የበላይ በፍቃዱ ቡድን በቀጣይ ወደ ሰማያዊ ወይስ መኢአድ

Thursday, 05 February 2015 10:27

“ፓርቲያችን የፈረሰው በሰማያዊ ፓርቲ ድብቅ ሴራ ነው”

የአንድነት አመራር አባላት ከወህኒ ቤት

ከኃይሉ ባደግ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሰጠውን ውሣኔ ተከትሎ ማረፊያ ድርጅት ለመምረጥ እየተወያዩ የሚገኙት የቀድሞው የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች የአማራጭ አቋሞች ላይ በመቆም እየተወዛገቡ መሆናቸው ታወቀ።

በውስጣዊ እንቅስቃሴያቸው በተፈጠረ ማዕከላዊና መሰረታዊ ልዩነቶች የተነሳ ጉዳያቸው ወደ ከረረ ደረጃ ለመድረስ የቻለውን የአንድነትንና የመኢአድን ችግር ለመፍታት የሞከረው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የሰጠውን መመሪያ በተቀመጠላቸው ቀነ ገደብ ተግባራዊ ለማድረግ ባለመቻላቸው የመጨረሻውን ውሳኔ ለመቀበል መገደዳቸው ይታወሳል፡፡ ፓርቲዎቹን “ጠቅላላ ጉባኤውን ባላማከለና ድርጅታዊ መመሪያን ባልተከተለ መንገድ ከአመራርነታችን ተወግደናል” የሚል ቅሬታ ያቀረቡ አመራሮች እንዲመሩት ከወሰነ በኋላ የቀድሞው አመራሮች የአቅጣጫ ለውጥ ለማድረግ እየሞከሩ ባሉት ሁኔታ በአንድነት አመራሮች መካከል መከፋፈል ተፈጥሯል።

በአንድነት ውስጥ የተፈጠረውን የባለቤትነት ውዝግብ ለመፍታት የጠቅላላ ጉባኤው መጠራት ወሳኝ መሆኑን በማመን መመሪያ አስተላልፎ የነበረውን የምርጫ ቦርድ መፍትሄ ተግባራዊ ለማድረግ ፍላጐቱን ያላሳየውና በአቶ በላይ ፍቃዱ የሚመራው ቡድን ፓርቲውን በትዕግስቱ አወሉ ለሚመራውና “ተገኝተናል” የሚል አቤቱታ ላቀረበው ቡድን እንዲያስተላልፍ ከተደረገ በኋላ የባለቤትነት ውጤቱን ያጣው ተሰናባቹ ቡድን ቢሮውን አስረክቦ ሌሎች አማራጮችን ለማሰብ የተገደደበት ሁኔታ ነው ያለው።

የፓርቲውን ጽ/ቤት ለእነ ትዕግስቱ አወሉ ቡድን ለማስረከብ የቻለው የእነ በላይ ፍቃዱ ቡድን አባላት በቀጣይነት መከተል ስለሚገባቸው አቅጣጫ እያደረጓቸው በሚገኙ ውይይቶች ለመግባባት አለመቻላቸውንና በውስጣቸው ከፍተኛ ውዝግብ እየተፈጠረ መምጣቱን በመግለጽ ልዩነቱ ከጽ/ቤቱ የተሰናበተውን ቡድን ለአራት እንዲከፈል ምክንያት ሆኗል።

ተሰናባቹ ቡድን እየመከረ ባለው የቀጣይ መፍትሄ አቅጣጫ ላይ “መክፈል የሚገባንን መስዋዕትነት በመክፈል የጀመርነውን ትግል መቀጠል ይገባናል” የሚል የጋራ አቋም የተንፀባረቀ ቢሆንም የቀጣዩ ትግል ማረፍያን አስመልክቶ በሚቀርቡት ሃሳቦች ላይ የተነሳው ልዩነት ወደከረረ የሃሳብ ውዝግብ ውስጥና ውጥረት ውስጥ ከቷቸዋል። በቀጣይ የትግል መስመር ውስጥ በመግባት ትግላቸውን ለመቀጠል የጋራ አቋም የያዙት የተሰናባቹ የአቶ ፍቃዱ ቡድን አባላት ማረፊያቸውን አስመልክቶ ላነሱት ሃሳብ የመኢአድ አመራርነትን ወደተረከበው የአበባው መሃሪ ቡድንና ወደ ሰማያዊ ፓርቲ ለመግባት በሚንደረደሩ ሃሳቦች ተንጠልጥሎ ውዝግብ መፈጠሩና በዚህም የተነሳ ወደ አራት መከፋፈሉን እንዲሁም የዚህ ቡድን ዕጣ ፈንታ አሳሳቢ ወደሆነ ደረጃ መድረሱን የስንጣሪውን ምድብ ከፋፍለው በማቅረብ ይገልፃሉ።

የፓርቲውን የባለቤትነት ቦታ የተነጠቀው ይሄው ቡድን ወደ አራት መከፈሉን እንዲሁም ለአራት የተከፈሉት ጥቃቅን ቡድኖች በየቦታው የሚያደርጉት ስብሰባና እንቅስቃሴ በዝርዝር ሲቃኝ ይህን ይመስላል።

በአቶ አስራት ጣሴና በአቶ ግርማ ሰይፉ የሚመራውና ቀድሞም ቢሆን ለሌሎች ፓርቲዎች ዝቅተኛ ግምት በመስጠት የሚታወቀውን አንደኛው ቡድን ወደ ሰማያዊ ፓርቲ ለመቀላቀለ ከአባላቱ የተሰጠውን ሃሳብ በማውገዝ “ሰማያዊ ፓርቲ አይመጥነንም ከዚህ ትክክለኛ ጭብጥ በመነሳት እኛን ሊመጥነን የሚችለው መኢአድ ብቻ ነው” የሚል አቋም ማራመዳቸው በሌሎቹ አባላት ዘንድ ብዥታን ፈጥሯል። ይህ አቋም በፖለቲካዊ ጉዞ ላይ የሚያሳድረው ጥያቄ ቀላል የሚባል አለመሆኑን በመተቸት አውግዘውታል።

“ምርጫ ቦርድ በእኛ ላይ ሕገ-ወጥ ውሳኔ በማስተላለፍ የአገሪቱን የመድበለ ፓርቲ ተስፋ አስቆርጦታል የሚል አቋም በመያዝ ቅሬታችንን እያስተጋባን ባለበት ዕውነታ በእኛ ላይ እንደተሰራው ሽፍጥ መኢአድን ለመረከብ ከቻለው የአቶ አበባው መሃሪ ቡድን ጋር መቀላቀል ለምርጫ ቦርድ ውሳኔ እውቅና መስጠት ነው። ይሄም የፖለቲካ ክስረት ያመጣብናል” በማለት የተቃወሙትን አባላት ጆሮ ዳባ ልበስ ለማለት የወደዱት ሁለቱ አመራሮች ከዚህ ቀደም ከመኢአድ ጋር ተጀምሮ የነበረውና የተቋረጠው ድርድር ከአቶ አበባው መሃሪ አመራር ጋር እንዲቀጥል ለማስቻል ተፅዕኖ እየፈጠሩ ይገኛሉ።

ሌላው በቅሊንጦ ማረሚያ ቤት በሚገኘውና በአቶ ሀብታሙ አያሌው የሚመራው ቡድን በቅርቡ ወደ ማረሚያ ቤት በመጓዝ በጉዳዩ ላይ መመካከሩን የገለፁ ወገኖች በበኩላቸው የተደረገላቸውን የአቋም ማብራሪያ መስማታቸውን በማስረዳት መመሪያ መቀበላቸውን ለአባላቱ አስታውቀዋል።

ይህ በሁለተኛነት ደረጃ ጥቂት አባላትን ወደ ቅሊንጦ በመጥራት የግል አቋሙን ግልፅ ያደረገው የአቶ ሀብታሙ ቡድን እጅግ ጠንካራ የሆነውና ህዝባዊ ተቀባይነት ያለውን አንድነተን ለማፈራረስ በተደረገው ሴራ ውስጥ ከምርጫ ቦርድና ከገዥው ፓርቲ በላይ የላቀ ሚና የተጫወተው “ሰማያዊ ፓርቲ” ነው ብሏል። አንድነት የተሻለ ስለነበር ሰማያዊ ፓርቲ ቅናት ውስጥ እንዲወድቅ አስገድዶታል። ስለዚህም ወደ ስውር ሴራው ለመግባት ችሏል። ከአጠቃላይ ነጥብ በመነሳት አቶ በላይ ፍቃዱ የሚመራው ቡድን ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር መቀላቀል የለበትም የሚለውን ጠንካራ አቋም አስረግጦ ካሳወቀ በኋላ ይህ ቡድን ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር እንቀላቀላለን የሚል አቋም ከያዘ፣ ሕጋዊ በሆነ የፅሁፍ አቋም እራሱን ከፓርቲው እንደሚያገል ማስጠንቀቁ ለማወቅ ተችሏል።

ለየት የሚል አቋም የያዘውና አቶ አስራት አብርሃና ተክሌ በቀለ የመሳሰሉ አመራሮችና አባላት ያሉበት ሦስተኛው ስብስብ “በአቶ አበባው መሀሪ ቡድን ወደሚመራው መኢአድ መግባት የለብንም” የሚል ጠንካራ አቋም ይዟል። ይህ አይነቱ የመቀላቀል ፖለቲካ የምርጫ ቦርድ በእነ ትዕግስቱ አወሉ የሰጠውን ውሣኔ እውቅና በመስጠት፣ በእጅ አዙር አንድነት ላይ የተላለፈውን ውሣኔ እንደመቀበል የሚያስቆጥር መሆኑን በመግለጽ እየተቃወመ ይገኛል።

ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር ስለመቀላቀል የቀረበውን አቋም በእጅጉ በመተቸት ከእነ ግርማ ሰይፉ ጋር ተመሳሳይ አቋም የያዘውና በአንድነት ውስጥ በሦስተኛ ረድፍ ላይ የቆመው ይህ ቡድን “ሰማያዊ ፓርቲ ለብሔር ብሔረሰቦች ዕውቅና የማይሰጥ በመሆኑ ለትግል አመቺ አይደለም” የሚል አቋም ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።

ይህንን አቋም የሚያራምደውን የቀድሞው የአንድነት አመራርን ሦስተኛ ረድፍ ከሚያንቀሳቅሱት አመራሮችና አባላት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አስራት አብርሃ ቀደም ሲል ይንቀሳቀሱበት የነበረውን የዓረና ትግራይ ፓርቲን፣ ከአመራሮቹ ጋር በተፈጠረ ችግር አመራርነታቸውን በመልቀቅ ወደ አንድነት መቀላቀላቸውን አስታውሰው በአሁኑ ወቅት ምርጫ ቦርድ ከወሰነውን ውሣኔ ጋር በተያያዘ ወደ ቀድሞው ፓርቲ ለመመለስ ከዓረና አመራሮች ጋር ድርድር መጀመሩን ውስጥ አዋቂ ምንጮች ያስረዳሉ።

ወደ አንድነት ፓርቲ ከመጣ በኋላ በአመራር ላይ የነበረውን የኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራውን መንበረ ፓርቲ በመነቅነቅ የባለቤትነት መብቱን ይዞ የነበረውና ከምርጫ ቦርድ ውሣኔ በኋላ ይዞታውን የተነጠቀው የበላይ በፈቃዱ መራሹ ቡድን “ወደ ሰማያዊ ፓርቲ መቀላቀል አለብን” የሚል ጠንካራ አቋም መያዙን የሚያስረዱት ውስጥ አዋቂ ምንጮች በስውር እየተደረገ ያለው ድርድር ተቃውሞን እየጫረ በመምጣት የመተራመስ ወረርሽኙ ከአንድነት ወደ ሰማያዊ እንዲሸጋገር እያደረገው መሆኑን ይገልፃሉ።

የሽምግልና ተልዕኮ ይዘው መንቀሳቀስ ከጀመሩ ረዥም ጊዜ በሆናቸው በዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም በኩል ከኢንጂነር ይልቃል ጋር የተናጠል ውይይት ያደረጉት የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ በላይ ፍቃዱ በምስጢር ባደረጉት በዚህ ድርድር የሰማያዊ ፓርቲን ምክትል ሊቀመንበርነትን ጨምሮ የፓርቲውን አመራር እኩል እጅ ማግኘት እንደሚችሉ በተገባላቸው ቃልኪዳን መሰረት ወደዚሁ አማራጭ መቀላቀል የሚሻል መሆኑን በመግለፁ ጠንካራ ግፊት በማሳደር ላይ መሆናቸው ታውቋል።

“ይህንን አቋም የሚቃወሙ አመራሮች ካሉ የራሳቸው ጉዳይ ነው። የቀረበውን ዕድለ በመጠቀም ወደ ሰማያዊ ፓርቲ መግባት ከፈለጉ እሰየው ነው ካልደገፉ ግን በተናጠልም ሆነ እኛን የሚደግፉንን አባላት ይዘን ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር እንቀላቀላለን” የሚል ጠንካራ አቋም የያዙት አቶ በላይ “ሰማያዊ ፓርቲ የተጠናከረና በቁጥርም የበረከተ ተከታይ የሌለው በመሆኑ ከአመራሮች ጋር ተገናኝተን የምናደርገውን ድርድር በማፋጠን ለምርጫው ያዘጋጀናቸውን ዕጩዎች በፍጥነት እንዲመዘገቡ ማድረግ ይጠበቅብናል” በማለት ደጋፊዎቻቸውን ማነቃነቃቸው ታውቋል።

ከእነ በላይ በፈቃዱ ቡድን ጋር የሚደረገውን ምስጢራዊ ድርድር በዶ/ር ያዕቆብ ሸምጋይነት በኩል ብቻውን እያካሄደ የሚገኘውን የኢንጂነር ይልቃልን አቋም በማውገዝ ላይ የሚገኙ የፓርቲው አመራሮችና የማዕከላዊ ምክር ቤት አባላት በበኩላቸው እየተካሄደ ባለው ድርድር ላይ ማንም እንዳላማከራቸው በመግለፅ በወሬ ደረጃ የሚሰማውን ይሄንን ሂደት የተከታተለው አብዛኛውን አባል ምስጢራዊውን ድርድር በማውገዝ ከአንድነት የተሰናበተውን የእነ በላይ ቡድን ቅልቅልን ገና ከጅምሩ እየተቃወመ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ።

“ሕጋዊ እውቅና የተነፈገ ቡድንን ወደ ፓርቲያችን እንዲገባ ማድረግ የእኛም ፓርቲ እንደሌሎቹ ሁሉ ችግር ውስጥ የሚገባበትን ዘዴ ለመንደፍ ምክንያት እየፈለጉብን በሚገኙት ምርጫ ቦርድና ገዥው ፓርቲ እንዲመታ ለማድረግ ክፍተት ይፈጥራል” የሚሉት እነዚሁ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት “በርካታ የአመራር ቦታዎችን የሚፈልገው የበላይ ፍቃዱ ቡድን ከእኛ ጋር ከተቀላቀለ በተግባር የተፈተነውን አመራራችንን ቦታ የሚያሳጣ ነው” በማለት እየተቃወሙት ይገኛሉ። በቀጣይ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አሁን ላይ ሆኖ መገመት ቢከብድም፤ የሚሆነውን ግን አብረን የምናየው ይሆናል። ቸር እንሰንብት። 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1136 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1065 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us