Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 390

ለተጠናከረ የሸማቾች ጥቅም መከበር ማኅበረሰባዊ ተሳትፎ እንዲጠናከር ተጠየቀ

Wednesday, 13 November 2013 13:10

ኅዳር 1 ቀን 2006 ዓ.ም

ጋዜጣዊ መግለጫ

 

የኢትዮጵያ ኮንሲዩመርስ ፕሮቴክሽ አሶሴሽን ከአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር ጋር በመተባባር ያዘጋጀው የፕሮጀክት አፈጻጸምና ማሳያ ፕሮግራም የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት፣ ወጣቶችና ሴቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት እሁድ ህዳር 1 ቀን 2006 ዓ.ም በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት አዳራሽ በተካሄደ ደማቅ ሥነ ሥርዓት ተከናወነ።

      ይህ ፕሮግራም ባሳለፍነው የ2005 ዓ.ም እንዲሁም 2006ን ጨምሮ በኢትዮጵያ ኮንሲዩመርስ ፕሮቴክሽን አሶሴሽን ተነድፈው እንቅስቃሴ ከተካሄደባቸው ሥራዎች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰውን የሸማቾችን ጥበቃ ማኅበረሰባዊ ተሳትፎ ለማሳደግና ለማጠናከር አልሞ የተቀረፀ የፕሮጀክት እንቅስቃሴ አተገባበርና አፈጻጸም ማሳያ መድረክና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በሸማቾች በኩል በግብይት ሂደት ችግር ካጋጠመ በጋራ መፍትሄ ማፈላለግ በሚቻልበት ዙሪያ የተካሄዱትን ውይይቶችና የተደረሱትን ስምምነቶች ጨምሮ በዋና ተሳታፊነት ከወጣቶች ጋር የተሠራው ሥራ ከፍተኛ የነበረ መሆኑን ለማስቃኘት ሲባል የተዘጋጀ ነው።

      የኢትዮጵያ ኮንሲዩመርስ ፕሮቴክሽን አሶሴሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘለዓለም ዘመዴ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር እንዳስታወቁት “በፍትሐዊ የንግድ ሥርዓት ውስጥ የሸማቾች ጥበቃ ጽንሰ ሀሳብ ተግባራዊነት የሚለካው ዜጎችና ማኅበረሰቡ በዕውቀትና በፍላጎት ላይ የተመረኮዘ ተሳትፎ ማድረግ የሚችሉበት ደረጃ ላይ ማድረስ በመሆኑ ሥራውን የማኅበረሰቡ ዋና ክፍል የሆነውን ወጣት በማስተማር ሰፊ ተሳትፎ ለመፍጠር ያስችል ዘንድ አቅጣጫ በማስቀመጥ ከአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር ጋር በመተባበር የፕሮጀክት አፈጻጸምና ማሳያ ፕሮግራሙን በጋራ እንዳዘጋጁት ገልጸዋል።” አያይዘውም “በሸማቹና በነጋዴው መካከል ጤናማ ግንኙነት እንዲሰፍን ለማድረግ የተጀመረውን ተስፋ ሰጪ ጥረት ወደተፈለገው ግብ ለማድረስ ብሎም የሸማቹን ማኅበረሰብ ጥቅም በማስከበር ሀገራዊ የልማት አጀንዳን ትርጉም ባለው መልኩ ለማገዝ የሚመለከታቸው አካላት የእንቅስቃሴው ተዋናይ በመሆን የበኩላቸውን ርብርብ ያደርጉ ዘንድ ጥሪ አስተላልፈዋል።”

      የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር የአቅም ግንባታና ኢኮኖሚ ዘርፍ ምክትል ፕሬዘዳንት ወጣት ዮሐንስ ጣሰው በበኩሉ ባስተላለፈው መልዕክት “በሕገ ወጥ መንገድ የተሳሰረ ጥቂት ሕገወጦችን ተጠቃሚ በማድረግ ልማትን የሚያደናቅፍ የንግድ ሥርዓት ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ አይጠበቅብንም። በንግዱ ዘርፍ ያለውም ሕገወጥነት የማስወገድ ጥረት የመላውን ሕዝብ ተሳትፎና ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ትልቅ ታሪካዊ ኃላፊነት በመሆኑ ይህን ኃላፊነት በመወጣት ዜጎች በንግዱ ዘርፍ እኩል ተፎካካሪ በመሆን ራሳቸውንና ሀገራቸውን የሚጠቅሙበትን የንግድ ሥርዓት መፍጠር ለነገ የምንለው የቤት ሥራ አይደለም ብሏል።”

      በዚሁ የፕሮጀክት አፈጻጸምና ማሳያ ፕሮግራም ላይ ከአዲስ አበባ ወጣቶ ማኅበር የተውጣጡ ወጣችና ሴቶች በአዲስ አበባ በተመረጡ ገበያዎች ላይ ማለትም በመርካቶ፣ በሾላና ሳሪስ ገበያዎች ላይ በግብይት ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችንና መፍትሔዎቻቸውን በተመለከተ ለ60 ሺህ ያህል ሰዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሰጥተዋል። በአሥሩም ክ/ከተሞች በተመረጡ 10 ወረዳዎች ላይ ከሸማቾች ጋር የምክክርና የቅሬታ ማሰባሰብ ሥራዎችን ሠርተዋል። በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት በተከናወነው ሥነ ሥርዓት ላይ አቶ ዳኛቸው ንጋቱ የአዲስ አበባ ሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊና ኢንጂነር ዘውዴ ተክሉ የቀድሞ ከንቲባና የአዲስ አበባ የነዋሪዎች ፎረም ሰብሳቢ በክብር እንግድነት የተገኙ ሲሆን ልዩ ልዩ ዝግጅቶች ከመቅረባቸውም ባሻገር ስለሸማቾች ጥቅም መከበር የሚዳስስ መጽሔት ተመርቋል። “ሸማች ሕይወት ልማት” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ አጭር የዶክመንተሪ ፊልም ለእይታ በቅቷል።

      በበርካታ ሀገሮች የተጠናከሩ የሸማቾች ማኅበራት ተደራጅተው ሸማቹን ኅብረተሰብ ዋጋው ያለአግባብ ከናረ፣ ጥራት ከጎደላቸው፣ በሸማቹ ላይ ጉዳት ከሚያደርሱ ምርቶች እንዲሁም ከአሳሳችና ሞራልንና ሕግን ከሚጻረሩ ማስታወቂያዎች በመከላከል ረገድ የበኩላቸውን ሚና ይጫወታሉ። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ኮንሲዩመርስ ፕሮቴክሽን አሶሴሽን በገበያ ሥርዓት መዛባት ሂደት ውስጥ ሸማቹ ኅብረተሰብ እያጋጠሙት ያሉትን ችግሮ በተደራጀ ሁኔታ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሥራት መፍትሄ ማፈላለግን ዋና ዓላማው አድርጎ ላለፉት 13 ዓመታት በመንቀሳቀስ ላይ ያለና የበጎ አድራጎት ድርጅቶችንና ማኅበራትን ለመመዝገብና ለማስተዳደር በወጣው አዋጅ መሠረት የኢትዮጵያ ነዋሪዎች የበጎ አድራጎት ድርጅት ሆኖ በመመዝገብ በተለያዩ ማኅበረሰባዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ልማታዊ ተግባራት ላይ ተሠማርቶ እየተንቀሳቀሰ ያለ ሲቪል ተቋም ሲሆን ከአፍሪካ ጥቂት ማኅበራት አባል በሆኑበት በኮንሲዩመርስ ኢንተርናሽናልም አባል ነው።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1044 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us