ምርጫ እና መገናኛ ብዙሃን

Wednesday, 20 May 2015 12:30

በይርጋ አበበ

 

 

በአንድ ወቅት የአንድ መጽሄት አዘጋጅ “ምርጫ መጣ ፕሬስ ውጣ” ሲል መንግስት በመገናኛ ብዙሃን ላይ የሚያደርገውን ዘርፈ ብዙ ወከባ እና የማሸሽ ስልት አስነብቦ ነበር። በወቅቱ ጋዜጠኛው በተጠቀሰው ርዕስ ላይ ባሰፈረው ነጥብ ሲገልጽ መንግስት በምርጫ ሰሞን ችግሩን የሚጠቁምበትን ጋዜጣ እና ጋዜጠኛ ስለማይፈልግ በተለያየ ምክንያት ከገበያ ውጭ ማድረግ እንደሚወድ ካለፉት ጊዜያት ተሞክሮዎቹ በመነሳት አስቀምጧል።

የፕሬስ ተልዕኮ በአንዲት አገር ያለውን መረጃ በሚዛናዊነትና በገለልተኝነት ስሜት የጋዜጠኝነት ሙያን በመጠቀም ብቻ ለሕዝቡ የማቅረብ ተልዕኮን አንግቦ የሚንቀሳቀስ ምናልባትም መወገን በሚያስፈልገው ጊዜ ከህዝብ ጥቅሞችና ከብዙሃን ስሜቶች ጋር ብቻ የሚወግን ሙያ መሆኑን ቀደም ሲል ይታተም የነበረው አዲስ ጉዳይ መጽሔት በሚያዝያ 2005 እትሙ አስነብቦ ነበር።

ለመሆኑ በገበያው ላይ ያሉ የነጻው ፕሬስ መገናኛ ብዙሃን እና የመንግስት መገናኛ ብዙሃን በዘገባዎቻቸው ላይ የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች ወገንተኝነታቸው ለማን ያደላ ነው? ኃላፊነታቸውንስ እንዴት እየተወጡ ነው? የሚሉትንና ተያያዥ ነጥቦችን አንስተን የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር ከዚህ በታች ያለውን ጽሁፍ አዘጋጅተናል።

የመገናኛ ብዙሃን በምርጫ ላይ ያላቸው ሚና

ካይሮ ኢንስቲትዩት ፎር ሂውማን ራይትስ የተባለ ድርጅት ባቀረበው ጥናት “Discussion of the media’s functions within electoral context, often focuses on their ‘watchdog’ role” ይላል። የጥናቱ ውጤት እንደሚያሳየው በምርጫ ጉዳዮች ላይ የመገናኛ ብዙሃን አገልግሎት ትኩረት የሚያጠነጥነው ነቅቶ የመጠበቅ ሚና እንደሚኖራቸው ነው። በዚህ መሰረት አምስተኛውን አገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ በተመለከተ መገናኛ ብዙሃን እየተጫወቱ ያለውን ሚና ስንመለከት ነቅቶ የመጠበቅ ሚናቸውን ያልተወጡ መሆናቸውን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይናገራሉ።

የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት መጋቢት ላይ ታትሞ ከነበረው ዘመን መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ሚዲያ ተዘግቷል። በሚዲያ ነው ህዝብን የምታገኘው። ሚዲያ አራተኛው የመንግስት አካል ነው የሚባለው” ካሉ በኋላ አያይዘው በተለይ ከሬዲዮ ፋና ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ የተቀረጸው ድምጽ ከጣቢያው መጥፋቱን ከሬዲዮ ፋና እንደተነገራቸው ገልጸዋል። ከሬዲዮ ፋና ስቱዲዮ ጠፋ የተባለው የኢንጅነር ይልቃል ቃለ ምልልስ ግን በኢሳት ቴሌቪዥን ለሁለት ሰዓታት መተላለፉን ተናግረው ነበር። ይህ ክስተት ደግሞ የሚዲያ አፈና እንደሆነ እንደሚያምኑ ተናግረዋል። ሊቀመንበሩ አያይዘውም “ሚዲያው እኛን አይፈልግም። አንተም እንኳ (የዘመን መጽሔት ዘጋቢውን) ስትመጣ ሰማያዊ በተመሰረተ በሶስት ዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። መቶ ሚሊዮን ህዝብ ባለበት፣ 547 የምርጫ ወረዳ ባለበትና የኢትዮጵያ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ዝብርቅርቅ ባለበት ሁኔታ ፓርቲዎች መራጩን ለመድረስ የሚዲያ አስፈላጊነቱ ይታወቃል። ስለዚህ ከሚዲያ አስፈላጊነት አንጻር ስትመዝነው ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ሚዲያ የለም ዝግ ነው ማለት ይቻላል” ብለው ነበር።

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በበኩሉ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና ዛሚ ኤፍ ኤም ሬዲዮ የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክቴን ሳንሱር አድርገውብኛል በማለት ራሱን ከነጻ የአየር ሰዓት የምርጫ ቅስቀሳ ማግለሉን ሰንደቅ ጋዜጣ መዘገቡ ይታወሳል።

በኢህአዴግ ምክር ቤት ጽ/ቤት የህዝብ እና የግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደስታ ተስፋው በበበኩላቸው “መገናኛ ብዙሃን ስራቸውን የሚሰሩት በኃላፊነት ነው። የሰሩት ስራ ተጨባጭ ነው አይደለም ነው ጥያቄው። በእኛ በኩል ግን (ኢህአዴግን) መገናኛ ብዙሃኑ ሁሉንም ያማከለ እንደሆነ ባካሄድናቸው የጋራ ምክር ቤትም ሆነ የፓናል ውይይቶቻችን ያረጋገጥነው ይህንኑ ነው” ሲሉ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ለሁሉም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች በእኩልነት እያስተናገዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ሚና

በአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ የአፍሪካ ኃላፊ ሆና ትሰራ የነበረችዋ ጀኔፈር ፓርሜላ የተባለች ባለሙያ በ1991 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ለጋዜጠኞች ስልጠና ሰጥታ ነበር። በወቅቱ ስልጠናውን የተካፈሉት ባለሙያዎች የመጡበትን መገናኛ ብዙሃን ሲናገሩ የመንግስት እና የግል እያሉ መግለጻቸው ባለሙያዋን አስገርሟት እንደነበረ እና “እንዴት በአንድ አገር ውስጥ የግል እና የመንግስት የሚባል ሚዲያ ሊኖር ይችላል” በማለት እንደተደነቀች ቀደም ሲል ይታተም የነበረ አንድ መጽሄት አስነብቧል። ፓርሜሌ የቱንም ያህል ብትገረመም በአገራችን ያለው እውነታ ግን የመንግስት እና የግል ተብሎ የተከፈለ በአናቱም በየፊናቸው ጽንፍ የያዙ የመገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች መኖራቸውን ነው።

መገናኛ ብዙሃኑ በሁለት ጎራ ተከፍለው እንካ ስላንትያ መግጠም አለባቸው ተብሎ ባይታመንም ለእንካ ስላንትያው መፈጠርም ሆነ መቀረፍ መንግስት እና የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ሊወስዱት የሚገባ ኃላፊነት መኖሩን ቀደም ሲል የገለጽኩት የካይሮ ኢንስቲትዩሽን ኦፍ ሂውማን ራይትስ ጥናት ይገልጻል። በ2012 የወጣው የተቋሙ የጥናት ሪፖርት በሶስተኛ እትሙ “The task of the media, especially national media outlets, is not and should not be to function as a mouthpiece for any government body or particular candidate. Its basic role is to enlighten and educate the public and act as a neutral, objective platform for the free debate of all points of view.” ወይም በአማርኛ “የመገናኛ ብዙሃን በተለይም ብሔራዊ መገናኛ ብዙሃን ውጤቶች ለየትኛውም የመንግስት አካል ወይም ለተለየ እጩ ጥብቅና መቆም የለባቸውም። የተቋማቱ ተቀዳሚ ሚናቸው ህዝቡን የማስገንዘብና የማስተማር ሚናቸውን ገለልተኛ በመሆን ነጻ የውይይትና የክርክር መድረክ የመፍጠር ሚና ሊወጡ ይገባቸዋል” ሲል የመገናኛ ብዙሃንን በተለይም የብሔራዊ መገናኛ ብዙሃንን ሚና እና ኃላፊነት አስቀምጧል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን በጀት የሚመደብላቸውም ሆነ የድርጅቶቹ ኃላፊዎች የሚሾሙት በገዥው ፓርቲ በጎ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ግልጽ ነው። በዚህም በተደጋጋሚ ጊዜ በተለይም የምርጫ ወቅት በሚቃረብበት ወቅት ከመንግስት ተቃራኒ ጎራ የተሰለፉ የፖለቲካ ድርጅቶችን የሚተቹ ዘገባዎችን ሲያስነብቡና ሲያሳዩ ይስተዋላል እየተባሉ ይተቻሉ። በዘንድሮው ምርጫም በአንዳንድ የተቃውሞው ጎራ ፓርቲዎች ላይ በተለይም በሰማያዊ ፓርቲ ላይ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን የሚያቀርቧቸው ዘገባዎች ሚዛናዊነት የጎደላቸው ናቸው ሲሉ አስተያየታቸውን ለሰንደቅ የሰጡ ሰዎች ተናግረዋል። አስተያየት ሰጪዎቹ ለንግግራቸው ማጠንከሪያ የሚያቀርቧቸው ሁለት መሰረታዊ ሁነቶችን ሲያነሱ በቅርቡ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የቴሌቪዥን ስርጭት ላይ የቀረበው “የተዘጋው መንገድ” የሚል ዘጋቢ ፊልም እና ሚያዝያ 29 ቀን 2007 ዓ.ም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ አጀንዳ አምድ ላይ የቀረበው “የነውጥ መንገድን የሚያማትረው ሰማያዊ ፓርቲ” የሚሉ ዘገባዎችን ነው።

በተጠቀሱት የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ላይ “ከሁለቱ ርዕሶች በተጨማሪ በተደጋጋሚ የፓርቲውን ስም የሚያጠለሹ ዘገባዎች እየቀረቡ ነው። ድርጅቶቹ ከዚህ ተግባራቸው የማይታቀቡ ከሆነም ወደ ፍርድ ቤት እንሄዳለን” ሲል ሰማያዊ ፓርቲ መግለጫ ማውጣቱም የሚታወስ ነው።

የግል መገናኛ ብዙሃን ሚና

በዚህ ዘመን የነጻው ፕሬስ ፈተናዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ አስጊ ደረጃ ላይ የደረሱበት ዘመን ነው ብለው የሚናገሩ ጸሐፊያንና ምሁራን አሉ። በተለይ በአንድ ወቅት ከአንድ የአገሪቱ መጽሔት ጋር ቃለ ምልልስ አድርገው የነበሩት ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ ወቅቱ ለነጻው ፕሬስ ከባድ መሆኑን ተናግረው ነበር። ያም ሆኖ በዚህ ወቅት ለንባብ ከሚበቁት ውስን ጋዜጦችና መጽሔቶች በተጨማሪ ከገዥው ፓርቲ ብዙም የተለየ ፖሊሲ የሌላቸውና ብሎም ከመዝናኛነት ያልዘለለ ሚና ያላቸው ውስን የግል ማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች አሉ።

በእነዚህ የነጻው ፕሬስ (የግል መገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች) በኩል ለአምስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ የተደረገው ሙያዊ ኃላፊነት ምን ያህል ስኬታማ ነው? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ጥናቶች የሚያስፈልጉት ጉዳይ ቢሆንም አስተያየታቸውን ከሰጡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች መልስ ተነስተን ለጥያቄው መልስ ለመስጠት እንሞክራለን።

ታላቁ የአገሪቱ ህግ “ህገ መንግስቱ” የሰጣቸውን መብት ተጠቅመው ለአገርና ለህዝብ ይበጃል ብለው ያመኑትን ሃሳብ ለንባብ እያቀረቡ ካሉ የነጻው ፕሬስ ውጤቶች አንዱ ሰንደቅ ጋዜጣ ነው። ሰንደቅ ጋዜጣ ምርጫ 2007 ለመካሄድ ከታሰበበት ማለትም ከመራጮች ምዝገባ በፊት ጀምሮ መጠነ ሰፊ ዘገባ ሲያቀርብ መቆየቱ ይታወሳል። በተለይም “የኢትዮጵያ ህዝብ ግብር እየከፈለ የሚያስተዳድራቸው የመንግስት መገናኛ ብዙሃን በራቸውን እስከወዲያኛው ወለል አድርገው የሚከፍቱት ለአለቃቸው ለገዥው ፓርቲ እንጅ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች አይደለም። በዚህም ድምፃችንን የምናሰማበት መድረክ አጥተናል” ብለው ቅሬታ ለሚያቀርቡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሃሳባቸውን እንዲገልጹ በሩን ከመክፈቱም በዘለለ ገዥው ፓርቲም እየቀረበበት ያለውን ትችት መልስ እንዲሰጥም ሁኔታዎችን ሲያመቻች ቆይቷል።

የምርጫ ሰሞን ዘገባዎች

በምርጫ ሰሞን የሚታተሙ የነጻው ፕሬስ የህትመት ውጤቶችም ሆኑ የመንግስትን አቋም ደግፈው የሚተላለፉ የመገናኛ ብዙሃን ውጤቶች (ቴሌቪዥን፣ ሬዲዮ እና ጋዜጦች እንዲሁም የድረ ገጽ ጋዜጦች) በተከታታዮቻቸው (ኦዲየንስ) ሞገስን ለማግኘትና ተፈላጊ ለመሆን የተለየ ጥረት ሲያደርጉ ይታያሉ።

በግለሰቦች ገንዘብ የሚተዳደሩት የነጻው ፕሬስ የህትመት ውጤቶች ጋዜጣቸውም ሆነ መጽሔታቸው እንዲሸጥ “ገበያ መር” ጽሁፎችን ይዘው ይወጣሉ። እንደዚህ አይነት የህትመት ውጤቶች በውጭው ዓለም “የሎው ጆርናሊስትስ ወይም ሰንሴሽናል ጆርናሊስትስ” የሚል ስያሜ ይሰጣቸዋል። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በማደግ ላይ ያሉ እና ዴሞክራሲያዊ መንግስት የሌላቸው አገሮች በሰንሴሽናል ጋዜጠኞች ላይ ፊታቸውን ያጠቁራሉ።

በህዝብ ግብር የሚተዳደሩትና በመንግስት ቁጥጥር ስር የዋሉት የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ደግሞ በብዛት መንግስት የሰራቸውን መሰረተ ልማቶች በማሳየትና አልፎ አልፎም መንግስትን የሚቀናቀኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የሚያንኳስሱ ዘገባዎችን ሲያቀርቡ ይታያሉ። የመንግስት መገናኛ ብዙሃን የምርጫ ሰሞን ዘገባዎች ዓላማቸው አንድም መንግስት የሰራቸውን የልማት ስራዎች ለህዝቡ በማሳየት በምርጫው ወቅት የመራጩን ልብ ለማግኘት ሲሆን ወዲህ ደግሞ ተቃዋሚዎች በመራጩ ህዝብ ቅቡልነት እንዲያጡ ያነጣጠረ መሆኑን ነው አስተያየታቸውን ለሰነደቅ የሰጡት ሰዎች የተናገሩት።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1213 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1026 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us