መሪ አልባው ፓርቲ - 2

Wednesday, 29 October 2014 15:17

በአፈወርቅ በደዊ

E-mail- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Blog: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.


መቅድም

እኔ የምወደውን፣ የማከብረውን እንዲሁም ስለጥቅሙ እና ስለክብሩ አስፈላጊውን መስዋዕትነት የምከፍልለትን የሃገሬን ህዝብ ጥቅም አስበልጬ ፃፍኩ። ከእዚህ በፊትም የፃፍኩትም ሆነ ከዚህም በኋላ የምፅፈው እውነት ነው። እውነትን ስናገር የእውነትን ዋጋ በሚገባ አውቃለሁ። ያንንም ለመክፈል ዝግጁ ነኝ።

ከዚህ በፊትም እንዳልኩት አሁንም የምደግመው ትችቴን የሰነዘርኩት በሰማያዊ ፓርቲ የሥራ አስፈፃሚ (ሁሉንም ላያካትት ይችላል) አባላት ላይ ሲሆን ሁሉም ልቦናው የሚያውቀውን እና ይገባኛል የሚለውን ብቻ ይወሰድ። እንደሌለ እርግጠኛ ብሆንም ባለቤት የሌለው ትችት ካለ ወደ እኔ ይመለስ። ይህ ችግር አለ ብሎ ለመፃፍ ያላፈረው ብዕሬ “ተሳስቻለሁ” ለማለት የሚያፍር አይመስለኝም። “ለምን ተባለ? የት ተባለ? ወይም እንዴት ተባለ?” እና የመሳሰሉት ጥያቄዎች ወደ መፍትሔ ሊያደርሱን ስለማይችሉ “ምን ተባለ?፣ ከተባለውስ የትኛው እውነት ነው? የትኛውስ ውሸት ነው? መፍትሔውስ ምንድን ነው?” እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ከግምት እያስገባን መነጋገር እስካልቻልን ድረስ ችግሩን መፍታት የሚቻለን አይመስለኝም። በተባለው ነገር ላይ ትኩረት አድርጎ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው ብቻም ሳይሆን ማንኛውም ግለሰብ የተሰማውን መፃፍ ይችላል።

እዚህ ጋር ሳልጠቅሰው ማለፍ የሌለብኝ ፓርቲው በሰማያዊው ጃንጥላው ስር ያስጠለላቸው ስለ ሃገራቸው መልካም ራዕይ ያላቸው እንዲሁም የሃገራቸውን ነፃነት በደም እና በአጥንታቸው መሰዋዕትነት ጭምር ለመዋጀት የቆረጡ አባላት እና ደጋፊዎች ያሉበት ፓርቲ ነው። ስለዚህም እነዚህን አባላት በስሩ ላቀፈ ፓርቲ አሁንም አክብሮቴ ከመቼውም ጊዜ በላይ የላቀ ነው። ነገር ግን አባላት እና ደጋፊዎች የተጠለሉበት ጃንጥላ ሃላፊነት በማይሰማቸው ጥቂት ግለሰቦች እጅ ስለሆነ አባላቱ እና ደጋፊው ለዝናብ እና ለፀሐይ ተጋልጧል። አሁንም እደግመዋለሁ “ይህ ሃሳብ ስህተት ነው” የሚል አካል ካለ እኔን ብቻ ሳይሆን በእኔ ስህተት የተሳሳተውን ህብረተሰብም ጭምር የማረም ሃላፊነት ስላለበት ይህንን ግዴታውን እንዲወጣ አበክሬ አሳስባለሁ።

መልካም ንባብ

        

መግቢያ

በቅድሚያ የዚህን ፅሑፍ የመጀመሪያውን ክፍል ተመልክታችሁ የተለያየ አይነት (የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ) አስተያየታችሁን በተለያየ መንገድ ለገለጣችሁልኝ ልባዊ ምስጋናዬን እያቀረብኩ ባለፈው ሳምንት የሰማያዊ ፓርቲ አመራር ከአባላቱ መካከል የሚፈጠርበትን የፖለቲካ ውጥረት ለማርገብ የሚጠቀምባቸው ስልቶች በከፊል ለመዳሰስ ሞክሬያለሁ። በባለፈው ሳምንት ፅሑፌ የፍረጃ ፖለቲካን እና ስብሰባን የመበጥበጥ አካሔድን እንደ ውጥረት ማርገቢያ ስልት በጥቂቱም ቢሆን አንስቼው እንደነበር ይታወሳል። በዚህ ክፍል ደግሞ ተጨማሪ የአመራሩን ድክመቶች እንመለከታለን።

ባለፈው ሳምንት ካነሳኋቸው በተጨማሪ ሌላኛው የፓርቲው አመራሮች የተለየ ሃሳብ አራማጆችን ለማስወገድ እና የሚፈጠርባቸውን የፖለቲካ ውጥረት ለማርገብ የሚጠቀሙበት እስትራቴጂ “የእገዳ ፖለቲካ”ን ነው። የትኛውም የአመራሩን መስመር ወይም ከላይ ወደ ታች የሚለውን ያረጀ መርህ ያልተከተለ ግለሰብ አሊያም ቡድን በአመራሩ በፓርቲው ካለው የስራ ድርሻ (ከአባልነትም ቢሆን) እንዲታገድ ይደረጋል። በተለይ በስራ አስፈፃሚ አባልነት እና በቋሚ ኮሚቴ አባልነት ያገለግሉ የነበሩ መስራች እና ቀደምት አባላት ላይ ይህ እርምጃ መወሰዱን በፓርቲው ዙሪያ የሚገኙ ሁሉ የሚያውቁት ነው። እንደምሳሌ ለማንሳት ያክል የፓርቲው መስራች እና የሴቶች ጉዳይ ኃላፊ የነበሩት ላይ የተወሰደውን እንዲሁም በቅርቡ የፓርቲው ምክር ቤት እና ድርጅት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባል በነበረ ወጣት የፓርቲው ቀደምት አባል ላይ የተወሰደው የእግድ እርምጃን ማንሳት ይቻላል።

በየትኛውም የፖለቲካ ተቋም ውስጥ ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ቡድን የፈለገውን አስተሳሰብ የማራመድ መብት ሊኖረው ይገባል። ይህ መብቱ በማንኛውም መንገድ ሊገልጥ የሚችል ሲሆን ይህንን መብት የማገድ ስልጣን ያለው አንዳችም አካል ሊኖር አይገባም። አንድ ሰው የተለየ ሃሳቡን እንኳ በተለያየ መንገድ መግለፅ ሳይችል ምን አይነት ከኢህአዴግ የተለየ ዲሞክራሲ ለማምጣት እንደምንታገል አይገባኝም። ይህ የተለየ አስተሳሰብን በግልፅ የማራመድ ፍራቻ አባላቱ እስከማሸማቀቅ የደረሰ ሲሆን አብዛኛውን አባላት ሃሳባቸው ማንነታቸውን ደብቀው (በብዕር ስም በመጠቀም ጭምር) በተለያየ መንገድ እና በተለያየ ቦታ እንዲገልጡ አስገድዷል። የአባላት መብት እንደ ኢህአዴጎቹ እየገደቡ ኢህአዴግን መታገል ፈፅሞ አይቻልም። ቢቻልም ሌላ ኢህአዴግ (በግብር አንድ አይነት በስም ብቻ የተለየ) ከመፍጠር የዘለለ ለውጥ አያመጣም። ዋናው እና ትልቁ ነገር ትግላችን የተመሰረተው “ለምን እንታፈናለን?” በሚል ጥያቄ አዘል መርህ ላይ ወይስ “ለምን በወያኔ እንታፈናለን?” በሚል መሰረት ላይ ነው? ብለን እራሳችን መጠየቅ ይገባናል።

በሌሎች እጅ መታፈንን የሚጠላ ሰው በእራሱ እጅ ማፈንን ሊጠየፍ ይገባል። በሌሎች እግር መረገጣችንን ከመኮነናችን በፊት እግራችን የት እና ምን ላይ እንደቆመ ማስተዋል ተገቢ ነው። እኛ እያፈንን አልታፈንም ማለት፣ እኛ እየረገጥን አንረገጥም ማለት እንዲሁም ጎሰኝነትን ጠባብነትን እየኮነንን እራሳችን ከዛም ጠበን ጎጠኛ እና መንደርተኛ መሆን እጅግ ይጎፈንናል። መደረግ የሌለበትን ነገር መታገል ባለማድረግም ጭምር ነው። ኢህአዴግ እንደ መንግስት የተለየ አስተሳሰብ እና አማራጭ ያላቸውን ቡድኖች ሃሳባቸውን የሚያራምዱባቸውን ቀዳዳዎች ሁሉ ለመድፈን የሚያደርገው ጥረት በእውነት የሚያመን ከሆነ ይህንን አለማድረግን በእራሳችን ቤት እንጀምር። የተለየ አስተሳሰብ ወይም አማራጭ መንገድ ያላችውን ሰዎች ሃሳባቸውን እንዳያራምዱ ስብሰባ እየበጠበጥን እንዲሁም እያገድን እና እየፈረጅን እንዴት ተብሎ ከዛሬ የተሸለ ነገን ማሰብ ይቻላል። በሃገራችን ውስጥ ያውን የተለያዩ አስተሳሰቦች የሚራመዱበት የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋት ዘመቻ በቤታችን ውስጥ ያለውን ምህዳር በማስፋት መጀመር ይኖርበታል።

ሕዝባችን ኢህአዴግን ከስልጣን ለማውረድ ከሰዓታት በላይ እንደማይወስድበት ኢህአዴግም ሆነ ተቃዋሚዎቹ በሚገባ እናውቃለን። ነገር ግን ህዝብ ይህንን ተግባር ከመፈፀሙ በፊት ነገን አሻግሮ ይመለከታል። ተኩላውን ለመተካት በአማራጭነት የቀረቡት ሁላ የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች ወይም የባሱ እንደሆኑ ሲረዳ “ቀን እስኪያልፍ ያባቴ አሽከር ያግባኝ” እንዳለችው ወይዘሮ ነገን ተስፋ አድርጎ በዝምታ ይታገሳል። ህዝብን “አምባገነን አንሆንም፣ አንጨቁንም፣ አንበድልም፣ ፍትህ አናጓድልም…” እናም ሌሎችን እያነሳን ምራቁን ብናስውጠው ከቃላችን አሻግሮ ቤታችንን ይመለከታል። በየትኛውም (በሃይልም ሆነ በሰላማዊ) መንገድ ሃገርን ያክል ትልቅ ነገር አሳልፎ በእጃችን ከመስጠቱ በፊት በቤታችን ከላይ የዘረዘርናቸው አለመኖራቸውን ያስተውላል።

እውን በቤታችን አፈናው፣ ኢ-ፍትሃዊ ድርጊቱ፣ ….እና ሌሎችም ተግባራት የሉም? እንደ ኢህአፓ እና መኢሶን ያልተጋደልነው እንዲሁም እንደ ደርግ እና ወያኔ ያልገደልነው እና ያላጋደልነው ለምን ይሆን? ስለማንፈልግ ወይስ መሳሪያው ስለሌለን? ጅብ አህያን “አልበላሽም ነይ” ቢላት “መምጣቱንስ እመጣለሁ፤ ግን አልበላሽምን ምን አመጣው” አለች አሉ። ሰው አብሮ በሚሄድ ቃል እና ተግባር እንጂ እንደሾርባ በማንኪያ አይቀመስም። ተግባራችን እና ቃላችን ለየቅል ከሆነ አሊያም ጥቂት ሰርተን ብዙ የምናወራ ከሆነ ህዝቡ “አልበላሽምን ምን አመጣው” ማለቱ አይቀርም።

ደርግም ሆነ ኢህአዴግ ስልጣኑን ሲይዙ እኛ አሁን እያልነው ያለውን ሁሉ ሲሉት ነበር። “የተለያየ አስተሳሰብ የሚራመድበት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንፈጥራለን” የሚለው የኢህአዴጎቹ ንግግር መክፈቻ ነበር። ነገር ግን ዞር ብለን የመጡበትን እና ያለፉበትን መንገድ ስንመለከተው ፈፅሞ ከዚህ ቃላቸው ጋር የሚመሳሰል አይደለም፤ የሚቀራረብ አንድም ተግባር አልነበራቸውም። ስንቶች በተኙበት የታረዱት እኮ ለምን የተለየ አስተሳሰብ አራመዳችሁ ተብለው ነው። ስንቶች ጀግኖች እንደፈሪ ጀርባቸውን በጥይት የተደበደቡት፤ ወደወህኒ የተጋዙት የያዙትን የተለየ አስተሳሰባቸውን ጠረጴዛ ጋር ከመድረሱ በፊት በአጭሩ ለመቅጨት ነበር። ታዲያ እኛስ በምን ተለየን? ቃላችን ከግብራችን ፍየል ወዲያ አልሆነም?

“አዲስ ፓርቲ??”

እጅግ ብዙ ጊዜ ከፓርቲው አመራር የሚሰማው “ሰማያዊ ፓርቲ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አዲስ መንገድ ይዞ የመጣ ፓርቲ ነው” የሚለው ነገር ነው። በመጀመሪያ “አዲስ” ማለት ምን ማለት ነው? በእራሴ እይታ ስመለከተው አንድ ነገር በሁለት መንገድ አዲስ ሊባል ይችላል። አንደኛው በተመሳሳይ ተግባር ላይ የተሰማራ በእርሱ ስም የሚጠራ ሌላ ድርጅት ወይም ተቋም አለመኖር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በተመሳሳይ ተግባር ላይ የተሰማራ በእርሱ ስም የሚጠራ ሌላ ድርጅት ወይም ተቋም አለመኖር ብቻ ሳይሆን ይህም ድርጅት ሌሎች ከሚሔዱበት መንገድ የተለየና የተሻለ አካሔድ ሲኖረው ነው። ታዲያ ሰማያዊ ፓርቲ እራሱን በየትኛው አዲስ ውስጥ እንደሚያካትት አላውቅም። ስለዚህ በእኔ አስተሳሰብ ሰማያዊ ፓርቲ አሁን ባለው አመራር ስር በትላንት በሬ የሚያርስ እና ስኬታማ ባልሆነው የሃገራችን ፖለቲካ የትላንት መንገድ የሚሔድ የስም አዲስ ፓርቲ ነው።

ሰማያዊን ከሌሎች ምን ይለየዋል?

  1. ለወጣት እና ሴቶች “በሰጠው ትኩረት”

በኢትዮጵያው ውስጥ ያለው ፖለቲካዊ ችግር እና የፖለቲካው ችግር ነፀብራቅ የሆኑት ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በህብረተሰቡ ውስጥ የሚያደርሱት ጫና ያለምንም የጎሳ፣ የፆታ እና የእድሜ ልዩነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ህልውና ላይ በትሩን አሳርፏል። ይህንን ችግር ዳግም በማያንሰራራበት ደረጃ ለመቀልበስ የሚፈልግ የፖለቲካ ተቋም አብዛኛው (ከ65 እስከ 70 በመቶ) የህዝብ ክፍል ወደሚያካትተው “ወጣት እና ሴት” ማድላቱና ለእነዚህም የህብረተሰብ ክፍሎች ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀሱ ተደራሽነቱን ለማስፋት እንዲሁም እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች በማህበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ተፅዕኖ የመፍጠር አቅም ከግምት በማስገባት የማስፈፀም አቅሙን ለማጎልበት ትልቅ ድርሻ ማበርከት እንደሚችል ይታመናል። የሰማያዊ ፓርቲም በወረቀት ላይም ቢሆን ይህንን ከግምት ውስጥ አስገብቶ ለመንቀሳቀስ ያደረገው ሙከራ ሊያስመሰግነው ይገባል።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ወጣትን (ያለ ምንም የፆታ ልዩነት) በከፍተኛ ደረጃ በማደራጀትም ሆነ በግብዓትነት በመጠቀም የ1960ዎቹን ቀዳሚ ናቸው። እስከ አሁንም ድረስ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የ60ዎቹን ፖለቲካ ተቋማት ያክል የወጣቶች በጥቅም ላይ ያዋለ አንዳችም የፖለቲካ ድርጅት የለም። ትላንት ኢህአፓ እና መኢሶን ትኩረት ሰጥተው በተግባር የታየ እጅግ እልፍ ወጣቶችን ከጎናቸው ማሰለፍ ችለው ነበር። ነገር ግን እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች በወጣቱ መጠቀም የሚችሉትን ያክል መጠቀም ሳይችሉ በመቅረቱ እንዲሁም በወቅቱ የነበረውን ወጣት አላስፈላጊ መሰዋዕትነት በማስከፈሉ ለዛሬው ወጣት ከፖለቲካው ጎራ መሸሽ የጎላውን ድርሻ እንዲወስድ አስችሎታል። አብዛኛው የአሁኑ ወጣት ወላጆችም በወቅቱ ወጣቱ የእሳት እራት እየሆነ ላላስፈላጊ መሰዋዕትነት ሲውል የተመለከቱ እና በፈጣሪ ቸርነት የተረፉ ስለሆኑ ደፍረው ልጆቻቸውን ወደ ትግል ለማሰማራት ድፍረቱ ሊኖራቸው አይችልም።

በዛን ወቅት የነበሩ የፖለቲካ ተቋማት ትልቁ ችግር ወጣቱን በጥቅም ላይ ማዋላቸው አልነበረም፤ የእነዛ ተቋማት ትልቁ ችግር ወጣቱን ለመሰዋዕትነት ማዘጋጀታቸው አልነበረም፤ የእነዛ ተቋማት ትልቁ ችግር ሁሉን አቀፍ የትግል ስልት መምረጣቸው አልነበረም፤ የእነዛ ተቋማት ትልቁ ችግር የከተማ ውስጥ የትጥቅ ትግልን እንደ አማራጭ ትግል ስልት ይዘው መቅረባቸው አልነበረም። የእነዛ ተቋማት ትልቁ ችግር ወጣቱን ትንሹን መሰዋዕትነት ሲያስተምሩት ትልቁን መሰዋትነትን መርሳታቸው ነበር። ከመሰዋዕትነት ሁሉ ትንሹ ሞት ሲሆን ከመሰዋዕትነት ሁሉ ትልቁ የብዙሃን ሃሳብን የበላይነትን አምኖ ለመነጋገር ፍቃደኛ መሆንን እና የሃሳብ የበላይነት የሚያስከትለውን ሽንፈትን አምኖ መቀበል ነው። ስለዚህ በአባልነት ያቀፍናቸው ወጣቶች ስንቶቻቸው በመነጋጋር ችግሮች እንደሚፈቱ ያምናሉ? ስንቶችስ ያውቃሉ? የሃሳብ ልዩነት በመነጋጋር እንደሚፈቱስ በቃል ሳይሆን በተግባር አሳይተናቸዋል ወይ?

ስለዚህም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያልነበረው ወጣቶች እና ሴቶችን መሰረት አድርጎ የመመስረት ችግር አይደለም። ትላንትም ያለው እስከ አሁን የቀጠለው ያለመነጋገር እና በመነጋገር ችግሮችን ያለመፍታት ችግር ነው። ዛሬ “በወጣቶች እና ሴቶች ተመስርተናል” የሚለው ሳይሆን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አዲሱ ነገር “በመነጋጋር ችግሮችን እና ልዩነቶችን በመፍታት በሚያምኑ ወጣቶች እና ሴቶች ተመስርተናል” የሚለው ነው። እንደው ሌላው ሁሉ ይቅር እውነቱን ለመናገር በፓርቲው ውስጥ በተግባር ይቅርና በወረቀት ላይ በወጉ ስማቸው የሰፈረ ስንት መቶ ወጣት እና ሴት አባላት በፓርቲው ውስጥ እንዳሉ ደፍሮ ሚናገር አለ? ካሉትስ ውስጥ ምን ያክሉ የፓርተውን ፕሮግራም እና መተዳደሪያ ደምብ በቅጡ ያውቁታል?

2. ለሰላማዊ ሰልፍ የሰጠው ትኩረት

ህዝባችን ከ1966ቱ አብዮት ቀደም ብሎ በተለያዩ መንገድ በመንግስት ላይ ያለውን ተቃውሞ ሲገልጥ ኖሯል። ከእነዚህም መንገዶች ዋነኛው በወቅቱ የነበረውና አድራጊ ፋጣሪ የሆነውን ዘውዳዊ ስርዓት በመቃወም በተለያዩ አከባቢዎች በሚደረጉ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ዋነኛ ነበረ። እነዚህ የተቃውሞ ሰልፎች አብዛኞቹ መጨረሻቸው በዘውዳዊ ስርዓቱ ጠባቂዎች ጋር የሚደረግ ግብግብ ነው። በእነዚህ ግብግቦች ህዝቡ የአካል እና የህይወት ዋጋ እንዲከፍል ሆኗል። የወቅቱ ዋነኛ ጥያቄ የነበረው ህዝባዊ ተጠቃሚነት ነው። የተለያዩ ፀሐፍት ይህንን ወቅት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ‹‹ዘመነ ህዝብ›› ብለው ይጠሩታል። ስያሜውም ይህንን በቀጥታ በህዝብ ስም ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መሻሻልን የሚጠይቅ፣ ህዝብን የሃገር ሃብት እና የፖለቲካ ስልጣን ባለቤት አድርጎ የሚያቀርበውን፣ በአዲስ የፖለቲካ አተያይ የታጀበውን የሃገራችንን አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ የሚያመላክት ነበር።          

በተለይም ንጉሱ ወደ መንበረ ስልጣኑ ከመጡ በኋላ በየክፍላተ ሃገሩ የነበረውን መሳፍንት እና መኳንንት መና ያስቀረ ሃገራዊ አስተዳደርን ከማዕከሉ የሚዘውር ዘመናዊ ቢሮክራሲ በተከሉበት ዘመን ያኮረፈ መኳንንት እና መሳፍንት እንዲሁም ተያይዞም በሃገሪቷ የተከሰተው ማህበራዊ ቀውስ እና አለመረጋጋት፤ ስልጣን ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚያስችል ደረጃ ወደ ማዕከል የተጠቀለለበት ሁኔታ በመፈጠሩ ይህንንም ተከትሎ አብዛኛው የመሳፍንቱ እና የመኳንንቱ ሹመኛ እና ጀሌ እንዲሁም ንክኪ ከስልጣኑ እና ከጥቅሙ እንዲነቀል የተደረገበት ብሎም አብዛኛው ሰው በተስፋ የሚኖርበት፣ በችሎታ እና በጥረት ማህበራዊ ቦታውን ሊያሻሽል የሚችልበት እድሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ በጣም እየጠበቡ መምጣታቸው ይህም ያስከተለው የስብዕና መሸበር አስፈሪ እና አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ህዝቡን ተቃውሞውን በሰላማዊ ሰልፍ እንዲገልጥ አድርጎታል። በወቅቱ የንጉሱ ወታደሮች በተለይም በአዲስ አበባ የሚካሔደውን ተቃውሞ ሰልፍ ለማፈን የተቻላቸውን ያክል የሃይል እርምጃ ቢወስዱም አመፁ ግን እንደ ሰደድ እሳት አንድ ቦታ የጠፋ ሲመስል ሌላ ቦታ ብቅ ሲል እስከ አብዮት ድረስ ተጉዟል።

ደርግም በግርግር እጁ ላይ የወደቀውን ስልጣን ከያዘ በኋላ ካደረገው ጥብቅ ቁጥጥር አንፃር ብዙ ሊባሉ የሚችሉ የተቃውሞ ሰልፎች ቢደረጉም መንግስት በሚወስደው እርምጃ ከፍተኛ የህይወት መጥፋት እና የአካል ጉዳቶች ተከስተዋል። በወቅቱ የደርግ መንግስት ስልጣኑን ከተረከበ ጀምሮ ከወያኔ መንግስት ባልተናነሰ እጅግ ከፍተኛ አፈናዎችን ያካሔደ ቢሆንም ህዝቡ ይህንን ሁሉ ተቃውሞ እንቅስቃሴውን ማድረጉ አልቀረም።

የወያኔ መንግስትም በተራው ስልጣኑን ከተቆናጠጠ በኋላ በወረቀት ላይ ካሰፈረው በተቃራኒ በሃገሪቷ ከደርግም ሆነ ከንጉሳዊ ስርዓቱ የባሰ አፋኝ ስርዓት ተግባራዊ አደረገ። የአገዛዝ ስርዓቱ ለስልጣኑ አስጊ ይሆናሉ ያላቸውን ማናቸውም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ለማኮላሸት እና ስልጣኑን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ማንኛውንም ቀዳዳ ለመድፈን ያስችለው ዘንድ ሁሉም በሃገሪቷ ውስጥ የሚደረጉ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በሙሉ በመንግስት ቁጥጥር እና ይሁንታ ስር እንዲሆኑ አድርጓል። ይህም የሃገሪቷን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እጅጉን እንዲዳከም ያደረገ ቢሆንም ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት ሳይቻለው ቀርቷል። እስከ ምርጫ 1997 ድረስ ከፍ ዝቅ ሲል የነበረው የሃገራችን ፖለቲካ ከእንቅልፉ ድንገት የባነነበት እና በየአካባቢው ያለው ህዝብ በመንግስት ላይ ያለው ተቃውሞ እና ቅሬታ በአደባባይ ወጥቶ ያሳየበት በተለይም በመሃል ሃገር አከባቢ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የተቃውሞ ሰልፍ አድርጓል። ይህንንም ተከትሎ በተካሔደው ምርጫ መንግስት እጅግ አሳፋሪ ሽንፈትን ቢከናነብም ለመቀበል ፍቃደኛ ካለመሆንም በተጨማሪ በአዋጅ የህዝቡን ዲሞክራሲያዊ እና ሰብዓዊ መብት ያገደበት ሁኔታ አስከተለ። ህዝቡም አዋጁን እየጣሰ መንግስት የህዝቡን ዲሞክራሲያዊ ድምፅ ላለመቀበል ያሳየውን እምቢተኝነት በያከባቢው ለመቃወም ያደረገው እልህ አስጨራሽ እንቅስቃሴ ከመንግስት ስልጣን ጠባቂዎች በሚተኮስ ጥይት አካሉን እና ውድ ህይወቱን ለመገበር ተገዷል።

ይህንንም ተከትሎ የአገዛዝ ስርዓቱ ህዝባዊ ድጋፍ እንደሌለው በሚገባ ስለተረዳ በድህረ-97 የሚደረጉ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ላይ በጥርጣሬ አይኑ እንዲያይ ያደረገው በመሆኑ እና ይህንንም ተከትሎ በወጡ አፋኝ ህጎች እና አዋጆች በሃገሪቷ ያለውን የተቃውሞ ጎራ ለማሽመድመድ ያስቻለው እና የተቀሩትም የመንግስት ካድሬዎች መፈንጫ እንዲሆኑ ተደርጓል። የሃገሪቷ ፖለቲካ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንደዳለ በአንድነት ፓርቲ ውስጥ በተከሰተ የሃሳብ እና የአካሔድ አለመግባባት ተከትሎ ከአንድነቱ ያፈነገጡ ጥቂት ወጣቶች እራሳቸውን በማደራጀት ሰማያዊ ፓርቲ መሰረቱ።

ይህም ፓርቲ ከቅድመ 97 ምርጫ በኋላ ከተደረጉ ሰልፎች በተለየ ሁኔታ ብዙ የአዲስ አበባ ነዋሪ የተሳተፈበት በመንግስት እውቅና የተሰጠው ሰልፍ በማድረግ በአዲስ አበባ እና አካባቢው ህዝብ ልብ ውስጥ ለመግባት ቻለ። እዚህ ጋር የሰልፉ አዘጋጆች ሰልፉ ለማድረግ ከመንግስት ጋር ያደረጉትን ትንቅንቅ ሳላደንቅ አላልፍም። የዚህ ሰልፍ ህዝባዊ ድጋፍ በፓርቲው የወደፊት ጉዞ ላይ የራሱን መልካም አሻራ ማሻረፍ የቻለ ቢሆንም በአብዛኛው የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ እና ሎሌዎቻቸው ዘንድ ግን ሰልፉ ለወደፊት ስኬታማ ጉዞ ከማትጋት ይልቅ እንዲኮፈሱ እና ለእያንዳንዷ ችግር እጅግ ብዙ ወጪ ያስከተሉ ተደጋጋሚ እና ተመሳሳይ ተቃውሞ ሰልፎችን እንደመፍትሔ ማቅረብ አስቻላቸው።

ፓርቲው አሁን ባለው አመራር ስር ያደረጋቸው የሰላማዊ ሰልፎች ቁጥር ከአንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የስብሰባ ቁጥር ጋር ይስተካከላል። በአንድ በኩል ይህ እንደ አንድ እመርታ ሊወሰድ የሚችል ቢሆንም ፓርቲውን ግን ሰላማዊ ሰልፍን ለእያንዳንዱ ችግር መፍትሔ አድርጎ መንቀሳቀሱ የአመራሩን የማገናዘብ አቅም እጦት ያመላክታል። ሰላማዊ ሰልፎቹ ካመጡት መፍትሔ ይልቅ ያስከተሉት ወጪ ፓርቲውን እጅግ እንዲዳከም አድርገውታል። ለምሳሌ ለሰላማዊ ሰልፍ ማስፈፀሚያ ተብሎ በመቶ ሺኅ ብሮች ወጪ እየተደረጉ በነበረበት ወቅት ፓርቲው በተለያዩ የሃገሪቷ ክፍሎች ከፍቷቸው ከነበሩ በጣት የሚቆጠሩ ቢሮዎች ውስጥ አብዛኞቹ (ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚቻልበት ደረጃ) የቢሮ ኪራይ መክፈል ተስኗቸው እንዲዘጉ ተደርገዋል። ፓርቲው ለሰላማዊ ሰልፍ የሰጠውን ትኩረት ያህል መዋቅራዊ ስፋት እና ጥንካሬ ለመፍጠር ታትሮ መስራት ቢችል ኖሮ ዛሬ በአብዛኛው የሃገሪቷ ክፍል በሚገባ የተደራጀ የጠንካራ እና የሰፊ መዋቅሮች ባለቤት መሆን በቻለ ነበር።

የሰማያዊ ፓርቲ መዋቅራዊ ስፋት እና ጥንካሬ

የአንድ ፓርቲ ጥንካሬ መሰረቱ በየክፍለ ሃገሩ የከፈታቸው መዋቅሮች ስፋት (ብዛት) እና ጥንካሬ ነው። የመዋቅሩ ስፋት ፓርቲው በሃገር አቀፍ ደረጃ ያለውን ተደራሽነት እንዲሁም የመዋቅሩ ጥንካሬ ደግሞ አባላቱ የፓርቲው ሃገራዊ አላማ አውቀው ለተፈፃሚነቱ ያላቸውን ፅናት እና ቁርጠኝነትን ያሳያል። የአንድ ፓርቲ አመራር ከፍተኛ የስራ ድርሻ ሊሆንም የሚገባው ፓርቲውን በሃገር አቀፍ ደረጃ በማይናወጥ የፀና መሰረት ላይ መገንባት ነው። በየትኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በማለፍ የፓርቲውን አላማ ከግብ የሚያደርስ አባል የሚፈጠረው ከሰፊ እና ጠንካራ መዋቅር ነው። እነዚህ ሁለት ነገሮች ጎን ለጎን የሚሔዱ ሲሆን አንዳቸው ያለ አንዳው ትርጉም የላቸውም። አንዳንድ ፓርቲዎች ሰፊ መዋቅር ሲኖራቸው በእነዚህ መዋቅሮች ስር ያሉ አባላት ጥንካሬ እጅግ ደካማ ይሆናል። አንዳንዴ ደግሞ ጠንካራ አባላት እና ደጋፊዎች ያሉት ፓርቲ እረኛ እንዳጣ መንጋ በየሜዳው የተኩላ ሲሳይ ሲሆን ይስተዋላል። ስለዚህ አንድ ፓርቲ ጠንካራ ነው ለማለት የሰፋ እና የጠነከረ መዋቅር ባለቤት መሆን አለበት።

የሰማያዊ ፓርቲው አመራር ድክመት እንደመስታወት ቤት ግልፅ አድርጎ የሚያሳየው የፓርቲው መዋቅራዊ ስፋት እና ጥንካሬን ነው። ፓርቲው ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ በምስራቅ የሃገሪቷ ክፍል አንድ፣ በደቡብ አንድ ወይም ሁለት እንዲሁም በሰሜን የሃገሪቷ ክፍል ሁለት ወይም ሶስት በጠቅላላው ከስድስት የማይበልጡ ፅህፈት ቤቶችን ከፍቶ ነበር። ነገር ግን ከማዕከል የሚደረግላቸው የገንዘብ፣ የማቴሪያል እና የቴክኒክ ድጋፍ ማጣት ጋር በተያያዘ በአሁኑ ሰዓት አብዛኞቹ ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት መስጠት በማይችሉ ደረጃ ላይ ደርሰው ተዘግተዋል። በየክፍለ ሃገሩ የሚገኘው አባል መዋቅሩ ከማዕከል ሊደረግለት የሚገባው ድጋፍ ሊደረግለት ባለመቻሉ እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፓርቲው ስራ ኃላፊዎች በተለይም ድርጅት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አመራሮች በየክፍለ ሃገሩ ላሉ ቢሮዎች ያሳዩት ቸልተኝነት እንደሆነ ሲገልጡ በማዕከል ያሉ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አመራሮች ደግሞ የየክፍለ ሃገሩ ቢሮዎች አባሎቻችውን አደራጅተው እራሳቸውን ባለመቻላቸው እና በማዕከሉ ላይ ጥገኛ ስለሆኑ መዘጋታቸውን እንደ ምክንያት ያቀርባሉ።  

ዋናው ነገር እዚህ ጋር መነሳት ያለበት እንኳ በየክልሉ የሚገኘው ህብረተሰብ ባለው ዝቅተኛ በሆነ የፖለቲካ ንቃተ ህሊና እና በመንግስት ካድሬዎች የሚቃጣበትን ከፍተኛ የሞራልና የኃይል ጫና ተቋቁሞ የቢሮ ወጪዎችን ክፍያ ሊሸፍን ይቅርና በማዕከሉ አዲስ አበባ የሚገኘው አባል እና ደጋፊ ወርሃዊ መዋጮ ከፍሎ የፓርቲውን ፅሕፈት ቤት ወጪ መሸፈን ይችላልን? እኔ እስከማውቀው ድረስ የፓርቲው ከፍተኛ የገቢ ምንጭ የሃገር ውስጥ አባላት መዋጮ ሳይሆን በውጪ የሚገኘው አባላት እና ደጋፊዎች የሚያደርጉት የገንዘብ ድጋፍ ነው። ይህ ድጋፍ ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘው በማዕከላዊ ጽሕፈት ቤቱ ወጪ በተለይም ባልተጠኑ እና በዕቅድ ውስጥ በሌሉ በሰላማዊ ሰልፎች ላይ ነው።

ከውጪ የሚገኘው የገንዘብ ድጋፍ አዳዲስ ፅሕፈት ቤቶችን ለማደራጀት እና ያሉትንም ለማጠናከር መዋል ካልቻለ በየትኛው መንገድ ፓርቲውን ለማጠናከር እንደሚውል ሊገባኝ አይችልም። ዋናው ጥያቄ መሆን የሚገባው ‹‹ለህብረተሰቡ ምንም አይነት ጥቅም በማያመጣ አንድ ሰልፍ ላይ በመቶ ሺህ ብሮች ማውጣት ነው ወይስ ፓርቲውን ተደራሽነት ለማስፋት ሰፊ እና ጠንካራ መዋቅር መገንባት?›› የሚለው ነው። ፓርቲው ያለው መዋቅራዊ ስፋት (ተደራሽነት) ከአዲስ አበባ ሳይወጣ በምንም አይነት መንገድ በየጎሳው እና በየጎጡ እንዲሁም በየመንደሩ የሚደራጁ የፖለቲካ ተቋማትን መውቀስ የሚያስችል የሞራል ብቃት ሊኖርው አይችልም። ፓርቲው በኦሮምኛ ተናጋሪው ማህበረሰብ ውስጥ አንዳችም እንቅስቃሴ ማድረግ ሳይችል በኦሮምኛ ተናጋሪው ማህበረሰብ (ክፍለ-ህዝብ) ስም ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ጎሳ ተኮር የፖለቲካ ተቋማትን ሊኮንን አይችልም።

የኦሮምኛ ተናጋሪው ማህበረሰብ እና የሰማያዊ ፓርቲ

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ካላቸው ማህበረሰቦች ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ወይም ከ30 በመቶ በላይ የሃገሪቷ ህዝብን በውስጡ የያዘው የኦሮምኛ ተናጋሪው ማህበረሰብ ነው። ይህ ማህበረሰብን በወስጡ ያላካተተ የትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ስኬታማነት አደጋ ውስጥ ነው ማለት ይቻላል። እስከአሁን ድረስ በሃገሪቷ ውስጥ በመንቀሳቀስ ላይ የነበሩ የፖለቲካ ተቋማት እንቅስቃሴ የኦሮምኛ ተናጋሪውን ማህበረሰብ ያማከለ አልነበረም። ይህም በመሆኑ የሃገሪቷ ፖለቲካ ወደ ፊት መራመድ የነበረበትን ያክል ርቀት መጓዝ ሳይችል በጎሳ ተኮር ፖለቲካ ተርመጥምጠን እንድነቀር ዋነኛ ምክንያት ሆኗል።

በኦሮምኛ ተናጋሪው ማህበረሰብ ውስጥ ገብቶ ያለመስራት ችግር ከመሰረቱ ማስወገድ ይችላል የሚል እምነት ከተጣለባቸው ብሔራዊ ፓርቲዎች መካከል አንዱ ሰማያዊ ፓርቲ ነው። ነገር ግን ይህ ፓርቲ ያለምንም በቂ ምክንያት ይህንን የሃገራችን ክፍለ ህዝብ ያማከለ አንድም ተግባር አለመፈፀሙ አሳዛኝም አሳፋሪም ነው። ይህንን ችግር ለመፍታት ያደረገውም ጥረት አለመኖሩ ደግሞ ከችግሩ ጋር አብሮ ለመኖር የመረጠ መሆኑን አመላካች ነው። ፓርቲው በኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪው ማህበረሰብ ውስጥ ገብቶ ለመስራት የገጠመው ችግር የፓርቲው አመራሮች ፍራቻ ነው። ይህም ፍራቻ ፓርቲው የታላቁን ኢትዮጵያዊ የነፃነት ፋኖ ዳግማዊ አፄ ምንሊክ 100ኛ የሙት አመት ከማክበሩ ጋር የተያያዘ ነው።

እኔ እስከማውቀው ድረስ እንደ አንድ በወቅቱ የፕሮግራሙ ተሳታፊ እና አስተባባሪ ቀኑን ስናከብር ከግምት ውስጥ አስገብተን የነበረው ዋነኛ ነገር ሃገራችንን ከውጪ ሃይሎች ተከላክለው ነፃነታችንን ስላስከበሩት እንዲሁም ሃገሪቷን ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ጋር በማስተዋወቅ ላበረከቱት ትልቅ ተግባራቸው እንጂ እኚህ ንጉስ በስልጣን ዘመናቸው ላጠፉት ጥፋት ክብር ለመስጠት የተደረገ ተግባር አለመሆኑን ነው። የታሪክ ወለምታ ካለባቸው ጥቂቶች በቀር አብዛኛው የኦሮምኛ ተናጋሪው ማህበረሰቡ ክፍል ይህንን በሚገባ ይረዳል። ነገር ግን የፕሮግራሙን መዘጋጀት ምክኒያት በማድረግ ጥቂቶች ጠባብነት ያጠቃቸው እና የማህበረሰቡ ግንጥል ፖለቲካ የተመቻቸው ግለሰቦች በከፈቱት የኤሌክትሮኒክ ሚዲያው ዘመቻ የፓርቲው አመራር በመደናገጡ እስከ አሁን ድረስ ወደዚህ ማህበረሰብ ገብቶ ለመስራት ምንም ሙከራ ማድረግ አልቻለም።

ፓርቲው የምርጫ ፓርቲ እንደመሆኑ ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ከተስተካከሉ በመጪው ሃገር አቀፍ ምርጫ መሳተፉ አይቀሬ ነው። ታዲያ ይህ ፓርቲ ወደዚህ ምርጫ ሲገባ ይህንን ማህበረስብ በሚገኝበት ቦታ ለመወዳደር የሞራል ብቃት ይኖረዋልን? ይህንን አነሳ ዘንድ ያስገደደኝ ፓርቲው ከመሃል ሃገር ተነስቶ በሰሜን እስከ ጎንደር፣ በምስራቅ እስከ ድሬዳዋ እና በደቡብ እስከ አርባ ምንጭ ድረስ እየተጓዘ ለመንቀሳቀስ ባደረገው ሙከራ እየረገጣቸው ስለሔደው የኦሮምኛ ተናጋሪ ማህበረሰብ መኖሪያ አካባቢዎች ላይ ለመስራት አንዳችም ሙከራ አለማድረጉ ምክንያት አልባ እጅግ አሳፋሪ ተግባር ነው። እንደ ፓርቲው አርማ ከመሃል ወደ ዳር ሃገር እየሰፋን መሄድ ይገባን ነበር። ፓርቲው ካለው የገንዘብ እና የሰው ሃይል እጥረትም ይሔኛው የተሻለ ተግባር ነበር። አሁንም እጠይቃለሁ።

ፓርቲው በኦሮምኛ ተናጋሪው ማህበረሰብ ውስጥ ገብቶ ለመስራት ያልቻለበት ምክኒያት ምንድነው? ይህንን ህብረተሰብ ሳያሳትፍ የሚያደርገው የነፃነት ጉዞስ ቅዠት አይሆንም? አብዛኛውን ህዝብ ውስጥ ገብቶ ለመስራት ሳይሞክር በስም ብቻ ብሔራዊ ፓርቲ ብሎ እራስን መኮፈስስ የት ያደርሰናል? 5% ያክል እንኳ የሃገሪቷ ህዝብ መድረስ ሳይችል እንኳ በአምባገነን መንግስት ሙሉ ቁጥጥር ስር በሆነ ምርጫ እና ከህዝብ ድምፅ በላይ የመሳሪያ ድምፅ በሚሰማበት ሃገር በዲሞክራሲያዊ ምርጫም ስልጣን ለመያዝ ማቀድ ፌዝ አይደለም ወይ?                    

ለአብላጫ ድምፅ አለመገዛት

ሁለት የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት፣ አንድ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት እና እኔ በአንድ ሬስቶራንት ውስጥ ለቁርስ ተቀምጠናል። ያዘዝነውን ቁርስ እየጠበቅን ሞቅ ያለ ውይይት ይዘናል። የክርክሩ አጀንዳ “ለሃገራችን ፖለቲካ የፓርቲዎች ውህደት ይጠቅማል ወይስ አይጠቅምም” የሚል ነበር። አንዱ የሰማያዊ ፓርቲ የብሔራዊ ምክር ቤት እና የህዝብ አደረጃጀት ቋሚ ኮሚቴ አባል የሆነ ወጣት የፓርቲዎች ውህደትን በመደገፍ የፀና አቋሙን ሲያንፀባርቅ የተቀሩት ሁለቱ (አንድ የሰማያዊ ብሔራዊ ምክር ቤት እና አንድ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባለት) ሃሳቡን በመንቀፍ አበክረው ይከራከራሉ። እኔ ጉዳዩን በገለልተኛነት እየሰማሁ ከቆየሁ በኋላ “አብዛኛው አባል ፓርቲያችን ከሌሎች ጋር እንዲዋሃድ እንፈልጋለን ቢል የእናንተ በተለይም የስራ አስፈፃሚው አባላት ውሳኔ ምን ይሆናል?” የሚል ጥያቄ ሰነዘርኩ። የስራ አስፈፃሚው አባል ከአፌ ቀበል አድርጎ “ፓርቲውን እለቃለሁ” ነበር ያለው። አስከትዬ ያልኩት ነገር አሁን ድረስ ትዝ ይለኛል። “ስለዚህ ሃሳባችሁ የበላይ እስከሆነ ድረስ ነው ማለት ነው በፓርቲ ውስጥ የምትቀጥሉት?” መልስ የለም።

የዲሞክራሲ ፅንሰ ሃሳብ የተመሰረተው “ለብዙሃን ሃሳብ የበላይነት መገዛት እና ለትቂቶች አስተሳሰብም ቢሆን ተገቢውን አክብሮት መስጠት” በሚል መርህ ላይ ነው። ይህ ከላይ ያስቀመጥኩት አጋጣሚ በተለያየ ጊዜ ጥቂት የማይባሉ የስራ አስፈፃሚ አባላት ሲያራምዱት የነበሩት አስተሳሰብ ነው። እነዚህ አባላት በፓርቲ ውስጥ መቀጠል የሚፈልጉት እንደ አህያ አስተሳሰባቸውን በሌሎች ላይ መጫን እስከቻሉ ድረስ ብቻ ነው።

የሰማያዊ ፓርቲው የኦዲት እና ክትትል

በፓርቲው ውስጥ ያለውን ችግር ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ከሚገኙ የፓርቲው መዋቅር ውስጥ ቀዳሚው እና ዋነኛው የኦዲት እና ክትትል ቋሚ ኮሚቴ ነው። ይህ ቋሚ ኮሚቴ በተደጋጋሚ ችግሩ ለመፍታት በፓርቲው አካሔድ ላይ ቅሬታ ከሚያቀርቡ ግለሰቦች ጋር በመነጋገር ያደረገውን ጥረት ሳላመሰግን ማለፍ ተገቢ አይደለም።

በተደጋጋሚ ከቋሚ ኮሚቴው አባላት ጋር በችግሮች እና መፍትሔያቸው ዙሪያ ውይይት አድርገናል። ነገር ግን አመራሩ ችግሩን ለመፍታት ያለው ቁርጠኝነት እጅግ አናሳ መሆኑ በዚህ ቋሚ ኮሚቴ ተግባር ተፅዕኖ አሳድሯል። ለምሳሌ በቅርቡ ቋሚ ኮሚቴው ጥፋተኛ ባላቸው አባላት እና ከፍተኛ አመራር ላይ ከገንዘብ መቀጮ እስከ ከስልጣን ማንሳት ድረስ ውሳኔ ያሳለፈ ቢሆንም ስራ አስፈፃሚዎቹ ውሳኔውን እንደማይቀበሉ እና ውሳኔውን ያሳለፈው የኦዲት እና ክትትል ቋሚ ኮሚቴ ይቅርታ እንዲጠይቃቸው አዘዋል። የህግ የበላይነትን ማክበርን በቤታችን እንማር!!!  

መደምደሚያ

“ትንሽ ሰው ትንሽ ነው አንሶ ያሳንሳል፤…” ሆኖብኝ እንጂ በዚህ ደረጃ ላይ ወርጄ መናገር ባልተገባኝ ነበር። አንባቢያን ይቅርታ አድርጉልኝ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሰዎች ይገባቸው ዘንድ በዚህ ደረጃ ወረድኩ። የህዝቡን ጥያቄ በቅጡ ሳይመረምሩ ብሎም አጥጋቢ ምላሽ ሳይዙ አዲስ የፖለቲካ ፕሮግራም ማውጣት፣ አዲስ ድርጅት ማቆም፣ ወይንም አሮጌውን ድርጅት አዲስ ስም መስጠት ብሎም ህዝብንም “ግፉ እና ግብሩ በዝቶብሃል ተከተለኝ” ማለቱ ትርጉም የለውም። ትላንት በሃገራችን ፖለቲካ ውስጥ የተከሰተው የአላማ እና የግብር መዛነፍ እንዴት ሊሆን ቻለ? ብለን እራሳችንን እየጠየቅን ትላንትናችንን መመርመር ግዴታ ነው። በተለይም የተመሰቃቀለ የሃገራችንን የፖለቲካ ሁኔታ ለመረዳት፣ በህዝባችን መፃኢ-እጣ ላይ ያሰፈሰፈውን መዓት ለመቋቋም ህዝቡን በእውነት እና ስለእውነት በማደራጀት የትላንት ችግሮቻችንን መፍታት የማይታለፍ ግዴታ ነው።

ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1359 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1061 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us