የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ምን እየሆነ ነው?

Wednesday, 24 June 2015 12:15

በቀልቤሳ መኮንን

የኮምዩኒኬሽን ስራ አስፈላጊነት በተለይ አሁን ባለንበት እጅግ ግዙፍ መረጃ፣ እጅግ ፈጣን በሆነ ሁኔታ በሚርመሰመስበት ዓለም አንዱ ወሳኝ መስክ ነው። ከመንግስታት እስከ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከግለሰቦች እስከ ኩባንያዎች በመሰረታዊ ማንነታቸው፣ አላማቸውና እቅዳቸው ዙሪያ ይመለከተዋል የሚሉትን አካል የማሳወቅ የማሳመን ስራ በቀጣይነት ይሰራሉ። ዘመናችን የመረጃ ዘመን ነው። መታመንና መጠርጠር፣ መወደድና መጠላት፣ መግነንና መረሳት ወዘተ… ከመረጃና መረጃውን ቀምረን ኮምዩኒኬት ከምናደርግበት አግባብ ጋር በእጅጉ የሚተሳሰርበት ሁኔታ ሰፊ ነው። በእኛ ሁኔታ ዴሞክራሲያችን የህዝቡ ቀጥታ ተሳትፎና ተከታታይነት ያለው የመረጃ ፍሰት የሚጠይቅ ነው። ህዝቡን በቀጣይነትና በስፋት የማሳተፍ ጉዳይ በፋይዳውና በሂደቱ የማሳመን፣ ከልምዱ እየቀመሩም ለቀጣይ ተልዕኮ ንቁ ተሳታፊ የሚሆንበትና በሂደቱ ውስጥም ትክክለኛው አስተሳሰብ ላይ የማይናወጥ መግባባት የመፍጠር ስራ ያስፈልጋል። ለዚህም በመሰረቱ የተዋጣለት የኮምዩኒኬሽን ስራ ያስፈልጋል። የህዝብ ግንኙነት ስራችን ሳይንሳዊና ጥበባዊ ገፅታ በማሳደግ ስራ ላይ ማዋል የግድ ይላል።

እስካሁን የነበረንን የጦርነት የረሃብና የልመና ገፅታን የማስወገድ ስራም ከውስጥ በምናመጣው ስኬት ላይ ተንተርሶ ነገር ግን ራሱን የቻለ ፋይዳ እንዳለው ጉዳይ ተወስዶ መሰራትም የሚገባው መሆኑ እሙን ነው።

ወደ ተነሳሁበት ርእስ ልመለስና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በህዝብ ግንኙነት ዙሪያ የተጀማመሩ መልካም ስራዎች አሉ። የጉዳዩ አንገብጋቢነት ያህል ግን ለዚህ ዘርፍ ብዙ ትኩረት አልተሰጠውም። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሀገራዊ የህዝብ ግንኙነት ስራ በመጠኑም ቢሆን መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው። ስራዉንም በመንግስት ከነበረው የዘርፉ አመለካከት አንፃር በተሻለ ደረጃ የተጓዘበትና ይበል የሚያሰኝ ነው። ተጠናክሮ መቀጠል ያለበትም ይመስለኛል።

ይሁን እንጂ የህዝብ ግንኙነት ስራ በዕውቀት፣ በክህሎትና በመልካም ስነምግባር ካልታገዘ፣ እንዲሁም ባለሙያው ሊያሳምነው የሚፈልገውን ለራሱ አምኖና ሆኖ የማይገኝ ከሆነ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። ኮምዩኒኬተሩ በተለያዩ ጊዚያት በሚያገኛቸው ህትመቶችና ኤልክትሮኒክስ ሚዲያዎች ራሱን ማበልፀግ ይኖርበታል። ይሄ መንግስት ከሚያመቻችለት አጫጭር ስልጠናዎች ጋር ተዳምሮ ለሙያው አጋዥ ይሆናል የሚል ግምት አለኝ። የረጅም ጊዜ ትምህርት ፕሮግራም ተቀርፆ ኮምዩኒኬተሩ በዕውቀት ከፍ የሚልበት ሁኔታ ቢመቻች ደግሞ የበለጠ ይሆናል።

የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ይህን ዘርፍ ይበልጥ ለማጠናከር ወደ ተለያዩ የፌዴራል መስሪያ ቤቶች ኮምዩኒኬተሮች ሲመድብ ቆይቷል። ከአምስት ዓመት በፊት የምደባ ስርዓቱ ከሞላ ጎደል ግልፅና የበላይ ኃላፊዎች ኮሚቴ አዋቅረው የሚመድቡበት አካሄድ ነበር። የነበረው የምደባ ስርዓት ከሞላ ጎደል ግልፅና አብዛኛውን የሚያረካ ነበር። ይህ የሆነበት ዋነኛ ምክንያት ከተለያዩ መምሪያዎች በተውጣጡ ኃላፊዎች ምደባው በመካሄዱ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ፅ/ቤቱ ከተነሳለት ዓላማ ጋር በሚጋጭ መልኩ የምደባ ስርዓቱ ሲካሄድ እያስተዋልን ነው። የዚህ ዋነኛ መንስኤ ደግሞ የፌዴራል ኮምዩኒከተሮች ምደባ ለአንድ ዳይሬክቶሬት ብቻ በመሰጠቱና ሌሎች በፅ/ቤቱ የሚገኙ ዳይሬክቶሬቶች በዚህ የአመዳደብ ስርዓት ላይ ምንም ዓይነት ስልጣን ስለሌላቸው ነው። ይሄ ስል ግን ሌሎች ዳይሬክቶሬቶች ስራ የላቸውም እያልኩ እንዳይደለሁ ግንዛቤ ይያዝልኝ። በፅ/ቤቱ ውስጥ ስላለሁ ሌሎች ዳይሬክቶሬቶች የበኩላቸውን እየተወጡ እንደሆኑ አውቃለሁና። ኮምዩኒኬተሮች በኃላፊነት ደረጃ ሲመደቡ አንድ ዳይሬክቶሬት ብቻ ለምኒስትሩ የውሳኔ ሃሳብ ማቅረብ አይገባውም። ኮምዩኒኬተሮች የመመደብ ስራ የአገሪቷ ገፅታ ከመገንባት አንፃር ትልቅ አገራዊ ፋይዳ ያለው ስራ በመሆኑ በምክረ-ሃሳቡ ላይ ወሳኝ የስራ ሂደት የሚባሉ ዳይሬክቶሬቶች የራሳቸው ሚና ሊኖራቸው ይገባል።

ኮምዩኒኬተሮች እንዲመደቡ የማድረግ ስልጣን ለአንድ ዳይሬክቶሬት መሰጠቱ ባልከፋ ነበር። በዚህ ዳይሬክቶሬት እየተሰራ ያለውን ስራ አገሪቷ ከያዘችው ራዕይ አንፃር ቃኝቶ ኮምዩኒኬተሮች የመመደብ ጉዳይ ላይ አሁን ከምፅፈው በላይ ሰፊ ክፍተት ይታይበታል።

ይህን ትልቅ ስራ የሚያከናውነው ዳይሬክቶሬት፣ ለአገሪቷ ገፅታ ግንባታ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ዳይሬክቶሬት የሚያከናውናቸው ስራዎች ከአድልዎ የፀዳ፣ ዕሕፈት ቤቱ የያዘውን ራዕይ ለማሳካት ቅድሚያ የሚሰጥ፣ ከበላይ አመራር የሚሰጡ አቅጣጫዎች ሳያሸራርፍ የሚተገብር መሆን ይጠበቅበታል።

ይሁን እንጂ ዳይሬክቶሬቱ በህዝብ ግንኙነት አመዳደብ ላይ ኃላፊነቱን በሚገባ ተውጥቷል የሚል ግምገማ የለኝም። ምደባ ሲካሄድ ግልጽነት በጎደለውና ከጥቅም ሰንሰለት ጋር የተያያዘ ነው። በዚህ የጥቅም ሰንሰለት ከዳይሬክቶሬቱ ጋር ንክኪ ያለው ሰው ግልፅ ባልሆነ መስፈርት የሚሾምበት፣ ሰንሰለቷ ጋር አልጠጋም ያለ የሚገለልበት ሁኔታ በሰፊው እየታየ ነው ያለው። ዳይሬክቶሬቱ እየተመራ ያለው መንግስት ባስቀመጣቸው ፖሊሲና ስትራቴጂ እንዲሁም እነዚህን ስትራቴጂዎች በቆራጥነት እና በሐቀኝነት በመተግበር ሳይሆን በአድርባይነት ነው።

የአመለካከት ችግሩ በዘርፉ የሚሰማራው ባለሙያን በስፋት የሚመለከት ነው። የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ይህንን ዘርፍ ይበልጥ ለማሳደግ እና በዕውቀት፣ በክህሎት እንዲሁም በአመለካከት የተገራ ዜጋ ለማፍራት በሚፈለገው መልኩ ባይሆንም በተወሰነ መልኩ ደፋ ቀና ሲል ይስተዋላል። በዚህ ፅ/ቤት ያለውን መዋቅር ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ሲታይ በተነፃፃሪ ሊያሰራ የሚችል ነው። መዋቅሩ የሚያበረታታ ቢሆንም በመዋቅሩ በወሳኝ የስራ ሂደት የሚመደቡ ዳይሬክተሮች ግን ከሞላ ጎደል በእውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት ደረጃ ለፅ/ቤቱ ይመጥናሉ የሚል አመለካከት የለኝም። ጥሩ መዋቅር በተዛነፈና አደገኛ አመለካከት ያለው አድርባይ አመራር ከታጀበ መጨረሻው ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል።

በአሁኑ ጊዜ በኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ጠንካራና እውነትን አፍርጦ የሚያሳይ ብሎም የሚያስተምር ግምገማ ከጠፋ ሰነባብተዋል። የኮሪደር ወሬ እና ሐሜት በእጅጉ ተስፋፍቷል። ጠንካራ የሚባሉ ኮመዩኒኬተሮች ባለው የአድልዎ አሰራር ተስፋ ቆርጠው ዝምታን መርጠዋል። አድርባይነት የበላይነቱን ይዘዋል። በፅ/ቤቱ የሚገመግም፣ ገምግሞ የሚያስተካክል ሰው ማግኘት ወደማይቻልበት ሁኔታ ደርሰዋል። አንዳንድ ደፍረው የሚገመግሙ ሰዎችም ጥርስ ውስጥ ገብተው የሚገባቸውን ሲያጡ ይስተዋላል። ፅ/ቤቱ አድርባይ የሆነ ሰው የሚጠቀምበት ችግሮች ለማስተካከል ሙከራ የሚያደርግ የሚጎዳበት ሆኖ ነፋስ እንደነካው ዛፍ ወደዚህና ወደዛ እየዋለለ ይገኛል።

“ገፅታ ገንቢው” ዳይሬክቶሬት ሕገ-ወጥ ስራውን በዚህ ቢያበቃ መልካም ነበር። ለመፃፍ በሚከብድ መልኩ በተለያዩ አግባብ ያልሆኑ መስፈርቶች / መስፈርቶቹ ዛሬም ነገም ለአገራችን የማይጠቅሙ ናቸው/ በጥቅም የተሳሰሩና ግንኙነት ያላቸው ሰዎች በህዝብ ግንኙነት መስክ በኃላፊነት ደረጃ በተመረጡ መስሪያ ቤቶች ግልፅ ባልሆነ አሰራር እንዲሾሙ ማድረጉ ሳይበቃ፣ ምናልባት በአመለካከት ከዳይሬክቶሬቱ የሚጋሩት ሌሎች ሰዎች በባለሙያነት ደረጃ በየመስሪያ ቤቱ መመደብ ጀምሯል። በኃላፊዎች አመዳደብ እና በባለሙያዎች አመዳደብ ያለውን ልዩነት ኃላፊዎች ሲመደቡ በዳይሬክቶሬቱ ምክረ-ሃሳብ ቢሆንም በሚኒስትሮቹ ዕውቅና እና ትእዛዝ ነው። በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ ወደ ተለያዩ መስሪያቤቶች እየገቡ ያሉ ባለሙያዎች ግን ከፅ/ቤቱ ኃላፊዎች ዕውቅና እና ትእዛዝ ውጪ በዳይሬክቶሬቱ ሕጋዊ ያልሆነ ስልጣን ነው። ይሄን ሕገ-ወጥ ስራ እየተሰራ ያለው በዳይሬክቶሬቱ ብቻ ሳይሆን በዳይሬክቶሬቱ እርዳታና ሙሉ ድጋፍ በህዝብ ግንኙነት ኃላፊነት ከተመደቡ ክሊኮች ጋር በመሆን ነው።

የአገሪቷ ገፅታ በሚፈለገው መልኩ ለመገንባት የተቋቋመ ተቋም እንደዚህ ዓይነት ያልተገባ ስራ ሲሰራ እስካሁን ድረስ ለምን ዝም አለ የሚል ጥያቄ ሊመለስ የሚገባው ነው። በርካታ ባለሙያዎች ከኮምዩኒኬሽን ፅ/ቤት ዕውቅና ውጪ በዳይሬክቶሬቱ አደራዳሪነት ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ እንዲመደቡ ተደርጓል። የፌዴራል መስሪያቤቶች የኮምዩኒኬሽን ባለሙያ እንዲሟላላቸው ሲጠይቁ፣ የኮምዩኒኬሽን ፅ/ቤት ኃላፊዎች እንጂ ባለሙያዎች የመመደብ ስልጣን የለውም። እንደ ዳይሬክቶሬት ግን ሰዎች ልንጠቁማችሁ እንችላለን በማለት በየመስሪያቤቱ የቅርብ ዘመዶቻቸውና ጓደኞቻቸው እያስገቡ ይገኛሉ። ከባለሙያዎቹ የሚያገኟቸውን ጥቅማ ጥቅም ብዙዎቻችን እናውቀዋለን። የኮምዩኒኬሽን ባለሙያዎች አንድም በኮምዩኒኬሽን ፅ/ቤት አሊያም በውድድር መመደብ ሲገባቸው በሕገ-ወጥ መንገድ ብዛት ያላቸው ጅምር ክሊኮች በዳይሬክቶሬቱ ደላላነት ተመድበዋል።

ሰሞኑን የኮምዩኒኬሽን ፅ/ቤት የኮምዩኒኬሽን ስልጠና ያላገኙ ባለሙያዎች በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ እያሰለጠነ ይገኛል። እንደማንኛውም ዜጋ ተወዳድረው ወይም በኮምዩኒኬሽን ፅ/ቤት ተመድበው በየመስሪያቤቱ የገቡ ዜጎች እንዳሉ ሆኖ፣ በገፅታ ገንቢው ዳይሬክቶሬት ደላላነት እና ተዘዋዋሪ አመራር የተመደቡ ባለሙያዎች በዚህ ስልጠና በቀጥታ እንዲሳተፉ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። በተወሰነ መልኩም ተሳክቶላቸዋል። እኔ እና የቅርብ ጓደኞቼ ወደ ስምንት የሚሆኑ ሰዎች በገፅታ ገንቢው ዳይሬክቶሬት ቀጭን ትእዛዝ በዚህ ስልጠና እየተሳተፉ መሆናቸውን እናውቃለን።

    የኮምዩኒኬሽን ፅ/ቤት ህብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ እየሰራቸው ያሉ ስራዎች አበረታታች ውጤት ማምጣታቸው የማይካድ ሐቅ ነው። ይሁን እንጂ በፅ/ቤቱ ብሎም በሌሎች ፌዴራል መስሪያቤቶች መልካም አስተዳደር እንዳይሰፍን፣ ሙስና እንዲበረታታ፣ ያለአግባብ የእርከን ዕድገት እንዲኖር እና የአመራር ሰንሰለት እንዳይከበር የራሳቸው ድብቅ ዓላማ ይዘው በግላጭ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ግለሰቦች አደብ ይገዙ ዘንድ ኃላፊነቱን እንዲወጣ እላለሁ። “ገፅታ ገንቢ” ዳይሬክቶሬት ጥላሸት ቀቢ ሲሆን ማየት አሳሳቢ ነውና!!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1296 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1046 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us