You are here:መነሻ ገፅ»የኔ ሃሳብ
የኔ ሃሳብ

የኔ ሃሳብ (393)

 

 

ጉዳዩ: የኢትዮጵያ መብትና ጥቅም የሚፃረረውን የአልጀርስ ስምምነት መሻርን ይመለከታል

 

አበበ ተክለሃይማኖት (ሜጄር ጄኔራል)

 

የኢህአዴግ ሰራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በአልጀርስ ስምምነትን እና የድንበር ኮሚሽን ውሳኔውን ከተቀበሩበት ጉድጓድ አውጥቶ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኑ ይፋ ሆኗል። ውሳኔው በመንግስት ነው ወይስ በኢሀዴግ የሚለውን ጥያቄ ለጊዜው ትተን ውሳኔው ግን አስደንጋጭ ነው።


በርካታ ምሁራን ኤርትራ ነፃ አገር መሆኗን ተከትሎ የኢትዮጵያ ልዑላዊ የባህር በር መብት በሚመለከት በተደጋጋሚ እየፃፉ መንግስትን ያሰገነዝቡ ነበር:: ኤርትራ ኢትዮጵያን ከወረረ በኋላ ጥያቄው አገርሽቶበት እንደገና በብዕራቸው በመንግስት ስልጣን ለተቆጣጠረው እና ለባለጠመንጃው መወትወት ጀመረ። በትዕቢት ተወጥሮ ድንቁርና የተከናነበው መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ጥናት ሳያካሂድ አልጀርስ ላይ ሄዶ ተዘፈቀበት። ምሁራን ዓለም አቀፍ ህግን መሰረት አድርገው ነበር የሚከራከሩት ።


ይህ ስምምነት ወራሪ እና ተወራሪ አሸናፊ እና ተሸናፊ እኩል የሚያደርግ መሆኑ አሳፋሪ ቢሆንም የአገራችንን መብት አሳልፎ የሰጠ በመሆኑ ዘላቂ ሰላም ሊያረጋግጥ አይችልም:: በኢትዮጵያ አጠቃላይ ደህንነት በተለይም በኢኮኖሚ ደህንነት አደጋ ውስጥ የሚያስገባ ነው። የኢትዮጵያ ታሪክ እና ክብር የማይመጥን ስምምነት ነው።


የያኔው መንግስት የሀገር ጉዳይ በሁለተኛ ደረጃ አስቀምጦ የራሱን ስልጣን የማደላደል ጉዳይ ቅድሚያ በመስጠት በአልጀርስ ስምምነት ውስጥ ሆነን እንኳን ሊገኝ ይችል የነበረው በድንበር መካለል ድል አሳልፎ ሰጥቷል። በእንዝህላልነት ምክንያት ፍትሀዊ ያልሆነ ውሳኔ ኢትዮጵያ እንድትቀበል ተገደደች። ውሳኔውን እንኳን በቅጡ መገንዘብ ያልቻለ፣ የኢትዮጵያዊያን ጊዜአዊ የልብ ትርታ ለማሸነፍ በሩጫ መግለጫ ተሰጠ። የተባለው ግን ዉሸት ሆነ፤ ይቅርታም አልተባለበትም። ቄሱም ዝም መፅሐፉም ዝም ሆነ። በጦርነት አሽንፈን በአልጀርስ ተሸንፍን፣ በኮሚሽን ውሳኔ ልባችን ተሰብሮ እንገኛለን።

 

አሁን ምንስ የሚያስገድድ ሁኔታ አለ?!


አገራችን በለውጥ ተስፋ በምትገኝበት በአሁኑ ግዜ የለውጥ ሂደቱን ለመቀየር (Divert) ለማድረግ ለምን የሞተውን አጀንዳ ለማንሳት ተፈለገ? አለማዊ፣ አካባቢያዊ እና አገራዊ የሚያስገድድ ሁኔታ ምን አለ?!


በአልጀርስ ስምምነት ኢትዮጵያ እያለቀሰች ነው። መንግስት በኤርትራ ትንኮሳ ላይ በሚከተለው የኮንተይንመንት (Containment) ፖሊሲ ምክኒያት ኢትዮጵያ እየደማች ነው። የኤርትራ በትርና ትንኮሳ ባጋጠመ ቁጥር ፓርላማ እየቀረቡ የሚያለቅሱ ጠቅላይ ሚኒስቴሮች የበለጠ አሳዝነዉን ነበር። በድንበር ያሉ ህዝቦች በእውነት እየተሰቃዩ ነው፤ በየጊዜው እየተዘረፋ ነው፣ እየሞቱ ነው። ከልማት እጅጉን እርቀዋል:: ጊዜአዊ ድጐማ መደረግ ያለበት ቢሆንም (እስካሁን ምንም ዓይነት ድጎማ አልተደረገም) ለእነሱም ቢሆን ዘላቂ መፍትሄ የሚሆነው የአልጀርስ ስምምነት መሻር እና የኤርትራ መንግስት ትንኮሳ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስቀረት ነው። በድንበር አካባቢ ያሉት ህዝቦች እንባ የሚመለሰው የኢትዮጵያ መብት ሲከበር እና ለማተራመስ የሚፈልጋትን ሀይል ሲወገድ ነው።


አሁን ያለው የለውጥ ተስፋ እና እንቅስቃሴ በፊደራል ደረጃ የሚመራ ነው። በሁሉም ክልሎች ያለው የለውጥ ሂደት ምን ላይ እንዳለ ባለውቅም የለውጥ ንፋስ የለውጥ ሽታ በሌለበት ትግራይ ግን ለኤርትራ አዋሳኝ በሆኑ የባድመ እና ኤሮኘ ግዛቶች ያለበት በመሆኑ ወጣቱ ስለ ዲሞክራሲ፣ የህግ የበላይነት፣ ስለፍትህ አጠንክሮ የያዘውን አጀንዳ አቅጣጫ ለመቀየር የተደረገ ነው እንዴ? የሚያሰኝ ነው። አንድም ህዝቡን ተስፋ የሚሰጥ አጀንዳ አሰናድቶ የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ህዝባዊ ጥያቄዎች አጣብቂኝ ዉስጥ የከተተው ህወሓት ይህንን አጀንዳ እንደ ማስቀየሻ አንስቶት ይሁን ብለን ማሰባችን አልቀረም።


እነሱ ስለተሸነፉ የትግራይ ህዝብ የተሸነፈ የሚመስላቸው ሰዎች በፌዴራል ደረጃ የሚታየዉን ለዉጥ መቀበል አቅቷቸው የትግራይን ህዝብ በስጋትና በቁጭት ከተው ከፌዴራል መንግስት ጋር ለማላተም የታለመ በሚመስል መልኩ የዚህ ጉዳይ ሃሳብ አመንጪዎች መሆናቸው ሳውቅ ነገርየው ወጥመድ ይሆን እንዴ? ብዬ ለመጠየቅ ተገድጃለሁ።


ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ ለመከላከያ ሠራዊታችን መመሪያ በሰጡበት ስብሰባ የጠንካራ ባህር ሐይል መገንባት ጉዳይ በሚያነሱበት ግዜ የሀገራችን የለወጥ ሂደት ሉዐላዊ የባህር በር መብታችንን በሚያረጋግጥ መንገድ ድርብ ድል የምናገኝበት ኢትዮጵያ ከአንድ ስኬት ወደ ሌላ ስኬት እየተጓዘች ነች እንዴ? ብለን መሪያችንን ለማመስገን ስንዘጋጅ ይህ አስፈሪ የአንድ ፓርቲ ውሳኔ ሰማን።

 

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር


(No Peace - No War) ሁኔታ በአንድ በኩል የኤርትራ መንግስት የመዝረፍና የመወረር ፍላጐት በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ መንግስት ልፍስፍስነት ምክንያት የተፈጠረ የአልጀርስ ሰምምነት ዉጤት ነው። ወራሪ በመሆኑ የኤርትራ መንግሥት የሚቀጣ ማለት ላደረሰው ዉድመት የሚመጥን ተመጣጣኝ ካሳ ብቻ ሳይሆን በሠራዊቱ ቁጥር የማይገደብ ስምምነት እንዲሁም የኢትዮጵያ ሉዐላዊ የባሕር በር መብት የሚያረጋርጥ ቢሆን ኖሮ ይህ ሁኔታ አይፈጠርም ነበር።


የኤርትራ መንግስት በየጊዜው ኢትዮጵያን በማተራመስ እንቅስቃሴው የአልጀርስ ስምምነት ውጤት ነው:: ከስምምምነቱ በፊት የኢትዮጵያ ሰራዊት ጀምሮት በነበረው የማጥቃት ሂደት የኤርትራን ሠራዊት አዳክሞ ላንዴና ለመጨረሻ ግዜ አደጋ የማይሆንበት ደረጃ ቢያደርስ ትልቅ ክንዉን ይሆን ነበር። ይህ ባይሆንም እንኳ በአልጀርሱ ስምምነት የኤርትራ መንግስት እንደ ጠብ አጫሪነቱ በተሸነፈበት ማግስት ከበድ ያለ የካሳ ክፍያና በዛ ያለ የወታደራዊ አቅም ቅነሳ የሚያስገድድ ስምምነት ስለሌለው የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያን የማተራመስ እድል የሚሰጥ የአልጀርስ ስምምነት ሆኖ እናገኘዋለን:: ሰላምና ጦርነት አለመኖር ኢትዮጵያ ደምታለች በተለይ በድንበር ያሉት ህዝቦችም እጅጉን ተሰቃይተዋል ከልማት፣ ከሰላም እርቀዋል። አሁን ያለው ችግር መንስኤው የአልጀርስ ስምምነት ነው፤ መፍትሔው ደግሞ ስምምነቱን አሽቀንጥሮ መጣል ነው።

 

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር


እንደሚያዉቁት ኤርትራ ኢትዮጰያን የወረረው በድንበር ጉዳይ አልነበረም:: የሁለቱ አገር የድንበር ኮሚሽነሮች የድንበር መካለሉ እንዴት ይሁን? ብለው በውይይት አዲስ አበባ ተቀምጠም እያሉ ነበር የኤርትራ ታንኮች ሉዓላዊ መሬታችንን የወረሩት። የኢትዮጵያ መንግሥት ከኤርትራ ጋር የነበረው ልቅ የሆነ የኢኮኖሚክ ግንኙነት እንዳይኖር መቆጣጠር ስላስጀመረ ነው ወረራው የደረሰብን። የአልጀርስ ስምምነት የኤርትራን መንግስት ሽሮት ነበር። ጊዜአዊ የደህንነት ቀጠና (Temporary Security Zone) በማፍረስ የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ሀይሉን ያባረረ ነው። ስለዚህ አሁን ኢህአዴግ የወሰነው ዉሳኔ የኤርትራ መንግስት ያፈረሰዉን ዉል መሰረት አድርጎ ነው።


አሁን ያለው የኤርትራ መንግስት በሌሎች ሀብት ለመኖር የሚፈልግ መዥገር ነው:: በሌላ መልኩ ኢትዮጵያ ልማት እንዳትጐናፀፍ ከሚፈለጉ ሀይሎች ጎን በመሰለፍ ተመፅዋች ሆኖ የተላላኪ ሥራ የሚሰራም ነው። ሠላም የማይፈልግ በሁከት ንግድ የተሰማራ ተላላኪ መንግስት ራሱ በድርጊቱ የሻረዉን የአልጀርስ ስምምነት ተግባራዊ በማድረግ ሰላም ይመጣል ብሎ ማስብ ቂልነት ነው። ባድመና ኤሮኘ ሰጥቶ ሰላም እናገኛለን ማለት ሞኝነት ነው።


ብዙ ምርጥ የኢትዮጵያን ልጆች ያጣንበት፣ ብዙዎች የተፈናቀሉበት፣ ከፍተኛ ሀብት ያፈሰስንበት ብቻ ሳይሆን ለወደፊትም የባህር በር አልባ መሆን አሁን ባለው የአካባቢያችን ጂኦ ፖለቲካ የከፋ ህይወት እንግልት እና ጥቃት የሚያደርስብን በመሆኑ ከወዲሁ ተሰርዞ አዲስ ውይይት (Negotiation) መደረግ ይኖርበታል። እንደሚያውቁት ሉአላዊ የባህር በር ጉዳይ ሀገራችን ባለው የለውጥ መንፈስ ለሰላም፣ ለዲሞክራሲ እና ልማት ወሳኝ ነው። ስለዚህም ክቡርነትዎ ከፍተኛ የዘርፍ ምሁራን በማሰባሰብ ከአለም አቀፍ ህግ አንፃር እላይ የተጠቀሰው መብት እንዲረጋገጥ ቢያደርጉና እስከዛ ድረስ ግን የኮሚሽኑ ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ የሚደረገው እንቅስቃሴ እንዲቆም በክብር እጠይቃለሁ።፡


ይህ ደግሞ የተሟላ ተፅእኖ የሚያሳድር (Full Package) ማለት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ስነአእምሮአዊ፣ ዲኘሎማሲያዊ እና የደህንነት Package በማዘጋጀት የኤርትራ መንግስት አስገድዶ አዲስ ስምምነት ላይ መድረስ ይጠይቃል። ክቡርነትዎ የኢትዮጵያ መብትና ጥቅም
የሚፃረረውን የአልጀርስ ስምምነት ይሰረዙ!!¾

 

ዳንኤል ክብረት

http://www.danielkibret.com

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጠዋት ወደ ቢሯቸው ማልደው ሲገቡ የእንግዳ መቀበያ ክፍሉ ወንበሮች ተሰልፈው ጠበቋቸው። ነገሩ እንግዳ ሆነባቸው። የዚህን ቤተ መንግሥት ባሕል ገና አልለመዱትም። የተለመዱ ችግሮችን ባልተለመደ መንገድ እፈታለሁ ብለው ለተነሡት ጠቅላይ ሚኒስትር ነገሩ ከተለመደውም የወጣ መሰላቸው።

‹ምንድን ነው?› አሉ ሳቅ ይዟቸው።      

‹አሰናብቱን› አለ ደንዳሳ ትከሻ ያለው የቆዳ ወንበር።በታሪኩ ለመንግሥት ቅርብ የሆኑ እንግዶችን በማስተናገድ ይታወቃል።

‹ለምን? የት?› አሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ

‹በቃ እኛንም ጡረታ ያውጡና› አለ ሌላ እምቡር እምቡር የሚል ወንበር፤ የባለሥልጣን መቀመጫ መሆኑን የሥላሴን ዙፋን ከተሸከሙት ኪሩቤል በላይ ይኮራበታል። ‹እንትናኮ እኔ ላይ ነው የሚቀመጠው› እያለ መጎረር ይወዳል።

‹ምን ሆናችሁ› አሏቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እጃቸውን አገጫቸው ላይ አድርገው።

‹እኛ ከመጀመሪያው ስንገዛ ለዚህ ዓይነት ነገር መሆኑን የነገረን የለም። አሁን እየተሠራ ያለው ከለመድነው ውጭ ነው። ከተገዛንበት ዓላማ ውጭ ነው። የመርሕ መደባለቅ እያየን ነው› አለ ባለ ደንዳሳ ትከሻው ወንበር።

‹ለምን ዓላማ ነበር የተገዛችሁት?› አሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያልሰሙት የቤተ መንግሥት ምሥጢር መኖሩን እየጠረጠሩ።

‹እኛኮ እዚህ ቦታ ብዙ ጊዜ ኖረናል› አለቺ አንዲት ቆንጠር ቆንጠር የምትል ድፉጭፉጭ ወንበር። ‹እዚህ ስንኖር እነማን ይታሠሩ፣ ይባረሩ፣ አገር ጥለው ይጥፉ፤ ምን ዓይነት አሣሪና ጨምዳጅ ሕግ ይውጣ፣ እነማን ይመቱ፣ እነማን ይገለሉ፣ እነማን ይታገዱ፣ እነማን ይወገዱ፣ እነማን ይውደሙ፣ እነማን ይጋደሙ የሚል ነገር ነው ስንሰማ የኖርነው። እኛ የተገዛነው ይሄን የመሰለ ምክር ሊመከርብን ነው። እኛ እዚህ ቢሮ ስንኖር የተቀመጡብን ሰዎች በጣም የተከበሩ ናቸው። እዚህ እኛ ላይ በተመከረ ምክር ስንት አገር ተተራምሷል፤ ስንቱ ታሥሯል፣ ስንቱ ተገድሏል፤ ስንቱ ቀምሷል፣ ስንቱ ነፍዟል። አሁን የምንሰማው ነገር ግን የሚያዛልቀን አይደለም› አለቺ መሬቱን በስፒል እግሯ እየፈተገች።

‹ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አሁን እርስዎ የሚናገሩት ቋንቋ እኛን ሊገባን አልቻለም፤ ለዚህ ቢሮ አዲስ ቋንቋ ነው። ለኛም ለወንበሮቹ አዲስ ልሳን ነው። ስናየው በልሳን እየተናገሩ ይመስለናል› አለ፤ ሁለት ሰው እንዲይዝ ሆኖ የተሠራው አጭሬ ወንበር።

‹እንዴት ነው ቋንቋዬ የማይገባችሁ። የማወራው አማርኛ ነው፤ ትግርኛ ነው፤ ኦሮምኛ ነው፤ እንዴት ነው ቋንቋዬ የማይገባችሁ?› አሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ወደ ውስጠኛው ቢሮ መግባቱን ተዉትና በሩ ላይ ቆሙ። የጽ/ቤት ኃላፊያቸውና አጃቢዎቻቸው በአግራሞት የሚሆነውን ሁሉ ይከታተላሉ።

‹ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር› አለ ባለ ደንደሱ ትከሻ። ‹ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ፍቅር፣ ይቅርታ፣ ኢትዮጵያዊነት፣ ይሄ የምናውቀው ቋንቋ አይደለም። በእርስዎ ደረጃ ሰምተንም አናውቅም። ምናልባት ዶክተር ሲባሉ ሰምተናልና ከውጭ ተምረውት ያመጡት ይመስለናል። እዚህ ሀገር እዚህ ቢሮ በዚህ ቋንቋ ሲወራ ሰምተን አናውቅም። ጭራሽ ማሠር እንጂ መፍታት የሚባል በዚህ ቢሮ መዝገበ ቃላት ውስጥ የለም። ውጡ እንጂ ግቡ የሚል ቃል አዲስ ነው ያመጡብን። ተለያዩ መባል ሲገባው ታረቁ፣ ተስማሙ፣ አንድ ሁኑ የሚባል መጋኛ እየመጣብን ነው። እነዚህ ሁሉ በአማርኛ፣ በትግርኛና በኦሮምኛ ካሉ ለምን እስከዛሬ እዚህ ቢሮ ውስጥ አልሰማናቸውም?› ባለ ደንደሱ ትከሻ የአንገት መደገፊያውን በኀዘን ነቀነቀው።

‹ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር› አለ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መቀመጫነት የተዘጋጀው ወንበር።

‹ጭራሽ አሁን ስንሰማማ በሽብር የተከሰሰን ሰው፣ ሞት የተፈረደበትን ሰው መፍታት ሳያንስዎት እዚህ ጠርተው እጁን ሊጨብጡት፤ እኛ ላይ አስቀምጠው ሊያናግሩት ነው አሉ? ይኼንን ከምናይ ምነው ድሮ ተቀዳደን በወደቅን ወይም በሐራጅ በተሸጥን? እና ይሄ ሰውዬ መጥቶ የት ሊቀመጥ ነው? ከኛ ማናችንም ብንሆን እንዲቀመጥብን አንፈቅድም። ለእርስዎም ለስምዎ ጥሩ አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትርኮ እቆርጣለሁ፣ እፈልጣለሁ፣ አሥራለሁ፣ እቀፈድዳለሁ፣ ሲል ነው የሚያምርበት።

‹እና እንዋጋለን፣ እንሸፍታለን፣ መንግሥት እንገለብጣለን፣ ሲሉ የኖሩት ሁሉ ብረታቸውን እያስቀመጡ እየመጡ ሊቀመጡብን ነው? ትናንትና እኛ ላይ ቁጭ ባሉት ባለ ሥልጣናት አሸባሪ፣ አደናባሪ፣ አቀናባሪ፣ ሲባሉ እንዳልነበር ዛሬ ዘመን ተቀየረ ብለው መጥተው ሊቀመጡብን?› ሞት ይሻለናል› አለ ሁለት ሰው የሚይዘው አጭሬ ወንበር።

‹ክብራችን ተነክቷል ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር› አለቺ ድፉጭፉጯ ወንበር። ‹ጭራሽኮ አሁንማ ቤተ መንግሥቱን ሰው መጎብኘት አለበት እያሉ ነው። ታድያ በኛና በሰፊው ወንበር መካከል ምን ልዩነት አለው? የቤተ መንግሥት ወንበር በመሆንና የቤት ወንበር በመሆን መካከል ምን ልዩነት ሊኖር ነው? መከበራችን፣ መታፈራችን፣ መፈራታችን፣ ሊቀርኮ ነው። ተራውን ሕዝብ ሁሉ ቤተ መንግሥት ጠርተው መጋበዝዎት ሳያንስ ጭራሽየቤተመንግሥቱንቆሌ ገፍፈው ሊያስጎበኙት? እና የየሠፈሩን ሰዎች እዚህ ግቢ ውስጥ በመስኮት ልናያቸው? ሞተናላ!›

‹ሲደበደብ ከኖረ ቆዳ የተሠራ ከበሮ ዜማው ሁሉ በለው በለው ይመስለዋል› አሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

‹አባቶቻችን ድንበር ሲያስከብሩ ኖሩ፤ እርስዎ ግን ድንበሩን ሁሉ ናዱት› አለ ዝም ብሎ ሲመለከት የነበረ በአገልግሎት ብዛት አርጅቶ አናቱ የተላጠ ወንበር› ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከውስጥ የሚሰሙትን የስልክ ጥሪ የጽ/ቤት ኃላፊያቸው እንዲያነሣ አዝዘው ማዳመጥ ቀጠሉ።

የቱን ድንበር ነው የናድኩት?› አሉት ፈገግ ብለው በትዕግሥት ቆመው።

‹በተቃዋሚና በደጋፊ፣ በገዥና በተገዥ፣ በውጭና በውስጥ መካከል የጸናውን ድንበር ናዱትኮ። እግዜር ያሳይዎና ኢቲቪና ኢሳት አንድ ዓይነት ዜና እንዲያቀርቡ አደረጓቸውኮ። አሁን ጭራሽ ውጭ ሊሄዱ ነው አሉ። ዕንቁላል መወርወሩ ቀርቶ የዕንቁላል ሳንዱች ሊቀርብልዎት ነው አሉ? ከዚህ በላይ ድንበር መናድ የት አለ?› የተላጠ አናቱን አነቃነቀ።

‹እናም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ያሰናብቱን፤ አመለካከታችንን ከምንለውጥ ጾታችንን ብንለውጥ ይሻለናል። ዐርባ ዓመት ያልሰማነውን ቋንቋ ከምንሰማ - ጡረታ ወጥታችኋል የሚለውን ብንሰማ ይሻለናል። አዲሱን ወይን ጠጅ በአሮጌው አቁማዳ ማስቀመጥ አቁማዳውንም መቅደድ ወይኑንም ማፍሰስ ነው።›

ባለ ደንደሱ ትከሻ ወንበር ወደ ውጭ ሲወጣ ሌሎችም ተከትለውት ወጡ። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ብዕሮችና ወረቀቶች ግን ጤና አልተሰማቸውም። ‹እነዚህ ወንበሮች እውን በጤናቸው ነው ቢሮውን ለቅቀው የወጡት? ወይስ በበር ወጥተው በመስኮት ሊመለሱ ነው?› አለ አንዱ እስክርቢቶ።

‹ያኔም አመጣጣቸው ግራ እንዳጋባን ዛሬም አካሄዳቸው ግራ ሊያጋባን ነው መሰል› አለና ሌላኛው እስክርቢቶ መለሰለት።

 

ገመቺስ ደምሴ (www.abyssinialaw.com)

 

መግቢያ


ወንጀል በአጠቃላይ ፀር መሆኑ እሙን ነው። ከክቡር የሰው ህይወት አንስቶ፣ ጤንነትን፣ ክብርን፣ ደህንነትን፣ ንብረትን፣ አስተሳሰብን፣ ሰላምንና አጠቃላይ የሀገርን ማህበረሰባዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ጥቅም ባህላዊ መረጋጋቶች ላይ ጥላ የሚያጠላና የሚያናጋ መሆኑ አያጠራጥርም። ይህ ሁኔታ እንዳይከሰት ጥበቃ የሚያደርጉ የተለያዩ ህጎች ቢኖሩም የወንጀል ህግ አይነተኛ መሳሪያ ተደርጎ ይወሰዳል። የወንጀል ህግ ማህበረሰባዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥበቃዎችን በሚያደርግበት ወቅት የማህበረሰቡንና የግለሰብን (ወንጀል አድራጊን) መብት ባማከለ መልኩ የሚቀረፀም የህግ አይነት ነው። በህግ ፍልስፍናውም ሆነ በኢትዮጵያ የወንጀል ህግ ላይ ይህ አይነት ሚዛናዊነት (Balance) በአግባቡ የሚነሳና የሚንፀባረቅ ነው። ከእነዚህ ሚዛናዊነት መካከል የግለሰቦች ነፃ ሆኖ የመገመት መብት (presumption of innocence) አይነተኛ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ከአለም አቀፍ ስምምነቶች እንደ International Convention on Civil and Political Rights (ICCPR) እና በኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀፅ 14(2) እና 20(3) እንደቅደም ተከተላቸው ነፃ ሆኖ የመገመት መብት ተደንግጎ የሚገኝ መሆኑን ማየት እንችላለን። ነፃ ሆኖ የመገመት መብት የሚዘልቀው ወንጀል አድራጊው በፍ/ቤት ጥፋተኛ እስኪባል ድረስ ሲሆን እስከዚያ ድረስ ወንጀለኛ ተብሎ ሊጠራም ሆነ እንደወንጀለኛ ሊታይና ሊስተናገድ አይችልም። አንድ ግለሰብ ደግሞ በፍ/ቤት ጥፋተኛ የሚባለው ወንጀሉን መፈፀሙ ሲረጋገጥ ነው። ወንጀል ተፈፀመ የሚባለው ደግሞ በወንጀል ህጋችን አንቀፅ 23(2) መሰረት ሕጋዊ፣ ግዙፋዊ እና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች በአንድነት ተሟልተው ሲገኙ ነው።


እያንዳንዱ ፍሬ ነገር ሰፊና ጥልቅ ሀሳብ ያዘሉ በመሆኑ ለዚህ ፅሁፍ አላማ ሲባል አጭር ማብራሪያ ብቻ ቀርቧል።

 

ወንጀልን ስለሚያቋቁሙ ፍሬ ነገሮች


ሕጋዊ ፍሬ ነገር


ሕጋዊ ፍሬ ነገር የሚባለው ባጭሩ የሚከለክል ወይም የሚያስገድድ ህግ ሊኖር እንደሚገባ የሚያትት መርህ ነው። ለምሳሌ መስረቅ ክልክል እንደሆነ ካልተደነገገ የሌላን ግለሰብ ንብረት ያለፈቃድ መውሰድ ወንጀል ሊያሰኘው አይችልም። ሌላ ምሳሌ ለመጨመር ያክል ግብር መከፈል እንዳለበት የሚደነግግ ህግ ከሌለ ግብር አለመክፈል ጭራሹን ወንጀል ሊሆን አይችልም።

 

ግዙፋዊ ፍሬ ነገር


ግዙፋዊ ፍሬ ነገር የሚባለው ደግሞ በወንጀል ህግ የተደነገገውን ወይም ከላይ ሕጋዊ ፍሬ ነገር ያልነውን መጣስ ነው። ግዙፋዊ ፍሬ ነገር ወይም ድርጊት የሚባለው በህግ አድርግ የተባለውን አለማድረግ (Omission) ወይም አታድርግ የተባለውን ነገር ማድረግ (Commission) ነው! ለምሳሌ፡- ከበደ 500 ብር ከአለማየሁ ቢወስድ፤ ያለአለማየሁ ፈቃድ መውሰዱ ግዙፋዊ ፍሬ ነገር ወይም በማድረግ የሚፈፀም ድርጊት ነው (crime by commission)። አለማየሁ ግብር መክፈል እያለበት ባይከፍል፤ ግብር አለመክፈሉ ግዙፋዊ ፍሬ ነገር ወይም ባለማድረግ የሚፈፀም ድርጊት ነው (crime by omission)።

 

ሞራላዊ ፍሬ ነገር


ሞራላዊ ፍሬ ነገር ወይም ወንጀልን የማድረግ ሀሳብ ሲባል ሊጨበጥ፣ ሊዳሰስ ሊታይ የማይችል በወንጀል አድራጊ አስተሳሰብ ላይ ያነጣጠረ ጉዳይ ነው። ይህም ሲባል ግዙፋዊ ፍሬ ነገሩን ያደረገው አስቦ፣ ቸልተኛ ሆኖ ወይም ያለሀሳቡና ያለቸልተኛነቱ በድንገተኛ አጋጣሚ (Accident) የመፈፀሙን ሁኔታ የሚያይ መሆኑን ከወንጀል ህጉ አንቀጽ 57 እና ተከታዮቹ መረዳት ይቻላል።

 

ቸልተኛነት /Negeligiance/


ቸልተኝነት በአጠቃላይ አንድ ግለሰብ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አለማድረጉን የሚያይ ክፍል ነው። አንድ ወንጀል አድራጊ ሆነ ብሎ ወንጀሉን ባያደርግም እንኳ ተገቢውን ጥንቃቄና ንቃት አክሎ ቢሆን ኖሮ ወንጀሉ አይፈፅምም ነበር የሚባልበት አይነት ሲሆን ነው። ቸልተኛነት ቀጥተኛና ኢ-ቀጥተኛ ተብለው ለሁለት ይከፈላሉ። በአጭሩ ቀጥታዊ ቸልተኛነት /Direct or Advertent Negligence/ የሚባለው ወንጀል አድጊው የሚፈጽመው ተግባር ህገ-ወጥ ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል ቢያውቅም አይደርስም ብሎ ክዶ አልያም ግምት ወስዶ የፈፀመ ሲሆን ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ወንጀል አድራጊው የሚፈፅመው ተግባር ህገ-ወጥ ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል የማያውቅ ሲሆን ነገር ግን ማወቅ የሚችልበት ምቹ ሁኔታ እያለ ይሄን ባለመገመት ወይም ባለማሰብ በሚፈፅምበት ጊዜ ኢ-ቀጥታዊ ቸልተኝነት /Indirect or Inadvertent Negligence/ ይባላል። ለምሳሌ አለማየሁ መኪናውን በሚያሽከረክርበት ወቅት ከፍጥነት በላይ ቢያሽከረክርና በመንገደኛ ላይ አካል ጉዳት ቢያደርስ ቸልተኛ በመሆኑ ላደረሰው ጉዳት ይጠየቃል።

 

አስቦ ወንጀል ማድረግ /Intention/


ሌላው የሀሳብ ክፍል አስቦ ወንጀል ማድረግ የሚባለው ክፍል ነው። ይሄ ክፍል ወንጀል አድራጊው ስለወንጀሉ ሙሉ ግንዛቤ ማለትም ዉጤቱን የሚያወቅ መሆኑና ለዚህም ፈቃደኛ የሆነ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ይህ ማለት ወንጀልን አስቦ ማድረግ ሁለት ዋና ዋና ክፍሎች እንዳሉት መገንዘብ ይቻላል። አንደኛው አንድ ግለሰብ ሊያደርግ ያለው ድርጊት ምን ውጤት እንዳለው የመገንዘቡ ሁኔታ (full knowledge) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የወንጀሉን ውጤት ለመቀበል የወሰነ ወይም ለውጤቱ ፍላጎት ያለው (Will or Volition) መሆኑ ነው። የድርጊቱን ውጤት መገንዘብ ሲባል ሊያደርግ ባለው አንድ እንቅስቃሴ ምክንያት ተከትሎ የሚመጣውን ውጤት በአግባቡ መረዳት ሲሆን ምክንያቱም ሆነ ውጤቱ በሕግ የማይፈቀድ መሆኑን የተረዳ መሆኑንም ያሳያል። ለምሳሌ አንድን ግለሰብ በሽጉጥ ጭንቅላቱን ተኩሶ መምታት የሚገድል ተግባር መሆኑን የሚያውቅና የተገነዘበ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ሌላው የሀሳብ ክፍል ደግሞ ውጤቱን የተቀበለ ወይም የፈቀደ መሆኑ ሲሆን ውጤቱን ለማግኘት ተገንዝቦ የፈቀደ፣ ፍላጎት ያለው ወይም ይሁን ያለው ነው። ወንጀልን አስቦ የማድረግ ሀሳብ በሁለት የሚከፈሉ ናቸው። የመጀመሪያው ቀጥተኛ /Direct Intention/ የሚባለው ሲሆን ወንጀል አድራጊው በሚያደርገው ተግባር ሊገኝ የሚችለውን ዉጤት ተገንዝቦና ለማግኘትም ፈልጎ /full knowledge/ ድርጊቱን ፈቅዶ /will or volition/ ያደረገ እንደሆነ ነው። ኢ-ቀጥተኛ /Indirect Intention/ የሚባለው በአንፃሩ ደግሞ ወንጀል አድራጊው በሚያደርገው ተግባር ሊገኝ የሚችለውን ውጤት የተገነዘበ ሲሆን ነገር ግን ለውጤቱ ቀጥተኛ የሆነ ፍላጎት ባይኖረውም ድርጊቱን ከመፈፀም ከመታቀብ ይልቅ ውጤቱን የተቀበለና የመጣው ይምጣ ብሎ የተጓዘ መሆኑን የሚያሳይ ነው። እነዚህን የሀሳብ ከፍሎች ከግለሰቡ ተግባር እና ከባቢያዊ ሁኔታዎች መገንዘብ የሚቻልና ከሳሽ ዐ/ህግ ይህን እርግጠኛ ሆኖ ክሱን ማቅረብ ይኖርበታል። ከላይ ባየነው ምሳሌ ላይ ከበደ ገንዘቡን ሆነ ብሎ መውሰዱ የወንጀል አድራጊውን የሀሳብ ክፍሉን ወይም ሞራላዊ ፍሬ ነገሩን ያሳየናል።


በሌላ በኩል ተገቢ የሆኑትን የትራፊክ ህግጋቶች ጠብቆ የሚያሽከረክር ግለሰብ ያለጥፋቱ በመንገደኛው ስህተት ቢገጭና ቢገድል ጥፋተኛ ሊሆን እንደማይችል የወንጀል ህጉ አንቀፅ 57(3) ይደነግጋል፤ ምክንያቱ ደግሞ ሞራላዊ ፍሬ ነገር ማለትም ችልተኝነትም ሆነ በማሰብ ወንጀልን የማድረግ ሀሳብ የለውምና።

 

የወንጀል ኢ-ሀላፊነት


የወንጀል ኢ-ሀላፊነት የሚባለው ወንጀል አድራጊው በወንጀል ህግ ተጠያቂና ተቀጪ ሊሆን የማይችልባቸው ሁኔታዎች ሲሆኑ የወንጀል ተግባር ወይም ግዙፋዊ ፍሬ ነገር ተፈፅሞ ሞራላዊ ፍሬ ነገር ሊጓደል የሚችልባቸው ሁኔታዎች ናቸው። እነዚህ ሁኔታዎች ከግለሰቡ ሞራላዊ ቅኝት አንፃር የሚታዩ ሲሆን በወንጀል ህጉ አንቀጽ 48 እና 49 ላይ ተመልክተዋል። እስከ 9 ዓመት ድረስ ያሉ ልጆች፣ በሚያደርጉት ድርጊት የሚያስከትለውን ውጤት የማይገነዘቡ ወይም ውጤቱን ተገንዝበው ፍላጎታቻውን ወይም ፈቃዳቸውን መቆጣጠር የማይችሉ የአእምሮ ህሙማን እና በሌሎች ስነ-ህይወታዊ ምክንያቶች የተግባራቸውን ውጤት አልያም የፍቃዳቸውን ሁኔታ መገንዘብ ወይም መቆጣጠር ያልቻሉ ግለሰቦችን በተመለከተ ተገቢው እርዳታ የሚደረግላቸው እንጂ የሚቀጡ እንዳልሆኑ ህጉ ይደነግጋል። (እዚህ ላይ ምንም እንኳ በኋላ በዝርዝር የምንመለከተው ቢሆንም በፍሬ ነገር መሳሳትን በተመለከተ አንቀጽ 48 እና 49 ላይ ያልተካተተ መሆኑን ልብ ይሏል!) ለምሳሌ አንድ የአእምሮ ህመምተኛ አንድን ግለሰብ ሊገል ካለው ጠላት እየተከላከለለት መስሎት ግለሰቡን ቢገድልና በእውነቱ ግን ይህን ግለሰብ ሊያጠቃ የመጣ ሌላ ግለሰብ ባይኖር ይህ የአእምሮ ህመምተኛ የተግባሩን ውጤትም ሆነ ለውጤቱ ፍላጎት የሌለው በመሆኑ በወንጀል ህግ ሊቀጣ አይችልም።


በህግ የተፈቀዱ፣ የማያስቀጡና ይቅርታ የሚያሰጡ


ሌላው በወንጀል ሕጉ ግዙፋዊ ፍሬ ነገር ተፈፅሞ ነገር ግን ቅጣት ተፈፃሚ የማይሆንበት ሁኔታ እንዳለ ከአንቀፅ 68 እስከ አንቀፅ 81 ድረስ ያሉትን ድንጋጌዎች መመልከት እንችላለን። እነዚህ ድንጋጌዎች ድርጊቱ እንዲፈፀም በሕግ የተፈቀዱ ወይም ክልከላ ያልተደረገባቸው ወይም የማያስቀጡና ይቅርታ የሚያሰጡ ሲሆኑ ከላይ ከህጋዊነት መርህ ወይም ፍሬ ነገር ጋር ሊገናኙ የሚችሉ ናቸው። በህጋዊነት መርህ ላይ አታድርግም አድርግም ብሎ የሚያዝ ደረቅ የሆነ ህግ ባለመኖሩ ምክንያትና ብሎም ሁኔታዎችን መሰረት ባደረገ መልኩ ማድረግ የተፈቀደበት ሁኔታ መኖሩን ከሕጉ መገንዘብ ይቻላል። በአንቀጽ 68 ላይ ወታደራዊ ወይም መንግስታዊ ስራዎችን ለማከናወን የሚፈፀሙ ድርጊቶች የተፈቀዱ ድርጊቶች ወይም ያልተከለከሉ በመሆናቸው ሊያስቀጣ እንደማይችል ይደነግጋል። ለምሳሌ አንድ ወታደር በጦር ሜዳ ውስጥ ለሚገድለውና ለሚያቆስለው እንዲሁም ለሚያወድመው ንብረት የሕግ ተጠያቂነት እንደሌለበት መገንዘብ ይቻላል። አንዲሁም በአንቀፅ 69 መሰረት የሙያ ግዴታን ለመወጣት ሙያዊ ስነ-ምግባርን ተከትሎ እስከተከናወነ ድረስ የተፈቀደ ተግባር በመሆኑ ሊያስጠይቅ አይችልም። እንደምሳሌ የቀዶ ጥገና ህክምናን ሙያ ብንወስድ የአንድ ግለሰብ አካል ላይ ጉዳት አድርሶ የሚከናወን ህክምና ቢሆንም ሙያዊ ስነ-ምግባርን ተከትሎ እስከተፈፀመ ድረስ የተፈቀደ ተግባር ነው። የማያስቀጡና ይቅርታ የሚያሰጡ ጥፋቶችን በተመለከተም የወንጀል ህጉ ከአንቀጽ 70 እስከ 81 ድረስ ደንግጓቸው እናገኛለን። እነዚህ ሀሳቦች በመሰረቱ ወንጀልን ከሚያቋቁሙ ሶስት ፍሬ ነገሮች መካከል አንዱን የሚያጓድሉ ሁኔታ ሳይሆኑ ከተለያዩ ነገሮች በመነሳት ያለመቅጣትና ይቅርታን ተፈፃሚ የማድረግ ሁኔዎች ናቸው። ከነዚህም መካከል በስህተት ወንጀልን ስለማድረግ የሚያትተው የህግ ድንጋጌ በአንቀፅ 80 እና 81 ላይ ሲሆን በአንቀፅ 80 ላይ በፍሬ ነገር መሳሳትን በአንቀፅ 81 ላይ ደግሞ በሕግ ላይ መሳሳትን ደንግጓል /በዚህ ፅሁፍ ውስጥ ከአላማው አንፃር በህግ ላይ መሳሳት አልተካተተም/። በመቀጠል በፍሬ ነገር መሳሳትን በዝርዝር እንመልከት።

 

በፍሬ ነገር መሳሳት /Mistake of Fact/


በፍሬ ነገር መሳሳት ማለት በማሰብ ሳይሆን ቅንና ሐቀኛ በሆነ መንገድ አንድ ሁኔታ፣ ክስተት ወይም ፍሬ ነገር በተጨባጭ ቢኖርም ባይኖርም የራስን ግንዛቤ በመያዝ የሚፈፀም ድርጊት ነው። በዚህ ትርጉም ውስጥ በአንድ በኩል የግለሰቡ ግንዛቤ በተጨባጭ ካለው ሁኔታ ጋር በከፊልም ሆነ በሙሉ የማይገናኝ እንደሆነ መረዳት የሚቻል ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በተጨባጭ ያለው ክስተት ወይም ሁኔታ ሊኖርም ላይኖርም የሚችል መሆኑን ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል። ፍሬ ነገሩ ሌላ ሆኖ የግለሰቡ ግንዛቤ ደግሞ ሌላ በመሆኑ ሳቢያ የተፈፀመውን ድርጊት በስህተት ላይ የተመሰረተ ያደርገዋል። ይህ እሳቤ የሚያጠነጥነው በግለሰቡ የሀሳብ ክፍል ላይ እንደሆነ ማየት የሚቻል ሲሆን የወንጀል አድራጊው የሀሳብ ክፍል ሕጋዊ ነገሮችን ለማድረግ ያሰበ ቢሆንም በስተመጨረሻ ላይ ግን ሕገ ወጥ ተግባርን የማድረግን ሁኔታን የሚያሳይ ነው። በአጠቃላይ የግለሰቡ ግንዛቤና ፈቃድ ካደረገው ተግባር ጋር የሚጣጣምና የሚገናኝ አይደለም። በሌላ አነጋገር ሁኔታውን የተገነዘበ ቢሆን ኖሮ የወንጀል ተግባሩን እንደማያደርገው ወይም እንደማይፈፅመው የሚታወቅና እርግጠኛ ሊሆን የሚቻልበትን ሁኔታ ነው። ታዲያ ይህ ሁኔታ በተከሰተበት ወቅት ግለሰቡ በሕግ የሚጠየቅበት ወይም የሚቀጣበት አግባብ አንደማይኖር የህግ ፍልስፍናውም ሆነ የሀገራት የወንጀል ህግ ያስገነዝቡናል። በሕግ ፍልስፍናው አንድ ግለሰብ ሊጠየቅና ሊቀጣ የሚገባው የሀሳብ ክፍሉ ሲሟላ እንደሆነ ቀደም ብለን አይተናል። በዚህ መለኪያ መሰረት ደግሞ በስህተት የተፈፀመ ወንጀል የሀሳብ ክፍሉ እንደሌለው ማየት ይቻላል። አንድ ግለሰብ ሊያደርግ ያለው ድርጊት ምን ወጤት እንዳለው የመገንዘቡ ሁኔታ (full knowledge) በግንዛቤው ሳቢያ የተዛባ በመሆኑና የወንጀሉን ውጤት ያልተቀበለበት ሁኔታ በመኖሩ ወይም የወንጀሉን ሁኔታ ቢቀበልም እንኳን በህግ በተፈቀደለት መሰረት (ይህ ሁኔታ በጥንቃቄ በእያንዳዱ ጉዳዮች ሊታዩ የሚገባቸው መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል) ተግባሩን እየተወጣ መሆኑን ተረድቶ የወሰነ ወይም ለውጤቱ ፍላጎት ያለው (Will or Volition) በመሆኑ የሀሳብ ክፍሉን ስንኩል ወይም ያልተሟላ ያደርገዋል። ይህ ደግሞ ወንጀል እንደተፈፀመ የማያስቆጥር በመሆኑ ግለሰቡ በሕግ ሊጠየቅም ሆነ ሊቀጣ አይችልም።


በፍሬ ነገር መሳሳት ሁለት አይነት ሊሆን ይችላል። የመጀመሪያው መሰረታዊ ስህተትን መፈፀም /Fundamental mistake/ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ መሰረታዊ ያልሆነ ስህተትን መፈፀም /Non-Fundamental/ ነው።

 

መሠረታዊ ያልሆነ ስህተት /Non-Fundamental/


መሠረታዊ ያልሆነ ስህተት /Non-Fundamental/ የሚባለው ወንጀሉ የተፈፀመበት ግለሰብ ወይም የግል ተበዳይ እና ወንጀል ለማድረግ ከታቀደበት ግለሰብ ጋር ልዩነት መኖሩ /Mistake of identity of Victim/ ሲሆን ሌላኛው ድርጊቱ የተፈፀመበት ነገር /Object/ ወንጀል ለማድረግ ከታሰበው ነገር /Object/ ጋር ልዩነት ያለው መሆኑ /mistake of Object of the Offence/ ነው። እንደ እንግሊዝና ካናዳ ያሉ ሀገሮች ደግሞ ይህንኑ ሀሳብ የተሻገረ ወንጀል የማድረግ የሀሳብ ክፍል /Transferred Intent/ በሚለው የሚገልፁት ሲሆን ተመሳሳይነት ያላቸው ሀሳቦች ናቸው። ይህ አይነት ስህተት በወንጀል አድራጊው የሀሳብ ክፍል ውስጥ ያለው እሳቤ ለይቶ በሚያውቀው ግለሰብ ላይ ሊፈፅም የፈለገውን ድርጊት በሌላ ባላሰበው ግለሰብ ላይ የፈፀመው እንደሆነ ነው። ይህ አይነት መሳሳት መሰረታዊ ስህተት ሊባል የማይችል ሲሆን ወንጀል አድራጊውም በሕግ ተጠያቂ ሆኖ ሊቀጣ እንደሚገባ በወንጀል ሕጋችን 80(3) ላይ በግልፅ ተመልክቷል። ይህ የሆነበት ምክንያት በዋናነት የወንጀል አድራጊው ወንጀል የማድረግ የሀሳብ ክፍል አልተሟላም ለማለት የማያስችል ሲሆን ግለሰቡ ሌላ ግለሰብን ለማጥቃት ያሰበና ውጤቱንም ተቀብሎ የፈቀደ በመሆኑ የተሟላ የሀሳብ ክፍል አዝሎ ተንቀሳቅሷል ሊባል የሚችል ነው። የወንጀል አድራጊው መሳሳት የግል ተበዳዮች መቀያያርን ብቻ ያስከተለ በመሆኑ መሰረታዊ ስህተት አያሰኘውም። የህጉ አላማ ግለሰቦችን ከመጠበቅ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ወንጀል አድራጊው ያሰበው ግለሰብ ላይም ሆነ ያላሰበው ግለሰብ ላይ ጉዳት እስከ ደረሰ ድረስ ሕጉ ወንጀል አድራጊውን ይጠይቃል፣ ይቀጣል። ለምሳሌ አንድ ግለሰብ ከበደ የተባለውን ለመግደል በማታ መሸጎ ጠብቆ ሳለ አየለ የተባለን ግለሰብ ቢገድል በሕጉ መሰረት ይጠይቃል። ሕጉ ወንጀል አድራጊው ወንጀሉን የፈፀምኩት በስህተትነው ሊል እንደማይችል በግልፅ ያስገነዝበናል። ሌላው መሰረታዊ ያልሆነው ስህተት በወንጀሉ አላማ ወይም ነገር ላይ የተፈፀመ ልዩነት /mistake of Object of the Offence/ ሲሆን ግለሰቡ አላማ አድርጎ የተነሳውን ፈፅሜያለሁ ብሎ ያሰብ ቢሆንም ነገር ግን እንደ እቅዱ ሳይሆን ከዛ በተለየ የወንጀል ፍሬ ቢይዝ ወይም ቢያገኝ ማለት ነው። ለምሳሌ አንድ ግለሰብ እጅግ ውድ የሆነ እንቁ የሰረቀ መስሎት እውነተኛ ያልሆነ ወይም አርቴፊሻል እንቁ ቢሰርቅ በወንጀል ተጠያቂ ልሆን አይገባም ማለት አይቻልም። ሕጉ እንዲህ አይነት ስህተቶችን ከለላ ያልሰጣቸው ስህተቶች ናቸውና ተጠያቂነትን አስከትሎ ቅጣትን ተፈፃሚ ያደርጋል።


መሠረታዊ ስህተት /Fundamental mistake/


ሌላው መሠረታዊ ስህተት /Fundamental mistake/ የሚባለው አይነት ሲሆን በወንጀል ህጋችን አንቀፅ 80(1) የተመለከተና ወንጀል አድራጊውን ከቅጣት ነፃ የሚያደርግና ይቅርታ የሚያሰጥ አይነት ስህተት ነው። ይህ አይነት ስህተት የወንጀል አድራጊውን ወንጀል የማድረግ ሀሳብ ቀሪ የሚያደርግ በመሆኑ ግለሰቡን ያለሀሳቡ ተጠያቂ ማድረግ ስለማይቻልና ፍትሀዊ ስላልሆነ ከተጠያቂነት ነፃ የሚሆንበት የህግ ስርዓት ነው። ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ፍሬ ነገሩ ሌላ ሆኖ የግለሰቡ ግንዛቤ ደግሞ ሌላ በመሆኑ ሳቢያ የተፈፀመው ድርጊት እንደ መሰረታዊ ስህተት ተቆጥሮ በወንጀል ህጉ አንቀፅ 80(1) መሰረት ተጠያቂነትንና ቅጣትን አያስከትልም። እዚህ ላይ የምንገነዘበው በወንጀል አድራጊው ተግባርና በወንጀል አድራጊው ግንዛቤ፣ ፍላጎት ወይም ፈቃድ መካከል ግንኙነት የሌለ መሆኑን ነው። በሌላ አነጋገር የወንጀል ድርጊቱ ኖሮ የሀሳብ ክፍሉ የሌለበት ሁኔታን የሚያሳይ ነው። መሰረታዊ ስህተት በሶስት አይነት መልኩ ሊንፀባረቅ ይችላል። የመጀመሪያው መሰረታዊ የስህተት አይነት እውነታውና የወንጀል አድራጊው ግንዛቤ የተለያየ ሲሆን ነው። ይህ አይነት ስህተት በመሰረቱ ያልተፈቀደና ክልከላ የተደረገበት ተግባር የተፈፀመ ቢሆንም ሆን ተብሎ ያልተፈፀመ በመሆኑ ሕጉ የሚሰጠው ልዩ አስተያየት ነው። ለምሳሌ በካፌ ውስጥ አንድ ግለሰብ የራሱ የሞባይል ስልክ መስሎት የሌላን ግለሰብ ስልክ ይዞ ቢሄድ እንደማለት ነው።


ሁለተኛው መሰረታዊ የስህተት አይነት የወንጀል አድራጊው ድርጊት የተፈቀደ ወይም ክልከላ ያልተደረገበት ሆኖ ነገር ግን ድርጊቱ የተፈፀመው በህግ በተፈቀደው አግባብ (በወንጀል ሕጉ 68 እና 69) ባለመሆኑ ምክንያትና ግለሰቡ በህግ በተፈቀደው መሰረት ተግባሩን እያከናወነ መስሎት ያደረገው ተግባር ነው። ለምሳሌ አንድ ፖሊስ በሕጉ በተፈቀደለት መሰረት ወንጀል የፈፀመን ተጠርጣሪ ለመያዝ ብሎ ነገር ግን ወንጀል ያልፈፀመን ሌላ ግለሰብ ቢይዝ የወንጀል ሕጉ ይቅርታ የሚሰጥበት ሁኔታን ይመለከታል። ነገር ግን ይህ ግንዛቤ አግባብ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን በተመለከተ ፍ/ቤቱ ግላዊ፣ ከባቢያዊና ምክንያታዊ ሁኔታን ተመልክቶና የግለሰቡን ትክክለኛ ሀሳብ ለመገንዘብ ከታች የምንመለከታቸውን መመዘኛዎች መሰረት በማድረግ የሚመዝነው ወሳኝ ጭብጥ መሆኑን ልብ ይሏል።


ሶስተኛው መሰረታዊ የስህተት አይነት የሚባለው ወንጀል አድራጊው ወንጀሉን ለማድረግ ወስኖ የተንቀሳቀሰ ቢሆንም በማክበጃነት የተመለከቱትን ፍሬ ነገሮች በፍፁም ያልተገነዘበውና ያልፈለገው ነገር ግን የፈፀመው ድርጊት ነው። ለምሳሌ ወንጀል አድራጊው አንድን ግለሰብ ቢሰድበውና ቢያዋርደው ነገር ግን ግለሰቡ የመንግስትን ስራ በማከናወን ላይ ያለ ቢሆን ወንጀል አድራጊው ይህን ጉዳይ እስካልተገነዘበ ድረስ በከባድ ድንጋጌ ማለትም በወንጀል ሕጉ 618 ሳይሆን የሚጠየቀውና የሚቀጣው ባወቀው ልክ ብቻ ማለትም በአንቀፅ 615 መሰረት ነው።


መሰረታዊ ስህተት የማያስቀጣና ይቅርታ በሕጉ መሰረት የሚያሰጥ መሆኑ በመርህ ደረጃ የተቀመጠ ቢሆንም በልዩ ሁኔታ ደግሞ በቸልተኛነት እና በሌላ አስከትሎ ባደረገው ወንጀል ልክ የሚጠየቅ መሆኑን በአንቀፅ 80(2) ላይ ያስቀምጣል። ምንም እንኳ ግለሰቡ ወንጀሉን የፈፀመው ሆነ ብሎ ባይሆንም ነገር ግን ሊወስድ የሚገባውን ጥንቃቄ ቢወስድ ኖሮ ወንጀሉን አይፈፅምም ነበር የሚያስብል እንደሆን ወንጀል አድራጊው በቸልተኛነት ወንጀሉን በመፈፀሙ ሊጠየቅ ይችላል። በሌላ ሁኔታ ደግሞ ምንም እንኳን በአንድ በኩል የተፈፀመው ወንጀል በወንጀል አድራጊው የሀሳብ ክፍል ውስጥ የሌለ ቢሆንም በሌላ መልኩ ደግሞ ሌላ ወንጀልን ሊያቋቁም የሚቻልበት ሁኔታ አለ። ይሀ አይነት ሁኔታ በአብዛኛው በተደራራቢ ወንጀሎች ላይ የሚንፀባረቅ ነው።


ከላይ ያየናቸውን የፍሬ ነገር መሳሳት ጉዳዮች እንዴት መመዘን ይቻላል የሚለውን ቀጥሎ ድግሞ እንመልከት።

 

በፍሬ ነገር የመሳሳት መመዘኛ


መሰረታዊ የፍሬ ነገር ስህተት /Fundamental mistake/ መኖር አለመኖር ለማወቅና ለማረጋገጥ በተለያዩ ሀራት የተለያዩ መመዘኛዎችን ይጠቀማሉ። እነዚህ መመዘኛዎች ከግለሰብ /ወንጀል አድራጊው/፣ ከወንጀል ህጉ አላማ እና ከማህበረሰቡ ደህንነትና ጥቅም አኳያ ሚዛናቸውን የጠበቁ መሆን እንዳለባቸው ይታመናል። ሆኖም የተለያዩ ሀገራት ወደ አንዱ የሚያጋድሉበት ሁኔታዎች እንዳሉ የሚስተዋል ነው። በአለማችን ላይ ካሉ መመዘኛዎች መካከል ቅቡል እየሆኑ የመጡ ሁለት መመዘኛዎች ሲኖሩ የመጀመሪያው መመዘኛ ሀቀኝነት /Honest/ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ምክንያታዊነት /Reasonableness/ ናቸው። አንዳንድ ጊዜም ሀቀኝነትና ምክንያታዊነት /Honest and Resonablness/ በጋራ ተግባር ላይ ሲወሉ እንደ ሶስተኛ መመዘኛ ተደርጎ የሚታይበት ሁኔታም አለ።


እነዚህ ሁለት መመዘኛዎች በአንዳንድ ሀገራት በተናጥል ሲጠቀሙባቸው ሌሎች ሀገራት ደግሞ በአንድነት ይጠቀሙባቸዋል (ሶስተኛ መመዘኛ)። ለዚህ መለያየት በዋናነት በፍሬ ነገር መሳሳት የሚታይበትና የሚስተናገድበት ሁኔታ ነው። በአንዳንድ ሀገሮች ወንጀል ከማድረግ ሀሳብ ክፍል ጋር እጅጉን በማቆራኘት መሳሳቱ እስከተፈጠረ ድረስ ከሳሽ ዐ/ህግ ይህ ስህተት ወንጀል የማድረግ ሀሳቡን ቀሪ እንዳላደረገ ተግቶ ማስረዳት እንዳለበት ሲያስገነዝቡ /ይህ አይነቱ ሀሳብ ከወንጀል ህጋችን አንቀጽ 48 እና 49 አንፃር ሊታይ ይገባዋል/ ሌሎች ሀገሮች ደግሞ ይህ አይነቱ ስህተት ተከሳሹ ሊከላከልበትና ለፍ/ቤቱ ሊያስረዳ የሚገባው እንዲሁም በልዩ ሁኔታ ሊታይ በጠባቡም ሊተረጎም እንደሚገባ ያስቀምጣሉ /In other words, where some regard mistake of fact in relation with negation of guilty intention others see it as an affirmation of positive defense by the accused/።


ሀቀኝነት /Honest/ የሚባለው መመዘኛ ወንጀል አድራጊው ወንጀሉን በሚፈፅምበት ወቅት የነበረው የሀሳብ ክፍል ወንጀል የማድረግ ሀሳብ እንዳልነበረውና ፍፁም ቅንነትና ሀቀኝነት የተሞላበት መሆኑን ብቻ የሚያይ ነው። ተንኮል አለው ወይስ የለውም የሚለውን ያያል። ምንም እንኳ አንድ ምክንያታዊ ሰው ወንጀል አድራጊው በተረዳው መንገድ ሊረዳው እንደማይችል ቢታወቅም ብሎም ወንጀል አድራጊው የተረዳበት መንገድ ጭራሹን የሚያስቅ ቢሆን እንኳን ሀቀኛ /Honest/ እስከነበረ ድረስ በወንጀል ሊጠየቅና ሊቀጣ እንደማይገባ የሚያስገነዝብ ነው። ይሄ መመዘኛ መሰረት የሚያደርገው የግለሰቡን የወንጀል የማድረግ ሀሳብ በራሱ አለው ወይስ የለውም የሚለውን ግላዊ /Subjective/ መመዘኛን ነው። (ይህ አይነት መመዘኛ በሀገራችን እድሜያቸው ከ9 ዓመት በታች እና በስነ-ህይወት ሳቢያ ሀሳብና ፈቃድ የሌላቸውን ግለሰቦች ብቻ የሚመለከት መለኪያ እንደሆነ ልብ ይሏል) ለዚህ መመዘኛ አይነተኛ ምሳሌ የምትሆነን ሀገር ካናዳ ነች። የካናዳ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰጠው ውሳኔ የወንጀል አድራጊው እምነት ወይም ሀቀኝነት ሊታይ የሚገባ እንጂ አድራጎቱ ምክንያታዊ ነበር የሚለው መመዘኛ ግምት ውስጥ ሊገባ እንደማይገባ አስገንዝቧል። ነገር ግን የግለሰቡን ሀቀኝነት ለመመዘን ከባቢያዊ ሁኔታዎችን መፈተሽ አስፈላጊ ነው። በዚህም ፍተሻ ወቅት ወንጀል አድራጊው ሀቀኛ ነበር ወይስ አልነበረም የሚለውን ለማወቅ ምከንያታዊነትን ከግምት ውስጥ የሚገባበት ሁኔታ አለ።


ሌላው መመዘኛ ምክንያታዊነት /Reasonableness/ ሲሆን ይህ አይነት መመዘኛ የግለሰቡን ወንጀል የማድረግ ሀሳብ ሀቀኛ ነበር ወይስ አልነበረም ከሚለው ባሻገር ተጠራጣሪ የሆነና ወንጀል አድራጊው የደረሰበት ግንዛቤና ድምዳሜ ላይ አንድ ምክንያታዊ ሰው በቦታው እና በሰዓቱ ቢኖር ኖሮ ተመሳሳይ ግንዛቤና ድምዳሜ ላይ ይደርስ ነበር ወይ የሚለውን ይፈትሻል። በዚህ መለኪያ መሰረት የወንጀል አድራጊው ሀሳብ የሚፈተሸው በአንድ ምክንያታዊ ሰው /Reasonable Man/ አስተሳሰብ ሲሆን አስቂኝ አረዳዶች ብሎም ከምክንያታዊው ሰው በታች ያሉ ግንዝቤዎች ተቀባይነት የላቸውም። በመሰረቱ የአንድን ግለሰብ የሀሳብ ሁኔታ ፈትሾ ማወቅ እጅግ አዳጋች ሲሆን በተለይ ፍተሻው ያለመመዘኛ ወይም ከራሱ ከወንጀል አድራጊው በመነሳት ፍተሻ የሚደረግ እንደሆን የወንጀል ህጉን አላማና የህብረተሰብን ጥቅም በእጅጉ ችግር ውስጥ የሚከትና የፍትህ መጓደልን ሊያስከትል ይችላል። የምክንያታዊነት /Reasonableness/ መመዘኛ ግላዊ ያልሆነ /Objective/ ሲሆን ይህን አይነት መለኪያ የሚጠቀሙ ሀገሮች የፍሬ ነገር መሳሳትን በልዩ ሁኔታ የሚያዩና በመከላከያነት የሚቀርብ /Affirmative Defense/ መሆኑን በህጋቸው የደነገጉ ሀገራት ናቸው። ይህም ማለት ሕጉ ወንጀል አድራጊው ጥፋት አላጠፋም የሚለውን ሀሳብ ለማንፀባረቅ ሳይሆን ከነባራዊው ሁኔታ በመነሳት የቅጣትን እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ በይቅርታ ማለፍን የመረጠ ከመሆኑ ጋር የሚያያዝና በጠባቡ የሚተረጎም የህግ ፍልስፍና ነው። አሜሪካ የምክንያታዊነትን /Reasonableness/ መለኪያ የምትገለገል መሆኑን ከተለያዩ ፅሁፎች መገንዘብ ይቻላል። ይህ ሲባል የግለሰቡን የወንጀል የማድረግ ሀሳብ መኖር አለመኖሩን የምትመዝነው በምክንያታዊው ሰው /Reasonable Man Standard/ አስተሳሰብ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል (The Mistake of Fact Defence and the Reasonable Requirment, Margaret F. Brinig)።


ሌሎች ሀገሮች ደግሞ ሁለቱንም መመዘኛ በአንድ ላይ ይገለገሉበታል። እንግሊዝ ሁለቱንም መመዘኛ የምትገለገል ሀገር መሆኗን ማወቅ ይቻላል (Mistake of fact, Canadian Bar Association, National Justice Section Committee on Criminal Code Reform)። ይህ መለኪያ ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት መለኪያዎችን በጋራ ተግባር ላይ የሚያውል ከመሆኑ ባሻገር የትርጉም ልዩነት የለው።


ኢትዮጵያ በፍሬ ነገር መሳሳትን በተመለከተ በወንጀል ህጓ አንቀጽ 80 ላይ የደነገገች መሆኑን ቀደም ሲል አይተናል። ይህ መሳሳት ከላይ ካየናቸው 2 (ወይም 3) መመዘኛዎች አንፃር ህጉ የቱን ይደግፋል የሚለውን ማየት ተገቢነት አለው። በአንድ በኩል ድንጋጌው በቀጥታ ሲታይ የወንጀል አድራጊውን የተሳሳተ ግንዛቤ መሰረት በማድረግ የሚታይ መሆኑን (ሀቀኝነትን /Honesty/) ሲያስገነዝብ በሌላ በኩል ደግሞ የህጉ አደረጃጀት በመከላከያነት /Affirmative defense/ የሚቀርብ እና በጠባቡ የሚተረጎም ልዩ አይነት ድንጋጌ እንደሆነ ከክፍሉ መገንዘብ ይቻላል (የወንጀል ህጉ ክፍል ሁለት የሚለውን ርዕስ ይመለከተዋል)። ይህ መሳሳት በአንቀጽ 48 እና 49 ላይ ከተመለከቱት ፍሬ ጉዳዮች (ማለትም እድሜንና የስነ-ህይወትን ጉዳይ ከተመለከቱት) ውስጥ ይልተካተተና በልዩ ሁኔታ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 80 ላይ ሰፍሮ እናገኘዋለን። ይህም ማለት ሕጉ በመከላከያነት ከሚቀርቡ /Affirmative defense/ ፍሬ ጉዳዮች ጋር እንዲታይና እንዲስተናገድ አልሞ ያሰፈረው ሀሳብ ነው። ይህ እንደሆን ደግሞ የማስረዳት ግዴታን በተከሳሹ ላይ የሚጥል በመሆኑ ልቅ ሆኖ የሚተረጎም ሳይሆን ምክንያታዊነትን /Reasanableness/ መሰረት አድርጎ የሚታይ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። ነገር ግን ህጉ ከአደረጃጀቱና ከድንጋጌው በመነሳት ቅይጥ መለኪያን ይተገብራል ቢባል መሳሳት አይሆንም። ይህም ሲባል የሀቀኝነትን /Honest/ እና የምክንያታዊነትን /Resonableness/ መመዘኛዎች በጋራ ህጉ አካቷል ለማለት ነው። በተጨማሪ የወንጀል ሕጉን አቀራረፅ ብንመለከት ከ1949 ዓ.ም ወንጀለኛ መቅጫ ህግ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሲሆን በፍሬ ነገር የመሳሳትን ጉዳይ በሁለቱም ህጎች ተደንግጎ እናገኘዋለን። የወንጀለኛ መቅጫ ህግን የቀረፁት ፊሊፕ ግሬቨን /phillipe Graven/ የፍሬ ነገር መሳሳትን ምዘና ለማድረግ ሁለቱን መመዘኛዎች ባማከለ ሁኔታ የተደነገገ መሆኑን በፅሁፋቸው ሲያስገነዝቡ አሁን በስራ ላይ ያለው የወንጀል ህግም ከቀድሞ የተቀዳ በመሆኑ በዚህኛውም ህግ መለኪያው ተመሳሳይ እንደሆነ መረዳት ይቻላል ማለት ነው። 


በአጠቃላይ በፍሬ ነገር በመሳሳት የሚፈፀም ወንጀል መሰረታዊ ስህተት መሆን እንዳለበት፤ የሀቀኝነትን /Honest/ እንዲሁም የምክንያታዊነትን /Resonableness/ መለኪያ በጋራ በመየዛ ሊመዘን የሚገባው ጉዳይ ነው። እነዚህን መመዘኛዎች ግልጋሎት ላይ ለማዋል የወንጀሉ አፈፃፀም፣ ቀጥታዊና ከባቢያዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ማስገባትም የሚገባ ይሆናል። 

 

ንጉሴ ረዳኢ www.abyssinialaw.com

1. የመዘዋወር ነፃነት አለም አቀፋዊ አንድምታው

 

የሰው ልጅ ሰው ሆኖ በመፈጠሩ ከሚያገኛቸው አያሌ የተፈጥሮ መብቶች ውስጥ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነት በቀዳሚነት ይጠቀሳል። የሰው ልጆችን ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነት ከሐይማኖት፤ ከባህል እና ከሌሎች የተፈጥሮ ህግጋት ጀምርን ስንመለከተው ፅኑ መሰረት ያለው ሆኖ እናገኘዋለን። በአለማችን ታሪክ ይህ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር መብት በአንዳንድ የታሪክ አጋጣሚዎች ላይ ተገድቦ የነበረ ቢሆንም በአብዛኛው ግን ሰዎች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር መብታቸው ሲከበር ቆይቷል። ይሄንን ተፈጥሮአዊ መብት በመጠቀም የተለያዩ የአውሮፓ ሰዎች አዲስ ግኝትን፤ የመካከለኛውና የሩቅ ምስራቅ ሀገሮች ደግሞ ንግድን በማጧጧፍ ለሀገራቸው እና ለአህጉራቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አበርክተዋል። ይህንን ጥቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደ ማግና ካርታ (Magna Carta) አይነት ጥንታዊ ሰነዶች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር መብትን አውጀዋል። ከዚህ በተጨማሪ በታላቋ ሮም የነገሱ አብዛኛው ነገስታት ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነትን ሲያከብሩ መቆየታቸውን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።


ይሁን እንጅ አለማችን በታሪኳ ካጋጠሟት ጠባሳ ታሪክ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የሁለተኛው የአለም ጦርነት እና ከዚህ ጦርነት ጋር በተያያዘ ከተከሰቱ እጅግ አስከፊ የመብት ጥሰቶች መካከል ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነት ይጠቀሳል። አንድ ችግር ሲፈጠር ለችግሩ መፍትሄ መስጠት ወይም መንገድ ማበጀት የሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ ባህሪው በመሆኑ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት የተፈጠሩ የመብት ጥሰቶችን በማስመልከት የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደው ነበር። ከተወሰዱ እርመጃዎች መካከል አለም አቀፍ የሰበዓዊ መብት ተቋማትን መመሰረትና አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሰነዶችም ማዘጋጀት ይጠቀሳሉ። በዚህም መሰረት በተቋም ደረጃ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሲቋቋም በሰብዓዊ መብት ሰነድ ደረጃ ደግሞ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ (Universal Declaration of Human Rights) እና ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት (International Covenant on Civil and Political Rights) በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ በአንቀፅ 13[1] ላይ በግልፅ ለመዘዋወር ነፃነት እውቅና የሰጠ ሲሆን የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት ደግሞ በአንቀፅ 12 ላይ ተመሳሳይ ድንጋጌ አስቀምጧል። በተለይ ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት በአንቀፅ 12 ላይ በመርህ ደረጃ ይህ መብት ገደቦች የሌሉበት ቢሆንም በልዩ ሁኔታ በህግ በተደነገጉ ቀድመ ሁኔታዎች አማካኝነት ሊገደብ የሚችልበት ሁኔታዎች አሉ። እነዚህ ሁኔታዎች ከብሔራዊ ደህነት፤ ከህዝብ ሞራል እና ጤና ጋር የሚያያዙ ናቸው። እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎችን መሰረት አድርጎ የሚወጣ ህግ ከአድሎ ነፃ የሆነ እና የትኛውንም ህዝብ በተለይ የሚጎዳበት አግባብ ሊኖር እንደማይገባው ይደነግጋል። በአጠቃላይ አለማችን አሁን በደረሰችበት የአእምሮ ማሰብ አድማስ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነት የሰው ልጅ ከተሰጡ መሰረታዊ መብቶች ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ከመሆኑ አንፃር የአለማችን የህግ ሰዎችም ሆኑ ፖለቲከኞች በአስፈላጊነቱ ዙሪያ ሙሉ ለሙሉ ይስማማሉ ማለት ይቻላል። በመሆኑም በአለም አቀፍ የልማዳዊ ህግ መስፈርቶች መሰረት ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነት የአለም አቀፍ የልማድ ህግነት ደረጃ ደርሷል ማለት እንችላለን። በመሆኑም ማነኛውም ሀገር፤ በሀገር ውስጥ ያለ አስተዳደራዊ ክልል እንዲሁም ማነኛውም መንግስታዊ ያልሆነ ተቋም ይህንን መብት የማክበር እና የማስከበር ግዴታ አለበት።
 
2.  ኢትዮጵያ የመዘዋወር ነፃነትን እንዴት ትመለከተዋለች?
 
የኢትዮጵያን ታሪክ ስንመለከት ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነት ከሌሎች መብቶች በተሻለ ሲከበር እንደነበር ማየት እንችላለን። ከኦሮሞ የጉድፈቻ ባህል ጀምረን እስከ አማራ እና ትግራይ የእንግዳ ተቀባይነት ልማድ ስንመለከት ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ነፃነት ከህግ አልፎ ህብረተሳባዊ መሰረት እንዳለው እንረዳለን። ከዚህ በተጨማሪ በአብዛኛው የኢትዮጵታ ክፍሎች የሚታወቀው “ቤቱ ስትሄድ የሚጮህ ውሻ ብቻ ነው” የሚለው አባባል ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነት የህዝቡ የቆየ ባህል እንደሆነ ያስረዳናል። በመሆኑም አንድ ማህበረሰብ ለአካባቢው አዲስ የሆነ በተለምዶ አጠራሩ ፀጉረ ልውጥ ወደ ቀየው ሲሄድ የተለየ እንክብካቤ እንደሚደረግለት ለማወቅ የገጠሪቱ ኢትዮጵያን ክፍል አንደ ጊዜ መጎብኘት በቂ ነው። በተናጠል ከሚደረገው መዘዋወር በተለየ በሀገራችን በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች የተነሳ በተከሰቱ የቡድን የህዝብ ዝውውሮች በተሳካ ሁኔታ ተፈፅመው አንዱ ህዝብ ከሌላው ህዝብ ጋር በአሁኑ ሰዓት ለመለየት እስከሚያስቸግር ድረስ ተዋህደው እየኖሩ ይገኛሉ።ይሄንን የኑሮ ዘይቤ በሚያጠናክር ሁኔታ የሚነገር “ሩቅ ካለ ዘመዴ ጎረቤት ያለ ባእድ ይሻለኛል”  የሚለው አባባል እንግዳን ተቀብለው አብረው ከሚኖሩ ህዝቦች በዘለለ በማያውቁት ቀየ በመሄድ ጎጇቸውን የሚቀለሱ ህዝቦች ከሌሎች ህዝቦች ጋር ያላቸውን ተላምዶ የመኖር ባህል ያሳየናል። በመሆኑም በህግ የተሰጠው ትርጓሜ በቀጣይ የሚታይ ሲሆን በማህበረሳዊ አንድምታው ስናየው በኢትዮጵያ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት እንደ ባህል የሚታይ ልማድ ነው። 


በኢትዮጵያ የመንግስት አስተዳደር የመዘዋወር ነፃነትን ስንመለከተው በሰነድ ማስረጃ የተደገፈ የመዘዋወር ነፃነት የሚገድብ ታሪካዊ ክስተት ለማግኘት ያስቸግራል። በተቃሪኒው የኢትዮጵያ ያለፉት መንግስታት በተለያዩ በተፈጥሮም ይሁን ሰው ሰራሽ በሆኑ ምክናያቶች ለሚከሰቱ ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት አንድን ህዝብ ከአንድ አካባቢ አንስተው ወደ ሌላ አካባቢ መወሰድ የተለመደ አሰራር ሆኖ ቆይቷል። በመሆኑም ኢትዮጵያ የመዘዋወር ነፃነትን ወጥ በሆነ መንገድ ተቀብላው እንደቆየች የባህል እና መንግስታዊ አሰራሮች ያስረዱናል። 
 
3.  የመዘዋወር ነፃነትን የሚመለከቱ ህጎች በአሁኗ ኢትዮጵያ
 
ከላይ የተመለከትነው ታሪካዊ እና ማህበረሰባዊ እውነታ በመንግስት አስተዳደር ውስጥ ነፍስ ዘርቶ እንዲሄድና ተፈፃሚ እንዲሆን በህግ አግባብ መውጣት ይኖርበታል። ይሄንን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በ1983 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው ኢህአዴግ የተለያዩ ህጎችን ሲያወጣ የመዘዋወር ነፃነትን በተመለከተ ድንጋጌዎችን በማካተት እና የመዘዋወር ነፃነት የሚመለከቱ አለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችን በመፈረም የመጀመሪያውን ቅድመ ሁኔታ ለማሟላት ጥረት አድርጓል። በመሰረቱ የአንድን ሃገር በአንድ ጉዳይ ላይ ያላትን የህግ አቋም ስንመለከት ከሀገሪቱ የበላይ ከሆነው ህግ መጀመር የተለመደ ነው። በዚህም መሰረት በ1995 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት ስናየው የመዘዋወር ነፃነትን የሚመለከት ድንጋጌ አካቷል። በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 32(1) መሰረት ማነኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ ሀገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ዜጋ በመረጠው የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከሀገር የመውጣት ነፃነት አለው። በዚህ አንቀፅ መሰረት አንድ ኢትዮጵያዊ በመረጠው በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወር ነፃነት ሲኖረው ከዚህም በላይ ይህ ግለሰብ በተዘዋወርበት አካባቢ በተመቸው ቦታ ላይ መኖሪያውን መስርቶ የመኖር ነፃነት ተሰጥቶታል። ከዚህ አንቀፅ ጋር በተያያዘ የሕገ-መንግስቱ ሌላው ድንጋጌ አንቀፅ 41(1) እንደሚገልፀው ማነኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ ውስጥ በማነኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የመሰማራትና ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመሥራት መብት አለው። ከዚህ አንቀፅ እንደምንረዳው ማነኛውም ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ የትኛውም አካባቢዎች በመሄድ የፈለገውን ስራ በመመረጥ የመስራት መብት እንዳለው ነው። በመሆኑም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 31 እና 41 መሰረት ማነኛውም ኢትዮጵያዊ በራሱ ፈቃድ በመረጠው የትኛውም የሀገሪቱ ክፍል በመሄድ መኖሪያውን የመመስረት እና በፈለገው ሙያ ላይ የመሰማራት መብት አለው። ከሕገ-መንግስቱ ድንጋጌዎች ስንወጣ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችን እናገኛለን። እነዚህ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 9(4) መሰረት የሀገሪቱ ህግ አካል በመሆናቸው ኢትዮጵያ እነዚህን ስምምነቶች የማክበር ግዴታ አለባት። ከላይ እንደተመለከትነው የመዘዋወር ነፃነትን በሚመለከት ከወጡ እና ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች መካከል ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ (Universal Declaration of Human Rights) እና ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት (International Covenant on Civil and Political Rights) በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ በአንቀፅ 13 ላይ በግልፅ ለመዘዋወር ነፃነት እውቅና የሰጠ ሲሆን የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት ደግሞ በአንቀፅ 12 ላይ ተመሳሳይ ድንጋጌ አስቀምጧል። በመሆኑም ኢትዮጵያ በራሷ ተነሳሽነት ካፀደቀችው ሕገ-መንግስት በዘለለ በፈረመችው (ባትፈርመው እንኳን የአለም አቀፍ የልማዳዊ ህግነት ደረጃን በደረሱት) የመዘዋወር ነፃነትን በሚመለከቱት እነዚህን አለም አቀፍ ስምምነቶችን የማክበር ግዴታ አለባት።  


በመርህ ደረጃ አንድ ህግ ሲዎጣ የወጣውን ህግ ተፈፃሚነቱን ለማረጋግጥ እንዲያስችል ህጉ የሰጠውን መብት ጥሰው በተገኙ አካላት ላይ ቅጣት ማስቀመጥ የተለመደ ነው። በዚህ መሰረት ስንመለከተው የመዘዋወር ነፃነትን በተመለከተ ማነኛውንም ጥሰት የፈጠረ አካል ላይ የወንጀል ቅጣት እንደሚጠብቀው በ2004 ዓ.ም የወጣው የወንጀል ህግ ያስረዳናል። በዚህ የወንጀል ህግ አንቀፅ 607 መሰረት ማንም ሰው በሕግ ሥልጣን ሳይኖረው ሌላው ሰው በኢትዮጵያ ውስጥ በነፃ እንዳይዘዋወር የከለከለ እንደሆነ በቀላል እስራት ወይም መቀጮ እንደሚቀጣ በመግለፅ ጥፋቱን የፈፀመው የመንግስት ሰራተኛ ከሆነ ግን ጉዳዩ በአንቀፅ 407 መሰረት እንደሚታይ ይገልፃል። የወንጀል ህጉ አንቀፅ 407 ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀምን የሚመለከት ሲሆን እንደቀረበው ጉዳይ ቅጣቱ ከአንድ አመት እስከ 15 ዓመት ከባድ ቅጣት ሊደርስ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ እንደቀረበው ማስረጃና ጉዳዩ ከተፈፀመበት ሁኔታ አንፃር ጉዳዩን ዘር ማጥፋትን ወደ ሚመለከተው አንቀፅ 269 (ሐ) መሰረት የሚታይበት የህግ አግባብ ተቀምጧል። በመሆኑም በአሁኑ ሰዓት ባለው የኢትዮጵያ ህግ አንፃር የመዘዋወር ነፃነት በህግ ሙሉ ለሙሉ እውቅና የተሰጠው ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ይሄንን ነፃነት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ መገደብ ከቀላል እስራት እስከ ሞት ድረስ የሚያስቀጣ የወንጀል ሃላፊነትን ያስከትላል።
 
4. በክልል የተገደበው የመዘዋወር ነፃነት
 
የአለም አቀፍ ህግ ሙህራን አንድ ሃገር ሰብዓዊ መብቶችን ለማክበር የሚጠበቅባትን ደረጃዎች ያስቀምጣሉ። ከእነዚህ ደረጃዎች ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የህግ ማእቀፍ መዘርጋት ሲሆን ከዚህ በመቀጠል ግን ተቋማትን መመስረትና ሌሎች የወጣውን ህግ የሚያስፈፅሙ እርምጃዎች መውሰድ ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ። ህግ ማውጣት የሚያወሩትን ላውራ (talking the talk) የሚባል ዋስትና የሌለው እርምጃ በመሆኑ ሌሎች የወጣውን ህግ በትክክል የሚያስተገብሩ እርምጃዎች (walking the talk) መውሰድ በአለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ዘንድ ትኩረት ሲሰጥበት ቆይቷል።ሐገራችን ኢትዮጵያ ከቀድሞ መንግስታት ጀምሮ እስከአሁን ድረስ አለም አቀፍ ስምምነቶችን የመፈረም ችግር ሳይታይባት ቆይቷል። ይሁን እንጅ በየጊዜው ከሚከሰቱ ችግሮች እንደምንረዳው እነዚህ የሚዎጡ ህጎችና የሚፈረሙ ስምምነቶች በተለይ በአስፈፃሚ አካላት ተነበው የማያውቁ በአልፎ ሂያጅ ብቻ ለትምህርትነት የሚያገለግሉ ሰነዶች ሁነው ቆይተዋል። የመዘዋወር ነፃነትን በተመለከተ ጉዳዩን ይበልጥ የሚያወሳሰብ እና ከላይ ያየናቸውን የወግ እና የባህል ሁኔታዎችን ጥያቄ ውስጥ ባስገባ መልኩ መከሰት የጀመረው የመብት ጥሰት በተለይም ሀገሪቱ የፌደራል ስርዓትን መከተል ጀምሬያለሁ ባለች ማግስት ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ሁሉም አካባቢዎች በቋንቋ እና በተለያዩ ማንነቶች መሰረት በክልል ከመከፋፈላቸው ጋር ተያይዞ በተለያየ አጋጣሚዎች የመዘዋወር ነፃነት ትልቅ እክል ሲገጥመው ቆይቷል። በተለይም የአማራ ብሔር ተወላጅ የሆኑ ሰዎች ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ከአብዛኛው የሃገሪቱ አካባቢ ቤት ንብረታቸው እየተቀማና እየተቃጠለ፤ አለፍ ሲልም ህፃናትና አዛውንት ሳይቀሩ ሲገደሉ እና ሲፈናቀሉ መቆየታቸውን በተለያዩ አጋጣሚዎች መረጃዎች ቀረበው ተሸፋፍነው አልፈዋል። ይህ የአማራ ተወላጆች ላይ ብቻ ሲፈፀም የነበረው የመፈናቀል እና የመዘዋወር ነፃነትን የመነጠቅ ድርጊት ባለፉት አራት እና አምስት አመታት አድማሱን አስፍቶ በኦሮሞ እና በትግራይ ተወላጆች ላይም ተፈፅሟል። ይሁን እንጅ በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ የሚፈፀመው የመፈናቀል እና የመዘዋወር ነፃነትን የመነጠቅ ወንጀል እንደሌሎች ሁሉ በጊዜ እና በቦታ የተገደበ እና ጊዜያዊ አለመሆኑን በዚህ አመት ተፈፀሙትን ሁነቶች ብቻ መመልከት ይበቃናል። በተለይ ከሰሞኑን ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በቦሎ ዲዴሳ ቀበሌ መስተዳደር ተፃፈ ተብሎ የተሰራጨውን ደብዳቤ እና ከክልሉ ተፈናቅለው ባህርዳር የሚገኙትን ህፃናት፤ አዛውንቶች እና ሴቶችን ስንመለከት ጉዳዩ በቶሎ የህግ እርማት ካልተሰጠው ለሃገሪቱ ህልውናን የሚፈታተን ሁኔታ ይፈጥራል። የፁሁፉ አላማ አይደለም እንጅ የተለያዩ በሀገሪቱ በግልፅ የተፈፀሙ የመንቀሳቀስ መብትን የሚጥሱ ሁኔታዎችን መዘርዘር ይቻል ነበር።


በመሆኑም ሀገሪቱን የሚያስተዳድራት አካል የሚከተሉትን ጥያቄዎች ተመልክቶ አስፈላጊውን መልስ በመስጠት መፍትሄ ማምጣት ይኖርበታል። የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግስት አንድ ግለሰብ ከሚኖርበት አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ ሄዶ እንዳይሰራ በሚከለክል መልኩ በክልል መስተዳድሮች የማፈናቀል ስራ ሲሰራ በተዘረጋው የህግ ማእቀፍ አማካኝነት አጥፊዎች ወደ ህግ እንዲይቀርቡ የማይደረግበት ምክናያት ምንድን ነው? በተለይም የክልል መስተዳድሮች በክልል የመስራት መብትን ለዚህ ክልል ተወላጅ ብቻ በመቁጠር የተለያየ ግፎችን እና ወንጀል ሲሰሩ ጉዳዩ የሚመለከተው አቃቤ ህግ ለምን ዝምታን መረጠ? እነዚህን ጉዳዮች እልባት ይሰጣሉ ተብለው የተቀመጡት የሕገ-መንግስቱና የወንጀል ህጉ ድንጋጌዎች በዳኞችችን ተነበው በአጥፊዎች ላይ የሚበየኑት መቸ ይሆን? በተለይም በአሁኑ ሰዓት እንኳን መፈናቀልን የሰፈር ፀብን በተለያየ ማስረጃ በሚያዝበት ወቅት የማስረጃ ጥያቄ እንደ ችግር ሊነሳ አይችልም። እንደዛ ከሆነ በሽህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን በሽብርተኘነት የሚከስ አቃቢ ህግ እንዴት በግልፅ ወንጀል የሰራን የክልል ባለስልጣን ለመጠየቅ ወኔ አጣ? የትላንት አምራች ዜጎች ዛሬ ተፈናቅለው ሸራ ዘርግተው በየጎዳናው የወደቁ ለማን አቤት ይበሉ? በተለያዩ የማህበራዊ ድረገፆች የሚታዩ ማስረጃዎችን እንደ በቂ ጥርጣሬ በመውሰድ ምርመራ ለመጀመር የሚስችለውን የፖሊስ ወኔ ማን ሰለበው? በአጠቃላይ ጥያቄው ህግ ይከበር ነው! ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ስራቸውን ይስሩ! ወንጀለኞች ወደ ህግ ይቅረቡ። አሁንም በዙ ነፍሶች መልስን ይሻሉ። ጉዳዩን በተዳፈነ ቁጥር እያበጠ ስለሚሄድ አላስፈላጊ ነገር ውስጥ እየተገባ ነው።  
 
በህዝቦቿ እኩልነት የምታምን ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!   

ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነን ሰንደቅ ጋዜጣ ሚያዝያ 24 ቀን 2010 የረቡዕ ዕትሙ በዜናና በዓምድ ዘገባው ያሰፈረው “የፌዴራል ዳኞች ምልመላ ቅሬታ አስከተለ” የሚለው የተሳሳተ ዘገባ ነው። ጋዜጣው ቅሬታ አቀረቡልኝ ያላቸውን አቤቱታ አቅራቢዎች ጠቅሶ እንደዘገበው የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ለሶስቱም የፌደራል ፍ/ቤቶች ዕጩ ዳኞችን ለመመልመል በቅርቡ ያካሄደው የማጣሪያ ምልመላ “ህግን ያልተከተለ አድልኦና መገለል ያለበት አሰራር ነው” በማለት ያትታል። ቅሬታ አቅራቢዎቹ ይህንን አስመልክተው ለኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ያቀረቡት ማመልከቻም ጋዜጣው በዚሁ እትሙ ማውጣቱ ይታወቃል። ወደ ጉዳዩ ከመግባታቸው በፊት አንድ ቅሬታ የቀረበበት ጉዳይ ቅሬታውን መርምሮ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ አቤቱታው የቀረበለት “ቅሬታ ሰሚ አካል” በኩል በቀረበለት ጉዳይ ላይ ውሳኔውን ከማሳወቁ በፊት (ጉዳዩ የቀረበለት አካል ቅሬታውን በይግባኝ የማየት በህግ የተሰጠው ግልፅ ስልጣን አለው የሚለውን ግምት ወስደን) ቅሬታ አቅራቢውም ሆነ አንድ የፕሬስ ውጤት በእንጥልጥል ላይ ያለን ጉዳይ ያውም ክስ የቀረበበት አካል ሳይጠየቅና ምላሹን ሳይሰጥ በሚዲያ ማሰራጨት ተገቢ ነው ወይ? በቅሬታ ሰሚው ላይ ከወዲሁ ተፅዕኖ ለማሳደር ወይም የምልመላ ሂደቱን ለማደናቀፍና ብዥታ ለመፍጠር ታስቦ የተወጠነ አይመስልም ወይ? የሚሉትን ጥያቄዎች እንደምንመለስበት ታሳቢ በማድረግ በቀጥታ ወደ ጉዳዩ እንግባ። ከሁሉም በፊት አንባቢ በተነሳው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተገቢ ግንዛቤ እንዲኖረው በማሰብ ስለ ፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ስልጣንና ተግባር እንዲሁም የእጩ ዳኞች የምልመላ ስርዓት ትንሽ ማለቱ ተገቢ ይሆናል።

በኢትዮጵያ ታሪክ ትኩረት ተነፍጓቸው ተዳክመውና ተልፈስፍሰው ከቆዩት መንግስታዊ ተቋማት መካከል ፍ/ቤቶች በመጀመሪያ ረድፍ ይሰለፋሉ ቢባል ማጋነን አይሆንም። ዘመናዊ ዳኝነት በኢትዮጵያ ከተዘረጋ ከ1934 ጀምሮ ለሁሉም ዜጎች ክፍት የሆነ፣ አሳታፊ፣ ግልጽነት የተላበሰና በብቃት ላይ የተመሰረተ የአሿሿም ስርዓትና በሚታወቅ ዝርዝር መስፈርት የተመሰረተ የዳኝነት የምልመላ ስርዓት እንዳልነበረ ለማንም የተሰወረ አይደለም። ለዳኛ የሚያበቁ ግልጽ መስፈርቶች ወጥተው መስፈርቱን እናሟላለን የሚሉ ዜጎች እንዲወዳደሩ የተሰጠ ዕድል አልነበረም። ዳኛ የመመልመልና የመሾም ወይም የማሾም ሙሉ ስልጣኑ የአስፈፃሚ ከመሆኑም በላይ አንድ ሰው በየደረጃው ላሉ ፍ/ቤቶች እንዴት በዳኝነት እንደሚሾም፤ ከተሾመ በኋላ ያለውን ነፃነትና የተጠያቂነት ስርዓት በዝርዝር የህግ ማዕቀፍ የተደገፈ ስርዓትም ሆነ የዳኝነት አካሉን ከምልመላው ጀምሮ የስራ አፈፃፀሙን የመከታተልና የመቆጣጠር ስልጣን ያለው ገለልተኛ አካል አልነበረም ማለት ይቻላል።

በኢትዮጵያ ታሪክ በዳኞች ምልመላና አሿሿም ላይ መሰረታዊ ለውጥ የመጣው የፌዴራል የዳኝነቱ አካሉን በገለልተኛ አካል ማስተዳደር ከተጀመረ በኋላ ነው። የተሻሻለው የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ አዋጅ ቁጥር 684/2002 ለዚህ ተጠቃሽ ነው። በዚህ አዋጅ የዳኝነት ነፃነትና ገለልተኝነትን ለመጠበቅ ሲባል የጉባኤው አባላት ስብጥር ከአስፈፃሚው ውጭ ተደርጓል። (ጉባኤው ከፌደራል የዳኝነት አካል አምስት፣ ከህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሶስት፣ ከአስፈፃሚ አንድ፣ ከጠበቆች ማህበር አንድ፣ ከዩኒቨርስቲ የህግ ተቋም አንድ፣ ከታዋቂ ሰው አንድ ያቀፈ ሆኖ የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት የጉባኤው ሰብሳቢ ናቸው። አዋጁ የፌዴራል ፍ/ቤቶች ዳኞችን የመመመልመል ሥልጣን ለጉባዔው ይሰጣል። ጉባዔው አዋጁን ለማስፈፀም ደንብ ወይም መመሪያ ሊያወጣ እንደሚችል በአዋጁ አንቀጽ 14 በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት በ2003 ዓ.ም የፌዴራል ፍ/ቤቶች ዕጩ ዳኞች ምልመላ ሥርዓት አፈፃፀም መመሪያ አውጥቶ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።

ይኸው አሳታፊ ግልፅነት የተላበሰና በኢትዮጵያ የዳኝነት ታሪክ እንደ አንድ እመርታዊ ለውጥ የሚታየው የምልመላ ሥርዓት የተወዳዳሪዎች የምዝገባ ሂደት፣ የማስታወቂያ አገላለፅና የማጣሪያ ሥርዓቶች፣ እንዲሁም ውጤት አገላለጽ ግልጽነት ባለው መንገድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ እኩል ዕድል በሚሰጥ አቅጣጫ እየተመራ ይገኛል። የምልመላ ስርዓቱ ግልጽነት ለተወዳዳሪዎች ብቻ ሳይሆን ሂደቱን መከታተል ለሚፈልግ ሶስተኛ ወገንም ሆነ ለሕዝብ ተደራሽ እንዲሆን በማሰብ በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች ጭምር በመጠቀም ሂደቱን አሳታፊና ግልፅነት የተላበሰ ለማድረግ የተጓዘው ርቀት ቀላል የሚባል አይደለም። ስለሆነም የጉባኤው የዳኞች የምልመላና የአሿሿም ስርዓቱ ለሌሎች ተቋማት እንደ አንድ የጥሩ ተሞክሮ ማዕከል ሆኖ ያገለግል እንደሆነ እንጂ የሚያስወቅሰው አይሆንም። እያንዳንዱ የምልመላ ሂደት ከተወዳዳሪዎች ጥሪ ማስታወቂያ ጀምሮ የምዝገባ፣ የቅድመ ማጣሪያ፣ የፅሁፍ ፈተና፣ የቃለ መጠይቅ ሂደቱም ሆነ በመጨረሻም በዚህ መንገድ የተመለመሉትን ዕጩ ዳኞች ለሹመት ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ከመቅረባቸው በፊት ሥነ-ምግባራቸው ለሕግና ለሕገ-መንግሥቱ ያላቸው ተገዢነትና እምነት በተመለከተ በሕዝብ አስተያየት እንዲሰጥባቸው ይደረጋል። ስለሆነም በጉባኤው የሚመራው የፌዴራል ዳኞች የምልመላ ሥርዓት ከማንም ተቋም በላይ በግልፅ መስፈርት ተመስርቶ የሚከወን አሳታፊና በግልጽነት የተሞላ ብቻ ሳይሆን በሂደቱ ቅሬታ ያለው አካል ቅሬታውን የሚያቀርብበትና ምላሽ የሚያገኝበት ስርዓት ዘርግቶ የሚካሄድ መሆኑ ሂደቱን ሙሉዕ ያደርገዋል።

በዚሁ መሰረት ባለፉት ሰባት ዓመታት ለሶስቱም የፌደራል ፍ/ቤቶች የተደረገው የዕጩ ዳኞች ምልመላ ስርዓት (በ2004፣2006 እና 2008) ለተወዳዳሪዎች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ዜጋ ግልፅ አሳታፊ፣ ተደራሽና ተአማኒ እና ብቃት ላይ በተመሰረተ መንገድ መፈፀም ተችሏል።

በ2010 እየተካሄደ ያለው የፌዴራል ፍ/ቤቶች የዕጩ ዳኞች የምልመላ ሂደትም ከላይ የተጠቀሱትን የህግ ማዕቀፎችና መስፈርቶች ተከትሎ እየተከናወነ ይገኛል። ጉባዔው ለሶስቱ ፍ/ቤቶች ዳኞችን መመልመል እንደሚፈልግ ተደራሽ በሆኑ የህትመትና የኤሌክትሮኒክ ሚዲያዎች፣ በፍ/ቤቱ ማህበራዊ ሚዲያ እንዲሁም በክልልና በፌዴራል ፍ/ቤቶች በመለጠፍ ለሁሉም ጥሪ አድርጓል። በዚህ መንገድ በወጣው የቅድመ ዕጩ ዳኝነት ምዝገባ ማስታወቂያ መሰረት ለሶስቱም ፍ/ቤቶች 3330 አመልካቾች ተመዝግበዋል። ይህ ቁጥር ጉባኤው ከዚህ በፊት በስድስት ዓመታት ካካሄዳቸው ሶስት የፌዴራል ዳኞች የምልመላ ሂደቶች በተመዝጋቢ ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ልብ ማለት ይገባል። ጉባኤው በአዋጁና በመመሪያው በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት ከአመልካቾቹ መካከል የተሻለ ብቃትና የስራ ልምድ ያላቸውን በጥንቃቄ በመለየትና በማጣራት ለፅሁፍ ፈተና ያለፉ አመልካቾች ስም ዝርዝር በፍ/ቤቱ ማህበራዊ ሚዲያ ጭምር ይፋ ሆኗል። ይህንን ተከትሎም ሚያዝያ 13 ቀን 2010 በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የፅሁፍ ፈተናው እንዲሰጥ አድርጓል።

ለፅሁፍ ፈተና ያለፉትን በፍ/ቤቱ ድረ-ገፅ ይፋ ከተደረገ በኋላ ለሶስቱም የፌዴራል ፍ/ቤቶች ለዕጩ ዳኝነት ካመለከቱት መካከል ጥቂቶቹ የተዘረጋውን የአቤቱታ አቀራረብ ስርዓት በመጠቀም ቅሬታቸውን ለጉባኤው ጽ/ቤት በፅሁፍ አቅርበዋል። የጉባዔው ጽ/ቤት አቤቱታቸውን መርምሮ ምላሽ ሰጥቷል። በጽ/ቤቱ ምላሽ ያልረኩ ወገኖች ቅሬታቸውን በይግባኝ መልክ ለጉባዔው ሰብሳቢ አቅርበው ጉዳያቸውና ማስረጃቸው በመመርመር ውሣኔ ተሰጥቷቸዋል።

ጉባኤው የዘረጋው ይህ አይነቱ ግልጽነት የተላበሰ ስርዓት በመታገዝ በጽሁፍና በአካል ጭምር ግልጽና አሳማኝ ምላሽ ከተሰጣቸው ከነዚህ አካላት መካከል ጥቂት ለፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የቀረቡት የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ዳኞች አመልካቾች (በ2006 ዳኛ የሆኑ ናቸው) በሰንደቅ ጋዜጣ ቀርበው ሕግን ባልተከተለና አድልኦ በተሞላበት ሁኔታ ከሂደቱ ተገልለናል በማለት ቅሬታ ያቀረቡት። እነዚህ አቤቱታ አለን የሚሉት ዳኞች ጉባዔው በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ያቀረቡትን የዳኝነት የሥራ ልምድ ከሌሎች ተወዳዳሪዎቻቸው ያነሰ በመሆኑ ማጣሪያውን ማለፍ እንዳልቻሉ ያቀረቡትን ማስረጃ በማገናዘብ ምላሽ የተሰጣቸው መሆናቸውን አንባቢው ሊገነዘብልን ይገባል።

በጋዜጣው ላይ ቅሬታቸውን ያቀረቡት እነዚህ ወገኖች ለአቤቱታቸው መነሻ ሆነን ያሉትን የህግና የአሰራር ጥሰት እያነሳን እውነታውን ወደ መመልከት እንግባ። እንደ አቤቱታ አቅራቢዎቹ አገላለፅ ጉባዔው ባደረገልን የማስታወቂያ ጥሪ መሰረት ከተመዘገብን በኋላ ወደ ቀጣዩ የፅሑፍ ፈተና የሚቀርቡትን ለመለየት ያካሄደው የማጣራት ሥራ በአዋጅ 684/2002 አንቀጽ 11 ስለ ፌደራል ዳኞች አሿሿም የተዘረጋው ስርዓት የጣሰና ሕግን ያልተከተለ ነው ይላል። ቀጠል በማድረግም “ዕውቅና ካለው ከፍተኛ ትምህርት ተቋም በሕግ ትምህርት ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪ በከፍተኛ ውጤት የተመረቀ/ች/ የሚጠይቅ ሆኖ እያለ ከምዝገባ በኋላ ጉባዔው ይህንን የሚፃረር አዲስ መስፈርት አውጥቷል” በማለት ጉባዔውን ወንጅለውታል። እዚህ ላይ አንባቢ እንዲገነዘብልን የምንፈልገው በጋዜጣው የተገለፀው መስፈርት ዝቅተኛ ተፈላጊ ችሎታ እንጂ ከዚህ በላይ ብቃትና ልምድ ያላቸውን እንዳይመረጡ የሚከለክል ህጋዊ መሰረት የለም ብቻ ሳይሆን የተሻለ የዳኝነት ልምድ ያላቸው ከማንም ተወዳዳሪ በላይ የተሻለ የመመረጥ እድል አላቸው።

ዳኛ ሆኖ ለመሾም ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንዳሉት በአዋጁ አንቀጽ 11/1/ከሀ እስከ ረ የተዘረዘሩ ዝቅተኛ ተፈላጊ መስፈርቶች ማሟላት እንዳለበት ይዘረዝራል። ይህ አንቀጽ አንድ ለቅድመ ዕጩነት የሚቀርብ አመልካች ወይም ተወዳዳሪ ዝቅተኛ የተፈላጊ ችሎታ መስፈርት እንጂ ወደ ማጣሪያ ለማለፍ ከተጠቀሰው በላይ የካበተ የስራ ልምድ ያላቸው ተወዳዳሪዎች እንዳይመረጡ የሚከለክል ሕግም ሆነ በሕግ የተደገፈ ምክንያት የለም። በአዋጁ መንፈስ መሰረት ማድረጉ የማይቻለው የተጠቀሱት አስገዳጅ ዝቅተኛ መስፈርቶችን የማያሟላ አመልካች ለጽሁፍ ፈተና ማቅረብ የማይቻል መሆኑ ነው። በማጣረያ ሂደት አስገዳጅ የሆነውን ዝቅተኛ ተፈላጊ መስፈርቱን በሚያሟሉ መካከል በማበላለጥ መምረጥ የተለመደ አሰራርና የህግ ድጋፍ ያለው ነው። የሚፈለገው የዕጩ ዳኞ ብዛት ከቀረቡት ተወዳዳሪዎች ብዛት እያመዛዘነ መመሪያውን ተግባራዊ የማድረግ ኃላፊነት ለጉባኤው የተሰጠ ስልጣን መሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል።

አዋጁን ተንተርሶ በ2003 የወጣው የፌዴራል ፍ/ቤቶች ዕጩ ዳኞች ምልመላ ስርዓት አፈፃፀም መመሪያ በአንቀጽ 15/2/ እንዲህ በማለት ይገልፀዋል። “እንደሚፈለገው የተወዳዳሪዎች ብዛት እየታየም የተሻለ የሥራ ልምድ ያላቸው ተወዳዳሪዎች ቅድሚያ እንዲያገኙ ሊደረግ ይቻላል” ይላል። ጉባዔው ያደረገውም ይህንኑ ነው። ዘንድሮ ከፍተኛ ብዛት ያለው አመልካች ስለቀረበ ወደ ፅሁፍ ፈተና የሚቀርቡትን ለማጣራት ለስራ ልምድ በተለይ ለዳኝነት የስራ ልምድ ትኩረት እንዲሰጥ ጉባኤው ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት የተፈፀመ ህጋዊ አሰራር ነው። ከዚህ ውጭ ጉባዔው ያሻሻለው አዲስ መመሪያ የለም። ሥራ ላይ ያለውን መመሪያ የአዋጁን መንፈስና ዓላማ በተከተለ መንገድ ለማስፈፀም የተሰጠውን ሥልጣን መሠረት ተደርጎ የተከናወነ ተግባር ነው። ጉባኤው ቅሬታ አቅራቢዎቹ “መስፈርቱን ባናሟላም ቅድሚያ ልትሰጡን ይገባል” በማለት ሕግን ያልተከተለና ሚዛናዊነት የጎደለው ጥያቄያቸውን ባለማስተናገዱ የጉባዔውን ሥርዓት የተከተለ አሰራር ማጥላላት ተገቢም አይደለም፤ በህግም ያስጠይቃል።

ጋዜጣው ቅሬታ አቅራቢዎቹን ጠቅሶ እንደዘገበው ጉባኤው ያደረገው የማጣራት ሂደት ለዳኝነት የሥራ ልምድ ልዩ ትኩረት መስጠቱ ተገቢ አይደለም የሚል አስገራሚ ትችትም አስደምጦናል። ዳኝነትን ለመሰለ በሰው ህይወት፣ ነፃነትና ንብረት ላይ አስገዳጅ ውሳኔ የሚወስን ሙያዊ መንግሥታዊና ህዝባዊ ሹመትን ያጣመረ ከባድ ኃላፊነት የተሸከመ ስራ ይቅርና ለማንኛውም የአገልግሎት ሰጪ ተቋም የወጣ የተፈላጊ የሥራ መደብ ማስታወቂያ ለሚፈለገው የሥራ ኃላፊነት የተሻለ ቅርበት ያለው ባለሙያ ቅድሚያ እንደሚሰጠው ቅሬታ አቅራቢዎቹ የህግ ባለሙያዎች ስለሆኑ ለቀባሪ ማርዳት ሊሆን ይችላል። በዳኝነት ለሚሰራ ዕጩ ዳኛን ለመመልመል በዳኝነት የተሻለ አገልግሎት ላለው ተወዳዳሪ ቅድሚያ መስጠት ተገቢ ብቻ ሳይሆን ቅቡልነት ያለው ሕጋዊ አሰራር ነው። ሌክቸረር ለመቅጠር የፈለገ አንድ የዩኒቨርስቲ ተቋም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የማስተማር ልምድ ያውን መምህር ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚቀጥር ሁሉ ዐቃቤ ሕግ ለመሾም የፈለገ የፍትህ ተቋም የዐቃቤ ሕግነት የሥራ ልምድ ያለውን ቅድሚያ ሰጥቶ ማጣሪያውን እንዲያልፍ እንደሚመርጠው ሁሉ ዳኛ ለመመልመል በዳኝነት በርከት ላሉ ዓመታት ለሰሩት ቅድሚያ መስጠቱ ሃጢያቱ የቱ ላይ ነው? ለነገሩ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ሌክቸረሮችን፣ ዓቃቢያን ህግን ሌሎች የህግ ባለሙያዎች ከምልመላው ተገልለዋል የሚል ስሞታ ያቀረቡት ለተነሱበት ሕገወጥ ዓላማ ከጎናቸው ለማሰለፍ ታስቦ እንጂ ስለሌሎቹ ተወዳዳሪዎች አስጨንቋቸው እንዳልሆነ ለማንም ግልፅ ይመስለናል። ጉባዔው ቀደም ሲል ያወጣው የፌዴራል ፍ/ቤቶች ዕጩ ዳኞች የምልመላ ሥርዓት አፈፃፀም መመሪያ በሕግ ዕውቀታቸው ብቻ ሳይሆን በዳኝነት ልምዳቸው የተሻለ አገልግሎት ያላቸውን ቅድሚያ እንዲሰጥ ከማንም በላይ እነሱ ጠንቅቀው ያውቁታል።

በነገራችን ላይ የዳኝነት አካሉ ባለድርሻ አካላት ከሆኑት ጠበቆች፣ ዓቃቢያነ ህግ፣ ነገረፈጆችና ሌሎች ተገልጋዮች ከሚያቀርቧቸው ቅሬታዎች መካከል ዋነኛው በየደረጃው ለሚገኙ ፍ/ቤቶች የምትሾሟቸው ዳኞች መካከል ቀላል የማይባል ቁጥር በቂ የዳኝነት የሥራ ልምድ ስለሌላቸው በችሎት አመራርና በፍርድ ጥራት ላይ ሰፊ ክፍተት እየተፈጠረ መሆኑን ሲገልፁ ይደመጣሉ። ዛሬ ዛሬ ዳኛ ለመሆን የሚያበቁ መስፈርቶች ጠበቅ ያሉና ብቃትን፣ የስራልምድን፣ ሥነ-ምግባርንና ህዝባዊ አመለካከትን መነሻ ያደረጉ መሆን አለባቸው የሚለው ሃሳብ ሚዛን እየደፋ የመጣውም ዳኞች ከተሸከሙት ወገብ የሚያጎብጥ ኃላፊነትና ከባድ ሸክም ጋር ለማጣጣም እንደሆነ ግልፅ እየሆነ መጥቷል። ስለዚህ በተለይ ከባድና ውስብስብ የፍትሀብሔርና የወንጀል ጉዳዮች ለሚመለከቱ የከፍተኛ ፍ/ቤት ዳኞች የካበተ የዳኝነት ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች መሾም ህጋዊም ተገቢም መሆኑን ለመረዳት ምርምር የሚያስፈልገው ጉዳይም አይደለም።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ ብለውታል እንደተባለው ጉባዔው በምን መልኩ ከሕግ አግባብ ውጭ እንደተጓዘና አድልዎ እንደፈፀመ ፍንጭ የሚሰጥ አንዳችም በሕግና በማስረጃ የተደገፈ የቀረበ ነገር የለም። ሂደቱም የምልመላው ግልፅነትና አሳታፊነት ያጎላው እንደሆነ እንጂ ለትችት የሚዳረገው ነገር አለ ብለን አናምንም።

አቤቱታ አቅራቢዎች አንባቢውን ለማደናገር እና ጉባኤው እያካሄደ ያለውን የዕጩ ዳኞች የምልመላ ሂደት ለማደናቀፍ ቆርጠው መነሳታቸውን የሚያመላክተው ሌላው ጉዳይ ቅሬታ አቅርበው የጉባዔው ጽ/ቤትና የጉባኤው ሰብሳቢ ለቅሬታቸው ምላሽ እንደሰጧቸው እንኳ ለመግለፅ ድፍረት አላገኙም። አንባቢንና የመንግሥት አካላትን ለማደናገር እነሱ ከሕግ ውጪ ተጠቃሚ ባለመሆናቸው ብቻ በህግ ማዕቀፍ እየተመራ ያለውን የምልመላ ሂደት ማጠልሸት ተገቢ አይሆንም። እኔ ካልተመለመልኩ ሁሉም ነገር ገደል ይግባ የሚል መፈክር ያነገቡ እነዚህ ወገኖች እነሱ የማይካተቱ ከሆነ እየተካሄደ ያለው የዳኞች የምልመላ ሂደቱ እንዲሰረዝ ድፍረት የታከለበት ጥያቄ ማቅረባቸውም ተሰምቷል። እንዴት ነው ነገሩ? በሕግና በሥርዓት በሚመራ አገር እንዲህ አይነት አጉራ ዘለል ጥያቄ ማቅረብ ያውም የህግ እውቀት ካለው ሰው ተገቢነት አለውን? ዓላማው ግልፅ ነው። ሂደቱን ሆን ብሎ ለመረበሽና ለማደናቀፍ የታሰበ ከመሆኑም በተጨማሪ በሂደት ላይ ያለን የምልመላ ስርዓት ተዓሚኒነት እንዲያጣ፣ ተወዳዳሪዎች ተስፋ እንዲቆርጡ በውጤቱ የምልመላ ስርዓቱ ዋጋ ለማሳጣት የሚደረግ ሴራ መሆኑ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል።

“እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” መፈክር ያነገቡ እነዚህ ቅሬታ አቅራቢዎች መስፈርቱን ባለማሟላታቸው ምክንያት ከማጣሪያው እንደቀሩ እያወቁና ጉባዔው በዘረጋው የቅሬታ አቀራረብ ሥርዓት መሰረት ቅሬታቸውን አቅርበው በቂ ምላሽ ተሰጥቷቸው እያለ ጉባዔው የጀመረውን ግልጽነት የተላበሰ አሳታፊና ብቃት ላይ የተመሰረተ የምልመላ ሂደት እንዲሰረዝ በድፍረት ጠይቀዋል። ቅሬታ ማቅረብ መብት ቢሆንም ማንኛውም የሚቀርብ ጥያቄ ሕግንና አሰራርን የተከተለና እውነት ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት ይቅርና የህግን ሀሁ የሰነቁ ሰዎች ሌላው ዜጋም ይዘነጋዋል ተብሎ አይጠበቅም። እውነታው ይህ ከሆነ ህግን ያልተከተለ አሰራር ያማረው ታዲያ ማን ነው? ጉባኤው ወይስ ቅሬታ አቅራቢዎቹ?

የሚገርመው ነገር ሰንደቅ ጋዜጣ የአንድ ወገን ያውም በሂደት ላይ ያለ ያላላቀ ጉዳይን ለህዝብ ያሰራጨው በአቤቱታ አቅራቢዎቹ ክስ የቀረበበት የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤን በጉዳዩ ላይ ሳያናግርና ሳይጠይቅ መሆኑ ነው። ያልተረጋገጠና ለአንድ ወገን የወገን ወሬ ይዞ መውጣት የፕሬስ ህግና የጋዜጠኝነት ስነምግባር እንደማይፈቅድ ይቅርና በፕሬስ ስራ የተሰማራ ባለሙያ ተራ ዜጋም ያውቀዋል። ዓላማው ህዝብ እውነታውን እንዲያውቅ ታስቦ ከሆነ ዘገባውን ይዞ የወጣው ሰንደቅ ጋዜጣ በጉዳዩ ላይ የጉባኤውን ጽ/ቤት ማነጋገርና ምላሹን ለማድመጥ ያልተፈለገው ለምን ይሆን? እየተካሄደ ያለን የዕጩ ዳኞች የምልመላ ሂደትን ለማደናቀፍ የተሰጠን የአንድ ወገን አስተያየት ይዞ መውጣት ከሁሉም በፊት የጋዜጠኝነት ሙያ የሚጠይቀውን የሚዛናዊነት መርህ እንደሚጥስ ለጋዜጣው አዘጋጅ ይጠፋዋል የሚል እምነት የለንም። እንዲህ አይነት የተቀነባበረ ወሬ የሚያስከትለውን ውጤት ተገንዝቦ ጉዳዩን ሚዛን ለመጠበቅ አዘጋጁ ጥረትና ትጋት ማድረግ እንደነበረበት ማስታወስም አያስፈልገውም። ሰንደቅ ጋዜጣ በዚህ ረገድ የፈፀመው የህግና የሙያ ጥሰት አንባቢዎቹን ይቅርታ እንዲጠይቅ በዚሁ አጋጣሚ ለመጠቆም እንወዳለን። ስለሆነም ግልጽነት በተላበሰ፣ አሳታፊና ብቃትን ማዕከል ባደረገ መልኩ እየተከናወነ ያለውን የፌዴራል ፍ/ቤቶች የዕጩ ዳኞች ምልመላ ለማደናቀፍ፣ ሂደቱን ከእውነታው በራቀና በተወናበደ መንገድ ተአማኒነት ለማሳጣትና ተወዳዳሪዎችን ተስፋ ለማስቆረጥ የተጀመረው ዘመቻ መቆም እንዳለበት ለማሳሰብ እንወዳለን።

 

                 ሰለሞን በላይ

            የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጽ/ቤት ኃላፊ

                  (ፊርማና ማህተም አለው)

 

በእንዳልካቸው ወርቁ (www.abyssinialaw.com)

 

መግቢያ


የሰው ልጆች በዚች ምድር ላይ ሲኖሩ የተለያዩ ሕጋዊ ውጤት ያላቸውን ድርጊቶች ያከናውናሉ። ለአብነት ያክንል ቤት ይከራያሉ ያከራያሉ፣ ጋብቻ ይፈፅማሉ፣ ንብረት ይሸጣሉ ይገዛሉ፣ ወዘተ። ሕጋዊ ውጤት ከሚያስከትሉ ተግባራት አንዱ ውል ነው። ውል ሰዎች በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሕይወታቸው ውስጥ ከሚያከናውኗተው የግንኙነት መገለጫዎች አንዱ ሲሆን የፍትሐብሔር ግዴታ አንዱ ዘርፍ ነው።


በእልት ተእለት የኑሮ እንቅስቃሴያቸው ውስጥ የተለያዩ ውሎችን ይፈፅማሉ። ወደ ሱቅ ሂደው ሸቀጥ ሲገዙ፣ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለመንቀሳቀስ ታክሲ ሲጠቀሙ፣ ለንግድም ሆነ ለመኖሪያ ቤት ሲከራዩ፣ ወዘተ። እኒህ የውል ጌዴታ ውስጥ ሚገቡት የማህበረሰቡ አካል የሆኑ ሰዎች ናቸው። በሌላ አባባል ውል የሚኖረው የውል ግዴታ ውስጥ የሚገቡ (የሚዋወሉ) ሰዎች ሲኖሩ ነው። ሰዎች ስንል በፍትሐብሔር ሕጉ መሠረት የተፈጥሮ ሰዎች ወይም ሕጋዊ ሰውነት የተሰጣቸው ድርጅቶች ናቸው።


ከላይ እንደተገለፀው ሰዎች በማህበራዊ ሕይወታቸው ውስጥ ሁልጊዜም ቢሆን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት የሚያስከትል ድርጊቶችን ይፈፅማሉ። ዕቃ ለመግዛት፣ አገልግሎት ለማግኘት፣ ወይም ሥራ ተቀጥሮ ለመስራት እና የመሳሰሉ ተግባራትን ሰዎች በማህበራዊ መስተጋብራቸው ይፈፅማሉ። እንዚህን ተግባራት ለመፈጸም ደግሞ ከሌሎች ሰዎች ጋር ውል ወይም ስምምነት ይፈፀማሉ።


የሰውል ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቱን ለማሟላት የተለያዩ ስራውችን በእለት ከእለት ይከውናል። የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎት ተብለው ከሚታወቁት ወነኞቹ ውስጥ አንዱ የመኖሪያ ቤት ይገኝበታል። ይህን የመሮሪያ ቤት የማግኘት የዜጎች መብት መሆኑን ኢትዮጵያ ተቀብላ ባፀደቀችው የአለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ውስጥ ተቀምጧል።


በዚህ አጭር ጽሑፍ ውስጥ በሀገራችን የፍትሐብሔር ሕግ መሠረት በጠቅላላው የውልን ምንነት፣ እንዴት እንደሚፈፀም በማየት የቤት ኪራይ ውል ያለውን የሕግ ማዕቀፍ እንመለከታለን።

 

የውል ምንነት


ውል ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን ስንመለከት የዘርፉ ሙሁራን እና የፍትሐብሔር ሕጋችን የተቀራረበ ትርጉም ሰጠተውት እናገኛለኝ። በእውቁ የሕግ መዝገበ ቃላት ብላክስ ሎው መዝገበ ቃላት ላይ “ውል ማለት በሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች በመካከላቸው አንድን ድርጊት ለማድረግ ወይንም ላለማድርግ በመስማማት ግዴታ የሚፈጥሩበት መንገድ ነው” በማለት ትርጉም ይሰጠዋል። ፕሮፌስር ጥላሁን ተሾመ የኢትዮጵያ የውል ሕግ መሠረተ ሀሳቦች በሚለው መፅሃፋቸው ውስጥ “ውል አንድን ግዴታ ወይም ከዚሁ ግዴታ የተያያዙ ሌሎች በርከት ያሉ ግዴታዎችን የሚቋቁም ተግባርን የሚያመለከትት አነጋገር ነው በማለት ይተረጉሙታል። በዚህ ግዴታ ባለገንዘብ የሆነው ወገን አንድ ነገር እንዲፈጸምለት የመጠየቅ መብት የሚኖረው ሲሆን ባለዕዳው ደግሞ አንድን ነገር የመፈጸም ግዴታ ይጠበቅበታል” በማለት አብራርተው ገልፀውታል። እንዲሁም በፍትሐብሔር ሕጋችን መጽሐፍ አምስት ስለግዴታዎች በሚደነግገው ክፍል አንቀፅ 1675 ላይ “ውል ማለት ንብረታቸውን የሚመለከቱ ግዴታዎችን ለማቋቋም ወይም ለመለወጥ ወይም ለማስቀረት ባላቸው ተወዳዳሪ ግንኙነት በሁለት ወይም በብዙ ሰዎች መሀል የሚደረግ ስምምነት ነው” በማለት ትርጉም ሰጥቶታል።


በሕጋችንም ሆነ በዘርፉ ምሁራን ውልን በተመለከተ የሰጡት ትርጎሜ በመሰረታዊነት ተመሳሳይ ነው። ከትርጉሙ እንደምንረዳው ውል፡-


1ኛ. በሁለት እና ከዚያ በላይ በሆኑ ሰዎች መካከል የሚፈፀም ተግባር መሆኑን። ይህም ማለት አንድን ውል ለመዋዋል ቢያንስ ሁለት ሰዎች የሚያስፈልጉ መሆኑን። (ሰዎች ስንል በፍትሐብሔር ሕግ መሠረት የተፈፅሮ ሰው እና የሕግ ሰውነት የተሰጠውን ማንኛውንም ድርጅት የሚጨምር ነው።)


2ኛ. የውል ግዴታ ይዘት ከተዋዋዮቹ ንብረት ወይም ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ጋር የተገናኘ መሆኑን። ይህም ማለት ሰዎች የውል ጌዴታ ውስጥ የሚገቡት በንበረታቸው ወይም በኢኮኖሚያዊ ጥቅም በሚያስገኙ ነገሮች ላይ ነው።


3ኛ. የውል ግዴታ ከተዋዋዮች የሀሳብ መግባባት የሚመነጭ ስምምነት መሆኑን። ይህም ማለት ተዋዋይ ወገኖች በንብረታቸው ወይም ኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸው ላይ አንዱ በአንዱ ላይ ግዴታ ለመፍጠር አስቀድመው በሀሳብ በመግባባት የሚያድርጉት ነው።


4ኛ. ውል የሚመሠረተው ግዴታዎችን ለማቋቋም ወይም ለመለወጥ ወይም ለማስቀረት መሆኑን። ይህም ማለት በንብረታቸውን ወይም ኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸውን በተመለከተ ግዴታ ያቋቁሙበታል ወይም የተቋቋመ ግዴታን ያሻሽሉበታል ወይም የተቋቋመን ግዴታ ቀሪ ያደርጉበታል።

 

የውል አመሠራረት


ከላይ እንደተገለፀው ውል ስምምነት ነው። ነገር ግን ውል ስምምነት ቢሆንም ከሌሎች ስምምነቶች የሚለየው በአፈፀሙ ከበስተጀርባው የሕግ ድጋፍ ያለው ስምምነት መሆኑ ላይ ነው። ይህም ማለት ተዋዋይ ወገኖች የተስማሙበትን ነገር እንደ ስምምነታቸው ባይፈፅሙ ላልፈፀሙትን ነገር በሕግ ተገደው እንዲፈፅሙ ይደረጋሉ። ይህም የሚያሳየን ውል በተስማሚዎቹ አካላት መካከል እንደ ሕግ ሆኖ የሚያገለግል መሆኑን ነው።


ውል በተወያይ ወገኖች መካከል ሕጋዊ ውጤት እንዲኖረው አስቀድሞ የውል አመሰራረቱ ሕጋዊ መስፈርቱን ማሟላት አለበት። በፍትሐብሔር ሕጋችን ስለ ውል አመሰርረት በሚደነግገው ክፍል አንቀፅ 1678 ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው የሚፀና ውል ነው ለማለት መሟላት ያለባቸውን ሁኔታዎች አስቀምጧል። እነሱም፡ -


1ኛ. ውል የሚፈፀመው ለመዋዋል ችሎታ ባላቸው ሰዎች መካከል መሆኑን። ይህም ማለት በሕግ ፊት የሚፀና ውል ለማድረግ ተዋዋዮች በሕግ ችሎታ ያላቸው መሆን አለባቸው። በፍትሐብሔር ሕጋችን ላይ ስለ ችሎታ በሚደነግገው ክፍል አንቀፅ 192 ላይ በመርህ ደረጃ ማንኛውም ሰው በሕግ ችሎታ እንደሌለው ካልተገለፀ በቀር ማንኛውንም ሕጋዊ ድረጊት ለማድረግ ችሎታ እንዳለው እንደሚቆጠር ተደንግጓል። በዚሁ ሕግ አንቀፅ 193 ላይ እንደተደነገገው እድሜው ለአቅመ አዳም/ሄዋን ያልደረሰ/ሰች ወይም አይምሮው ህመም ያለበት ሰው ወይም በፍርድ ቤት የተከለከለ ሰው ችሎታ እንደሌለው ይቆጠራል። ከላይ እንደተገለፀው ውል ሕጋዊ ተግባር ነው ስለሆነም እድሜው ለአቅመ አዳም/ሄዋን ያልደረሰ/ሰች ወይም አይምሮው ህመም ያለበት ወይም በፍርድ ቤት የተከለከለ ሰው ውል መዋዋል አይችልም።


2ኛ. ውል የሚፈፀመው በተወያያቹ ነፃ ፍቃድ ብቻ መሆኑ። ይህም ማለት ተወያይ ወገኖች ውል ውስጥ የሚገቡት ያለማንም ጫና አድራጊነት በራሳቸው ገዛ ፍቃድ መሆን አለበት ማለት ነው። አንድ የውል ግዴታ የተቋቋመ መሆኑ የሚረጋገጠው የተዋዋዮቹ ፈቃድ በሕግ አግባብ መገለፁ ሲታወቅ ነው። ተዋዋዮቹ በመሀከላቸው በሕግ ፊት የሚፀና ግዴታ ለማቋቋምና ይህም ግዴታ በሚያስከትለው ውጤት ለመገዛት ስምምነት ያላቸው መሆኑ ይፋ ሲያደርጉ ፈቃዳቸውን ገለፁ እንላለን። በፍትሐብሔር ሕጉ አንቀፅ 1679 ላይ ይህን አባባላችን በሚያጠናክር መልኩ “ውል ተዋዋዮች በገቡባቸው ግዴታዎችና እነዚህም አስገዳጅ እንዲሆኑ የተስማ መብትን በሚገልፀው የፈቃድ መስጠት ላይ የተመሠረተ ነው” በማለት ተደንግጓል።


3ኛ. ተወያይ ወገኖች የሚዋዋሉበት (ውል ውስጥ የሚገቡበት) ጉዳይ በእርግጠኝነት የሚቻል እና ሕጋዊና ሞራላዊ ጉዳይ ላይ መሆኑ። የውሉ ፍሬ ነገር በሰው ልጅ አቅም መፈጸም የሚችል እና ሕጋዊና ሞራላዊ የሆነ መሆን አለበት። በሰው ልጅ አቅም መፈፀም የሚቻል ተግባር ማለት የሰው ልጅ በተፈጥሮው ማከናወን የሚችለው ማለት ነው። ለአብነት የውሉ ፍሬ ነገር እንደ እርግብ መብረር ቢሆን በሰው ልጅ ተፈጥሮ የማይቻል ተግባር ነው። ሌላው የውሉ ፍሬ ነገር በሕግ ያልተከለከለ ወይም ህገ-ወጥ ያልሆነ እና በህብረተሰቡ ባህልና ወግ ተቀባይነት ያለው ነገር ላይ (በሌላ አባባል ከህብረተሰቡ ሞራል ጋር የማይቃረን) መሆን አለበት። ለአብነት ፍሬ ነገሩ ሰው ለመግደል ቢሆን በሕግ የተከለከለ እንዲሁም ክህረተሰቡ ሞራል ጋር የሚቃረን ነው።


4ኛ. የውል አቀራረጹ ወይም አፃፃፉ በሕግ (ፎርም) ተለይተው የተቀመጡ ወይም ተዋዋይ ወገኖች ተለይቶ እንዲቀመጡ ከተስማሙበት የውል ጉዳይ በቀር የተለየ የውል ፎርም የማያስፈልግ መሆኑ። በፍትሐብሔር ሕጋችን አንቀፅ 1678(3) ላይ እንደተደነገገው በግልፅ በሕግ ይህን የውል ፎርም ተከተሉ ተብሎ ካልተደነገገ በቀር ተዋዋይ ወገኖች ውላቸውን በፈለጉት አይነት ማድረግ ይችላሉ። ከዚህም በተጨማሪ በዚሁ ሕግ አንቀፅ 1719(1) ላይ ተዋዋይ ወገኖች የመዋዋል ነፃነት እንዳላቸው ሁሉ የሚዋዋሉበትን ውል አቀራረፅ የመወሰን ነፃነትም እንዳለቸው በግልፅ ተደንግጎ ይገኛል። በመሆኑም በተለየ ሁኔታ በሕግ ውሉ በዚህ መልክ ይቀመጥ ካልተባለ በስተቀር ተዋዋዮቹ ወገኖች ውላቸውን በፈለጉት ፎርም ማድረግ ይችላሉ።
የውል አመሰራረትን በተመለከተ ከላይ የተመከትናቸው ማለትም ችሎታ፣ ፍቃድ እና የሁሉ ፍሬ ነገር ሕጋዊና ሞራላዊ መሆን ለሁሉም አይነት ውሎች በጋራ ተሞልቶ መገኘት የሚገባቸው መሰረታዊ ነገሮች ሲሆኑ የውል ፎርም ግን በሕግ በግልፅ ተለይቶ ተዋዋይ ወገኖች በዚህ ፎርም ብቻ ሊከተሉ ይገባል ላላቸው የውል አይነቶች ብቻ ተፈፃሚ የሚሆን ነው። ስለሆነም አንድ ውል ሲመሠረት ተዋዋይ ወገኖች ወይም አንዱ ተዋዋይ ችሎታ የሌለው እንደሆነ፣ ተዋዋይ ወገኖች ወይም አንዱ ተዋዋይ ፍቃዱን በነፃነት ያልሰጠ ከሆነ ወይም የውሉ ፍሬ ነገር የማይቻል፣ ህገወጥ ወይም ኢሞራላዊ ከሆነ እንዲሁም ውሉ በግልፅ በሕግ በተለየ ፎርም እንዲደረግ የሚያስገድድ ሆኖ ሳለ ተዋዋዮቹ ይህን ፎርም ካልተከተሉ ውሉ ሙሉ በሙሉ ፈራሽ ይሆናል። ይህም ማለት ውሉ እንዳለተፈፀመ ይቆጠራል።


ከዚህ በላይ የተመለከትነው የውል ትርጉም እና የውል አመሰራረት ለሁሉም አይነት ውሎች የሚያገለግል ደንብ ነው። ይህም የውል ጠቅላላ ደንብ በመባል ይጠራል። ይህም የሆነበት ምክንያት ይህ ደንብ ለጠቅላላ ውልም ይሁን ለልዩ ውሎች የሚያገለግል ስለሆነ ነው።


በፍትሐብሔር ሕጋችን ከጠቅላላ ውል (General contract) በተጨማሪ ልዩ የውል (special contract) ደንቦች ተደንግገው ይገኛሉ። ልዩ የውል (special contract) አይነቶች ተብለው በሕጋችን ከተጠቀሱት ውስጥ ለአብንት የሽጭ ውል፣ የስጦታ ውል፣ የማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የሚደረግ ውል፣ ወዘተ የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ።


ልዩ የውል አይነት ከሆኑት ውስጥ በማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ላይ ከሚደረጉ የውል አይነቶች ውስጥ አንዱ የቤት ኪራይ ውል ነው። የቤት ኪራይ ውልን በተመለከተ በፍትሐብሔር ሕጋችን የተመለከተውን ጉዳይ በዝርዝር ከዚህ በታች እንመለከተዋለን።

 

የቤት ኪራይ ውል


የቤት ኪራይ ውልን በተመለከተ በፍትሐብሔር ሕጋችን አምስተኛ መጽሐፍ አንቀፅ አስራ ሰምንት የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን በሚመለከት በሚለው ክፍል ውስጥ የቤት ኪራይን የሚመለከቱ ልዩ ደንቦች በሚል ርዕስ ስር ከአንቀፅ 2945 እስከ 2974 ድረስ የተደነገጉ ድንጋጌዎች ተግባራዊ ይሆኑበታል። በመቀጠልም ዋና ዋና የሆኑ ነገሮችን በዝርዝረር እንመለከታለን።

የቤት ኪራይ ውል ትርጉም


በሕጋችን ላይ የቤት ኪራይ ውል ማለት ይህ ነው በማለት ትርጉም ባይሰጠውም ከሕጉ ድንጋጌዎች በመነሳት ምንነቱን ወይም ትርጉሙን መረዳት እንችላለን። በመሆኑም የቤት ኪራይ ውል “አንድ የቤት ወይም ህንፃ ባለቤት ወይም ባለይዞታ የሆነ ሰው (አከራይ ብለን የምንጠራው) ቤቱን ወይም ህንፃውን ሙሉ በሙሉ ወይም የተወሰኑ ክፍሎችን ወይም አንዱን ክፍል ለሌላ ሰው (ተከራይ ብለን ለምንጠራው) ከነዕቃው ወይም ባዶውን የተወሰነ የኪራይ ዋጋ በመቀበል ለተወሰነ ጊዜ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ አስተላልፎ ማስጠት /ማከራየት/” ማለት ነው በማለት በግርድፉ ትርጉም ሊሰጠው ይችላል። ነገር ግን የሆቴል ክፍልን ለተወሰነ ጊዜ ተከራይቶ መኖርን አያካትትም።

 

የተፈፃሚነት ወሰን


ቤት በተፈጥሮው የማይንቀሳቀስ (ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ቤቶች ቢኖሩም) ንብረት ነው። በፍትሐብሔር ሕጋችን ውስጥም ቤት የማይቀሳቀሱ ንብረቶች ውስጥ አንዱ እንደሆነ ተደንግጓል። በፍትሐብሔር ሕጋችን የቤት ኪራይን በተመለከተ ልዩ ደንቦች ተብለው ከአንቀፅ 2945 እስከ 2974 የተደነገጉት ተፈፃሚ የሚሆኑት የአከራይና ተከራይ ውል ቤትን ከነዕቃው ወይም ያለ ዕቃ ወይም አንድ ባለክፍሎች ቤት ወይም አንድ ክፍል ቤት ወይም ማናቸውንም አንድ ሌላ ሕንፃ ወይም የሕንጻ አንዱን ክፍል ላይ በሚደረግ የቤት ኪራይ ውል ላይ ይሆናል። ይህም ማለት አከራይ የሆነው ሰው እና ተከራይ የሆነው ሰው አንድን ቤት በጠቅላላው ወይም ከቤቱ አንዱን ከፍል ወይም የቤቱን የተወሰኑ ክፍሎች ባዶውንም ሆነ ከነእቃው ወይም አንድን ሕንፃ ሙሉውን ወይም የሕንፃውን ክፍል ላይ የኪራይ ውል ቢፈፅሙ ይህን ውላቸውን የሚገዛው ወይም የሚመራበት ሕግ ከአንቀፅ 2945 - 2974 ያለው ይሆናል። /የፍ/ሕግ አንቀፅ 2945(1)/።


ነገር ግን በፍታትሐብሔር ሕጋችን ስለሆቴል ስራ ውል ከአንቀፅ 2653- 2671 የተደነገገው እንደ ቤት ኪራይ ውል ስለማይቆጠር በቤት ኪራይ ውል ደንብ መሠረት አይገዛም። በሌላ አነጋገር የቤት ኪራይ ውል ደንብ ተግባራዊ የሚሆነው ለቤት ኪራይ ውል ላይ ብቻ ነው። በመሆኑም አንድ ሰው ሆቴል ሄዶ ለአነድ ቀን ወይም ለተወሰነ ቀን የሆቴሉን ክፍል ተከራይቶ ቢቆይበት እንደ ቤት ኪራይ ውል ተቆጥሮ በዚህ ደንብ መሠረት አይመራም። ይህን አባባላችንን በፍትሐብሔር ሕጋችን አንቀፅ 2945(2) ላይ “በዚህ ሕግ አገልግሎት መስጠትን ስለሚመለከቱ ውሎች የተነገሩት ስለ ሆቴል ውል የተደነገጉት ደንቦች የተጠበቁ ናቸው” በሚል ተደነገገው ያጠናክርልናል።

 

ስለሞዴል የቤት ኪራይ ውሎች


የቤት ኪራይ ውልን በተመለከተ ተዋዋይ ወገኖች በፈለጉት አይነት (ለምሳሌ በጽሑፍ ወይም በቃል) ማደድረግ ይችላሉ። ይህን በተመለከተ በፍትሐብሔር ሕጋችን በጠቅላላ የውልን በሚመራው ክፍል አንቀፅ የውል 1678(3) ላይ አቀራረጹ ወይም አፃፃፉ በሕግ (ፎርም) ተለይተው የተቀመጡ ወይም ተዋዋይ ወገኖች ተለይቶ እንዲቀመጡ ከተስማሙበት የውል ጉዳይ በቀር የተለየ የውል ፎርም የማያስፈልግ መሆኑ ተደንግጓል። በመሆኑም በልዩ ክፍል ውስጥ የቤት ኪራይ ውል በዚህ መልክ ይቀመጥ ተብሎ ያልተደነገገ በመሆኑ ተዋዋይ ወገኖች በፈለጉት አይነት ማድረግ ይችላሉ።


ተዋዋይ ወገኖቹ የቤት ኪራይ ውላቸውን በጽሑፍ ለማድረግ ከተስማሙ ግን የኪራይ ቤት ውል ሞዴልን በተመለከተ በአንድ ከተማ ውስጥ ባሉ ቤቶች ላይ የሚደረግ የኪራይ ቤት ውል ሞዴልን የከተማው ማዘጋጃ ቤት ሊያዘጋጅ ይችላል። ተዋዋይ ወገኖችም እነዚህን የቤት ኪራይ ውል ሞዴሎችን ተጠቅመው የቤት ኪራይ ውል ሊፈፅሙ ይችላሉ። ነገር ግን በፍትሐብሔር ሕጋችን አንቀፅ 2946 ላይ እንደተደነገገው ተዋዋይ ወገኖች የቤት ኪራይ ውልን በተመለከተ በከተማው ማዘጋጃ ቤት ባዘጋጀው የውል ሞዴል ብቻ ውል እንዲፈፅሙ አይገደዱም። በመሆኑ ተዋዋይ ወገኖች (አከራይና ተከራይ) የውልን ሞዴል ከፈለጉ በራሳቸው ማዘጋጀት ይችላሉ።

 

የኪራዩ ክፍያ መጠን እና ጊዜ


ተዋዋይ ወገኖች (አከራይ እና ተከራይ) በቤት ኪራይ ውላቸው በስምምነት ከሚወስኖቸው ነገሮች ውስጥ ዋነኞቹ ስለ ውሉ የሚቆይበትን ጊዜ፣ ቤቱ ኪራይ ዋጋ እና ኪራዩ የሚከፈልበትን ጊዜ ነው። ተዋዋዮቹ ለፈለጉት ጊዜ ያህል በውላቸው እንዲቆይ፣ በፈለጉት ዋጋ እና በተስማሙበት ጊዜ ክፍያው እንዲፈፀም በውላቸው ውስጥ ሊስማሙ ይችላሉ። ነገር ግን ተዋዋይ ወገኖች (አከራይ እና ተከራይ) በውላቸው ውስጥ እነዚህን ነገሮች ካልገለፁ በሕጉ የተቀመጡ ተፈፃሚ ይሆናል። ይህንንም በተመለከተ በፍትሐብሔር ሕጋችን አንቀጽ 2950(2) ላይ ተዋዋይ ወገኖች በውላቸው ውስጥ የኪራዩን መጠን ካላስቀመጡ ወይም በሚያጠራጠር ጊዜ የማዘጋጃ ቤት ባለስልጣናት በወሰኑት ታሪፍ ወሠረት ወይም የተወሰነ ታሪፍ የሌለ እንደሆነ የቦታዎቹን ልማድ በመከተል የሚወሰን መሆኑ ተደንግጓል። የውሉን ቆይቶ ጊዜ በተመለከተ ለተወሰነ ጊዜ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ ሊሆን እንደሚችል በዚሁ ሕግ ተመላክቶል።


የኪራዩ ዋጋ የሚከፈልበትን ጊዜ በተመለከተ በፍትሐብሔር ሕጋችን አንቀጽ 2951 ላይ ተዋዋይ ወገኖቹ በውላቸው ውስጥ ያልተስማሙበት ከሆነ፡-


የቤት ኪራይ ውሉ ለአንድ ወይም ለብዙ አመታት ተደርጎ እንደሆነ ኪራዩ በሶስት ወር መጨረሻ የሚከፈል ይሆናል። ይህ ማለት ተዋዋዮቹ በቤት ኪራይ ውል ውስጥ ለአንድ ወይም ከአንድ አመት በላይ ሆኖ ለታወቀ ጊዜ ያክል ለምሳሌ ለአምስት፣ ለአስር አመት፣ ወዘተ ተብሎ የተስማሙ ከሆኖ የክፍያ ጊዜውን ካልተስማሙ በየሶስት ወር መጨረሻ ሚከፈል መሆኑ ተደንግጓል። (አንቀጽ 2951/1/)


የቤት ኪራይ ውሉ በጣም አጭር ለሆነ ጊዜ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ ተደርጎ እንደሆነ በየወሩ መጨረሻ ላይ የሚከፈል ይሆናል። (አንቀጽ 2951/2/)
ነገር ግን በማንኛውም ሁኔታ ቢሆን ክፍያው የቤት ኪራይ ውሉ ሲያልቅ (ሲያቆም) መከፈል አለበት። ይህም ማለት ተዋዋዮች በቤት ኪራይ ውላቸው ውስጥ ኪራይ የሚከፈልበት ጊዜ ባይቀመጥም እንዲሁም ከላይ የተቀመጡት ሁኔታም ክፍያው ባይፈፀም እንኳን የቤት ኪራይ ውሉ ሲያልቅ (ሲያቆም) የሚከፈል ይሆናል።

 

የተከራዩትን ቤት ስለማደስ


ተዋዋይ ወገኖች የቤቱ እድሳት በተመለከተ በውላቸው ውስጥ በስምምነት ሊወስኑት ከሚችሏቸው ጉዳዮች ውስጥ አንድ ነው። በመሆኑም ተዋዋይ ወገኖች በቤት ኪራይ ውሉ ውስጥ የቤቱን እድሳት በተመለከተ (ማን ያድሳል፣ ማን ምኑን ያድሰል፣ የእድሳቱን ወጪ ማን ይችላል፣ ወዘተ) ከተስማሙ በውሉ መሠረት የቤቱ እድሳት ይፈፀማል ማለት ነው። ነገር ግን ተዋዋዩቹ ስለ ቤቱ እድሳት በውላቸው ላይ የገለፁት ነገር የሌለ ከሆነ የፍትሐብሔር ሕጉ የቤት ኪራይን የሚመራው ልዩ ድንብ ክፍል የሆነው ከአንቀፅ 2953- 2956 ያለው ተግባራዊ ይሆናል። በዚህ ሕግ መሠረት ማድስ ማለት የቤቱን መዝጊያዎችን ወይም መስኮቶችን፣ የቤቱን ወለሎችን ወይም ንጣፎችን፣ የውሃ መስመሮችንና የፍሳሽ ማስወገጃዎችን ማደስ እና ቤቱን የማፅዳት እና በደንብ መያዝ መሆኑን በአንቀፅ 2954(2)ና(3) ላይ ተደንግጎ እናገኘዋለን። ይህ ሕጉ የሰጠው ትርጉም ቢኖርም ተዋዋዮቹ ትርጉሙን በውላቸው ከዚህ በላይ ማስፋት ይችላሉ።


በቤት ኪራይ ውሉ ውስጥ ተከራዩ ማደስ ይገባዋል የተባሉት (የሚባሉት) በኪራይ ውል ተከራዩ ይፈፀማቸዋል ተብለው የተወሰኑት ናቸው። ተከራዩ ሊያድሳቸው የሚገባውን የተከራያቸውን ቤቶች በራሱ ኪሳራ ለማደስ ይገደዳል በማለት በፍትሐብሔር ሕጉ አንቀፅ 2953 ላይ ተደንግጓል። ይህም ማለት ተከራዩ በኪራይ ውሉ ውስጥ ለማድስ በተስማማው መሠረት በራሱ ወጭ ለማድስ ይገደዳል ማለት ነው። ነገር ግን ቤቶቹ በማርጀት ወይመ ካቅም በላይ በሆነ ነገር ብቻ የተበላሹ ሲሆኑ ተከራዩ ማናቸውንም ቤቶችን የማደስ ስራዎች መፈፀም አይጠበቅበትም። ነገር ግን በቤት ኪራይ ውላቸው ውስጥ በማርጀት ወይም ካቅም በላይ በሆነ ነገር የተበላሹትንም ጭምር አድሳለው በማለት ተከራዩ የተስማማ ከሆነ ብቻ እንዲያድስ የሚገደደው።


በተዋዋዮች መካከል የፀና የቤት ኪራይ ውል ባለበት ጊዜ ውስጥ አከራዩ የቤቱን የማይንቀሳቀስ ንብረት በሚያድስበት ጊዜ የማደስ ስራው ከአስራ አምስት ቀን በላይ የፈጀ ከሆነ ተከራዩ ለዚህ ለተወሰነ ጊዜ በቤቱ ሳይገለገልብት የቆየ ከሆነ ለዚህ ሳይገለገልብት ለቆየው ጊዜ ከቤት ኪራዩ ይቀነስለታል።

 

የተከራዩትን ቤት ስለማከራየት


በመርህ ደረጃ ተከራይ የተከራየውን ቤት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ለማከራየት ይችላል። ነገር ግን አንድ ሰው የተከራየውን ቤት ሊያከራይ የሚችለው አከራዩ ለዚህ የኪራይ ኪራይ ተቃውሞ የሌለው ከሆነ ብቻ ነው። የቤቱ አከራይ ውል ውስጥ “ተከራዩ የተከራየውን ቤት እንዲያከራይ ወይም ተከራዩ ከማከራየቱ በፊት የአከራዩን ፈቃድ መቀበል ያስፈልጋል” በማለት መስማማት ይችላሉ። በዚህ ሁኔታ ተዋዋይ ወገኖች ተስማምተው ሳለ ተከራዩ የተከራዩን ቤት ሲያከራይ አከራዩ ያለ ምክንያት ፈቃዱን የከለከል እንደሆነ ተከራዩ የኪራይ ውሉ እንዲፈርስ ለመጠየቅ ይችላል በማለት በአንቀፅ 2959(2) ላይ ተደንግጓል።


በአንቀፅ 2960 ላይ እንደ ተደነገገው አከራዩ ተከራዩ የተከራየውን ቤት እንዲያከራይ ፍቃዱን ቢሰጥም እንኳን ተከራዩ ያለበትን ጌታዎች አያስቀርም። ይህም ማለት በኪራይ ውሉ መሠረት ለአከራዩ ለገባቸወ ግዴታዎች ተገዳጅ ይሆናል።


ከተከራይ የተከራየ ሰው በኪራይ የተሰጡትን ቤት በተመለከተ የዋናው የቤት ኪራይ ውል ውስጥ የተቀመጡትን ግዴታዎች በሙሉ የማክበር ግዴታ አለት። አከራዩን በዋናው ውል የተቀመጡ ግዴታዎችን እንዲፈፅም ከተከራይ የተከራየ ሰው በቀጥታ ሊጠይቅ ይችላል። ይህን ማለት ለአብነት በዋናው ውል ውስጥ ተከራይ ቤቱን የማደስ ግዴታ ቢኖርበት አከራዩ ከተከራይ የተከራየ ሰው ቤቱን እንዲያድስ ሊጠይቀው ይችላል ማለት ነው። ዋናው አከራይ ከተከራይ የተከራየ ሰው ላይ የተከራየበትን ዋጋ በቀጥታ በእጁ ለርሱ እንዲከፍለው ለማስገደድ እንደሚችል በአንቀፅ 2962/2/ ላይ ተደንግጓል። ነገር ግን ከተከራይ የተከራየ ሰው እርሱ ከተስማማበት የኪራይ ዋጋ በላይ ላለው ተጠያቂ አይሆንም።


ዋናው የኪራይ ውል (በአከራይና በተከራይ መካከል ያለው) ቀሪ ሲሆን ከተከራይ የተከራየ ሰው ከተከራይ ጋር (የተከራይ ተከራይ ውል) ያደረገውን ውል ቀሪ እንደሚሆን በአንቀፅ 2964/1/ ላይ ተደንግጓል። ይህም ማለት ዋናው እና የመጀመሪያው የቤት ኪራይ ውል ሲፈርስ በዚሁ ቤት ላይ በተከራይ እና ከተከራይ የተከራየ ሰው መካከል የተደረገው ውል ይፈርሳል ማለት ነው። ነገር ግን አከራዩ በግልፅ ተከራዩ እንዲያከራይ ፈቅዶ እንደሆነ ዋናውን የኪራይ ውል ለመፈፀም ሁለተኛ ተከራይ (ከተከራይ የተከራየ ሰው) በዋናው ተከራይ ፋንታ ሊተካ ይችላል በማለት አንቀጽ 2964/2/ ላይ ደንግጎታል። ይህም ማለት አከራዩ በግልፅ ተከራዩ እንዲያከራይ ፈቅዶ ቀጣዩ ውል በተከራይ እና ከተከራይ የተከራየ ሰው መካከል ውሉ የተፈፀመ እንደሆነ ዋናው ውል ቢፈርስም ቀጥሎ የተደረገው ውል በዋናው አከራይ እና ከተከራይ የተከራየ ሰው መካከል እንደተደረገ ተቆጥሮ ውሉ ይቀጥላል ማለት ነው።


የቤት ኪራይ ክፍያን በጊዜው አለመክፈል ውጤት


ከላይ በንዑስ ክፍል 3.4 ላይ የቤት ኪራይ መች እንደሚከፈል አይተናል። ነገር ግን ተከራይ የሆነው አካል የቤት ኪራይ ክፍያውን በጊዜው ያልከፈለ እንደሆነ ወይም ሳይከፍል የቆየ እንደሆነ የሚያስከትለው ውጤት በፍትሐብሔር ሕጋችን አንቀፅ 2952 ላይ ተቀምጧል። በዚሁ መሠረትም


የቤት ኪራይ ውሉ ለአንድ ወይም ለአንድ ለበለጠ ጊዜ ተደርጎ እንደሆነ አከራዩ የሠላሳ ቀን ማስጠንቀቅያ በመስጠት፣


የቤት ኪራይ ውሉ ለአጭር ለሆነ ጊዜ ተደርጎ እንደሆነ አከራዩ የአስራ አምስት ቀን ማስጠንቀቅያ በመስጠት፣


በዚህ ጊዜ ውስጥ ተከራዩ ኪራዩን ያልከፈለ እንደሆነ አከራዩ ውሉን የሚያቆርጥ መሆኑን መንግር ይችላል። በዚህ በተሰጠው የማስጠንቀቂያ ጊዜ ውስጥ ተከራዩ ያልከፈለ እንደ ሆነ አከራይ ውሉን ለማቋረጥ በቂ ምክንያት ይሆናል።


ተዋዋይ ወገኖች በማንኛውም ሁኔታ እንዚህን ከላይ የተቀመጡ የማስጠንቀቂያ ጊዜ የሚያሳጥሩ ወይም ኪራዩ ባለመከፈሉ ምክንያት ወዲያው ውሉን የማፍረስ መብት ለአከራዩ የሚሰጡ የውሉ ቃሎች ፈራሾች ናቸው። (ፍ/ህ አንቀጽ 2952/3/)

 

የቤት ኪራይ ውሉ የሚፈርስበት ምክንያቶች


በተዋዋይ ወገኖች (አከራይ እና ተከራይ) በማህላቸው ያደረጉት የቤት ኪራይ ውል በተለያየ ሁኔታ ሊቋረጥ ይችላል። ከሚቋረጥባቸው ምክንያት
የቤት ኪራይ ውሉ ለተወሰነ ጊዜ ተደርጎ የውሉ ጊዜ ሲያበቃ።


ተዋዋይ ወገኖች በስምምነት ውላቸውን ለማቋረጥ ከተስማሙ።


ተከራይ ኪራዩን በጊዜው በለመክፈሉ አከራዩ የማስጠንቀቂያ ጊዜ ሰጥቶት በዚህ ጊዜ ውስጥ ያልከፈለ እንደሆነ አከራዩ ውሉን ካቋረጠው፣


አከራዩ ቤቱ ሲያድስ ለተከራዩና ለቤተሰቡ አስፈላጊ የሆነውን መኖሪያ ሊጠቀምበት የማይችል ያደረገው እንደሆነ ተከራይ አከራዩን በመጠየቅ ሲያፈርስ። (በፍ/ህ አንቀፅ 2956/2/)


አከራይ ቤቱን ፈልጎት ለተከራይ ማስጠንቀቂያ ጊዜ በመስጠት ወይም ተከራዩ ቤቱን መልቀቅ ፈልጎ ለአከራዩ ማስጠንቀቂያ ጊዜ በመስጠት ሲያቋርጥ፣


ከዚህ በላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች በአንድ የቤት ኪራይ ውል ሊቋረጥ ይችላል።


ነገር ግን አከራይ ቤቱን ፈልጎት ለተከራይ ማስጠንቀቂያ ጊዜ በመስጠት ሲያቋርጥ አከራዩ ሊሰጥ የሚገባው የማስጠንቀቂያ ጊዜ ምንያክል መሆን አለበት የሚለው በሕጉ መልስ አልተሰጠውም። ይህ ጉዳይ በህብረተሰቡ ውስጥም የተለያየ ውዥንብር እና ጭቅጭቅ ሲፈጠር ይታያል። ይህ ጉዳይ የፍትሐብሔር ጉዳይ መሆኑ እሙን ነው። በፍትሐብሔር ሕግን ስንተረጉም የምንከተለው መርሆች ውስጥ አንዱ ለተመሳሳ ጉዳይ ተመሳሳይ ሁኔታን (አናሎጂ) መጠቀም መተርጎም ይቻላል። በዚሁ መሠረትም አከራይ ቤቱን ፈልጎት ለተከራይ ማስጠንቀቂያ ጊዜ በመስጠት ሲያቋርጥ አከራዩ ሊሰጥ የሚገባው የማስጠንቀቂያ ጊዜ ተከራዩ ኪራዩን በጊዜው ባመለክፈሉ አከራዩ በፍትሐብሔር ሕግ አንቀፅ 2952 መሠረት የሚሰጠው የማስጠንቀቂያ ጊዜ ለዚህም ተግባራዊ ሊሆን ይችላል። ይህም ማለት፡ -


የቤት ኪራይ ውሉ ለአንድ ወይም ለአንድ ለበለጠ ጊዜ ተደርጎ እንደሆነ አከራዩ የሠላሳ ቀን ማስጠንቀቂያ በመስጠት፣


የቤት ኪራይ ውሉ ለአጭር ለሆነ ጊዜ ተደርጎ እንደሆነ አከራዩ የአስራ አምስት ቀን ማስጠንቀቅያ በመስጠት፣ ውሉን ሊያቋርጥ ይችላል።

 

ቤቱን የገዛ ወይም ያገኘ ሰው መብት


የፀና የቤት ኪራይ ውል ባለበት ቤት ላይ ሌላ ሰው የባለቤትነት መብት (ገዢ ወይም በስጦታ) ቢያገኝ ቤቱን የገዛው ወይም ያገኘው ሰው የነበረው የኪራይ ውል ለማቋረጥ እንዲችል መብት ተሰጥቶት እንደሆነና የኪራይ ውሉ እንዲቋረጥ ፈለገ እንደሆነ ቤቱ የተከራየው ለአጭር ጊዜ ከሆነ ይህ ጊዜ ሲያበቃ፣ እንዲሁም የቤት ኪራይ ውሉ ለአንድ ወይም ለአንድ ለበለጠ ጊዜ ተደርጎ እንደሆነ አከራዩ የሠላሳ ቀን ማስጠንቀቅያ በመስጠት ይህ ጊዜ ሲያበቃ መሆኑ በአንቀፅ 2967/1/ ተደንግጓል። ይህን ድንጋጌ በመቃረን የሚደረግ ውል ፈራሽ እንደሆነም በዚሁ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 2 ተደንግጓል።

 

ማጠቃለያ


ውል በሰዎች እለት ከእለት ኑሮ ውስጥ ከሚተገበሩ ተግባራት ውስጥ አንዱ ነው። ሰዎች በቀኑስጥ ብዙ አይነት ውሎችን ሊያደርጉ ይችላሉ አለብነት የቤት ኪራይ ውል። እነዚህ ውሎች የራሳቸው ሕጋዊ ውጤት ያስከትላሉ። ውሎቹ ሕጋዊ ውጤት እንዲያስከትሉ ደግሞ ሕጋዊ መስፈርቱን አሟልተው መመስረት ይሮርባቸዋል። ሕጋዊ መስፈርቱን አሟልቶ የተደረገ ውል ደግሞ በተዋዋዮቹ ወገን መካከል እንደ ሕግ የሚቆጠር ነው። ይህም ማለት በውሉ የተቀመጡ ግዴታዎችን አለመፈጸም ሕጋዊ የፍትሐብሔር ተጠያቂነትን ስለሚያስከትል።


የቤት ኪራይ ውል በፍትሐብሔር ሕጋችን ልዩ በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የሚደረጉ ውሎች ተብለው ከሚጠቀሱት ውሎች ውስጥ አንድ አይነት ነው። ተዋዋይ ወገኖች (አከራይና ተከራይ) የቤት ኪራይ ውሉን ሲያደርጉ በጠቅላላ የውል አመሰራረት የተቀመጡ አስገዳጅ የሆኑ ህጎችን በመከተል በፈለጉት አይነት ፎርም (በጽሑፍ ወይም በቃል) ሊያደርጉት ይችላሉ። ነገር ግን በጽሑፍ ቢያደርጉት እጅግ የተሻለ ነው።


የቤት ኪራይ ውል በተመለከተ ተዋዋይ ወገኖች የውሉን ይዘት ማለትም ስለውሉ ቆይታ፣ ስለ ክፍያ መጠንና ጊዜ፣ ስለእድሳት፣ ስለውል ማቋረጥ፣ ወዘተ የመሳሰሉትን በውላቸው ውስጥ ሊስማሙበት ይችላሉ። ነገር ግን ያልተስማሙባቸው ነገሮች ካሉ በፍትሐብሔር ሕጉ ላይ የተቀመጡት ድንጋጌዎች ተፈፃሚ ይሆናሉ።

 

ጌታሁን ወርቁ (www.abyssinialaw.com)

በማንኛውም አገር የመንግሥት አስተዳደር ከሕግ አውጪውና ከሕግ አስፈጻሚው እኩል የዳኝነት አካሉ አደረጃጀት፣ አወቃቀርና ጥንካሬ የሥርዓቱን ዴሞክራሲያዊነት ይወስናል። የዳኝነት አካሉ ገለልተኛና ነፃ ባልሆነ መጠን የሥርዓቱ ዴሞክራሲያዊነት ዋጋ ያጣል። የዳኝነት አካሉ መሠረታዊ ሕገ መንግሥታዊ መርሆችን ለማስፈጸም፣ የዜጎች የሰብዓዊ መብቶች እንዲጠበቁና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ገለልተኛ፣ ግልጽ አሠራርን የሚከተልና ጠንካራ እንዲሆን ያስፈልጋል። በ1987 ዓ.ም. የወጣው ሕገ መንግሥታችን በአንቀጽ 78 እና 79 እነዚህ መሠረታዊ የዳኝነት አካሉመገለጫዎችን ደንግጓል። ይሁን እንጂ ሕገ መንግሥቱ ከወጣ ከ25 ዓመታት በኋላም የዳኝነት አካሉ የአሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነት አመርቂ እንዳልሆነ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ይስማማሉ።

ለዚህ ነው የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ2015 ዓ.ም በሕዝብ ታማኝነት ያለው የዳኝነት አካል ለመሆን ራዕይ ይዞ የሚንቀሳቀሰው። ከ15 ቀናት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፀደቀው የዳኝነት ሹመት ጋር በተያያዘ በሕግ ባለሙያዎች በየዐውዱ የሚደረገው ክርክር የዚህ አንዱ መገለጫ ነው። ኃይለ ገብርኤል መሐሪ የተባሉ ጸሐፊ ሰኔ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. በሪፖርተርጋዜጣ የአስተያየት አምድ “ግልጽነት የጎደለው የዳኞች ምልመላ” በሚል በጻፉት ጽሑፍ የተሾሙት ዳኞች ምልመላበአጭር ጊዜ የተፈጸመ፣ በቂ ፈተናና ግምገማ ያልተደረገበት፣ የሕዝብ አስተያየት በአግባቡ ያልተወሰደበትና ግልጽነትየጎደለው እንደነበር ይገልጻሉ። ጸሐፊውን ጨምሮ በፍርድ ቤቶች አካባቢ የሚታዩ ጠበቆችም የዳኞቹ አመላመልናሹመት ጋር በተያያዘ ሊታዩ የሚገቡ ነጥቦች እንዳሉ ያምናሉ።

የዳኞች አመላመልና አሿሿም የዳኝነት አካሉን ነፃነት ከሚያረጋግጡ ቅድመ ሁኔታዎች ዋናው ነው። ዳኞችምከማንኛውም ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ ተፅዕኖ ነፃ በመሆን ፍትሕ እንዲሰፍን የሚሠሩት ምልመላውና አሿሿሙግልጽና ተጠያቂነት ሲኖረው ነው። የዳኞች አሿሿም የዳኝነት አካሉን ነፃነት ከሚያስገኙ የገለልተኝነት፣ የብቃት፣የሃቀኝነትና የነፃነት እሴቶች ጋር እጅጉን ይቆራኛል። የዳኝነት አካሉ በኅብረተሰብ ውስጥ ተገቢውን ቦታ እንዲያገኝበግልጽነት የዳኞችን የመሾም ሥርዓት ሊያከናውን ይገባል። ይህ የሚሳካው ደግሞ የዳኞች የአመራረጥና የአሿሿምዘዴ፣ የሚመረጡ ዳኞች ዕውቀትና ልምድ በጥንቃቄና በኃላፊነት ሲከናወን ነው። በዚህ ጽሑፍ ከዳኝነት አሿሿም ጋርበተያያዘ ጥንቃቄ የሚፈልጉ አንዳንድ ነጥቦችን ለመመልከት እንሞክራለን።

 

የዳኝነት አሿሿም ዘዴዎች

የዳኝነት አሿሿም እንደ አገሮቹ የፖለቲካ ባህልና ማኅበራዊ እሴት ይለያያል። አንድ ወጥ የአሿሿም ሥርዓት የለም። ማንኛውንም የአሿሿም ሥርዓት የሚከተል አንድ አገር የዳኝነት አካሉ ነፃ እንዲሆን የአሿሿም ሒደቱ ግልጽናኅብረተሰቡን ያሳተፈ ሊሆን ይገባዋል። ግልጽነትና የሕዝብ ተሳትፎ በአሿሿም ካለ ጥራትና ብቃት ያላቸው የሕግባለሙያዎች ዳኛ ይሆናሉ። ኅብረተሰቡ በዳኝነት አካሉ ላይ ያለው መተማመን ይጨምራል።

በተለያዩ አገሮች ተፈጻሚ የሚሆኑ የዳኝነት አሿሿም በደምሳሳው በሁለት ሊከፈል ይችላል። አንዱ በምርጫየሚከናወን ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በመሾም ሥርዓት የሚከናወን ነው።

ዳኞችን በምርጫ መሾም እንደማንኛውም የፓርላማ ምርጫ በሕዝብ ማስመረጥ ወይም በሕግ አውጪው አካልማ ስመረጥን ይመለከታል። ዳኞች በቀጥታ ወይም በፖለቲካ ፓርቲዎች አቅራቢነት ሕዝቡ አስተያየት ሰጥቶባቸውና መርጧቸው የሚሾሙ ይሆናል። ለምሳሌ በአሜሪካ የተወሰኑ ግዛቶች ይህ ዓይነት አመራረጥ ሥራ ላይ ይውላል። በሳውዝ ካሮሊና እና ቨርጂኒያ ተግባራዊ የሚሆነው አመራረጥ Legislative Appointment የሚባለው ሲሆን፣ የሕግ አውጪው አካል ከዜጎች ጋር በመተባበር በውስጡ ባቋቋመው ኮሚሽን አማካይነት ዳኞችን መርጦ ይሾማል። በካሊፎርኒያና በኒው ጀርሲ ተፈጻሚ የሚሆነው አሿሿም ደግሞ Executive Appointment የሚባለው ሲሆን፣ አስፈጻሚው ዳኞቹን መርጦ በሕግ አውጪው አካል ያሾማል።

እንዲህ ዓይነት ዳኞችን በምርጫ የመሾም ዘዴ ዳኞች በመደበኛነት ለመረጣቸው አካል ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚያስችል ሲሆን፣ አልፎ አልፎ ዳኞች ሕግም የማውጣት ድርሻ ስለሚኖራቸው በሕግጋቱ በሚገዛው ሕዝብ መመረጣቸውን ፍትሐዊ እንደሆነ የሚገልጹ አሉ። ይሁን እንጂ ይህ ዓይነት የዳኝነት አሿሿም ዳኞች በብቃታቸውና በልምዳቸው ሳይሆን በፖለቲካ ታማኝነታቸው፣ በሙያቸው ሳይሆን በምርጫ ዘመቻቸው እንዲመረጡ ያደርጋል። በተጨማሪም መራጩ ሕዝብ ስለ ሙያው ያለው ዕውቀት አናሳ ስለሚሆን ብቁ ያልሆኑ ዳኞች ሊመረጡ ይችላሉ።

ሁለተኛውና በብዙ የዓለማችን ክፍሎች ተግባራዊ የሚደረገው ዳኞች በአስፈጻሚው የመንግሥት አካል ተመርጠው በሕግ አውጪው አካል የሚሾሙበት ወይም የሚፀድቁበት ሁኔታ ነው። የዳኞች መረጣው ሙሉ በሙሉ በአስፈጻሚው የሚሠራ ከሆነ አስፈጻሚው ለራሱ የፖለቲካ ጥቅም ስለሚያውለው የዳኝነቱን ነፃነት ዋጋ የሚያሳጣ ይሆናል። አስፈጻሚው ከሕግ ባለሙያዎችና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተውጣጡ ገምጋሚዎች (Jurists and commentators) ሊታገዝ ያስፈልጋል። በዚህ ዓይነት የዳኞች አመራረጥና አሿሿም ሦስት መሠረታዊ ሒደቶች በጥንቃቄ ሊፈጸሙ እንደሚገባ ጸሐፍት ይገልጻሉ። እነዚህም በሕግ አውጪው አካል የማጽደቅ (Parliamentary Approval) የዳኝነት አካሉንና የሕግ ባለሙያዎችን የማማከር (Consultation with Judiciary and Legal profession) እንዲሁም ገለልተኛ ኮሚሽንን የመጠቀም (Use of an independent commission) ሒደት ናቸው።

በፓርላማ የማጽደቅ ሒደት በመጀመሪያ አስፈጻሚው የመንግሥት አካል ለዳኝነት ዕጩ የሆኑትን ይመርጥና ፓርላማው ሲያፀድቀው ብቻ ዳኞቹ የሚሾሙ ይሆናል። ለምሳሌ በአሜሪካ ፕሬዚዳንቱ የፌደራል ዕጩ ዳኞችን ለሴኔቱ ያቀርባል ሴኔቱ ይሾማል። እንዲህ ዓይነት አሿሿም ሕግ አውጪው አስፈጻሚውን ለመቆጣጠር የሚያስችለው ሲሆን፣ በሒደቱም ሕዝቡ ዕጩዎችን በመገምገም እንዲሳተፍ ይረዳል። እንዲህ ዓይነት የአሿሿም ሥርዓት የራሱ ውስንነት አለው። ፓርላማው በዕጩ አመራረጥ ሒደቱ ስለማይሳተፍ አስፈጻሚው ለራሱ የፖለቲካ ዓላማ መሣሪያነት ሊጠቀምበት ይችላል። በተለይ በፓርላማው ውስጥ ብዙ የአንድ ፓርቲ አባላት ከተገኙበት የአሿሿም ሥርዓቱ በፖለቲካ ደጋፊነት (Political Patronage) ዳኞች የሚሾሙበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።

በዳኞች አሿሿም የዳኝነት አካሉንና የሕግ ባለሙያዎችን ማማከር ነፃና ገለልተኛ ዳኞች እንዲሾሙ እንዲሁም በብቃትና በልምዳቸው የተመሰከረላቸው ዳኞች እንዲሾሙ ያስችላል። ዳኞች ለዳኝነት ብቁ የሆኑ ዕጩዎችን ለመገምገም፣ ዕጩው ዳኛ ለዳኝነት ብቁ የሚያደርግ ዕውቀትና ክህሎት እንዳለውና እንደሌለው ለመመዘን የተሻሉ ናቸው። የሕግ ባለሙያዎችንም ማማከር ጠቃሚነቱ የጎላ ነው። ከተለያዩ የሕግ ባለሙያዎች የተውጣጣ አካል የተመረጠው የሕግ ባለሙያ ፀባዩን፣ ችሎታውንና ለቦታው የሚመጥን መሆን አለመሆኑን ለመገምገም የሙያ ቅርበት ይኖራቸዋል። ይህ ዓይነት የማማከር ሒደት ብቁ ዳኞች እንዲመረጡ፤ ሕዝቡም በዳኝነት አካሉ ላይ ያለው መተማመን እንዲጨምር የማድረግ ውጤት ቢኖረውም የተወሰኑ ውስንነቶች አሉበት።

አስፈጻሚው አካል ዳኞቹንና የሕግ ባለሙያዎቹን የሚያማክረው ለይስሙላ ከሆነ ወይም ባለሙያዎቹ የሚሰጡትን ምክር፣ ግምገማና አስተያየት ከመጤፍ የሚቆጥር ከሆነ ማማከሩ ትርጉም የለውም። በዚህ ረገድ የህንድ ሕገ መንግሥት ፕሬዚዳንቱ የጠቅላይና የከፍተኛ ፍርድ ቤትዳኞችን ሊሾም የፍርድ ቤቶቹን ፕሬዚዳንቶች ጨምሮ የፍርድ ቤቶቹን ዳኞች፣ የሕግ ባለሙያዎችን የከተማ ገዥዎችን የማማከር ግዴታ እንዳለበት በግልጽ ይደነግጋል።

በብዙ የዓለማችን አገሮች ተቀባይነት ያለው አሠራር ገለልተኛ ኮሚሽን አቋቁሞ የዳኞችን ጥቆማ መቀበል፣ የመገምገምና ዕጩዎችን የመምረጥ አሠራር ነው። እንዲህ ዓይነት ዳኞችን የሚመርጥ ገለልተኛ ኮሚሽን ወይም ኮሚቴ በካናዳ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በብዙ የአሜሪካ ግዛቶች፣ በአየርላንድ፣ በእስራኤል ወዘተ. ተግባራዊ ይደረጋል። ኮሚሽኑ ወይም ኮሚቴው ከዳኞችና ከተለያዩ የሕግ ባለሙያዎች የሚውጣጣ ሲሆን፣ ዳኞችን የመምረጥ ወይም የመጠቆም ወይም ከተወሰኑ ዝርዝሮች ውስጥ አስፈጻሚው እንዲመርጥ የመጠቆም ድርሻ ይኖራቸዋል። የእንዲህ ዓይነት ኮሚሽን ውጤታማነት የሚወሰነው በአባላት ስብጥሩና በሚከተለው ሥርዓት ነው።

ኮሚሽኑ ከዳኞች፣ ከታዋቂ የሕግ ባለሙያዎች፣ ከሕግ ምሁራን፣ ከኅብረተሰቡና ከፓርላማው የተወሰኑ ተወካዮችን ሊያካትት ይችላል። ኮሚሽኑ ውጤታማ ከሆነ ለዳኝነት አካሉ የሚመጥኑ ምርጥ ዕጩዎችን ያቀርባል፣ ለሕዝብ ያስገመግማል። ይህን በማድረጉም የአስፈጻሚውን ተፅዕኖ ይቀንሳል ሕዝቡ ለዳኝነት አካሉ የሚኖረውን መተማመን ይጨምራል። በዚህ ረገድ የአፍሪካዊቷ አገር የደቡብ አፍሪካ ምሳሌ እጅግ ጠቃሚ ነው።

በደቡብ አፍሪካ ከ10 በላይ ባለድርሻ አካላት ዳኞች፣ የፍትሕ ሚኒስቴር፣ ጠበቆች፣ የሕግ አስተማሪዎች፣ ተቃዋሚዎችን ጨምሮ የፓርላማ አባላት ከአስፈጻሚው አካል ወዘተ. የሚውጣጡ ይሆናሉ። ይህ ኮሚሽን ለዳኝነት መወዳደር የሚፈልጉ የሕግ ባለሙያዎችን በሥራ ማስታወቂያ (Advertising Judicial Vacancy) ይጠራል፣ በግልጽ የተመረጡ ተወዳዳሪዎችን ቃለ መጠይቅ ያደርግና እንዲሾሙ ከሚፈለገው የዳኞች ቁጥር ሦስት ያህል ተጨማሪ ዕጩ በመጨመር ለፕሬዚዳንቱ ያስተላልፋል። ይህ ረዥም ጥብቅ የአመራረጥ ሒደት ለዳኞቹ ጥራትና ብቃት ዋስትና ይሰጣል።

 

የዳኞች አሿሿም በአገራችን

የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ነፃ የዳኝነት አካል ያቋቋመ ሲሆን፣ የፍርድ ቤቶችን ቅርጽና ሥልጣን በዝርዝር ደንግጓል። የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አባላት የፌዴራል ዳኞችን በተመለከተ ዕጩዎችን መልምሎ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲያፀድቅ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይልካል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፌዴራል ዳኞች በተጨማሪ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትንና ምክትል ፕሬዚዳንትን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ያፀድቃል። ሕገመንግሥቱ የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የአባላትን ስብጥር፣ ሥልጣንና ተግባር የዳኞች አመላመል ዘዴና ተያያዥ ጭብጦችን የተመለከተ ድንጋጌዎች በዝርዝር አልያዘም።

እነዚህ ጉዳዮች በዝርዝር የታዩት በፌዴራል የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 24/1988 ሲሆን፣ ይህ አዋጅ የዳኞችን ተጠያቂነት ለማስፈንና የጉባዔውን ስብጥር ለማስፋት በሚል ዓላማ በአዋጅ ቁጥር 684/2002 እንዲተካ ተደርጓል። በአዋጁ መሠረት ይህ ጉባዔ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ጥያቄ ለፌዴራል ዳኝነት ቦታዎች ዕጩዎችን የመለየት፣ ብቁ የሆኑትን የመለየት፣ የፍርድ ቤትሠራተኞችን ደመወዝ፣ አበልና ጥቅማ ጥቅም መወሰን፣ የሥነ ምግባር ደንብ፣ የዲሲፕሊን ክስ ሥነ ሥርዓት ደንብናየሥራ አፈጻጸም መመዘኛ መሥፈርት ማውጣትና ተግባራዊነቱን መከታተል ከሥልጣኑ የተወሰኑት ናቸው።

የጉባዔው አባላት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት፣ ሦስት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትአባላት፣ የፍትሕ ሚኒስትር የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶች፣ ከጠበቆች፣ ከዳኞችና ከታዋቂ ግለሰብ የሚመረጡ ከእያንዳንዳቸው አንድ አንድ አባላት ይኖሩታል። የጉባዔው አባላት ቁጥርና ስብጥር በቀድሞው አዋጅ ከነበረው እንዲጨምር ተደርጓል።

አዋጁ ለዳኝነት ለመሾም የሚያበቁ ሁኔታዎችን በተመለከተ ሰባት መሥፈርቶችን በዝርዝር አስቀምጧል። በዳኝነትሙያ ለመሰማራት ፈቃደኛ የሆነ፣ ዕድሜው ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ከ25 ዓመት ያላነሰ፣ ለፌዴራል ከፍተኛና ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከ30 ዓመት ያላነሰ፣ ዕውቅና ካለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም በሕግ ትምህርት ቢያንስ በመጀመሪያ ዲግሪ በከፍተኛ ውጤት የተመረቀ፣ ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ የሆነ፣ ጉባዔው በሚያደርግለት ቃለመጠይቅ፣ የማጣሪያ ፈተናና ሌሎች የባህርይ ምርመራዎች በዕውቀቱ፣ በታታሪነቱ፣ በሥነ ምግባሩ፣ በፍትሐዊነቱና በሕግ አክባሪነቱ መልካም ስም ያለው፣ የቅድመ ዕጩነት ሥልጠና የሚያጠናቅቅ፣ በጽኑ እስራት ተቀጥቶ የማያውቅ የሆነ በዳኝነት ቦታ ሊታጭ ይችላል።

ሕገ መንግሥቱ ከወጣ በኋላ በተለይ የመጀመሪያው የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ከተቋቋመ በኋላ የተደረጉ ሹመቶችን ካስተዋልን የፌዴራል ሥርዓቱ የሚጠይቀውን የዳኞች ብዛት ከማሟላት ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ከሕግ ትምህርት ቤት የተመረቁ የሕግ ምሁራን ያለብዙ ውጣ ውረዱ የሚሾሙበት አጋጣሚ ነበር። በዓለም ባንክ እ.ኤ.አ. በ2004 የተሠራ የኢትዮጵያ የሕግና የዳኝነት ሴክተር ግምገማ ጥናት በጊዜው የነበሩት በዳኝነት አሿሿም ላይ የሚታዩትን ችግሮች እንዲህ ሲል ይገልጸዋል።

“The new levers of decentralized federal/ state judicial systems introduced in the 1995 constitution created numerous new courts as well as enormous staffing demands. The remaining pool of legally - trained personnel was utterly insufficient to meet these demands. Consequently, professional qualifications were relaxed to meet immediate needs and to bring younger judges in to the new system who were unconnected with the prior regime.”

በጊዜው በፌዴራል ሥርዓተ መንግሥት አወቃቀር የተፈጠረውን የዳኝነት ፍላጎት ለማሟላት በቁጥር አነስተኛ የነበሩትን የሕግ ተመራቂዎች በዝቅተኛ መሥፈርት በልጅነታቸው በመሾም በጊዜው የነበረውን ችግር ለመቅረፍ ጥረት ተደርጓል። በዚያ ወቅት የነበሩት ዳኞች በብዙ መሥፈርት በብቃት የዳኝነት ሥራውን እንደተወጡት ቢታመንም፣ በጊዜው ከበቂ ሥልጠናና ልምድ ማነስ ጋር የሚታዩ ቅሬታዎች እንደነበሩ ይኼው ጥናት ይጠቁማል። ዳኞቹ በፍርድ ቤት ቆይታቸው እየበሰሉና ልምድ እያካበቱም ሲመጡ በጊዜው ይከፈል የነበረው ደመወዝ አነስተኛ ከመሆኑ የተነሳ ልምድ ያላቸው ዳኞች ወደ ጥብቅናው ዓለም ወይም ወደ ግል ሴክተሩ እየተቀላቀሉ የሕግ ምሩቃን ከሁለትና ሦስትዓመታት በላይ በፍርድ ቤት የማያገለግሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህም የዳኞችን እጥረት እያስከተለ፣ የመዛግብት ብዛት እየጨመረ ፍርድ ቤቶች የኅብረተሰቡን ፍላጎት ለማርካት አስቸግሯቸው ነበር።

በጊዜው የነበረው የዳኝነት አሿሿምም ግልጽና ወጥ መሥፈርትና ሥርዓት የሌለው፣ የፌዴራል የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የዳኞች አመራረጥና ዕጩ አቀራረብ ግልጽነት የጎደለው፣ የጥናት ማነስና የውሳኔ አሰጣጥ ተገማችነት አለመኖር በአጠቃላይ የፕሮፌሽናሊዝም እጦት በችግርነት እንደሚጠቀስ ከላይ የጠቀስነው የዓለም ባንክ የግምገማ ጥናት ይዘረዝራል።

በአሁኑ ወቅት ተፈጻሚ የሆነው የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ማቋቋሚያ አዋጅ ከላይ የተዘረዘሩትን ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችሉ ድንጋጌዎችን አካቷል። የጉባዔውን አባላት ቁጥርና ስብጥሩን ማብዛቱ፣ ለዕጩ ዳኞች አስፈላጊ የሆነውን አነስተኛ ዕድሜ እንደ ፍርድ ቤቱ ዓይነት የተለያየ ማድረጉ፣ ለዳኝነት የሚፈለገው የትምህርት ደረጃ ወደየመጀመሪያ ዲግሪ ከፍ መደረጉ፣ ዳኞች የሚመለመሉበትን በማስታወቂያ የመጥራት፣ ቃለመጠይቅና የማጣሪያ ፈተና እንዲኖር በማድረጉ ከቀድሞው ይለያል። በዳኞች አመራረጥና አሿሿም ላይ ትኩረት አደረግን እንጂ ሌሎች ልዩነቶችንም መጥቀስ ይቻላል።

ይሁን እንጂ የዚህን አዋጅ ይዘት፣ አፈጻጸምና የዳኞችን አሿሿም በተመለከተ የሚነሱ ትችቶች አሉ። በዋናነት በዚህ ጽሑፍ መግቢያ ለመጥቀስ እንደሞከርነው የዳኞች አመራረጥና አሿሿም ዓላማ የዳኞች ነፃነት በተግባር እንዲገለጥ፣ ብቁና ጥራት ያለው ዳኛ እንዲሾም እንዲሁም የዳኝነት አካሉ ከአስፈጻሚው አካል ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ የሕዝብ አመኔታው እንዲጨምር ማድረግ ነው። ከዚህ አንፃር አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች የዕጩ ዳኞቹ አመራረጥና አሿሿም በበቂ ጊዜና የኅብረተሰብ ተሳትፎ እንዲሁም በጥንቃቄ ስለመከናወኑ ሥጋት አላቸው። ምንም የተቃዋሚ አባል በሌለበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለዳኝነት የሚቀርበው መሥፈርት፣ መራጩና ሿሚው ጥንቃቄ ካላደረገ የአስፈጻሚው ተፅዕኖ እንዳይሰፋ ሥጋት አለ።

እስካሁን የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አሳልፎት፣ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ለሹመት ያቀረቡት ግንበምክር ቤቱ ተቀባይነት ያጣ ሹመት አለመኖሩን አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች ለጥንቃቄ ትኩረት ለማነሱ እንደማስረጃ ይጠቅሳሉ። የዳኝነት አሿሿም ከሦስቱ ዋና የመንግሥት አካላት አንዱን ክንፍ መሾም እንደመሆኑ በአፅንኦት ሊከናወንሲገባ፣ የሕዝብ አስተያየት እየተደመጠበት በስፋት በውይይት ሊሆን ሲገባ የሹመቱ አጀንዳ በሕዝቡ ውስጥመነጋገሪያ እስኪሆን ድረስ የሕዝብ ተሳትፎ ማረጋገጥ አለመቻሉ ፈተና ሳይሆን አልቀረም። በአዲሱ አዋጅ ዳኞችንበፈተና የመምረጥ ሒደት እንደመሥፈርት ከመቀመጡ ውጭ ለዳኝነት ብቁ የሆነ ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ማስገኘቱንበማስረጃ ማረጋገጥ አስቸጋሪ ይሆናል። ከፈተናው እኩል ወይም ይልቅ የአመለካከት ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው ይመስላል።

ፈተናውን ማን ነው የሚያወጣው? ይዘቱን በተመለከተ የተቀመጠ መመርያ (Guideline) አለ ወይ የፈተናው ይዘትስ ለዳኝነት ብቁ የመሆን ዕውቀትና ክህሎትን ይመዝናል ወይ? የሚለው ራሱን የቻለ ጥናት የሚፈልግነው። ኃይለ ገብርኤል መሐሪ፣ በጽሑፋቸው 700 ተፈታኞች በአንድ አዳራሽ፣ እርስ በርስ መኮራረጅ ባለበት ሁኔታ ‹‹ፈተና›› መደረጉን መሞገታቸው ለዚህ ነው። በጥሞና የፈተና መሥፈርትን ለገመገመው ዳኝነት ማንኛውም በሕግየተመረቀ ሰው የሚሞክረው እንጂ ፍላጎት፣ ትጋት፣ ክህሎት፣ ቁርጠኝነት ያለው የሚያገኘው ለተገቢው ብቁ ባለሙያብቻ ክፍት የሆነ አያስመስለውም። ከዚህ ውጭ ሌሎች መሥፈርቶችም ላይ አንዳንድ የሕግ ምሁራን የሚያነሷቸው ትጋቶች አሉ።

የ25 ዓመት የዕድሜ ገደብ ለአብዛኞቹ ተሿሚዎች ባልበሰሉበት ዘመን (የማኅበረሰቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ባልተረዱበት፣ የሚሰጡት ፍርድ በኅብረተሰቡ ውስጥ ሊኖረው የሚችለውን ውጤት በማይገምቱበት፣ በአግባቡ ጭብጥ ለመመሥረትና ለመመርመር ክህሎት ባልዳበረበት ዕድሜ) መሆኑ ጥራቱ ላይተፅዕኖ እንደሚያደርግ መገመት አያስቸግርም። ለሁሉም ባይሠራ ለብዙኃኑ ሊሠራ ይችላል። ከፍተኛ ውጤት (ስንትመሆኑ በግልጽ በማይታወቅበት) የመሥፈርቱም አስፈላጊነት አከራካሪ በሆነበት መሥፈርቱን ማሟላት አስቸጋሪ መሆኑን የሚገልጹ አሉ።

በአጠቃላይ ከላይ ያነሳናቸው ነጥቦች የዳኝነት አመራረጥና አሿሿም ላይ ሥርዓቱ የበለጠ እንዲሠራ፣ ነፃነትና የሕዝብ ታማኝነትን ለመጨመር በጥንቃቄ ሊሠራ እንደሚገባ አመላካች ነው።

 

· ተቀባይነትን ያስገኘላቸውና ተደናቂነትን ያተረፈላቸው፣ ከበዓለ ሢመታቸው ጀምሮ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ በማድረግ የሚገልጹባቸው ውብና ወርቃማ ቃላት በመኾናቸው፣ ስለ ተግባራዊነታቸው ዘወትር ሊያስቡበት ይገባል፤


· ኢትዮጵያን የማያውቅ ትውልድ እየተፈጠረ በመኾኑ፣ በአስተዳደር ዘመናቸው፣ የአንዲት እናት ሀገር ልጆች፣ የጠላት መሣሪያዎች ኹነን፣ በጎጥና በድንበር ተከለን ዐይንህ ላፈር የምንባባልበት የጎጣጎጥ ጉዳይ ሊያበቃና ትውልዱ አንድ በሚኾንበት ጉዳይ ላይ መሥራት ያስፈልጋል፤


· የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፥ የኢትዮጵያ ባለአደራ፣ ጥንታዊት፣ አንጋፋና እናት ቤተ ክርስቲያን መኾኗ የማይካድ ሐቅ ቢኾንም፣ ውለታዋ ተዘንግቶ፣ በሃይማኖት እኩልነትና ነፃነት ስም እንርገጥሽ የተባለችበት ዘመን ኾኗል።


· ዛሬም የኢትዮጵያን ታሪክ ለማሳየት የምትጥረዋን እናት ቤተ ክርስቲያን፣ ትውልዱ ማክበር ለምን ተሳነው? በምሥራቁና በደቡቡ፣ መንግሥታዊ አደራን ረግጠው ራሳቸውን የሃይማኖት መሪ ባደረጉ ባለሥልጣናት ጣጣው እየበዛባት፣ ፈተናው እየከበዳት ነው፤


· እባክዎ ክቡርነትዎ፣ በአስተዳደር ዘመንዎ፡-እኩልነት፣ ሰላም፣ አንድነት፣ መቻቻል በቃል ሳይኾን በተግባር ሰፍኖ፤ አልይህ፣ አልይህ መባባል ቀርቶ፣ በትምህርት እንጅ በሰይፍና በጥቅምጥቅም፣ በዱላና በአባርርሃለሁ ባይነት ያልተመሠረተ፣ ሰላማዊነት እንዲሰፋና እንዲሰፍን አደራ እልዎታለሁ፤


· አባቶቻችን፥ ስምን ፈረሰኛ አይቀድመውምና ልጄ ተጠንቀቅ፤ ይላሉ፤ በበጎ ጀምረውታል፤ በበጎ እንዲደመድሙት፤ በጎ በጎውን ምክር የሚመክርዎትን፣ በጎ በጎ ሐሳብ የሚያመጡልዎትን ተከትለው ይምሩን፤


· እንዲህ እስከመሩን ድረስ፣ ሹመትዎ ከእግዚአብሔር ነውና፣ እጅግ ውብ በኾነ ዐረፍተ ነገር የመሰከሩላት ኢትዮጵያ፣ ከቃል ወደ ተግባር ተለውጣ፣ ሺሕ ዓመት ያንግሥዎት እንድንል እንገደዳለን፤ እንደ ጥንቱ።  


· ኢትዮጵያዊነት ሲሸረሸር እንደቆየና እየተካደም እንዳለ ለባሕር ዳርና አካባቢው ነዋሪዎች የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ መጠገንና መታከም እንዳለበት አሳስበው፣ ለዚህም ቀና ቀናውን ማሰብ፣ ያሰብነውን መናገር፣ የተናገርነውንም ተደምረን መተግበር እንዳለብን አስገንዝበዋል፤


· መደመር በአንድ ጀንበር እንደማይመጣና ጊዜና መደጋገፍ እንደሚፈልግ ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ፣ ቂምን ከመቁጠር ይልቅ በይቅርታ ልብ ተደጋግፈን፣ ከትላንቱ ተምረን መልካሙን በመያዝ፣ ክፋቱ አይበጅም፤ አይደገምም ተባብለን ኢትዮጵያን ማስቀጠል እንዳለብን መክረዋል፤


· “በኦሮሞ ኮታ አታስቡኝ፤ የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የትግራይ፣ የአፋር፣ የሶማሌ ጠቅላይ ሚኒስትር ነኝ፤ እኩል ነው የማገለግላችሁ፤” በማለት አስታውቀው፣ “የሃይማኖት አባቶች፥ በጸሎትና በምክርም እንድታግዙኝ እጠይቃለሁ፤” ብለዋል።


· የሃይማኖት አባቶችም፥ትሕትናን፣ አክብሮተ ሰብእን፣ ግብረ ገብነትን፣ ክፉ ሥር የኾነውን ሌብነትን መጸየፍን ለትውልዱ በማስተማር ድርሻቸውን እንዲወጡና እንዲደግፉ ጠይቀዋል፤


· አገራዊ ዕውቀት እንዲያብብ ጥንታውያኑ ጣና ቂርቆስ፣ ደብረ ኤልያስ እና ዲማ ጊዮርጊስ የመሳሰሉ ታላላቅ አድባራትና ገዳማት፤ ከእነርሱም የተገኙ ሊቃውንትና አይተኬ አስተምህሮዎች፣ በኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ ውስጥ ሐሳቦችን በማመንጨትና ትውልድን በመቅረጽ መሠረታቸውን ያኖሩ ባለውለታዎች እንደኾኑ ጠቅሰዋል፤


· አራት ዐይና ጎሹና መምህር አካለ ወልድ፣ ከሊቅነታቸው ባሻገር በማኅበራዊ የሽምግልና ሚናቸውና ምክራቸው እንደሚታወቁ፤ አለቃ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ፣ ወለጋ ቢወለዱም ጎጃም-ደብረ ኤልያስ ተምረው በጎንደርም እንዳስተማሩ አንሥተዋል፤


· ዘመናዊ ትምህርት ባልተጀመረበት የአገራችን ታሪክ፣ የአስተዳደሩ መዋቅር ይሸፈን የነበረው ከአብነት ት/ቤት ተመርቀው በሚወጡ ምሁራን እንደነበር አውስተው፤ ዛሬም የባህል፣ የጥበብና የዕውቀት ገድሉን በማስቀጠልና የላቀ ትውልድ ለማፍራት ብዙ መጣር ይጠበቅብናል፤ ብለዋል፤

 

የብፁዕነታቸው ንግግር ሙሉ ቃል፡-


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን


· ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር


· ክቡር ፕሬዝዳንት


· ክቡር ከንቲባ


· ክቡራን ሚኒስትሮችና በዚህ ጉባኤ የተገኛችሁ በሙሉ፤

 

ብፁዕ አቡነ አብርሃም: የባሕር ዳር እና ምዕራብ ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ


ከሁሉ አስቀድሞ ልዑል እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ኾኖ በዚህ ዕለት ከልዩ ልዩ ነገር፣ እኛ ከማናውቀው እርሱ ከሚያውቀው ፈተና ሰውሮ ከመሪያችን ጋራ በአንድነት ስለ ሀገራችን እንድንወያይ፣ እንድንመካከር፤ ከአዲሱ መሪያችንም መመሪያ እንድንቀበል፣ ጊዜውን ፈቅዶና ወዶ በዕድሜያችንም ላይ ተጨማሪ አድርጎ የሰጠን እግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይኹን።


ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ምንም እንኳ እንግዳ ባይኾኑም ወደሚመሩት ሕዝብዎ በመምጣትዎ ቤት ለእንግዳ  የምትለው ሀገር እንኳን ደኅና መጡ፤ ትላለች። ዘመንዎ ኹሉ፥ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የመግባባት፣ የብልጽግና ይኾን ዘንድ  ምኞትዋንም ትገልጻለች።


ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ እኔ ልናገር የምፈልገው ክቡርነትዎን በተመለከተ ነው የሚኾነው። በድፍረት ሳይኾን በታላቅ ትሕትና።
ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ማንም ማን አይሾምም። በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርታችን፣ ማንኛውም ሰው በታላቅም ደረጃ ይኹን በቤተሰብ አስተዳደር ከታች ጀምሮ እግዚአብሔር የፈቀደለት ይሾማል። እግዚአብሔር ፈቅዶልዎትም በመራጮችዎ አድሮ ሹሞታል። ያከበርዎትና የሾሞት እግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይኹን።


እግዚአብሔር ሲሾም ግን፣ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት፣ ኹለት ዐይነት አሿሿሞች አሉ። የክቡርነትዎ የትኛው ነው? በጎው እንደሚኾን ሙሉ ተስፋ አለኝ፤ አኹን ከሚታየው። እግዚአብሔር፥ አንዱን ለጅራፍነት፣ ለአለጋነት ይሾማል። ሕዝብ ሲበድል፣ ሕዝብ ሲያምፅ፣ እግዚአብሔርነቱን ሲረሳ፣ አልታዘዝም ባይነት ሲገን፤ የሚገርፍበትን፥ ጨንገሩን፣ አለጋውን፣ ጅራፉን፣ እሾሁን ይሾማል። በሌላ መልኩ ደግሞ፣ ሕዝብ ሰላማዊ ሲኾን፣ በአምልኮቱ ሲጸና፣ ፍቅርና መከባበር ሲኖረው ደግሞ የሚያከብረውን፣ የሚያለማለትን፣ የሚቆረቆርለትን፣ አለሁ የሚለውን ይሾማል።


በእኔ እምነት እስከ አሁን ድረስ፣ ከበዓለ ሢመትዎ ጀምሮ በሚያስተላልፏቸው ወርቃማ ቃላት፣ ኅብረ ቀለማትን የተላበሱ፣ ሰንሰለት በሰንሰለት ተሳስረው እንደ ሐረግ እየተመዘዙ በሚወርዱ ውብ ዐረፍተ ነገሮች፤ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ አድርገው እጅግ ደስ በሚያሰኝ መልኩ እናትነትን የመሳሰሉትን ዝርዝር ሳልገባ ሲገልጹ ሰንብተዋል። በእኒህ የአጭር ጊዜ የሹመት ሳምንታትም፣ ዳር እስከ ዳር፣ ካህን ነኝና “ወጥን ማን ያውቃል ቢሉ ቀለዋጭ” እንዲሉ እንደ ካህንነቴ ብዙ ስለምሰማ፣ ተደናቂነትን አትርፈዋል። በዚህ እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን።


ክቡርነትዎን ግን አደራ የምለው፣ መናገር ቀላል ነው፤ ማድረግ ግን ከባድ ነው። ማውራት ይቻላል፤ በአንድ ቀን ሀገርን መገንባት፣ ማልማት ይቻላል - በወሬ ደረጃ፤ መሥራት ግን ፈታኝ ነው። ፈታኝ የሚያደርገው፣ ውስብስብ እየኾነ በተለያየ መልኩ የሚቀርበው ጣጣ ነው። ስለዚህ ከተለያየ አቅጣጫ የሚቀርበው ውስብስብ ነገር፣ የተናሯቸውን ኢትዮጵያዊነትን፣ አንድነትን፣ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ የጋራነትን፤ አሁንኮ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ትልቁ ችግር፣ እኔነት የሚል ራስ ወዳድነት ሠልጥኖ እኮ ነው። ለእኔ ከሚል ይልቅ ለወንድሜ፣ ለእኅቴ፣ ለጎረቤቴ፣ ለሀገሬ፣ ለወገኔ የሚለው ስሜትኮ በእያንዳንዳችን ቢሠርጽ ሌላ ችግር አይኖርም፤ ነገር ግን በእያንዳንዱ አእምሮ የሠረጸው የእኔነት ጠባይዕ ነው፤ ራስ ወዳድነት ነው። እንደ እንስሳዊ አባባል፣ “እኔ ከሞትኩ ሠርዶ አይብቀል”  የሚል አስተሳሰብ በመፈጠሩ ነው።


ስለዚህ፣ ይህን ችግር ለመናድ፣ ይህን ችግር ለማስወገድ በተዋቡ ዐረፍተ ነገሮች የሚያስተላልፏቸው ቃላት እንደው ዘወትር እንደ መስተዋት ልበል፣ እንደ ግል ማስታወሻ ከፊትዎ ሰቅለው፥ ምን ተናግሬ ነበረ፤ የቱን ሠራሁት፤ የትኛው ይቀረኛል የሚል የዘወትር ተግባር እንዲኖርዎ፣ በቤተ ክርስቲያን ስም በታላቅ ትሕትና እገልጽልዎታለሁ። ምክንያቱም ይህን ዕድል ያገኘሁት ዛሬ ስለኾነ፣ ነገ ብቻዎን ስለማላገኘዎት አሁኑኑ ልናገር ብዬ ነው።


ብዙ ታሪክ አሳልፈናል። ስለኢትዮጵያዊነት መቼም፣ አሰብ ስለነበርኩ በአካል የማውቃቸው የአፋሩ ታላቅ አዛውንት መሪ የነበሩት በአንድ ወቅት እንደተናገሩት፣ “ኢትዮጵያን እንኳን እኛ ግመሎቻችን ያውቋታል[ከነባንዴራዋ]” ነው ያሉት አይደል። ግመሎች ያውቋታል፤ ነው ያሉት፤ አስታውሳለሁ። አሁን ግን ኢትዮጵያን የማያውቅ ትውልድ እየተፈጠረ ነው። ክቡርነትዎ ተደናቂነትን እያተረፉ ያሉት፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚገልጹባቸው ቋንቋዎች፣ እጅግ የተዋቡ በመኾናቸው ነው።


ሰሞኑን ኢየሩሳሌም ነበርኩ፣ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ። ከተለያየ አቅጣጫ ያልመጣ አልነበረም፤ ብዙ ሰው የሚያወራው ግን ትልቅ የምሥራች ነው፤ “እግዚአብሔር በርግጥም ይህችን ሀገር ከጥፋት ሊታደጋት ይኾን?” የሚል ጥያቄ ነው ያለው። አዎ፣ ያንዣበበው ፈተና፣ የደፈረሰውና የታጣው ሰላም አስጊ ነበር። ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም በቅዱስ ፓትርያርኩ መልእክት አስተላላፊነት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ ጮኻለች ወደ እግዚአብሔር። የሰላም አምላክ ሆይ፣ ሰላምህን ስጣት፤ አንድነትን ስጥ ለልጆችህ፤ እያለች። ቤተ ክርስቲያን ወሰን ስለሌላት፤ ቤተ ክርስቲያን ሁሉም ልጆቿ ስለኾኑ፣ ከልጆቿ አንዱም ማንም ማን እንዳይጎዳ ስለምትፈልግ፣ እግዚአብሔር ሆይ፣ ለሀገራችን ሰላምን ስጣት፤ እያለች ጸሎቷን ድምፅዋን ከፍ አድርጋ አሰምታለች። ወደፊትም ታሰማለች።


ስለዚህ ክቡርነትዎ፣ ይኼን የጎጣጎጡን ጉዳይ፣ የዚያ ማዶ የዚህ ማዶ የመባባሉን ጉዳይ ወደ ጎን ይተዉትና አልጀመሩትም፤ ይጀምሩታልም ብዬ አላስብም፤ ትውልዱ አንድ የሚኾንበትን ጉዳይ፣ ላለመደፈር፤ አባቶቻችንኮ ያልተደፈሩት አንድ ስለኾኑ ነው። ልዩነት ስለሌላቸው ነው፤ ከዚህ ቀደምም ተናግሬዋለሁ፤ በላይ በበራሪ በምድር በተሽከርካሪ የመጣውንኮ በኋላ ቀር መሣሪያ ያሸነፉትና ያንበረከኩት፣ በየትኛውም ዓለም ብንሔድ፣ ኢትዮጵያዊ አትዮጵያዊ ነኝ ብሎ በሙሉ ወኔ በየትኛውም ቦታ ገብቶ የመናገር፣ የመቀመጥ ዕድሉን ያገኙት በአንድነታቸው ነው። የእገሌ ወእገሌ መባባል ስለሌለባቸው።


አሁን ግን ወዳጆቻችን በሰጡን የቤት ሥራ፣ እዚሁ ተቀምጠን እንኳ በአሁን ሰዓት የእገሌ የቤት ሥራ፣ የእገሌ፣ የእገሌ እየተባባልን ነው። መቼ ነው ከዚህ ሸክም የምንላቀቀው ወገኖቼ? መቼ ነው ከጎጠኝነት የምንላቀቀው? መቼ ነው፣ በኢትዮጵያዊነት አምነን፣ አንች ትብሽ አንተ ትብስ ተባብለን እግዚአብሔር በሰጠን የነፃነት ምድር፣ አባቶቻችን የደም ዋጋ በከፈሉባት ምድር፣ አባቶቻችን አጥንታቸውን በከሠከሱባት ምድር፣ አባቶቻችን ዕንቁ የኾነውን ታሪካቸውን ለእኛ አሻራ አድርገው ትተውባት በሔዱት ምድር በእፎይታ የማንኖረው እስከ መቼ ነው? የአንድ እናት ልጆች፣ የአንዲት ሀገር ልጆች የጠላት መሣሪያዎች ኹነን፣ በጎጥና በድንበር ተከላለን ዐይንህ ላፈር የምንባባለው እስከ መቼ ነው? ስለዚህ በክቡርነትዎ ዘመን ይኼ እንዲበቃ ምኞቴም ነው፤ ጸሎቴም ነው። የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይኹንልን እላለሁ።


ሌላው ሳልጠቁም የማላልፈው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ክቡርነትዎ እንደሚያውቁት፣ የታሪክም ሰው እንደመኾንዎ፣ ቅድምም ሲናገሩ ዐይናማ የኾኑትን አራት ዐይናማ ሊቃውንት፣ ከየአቅጣጫው ኢትዮጵያዊነትን የሚገልጹትን በሙሉ እየጠቃቀሱ እንዳስረዱን ሁሉ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ትልቅ ባለውለታ፣ አንጋፋ እናት ቤተ ክርስቲያን ነች። ይኼ የማይካድ ሐቅ ነው። ርግጠኛ ነኝ፣ ሼኹም ይመስክሩ ሌላውም ይመስክር፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ እገሌ ወእገሌ ሳትል ሁሉንም በየእምነቱ ፊደል ያስቆጠረች፣ ያስነበበች፤ ለሀገር መሪነት ያበቃች አንጋፋ እናት ቤተ ክርስቲያን ነች። የእኔ ስለኾነች አይደለም የምመሰክረው። ስለዚህ ቢያንስ የእምነቱ ተከታዮች አይኾኑ፤ እናከብራቸዋለን፤ እንዲያከብሩን እንፈልጋለን። ግን ለባለውለታ፣ ሀገርን ዛሬም በሰንሰለቶቿ አስራ የኢትዮጵያን ታሪክ ለማሳየት የምትጥረዋን እናት ቤተ ክርስቲያን፣ ትውልዱ ማክበር ለምን ተሳነው? በሃይማኖት እኩልነት፣ በሃይማኖት ነፃነት እንርገጥሽ እየተባለች ያለችበት ዘመን ቢኖር ግን ዛሬ ነው።


ቤተ ክርስቲያንኮ ባለአደራ ናት። ክቡርነትዎ ጊዜ ቢኖርዎት፣ ክቡር ፕሬዝዳንት ጊዜ ኖሯቸው ቢያስጎበኙልኝ እስኪ እነዳጋ እስጢፋኖስን ይጎብኟቸው፤ የነገሥታቱን የእነዐፄ ሱስንዮስን የእነዐፄ ዳዊትን የእነዐፄ ፋሲለደስን የእነዐፄ ዘርዐ ያዕቆብን አዕፅምት ይዛ የምትገኝ፣ ባለአደራ ጥንታዊት እናት ቤተ ክርስቲያን ናት። ዛሬ ዛሬ በምሥራቁ ስንሔድ፣ በደቡቡ ስንሔድ፤ እዚህ አካባቢ ያው ጎላ በርከት ብሎ የኦርቶዶክሱ ተከታይ ስላለ ተቻችለን እንኖራለን፤ ወደ ሌላው ስንሔድ ግን ጣጣው እየበዛባት ነው ቤተ ክርስቲያን፤ ፈተናው እየከበዳት ነው ቤተ ክርስቲያን፤ መጀመሪያዎች ኋለኞች፣ ኋለኞች ፊተኞች ይኾናሉ፤ የተባለው ቃል እየተፈጸመባት ነው።


በሥልጣን ክፍፍልም ኾነ በአካባቢው ያሉ ሥልጣን ላይ ይቀመጣሉ፣ የመንግሥት ሓላፊነታቸውን ትተው፣ የተሰጣቸውን አደራ ረስተውና ረግጠው፣ ራሳቸውን የሃይማኖት መሪ እያደረጉ ይህችን እናት አንጋፋ ቤተ ክርስቲያን በዋለችበት እንዳታድር፤ ባደረችበት እንዳትውል እንደ ጥንቱ እንደ ሮማውያን ዘመን እየኾነ ያለበትም ቦታ አለና እባክዎ ክቡርነትዎ በአስተዳደር ዘመንዎ፡- እኩልነት፣ ሰላም፣ አንድነት፣ መቻቻል ሰፍኖ፤ ይኼ በቃል፣ በቋንቋ የምንናገረው ሳይኾን ተግባራዊ በኾነ መልኩ አንተን አልይህ፣ አንተን አልይህ መባባል ቀርቶ እምነትም ከኾነ በትምህርት ላይ የተመሠረተ እንጅ በሰይፍና በጥቅምጥቅም፣ በዱላና በአባርርሃለሁ ባይነት ያልተመሠረተ፣ ሰላማዊ የኾነ ነገር እንዲሰፋ እንዲሰፍን አደራ እልዎታለሁ።

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ


ከዚህ በተረፈ፣ ዘመንዎ ሁሉ፣ አጀማመርዎ ጥሩ ነው፤ አካሔዱን አይቶ ስንቁን ይቀሙታል፤ ይላሉ አባቶቻችን፤ በዚህ አካሔድዎ፣ እጅግ ደስ የሚልና በእያንዳንዱ አእምሮ ተቀባይነትን እያገኙ እንደሚቀጥሉ።


አባቶቻችን የሚሉት አንድ ነገር አለ፤ ስምን ፈረሰኛ አይቀድመውምና ልጄ ተጠንቀቅ፤ ይላሉ፤ እንደ ዛሬ አየር አይቀድመውም፤ እንደ ጥንቱ ግን ፈረሰኛ አይቀድመውም፤ አንድ ስም አንድ ጊዜ በክፉ ከወጣ አለቀ፤ አንድ ስም አንድ ጊዜ በበጎ ከወጣ ደግሞ አለቀ፤ ስለዚህ በበጎ ጀምረውታል፤ በበጎ እንዲደመድሙት፤ የእርስዎና የእርስዎ የቤት ሥራ ኹኖ እግዚአብሔር ከእርስዎ ጋራ ኹኖ፣ የትላንትናዋ ምልዕት ኢትዮጵያ፣ ቅድስት ኢትዮጵያ፣ አንድነት የሰፈነባት፣ መለያየት የሌለባት፣ ሁሉም በሔደበት ቤት ለእንግዳ ተብሎ የሚያልፍባት፤ አንተ እገሌ ነህ፣ አንተ እገሌ ነህ የማይባባልባት አገር ትኾን ዘንድ እግዚአብሔርን በመለመን፣ አማካሪዎችዎንም በማማከር፣ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ምክረ ኵይሲ እንለዋለን…ይኼ አላስፈላጊ ምክር የሚመክሩ እንደ ምክረ አሦር አሉ፤ ስለዚህ በጎ በጎውን ምክር የሚመክርዎትን፣ በጎ በጎ ሐሳብ የሚያመጡልዎትን ተከትለው እስከመሩ ድረስ፣ አዎ ርግጠኛ ነኝ፤ የተናገሩላት፣ እጅግ ውብ በኾነ ዐረፍተ ነገር የመሰከሩላት ኢትዮጵያ፣ ከቃል ወደ ተግባር ተለውጣ፣ ሺሕ ዓመት ያንግሥዎት እንድንል እንገደዳለን ማለት ነው፤ እንደ ጥንቱ። እግዚአብሔር ይስጥልን፤ እግዚአብሔር ይባርክልን።


ከዚህ በተረፈ፣ በመጨረሻ መቸም አንዳንድ ጊዜ የእኛ ልማድ፣ ከይቅርታ ጋራ ነው የምናገረው፣ አዲስ ባለሥልጣን መጣ ሲባል፣ እንግዳ መጣ ሲባል፣ ስሜታችንን መናገር የተለመደ ጠባያችን ስለኾነ ይቅርታ እየጠየቅሁኝ፣ እንደ እኛ እንደ እኛ እንደ ባሕር ዳር፣ ያለአድልዎ፣ በሚገባ፣ እኔም በማውቀው እኔም አንድ ጠያቂና ተመላላሽ ስለኾንኩ፣ የሚያስተናግዱንን ክቡር ከንቲባችንንም ኾነ ክቡር ፕሬዝዳንቱን፣ አጠቃላይ መሥሪያ ቤቱን ሳላመሰግን ባልፍ ኅሊናዬ ስለሚወቅሰኝ እግዚአብሔር ያክብርልኝ፤ እላለሁ፤ በጣም አመሰግናለሁ።
ምንጭ፡- ሀራ ተዋህዶ¾

ጌታቸው አስፋው

 

(የብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕቅድ ባለሙያ)

 

በገበያ የቀረበው የገንዘብ መጠን በገበያ ዋጋ ካልተለካው ምርት ጋር ሊመጣጠን ባለመቻሉ በዋጋ ግሽበት የሰደድ እሳት ተቃጠልን፣ በሸቀጥ ዋጋ ጭቅጭቅና ንትርክ ውስጥ ገባን፣ ዋጋዎች በቀናትና በሳምንታት ተለዋወጡብን። ገቢ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ቢሆንም የገቢ ዕድገት ከምርታማነት ዕድገት በላይ ስለሆነ ገንዘቡ ዋጋ አጣ። ግልጽ ሥራ አጥነት በስውር ሥራ አጥነት ተተክቶ ምርታማነትን ቀነሰ። በጥቃቅን የተደራጁት ወጣቶች በሙሉ አቅማቸው ሳይሰሩ በነርሱ ላይ ሌሎች ማደራጀት የቀድሞዎቹንም አዲሶቹንም በሙሉ አቅማቸው ሠርተው ምርታማ እንዳይሆኑ አደረጋቸው።


ሥራ ፈጠራ በብሎኬት ምርት፣ መስኮትና በር መግጠም፣ አልባሳት፣ ቦርሳና ቀበቶን የመሳሰሉ የግል መጠቀሚያዎችን ማምረት ጀምሮ አሁን ወደ ጀበና ቡና፣ ቦርዴ (ሻሜታ) ጠመቃ፣ የዐረብ ሱቅ፣ በቆርቆሮ ግድግዳ ደሳሳ ጎጆ የሆቴል ኪዎስክ ወርዷል። ከዚህ በታች ወዴት እንደሚወርድ አይታወቅም። በየመንገድ ዳሩ ጠላ ጠምቆ መሸጥ ይሆናል። አምርቶ ገንዘብ ማግኘት ካልተቻለ አጭበርብሮም ቀምቶም ሰርቆም የሰው አካልን ደልሎም ገንዘብ ለማግኘት ይሞከራል። በውድድር ሳይሆን በሽሚያ ገንዘብ ለማግኘት ለመክበር መስገብገብ መሻማት መሻሻጥ መታወቂያችን ሆኗል። በሦስት ሺሕ ብር ሥራ ጀምሮ በዓመቱ ሦስት ሚልዮን ብር ካፒታል ማስመዝገብ፣ መቶ ሺሕ ብር ለደላላ ከፍሎ ወደሞት ለመሄድ መደራደር፣ ለደቂቃዎች መዝናኛ በሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ ማውጣት፣ ቅጥ ላጣ የውጭ አገር ጉዞ የቅንጦት ወጪ ማድረግ፣ ጥሬ ገንዘብ ከጓሮ የሚሸመጠጥ ቅጠል አስመስሏል። በየቴሌቪዥኑ መዝናኛ ፕሮግራም አቅራቢዎች ለእንግዶቻቸው የሃያ ሺሕ ብር ሐምሳ ሺሕ ብር የቀን ውሎ ጉርሻ ሲሰጡ ታይቷል። በ1960ዎቹ ቦሌ አስፋልት ዳር የነበረ ዘመናዊ ቪላ ቤት በአምስት ሺሕ ብር ይሸጥ እንደነበር የሚያውቅ ሰው ይኽን ሁሉ ጉድ ሲያይ ምን ይል ይሆን?


አምና በመቶ ብር መነሻ ካፒታል የከተማ ሥራ ጀምሬ ዘንድሮ ሦስት ሚልዮን ብር ካፒታል አለኝ፣ በግማሽ ሔክታር መሬት የግብርና ሥራ ዐሥር ሚልዮን ብር ካፒታል አለኝ፣ የሬድዮና የቴሌቪዥን ፕሮፓጋንዳ የወጣቱን ሥነ ልቦና ሰለበ፤ የሥራ ባህል ጠፋ፤ ገንዘብ ተሠርቶ የሚገኝ ሳይሆን ከሜዳ የሚታፈስ፣ ጓሮ ከበቀለ ዛፍ የሚሸመጠጥ መሰለ፤ መቶ ሺሕ በትኖ ሚልዮን ለማፈስ የተሰናዳ ትውልድ ተፈጠረ፤ ከሠርቶ በሌው አውርቶ በሌውና ዘሎ በሌው በዛ፣ የዩኒቨርሲቲ ትምህርትን አቋርጦ ጊታር ማንሳት ተለመደ።


ግማሽ ያህሉን ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት በያዘው የአገልግሎት ምርት መሰማራት የሕዝቡን ገቢ ከምርታማነቱ በላይ በፍጥነት አሳደገ፣ ሎሚና እምቧይ ተቀላቅለው እየተቆጠሩ የአገር ውስጥ ምርት አብጦ ያደገ መሰለ። በአንዳንድ ሥራዎች ምርታማነት ሊጨምር ቢችልም በአገር ደረጃ ግን ምርታማነት ከመጨመር ይልቅ እየቀነሰ መጥቷል። የተናጠል ምርታማነት የአገር ምርታማነት ሊሆን አልቻለም።


በጤናውና በትምህርቱ ዘርፍ የሕዝቡን ምርታማነት ሊጨምሩ የሚችሉ ለውጦችና መሻሻያዎች ቢታዩም ሰውን ማልማት ባለዲግሪ መቁጠር መስሎን ቁጥር አምላኪዎች ሆነናል፣ በዚህም ላይ የምናፈራቸው ወጣቶች ፌርማታ ለባዕድ አገር ሎሌነት ሥራ መሆኑ ከቀጠለ አገራዊ ምርታማነት ሊያድግ አይችልም። በመሠረተልማት እና በሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ባለፉት ዓመታት የተሠሩት ስራዎች የህዝቡ የተጠቃሚነት ደረጃ እንደ የሀብት መደቡ፣ የሚኖርበት አካባቢ፣ የዕድሜው ክልል፣ ቢለያይም በጥቅሉ ለሁሉም ሰው ለኢኮኖሚ ዕድገትም ለልማትም ስለሚጠቅም መልካም ነው። በዚህ ምንም ተቃውሞና ትችት የለኝም።


ሆኖም ለግለሰብ ሊሸጥ የሚችልና በግለሰብ ሊለማና የገበያ ዋጋ ሊኖረውም ይገባ የነበረን የገበያ ሸቀጥ የጋራ ልማት ሥራ አድርጎ በመንግሥት እጅ አፍኖ ይዞ የገበያ ዋጋ እንዳይኖረው ማድረግ፣ ምርቱን ትክክለኛ ዋጋ እንዳሳጣው ሳልገልጽ ግን አላልፍም።


የጋራ በሆነ መሬት ላይ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ መሥራት የሚቻለው በጋራ ብቻ ነው። የጋራ የሆነም የግል አይደለም፤ የግል ያልሆነም ገበያ አይወጣም፤ ገበያ ያልወጣም የገበያ ዋጋ የለውም፤ የገበያ ዋጋ የሌለውም፤ በገበያ ዋጋ በገንዘብ አይተመንም። ስለዚህም በሪፖርት ከምናየውና ከሚነገረን ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን ገሚሱ የገበያ ዋጋ የሌለው ምናባዊ ስሌት ነው። የኑሮ መሐንዲሱ የኢኮኖሚ ባለሙያ ኑሮን ወደ ምናባዊ ስሌት ከወሰደው የህዝብ ገቢ መጠንና ኑሮም በገበያ ተለክቶ እውነቱ የሚታወቅ ሳይሆን ምናባዊ ይሆናል። አመለካከቱና አስተሳሰቡም የኑሮው ነጸብራቅ ነውና ኑሮውን ተከትሎ ምናባዊ ይሆናል። ሲያገኝም ሲያወጣም በምናባዊ ስሌት ነው።


ሳይበላ የበላ መስሎ፣ ሳይጠጣ የጠጣ መስሎ፣ ሳይደላው የደላው መስሎ፣ ያላመነውን ያመነ መስሎ፣ ያልተቀበለውን የተቀበለ መስሎ፣ የናቀውን ያከበረ መስሎ፣ የጠላውን የወደደ መስሎ፣ በመታየት በምናባዊ ዓለም ውስጥ ይኖራል። ከኢሕአዴገ አባላት ውስጥ ጥቂቶቹ የጥቅም ተካፋይ ሲሆኑ አብዛኞቹ ግን በዚህ ምናባዊ ቀፎ ውስጥ እንደ ንብ የሰፈሩ ናቸው። ሕዝቡም በምናባዊ ዓለም ውስጥ የሚኖር ነው፣ የምክር ቤት ምርጫ ሊያደርጉ የወጡ ሰዎች በነጠላ ተሸፋፍነው የሆነ ያልሆነውን በትዝብት ተከታትለው የአስመራጮቹ ዓይን አስፈርቷቸው፣ ኢሕአዴግን መርጠው ቤታቸው ሲገቡ፣ የሚያውቋቸውን ታቦቶች ሁሉ እየጠሩ ኢሕአዴግን ንቀልልኝ ብለው የእርግማን መዓት ያወርዳሉ።


ከመቶ ሚልዮን ሕዝብ ውስጥ ሁለት መቶ ሺሕ ሰው ሕንጻ ቢገነባ ከመቶ ሚልዮን ውስጥ ሦስት መቶ ሺሕ ሰው መኪና ቢገዛ አገር አደገች ማለት አይደለም። ብሔራዊ ሀብት በጥቂቶች በግል ይዞታ እየተሰረቀም ብሔራዊ ሀብት ሊሆን አልቻለም ተቆንጥሮ ተቆንጥሮ አልቋል፤ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ስሜትም ይሰረቃል። የኢትዮጵያውያን አገራዊ ስሜት ተሠርቆ አልቋል። ከገንዘብ ስርቆቱም በላይ ይኽ ስርቆት አገር እያጠፋ ነው።


ሕዝቡ ከምናባዊ ዓለም ወጥቶ ገሃዱን ዓለም እንዲቀላቀል የኢኮኖሚ ባለሟል አለ ብሎ በወረቀት ላይ የሚጽፈውን ምርት ለሽያጭ ወደ ገበያ አውጥቶ፣ በገበያ ዋጋ አስተምኖ፣ እውነተኛውን በገበያ ዋጋ የተለካ የምርት መጠን አሳይቶ አለ ያለው መኖሩን ሊያረጋግጥ ይገባዋል። ገብረማርያምን የኃይለማርያምን አይተህ ተጽናና ማለት አይቻልም። አንጀት ላይ ጠብ የሚለው ሺዎች ለሚልዮኖች አስበው ሲሰሩ ሳይሆን ሚልዮኖች ለራሳቸው አስበው በገበያ ውስጥ ተወዳድረው እንዲሠሩ በተሟላ የመንግስት ቁጥጥር ድጋፍና አመራር የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች ሲመቻቹላቸው ነው። “ጧት ጧት ደቧችንን ጠረጴዛችን ላይ የምናገኘው በዳቦ ጋጋሪው ጽድቅ ሥራ ሳይሆን ለራሱ ገንዘብ ለማግኘት ሲል በሚሠራው ሥራ ነው፤” ሲል የነጻ ገበያ ኢኮኖሚን ስውር እጅ አሠራር አዳም ስሚዝ አረጋግጧል። ከርሱ በኋላም ሌሎች ኢኮኖሚስቶች የብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አመራር የገበያውን ጉድለት እንዴት እንደሚቀርፍ አመልክተዋል። “ልማት ማለት አንድ ሰው ሊሆንና ሊያደርግ የሚፈልገውን ሕጋዊ ነገሮች የመሆንና የማድረግ ነጻነትና አቅም ሲያገኝ ነው፤” ሲሉ በ1998 በልማት ኢኮኖሚክስ የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት አማርተያ ሴን ነግረውናል።


ይኽን አይቶ መንግሥት የኢኮኖሚ ፖሊሲውን እንደገና ካልመረመረ የኢኮኖሚ አማካሪዎቹን ችሎታ ካልተጠራጠረ፣ የወረቀት ላይ ቁጥርን ብቻ ሳይሆን ገበያዎችን ተንትናችሁ ተርጉሙልኝ ካላላቸው ተያይዘን ገደል መግባታችን ነው። በፖለቲካው የተፈለገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዓይነት ማዕከላዊ ዕቅድን እና ነጻ ገበያውን ማቀላቀል ቢሆንም የቅልቅሉን ዓይነት በብልሃት መምረጥ፣ ምናባዊ ዕቅድና ክንውኑን ብቻ ሳይሆን በገሃድ በዓይን የሚታየውን የገበያውን ሁኔታ መከታተል፣ ተነጣጥለው ለየራስ እየሄዱ ያሉትን ማዕከላዊ እቅድና ገበያውን ማቀናጀት ያስፈልጋል።


የገበያውን ምልክትና ቋንቋ ያልተረዱ፣ ይኽ ከዚያ ይበልጣል ያ ከዚህ ያንሳል እያሉ ምናባዊ ቁጥር ገጣጥመው ማማለል የለመዱ፣ በምናባቸው አቅደው በምናባቸው የፈፀሙትን ማነጻጸር ብቻ የሚችሉ፣ ወደ ገበያ ወረድ ብለው ተጨባጭ ሁኔታን ያላዩ ቁጥር አምላኪ የኢኮኖሚ አማካሪዎች ገበያው በሽሚያ እርሾ እየቦካ መሆኑን ማየት ተስኗቸዋል። ሙያቸው ሰው እያስራበ፣ አያስኮበለለና እያስገደለ እንደሆነ አልተሰማቸውም፤ ልባቸው ደንድኗል።


በምርጫ 2002 ፋሲካ ሰሞን አርባ ብር የነበረ የዶሮ ዋጋ በምርጫ 2007 ፋሲካ ሰሞን አራት መቶ ብር ከገባ በምርጫ 2012 ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል፣ በምርጫ 2007 ሚልዮኖች ከተሰደዱ በምርጫ 2012 ምን ያህል ሊሰደዱ እንደሚችሉ መገመት ያስቸግራል። ያሰቃየን ካይዘንን፣ ውጤት ተኮርን፣ ቢ.ፒ.አርን፣ ቢ.ኤስ.ሲ.ን አለማወቅ አይደለም፣ ያሰቃየን ደላላው አይደለም። ነጋዴውም አይደለም። ያሰቃየን የእነኚህ ሁሉ ገዢ ቃል የሆነው ገበያው ነው። እኛው ከውድድር ወደ ሽሚያ የለወጥነው ገበያው ነው።


የበላን የበረሀ አሸዋ አይደለም፣ ባህርም አይደለም፣ ያረደንም ሰው አይደለም። የበላን ያረደን፣ ለስደት፣ ለስቃይ፣ ለሞት፣ ለዋይታ፣ የዳረገን ገበያው ነው። ሰው አገር ሞልቶና ተርፎ እኛ አገር የጠበበውና የተኮማተረው መኮማተሩንም ራሱን ሳይደብቅ የሚነግረን በመንግስት አስተዳደር ሳጥን ውስጥ ታስሮ ያለው የሥራና የእንጀራ ገበያ ነው። በአዋጅና በሕግ ስለተደነገገው ገበያ እንደ ካይዘኑ፣ እንደ ውጤት ተኮሩ፣ እንደ ‹ቢ.ፒ. አሩ›፣ እንደ ‹በ.ኤስ.ሲው› ልናውቅ ልናጠና ባለመፈለጋችን በኑሮ ተቀጣን እየተቀጣንም ነው። ገበያው ሰማይ ይሰቅለናል፤ መቀመቅ ያወርደናል፤ ገበያው ያሰድደናል፤ ያስገድለናል፤ ጥቂቶችንም ገበያው ያንቀባርራል፤ ያንደላቅቃል፤ ያመጻድቃል።


የሚጻፉትን ቁጥሮች እና የገበያውን ምልክት በማያገናዝቡ፣ የኛን የምርትና የሸመታ ምርጫ ሥነልቦና በማያውቁ፣ እኛ በገበያዎቻችን ውስጥ ልናገኛቸው የምንፈልጋቸውን የሸቀጦች ዓይነት በማይረዱ ባዕዳን አማካሪዎች እገዛ ምክርና ትዕዛዝ ገበያውን ማየትና የገበያውን ቋንቋ መስማት በተሳናቸው የአገር ውስጥ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ጓዳ ውስጥ በማዕከል ታቅዶ የሚተገበር ፖሊሲ ጎደሎ ነው። የውጭውን አገር ጽንሰ-ሐሳብና ልምድ ብቻ ይዞ ምድሩ ሳይታወቅ ሰማይ መቧጠጥ ነው። በሰው አገር ዕድገት ሞዴል ጉጉት ናፍቆትና ምኞት ራስን መደለል የልማትን ትርጉም ሳያውቁ ልማታዊ ነኝ ማለት የሕዝብ ሕይወትና ኑሮን የሙከራ ጊዜ ማድረግ ነው። ለአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታና ለህዝቡ ሥነልቦና በቂ ትኩረት አለመስጠት ነው።


ቁጥር ብቻ እየታየ የሸማቹን አቅም ለመገንባት የሚረጨው የጥሬ ገንዘብ መጠን ወደኋላ ተኩሶ ዋጋን በማናር ጀርባችንን አቁስሎታል። የአምራቹን አቅም ለማሳደግ ለጥቂቶች የሚሰጥ ያዝ ለቀቅ ድጋፍ ግብታዊ እርምጃም ነቀዝ ፈልፍሏል። ከቁጥር ቁማር ወጥተን ከፈጠርነው አርተፊሻል የሽሚያ ገበያ ተላቀን የገበያ ኢኮኖሚውን እና የልማት ኢኮኖሚውን ካላመጣጠን ላንነሳ ተሰናክለን እስከምንወድቅ ኑሯችን የአቦ ሰጥ እንደሆነ ይቀጥላል። በአቦ ሰጥ ይገኛል በአቦ ሰጥ ይታጣል።


የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ አወቃቀርና አካሄድ በውስጣዊ ኃይላት እቅስቃሴ የሚመራ ሥርዓት ነው። ላለመሰቃየት፣ ላለመሰደድ ላለመሞት ላለማልቀስ በአቦሰጥ ላለመኖር ከሽሚያ ገበያና ኑሯችንን ቤተሙከራ ከማድረግ ወጥተን ትክክለኛውን የነጻ ገበያ ሥርዓት መዘርጋትና የሥርዓቱን ውስጣዊ ኃይላት እንቅስቃሴ ማወቅና መጠቀም ያስፈልጋል።

 

በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ሦስት እጥፍ ያደገ ኢኮኖሚ


ከላይ በእንቆቅልሽ መልክ በተመለከተው የአገር ውስጥ ጥቅል ምርት ዕድገት የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ በማሻሻል ረገድ ፋይዳ ቢስ መሆኑን በገበያ መገለጫ ያረጋገጥን ቢሆንም በስታቲስቲካዊ መረጃውም የተሳሳተ እንደሆነ ማረጋገጥ ይቻላል። ብዙ ኢትዮጵያውን ስለ ኢኮኖሚው የመንግስትን መረጃ ፈጽሞ እንዳያምኑ ካደረጋቸው ምክንያቶች አንዱና ዋናው የጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ዕድገት ተብሎ የሚጠራው ነው። ገበያ ውስጥ ምርት ጠፍቶ ዋጋው በየጊዜው ከሚገባው በላይ ወደላይ እየተሰቀለ ምርቱና አቅርቦቱ በየዓመቱ በዐሥራ አንድ በመቶ አደገ ሲሉ ሕዝቡ ታዲያ እንዴት ይመናቸው?


ይኽ በፍጥነት አደገ የሚባል ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን የሕዝቡን ዓመታዊ ነፍስ ወከፍ ገቢን ከልክ በላይ አሳድጎ፣ በድህነት ቅነሳ መለኪያ አመልካች የሕዝቡ ኑሮ ደረጃ የተለወጠ በማስመሰል ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው ሆኖበታል። ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት በዓመት በአገር ውስጥ በሚኖሩ ሰዎች በገበሬው፣ በወዛደሩ፣ በፀጥታ አስከባሪው፣ በመከላከያ ሠራዊት አባሉ፣ በዳኛው፣ በጋዜጠኛው፣ በመምህሩ፣ በሐኪሙ፣ በቢሮ ሠራተኞች፣ በነጋዴው፣ በሙዚቀኛው፣ በፀጉር አስተካካዩ፣ በቤት ሠራተኛው፣ በሾፌሩ፣ በዘበኛው በጫማ አሳማሪው በዳንስ አስተማሪው በጭፈራ ቤት ሥርዓት አስከባሪው ወዘተ. ተመርቶ በሸቀጥ መልክ ለገበያ የቀረበ ወይም ለገበያ እንደቀረበ ተቆጥሮ ዋጋው የተተመነ ቁሳዊ ዕቃና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ነው።


ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት በገንዘብ ዋጋ በኹለት መልክ ይለካል። አንዱ ምርቱ በተመረተበት ዓመት የገበያ ዋጋ መለካት ሲሆን፣ ኹለተኛው የዋጋ ንረትን በምርቱ ልኬት ውስጥ ላለማስገባት በአንድ በተመረጠ ዓመት ቋሚ ዋጋ አማካኝነት የተከታታይ በርካታ ዓመታት ምርት መጠንን መለካት ነው። ምርቱ በተመረተበት ዓመት የገበያ ዋጋ የተለካ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን የየዓመቱን የዋጋ ንረቶች ስለሚጨምር እርግጠኛው የምርት መጠን አይደለም የዋጋ ንረቱ አሳብጦታል። ይኽ በዋጋ ንረት ያበጠ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ምስለ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት (Nominal GDP) ይባላል።


በሌላ በኩል እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት (Real GDP) በተመረጠ ዓመት ቋሚ የገበያ ዋጋ የተለካ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን ሲሆን በየዓመቱ የሚከሰተውን የዋጋ ንረት ስለማይጨምር በዋጋ ንረት ሳይበከል የተተመነ ምርት መጠን ነው። አንድ ገበሬ አምና ስምንት ኩንታል ስንዴ አምርቶ እያንዳንዱን ኩንታል በአንድ ሺሕ ብር ቢሸጥ የስምንት ሺሕ ብር ምርት አመረተ ማለት ነው። ዘንድሮ ዐሥር ኩንታል ምርት አምርቶ እያንዳንዱን ኩንታል በሺሕ ኹለት መቶ ብር ቢሸጥ የዐሥራ ሁለት ሺሕ ብር ምርት አመረተ ይባላል።


የአምናው ኩንታል ምርት በአንድ ሺሕ ብር ዋጋ ተለክቶ የዘንድሮው ኩንታል ምርት በሺሕ ሁለት መቶ ብር ዋጋ መለካቱ የዘንድሮውን ምርት የዋጋው ንረት አሳብጦታል።


የአምናው ስምንት ኩንታል ምርትና የዘንድሮው ዐሥር ኩንታል ምርት በተመሳሳይ የአምና ቋሚ ዋጋ አንድ ሺሕ ብር ቢለኩ ገበሬው ዘንድሮ ያመረተው ምርት መጠን ዐሥራ ኹለት ሺሕ ብር ሳይሆን ዐሥር ሺሕ ብር ነው። በአምናው ቋሚ ዋጋ የተለካው የዘንድሮ ምርት መጠን በዋጋ ንረት አልተበከለም። እርግጠኛውን የምርት መጠን ለመለካት የአገር ውስጥ ምርት መጠን በአንድ በተወሰነ የቀድሞ ዋጋ መሠረት ይለካል። የቀድሞዎቹን ዓመታት ትተን የቅርብ ጊዜ መረጃዎችን ብቻ ብንወስድ፣ በኢትዮጵያ ከ1992 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2003 ዓ.ም. ድረስ የየዓመቱ እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት በ1992 ዓ.ም. ቋሚ የገበያ ዋጋ ሲለካ ቆይቷል። ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ግን ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን መለኪያ ወደ 2003 ዓ.ም. ቋሚ የገበያ ዋጋ ተከልሷል።


ይኽ የሚሆንበት ምክንያትም ዋጋ ሳይከለስ ለረጅም ጊዜ ቢቆይ ትክክለኛውን የምርት መጠን ስለማይለካ ነው። ስለሆነም ሁሉም አገራት ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ የምርት መለኪያ ዋጋ ዓመታቸውን ይከልሳሉ። ኢትዮጵያ ኬንና ናይጄሪያ መከለሳቸውን ከዚህ ቀደም አይተናል ኢትዮጵያ ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዛሬ ባሉት ዓመታትም እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት እየተለካ ያለው የ1992ቱን ዓ.ም. መለኪያ ዋጋ በ2003 ዓ.ም. ቋሚ የገበያ ዋጋ አማካኝነት በመከለስ ነው። የዚህ እንድምታ ምን እንደሆነ ቀጥለን እንመልከት።


በጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን መለኪያ ቋሚ ዋጋ ከ1992 ወደ 2003 ዓ.ም. መከለስ ምክንያት የ2003 ዓ.ም. እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን ከ1992 እስከ 2003 በነበሩት የየዓመታቱ ዋጋ ንረቶች ተበክሎ አብጧል። ስለሆነም በዋጋ ንረት ተበክሎ በማበጥ አራት መቶ ሰባ ቢልዮን ብር የሆነው የ2003 ዓ.ም. እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን በ1992 ዓ.ም. ቋሚ ዋጋ የተለካውን አንድ መቶ ሐምሳ ስምንት ቢልዮን ብር የ2003 ዓ.ም. እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ሦስት ነጥብ ሦስት እጥፍ ሆኗል። ነፍስ ወከፍ ገቢም ከአንድ ሺሕ ዘጠኝ መቶ አርባ ስድስት ብር ወደ ስድስት ሺሕ ኹለት መቶ ስልሳ ሰባት ብር አብጧል።


የግብርናው የኢንዱስትሪውና የአገልግሎት ዕድገቶችም አብጠዋል። በዚህም መሠረት ስልሳ አምስት ቢልዮን ብር የነበረው የግብርና ምርት ወደ ኹለት መቶ ዐሥራ ሦስት ቢልዮን ብር፣ ሃያ አንድ ቢልዮን ብር የነበረው የኢንዱስትሪ ምርት ወደ ሐምሳ ቢልዮን ብር፣ ሰባ ሦስት ቢልዮን ብር የነበረው የአገልግሎት ምርት ወደ ኹለት መቶ ሰባት ቢልዮን ብር አብጠዋል። የሕዝቡ ኑሮ የአዲሱን ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን ያህል ሦስት እጥፍ አደገ ማለት ነው ወይስ ለቆጠራ ያህል ብቻ የሚያገለግል የወረቀት ላይ ዳማ ጨዋታ ነው? ጥያቄ የሚያጭር ጉዳይ ነው።


የአገር ውስጥ ምርቱ መለኪያ ቋሚ ዋጋ ከ1992 ወደ 2003 በመቀየሩ ምክንያት በወረቀት ላይ በሚጻፉ ቁጥሮች ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ቅጽበታዊ ሦስት እጥፍ ጭማሪ ነፍስ ወከፍ ገቢን ማሳደግና ድህነትን መቀነሰ ይቻላል ማለት ነውን። ይኽ የአገር ውስጥ ጥቅል ምርት መጠን ሳያድግ በዋጋ ንረት አማካኝነት ያደገ መምሰል ብዙ እንድምታዎች አሉት። የአገር ውስጥ ምርት ዕድገቱን መሠረት አድርገው የሚለኩ ሌሎች የሰውና ኢኮኖሚ ልማት መረጃዎች የተዛቡ ይሆናሉ። የዋጋ ንረትም በከፍተኛ ደረጃ የጨመረው ከዚህ ዓመት ጀምሮ ሲሆን መንግሥትም በዋጋ ንረቱ ምክንያት ለመሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች ድጎማ ለማድረግ ስንዴ፣ ዘይትና ስኳር በውጭ መንዛሪ እያስገባ ማከፋፈል የጀመረው በዚሁ ዓመት ነው።


ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ሁሉም አገሮች በተወሰኑ ዓመታት እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን መለኪያ ቋሚ ዓመተ ምሕረቱን ይከልሳሉ። በተባበሩት መንግሥታት የብሔራዊ ኢኮኖሚ ልኬት መርህም ተቀባይነት ያለው አሠራር ነው። ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠኑን ያሳበጠው የቋሚ መለኪያ ዓመቱ መከለሱ በራሱ ሳይሆን ከክለሳው በፊት የነበሩት እጅግ ከፍተኛ የዋጋ ንረቶች በክለሳው ውስጥ በመካተታቸው ነው። የዋጋ ንረት በኹለትና በሶስት በመቶ ብቻ በሚቆጠር መጠነኛ በሆነበት ኢኮኖሚ ውስጥ የመለኪያ ቋሚ ዓመቱ መከለስ ብዙ ለውጥ አያስከትልም። የዋጋ ንረት ከፍተኛ በሆነበት ኢኮኖሚ ውስጥ ግን የመለኪያ ቋሚ ዓመት ክለሳው የአገር ውስጥ ምርት መጠንን ከልክ በላይ ያሳብጠዋል።


በቋሚ መለኪያ ዓ.ም. ክለሳው ምክንያት ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት እና ዓመታዊ ነፍስ ወከፍ ገቢ በወረቀት ላይ በሚታይ ቁጥር ደረጃ ወደ መካከለኛ ኑሮ ደረጃ በፍጥነት እየተጠጉ ነው። ድህነትም በፍጥነት እየቀነሰ ነው። አብዛኛው ሕዝብ ግን በዋጋ ንረት ምክንያት ኑሮው በማዘቅዘቁ ከመካከለኛ ኑሮ ደረጃ እየራቀ እየደኸየም ነው። ወረቀቱ ነው ስለኑሯችን የሚመሰክረው ወይስ የገሃዱ እውነታ ነው? የየዓመቱ ገደብ የለሽ ዋጋ ንረቶች ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጭንቀቶችና ስቃዮች ናቸው። ጥቅል የአገር ውስጥ ምርትን እና ዓመታዊ ነፍስ ወከፍ ገቢን በፍጥነት አሳድገው በፍጥነት መካከለኛ ገቢ ውስጥ ለማስገባት ድህነትንም ለመቀነስ ሩቅ ዓልመው ሩቅ ለማደር ለሚተጉት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ባለሙያዎች በደስታ ጮቤ የሚያስረግጡ ናቸው። የጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን መለኪያ ዓ.ም. በየዐሥር ዓመቱ ስለሚከልሱት በ2013 እንደገና ተከልሶ የምርት መጠኑና ነፍስ ወከፍ ገቢው ሦስት እጥፍ አድገው እንደታለመው በቅርብ ዓመታት ድህነትን ለማጥፋት ወደ መካከለኛ ገቢ መጠን መቃረብም ይቻላል።


በ1980ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት የኢትዮጵያ እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ዐሥር ቢልዮን ብር ገደማ ነበር። የ2003 ዓ.ም. አራት መቶ ስልሳ ዘጠኝ ነጥብ አምስት ቢልዮን ከ1980ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት ዐሥር ቢልዮን ብር አካባቢ ጋር ሲነጻጸር ሐምሳ እጥፍ ግድም እንደሆነ ይታያል። በ2008ም ሰባት መቶ አርባ ሰባት ቢልዮን ብር ስለደረሰ ሰባ እጥፍ ደርሷል። ይኸ ዕድገት በእርግጠኛ የአገር ውስጥ ምርት ስሌት ሲሆን በምስለ የአገር ውስጥ ምርት ስሌትም በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ከሃያ ቢልዮን ብር በታች የነበረው ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ወደ ኹለት ተሪልየን ብር እየተቃረበ ስለሆነ ከመቶ እጥፍ በላይ አድጓል።


እንግሊዝ በኢንዱስትሪ አብዮቷ ዘመን ኢኮኖሚዋን እጥፍ ለማድረግ ስልሳ ዓመታት ፈጅቶባታል። አሜሪካ በ19ኛው ክፍ ለዘመን መጨረሻ ገደማ ኢኮኖሚዋ መመንጠቅ ሲጀምር ኢኮኖሚዋን እጥፍ ለማድረግ ሐምሳ ዓመታት ፈጅቶባታል። በፍጥነት ያደጉት የምሥራቅና ደቡብ ምስራቅ እስያ አገራትም ኢኮኖሚያቸውን እጥፍ ለማድረግ እስከ ዐሥር ዓመታት ፈጅቶባቸዋል። የእኛን አገር ኢኮኖሚ ዕድገት ከነዚህ አገራት እድገት ታሪክ ጋር ስናነጻጽር የኤሊና የጥንቸል ሩጫ ውድድር ይመስላል። እነርሱ ኤሊዎቹ እኛ ጥንቸሏ ነን። ይህ የሚታመን መረጃ ነውን በኢኮኖሚ ጥናት ሳይንስ ሊረጋገጥ ይችላልን።


እንደ የዓለም ባንክ፣ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት፣ ዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ድርጅት፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የመሳሰሉ የዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ሁኔታውን ያውቃሉ ወይስ አያውቁም? አውቀውስ ተቀበሉት ወይስ አልተቀበሉትም? አሳምረው ያውቃሉ። ከማወቅም አልፎ አምነው ተቀብለው መዝግበውታልም። የአገራትን መረጃዎች አጣጥለው በዚህ ሳቢያ በትውውቅና በሹመት የተገኘ ሥራቸውንና ወፍራም ደመወዛቸውን ከሚያጡ አዎን ብለው አጨብጭበው መቀበሉን ይመርጣሉ። ማን ለማን መስዋዕት ይሆናል? የተከበሩት ፈረንጆች የሙስና ተማሪዎች ሳይሆኑ አስተማሪዎች እየሆኑ ነው።


አገራትም አንዱ የሌላውን መረጃ ለማጣጣልና ላለመቀበል ወኔው የላቸውም። ከሶቭየት ኅብረት መውደቅና ከቀዝቃዛው ጦርነት ፍጻሜ በኋላ የመጣ ተቻችሎና ተግባብቶ የመኖር የዓለም ዐቀፍ ድርጅቶችና መንግሥታት ዘይቤ ነው። ይኽ የድርጅቶችና የመንግሥታት መቻቻል የታዳጊ አገራት ሕዝቦች ድህነት ይብቃን የሚያጠግቡን ይምሩን እንዳይሉ አደረጋቸው። መገናኛ ብዙሃን በእጃቸው በሆነ ባለሥልጣናትና የዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ሹማምንት የታዳጊ አገራት ድሃ ድምጻቸው ተቀማ። ከምዕራባውያን ጋር ተስማምተው እስከኖሩ ድረስ ሕዝባቸውን ቢያስርቡም ባያስርቡም ጉዳዬ ነው የሚል ጠፋ። ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶቹ እንደውም ለውጭ ኢንቬስተሮች ሁኔታዎች ይመቻቹ እንጂ የማያውቁትን ለመመስከር መጽሐፍ ቅዱስ ይዘውም ቢሆን ይምላሉ።


ኢትዮጵያ በራሷ እምነትና መንገድ ኢኮኖሚዋን በዚህን ያህል መጠን አሳድጌአለሁ ብላ ብትል፣ ይኽ አለካክ ትክክል አይደለም የሚልና የሚያጣጥለው የትኛው የሕዝብን ጉዳይ ከራሱ ጥቅም የሚያስቀድም ዓለም ዐቀፍ ድርጅት ወይም አገር ነው? በጥቂቱም ቢሆን ወኔው ያላቸውና መጻፍ ካስፈለጋቸው የሚጽፉትና በሳይንሳዊ መንገድ የሚተነትኑት አንዳንድ ታዋቂ የኢኮኖሚክስ ጥናት ተመራማሪ ዩኒቨርሲቲዎች እና የአንድ አገር ኢኮኖሚ ተመራማሪ ግለሰቦች ናቸው።


(www.facebook.com/TheBlackLionAfrica)

 

በግርማቸው መሪጌታ

በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚታተመው ዕለታዊው የኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 15/2018 (የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም) ዕትሙ ለአማራ ክልል ወልድያ ከተማ እና ጭልጋ ከተሞች የማረሚያ ቤት ሕንጻ ግንባታ ጨረታ ይዞ መውጣቱ ለዚህ ጽሁፌ መነሻ ሆኗል። የዚህ ማረሚያ ቤት ግንባታ ጨረታ የወጣው የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እስካሁን በሀገራችን ለተፈጠሩ ፖለቲካዊ ቀውሶች ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ቃል በገባበት ወቅት መሆኑ የተለየ ያደርገዋል። የግንባሩ ቅርብ ጊዜ መግለጫው በጠራራ ፀሐይ በሕግ ማስከበር ስም ሰብዓዊ መብት የሚረገጥበትን የፌዴራል ወንጀል ምርመራ በቀድሞ አጠራሩ ማዕከላዊ ዘግቶ ወደሙዚየምነት ለመቀየር መወሰኑን ይፋ አድርጓል። ይህንንም ውሳኔ ተከትሎ ከሳምንት በፊት ማዕከላዊ ተዘግቷል። ኢህአዴግ ማዕከላዊን ለመዝጋት የወሰነው እስርና የሰብዓዊ መብት ረገጣ በዚህች ሀገር እንደማይቀጥል ለማመላከት እንጂ ሙዚየም ማሳያ ህንፃ በማጣቱ አይደለም። እናም በቅድሚያ ህንፃውን ከመዝጋቱ አስቀድሞ የአመራሩ ሥነ ልቦና ውስጥ የበቀለው የእስር አባዜ ዶሴ መዘጋት ነበረበት። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ረሀብተኞች፣ በአካባቢያዊ ግጭቶች የተፈናቀሉ ወገኖች በበዙበት ሀገር እስረኛ ማሰሪያ (ማጎሪያ) ቤቶችን ማስፋፋት ዘመኑ የሚፈቅደው አስተሳሰብም አይደለም። የዲሞክራሲያዊ መንገድ እከተላለሁ የሚል መንግስት ባህርይም አይደለም።

እስርን በተመለከተ የአገራችን ሰው ሲመርቅ “የታሰሩትን ያስፈታልን!” ወይም “በወህኒ ቤት ለሚገኙት ወገኖቻችን የምህረት ጊዜ ይምጣ!” ይላል። ዛሬ በአገራችን “ማረሚያ ቤት” የሚባሉት “እስር ቤቶችን” ወይም “ወህኒ ቤቶችን” በተመለከተ ቀደም ሲል ከነበረው በቁጥር እየበዙ መምጣታቸው እጅግ የሚገርም ነው። “በወህኒ ቤትነት” ሳይሆን “በማቆያነት” አገልግሎት የሚሰጡ (የሚታወቁ” “እስረ ቤቶች ተለይተው ባለመታወቃቸው የተነሳ “ማን የት እንደታሰረ?” ፈልጎ ለማግኘት ከቂሊንጦ ወደቃሊቲ ከዚያም ወደዝዋይ ካልሆነም ሸዋ ሮቢት መሄድ ግድ ይላል። በተለምዶ “ከርቸሌ” እና “ዓለም በቃኝ!” የሚባለው ቦታ ወደ ቃሊቲ ሲሸጋገር አሁን “ቂሊንጦ” የሚባለውን ቦታ ወልዶ በዚህም ሳይወሰን የታሳሪው ቁጥር ሲበዛ ወደ “ሸዋ ሮቢት” እና “ዝዋይ” ከዚያም ባለፈ በየማሰልጠኛ ጣቢያው (ዲዴሳ እና ብላቴን) ወይም ብርሸለቆ ድረስ እስር ቤት የመሆናቸው ጉዳይ የአገራችንን ፖለቲካዊ ሁኔታ ያሳያል ዛሬ እነዚህ ቦታዎች ታሳሪ ባይኖርባቸውም ሁሉንም የአገራችንን እስር ቤቶች በተመለከተ ወደ አገልግሎት ሰጭነት ወይም የማሰልጠኛ ተቋም በማድረግ ገፅታቸውን መለወጥ ይገባል።

ኢህአዴግ “ራሴን ፈትሼ የአመራር ድክመት ነበረብኝ በማለት ጥልቅ ተሀድሶ” ባደረገ ማግስት “ማዕከላዊ ምርመራ” እንዲዘጋ ወስኗል። ሙዚየም እንደሚሆንም ተገልጿል። ቦታው እንደ “ዓለም በቃኝ!” ለተሻለ ህዝባዊ አገልግሎት እንዲበቃ ማድረግ ደግሞ የበለጠ ጠቀሜታ እንደሚያስገኝ ይታመናል። “ዓለም በቃኝ!” የሚባለው እስር ቤት ሙሉ ሉሙሉ እንዲፈርስ ተደርጎ ቦታው አህጉራዊ ድርጅት የሆነው የአፍሪካ ህብረት (AU) ዋና ጽ/ቤት ተገንብቶበት ለአገልግሎት በመብቃቱ አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫና የአፍሪካ መዲና በመሆን አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ትኩረት ማግኘቷ በአንድ በኩል የከተማውንና የአገራችንን ገፅታ ከመገንባት በተጨማሪ በኮንፍረንስ ቱሪዝም ተጠቃሚ መሆን ተችሏል። ይህ እውነት አሁን በአገራችን የሚገኙ እስርቤቶች (ወህኒቤቶች) ወይም ማረሚያ ቤቶችን ቁጥር (ብዛት) በመቀነስ ለህዝባዊና ለተሻሉ አገልግሎቶች እንዲውሉ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው። ደርግ በራሱ መስመር “ማዕከላዊ ምርመራ” እና “ቤርሙዳ” ከሚባሉ ቦታዎች በተጨማሪ የተለያዩ መመርመሪያና ማሰቃያ ቦታዎች እንደነበሩት ሁሉ ኢህአዴግ ያንን ተቀብሎ በማጠናከር በተለያዩ ከተሞች ጭምር ማጎሪያዎች እና እስር ቤቶች ማብዛቱ “ትሻልን ትቼ ትብስን…” ሆኗል። በየጊዜው ከሚነሱ ፖለቲካዊ ጥያቄዎችና ተቃውሞዎች ጋር ተያይዞ በርካታ ዜጎች በተለይም ወጣቶች በተለያዩ አካባቢዎች በእስር ቆይተው አሁን ባለው ሁኔታ ከእስር እንዲለቀቁ መደረጉ በበጎ ጎኑ ተቀባይነት ያለው ቢሆንም የእስር ቤቶቹ (ማቆያ ቦታዎቹ) ግን እንዳሉ አሉ። (ከማዕከላዊ ምርመራ መዘጋት በስተቀር)።

በእርግጥም ሰዎች በሕግ ተጠያቂ ሲሆኑ ወንጀል ሲፈፅሙ እንደጥፋታቸው ዓይነት ፍርድ እየተሰጣቸው ወደእስር ቤት እንደሚገቡ ይታወቃል። በዚህ መልኩ የሚታሰሩ ሰዎች የተወሰነባቸውን ቅጣት አጠናቀው እስኪወጡ ድረስ የሚቆዩበት (የሚታሰሩበት) ቦታ መኖር ግድ ቢልም እነዚህን ቦታዎች በተሻለ ሁኔታ በማዘመን “እስረኛው” ከጥፋቱ የሚታረምበት በተለየ ሙያ ብቁ ሆኖ የሚወጣበት ቦታ ሆነው ቢዘጋጁ “በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” እንደማለት ነው። ይህ አዳዲስ እስርቤቶች (ወህኒቤቶች) በመገንባት ሳይሆን ያሉትን በተሻለ የእስረኛ አያያዝ የመማሪያና የመታረሚያ ቦታ በማድረግ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል።

ዛሬ “ማረሚያ ቤት” የሚባለው ቦታ በእርግጥም ሰዎች የሚታረሙበት ስለመሆኑ ምንም የተካሄደ ጥናት የለም። ያ! ቢሆንና በእርግጥም የሚታረሙበት ቦታ ቢሆን ኖሮ በተደጋጋሚ በመታሰር የሚታወቁ ወንጀለኞች ባልኖሩ ነበር ስያሜው “ወህኒ ቤት” “ከርቸሌ” እስር ቤት “ማረሚያ ቤት” መባሉ እንዳለ ሆኖ በእንግሊዘኛው “ፕሪዝን (prison) “እስር፣ እስረኛ” ስለሆነ እስር ቤት ማለት ይበቃል።

ስለ እስር ቤት ህይወት ሲገለፅ “ከመታሰር ይሰውረን!” እንጂ በተለያዩ እስር ቤቶች ያለው እውነታ እንደእስረኛው ዓይነት ከመለያየቱም በላይ በግንብ አጥር ውስጥ ሆኖ ሰማይን ከማየት በስተቀር የሰው ናፍቆቱ የበዛ ነው። የታሰረ ሰው ጠያቂ ይፈልጋል፣ ሰው ይናፍቃል። ማዕከላዊ አሁን ተዘጋ እንጂ አራት በአራት በሆነ ክፍል ከ12 ሰዎች በላይ አንድ ላይ ታጉሮ ሙሉለሙሉ ብረት በሆነ በር በትልቅ የጓጉንቸር ቁልፍ ተቆልፎባቸው ከተለያዩ ስቃይና ግርፋቶች ጋር ማሳለፍ እጅግ ዘግናኝ ነው። ያ!እውነት ለታሪክ ይቀመጥ።

በከርቸሌ (ወህኒ ቤት) በተለይ አቃቂና ቂሊንጦ የታሰረ ሰው ደግሞ የራሱ ገጠመኝ አለው። በከርቸሌ “ደቦቃ” የሚባለው ቦታ አንዱ ሰው በሌላ ሰው ሰውነት የሚደበቅበት፣ በአንድ ጎን ብቻ የሚተኛበት፤ ሁለት ሰዎች ጆንያ የሚደረድሩ ይመስል የሌላውን እስረኛ እጅና እግር በማንጠልጠል በተጋደመ ሰው ሰውነት ላይ በመለጠፍ አንዱ ሰው የሌላውን እግር እየተንተራሰ በጎን በኩል በመደርደር መገላበጥ ጨርሶ በማይታሰብበት ሁኔታ መሽቶ የሚነጋበት ሁኔታ የበዛ ነው። የእስረኛው ክስ ግን በአያያዝ ጭምር የተለያየበት አሰራር አንዳንዱ ከፍተኛ ተፅዕኖ በመፍጠር መንገላታት የሚታይበት ነው።

የእስር ቤት ህይወት አሳዛኝ አስከፊና አስገራሚ የመሆኑን ያህል አስደሳች የሚሆንበት ወቅትም አለ። በመታሰራቸው ሞራላቸው የተነኩ በማይጠበቅ ሁኔታ ብርቱ የሚሆኑበት፣ ትልቁ የሚያንስበት፣ ትንሹ ትልቅ የሚሆንበት አጋጣሚ በርካታ ነው። የታመቁ እውነቶች ድብቅ ሀሳቦች በድንገት ሕይወት ዘርተው በመውጣት ለሌላውም አስተማሪ የሚሆኑ ልምዶችና ተሞክሮዎች የሚገኝበት ነው። እውነቱ ሰፊና በርካታ በመሆኑ በእስር ቤት ህይወት ጉዳይ ወደፊት በዝርዝር ለማቅረብ ይቻላል።

ወደዋናው ጉዳይ ስንመለስ ግን አሁን የምንገኝበት የአገራችን ሁኔታ እስር ቤቶች (ወህኒቤቶች) የሚገነቡበት ባለመሆኑ ያሉትን እስርቤቶችንም ጭምር ወደልማት ማዕከላት ለመለወጥ መስራት ያስፈልጋል። አዲስ ወህኒቤት ለመገንባት የተያዘ በጀት ካለም ወደሌላ የህዝባዊ አገልግሎት ተቋም ግንባታ በመቀየር እንደትምህርት ቤት ወይም የጤና ተቋማት (ሆስፒታል) በመገንባት ወደልማት ሥራ እንግባ። አሁን በግልፅ የሚታወቁትንና የማይታወቁትን እስር ቤቶች ቁጥር በመቀነስ ጭምር (በመዝጋት) ከእስረኛነት እንላቀቅ።

Page 1 of 29

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us