የዓድዋ ድልና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን

Wednesday, 04 March 2015 13:49

በዲ/ን ተረፈ ወርቁ

 

የዓድዋ ጦርነት ከመካኼዱ አምስት ዓመት በፊት አለቃ ለማ ኃይሉ በአዲስ አበባ ሥላሴ ቤ/ን የሐምሌ ሚካኤል ዕለት፣ የሚከተለውን ትንቢታዊ ቅኔ መቀኘታቸውን ልጃቸው መንግሥቱ ለማ፣ “መጽሐፈ ትዝታ ዘአለቃ ለማ ኃይሉ ወልደ ታሪክ” በሚለው መጽሐፋቸው ገልጸውታል። ቅኔው እነሆ፡-

ምኒልክ ግበር ላዕለ ሮምያ/ሮማ መጠነ እዴከ ትክል፣

አምጣነ ለአጺድ በጽሐ ማእረራ ወመዋዕሊሃ ለኃጉል፣

ዓዲ ተዘከር ውስተ ወንጌል፣

ላዕለ ሮምያ በለስ ኢሀሎ አስካል፣

ከመ ይቤ ወልደ ያሬድ ቃል።'

ትርጉም፡- ምኒልክ በሮማ ላይ እጅህ እንደቻለ መጠን አድርግ፣

መከሯ ለመታጨድ፣ ቀኗም ለጥፋት ቀርቧልና።

ዳግመኛ በወንጌል ያለውን አስብ፣

በሮምያ/በበለስ ላይ ፍሬ የለም እንዳለ ወልደ ያሬድ/ቃል(ወልድ)። ብዬ ፹፫ ተቀኘሁ። ምኒልክ በቤተስኪያን የሉም ይኸ ሲባል። ይኸ ጥንቆላ ነው፤ ያድዋ ጦርነት ሳይደረግ ነው። ኸጣልያን ጋር ስምም ናቸውያን ጊዜ አጤ ምኒልክ። አለቃ ወልድ ያሬድ 'መልካም መልካም!'አሉና፣ እሑድን ዋልነ። ሰኞ ጉባዔ አለ፤ አለቃ ተጠምቆ ናቸው እሚያኼዱ። አለቃ ወልደ ያሬድ እርሳቸው እልፍኝ አጠገብ ቤት ሰጥተውናል። እርሳቸው መጥተው ይቀመጣሉ ኸጉባዔ ለመስማት።

የኔታ ተጠምቆ'

አቤት!'

ኸኒያ ክፎች ጋር እኮ ጠብ ላይቀርልን ነው' አሉ።

እንግዴህ ትግሬ ናቸው አለቃ ተጠምቆ እነ ራስ አሉላ፣ እነ ራስ መንገሻ አሉ ኸኒያ መስሏቸው፤

ኸነማን ጌታዬ? ኸነማን?' አሉ ደንግጠው አለቃ ተጠምቆ።

ኸነጮቹ'

ምነው፣ ምነው?' አሉ።

'እንዴ! የልጅዎን ቅኔ በቀደም አልሰሙትም?'

በለማ ቅኔ ሆነ እንዴ ጦርነት?' አሉ አለቃ ተጠምቆ።

አናጋሪው ማን ይመስልዎታል?' አሉ።አለቃ ለማ በዚኹ ቅኔያቸው እንደተነበዩትም ከአምስት ዓመት በኋላ የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት አይቀሬ መሆኑ ታወቀ፣ ተረጋገጠ።

በዓድዋው ጦርነት ከክተት ዘመቻ ጥሪው አንስቶ እስከ ጦርነቱ ፍልሚያና ድሉ ድረስ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ተሳትፎና ደማቅ አሻራ አለበት። የዓድዋው ጦርነትለአውሮፓውያን ቅኝ ገዢ ኃይሎችና ለጦርነቱ ታዛቢዎች በታላቂቱና ጥንታዊቷ ሮማ እና በአፍሪካዊቷ ብቸኛ ነፃ አገር፣ ድኃና ያልሰለጠነ ሕዝብ የሚኖርባት ተብላ በምትቆጠረው አቢሲኒያ፣ በሮማ ካቶሊክና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ን መካከል የተደረገ የኃይል ሚዛንን ያልጠበቀ ጦርነት ተደርጎ ነበር የተቆጠረው።

ይህን የሁለቱ አገራት ፍጥጫና የዓድዋው ጦርነት ብዙዎችን፡- ግዙፉ ጎልያድና ብላቴናው ዳዊት በጦር ግንባር የተፋጠጡበትን፣ የአይሁዳውያኑንና የፍልስጤማውያኑን የጦርነት ታሪክን ከቅዱስ መጽሐፍ ዞር ብለው እንዲያስታውሱ የተገደዱበትን አጋጣሚ የፈጠረ፣ ዓለምን ሁሉ ያስደመመ፣ የቅኝ ገዢ ኃይሎችን ደግሞ አንገት ያስደፋ ታሪካዊ ጦርነት ሆኖ ነበር ያለፈው።

ይሁን እንጂ በዓድዋው ጦርነት ዋዜማ የኢጣሊያንን ሠራዊት ትጥቅና ድርጅት ያዩና ዝናውን በጆሮአቸው የሰሙ የዓፄ ምኒልክ የቅርብ መኳንንቶቻቸውና ባለሟሎቻቸው ወደ ምኒልክ ቀርበው፡-

“ጃንሆይ ጣሊያን በሚለው መንገድ ዕርቅ ማድረግ ይበጀናል፣ እነዚህን ሰዎች ኃያላን ናቸውና፣ በጦርነት ገጥመን ማሸነፍ የሚቻል አይመስልም።” ብለዋቸው ነበር። ይህን በመሰለው ፍርሃትና ንግግር ግራ የተጋቡት ምኒልክም ለመኳንንቶቻቸውና ለመሳፍንቶቻቸው ሲመልሱላቸውም፡-

“… አንፍራ እኔ እንደሆንሁ መዝመቴን አልተውምና ስለ ጣሊያን ገናናነት፣ ዘመናዊ መሣሪያና የተደራጀ ኃይል አትንገሩኝ። ኃይል የእግዚአብሔር ነው! ድንበሬን ጥሶ የመጣውን ጠላቴን እገጥመዋለሁ። ብትዘምቱም፣ ብትቀሩም ሬሳዬን ከጦር ሜዳ ፈልጉት። ይልቅስ ጠላትን በኋላ አስቀምጦ መዝመት አይቻልምና በየግዛታችሁ ያሉትን ኢጣሊያኖች አባሩ”ብለው ትዕዛዝ ሰጡ።

ምኒልክ በዚህ ስለ ሃይማኖት፣ ነፃነት፣ ስለ እውነትና ፍትሕ በሚደረግ ጦርነት ኃይሉም፣ ድሉም የእግዚአብሔር መሆኑን አስረግጠው ለመኳንንቶቻቸውና ለቅርብ ባለሟሎቻቸው የተናገሩት ኃይለ ቃል በተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ አገር የታሪክ ጸሐፍትና ድርሳናት ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል።

በተጨማሪም በተማሪነት ዘመኔ ለጉብኝት በተገኘሁባት በርእሰ አድባራት እንጦጦ ማርያም ቤ/ን ሙዚየም ከሚገኝ አንድ ጥንታዊ ጎራዴ እጀታ ላይ “የምኒልክ ኃይሉ እግዚአብሔር ነው!የሚል ኃይለ ቃል ማንበቤን አስታውሳለሁ። በወቅቱም የሙዚየሙ አስጎብኚ ጎራዴው የአፄ ምኒልክ መሆኑን የታሪኩ እማኞች የሆኑ በሕይወት የሌሉ ሰዎችን በመጥቀስ እንደተረከልን አስታውሳለሁ።

ታሪክ እንደሚመሰክረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከሰማያዊው፣ መንፈሳዊና ሐዋርያዊ ተልዕኮዋ ባሻገር በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ ባህል፣ ቅርስ፣ ኪነ-ጥበብ፣ ኪነ-ሕንፃ፣ ሥነ ጽሑፍወዘተ ውስጥ ግዙፍና ደማቅ አሻራ ያላት ሃይማኖታዊ ተቋም ናት። በተለይም ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከአገራችን ነጻነት፣ ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ክብር ጋር በተያያዘ ስሟ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስላት፣ ስለ ነፃነት፣ ፍትሕና የሰው ልጅ ክብር በቃልም በተግባርም ጭምር ያስተማረች ናት።

ከዚህም የተነሣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በተለያዩ ጊዜያት የውጭ አገር ወራሪዎች ዒላማ ሆና መቆየቷን የሚመሰክሩ በርካታ የታሪክ ድርሳናት አሉ። ለዚህ ደግሞ ዋንኛ ምክንያቱ ቤተ ክርስቲያኒቱ ስለ አገር ክብር፣ ስለ እውነት፣ ስለ ፍትሕ፣ ስለ ነፃነትና አንድነት የምታስተምር ተቋም በመሆኗ ነው። እናም ይህች ጠንካራ ሃማኖታዊ ተቋም መምታት ለብዙዎቹ የአገሪቱን የነፃነት ዋልታ ከመሠረቱ ማፍረስ መስሎ ስለሚሰማቸው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ሲያጠቋት ኖረዋል።

ለአብነትም ያህል ከዓድዋው ጦርነት ዐርባ ዓመት በኋላ ኢትዮጵያን ዳግመኛ የወረረው የፋሽስቱ የኢጣሊያ ሰራዊት ሰማዕቱን ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስን፣ አቡነ ሚካኤልን፣ በርካታ የቤ/ቱን ካህናትን፣ መነኮሳትን መፍጀቱና ገደማትንና አድባራትን ማቃጠሉም ከዚሁ እውነታ ጋር የተያያዘ ነው።

የኢትዮጵያ ቤ/ን ሕዝቡ በአገሩ፣ በነፃነቱ፣ በአንድነቱና በሃይማኖቱ ላይ የመጣውን ወራሪ ኃይል ሁሉ በአንድነት ሆኖ እንዲመክት፣ ከአምላኩ ዘንድ ለተቸረው ነጻነቱና ሰብአዊ ክብሩ ቀናኢ በመሆን ዘብ እንዲቆም ስታስተምር የኖረች መኾኗ በታሪክ ድርሳናት የተመዘገበ ሐቅ ነው። እስቲ ከላይ ያነሳሁትን እውነታ የሚያጠናክርልኝና የሚያስረግጥ አንድ ምስክርነት ከታሪክ መዛግብት ላጣቅስ።

ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያን በአካል ተገኝተው የጎበኙ አያሌ የውጭ ሀገራት ተጓዦች፣ አሳሾችና የታሪክ ተመራማሪዎች ስለ ኢትዮጵያና ስለ ሕዝቦቿ በጋራ የሚመሰክሩትና የሚስማሙበት አንድ እውነት አለ። ይኸውም፡- ኢትዮጵያውያን ለሃይማኖታቸውና ለነፃነታቸው ቀናዒዎች ናቸው።የሚል ነው።

በአንድ ወቅትም ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ ዳንኤል ሮፕስ እ.ኤ.አ ፲፱፻፷፫ አክሌዥያ በሚባል በፓሪስ ከተማ ለሚታተም ጋዜጣ፡- የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን ታውቃላችሁን?” በሚል ርዕስ ባሰፈረው ሐተታ እንዲህ ሲል ምስክርነቱን ሰጥቶ ነበር፡-

“…ኢትዮጵያ ወራሪዎች ምድርዋን በግፍ የያዙባት መሆኑን ታሪክ ያወሳል፤ ነገር ግን ሃይማኖቷ ኃይሏና የእንቅስቃሴዋ መሳሪያ ሆኖ በመገኘቱ ነፃነቷን መልሳ አግኝታለች። በማዕከላዊው ክፍለ ዘመን “የካህን የዮሐንስ ግዛት” በአረመኔው ዓለም ተከቦ የክርስቲያን ምሽግ ሆነዋል እየተባለ ስለ ኢትዮጵያ ይነገር የነበረው ሁሉ ፍጹም ልበ-ወለድ ታሪክ አይደለም።

ከሁለት ሺኅ ሜትር በላይ ከፍታ ያለውን ደጋማና ለምለም መሬት ቁልቁል የሚያዩት ቀይ፣ ጥቁርና ሰርጥነት ያላቸው የእሳተ ገሞራ ውጤት ባሕርይ ያላቸው ጠረጴዛ መሰል ተራራዎች የጊዜን ውሽንፍር እንዳሳለፉትና የባሕር ዓሣም ሳይበገርና ሳይላላ ማዕበሉን እንደሚያሳልፍ ክርስቲያኒቷ ኢትዮጵያም በታሪክ ውስጥ ጠንካራ ስፍራዋን ይዛ ቆይታለች…።” በማለት ጽፏል።

ይኽችው ጥንታዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን በዓድዋው ጦርነት ወቅትም ለጦርነቱ ዘመቻ የክተት ጥሪ ከማስተላለፍ ጀምሮ በተለያዩ የጦርነት ዓውድ ግንባሮች ሁሉ ላይ ሣይቀር በመሳተፍ ጭምር ታላቅ የሆነ መንፈሳዊና ታሪካዊ አደራዋን ተወጥታለች።

በዓድዋው ዘመቻ በመቶ ሺሕዎች ሆኖ የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር ከጥቂቱ በስተቀር አብዛኛው ጦር፣ ሰይፍ፣ ጋሻና የነፍስ ወከፍ መሳሪያ ይዞ ነው በዘመናዊ የጦር መሣሪያና በሚሊተሪ ሳይንስ ከሰለጠነ አውሮፓዊ ጦር ጋር ለመጋጠም “ስንቁን በአህያ ዓመሉን በጉያው” አድርጎ፣ የኢትዮጵያን አምላክ ተስፋ አድርጎ ወደ ጦርነቱ የተመመው።

ዐፄ ምኒልክ ሠራዊታቸውን ክተት ብለው ወደ ዓድዋ የዘመቱት የቅዱስ ጊዮርጊስን ታቦት፣ ሊቀ ጳጳሱን ግብፃዊውን አቡነ ማቴዎስን፣ በርካታ ካህናትንና መነኮሳትን ጭምር አስከትለው ነበር። የዓድዋን ጦርነት በሰፊው የዘገቡ የውጭ አገራትና የአገር ውስጥ ጸሐፊዎችና የታሪክ ተመራማሪዎች እንደጻፉትም፡-

በጦርነቱ ቀን ብዙ መነኮሳት የሰሌን ቆባቸውን እንደደፉ፣ ወይባ ካባቸውን እንደደረቡ የቆዳ ቀሚስ ለብሰው ግማሹ ከንጉሠ ነገሥቱ ዙሪያ፣ ግማሹ ከእቴጌ ጣይቱ ዘንድ የቀሩትም በተዋጊው መኳንንትና ወታደር ዘንድ ሆነው ወዲያና ወዲህ እየተላለፉ ሊዋጋ ወደ ጦርነቱ የሚገባውን እያናዘዙና ከጦርነቱ ሊሸሽ ያለውንም እየገዘቱ፣ ሲያበራቱና ሲያዋጉ መዋላቸውን ጽፈዋል።

የአፄ ምኒልክ ጸሐፊ ትዕዛዝ የሆኑት አለቃ ገ/ሥላሴ በዓድዋ ጦርነት የነበረውን ሁኔታ ስለ ዓፄ ምኒልክ ታሪክ በፃፉት መጽሐፋቸው እንዲህ በሥዕላዊ መንገድ አስቀምጠውታል።

ንጉሡ ወደ ጦርነቱ ቦታ ሲደርሱ አቡነ ማቴዎስና የማርያም ታቦት የያዙት ካህናት በኋላቸው ነበሩ። እቴጌ ጣይቱም ከዘበኞቻቸውና ከሠራዊቱ ጋር ሆነው በአቡነ ማቴዎስና በታቦቷ ጎን ነበሩ። የአክሱም ካህናት ቅዳሜ ማታ እንደ ጥንቱ አስተዳድሩን ብለው ለንጉሡ ለማመልከት መጥተው አድረው የነበሩት፣ በዚህን ጊዜ የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን ሥዕልና ሰንደቀ ዓላማ ይዘው በእቴጌ ጣይቱ ግንባር ተሰልፈው ነበር።

የጽዮን እምቢልተኞችም መለከታቸውንና እምቢልታቸውን እየነፉ በእቴጌይቱ ፊትና በሠራዊቱ ፊት ይጫወቱ ነበር። … ከሌሊቱ ፲፩ ሰዓት ጀምሮ ይላሉ አለቃ ገ/ሥላሴ ከሌሊቱ ፲፩ ጀምሮ እስከ ፬ ሰዓት ድረስ ተኩስ ሳያቋርጥ ከሁለቱም ወገን ሲተኮስ ድምፁ እንደ ሐምሌ ነጎድጓድ፣ ከተኩስም የሚወጣውም ጢስ የተቃጠለ ቤት ይመስል ነበር።

በዚህ ቀን በዓድዋ በዓይናችን ያየነውንና በጆሮአችን የሰማነውን ለመጻፍ ችግር ነው። በዚህ ጊዜ እቴጌ ጣይቱ በማጅራታቸው ድንጋይ ተሸክመው፣ በጉልበታቸው ተንበርክከው በጋለ ጸሎት ወደ ኢትዮጵያ አምላክ እግዚአብሔር ይማጸኑ ነበር።በማለት ጽፈዋል።

በሌላ በኩል ታዋቂው ታሪክ ጸሐፊ ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ፣ “አፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት” በሚለው መጽሐፋቸው ላይ እንደጠቀሱት፡-

እቴጌ ጣይቱ በተፋፋመው የአድዋው ጦርነት ውስጥ ጥላ አስይዘው ዓይነ ርግባቸውን ገልጠው በእግር እየተራመዱ በንጉሠ ነገሥቱ ልጅ በወ/ሮ ዘውዲቱና በደንገጡሮች ታጅበው በጦርነቱ መካከል መገኘታቸውን ጽፈዋል። አቡነ ማቴዎስም የማርያምን ታቦት አስይዘው ከቀሳውስትና ከመነኮሳት ጋር ሆነው የጊዮርጊስን ስብሐተ ፍቁርን እያዜሙ ሲከተሉ ዜማው ሳያልቅ በፊት ጦርነቱ በኢትዮጵያ አሸናፊነት መደምደሙን ጽፈዋል።

ኢጣሊያዊው ጸሐፊና የታሪክ ምሁር ኮንቲ ሩሲኒም ስለ ዓድዋው ጦርነት ውሎ ሲመሰክርም፡-

ከልዩ ልዩ ምንጭ እንዳገኘሁት፣ ከሐበሾችም ጽሑፍ እንደተረዳሁት፣ ጦርነቱ ሲጀመር ዓፄ ምኒልክ፣ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት፣ ራስ መኮንን፣ ራስ መንገሻ አቲከም፣ ፊታውራሪ ገበየሁ ሌሎችም የጦር ሹማምንትና መሳፍንቱ ሁሉ ከአካባቢው ሕዝብ ጋር በአንድነት ሆነው ከሌሊቱ ፲ ሰዓት ጀምሮ በዓድዋ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሲያስቀድሱና በጸሎት ሲማጸኑ ነበር…።ሲል ስለ ዓድዋ ጦርነት በተወው ማስታወሻው ላይ አስፍሮታል።

ዓድዋ ላይ በተካሄደው ጦርነት ኢትዮጵያውያን ሁሉ ዘር፣ ሃይማኖት ሳይለዩ፣ ሴት፣ ወንድ፣ ወታደር፣ ገበሬ፣ ካህን፣ መነኩሴ… ሳይባል ሁሉም የተሳተፉበት ነው። የድሉ መንሥዔም ይኸው የኢትዮጵያዊነት ፍቅር፣ አንድነትና ልዩ ኅብረት ነው።

ከዓድዋው ድል በኋላ አፄ ምኒልክ ለውጭ አገራት ወዳጆቻቸውና መንግሥታት በፃፉትም ደብዳቤያቸውም፣ ድሉ ከእግዚአብሔር የተገኘ እንደሆነ ከመግለፃቸውም በላይ የክርስቲያኖች ደም በከንቱ ስለ መፍሰሱ የተሰማቸውን ኀዘኔታም በመጋቢት ፳፫ ቀን ፲፱፻፹፰ ዓ.ም ለፈረንሳዊው ሙሴ ሸፍኔ በላኩለት ደብዳቤያቸው እንዲህ ገልጸውታል፡-

… ከአላጌ ጦርነት በኋላ፣ ጣሊያኖችን ጦርነት ይቅር፣ የክርስቲያንም ደም በከንቱ አይፍሰስ፣ ዕርቅ ይሻላል ብላቸው እምቢ ብለው መጥተው በጥጋባቸው ዓድዋ ላይ ተዋግተው ድል ሆኑ። እኔ ግን በድቁርናቸው ብዛት የነዚያን ሁሉ ክርስቲያን ደም በከንቱ መፍሰሱን እያየሁ ድል አደረኳቸው ብዬ ደስ አይለኝም። ነገር ግን በግፍ የመጡ ሰዎች ናቸውና እግዚአብሔር ግፉን አነጣጠረን…።

አፄ ምኒልክ ለሞስኮብ ንጉሥ ኒቆላዎስም በላኩት ደብዳቤያቸውም፡-

እንደ አውሮፓ ነገሥታት ሥራት ሁሉ ጠብ መፈለጋቸውን ሳያስታውቀኝ፣ እንደ ወምበዴ ሥራት ሌሊት ሲገሰግስ አድሮ ሲነጋ ግምባር ካደረው ዘበኛ ጋር ጦርነት ጀመረ። ጥንት ከአሕዛብና ከአረመኔ አገራችን ጠብቋት የሚኖር አምላክ ከእኛ ባይለይ በእግዚአብሔር ኃይል ድል አደረግሁት…።በማለት ድሉ ከኢትዮጵያ አምላክ ዘንድ የተገኘ መኾኑን ጽፈውላቸዋል።

በዓድዋው አንጸባራቂ ድል የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ኢትዮጵውያንን ሁሉ በማስተባበር የተጫወተችው ሚና፣ በድሉም ወቅት ውስጥ የነበራት ደማቅ አሻራና ትልቅ ድርሻ ሁልጊዜም ታሪክ የሚያስታውሰውና የሚዘክረው ለትውልዱ ሁሉ የሚተላለፍ ነው። ማኅበረ ቅዱሳንም ይህን ታላቅና ታሪካዊ ዕለት በየዓመቱ ለመዘከር የሚያደርገው እንቅስቃሴም ይበል የሚያሰኝ ነው።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1379 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 980 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us