የደርግና የኢዲዩ፣ ያይጥና ድመት ፍልሚያ

Wednesday, 08 July 2015 15:00

የመጽሐፉ ርዕስ -    “ትግል አይቆምም”

ደራሲው -          ዮሴፍ ያዘው (ሻለቃ)

የገፁ ብዛት -        285

አታሚው     -     አልፋ አታሚዎች

አስተያየት አቅራቢ - ማዕረጉ በዛብህ

 

ደራሲው መፅሐፉን ለምን እንደፃፉ በመግቢያው ሲያስረዱ ሁለት ምክንያቶች ያቀርባሉ። አንደኛው ምክንያት በደምብ ገብቶች ከሆነ በደርግ ዘመን ብዙ ትግሎች ቢካሄዱም ሁሉም በየፊናው ያካሄደው ትግል የሆነ የታሪክ ሰነድ ስለሌለ “ትግል አይቆምም” የተባለው መፅሐፋቸው የዚያን ጊዜ ሁኔታ ትረካ የተሟላ ለማድረግ ቢያግዝ ከሚል በመነሳት ነው። ሁለተኛው ምክንያታቸው ደግሞ ከሳቸው ትግል “የተገኘው ልምድ ለአሁኑና ለተተኪው ትውልድ” ትምህርትነት ሊኖረው ስለሚችል ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው በጽሁፍ እንዲያሰፍሩት ስላበረታቷቸውና እርሳቸውንም ስላሳመኑዋቸው ነው።

 

የመጽሐፉን ይዘት በሶስት ትልልቅ ክፍሎች መመደብ የሚቻል ይመስለኛል። የመጀመሪያው ክፍል የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የጦር አካዳሚ ሐረር ላይ መቋቋሙን፣ የተመልማዮችን የትምህርት ደረጃና በአካዳሚው ለ3 ዓመት ሰልጥነው ሲወጡ በተደረገላቸው የማዕረግና የደሞዝ ምደባ ቅሬታቸውን ለንጉሠ ነገሥቱ የማቅረባቸውን ትግል የሚገልጸው ነው። ሁለተኛው ክፍል የመጽሐፉ ደራሲ የደርግን ስልጣን ባለመቀበል ከጀኔራል አማን የተደረገላቸውን ጥሪ ተቀብለው ወደሀገር በመመለስ ከሌሎች ስድስት የአካዳሚ ምሩቃን ጋር በጀኔራሉ ቢሮ ስራ መጀመርንና ከጀኔራሉ ሞት በኋላ ደርግን ለመጣል የተደገው ሙከራ ባለመሳካቱ አገር ጥሎ መውጣትን የሚመለከት ነው። ሶስተኛው ደግሞ ከኬንያ ወደ ሱዳን በመግባት ከኢዲዩ ጋር አብሮ መስራትን፣ የኢዲዩ ከፍተኛ ኃላፊ መሆንና ፀረ- ደርግ ትግልን ማካሄዱን የሚያጠቃልለው ክፍል ነው።

 

 

የአካዳሚው ምሩቃን ቅሬታ

እንደሚታወቀው የሐረር አካዳሚ እንደ ብሪታንያው ባንድ ሐርስትና የአሜሪካኑ ዊስት ፓይንት የጦር አካዳሚዎች ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን ለማሰልጠን የተቋቋመ በመሆኑ በዚያ ተቋም የሚመደቡ መምሕራንም ሆኑ የሚሰለጥኑት ዕጩ መኮንኖች አመራረጥ በከፍተኛ ደረጃ የሚከናወን ነው። በተለይ ምልምሎቹ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መልቀቂያ ፈተናን በሚገባ ያለፉና የጤና ምርመራቸውንም ያላንድ ችግር ያስመሰከሩ መሆን ነበረባቸው። ታዲያ በዚህ በአፍሪካ አቻ በሌለው ብቸኛ የጦር አካዳሚ ሶስት ዓመት ሰልጥነው መኮንኖች ማዕረጋቸው ም/መቶ አለቅነት ደሞዛቸውም 115 ብርና የዲፕሎማ 90 ብር ተጨምሮ 215 ብር መሆኑ ምሩቃኑን እጅግ እንዳሳዘናቸው በሚገባ ተገልጿል። ቅሬታቸውንም “ከዩኒቨርስቲ ከሚመረቁ እኩዮቻችሁ አናሳንሳችሁም” ላሉዋቸው ለቀዳማዊ ኃይለስላሴ ማቅረባቸውንና ደራሲው ራሳቸው ከአቤቱታ አቅራቢዎቹ አንዱ እንደነበሩ ይተርካሉ። የመኮንኖቹ አቤቱታ በንጉሡ ፊት ቀርቦ ከተነበበ በኋላ ደራሲው እንደሚነግሩን ጃንሆይ የሰጡት መልስ “የተናገርከው አግባብ የለውም አይባልም፣ አግባብ አለው። ሆኖም አሁን አገራችን ባለችበት ሁኔታ ብዙ መታየት ያለበት ጉዳይ አለ። ለማንኛውም ጉዳዩን አጥንተን መልሱን ባለቆቻችሁ በኩል እናስታውቃችኋለን” የሚል እንደነበር ተዘግቧል።

 

ይህ አመዳደብ ለብዙ ጊዜ ሲያነጋግር የኖረ ኢፍትሃዊ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ ሳይቀሩ ጥቂቶቹን የአካዳሚ ምሩቃን ሲያነጋግሩ “ከናንተ አንጻር ሆኖ ለሚመለከት በርግጥ ተበድላችኋል። ጥያቄያችሁም መሠረት ያለው ነው። ይህ ችግር ሳይፈታ እዚህ መድረሱ ደግሞ በመንግሥት በኩል የቱን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ እንገነዘባለን። በኛም በኩል ስህተት አለ። ያነሳችሁት ችግር ከአካዳሚው መከፈት ጋር አብሮ ተጠንቶና ተወስኖ ቢሆን ኖሮ ያሁኑ ሁኔታ ባልተፈጠረም ነበር። አሁንም ቢሆን ትንሽ ጊዜ ሊወሰድ ይችላል እንጂ ሊታረም አይችልም ማለት አይደለም” ነበር ያሉት።

 

 

ሌላው ችግር አገራትዋ በወታደራዊ ትምህርት የሰለጠኑ መኮንኖችን ለማፍራት በየጊዜው የተከተላችው መርህ ነው። የክብር ዘበኛና የሆለታ የመኮንኖች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤቶች ስልጣኞቹን የሚመለምሉት የአንደኛ ደረጃን ከጨረሱ ተማሪዎች ሲሆን የስልጠና ጊዜያቸውም የክብር ዘበኛው ሶስት አመት የሆለታው ጦር ትምህርት ቤት ግን ከአንድ ዓመት በማይበልጥ ቆይታ ነው። ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የጦር አካዳሚው ግን በምክትል መቶ አለቅነት የሚያስመርቃቸው መኮንኖች የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያን ፈተና በሚገባ ያለፉ ሲሆን ከዓለም ታላላቅ አካዳሚዎች ጋር የሚወዳደረውን ከፍተኛ ትምህርትና ወታደራዊ ስልጠና የሚወስዱት ለሶስት ዓመታት ነው። በስራ ላይ ሲመደቡ ከሌሎቹ ም/መቶ አለቃ ምሩቃን የሚለዩት ለዲፕሎማ ተብሎ በሚከፈላቸው 90 ብር ብቻ ነው። ስለዚህ የአካዳሚው ምሩቃን ቅሬታ ባለሁለት ነጥብ ነው። አንደኛው ራሳቸው ንጉሠ ነገሥቱ የሰጡት ቃል “ከዩኒቨርስቲ ከሚመረቁ (450 ደሞዝ) እኩዮቻችሁ አናሳንሳችሁም” የሚለው አለመፈጸሙ ሲሆን ሁለተኛው ቅሬታ ደግሞ ከተለያየ የትምህርት ደረጃ ተመልምሎ አንድ ዓመት ወይም ሶስት ዓመት ሰልጥኖ ሲወጣ የመመረቂያው ማዕረግ ም/መቶ አለቃ መሆኑ ነው።

 

ሌላው ደራሲው በመጽሐፋቸው አፍላ ክፍሎች ላይ ሊያሳዩ የሚሞክሩት በወቅቱ የአገራችን የአሰራር ችግር ምክንያት የአካዳሚው ምሩቃን አቤቱታ ያላንዳች መፍትሔ ለሶስት ዓመት ከቆየ በኋላ “ከመቶ አለቃ እስከ ኮሎኔል ማዕረግ ላይ ለነበሩ የሠራዊቱ መኮንኖች በሙሉ ተሰምቶ የማይታወቅ ያልታሰበ ከፍተኛ የደሞዝ ጭማሪ” መደረጉን ነው። ለምሳሌ ያህልም የሻምበል ደሞዝ ቀድሞ ከነበረው 175 ብር እስከ 400 ብር እርከን መድረሱን፣ የሻለቃ ደሞዝም በፊት ከነበረበት 300 እስከ መጨረሻው እርከን እስከ 600 ብር መድረሱን ይገልፁልናል። ደራሲው ይህ ወደር የሌለው የደሞዝ ጭማሪ ለመኮንኖች ሲደረግ የበታች ሹማምንቱና የወታደሩ ሁኔታ ከግምት ውስጥ አለመግባቱ አሳስቧቸዋል። ጦሩ “ለለውጥ አላሚዎችና አንቀሳቃሾች” ልዩ የፕሮፓጋንዳ ሲሳይ ሆነላቸው በማለት በየካቲት 1966 አመጽ ጋር ያያይዙታል። ደርግና ኢዲዩ በዚህ ርዕስ መጽሐፉ የሚተርከው የወታደራዊ አስተዳደር ደርግን መቋቋም የጀኔራል አማን አንዶምን የመከላከያ ሚኒስትርና የደርግ ሊቀመንበር ሆኖ መሾም በደርግና በጀኔራል አማን መካከል እየተፈጠረ ስለሄደው መቃቃር፣ በተለይም በደርጉ ም/ሊቀመንበር በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምና በጀኔራሉ መካከል የተፈጠረውን የስልጣን ሽኩቻ፣ በደርግና በጀኔራል አማን መካከል የነበረውን መቃቃር ሲጽፉ ደራሲው በደርግ ላይ የነበራቸውን ተቃውሞ አልሸሸጉም። ደርግ የነበረውን መንግሥት “አፍርሶ ራሱን እንዲተካ፣ በሠራዊትም ሆነ በሕዝብ አልተመረጠም” የሚለውን አስተያየት በአጽንኦት አቅርበዋል። አብዮት ነው ከተባለም ደግሞ ደርግ ያንንም ለመምራት ብቃትም ችሎታም እንደሌለው አምናለሁ” ይላሉ። አብዮቱን ለመምራት ለምን “ብቃትም ችሎታም እንደሌለው” ግን ማስረጃ አለማቅረባቸው መጽሐፉን ከመረጃ ይልቅ ወደ ስሜታዊነት ይወስደዋል የሚል ስጋር ይፈጥራል።

 

ደራሲው ስለ ጀነራል አማን ያላቸው አድናቆት እጅግ ከፍተኛ ነው። “በመሪነታቸው የሚያስመሰግንና የሚያስወደድ ከፍተኛ ዝና ሲነገርላቸው እሰማለሁ። በሱማሌ ጦርነት ላይ ያስገኙት የሚያኮራ ድል፣ ከወታደሩ ጋር ያላቸው ቅርበት - ወታደሩ በሰፈረበት ሁሉ በየጊዜው እየሄዱ በድንኳን እያደሩ፣ ወታደሩ የሚበላውን አብረው እየበሉ ስለሚጎበኙት ከፍተኛ መወደድና እምነትን በወታደሩ ላይ አሳድሮበት ነበር” ይላሉ።

 

መጽሐፉ አንዳንድ አዳዲስ መረጃዎችን ያስነብበናል። የኢዲዩ ተቋም በውጭ አገር የነበረውን ተቀባይነትና የሚያገኛቸውን ዕርዳታዎች ይጠቋቁማል። በመሪዎቹ መካከል የነበረውን የስልጣን ሽኩቻ በመካከላቸው የነበረውን የአስተሳሰብ ልዩነት ይገልጻል። ደርግን ለመጣል የተደረጉትንም ሙከራዎችና ከውጭ የኢዲዩን እንቅስቃሴ ይደግፉ የነበሩትን ኃይሎች ከመግለፅ አኳያም መጽሐፉ ብዙ መረጃዎች ይዟል። በኢዲዩ ዋና ሊቀመንበር ጀኔራል ኢያሱ እና በም/ሊቀመንበሩ በልዑል ራስ መንገሻ መካከል የነበረው መቃቃር በልዑሉና በጄነራል ነጋ ተገኝ መካከል እያደገ የሄደውን አለመጣጣምም ተዘግቧል። እነ ሻለቃ ዮሴፍ ያዘው፣ ኢንጅኔር ሞገስ ብሩክ እና ሻለቃ/ዶር ተፈሪ ተ/ሃይማኖት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ነፃ አውጭ ትግልን (ኢብነአት)ን ከኢዲዩ ጋር ማዋሃድና ሶስቱ ኢብነአት መስራቾች በኢዲዩ ውስጥ ከፍተኛ የትግል አመራር ሚና መጫወትም በመጽሐፉ ውስጥ ሰፊ ቦታ ይዘዋል።

 

በመጽሐፉ ውስጥ አንዳንድ በጥያቄ መልክ የሚነሱ ተጠቋቁመው መልስ ያልተሰጠባቸው ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ በገጽ 173 ተጠቀሰው “የኢራን መንግሥት ለኢዲዩ ትግል እንቅስቃሴ መረጃ የሚውል ሰባት ሚልዮን የሱዳን ፓውንድ” የለገሰ መሆኑንና ጄኔራል ነጋን ገንዘቡን ሄደው እንዲረከቡ ከገለጸ በኋላ ጀኔራሉ ቴህራን ድረስ ቢሄዱም ገንዘቡን ሳይሰጣቸው መቅረቱ በምን ምክንያት እንደሆነ አይታወቅም። የሱዳን ፀጥታ ኃላፊ “አሜሪካ ደርግን ከሶቪየት ጎራ አውጥቶ ለመውሰድ” እየሞከረ ስለሆነ የኢራን መንግሥት እርዳታውን እንዳይሰጥ ጠይቀውት ይሆናል ከሚለው መላምት በስተቀር ግልጽ የሆነ ትክክለኛ መልስ አልተሰጠም። ሁመራ ላይ በተደረገው ጦርነት ኢዲዮ የደርግ ወታደሮችን እንዳሸነፈና ገንዘብ እንዳገኘ ተደጋግሞ ቢጠቀስም የገንዘቡ መጠንና ማን ገንዘቡን እንደተረከበ አልተገለፀም።

 

 

የኢትዮጵያ ቲቪ ደርግን ከስልጣን የማውረድ ሙከራ

ሶስቱ ቆራጥ ጓደኛሞች ሻለቃ ዮሴፍ ያዘው (ደራሲው)፣ ሻለቃ/ዶር ተፈሪ ተክለሃይማኖትና ኢንጅኔር ሞገስ ብሩክና እነርሱ ያዘጋጁዋቸው አቶ ይልማ ቀኛዝማች አዘነ ውቤንና አቶ ዘሪሁን ወዘተ ደርግን ከስልጣን ለማውረድ ማክሰኞ የካቲት 9 ቀን እንዲሆን በተወሰነው መሰረት በዚያ ምሽት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጣቢያን በተረኛ መኮንኖች እርዳታና ትብብር በመያዝ ደርግን ከስልጣን የሚያወርድ መግለጫ እንዲሰጥ ቀጠሮ ተደርጎ ነበር። ይህንን ስራ እንዲያከናውኑም የቡድኑ አባሎች የሆኑት ሌ/ኮ ጌታቸው ኃይሌ እና አቶ ይልማ ኃላፊነቱ ተሰጥቷቸው ነበር። ሆኖም በዚያ መልዕክቱ እንዲተላለፍ በተወሰነበት የዜና ሰዓት በሆነው በ2 ሰዓት ላይ ሲጠበቅ የመፈንቅለ መንግሥቱ ዜና አልነበረም። በቡድኑ ላይ በደረሰው ከባድ ድንጋጤ ሶስቱ የእንቅስቃሴው ጀማሪዎች ሻለቃ ዮሴፍ ኢንጅኔር ሞገስና ሻለቃ (ዶክተር) ተፈሪ ካገር ወጥተው ወደ ናይሮቢ አመሩ። ያ የቲቪ ፕሮግራሙ እቅድ ለምን እንደከሸፈ ኮሎኔል ጌታቸውና አቶ ይልማ ስልክ ደውለው ምን እንደሆነ ባለመግለፃቸው የአመጹ መሪዎች ከአገር ወደመውጣቱ ዝግጅት ነው ወዲውኑ የተሸጋገሩት። ሶስቱን የአድማውን መሪዎች ቀጥለን የምናገኛቸው ናይሮቢ የተቃዋሚ ቡድን ለማደራጀት ሲሞክሩና ቀጥሎም ሱዳን ገብተው ከኢዲዩ ጋር ተቀላቅለው ፀረ-ደርግ ትግሉን ሲቀጥሉ ነው። የከሸፈው ፕሮግራም ዝርዝር መረጃ በመጽሐፉ አልተሰጠም፤ ለምን?

 

ማናቸውንም የተደገነበትን ጥበቃ ለመደምሰስ የሚችል የተጠናከረ ኃይል የሌለው ቡድን የአንድን መንግሥት ቴሌቭዥን ጣቢያ ይዞ የአመጽ አዋጅ ለማስማት ማቀድ በጣም አስቸጋሪ ነው። መታቀዱ ራሱ ብዙ በራስ መተማመን ላይ የተመሰረተ ጀብደኝነት ነው የሚመስለው። ደራሲው ግን ስለ አድማው መክሸፍ በሰጡት አስተያየት “በመብትና ነፃነት ትግል ላይ ከመሳሪያ፣ ከድርጅትና ከሰው ብዛት ሃይል የበለጠ ሚዛን ያለው መንፈሰ ጠንካራ፣ ቆራጥ ፣ በትግል ልምድና የተሳሰረ ጥራት ያለው ቡድን ነው” ካሉ በኋላ እኛ ያን ቡድን ነበርን ወይ? ሲሉ ይጠይቃሉ። ቀጥለውም ነበርን ለማለት እንኳን ብንሞክር የትግሉ ውጤት ያሳጣናል። ምናልባት ከቡድኑ አባሎች ብዙዎች መንፈሰ ጠንካራና ቆራጥ ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን የተሳሰረ የትግል ልምድ ዓላማና ጥራት ገና በማዳበር ላይ እንደነበረ ታሪኩ ይመሰክራል። በጊዜው እኛም ጥቂቶቹ ይህን ስጋት አልሳትነውም፣ ነገር ግን ሁላችንም ይብስብናል ባልነው፣ ሕዝቡ በደርግ ላይ ባለው ጥላቻና ንዴት የተነሳሳው መንፈሱ ሳይረግብ፣ በወቅቱ ለመድረስ ቅድሚያ ሰጠን፣ እንዳቀድነው አልሆነም ትምህርቱ ከዚህ ላይና ይኽነው” ሲሉ አስተያየታቸውን ይደመድማሉ።

ለማጠቃለል ያህል ከመጽሐፉ ስለጀኔራል አማን አንዶም፣ ስለደርግ፣ ስለኢዲዩና ስለ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የጦር አካዳሚና ስለ አካዳሚው ምሩቃን ያገኘናቸው መረጃዎች በአብዛኛው አሳዛኝ ቢሆኑም ጠቃሚዎች ናቸው። ትምህርታዊነታቸውም አከራካሪ አይደለም። ደራሲው ከላይ በተጠቀሱትና ባልተጠቀሱት የወቅቱ ጉዳዮች ያቀረቡት ዝርዝር ትረካ ስፋቱ የሚያስደንቅ ብቻ ሳይሆን የቋንቋው ገላጭነትና ውበት ስነፅሁፋዊ ሂደቱን በዚህ አስተያየት አቅራቢ ዕይታ አጓጊና ተነባቢ አድርጎለታል። መቼም መልካም ስራንም እንከን አያጣውምና የነጥቦች ስርዓትን ከመከተል ላይ ከፍተኛ ችግር ይታይበታል። በሰረዞች፣ በነጠላ ሰረዞችና በአራት ነጥቦች ላይ ሊኖር የሚገባው ትክክለኛ አገልግሎት ተሸሮ መጽሐፉ በጠቅላላው በጥቂት አራት ነጥቦች፣ በጥቂት ነጠላ ሰረዞች ብቻ ሲስተናገድ በቀረው ቦታ ሁሉ በጥቅም ላይ የዋለው (ትክክል ባልሆነ መንገድ) በሰረዝ ብቻ ነው። በዚህ ስህተት ምክንያት ደራሲው ያሰፈሩዋቸውን ለምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሃብተወልድ ተናገሩት እንደተባለው ያለውን አንዳንድ ጠቃሚ አረፍተነገሮችን በትክክል ለመጥቀስ አስቸግሯል። በሚቀጥለው እትም በዚህ በነጥቦች አቀማመጥ ስርዓት (Punctuation) ሊተኮርበት ይገባል።

 

ሌላው እዚህ ላይ ሊነሳ የሚገባው የመጽሐፉ አርዕስት ጉዳይ ነው። “ትግል አይቆምም” የሚለው ዳያለክቲካዊ መፈክር ጭቆና እስካለድረስ ትግል ጨርሶ አይቆምም የሚለውን ሃሳብ ነው የሚገልፀው። በመጽሐፉ ውስጥ የምናየው ዋናው ጉዳይ ግን ደርግና ኢዲዩ የሚያደርጉትን እየተፈላለጉ መዋጋትና መጠፋፋትን ነው። ለዚህ ሂደት የሚሻለው ስያሜ ደግሞ በዚህ አስተያየት አቅራቢ አተያይ በዚህ ጽሑፍ ርዕስ ላይ የተቀመጠው “የደርግና የኢዲዩ፣ ያይጥና ድመት ፍልሚያ” የሚለው ነው። ፈረንሳይ “የቪቭ ላዲፈራንስ” (vive la Difference) ይል የለ።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
1671 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1085 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us