ሃናን የደፈራት ማህበረሰቡ ነው!

Wednesday, 03 December 2014 13:27

!

መላኩ ብርሃኑ

    

- ከሃናበፊትምብዙዎችንደፍሯል!

 

    

     የሃና የወሲብ ጥቃት ሰለባነት ዜና ብዙዎቻችንን አሳዝኗል። ከዚህ ቀደም ሃናን መሰል ብዙ እህቶቻችንና ልጆቻችን ነፍሳቸውን ባይቀሙም በወሲብ ጥቃት ሳቢያ ከሞት ጥቂት ከፍ ባለ፣ ከመኖር ግን ባነሰ የጤና፣ የስነልቡና፣ የመንፈስ ስብራት እና የአካል ጉዳት ችግር ተተብትበው ህይወት ጨልማባቸው ኖረዋል። ይህንን በአይኔ አይቻለሁ። ሌሎቹም እንዲያዩት ለማድረግ ሞክሬያለሁ። ያዘንኩትን ያህል እንዲያዝኑ፣ የቆጨኝን ያህል እንዲቆጫቸው፣ ያስቆጣኝን ያህል እንዲያስቆጣቸው ከሁሉም በላይ ሁሌም ልረሳው ያልቻልኩትን ያህል ሁሌም አንዳይረሱት ለማድረስ ጥሬያለሁ። የሙያ ባልደረቦቼም እንዲሁ ሲያደርጉ ኖረዋል።
     ለዓመታት የሰራሁበት የፖሊስ ጋዜጠኝነት ሙያ ከብዙ የወሲብ ጥቃት ሰለባዎች ጋር አገናኝቶኛል። የብዙ ህጻናትና አዋቂዎችን እንባ አይቻለሁ። እናቷ ለሱቅ ጠባቂዋ አደራ ትታት የሄደች 10 ወር ህጻን በዚሁ ጎረምሳ ተደፍራ ስትሰቃይ አይኔ አይቷል። እናቷ ደሟን አይታ እንዳትነቃበት ደፋሪው የህጻኗን ብልት በምላጭ ቆርጦ 'ምላጭ ቆረጣት' ብሎ ለማሳበብ ያደረገውን ኢሰብዓዊ ተግባርም እንዲሁ። የህጻኗ አባት ልጅቷ የተኛችበትን የሆስፒታል አልጋ ተደግፎ ስቅስቅ ብሎ ሲያለቅስ አብሬው አልቅሻለሁ። ይህች የ10 ወር ህጻን ምርር ብላ ስታለቅስ፣ ልጁ ግቢ ውስጥ ባለ ቧንቧ ወስዶ ደሟን ሲያጥብ ጎረቤቶች አይተዋል። ከእናትየው ጋር ጸብ ስለነበሩ ግን ዝም ነበር ያሉት። ይህንንም በሰራሁት ፕሮግራም በቁጭት አንስቼዋለሁ። ያቺ ህጻን የዕድሜ ልክ ፊስቱላ እና የማህጸን ችግር ተጠቂ እንደምትሆን ሃኪሙ እያለቀሰ ሲናገርም ለህዝብ አሳይቼዋለሁ።
     የ14 ዓመት ታዳጊዋ... የታመሙ እናቷን የምታደርጋቸው ብታጣ እያለቀሰች ከቤት የወጣች... በዚያው ፒያሳ ደላሎች ቤት ሄዳ ሰው ቤት ለመቀጠር የጠየቀች፣ ልቅጠራት ብሎ በ50 ብር ደሞዝ አስማምቶ የወሰዳት ባለመኪናና የሁለት ልጆች አባት በ50 ብር አስማምቶ ቤርጎ የከተታት፣ 3 ቀን ሙሉ ደረቅ ዳቦ እያበላ፣ እየተመላለሰ ጂን እየጠጣ የሃይል ጥቃት የፈጸመባት፣ አልጋ አከራዮች ተጠራጥረው ሲወጣ ጠብቀው በር ሲከፍቱ በደም ተበክላ ሸትታና ተጎሳቁላ ወድቃ ያገኟትን ያቺን ለጋ ህጻን አልረሳትም። ይህች ታማሚ እናቷን ለመርዳት የወጣች ደሃ አደግ ከማህጸን ጋር ለተያያዘ ከፍተኛ ችግር መጋለጧን ሃኪም ተናግሯል። እጆቿ በደረሰባቸው የመጠምዘዝ አደጋ ተልፈስፍሰዋል። የቤርጎዎቹ ሰራተኞች ግን ሰውየው ይዟት ሲገባ አይተው ዝም ብለዋል። በር ሳይከፈት 3 ቀን ሙሉ ስትቆይ እያዩ ዝም ብለዋል። በሽጉጥ ሲያስፈራራት የሚደርስላት አጥታ ስትጮህ ሰምተው ዝም ብለዋል። ይህንንም ለህዝብ አውርቼዋለሁ። ከለቅሶ እና ከአንድ ሰሞን ጉድ ጉድ በቀር ምን ተደረገ?
     የ60 ዓመቷ አዛውንት አገር አማን ብለው በአንድ ጭር ያለ መንገድ ለቅጠል ለቀማ ይሄዳሉ። ጎረምሶች መጡባቸው፣ በጠረባ መቷቸው፣ ወደቁ፣ ተፈራርቀው ደፈሯቸው። እኚህ ሴት የልጆች እናት ነበሩ፣ ለዚያውም የትላልቅ ልጆች እናት። ወገባቸው ተቀጨ፣ ሰውነታቸው አይታዘዝላቸውም፣ 'ምነው.. እናታቸው አልሆንም? ...እናት አንዲህ ትደረጋለች?' ብለው ሲያለቅሱ እያየሁ ላለማልቀስ መጣሬ ሞኝነት ነበር። እናቴ ብትሆንስ ብዬ እያሰብኩ የሚያወሩትን መስማት ሁሉ ተስኖኝ ነበር። ህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ፊርማ አሰባስቦ ሰላማዊ ሰልፍ የወጣው በዚያች ጨቅላ እና በእኚህ አዛውንት ላይ ፕሮግራም ከሰራሁ በኋላ ነበር። የሚገርመው ታዲያ ጎረምሶቹ እኚህን ሴት መድፈራቸውን ሰክረው ሲያወሩ ጠጪዎች ሰምተዋቸዋል። አንድም ሰው ግን ለፖሊስ አልተናገረም። ይህንንም ህብረተሰቡ ይማርበትዘንድ በፕሮግራሜ አካትቼው ነበር። የመጣው ለውጥ ምን ነበር? ከንፈር መጠጣ ብቻ!
     የሰው ቤት ተከራይታ የሙት ወላጆቿን አደራ ለመጠበቅ የ8 ዓመት ህጻን እህቷን የምታሳድግ ወጣት አንድ ቀን በሌለችበት አከራይዋ እህቷን ደፈረባት። ስታቃስት ደረሰች። ተደፋሪዋ ሰውየው ቤት የገባችው በአክስቱ ልጅ 'ነይና ቡና አፍዪ ' ተብላ ነው። ሴትየዋ ልጅቱን ለሰውየው አቅርባ ሄደች። ሰውየው አፍኖ ደፈራት። አሳዛኙ ነገር ኤች አይ ቪ ፖዘቲቭ ነው። እህት ይህንን ቁጭት ይዛ ፍርድ ቤት ለፍርድ ቤት ስትንከራተት ጎረቤቶች 'የመልካም ሰው ስም አጠፋች' እያሉ አይንሽን ለአፈር አሏት። ከአካባቢው አባረሯት። ኋላ ላይ ተሳክቶላት 18 ዓመት ስታስፈርድበት እያንሰቀሰቀ ያስለቀሳት ነገር ሰዉ ሁሉ ለተደፈረችው ደሃ እህቷ ሳይሆን ጨዋ ለተባለው ሰውዬ ጠበቃ መቆሙ ነበር። ማህበረሰቧን ጠላችው። ታማሚ እህቷን ታቅፋ እንጦጦ ጸበል ገብታ ቀረች።
     እንዲህና ይህንን የመሳሰሉ ባላጋንነው ከ50 በላይ የሚደርሱ ዘግናኝና ራስ የሚያዞሩ የወሲብ ጥቃት ፕሮግራሞችን ሰርቻለሁ። ብዙዎቹ ወንጀል ፈጻሚዎች ማህበረሰቡ ምንም እንደማያደርጋቸው፣ ቢያያቸውም አጋልጦ እንደማይሰጣቸው ያምናሉ። በዚህ ተማምነውም እህቶቻችንን፣ ልጆቻችንን ይደፍራሉ። ማን አንቅሮ ተፋቸው? ማን አወገዛቸው? ሁሉም በኔ ካልደረሰ ብሎ ዝም ጭጭ ነው።
     እነሆ ዛሬ ደሞ ሃና ስትደፈር ጎረቤት እያየ ዝም አለ ተባለ። የትናንት ማንነታችን ውጤት ነው። አሁንም ያው ነን። አልተለወጥንም። ህጋችን ወንጀል ሲፈጸም አይቶ ዝም ያለን የሚቀጣበት አንቀጽ አለው። ፖሊስ ማንን ሲከስስ አየን፣ ፍርድ ቤት ማንን ሲቀጣ አየን፣ ማንንም!!
     እናም ሃናንም ...ከላይ ባወራኋቸው በራሴ ገጠመኞች መነሻነት ሃናንም ይሁን ሌሎች እህቶቻችንንና ልጆቻችንንም የደፈረው ማህበረሰቡ የሚል አቋም ይዣለሁ። ጥፋትን አይቶ ዝም የሚል ማህበረሰብ አጥፊን ፈልፋይና አሳዳጊ ነው። አጥፊው እስኪደርስበት ምን አገባኝ ብሎ ቁጭ ያለው ማህበረሰብ የችግሩ መፍትሄ መሆን ከቶም አይችልም። ስራ ይጀመር ከተባለ መጀመር ያለበት ከዚህ ነው። በኔ ግምት ለሃናና ለሌሎቹም እህቶቻችን ጥቃት ተጠያቂዎቹ 'ጉች ጉች ያለ ጡት...' ከሚለው ዘፈናችን ያልተላቀቅነው፣ ያዝ እጇን ከሚለው ግጥም ያልተላቀቅነው.. እኛው ራሳችን ነን ...ለእኔ ከፈጻሚው ይልቅ ሲፈጸም አይቶ ዝም ያለው ትልቁ ወንጀለኛ ነው!! አሁንስ አይበቃንም! ነግ በኔ የሚለው ተረታችን ወሬያችንን አድማቂ ብቻ ሆኖ መቅረቱ አይበቃም?

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
1547 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1019 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us