ያለፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የተገኘ አሸናፊነት የመድበለ-ፓርቲ ሥርዓት ውድቀት ማረጋገጫ ነው

Wednesday, 08 July 2015 14:25

ከመኢአድ፣ ከኢዴፓ እና ከኢራፓ የተሰጠ የጋራ መግለጫ

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) እና የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ላለፉት የሰላማዊ ትግል ዘመናት የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱን ዕውን ለማድረግ በየበኩላችን መጠነ ሰፊ ትግል አድርገናል። የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን ለመገንባት በሁላችንም የፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል በፕሮግራማችን ውስጥ ተቀርጾ የትግላችን ምሰሶ በመሆን የምንችለውን ሁሉ ስናደርግ ቆይተናል። የዴሞክራሲ ሥርዓቱ ከጊዜ ወደጊዜ ፍሬያማ ከመሆን ይልቅ እየቀጨጨና እየኮሰመነ በመሄድ ላይ ይገኛል። ለመድበለ ፓርቲ ዋና መገለጫ የሆነው የምርጫ ሂደት ችግርም ቁልጭ አድርጎ እያሳየን ያለው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው እያሽቆለቆለ መሄዱን ነው። የምርጫ ስርዓቱም ሆነ ሂደቱ ለአገራችን ሰላማዊ ትግልና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንቅፋት ሆኖ አግኝተነዋል።

 

የአገራችንን ሰላም ለማረጋገጥ ዋናውና ቁልፉ ጉዳይ የዴሞክራሲ ሥርዓት ሂደት እውን መሆን ነው። ለዚህም በዋናነት ተጠቃሽ የሚሆነው ፍፁም ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እውን ሲሆን ብቻ ነው። በ2007 ዓ.ም የተከናወነው 5ኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ባለመሆኑ ምክንያት በአገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ላይ ጥቁር ነጥብ ጥሏል። ይህም በመሆኑ በአገራችን ያለው አንፃራዊ ሰላም አስተማማኝ አይሆንም የሚል ስጋት አድሮብናል።

 

እኛ ሦስቱ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለ5ኛው ዙር ምርጫ ፍትሐዊነትና ዴሞክራሲያዊነት የተጫወትነው ሚና መጠነ ሰፊ ነበር። የምርጫውም አጠቃላይ ውጤት በማንም ዘንድ ተዓማኒነት እንዲኖረው የየበኩላችንን ሚና ተጫውተናል። ነገር ግን በገዢው ፓርቲም ሆነ በሌሎች ዴሞክራሲያዊ ተቋማት በኩል የነበረው የምርጫ ሚና በአድሎአዊነት የተሞላ በመሆኑ ገዢውን ፓርቲ ብቻ ሙሉ በሙሉ አሸናፊ ያደረገ የምርጫ ውጤት እንዲታይ አስችሎታል። ይህም የወደፊቱን የአገሪቱን የፖለቲካ ጉዞና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደትን እያቀጨጨ የሚሄድ በመሆኑ በቀጣዩ የሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ላይ ከፍተኛ እንቅፋት እንደሚፈጥር በግልጽ ያሳያል።

 

በምርጫ ቦርድ የተገለፀው የምርጫ ውጤት በአህጉር ደረጃም ይሁን በዓለም አቀፍ የዴሞክራሲ ኃይሎች ተቀባይነት የሌለው ፍፁም አሳማኝ ያልሆነ እና የዴሞክራሲን አነስተኛ መመዘኛ እንኳን የማያሟላና እውነታ የማይገልጽ ነው። ይህ በተለያዩ አካላት ለማመን በሚያስቸግር ደረጃ የተገለፀን የምርጫ ውጤት መቀበል ሕገወጥነትን ማበረታታትና አምባገነኖችን መሸለም ሆኖ አግኝተነዋል።

 

የምርጫ ቦርድ አጠቃላይ የምርጫ ውጤቱን ሲገልጽ ኢህአዴግ 100% አላሸነፈም ለማለት የተጠቀመበትና አጋር የሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶችን 18% እንዳሸነፉ ተገልጾ ገዢው ፓርቲ ያሸነፈው 82% ብቻ ነው ብሎ ለማሳየት የተደረገው የውጤት አገላለጽ ከአንድ ገለልተኛ ነኝ ከሚል የምርጫ ቦርድ የማይጠበቅ በመሆኑ በእኛ በኩል አሳዛኝ ሆኖ አግኝተነዋል። በ2002 ዓ.ም ምርጫ አጋር ድርጅቶችን ጨምሮ ገዢው ፓርቲ 99 ነጥብ 6% አሸንፏል በማለት ምርጫ ቦርድም ሆነ ራሱ ገዢው ፓርቲ ሲገልፁት የነበረ የአደባባይ ሚስጢር ነበር። አሁን በ2007 ዓ.ም የምርጫ ውጤት አገላለጽን ስንመለከተው ምርጫ ቦርድ የገዥውን ፓርቲ አጋዥነትን ያረጋገጠ በመሆኑ ሂደቱ በፍፁም አሳዝኖናል። የምርጫ ቦርድን አድሎአዊነት በበለጠ ሁኔታ እንድናረጋግጥ አድርጎናል።

 

በምርጫው ሂደት ወቅትም ሆነ በመጨረሻ የተገለፀው አጠቃላይ የምርጫ ውጤት በሰላማዊ ትግሉ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ፈጥሯል። እኛ ወደ ምርጫ ውድድር ስንገባ ይፈፀሙብን የነበሩ የሕግ ጥሰቶች ሁሉ አሉታዊ ተጽዕኖ የፈጠሩብን ቢሆኑም፤ የሕግ ጥሰቶች እንዲስተካከሉ በመጠየቅና በመቻቻል መርህ የአገራችንን የመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ሥርዓት የተወሰነ ደረጃ እንገፋለን በማለት ነበር። ይሁን እንጂ የተስተዋለው አሉታዊ የምርጫ ውጤት እኛንም ተስፋ ያስቆረጠ ህዝብንም በምርጫ ላይ ያለውን እምነት ያሟጠጠበት ሂደት ሆኖ አይተነዋል። በመሆኑም ለቀጣዩ የሰላማዊ ትግል ትልቅ ተግዳሮት ሆኖ አግኝተነዋል።

 

ከምርጫ ቦርድ አጠቃላይ የውጤት መግለጫ በፊት ግንቦት 19 ቀን 2007 ዓ.ም ጊዜያዊ ውጤት መገለፁ ይታወቃል። ይህንንም ጊዜያዊ ውጤት መሠረት በማድረግ ሦስታችንም ፓርቲዎች በተናጠል በሰጠነው ጋዜጣዊ መግለጫ ውጤቱን ባለበት ሁኔታ ኢ-ዴሞክራሲያዊ፣ ኢ-ፍትሐዊና በህዝቡ ዘንድ ተአማኒ እንዳልነበር የተገለፀውን ውጤት የማንቀበል መሆኑን በተናጠል ገልፀናል። የማንቀበልባቸውን ምክንያቶች በቅድመ ምርጫውም ሆነ በምርጫው ዕለት የደረሱትን የሕግ ጥሰቶችና ህፀጾች በዝርዝር አስቀምጠናል። በተለይም በየደረጃው እና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በዕጩዎቻችንና ታዛቢዎቻችን እንዲሁም በአባሎቻችን ላይ የደረሱትን በደሎች በዝርዝር ገልፀናል። አሁንም ግንቦት 19 ቀን 2007 ዓ.ም የተገለፀውን ጊዜያዊ ውጤትም ሆነ ሰኔ 15 ቀን 2007 ዓ.ም የተገለፀውን የኢህአዴግን ሙሉ በሙሉ አሸናፊነት የማንቀበል መሆኑን እያረጋገጥን እኛ ሦስቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአጠቃላይ የወደፊቱ የፖለቲካ ትግል ሂደትና የሰላማዊ ትግል ጉዞን የተቃና ለማድረግ በተከናወነውም ምርጫ አጠቃላይ ሂደት ያለውን ችግር በማስመልከት የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥተናል።

 

1.  ከቅድመ ምርጫው፣ በምርጫው ዕለትም ሆነ ከምርጫውም በኋላ ምርጫን ሰበብ በማድረግ በዕጩዎቻችን፣ በአባሎቻችንና በደጋፊዎቻችን ላይ የስነልቦና ተፅዕኖ በመፍጠር፣ ከስራ በማፈናቀል፣ ካሉበት አካባቢ እንዲሰደዱ በማድረግና በማሰር የደረሰውን በደል እያወገዝን በደል ባደረሱት ላይ መንግስት ክትትል በማድረግ እርምጃ እንዲወስድ በጥብቅ እንጠይቃለን።

 

2.  በየደረጃው ባሉት አባላት ላይ በአሁኑም ሰዓት እየደረሰ ያለው ማንኛውም ተፅዕኖ በአስቸኳይ እንዲቆም እንጠይቃለን።

 

3.  በሀገራችን ዴሞክራሲ እንዲጠናከርና እንዲያብብ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ ተብለው የሚጠበቁ ተቋማት በምርጫው ሂደት ላይ የፈጠሯቸው ተግዳሮቶች በሰላማዊ ትግሉ ላይ ትልቅ ጋሬጣ በመሆናቸው የወደፊቱን ሰላማዊ ትግል እጅግ ውስብስብና አስቸጋሪ አድርጎታል። እነዚህ ተቋማት ሕገ-መንግስቱ በሚፈቅደው መሠረት ተግባራቸውን እየተወጡ ባለመሆናቸው የቻልነውን ሁሉ ሰላማዊ ትግል በማድረግ ተጽዕኖ ለመፍጠር በቁርጠኝነት እንታገላለን።

 

4.  ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እውን መሆን በተለይ ገዢው ፓርቲ ዋነኛ እንቅፋት መሆኑን ተገንዝበናል። ገዢው ፓርቲ ከዚህ ግትር አቋሙ ፈቀቅ የማይል ከሆነ የአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታም ሆነ አጠቃላይ የአገሪቱ ሰላም አጣብቂኝ ውስጥ ይገባል ብለን እናምናለን። በመሆኑም ገዢው ፓርቲ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት የምርጫ ዴሞክራሲያዊነትና ፍትሐዊነት መርሆዎችን ካላከበረ ህዝቡን ወደአልተፈለገ አቅጣጫ ይመራዋል ብለን እንሰጋለን። እኛ ሦስቱ ፓርቲዎች ከትግሎች ሁሉ ከፍተኛ መስዋዕትነትንና ቁርጠኝነትን የሚጠይቀውን የሰላማዊ ትግል መርህን አጥብቀን በመከተል ለዴሞክራሲና ፍትሐዊ ምርጫ እውን ይሆን ዘንድ በፅናት እንታገላለን።

 

5.  በመላው ዓለምም ሆነ በአገር ውስጥ የምትገኙ ዜጎች ለዚህች አገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያላችሁ ሚና የላቀ መሆኑን አጥብቀን እናምናለን። በመሆኑም ለሰላማዊ ትግሉ አሸናፊነት እውን መሆን ከመቼውም ጊዜ በላቀ መንገድ ከትግሉ ጎን እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

 

6.  በመንግስትና ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ሙሉ በሙሉ ተመርጫለሁ፤ በመሆኑም የመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፍ አግኝቻለሁ በሚል የተሳሳተ የምርጫ ውጤት ሳይታበይ አጠቃላይ የምርጫውን ሂደትና ውጤት አስመልክቶ እራሱን በመመርመር፣ በመገምገምና በመፈተሽ፤ የህዝቡን ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ለማጎልበት እንዲቻል ያገባኛል ከሚሉ ኃይሎች ጋር በመነጋገር ለችግሩ መፍትሄ መስጠት ይችል ዘንድ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

 

7.  በመጨረሻም እኛ ሦስቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በየፓርቲያችን የሰላማዊ ትግላችንን እያከናወንን በጋራ ሊያሰልፉን በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ለወደፊትም አብረን እንደምንሰራ እየገለጽን ሌሎችም አቻ ፓርቲዎች አብሮ ለመስራት ከጎናችን እንዲሰለፉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

 

ሰኔ 25 ቀን 2007 ዓ.ም

አዲስ አበባ

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
763 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us