.danielkibret.com)


 

የሀገሬ ገበሬ ዘር ያስቀምጣል። መርጦና መጥኖ። ሁሉም እህል ዘር አይሆንምና። በተቻለ መጠን ወፍ ያልቆረጠመው፣ ነቀዝ ያልቀመሰው፣ ሌላ ነገር ያልተቀላቀለበት፣ ያልተሸረፈና ያልተቦረቦረ፣ ሲያዩት የሚያምር፣ ሲበሉት የማያቅር ተመርጦ በልዩ ሁኔታ በልዩ ቦታ ይቀመጣል። አቀማመጡም የራሱ ሞያ አለው። ሞያውን ችሎ የሚያስቀምጠው ገበሬ ዘንድ ‹እገሌ ዘንድ ዘር አይጠፋም› እየተባለ አገር ይጠይቀዋል፤ ለሀገርም ዘር ያተርፋል።

 


 በዚህ ሁኔታ ጠብቆ ያኖረውን ዘር ሲዘራው ግን እንደ ገበሬው ቋንቋ የሚበቅለው ‹እህልና አረም ነው።›› ፈልጎ ከዘራው እህል ጋር የማይፈልገው አረም አብሮ ይበቅልበታል። መጽሐፉስ ‹ዘሩ በበቀለ ጊዜ አረሙ ደግሞ ያን ጊዜ ታየ› አይደል የሚለው። ገበሬው አረሙን ሁለት ጊዜ ነው የሚታገለው። መጀመሪያ እንዳይበቅል በመከላከል። ዘሩን የሚመርጠው፣ አበጥሮና አንጠርጥሮ፣ ለቅሞና ሸክፎ የሚይዘው ለዚህ ነው። ዘሩ የሚወድቅበትን መሬትም አስቀድሞ መንጥሮና አስተካክሎ፣ ጎልጉሎና ለቅሞ ያጸዳዋል። አረም እንዳይኖረው ሲል። ይህንን አልፎ ከዘሩ ጋር አብሮ አረሙ ሲበቅል ግን ቢችል ‹ሆ› ብሎ በደቦ ባይችል እርሱና ቤተሰቡ ወጥተው አረሙን ያርሙታል። ‹ለአረም ቦታ መስጠት ደግም አይደል›› ይላል ገበሬው። ቦታ ላለመስጠትም ከሥር ከሥሩ ያርማል፣ ሥር ከሰደደ ዋናውን እህል እስከመዋጥና እስከ ማጥፋት ይደርሳልና። ማሳውም የስንዴ፣ የጤፍ፣ የገብስ መባሉ ቀርቶ ‹የአረም እርሻ ይሆናል።

 


በኢትዮጵያችን የታሪክ ግንዛቤ ብንከተለው የሚበጀን ይኼ የገበሬው መንገድ ይመስለኛል። መቼም ማንም ገበሬ ሆን ብሎ አረም አይዘራም። ከአረም የሚያገኘው ጥቅም የለምና። ትርፉ ድካምና ኪሳራ ስለሆነ። ነገር ግን ሳይወደው አረሙ ከእህሉ ጋር ይበቅላል። በታሪካችንም ማንም ሕዝብ ጦርነት፣ እልቂት፣ በደል፣ ግፍና መከራን ይሁነኝ ብሎ ወይም ፈልጎ የዘራ አይኖርም። እምነቶቻችን እነዚህን እንድንጠላና እንድንጸየፍ የሚያስተምሩ ናቸው። ብዙዎቹ ተረቶቻችንን ብናይ እነዚህን የሚኮንኑና የሚያወግዙ ናቸው። በአብዛኛው ባሕላዊ ዘፈኖቻችን ግፍን፣ መከራን፣ መገዳደልን፣ መተላለቅንና ጭቆናንን የሚያማርሩ ናቸው። ነገር ግን እነዚህ ነገሮች ሳንወድ አብረውን በቅለዋል። ድልን፣ ስምን፣ ሥልጣኔን፣ ግዛት ማስፋፋትን፣ ሀብትን፣ ክብርን፣ ጀግንነትን፣ ሥልጣንን እንዘራለን ስንል ወይ ሳናውቀው አብረን ዘርተናቸዋል፣ ያለበለዚያም ሳንዘራቸው መሬቱ ተመችቷቸው በቅለዋል። ዘሩ ሲታይ አረሙም እንደዚያው አብሮ ታይቷል።

 


ከአኩሪው ታሪካችን ጎን አሳፋሪው፣ ከአንድነት ታሪካችን ጎን የመለያየት፣ ከመዋደድ ታሪካችን ጎን የጠብና ጥላቻ፣ ከሥልጣኔ ታሪካችን ጎን የኋላ ቀርነት፣ ከድል ታሪካችን ጎን የሽንፈት፣ ከክብር ታሪካችን ጎን የውርደት ታሪኮች አብረውን በቅለዋል። አንፈልጋቸውም፤ ሆን ብለንም አልዘራናቸውም፤ ነገር ግን በቅለዋል። ታድያ ምን እናድርጋቸው? ነው ጥያቄው።

 


እንደ ገበሬው ዕድል እንንፈጋቸው። ገበሬው ለአረም ዕድል አይሰጠውም። በአረሙና በእህሉ መካከል የሚፈጥረው ልዩነትም ይኼው ነው። እህሉ እንዲያድግ ይከባከበዋል፡፤ አረሙን ግን እንዳያድግ ዕድል ይነፍገዋል። አረሙ ይበቅላል፣ ብቅ ይላል፣ ከፍም ይል ይሆናል። ነገር ግን እንዳያድግ፣ አድጎም እንዳያፈራ፣ አፍርቶም ዘር እንዳይተካ ዕድል ይነፍገዋል። እኛም እንደ አረም ለበቀሉብን የጥላቻ፣ የመገዳደል፣ የመጨቋቆን፣ የመለያየት፣ የመከፋፈል፣ ታሪኮች እንዳያድጉ ዕድሉን እንንፈጋቸው። ፍግና ማዳበሪያ አናድርግላቸው። መሬቱን አናመቻችላቸው፤ ዝናቡን እንዲጠቀሙ አንፍቀድላቸው፤ እነርሱ ሳይፈለጉ የበቀሉ አረሞቻችን ናቸው። ብንችል በደቦ ‹ሆ› ብለን ወጥተን እናርማቸው። ካልተቻለም በቤተሰብና በግል ለአረሞች ዕድል እንንፈጋቸው።

 


ዘወትር ስለ እነርሱ እየተናገርን፣ ፊልምና ዶክመንተሪ እየሠራን፣ ሐውልት እያነጽና በዓል እያከበርን፤ ልጆቻችን አጥብቀው እርሱን ብቻ እንዲያውቁ እያደረግን፤ የንግግሮቻችን መክፈቻ የማንነታችን መመሥረቻ እያደረግን፤ ለአረሞቹ ዕድል አንስጣቸው። አዎ በቅለው ነበር፤ አዎ ዘሩ ሲታይ አብረው ታይተዋል፤ አዎ የታሪካችን አካል ናቸው። ነገር ግን የሚታረሙ እንጂ የሚበቅሉ አይደሉም። ሥር እንዳይሰዱ ዕድል የሚነፈጉ እንጂ አምመው ጠምጥመው እንዲወጡ ዕድል የሚሰጣቸው አይደሉም።

 


ይልቅ ለእህሉ ዕድል እንስጠው። ካልሆነ የታሪክ እርሻችን ‹የአረም እርሻ› ይሆናል። አረምና እህል አብረን እያበቀልን ብዙ አንዘልቅም። ያለ ጥርጥር አረሙ እህሉን ይውጠዋል። መዋጥ ብቻም አይደለም ያጠፋዋል። ከዚያም እህል እንዳልተዘራበት ሁሉ የአረም እርሻ ያደርገዋል። ያኔ ማሳው ለከብት እንጂ ለሰው አይሆንም። ኢትዮጵያችን ለዜጎቿ እንድትሆን ከፈለግን ከአረሙ ይልቅ ለእህሉ ዕድል እንስጠው። አረሙን ዕድል እንንፈገው።

 


በጎ ነገር እንዳልነበረን፣ አብረን ዘምተን አብረን ድል እንዳላደረግን፣ እንዳልተዋለድንና እንዳልተጋባን፣ የሰሜኑ ደቡብ፣ የደቡቡም ሰሜን እንዳልሄድን፤ የምዕራቡ ምሥራቅ፣ የምሥራቁም ምዕራብ እንዳልተሰደድን፤ ባሕልና እምነት፣ ከብትና መሬት እንዳልተዋረስን፤ አብረን ተነሥተን አብረን እንዳልወደቅን፤ አብረን እንዳልሞትንና አብረን እንዳልተቀበርን፤ ሌላው ቀርቶ ከጦርነቶቻችንና ከወረራዎቻችን እንኳን ውሕደትንና ቅይጥነትን እንዳላተረፍን ሁሉ ክፉ ክፏችንን ብቻ እየተረክን፣ ጥላቻውን ብቻ ነቅሰን እያወጣን፣ ግፍና መከራውን ብቻ ከፍ አድርገን እየተናገርን፣ አረሙን ሆን ብለን በማሳደግ ላይ ነን።

 


ምናለ ከገበሬው ብንማር፤ ለአረሙ ዕድል ባንሰጠው። አረም አረምን ይወልዳል። የትናንቱን አረም ዕድል እየሰጠነው ሥር ሰድዶ እንዲበቅልና ከፍ ብሎ እንዲታይ ባደረግነው ቁጥር ለተተኪውም ትውልድ አርሞ የማይጨርሰው ሌላ ገንጋና አረም እንዘራለታለን። ገበሬውኮ ለአረሙ ዕድል የሚነፍገው ወድዶ አይደለም። አረሙ እንደሆነ ገበሬው ሠራም አልሠራም፣ አረሰም አላረሰም፣ ዘራም አልዘራም ይበቅላል። ብቻ መሬት ያግኝ። የታረሰ ካገኘማ እሰየው። ግን ምንም ጥቅም የለውም። ጥቅም ለሌለው ነገር ለምን ይደክማል? የገበሬው ገበሬነት የሚለካውኮ ባጠፋው አረምና ባመረተው ምርት ልክ ነው።

 


የአንዲት ሀገር ሥልጣኔ፣ ታላቅነትና ዕድገት የሚለካው በአረሟ ብዛት አይደለም። በምርቷ ብዛትና ጥራት እንጂ። አረሙን እያረመች፣ እህሉን እያበዛች ስትሄድ ብቻ ነው። ሀገር አደገች ተመነደገች የምትባለው። ፈረንሳይና ጀርመን እርስ በርስ ተዋግተዋል፣ ተጋድለዋል፣ ተጠፋፍተዋል፤ ያ ግን አረም ነው ብለው አረሙት እንጂ ይበልጥ እንዲያድግ ዕድል አልሰጡትም። ከጦርነቱና መተላለቁ አረም ይልቅ ለአንድነቱና ኅብረቱ እህል ዕድል ሰጡትና የአውሮፓ ኅብረት ዋና መሥራቾች ሆኑ። የአሜሪካ ክፍለ ግዛቶች ጎራ ፈጥረው እርስ በርስ ተዋግተዋል፣ ተጋድለዋል፣ ተጫርሰዋል። ያ አረማቸው ነው። አረሙን ግን ዕድል አልሰጡትም። አረሙን ትተው ለእህሉ ዕድል እየሰጡ ይበልጥ አንድ፣ ይበልጥም ታላቅ ሆኑ።

 


በአረም ማደግ እንደማይቻል ሶማልያና ኮንጎ እያስተማሩን ነው። እንግሊዝና ስኮትላንድ እየመከሩን ነው። ብልህ ከጎረቤቱ፣ ብልጥ ከስሕተቱ ይማራል እንዲሉ ብንችል ከጎረቤት ካልቻልንም አረም በራሳችን ላይ ካመጣው መዓት ብንማር መልካም ነበረ።

 


አሁን እንኳን እንደገበሬው ምርጡን ዘር ለመዝራት እየሞከርን አይደለንም። በትምህርት ቤቶቻችን፣ በሚዲያዎቻችን፣ በሰብሰባዎቻችን፣ በንግግሮቻችን፣ በበዓሎቻችን፣ ስለየብሔረሰቡ በምንጽፈውም ታሪክና መግለጫ እየተጠነቀቅን አይደለንም። የተበላሸ ዘር እየዘራን ነው። እንደገበሬው አልተጠነቀቅንም። ዘሩን አልመረጥነውም፣ ክፉውን አልለቀምነውም፣ አረሙ እንዳይቀላቀል አላበጠርነውም። አረሙ ከዘሩ ጋር እየተዘራ፣ አረሙም ከዘሩ በላይ እየበቀለ፣ አረሙም እህሉን እየዋጠው ነው። እንደ ሀገር መቀጠል፣ እንደ ሀገር መቆም፣ እንደ ሀገር ማደግ፣ እንደ ሀገርም መሠልጠን ከፈለግን ለአረሙ ዕድል ልንነፍገው ይገባናል። ከአጥሩ ይልቅ ለድልድዩ፣ ከመለያያው ይልቅ ለመግባቢያው፣ ከመፋቻው ይልቅ ለመጋቢያው፣ ከርቀቱ ይልቅ ለግንኙነቱ ዕድል ልንሰጠው ይገባናል።

 


አንዳንዱ ነገራችን እንዲያውም ከአረሙ ይልቅ ለእህሉ ዕድል የሚነፍግ ነው። ትውልዱ በሀገሪቱ ውስጥ አረም ብቻ ሲዘራ እንደኖረ አድርጎ እንዲያስብ የሚያደርግ ነው። ያ ደግሞ አገርን “የአረም እርሻ” ያደርጋታል። በአረም ያደገና የሠለጠነ ሀገር ስለሌለ እስኪ እኛ እንሞክረውና ሪከርድ እንስበር ዓይነት ነው ጉዟችን።

 


አንዳንዴ ለአረም ዕውቅና መንፈግና ለአረም ዕድል መንፈግ የተምታታብን ይመስላል። አረም ነበረ፣ ይታወቃል። ሊካድም አይችልም። ታሪካችንም ምስክር ነው። ለአረሙ ዕውቅና መስጠት ማለት ለአረሙ የማደግ ዕድል መስጠት ማለት አይደለም። ‹አረም ነበረብን፣ ልናርመው ይገባል› ብሎ መወሰን ማለት እንጂ። አረሙን ማወቅ የሚጠቅመው አረሙን ለማጥፋት ዕድል ስለሚሰጥ ነው። ያላወቁትን ማጥፋት ስለማይቻል። በሌላም በኩል አረሙን ማወቅ የሚጠቅመን ‹አረሙን እንነቅላለን ስንል እህሉን አብረን እንዳንነቅለው› ሲባልም ነው። አረማችንን ዕንወቀው፤ ዐውቀንም እናርመው። “ዐውቀን እንታረም› ይሉ ነበር የቀድሞ ሊቃውንት። ለልጆቻችን ስለ አረሙ ስንነግራቸው ተጨማሪ አረም እንዲዘሩ፣ ወይም የበቀለውንም አረም ይበልጥ እንዲከባከቡና እንዲያሳድጉ አድርገን መሆን የለበትም። አረሙን ዐውቀው እንዲያርሙት፣ ሌላ አረም እንዳይበቅልም ዕድል እንዲነፍጉት መሆን አለበት እንጂ።

 

 

 

 

 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1408 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1035 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us