አንዳንድ ነጥቦች ስለ ቼስ

Wednesday, 10 June 2015 12:15

- ቀዝቃዛው ጦርነት በቼስ ዓለም

     የዘር፣ የሃይማኖት እንዲሁም የጾታ ልዩነት ሳያደርግ የቼሱን ዓለም አስተባብሮ አንድ ያደረገው የዓለም ቼስ ፌዴሬሽን (ፊዴ) ለሐምሌ 20 ቀን 1924 እ.ኤ.አ. ፈረንሳይ ውስጥ በፓሪስ ከተማ ተመሰረተ፡፡ በዓለም አቀፉም ኦሎምፒክ ኮሚቴ (አይ ኦ ሲ) በ1999 ሰኔ ወር ላይ እውቅና አግኝቷል፡፡
      ከዓለማችን ኃያል የስፖርት ፌዴሬሽኖች አንዱ የሆነው ይህ ተቋም በስሩ ለሚካሄዱ ውድድሮች (ቼስ ኦሎምፒያድ፣ የዓለም ቼስ ሻምፒዮና፣ አህጉራዊ ውድድር…) ሕጎችንና ደንቦችን ያወጣል፣ የቼስ ማዕረጎችን (ግራንድ ማስተር፣ ኢንተርናሽናል ማስተር፣ ፊዴ ማስተር፣ ኢንተርናሽናል አርቢትር...) ይሰጣል፡፡
     ዛሬ 181 አባል አገራት ያሉት የአለም ቼስ ፌዴሬሽን በ 91 ዓመት ታሪኩ 6 ፕሬዚዳንቶች ተፈራርቀው መርተውታል፡፡ የደቹ የህግ ሰው ዲፕሎማት እንዲሁም ኢንተርናሸናል የቼስ ዳኛ የነበሩት አሌክሳንደር  ሩብ ከ 1924-1949 ለ 25 አመታት የመጀመሪያው የ 'ፊዴ' ፕሬዚዳንት በመሆን አገልግለዋል፡፡በሙያቸው የህግ ሰው የነበሩት በወቅቱ የሲዊዲን ቼስ ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት ፎክ ሮጋርድ ለ 21 አመታት (1949-1970 ) የፊዴ ሁለተኛው ፕሬዚዳንት ሆነው ሲያገለግሉ፤ አያሌ አለም አቀፍ ወድድሮችን እንዳሸነፈ የሚነገርለት፣ የማቲማቲክስና ሜካኒክስ ፕሮፌሰር፣ አሌክሳንደር አሊኬንን በማሸነፍ 5ኛው የአለም ቼስ ሻምፒዮና መሆን የቻለው ማክስ ኢዊ ከ 1970-1979 እ ኤ አ 3ኛው የአለም ቼስ ፌዴሬሸን ፕሬዚዳንት በመሆን አገልግሏል፡፡
     እንዲህ እንዲያ እያለ በ 1995 ከፊሊንፒንሱ ካምፖማነስ በትረ ሰልጣኑን የተረከቡት 6ኛው የአለም ቼስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት - ኪርሳን ሉሚዥኖቭ ፊዴ ን ማስተዳደር ከጀመሩ ድፍን ሃያ አመታቸው፡፡
ዛሬ የቼሱ አለም በሁለት ተከፍሎ ከህይወት በመለስ ዋጋ የሚያስከፍል ጠንካራ ትግል ያካሂዳል፡፡ አንዱ ሌላውን  ለመጣል - ቀዝቃዛው ጦርነት፡፡ በቢሊየነሩ፣ ፖለቲከኛው፣ የሩሲያው ዲፕሎማት አና የካልሚኪያው ሪፑብሊክ ፕሬዚዳንት እንዲሁም የወቅቱ የፊዴ ፕሬዚዳንት የሚመራው ቡድን በአንድ ወገን.....ለ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መፈጠር ጉልህ አሰተዋጽኦ ያደረገው፣ ከአይ ቢ ኤም - ዲፕ ብሉ መሽን ጋር ሰብአዊ ፍጡርን በመወከል ውድድር ያደረገው፣ 13ኛው የአለም ቼስ ሻምፒዮና፣ በምዕራባውያን የሚደገፈው፣ ሩሲያን ለመምራት ከቭላድሚር ፑቲን ጋር ለፕሬዚዳንትነት የተወዳደረው፣ ፖለቲከኛው በዚህም ሳቢያ ከአገሩ ርቆ በስደት ዱባይ እንደሚኖር የሚነገርለት፣ የባኩው ተወላጅ ሩሲያዊው ግራንድ ማስተር ጌሪ ካስፕሩቭ በሌላው ወገን ...
     የቼሱን አለም ለመምራት የራሳቸውን ሰትራቴጂ ነድፈው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ተልዕኳቸውን የሚያሰፈጽምላቸው አጋር ፍለጋ ላይ ታች ይላሉ፡፡ ከሁሉም በላይ የአፍሪካ አህጉር የእነዚህ ኃይሎች ትኩረት አርፎበታል፡፡
     የአለም ቼስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የስራ ዘመን አራት አመት ሆኖ ምርጫ በየአራት አመቱ ይካሄዳል፡፡ ለአራት ተከታይ የምርጫ ዘመናት ከበድ ያለ ተግዳሮት ያልገጠማቸው ቱጃሩ የፊዴ ፕሬዚዳንት ኪርሳን የአምስተኛውን ጊዜ የምርጫ ዘመን በቀላሉ እንደማይወጡት ከወቅቱ ባላንጣቸው12ኛው የአለም ቼስ ሻምፒዮና ግራንድ ማስተር አናቶሊ ካርፖቭ ጠንካራ ዘመቻ መረዳት ስለቻሉ እንቅስቃሴውን ለማክሸፍ የሩሲያ መንግስት ድጋፍ አስፈልጓቸዋል፡፡ ሩሲያም ኤምባሲዎችን የዘመቻው አካል አደረገቻቸው፡፡
     በዚህም አላበቃም በ2010 ሩሲያ-ካንቲማንሲስክ ለተካሄደው 39ኛው ቼስ ኦሎምፒያድ አዘጋጇ ሩሲያ
የሁሉንም ተሳታፊ አገራት ከፊል የትራንሰፖርት ወጪ ለመሸፈን በአራት አገራት (ፕራግ፣ ሮም፣ ፍራንክፈርት እና ዱባይ ) ቻርተር አውሮፕላን አዘጋጀች፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ አገራት
ሙሉ ወጪያቸውን ሸፈነች፡፡ ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ.....
     እናም ኪርሳን አላፈሩም ገንዘባቸው ድል አደረገ፡፡ እርሳቸውም የምርጫውን ሂደት በሚገባ ሰለተገነዘቡ በወደቀው ባላንጣቸው ላይ ከመዘባበት ይልቅ አናቶሊ ካርፖቭን እጃቸውን ዘርግተው ተቀበሉት፡፡ ረዳታቸውም አድርገው ኃላፊነትን ሰጡት፡፡ (እኛ ኢትዮጵያውያን በዘመነ መሳፍንት ያደረግነውን ርሳቸው በ21ኛው ክፍለ ዘመን ...)
     ነጋም- መሸም ወራቶች አለፉ፡፡ ኪርሳንም ሆኑ ተከታዮቻቸው የቼሱን አለም ረሱት፡፡ እንደውም ጊዜ ስለተረፋቸውም ይመሰላል አለምን ያነጋገረ ድርጊት ኪርሳን ፈጸሙ፡፡ በቱኒስያ የተለኮሰው አረብ አብዮት አዌክኒንግ ይለበልባቸው የጀመሩትን ኮሎኔል አል  ቃዳፊን ለመጠየቅ ኪርሳን ምሽጋቸው ድረስ በመሔድ የቼስ ገበታ አቅርበው ይጫወቱ-ይወየዩ ባይታወቅም የተቀረጸው ፊልም ለዕይታ  በቃ፡፡ 2014- የኪርሳን ዘመን ያበቃለታል ተብሎ ቅድመ- ትንበያ የተነገረለት፦ ጌሪ ካስፕሩቭ በካስፓሮቭ፤ ፋውንዴሽን እና በምዕራባውያን ድጋፍ በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር በጀት መድቦ ተንቀሳቀሰ፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አገራት ጉብኝት አደረገ፡፡ የሚመስጡ ቃላቶችን አሰደመጠ፣ ለእርዳታም እጁን ዘረጋ፡፡
     እንደሚገባንም ባይሆን በጥረታችን ልክ የተመጠነ ድጋፍ አገኘን፡፡ በኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን አቅም የማይታሰበውን ወጪ ሸፍኖ ኖርዌይ-ትሮምሶ ለተካሔደው የ41ኛው ቼስ ኦሎምፒያድ ታዳሚ ለመሆን አበቃን፡፡ ዕርዳታውንም ለሚፈልጉ አገራት እንደየመሻታቸው አደረገ፡፡ በዚህን ጊዜ የኪርሳን ቀኝ እጅ የነበረው የፊዴ ዋና ጸሐፊ ሊዮንግ “ይሄ ነው ማምለጥ...” ብሎ ከካስፕሩቭ ጋር መሆኑን በይፋ ዐወጀ፡፡
     የኪርሳንንም ሚስጥር አወጣ፡፡ የፊዴ ኮንግረስ ስብሰባ ደረሰ፡፡ ምርጫውም በወጣለት መርሐ ግብር መሰረት ተካሄደ፡፡ በማይታመን ሁኔታ የኪርሳን ማሸነፍ ታወጀ፡፡ በቀዝቃዛው የ41ኛው ኦሊምፒያድ መዝጊያ ስነ ስርዐት ላይ ኪርሳን እየተዘባነኑ “የአለም ቼስ ፌዴሬሸን ጠላት፣ የቭላድሚር ፑቲን ጠላት.... እያሉ ካስፓሮቭን ወረፉ፡፡
     የቼሱ አለም በሁለት ጎራ መከፈል - ቀዝቃዛው ጦርነት እንደ ኢትዮ ላሉ አገራት ጥቅማቸው ነው፡፡ ዛሬ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር አውጥተን ወደ አውሮፓ፣ እስያ...ተጉዘን መወዳደር ይቅርና የልዑካን ቡድኑን አበል ለመክፈል ዐቅማችን ተፈትኗል፡፡ እንዲህ ዐይነቱስ አጋጣሚ ይዘልቅ ይሆን?... ለዚህም ነው ብልጦቹ አገራት ነገን ባለማመን ዛሬን ሙጥኝ ብለው በሚሊዮኖች ብር ሊገመቱ የሚችሉ የቼስ ቦርዶች በዕርዳታ እየተቀበሉ ያሉት (በቅርቡ ኬንያ ያገኘችውን 5000 የቼስ ቦርዶች ይመለከቷል) እኛስ ምን አተርፍን?...ለምን?...
                                                                                       ቸር እንሰንብት
                                                                                                               አበባው ከበደ
                                                                                                     የዓለም ቼስ ፌዴሬሽን ኢንስትራክተ

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1169 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1019 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us