በስኳር መላስ የሚፋጁ ፓርቲዎች እና ውሃ የማይቋጥር ምክንያቶቻቸው

Thursday, 05 February 2015 10:22

በከበደ ካሳ

በአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ /አንድነት/ ፓርቲ ቤት የተፈጠረው ክፍፍል የሰሞኑ ወቅታዊ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኖ ከርሟል። በርግጥ ይህ አይነት ችግር ያለው እነሱ ጋር ብቻ አይደለም። የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትም /መኢአድ/ እንዲሁ ለሁለት ተሰንጥቋል። የሁለቱን ችግር የሚያለያየው ነገር ቢኖር መኢአድ ሁልጊዜ ተሰንጥቆ የሚኖር ድርጅት ሲሆን አንድነት የሚሰነጠቀው ግን ምርጫ ሲደርስ ብቻ መሆኑ ነው። ይህን ነገር በደንብ ላብራራው።

በመኢአድ ቤት ሁልጊዜ ፀብና ድብድብ አለ። ድብድቡም አንዱ በአንዱ ላይ አሲድ እስከመድፋት የደረሰ ነው። መኢአድ ቤት በአራተኛው ዙር ምርጫ ወቅት ሠላም አልነበረም፤ በክልላዊና ማሟያ ምርጫ ወቅትም ሠላም አልነበራቸውም፤ አሁንም ይሄው ሠላም እንደራቃቸው ናቸው። በአንድ ወቅት የኃይል ሚዛኑን ተነጥቆ ግቢ እንኳን እንዳይገባ ታግዶ የነበረው የአቶ ማሙሸት አማረና በእሱ የሚመራው ቡድን አሁን በተራው ሲያባርር ከርሟል። በዛን ጊዜ ክንደ ብርቱ የነበረው የአበባው መሃሪ ቡድን አሁን ከውጭ ሆኖ ፅ/ቤቱን በሩቅ ሲያማትር ነበር። ምርጫ ቦርድ ባለፈው ሳምንት የሰጠው ውሳኔ ደግሞ የኃይል ሚዛኑን ቀያይሮታል።

እነዚህ ሁለት ቡድኖች ላለፉት ተከታታይ አመታት ፍርድ ቤት ሲመላለሱ ነበር። በሂደቱ አንዱ ሲታሰር አንዱ ሲፈታ አይተናል። የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት ዶ/ር ታዲዎስ ቦጋለ 17 ወራት ማረሚያ ቤት ከርመዋል። ዶ/ር ታዲዮስ የፓርቲውን ማህተም ያለአግባብ ተጠቅመዋል በሚል በኢ/ር ኃይሉ ሻውል ክስ ተመስርቶባቸው ነው ለእስር የተዳረጉት። ይህን ችግር በድርጅቱ ውስጥ መፍታት ሲቻል የትግል አጋራቸውን ለእስር መዳረጋቸው ኢ/ር ኃይሉን በብዙዎች አስተችቷቸዋል።

አንድነት ቤት ግን ምርጫ ካልመጣ ሁልጊዜ ሠላም ነው። የአንድነት መሪዎች ከምርጫ በፊት ያላቸው ፍቅር ወደር የለውም። አንዱ ሌላውን ማንቆለጳጰስ ይችሉበታል። ለፓርቲው ቅርብ የሆኑ ሰዎች እንደነገሩኝ መሪዎቹ አንድ ሲጋራ ለሁለት የሚያጨሱ፣ ፍቅራቸው የፀና ናቸው። ምርጫ 2002 ሲመጣ ግን በኢንጂነር ግዛቸው ሺፈራው የተመራው ቡድን በፕሮፌሰር መስፍን የተመራውን ቡድን አባረረ። የማባረር ሂደቱ ሰላማዊ አልነበረም። የአካልና የንብረት ጉዳት የደረሰበት ነው። ከምርጫው በኋላ ግን አንድነት ቤት እንደገና ሠላም ወረደ። 2007 ምርጫ ሲቃረብ ደግሞ ይሄ የመሰንጠቅ በሽታ መልሶ አገረሸ። የዛን ግዜ አባራሪ የነበረው የኢ/ር ግዛቸው ቡድን አሁን ተባራሪ ሆነ። ያኔ በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ቡድን ላይ በሩን ከውስጥ ሆኖ በቀረቀረው የኢ/ር ግዛቸው ቡድን ላይ አሁን እነበላይ ፍቃዱ ከውስጥ ሆነው በሩን ቀረቀሩበት። እናም በተራው ከውጭ ሆኖ እሪ ሲል ከረመ። አሁን ግን ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅናውን ለትዕግሰቱ አወል ቡድን መስጠቱ ለኢ/ር ግዛቸውም መልካም ዜና መሆኑ አይቀርም።

ለመሆኑ የአንድነት አመራሮች ፍቅር ምርጫ ሲቃረብ ብን ብሎ የሚጠፋው ለምንድን ነው? መኢአድስ ሁልጊዜ ሠላም ርቆት የሚኖረው ለምንድን ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ ይገባል። ለዚህ መልሴ የችግራቸው መንስኤ ገንዘብ ስለሆነ ነው የሚል ነው። እዚህ ላይ የሁለቱም ፓርቲዎች ችግር መንስኤ ተመሳሳይ ከሆነ ፓርቲዎቹ የሚሰነጠቁበት ጊዜ ለምን ተለያየ? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀሬ ነው። እንደእኔ እምነት ልዩነቱን የፈጠረው ገንዘቡ የሚቀዳበት ምንጭ መለያየቱ ነው። አንድነቶችን የሚያባላቸው ከውጭ የሚመጣ ዶላር ሲሆን መኢአዶችን የሚያናጫቸው ደግሞ የሀገር ውስጥ ብር ነው። እዚህ ላይ የአንድነት የገንዘብ ምንጭ ከውጭ ነው ስል ከሀገር ውስጥ ሰባራ ሳንቲምም አያገኝም ማለቴ አይደለም። በተመሳሳይ መኢአድ ከውጭ ምንም ገንዘብ አይመጣለትም እያልኩ እንዳልሆነ አስቀድማችሁ ተገንዘቡልኝ። በሚዛኑ ተመልከቱት።

ለአንድነት እጅጉን የሚበዛው የገንዘብ ምንጩ ፅንፈኛ ዲያስፖራው ነው። ዲያስፖራው ደግሞ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቀልቡን የሚስበው ምርጫ ሲቃረብ ነው። እናም በሌሎች አመቶች ሀገር ጥሎ የሄደበትን ጉዳይ ሲፈፅም ይከርምና ምርጫ ሲመጣ ፊቱን ወደ ሀገሩ ፖለቲካ ያዞራል። ፅንፈኛው ዲያስፓራ ምርጫ ሲቃረብ ገንዘብ እየሰበሰበ በርቀት መቆጣጠሪያ /ሪሞት/ ወደሚመራቸው ፓርቲዎች መላክ ይጀምራል። ገንዘቡ ከግለሰቦች ጀምሮ ከተቋሞች ወይም የኢትዮጵያን በጎ ከማይመኙ ሀገራት ጭምር የሚሰበሰብ ሊሆን ይችላል። ለአብነት ባለፈው አመት የቀድሞው ግንቦት 7 ከኤርትራ መንግስት ካገኘው ግማሽ ሚሊዮን ዶላር ውስጥ የተወሰነውን በሀገር ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ኃይሎች ለመስጠት ቃል መግባቱን ልብ ይሏል።

የዲያስፖራው ገንዘብ ከሚፈስላቸው ፓርቲዎች አንዱ አንድነት ፓርቲ ነው። ይሄ ገንዘብ ታዲያ አብሮ ሌላ መዘዝ ይዞ ይመጣል። አርፎ ተኝቶ የነበረው አንድነት ምርጫ ሲደርስ በሚመጣለት ገንዘብ የተነሳ መተራመስ ይጀምራል። በማጣቱ ጊዜ ተፋቅሮ የኖረው አመራር በማግኘቱ ጊዜ እርስ በርስ መናከስ ይጀምራል። እናም አንድነት በምርጫ 2002 እና በምርጫ 2007 ዋዜማ ለሁለት የተሰነጠቀው በዚህ የውጪ ገንዘብ ጋር ተያይዞ ነው።

በአንፃሩ እንደጠቀስኩት የመኢአድ የገንዘብ ምንጭ እዚሁ ስለሆነ ችግሩም በየእለቱ የሚታይ ነው። በግልፅ ለመናገር የመኢአድ የገንዘብና የችግር ምንጭ የቀድሞው ፕሬዝዳንቱ የኢ/ር ኃይሉ ሻውል ኪስ ነው። እንደሚታወቀው ኢ/ር ኃይሉ ሻውል ቢጠሯቸው የማይሰሙ ሃብታም ናቸው። ገንዘባቸውን ከሚያፈሱበት መስክ አንዱ ለረጅም ጊዜ በፕሬዝዳንትነት የመሩት መኢአድ ፓርቲ ነው። ይህን የሚያረጋግጥ አንድ ገጠመኜን ልንገራችሁ።

ወቅቱ ምርጫ 2002 ሊደርስ አካባቢ ነው። መኢአድ ጠቅላላ ጉባዔውን በአይቤክስ ሆቴል ያካሂዳል። የዚህ ጉባኤ አንዱ አጀንዳ የፓርቲውን ኦዲት ሪፖርት ማዳመጥ ነበር። ሪፖርቱ ሲቀርብ ታዲያ ፓርቲው እዳ እንዳለበት ተገለፀ። መጠኑን በትክክል ባላስታውሰውም ከ200ሺ ብር የማያንስ ነው። እኔ በዚህ ጉባኤ ላይ የተገኘሁት ለቀድሞው ኢቲቪ ዘገባ ነበርና አንዱን አመራር “ፓርቲው ይህን ያህል ገንዘብ ከሊቀመንበሩ ኢ/ር ኃይሉ መበደሩ ግለሰቡ ፓርቲውን እንዳሻቸው እንዲጠመዝዙት እድል አይሰጣቸውም ወይ?” የሚል ጥያቄ አቀረብኩለት።

ይህ የፓርቲው አመራር ታዲያ ‘በየዋህነቴ’ ተገርሞ ፈገግ አለና ተከታዩን ምላሽ ሰጠኝ። “ኢ/ር ኃይሉን ስለማታውቃቸው ነው። አሁን እኛ በሪፖርቱ አካተትነው እንጂ እሳቸው ይሄኔ ማበደራቸውንም ረስተውት ይሆናል” አለኝ። ይህ ሃቅ ኢንጂነሩ በፓርቲው ላይ ያላቸውን ጉልበት ያሳያል። ከፓርቲው በተለያዩ ጊዜዎች ያፈነገጡ ሁሉ የሚገልፁትም ግለሰቡ ፓርቲውን ልክ እንደግል ንብረታቸው እንደሚቆጥሩት ነው።

የኢንጂነር ኃይሉ ገንዘብ ወደ መኢአድ ካዝና የሚገባው ግን ምርጫ ሲቃረብ ጠብቆ አይደለም። ለእሳቸው መኢአድ ማለት ሌላው የግል ካምፓኒያቸው ነው። እናም በየቀኑ ይቆጣጠሩታል። ፓርቲው በቸገረው ጊዜ ሁሉ አሉለት። በዛው ልክ ፓርቲው በሚወስነው ጉዳይ ላይም አሉበት። አንዱን ወገን ያቀርባሉ፤ አንዱን ወገን ያርቃሉ። በመሆኑም የኢ/ር ኃይሉ ብር ሁሌ በመኢአድ ቤት አለ፤ ፀብና ድብድብም ሁሌ ፓርቲው ውስጥ አለ።

የኢ/ር ኃይሉን ፈላጭ ቆራጭነት በተመለከተ አንድ አብነት ላንሳላችሁ። በአይቤክስ ሆቴል በተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ኢ/ር ሃይሉ ሻውል የፓርቲው ሊቀመንበር ሆነው ዳግመኛ ተመረጡ። እሳቸው ታዲያ “እኔ አርጅቻለሁ፤ ደክሜያሁ፤ ይሁን ግድ የለምካላችሁ ግን አቶ ያዕቆብ ልኬ ምክትሌ ይሁን” ብለው ከጎናቸው አስቀመጡ። የያዕቆብ ምክትልነት ለጉባኤውም ሆነ ለብሔራዊ ምክር ቤቱ ዱብ እዳ ነበር። ይህንን ሹመት የተቃወሙትና “ምክትልነት ለእኛ ይገባናል” የሚል ጥያቄ የነበራቸው ማሙሸት አማረና ታዲዎስ ቦጋለ ታዲያ ቡድን አደራጅተው ከፍተኛ ተቃዉሞ አስነሱ።

ኢ/ር ኃይሉ በቀናት ውስጥ እነዚህን ሰዎች ከፓርቲው አገዷቸው። ቅሉ እነማሙሸት በቀላሉ የሚሸነፉ አልነበሩም። ወር ባልሞላ ጊዜ ያደራጁትን ሃይል ይዘው የፅ/ቤቱን ግቢ ተቆጣጠሩት። እነያዕቆብል ኬቢሮ አለን ብለው ሲመጡ እነማሙሸት ግቢ ውስጥ ሆነው ‘አናስገባም ሰርገኛ ከደጅተኛ’ እያሉ ሲጨፍሩ አገኟቸው። ያኔ ታዲያ ኢ/ር ኃይሉና በሳቸው የሚመራው ቡድን “ሁከት ይወገድልኝ” የሚል ክስ መስርቶ እነ ዶ/ር ታዲዮስ ቦጋለ፤ አቶ ማሙሸት አማረንና ኮሎኔል ታምሩ ጉልላትን በህግ አግባብ ከግቢው አስወጥቷቸዋል። በዚህ የተነሳ ኢ/ር ኃይሉና ማሙሸት አማረ ያለፉትን አራት አመታት አይጥና ድመት ሆነው አሳለፉ።

በዚህ አመት ደግሞ የኢንጂነር ኃይሉን ኪስ ፈላጭ ቆራጭነት የሚያረጋግጥ ሌላ ክስተት አየን። ጥቅምት አጋማሽ ላይ በተካሄደ ጉባዔ ለአራት አመት ከፓርቲ አባልነት እንኳን ታግደው የነበሩት ማሙሸት አማረ የፓርቲው ፕሬዝዳንት ሆኛለሁ ብለው ብቅ አሉ። አቶ አበባው መሃሪ ደግሞ ድንገተኛ ምርጫ ተካሂዶ መፈንቅለ ስልጣን ተካሂዶብኛል አሉ። ይህም ሌላ የመነጋገሪያ ጉዳይ ሆኖ ከከረመ በኋላ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ ህጋዊ እውቅና ለአበባው መሃሪ ባለፈው ሳምንት ተሰጣቸው። የሚገርመው ነገር ግን እነ አቶ ማሙሸት አማረ የተመረጡበትን ጉባዔ ቀስቅሰው የጠሩት ኢ/ር ኃይሉ ሻውል መሆናቸው ነው። በመካከላቸው እርቅ ተፈፅሞ እንጂ እነዚህ ሰዎች ከላይ እንደጠቀስኩት ከፍተኛ ግጭት ያስነሱ ነበሩ።

እነ ማሙሸት አማረ ከፓርቲው ፅ/ቤት ለመባረር ከዳረጋቸው ክስ ላይ ከተዘረዘሩት አንዱ የኢ/ር ኃይሉ ሻውልን መኪና መስተዋት መሰባበር ነበር። እንኳን ድንጋይ ሊወረወርባት በሙሉ አይን ለማየት የምታሳሳ መኪና መስተዋት ዱቄት አድርገዋት ነበር። አሁን ታዲያ ይቅር ተባብለን ተታርቀናል ይላሉ። መታረቅንስ ይታረቁ፤ ግን እርቁ በመርህ ላይ ተመስርቶ ነው ወይ? የሚለው መመለስ አለበት። እንደሚታወቀው አቶ ማሙሸት በኢ/ር ኃይሉ ላይ በተደጋጋሚ ያነሱት የነበረው ትችት ግለሰቡ “አምባገነን ናቸው፤ በፓርቲው ላይ ፈላጭ ቆራጭ ሆነዋል፤ ፓርቲውን የግል ድርጅታቸው አድርገውታል፤” ወዘተ… የሚል ነበር። ከእርቃቸው በኋላ ስለዚህ ጉዳይ ሲጠየቁ ግን “ኢንጂነሩ ምንም አያውቁም፤ አጠገባቸው የነበሩ ሰዎች አሳስተዋቸው ነው፤ አሁን እነዛ ሰዎች በአቅራቢያቸው የሉም” በሚል ለማስቀየስ መሞከር የእርቁን ዘላቂነት ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል።

እንግዲህ ከላይ በዝርዝር እንዳስቀመጥኩት ለፓርቲዎቹ መሰነጣጠቅ ምክንያቱ ገንዘብ ነው። እኔ ይህን ልበል እንጂ ሌሎቻችሁ ሌሎች ምክንያቶችን ልታነሱ ትችላላችሁ። በተደጋጋሚ የሚነሳው “መንስኤው የአላማ አንድነት በመካከላቸው አለመኖሩ ነው” የሚለው ሃሳብ ነው። ይሄን በምንም መልኩ ልገዳደረው የምችል ሃሳብ አይደለም። እሱ ላይ ያላተኮርኩት ግን የዚህ ፅሁፌ ትኩረት መጨረሻ ላይ ጎልቶ የወጣው ወይም ሰበብ የሆነው ጉዳይ /immediate cause/ ስለሆነ ነው። የጋራቸው የሆነ ጽኑ አላማ አለመኖር ለችግሩ መሰረታዊ ምክንያት /ultimate cause/ ተብሎ ሊወሰድ የሚችል ነው።

አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች በእነዚህ ፓርቲዎች መካከል ለሚፈጠረው ችግር መንስኤዎቹ በየጊዜው አፈንግጠው እየወጡ ችግሩን ኢቲቪን ጨምሮ ለመገናኛ ብዙሃን የሚያጋልጡ አመራሮችና አባሎች ፖለቲካዊ ስብዕናና የትግል ፅናት የጎደላቸው በመሆናቸው እንደሆነ ሲናገሩ እሰማለሁ። ይሄም የማይካድ ቢሆንም ለፓርቲዎቹ መከፋፈል ግን ምክንያት አይደለም። እንዲያ ቢሆንማ ኖሮ እነዚህ ሰዎች ሲባረሩ ችግሮቹ ሁሉ በተፈቱ ነበር። ለምሳሌ የአንድነትን ጉዳይ እንመልከተው። በ2003 ዓ.ም ሚያዚያ ወር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፤ ይልቃል ጌትነት /አሁን የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር/ እና ሌሎች አመራሮችን ጨምሮ በርካቶች ከአንድነት ተባረሩ። እነዚህ ሰዎች ‘መርህ ይከበር ’እና‘ ዝም አንልም’ በሚል ተደራጅተው ኢቲቪን ‘ደጅ እየጠኑ’ ዜና ያሰሩ ነበር። እነሱ ከፓርቲው ከተባረሩ በኋላም ታዲያ ፓርቲው ሠላም አላገኘም።

አንዳንዶች ደግሞ የችግሩ መንስዔ ኢሕአዴግ ነው ይላሉ። ይህም ትክክል አይደለም። ይህንንም በመረጃ አስደግፌ እሞግታለሁ። በምርጫ 2002 ዋዜማ አንድነት ለሁለት ሲከፈል አባራሪው ተባራሪውን ‘የኢሕአዴግ ፍጥረት' እያለ ሲዘልፍ ነበር። እንግዲህ ኢሕአዴግ የተባሉት እነፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፤ ይልቃል ጌትነት፤ ወዘተ መሆናቸው ነው። ያኔ ‘የኢሕአዴግ ተላላኪ’ ብሎ ሲፈርጃቸው የነበረው ተቃዋሚ ኃይል ግን አሁን እነዚህን ግለሰቦች የቁርጥ ቀን ታጋዮቹ አድርጎ ነው የሚያንቆለጳጵሳቸው እንጂ ኢሕአዴግ ሲላቸው አይሰማም። ምክንያቱም ከኢሕአዴግ አይደሉማ።

አንድ ማስረጃ ልጨምር፤ አንድነት ፓርቲ ታህሳስ 20 ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤ የፓርቲው ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት ኢ/ር ግዛቸው ያገኙት ድምፅ የተከበሩ ግርማ ሰይፉ ካገኙት ድምፅ ከ10 እጥፍ በላይ ይበልጣል። እኚህ ሰው ናቸው እንግዲህ ከስልጣናቸው በውጭና በውስጥ ጫና የተባረሩት። አሁን በእርሳቸውና በትዕግስቱ አወል የሚመራው ቡድን ፓርቲውን ለማፍረስ “በኢሕአዴግ የተደራጀ” ተብሎ እየታማ ነው። በዚህ አይነት በኢሕአዴግ የውስጥ አርበኛነት ያልተጠረጠረና ያልተተቸ የአንድነት ፓርቲ አመራር የለም። ስለዚህ በየተራ ‘ኢሕአዴግ’ የተባሉትን አመራሮች ደምረን ብንቆጥራቸው አንድነት እንደፓርቲ ሌላ ‘ኢሕአዴግ’ ነው እንደማለት ነው።

ይህን የግል እምነቴን የሚያንፀባርቀው ፅሁፌን በአጭሩ ላጠቃልለው። የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚመሰርቱና የሚመሩ አባላትና አመራሮች ኢሕአዴግን የጋራ ጠላት አድርገው ከመነሳት ውጪ አንድ የሚያደርጋቸው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አላማ አለመያዛቸው መሰረታዊ ችግራቸው ነው። ከዛ በመለስ እስካሁን ያጋጠሟቸውን መለያየቶች በጥልቀት ለተመለከተ ገንዘብ ፊት ለፊት ጎልቶ የሚታይ የችግራቸው መንስዔ ነው። ፓርቲዎቹ ይህን ጉዳቸውን ለመሸፈን የሚጠቀሙበት አፈንጋጮችን ‘የኢሕአዴግ ተለጣፊ’ አድርጎ የማሳየት የዘወትር ሰበብ ግን ዉሃ የሚቋጥር አይደለም። “ፓርቲያችን ህግና አሰራርን እየጣሰ ነው” በሚል የራሳቸውን ቡድን የሚያደራጁት ግለሰቦችም የየራሳቸው ግለሰባዊ ችግር ቢኖርባቸውም ለፓርቲዎቹ መከፋፈል ሁነኛ መንስዔ አለመሆናቸውን እነሱ ከተባረሩ በኋላ እንኳን ሠላም ያለመውረዱ ማረጋገጫ ነው። ከዚህም መረዳት የሚቻለው ፓርቲዎቹ ስኳር በመላስ የሚፋጁ መሆናቸውን ነው፡፡

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
1468 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1024 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us