“የኢትዮጵያ የመንግስትነት ቀውስ ከታሪክ አንፃር አልተፈታም”

Friday, 12 January 2018 17:13

“የኢትዮጵያ የመንግስትነት ቀውስ
ከታሪክ አንፃር አልተፈታም”

ፕሮፌሰር ማድሃኔ ታደሰ

 

ፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ ላለፉት ሃያ ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዳዮች በምሁርነታቸው ተሳታፊ ከመሆናቸው በላይ በርካታ ጽሁፎች አሰናድተው ለአንባቢያ አቅርበዋል። 

ፕሮፌሰር መድሃኔ በአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች ዙሪያ ከጸጥታ እና ከደህንነት ጋር በተያያዘ በርካታ አርቲክሎችና መጽሐፎች አዘጋጅተው አሳትመዋል።


በአሁን ሰዓት በእንግሊዝ ለንደን ከተማ በሚገኘው ኪንግስ ኮሌጅ የግሎባል ስተዲ መምህርና ተመራማሪ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።


የሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰን በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ ዙሪያ አወያይቶአቸዋል። በውይይቱም ፕሮፌሰሩ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀውስ ከመንግስተርነት ቀውስ ጋር የሚያያዝ እንጂ እንደሚባለው ከብሔርና ከማንነት ጋር በተያያዘ መቅረብ እንደለሌበት መከራከሪያ አንስተዋል። ለአንባቢዎች እንዲመች በዚህ መልኩ አቅርበነዋል።


ሰንደቅ፡- በኢትዮጵያ ውስጥ ባልተለመደ መልኩ ዜጐች በማንነታቸው መፈናቀል፣ መገደል እና መገለል እየደረሰባቸው እና ተያያዥ ችግሮች የሚስተዋልባቸው ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ነው። ከጠቀስኩትና አሁን ካለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር የችግሮቹ መነሻዎች ምንድን ናቸው?


ፕሮፌሰር መድሃኔ፡- እኔ የማያው መጀመሪያ ምንጩ ምንድን ነው? ምንጩ ፖለቲካዊ ነው። አሳታፊ የሆነ ፖለቲካ፤ ሕገመንግስታዊ ሥርዓት ያጠናከረ ፖለቲካ፤ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ያጎናጸፈ ፖለቲካ ከሌለ፤ ብዝሃነቱ ዋጋ የለውም። ስለዚህ በዚህ መልኩ ብዙ የተጓዝን አይመስለኝም።


ሕገመንግስት አለ፤ ፌደራሊዝም አለ፤ እነዚህን በዴሞክራሲ መግራት ማጠናከር አልቻልንም። የፖለቲካ ችግር ነው፤ አሳታፊ ስል ብሔረሰቦችን ብቻ ማለት አይደለም። የፖለቲካ አመለካከት፣ የተለያዩ ቡድኖች፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የነበሩ የተለያዩ ኃይሎችንም የምናቀራርብበት የፖለቲካ ምህዳር መፍጠር አለመቻላችን ነው።


ሁለተኛው፣ የህግ የበላይነት መፍጠር አለመቻላችን ነው። ሶስተኛ (በማንነቶች ደረሰ ለተባለው ጥቃት) ብሔርና ዜግነትን ማቀራረብ አለመቻላችን ነው። ብሔር ወይም የብሔረሰብ መብት የባህል እራስን የማስተዳደር መብት በሕገመንግስቱ ውስጥ አለ፤ አይካድም ጠቃሚ ነገር ነው። ነገር ግን ብሔር ብቻውን ሀገር አይገነባም። ዜግነት በሚለው ላይ አልተሰራበትም። ዜግነት ነው፣ የተለያዩ ብሔረሰቦችን ዜጎችን አንድ ቤተሰብ የሚያደርገው፤ አንድ ማሕበረሰብ የሚያደርገው። እንድንቀራረብ እንድንደጋገፍ በዜግነት ላይ ማተኮር ነበረብን።


ፖለቲካዊ ዕውቅና ለብሔረስብ መስጠት አንድ ጉዳይ ነው፤ መብት መስጠት አንድ ጉዳይ ነው፤ እራስ ማስተዳደር አንድ ጉዳይ ነው፤ ሀገር ለሚለው ትኩረት መስጠት ነበረበት። የሚያቀራርበን የሚያገናኘን ላይ ማትኮር ነበረብን። ዜግነት የሚለው ላይ ብዙ ሳይሰራ፣ በብሔር ላይ አደላን። ስለዚህ ይህ የፈጠረው ችግር አለ። በሕዝብ ብዛት እና በትውልድ ሽግግር (Demographic transition theory) ላይ ቅስቀሳ ሲደረግ ተቆይቶ፣ የተፈጠረ ትውልድ አለ። ይህ በራሱ የሚፈጥረው ችግር አለ፤ ከኢኮኖሚና ከፖለቲካ መገለል ጋር፣ ከዲሞክራሲ ጥበት፣ ከሕግ የበላይነት አለመኖር ጋር፣ በፖለቲካው አሳታፊ ካለመሆኑ፣ ከሕዝብ ብዛት እና ከኢኮኖሚው ችግር ጋር ተዳምሮ፣ ችግሮቹ ተፈጥረዋል።


ሰንደቅ፡- የተፈጠረው ችግር ጊዜያዊ ተደርጎ መውሰድ ይቻላል?


ፕሮፌሰር መድሃኔ፡- የተፈጠረው ችግር ጊዜያዊ ነው ብዬ አለወስደውም። ጊዚያዊ ሳይሆን መሰረታዊ መዋቅራዊ ችግር ነው። በሕገመንግስቱ መሰረት ዴሞክራሲን ሥርዓቱን ስናጠናክር ነው። ሲጀመር ፌደራሊዝም ያለ ዴሞክራሲ ባይሞከር ይሻላል። ፌደራሊዝም ካለ፣ ዴሞክራሲ ነው መኖር አለበት። የኤርትራ ፌዴሬሽን የፈረሰው ለምንድን ነው? ኢትዮጵያስ ምን ዋስትና አላት። ይህ ወሳኝ ነገር ነው።


ሌላው፣ ባለፉት ዓመታት ትልቅ ክፍተት የሚመስለኝ፣ የታሪክ ጉዳይ ነው። የኢትዮጵያ ታሪክ የት ነው ያለው? የኢትዮጵያ ታሪክ ሁሉንም በሚወክል መልኩ ሳይንሱና ዘመናዊ ትምህርቱ በሚያስቀምጠው መልኩ ተቃኝቶ ተዘጋጅቶ በጠንካራ ሁኔታ ለዜጋው መሰጠት አለበት። ታሪኩን የማያውቅ ትውልድ፣ አንድ ታሪክ ያለን ሕዝቦችን ነን ተብሎ ተደጋግሚ በማይወራበት ሕብረተሰብ አደጋዎች መፈጠራቸው አይቀርም። ይህ ክፍተት መሞላት አለበት፣ ዘግይቷል። ከፍ ብዩ እንዳነሳሁት ከሕዝብ ብዛት እና ከትውልድ ሽግግር ጋር ተዳምሮ የታሪክ ክፍተቱ የፈጠረው ብዥታ እና ድክመት አለ።


አንድ ሀገር ነው ያለን። የትኛውም መንግስት ኢኮኖሚው ላሳድግ ነው፣ ሕገ መንግስት ላስከብር ነው፣ የህግ የበላይነት ላሰፍን ነው፣ ፍትህ ላመጣ ነው፣ ለሕዝቡ ዳቦ እንዲያገኝ ላደርግ ነው፣ ማለቱ እንዳለ ሆኖ፣ ከእነዚህ በላይ ትልቁ ጉዳይ ግን ሀገር ማስቀጠል አለብኝ የሚለው ነው፤ ሀገር የማስቀጠል ኃላፊነት። ይህ ደግሞ ታሪካችን እና የታሪክ ትውስታችንን ማቀራረብ መቻል አለብን። ማጠላለፍ መቻል አለብን።


የኢትዮጵያ የመንግስት ምስረታ ትረካዎች ተፎካካሪ እና ተጠፋፊ ናቸው። እነዚህ ትልልቅ ናቸው፣ ማቀራረብ አለብን። እነዚህን አቀራርበን፣ ትረካዎችን ማቀራረብ አለብን። ይህንን ለማድረግ ሰፊ መድረኮች እና ነፃነቶች መኖር አለባቸው። የፖለቲካ ምህዳሩን ካላሰፋ እነዚህን ማቀራረብ አንችልም። ስለዚህ የኢትዮጵያ ሀገርነት እና የመንግስትነት ትረካዎችን የተለያዩ ትረካዎችን አንድ ላይ ማምጣት አለብን። የፖለቲካ ኢኮኖሚውን መቀየር የምንችለው። ከላይ ያሰፈርነውን ስናደርግ ነው፣ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ችግሩን የምንፈታው። እንደሚባለው ችግሩ የብሔር፣ የማንነት አይደለም።


ሰንደቅ፡- የፖለቲካ ኢኮኖሚ ችግርን በዋናነት ለተፈጠረው ቀውስ ማሳያ ካስቀመጡ፣ ችግሩን ለመፍታት ምን ዓይነት መዋቅራዊ ለውጦችና ሥራዎች መሰራት አለበት ይላሉ?


ፕሮፌሰር መድሃኔ፡- አንዱ፣ በሕገ መንግስቱ መሰረት መሥራት ነው። ሕገመንግስቱ የሚያስቀምጣቸውን የሲቪልና የፖለቲካ መብቶችን ማክበር ነው። ምህዳሩ እሱ ነው፤ ቀደም ብሎ ተቀምጧል። ሁለተኛ፣ በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል ለሚሉ ኃይሎች መድረክ መፍጠር። የትኛውም ሒደት ኢትዮጵያ ውስጥ ከአሁን በኋላ አንድ ቡድን በሚያደርገው ሒደት ወይም ጥረት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር ሊፈታ አይችልም።


የኢትዮጵያ የፖለቲካ የኢኮኖሚ የታሪክ ውጥረቶች፣ ከአንድ የፖለቲካ ቡድን በላይ ናቸው። ይህንን መገንዘብ ያስፈልጋል። አሁን ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች የኢትዮጵያን ችግር ብቻቸውን ይፈታሉ የሚል እምነት የለኝም። ለዚህም ነው የመንግስትነት እና የፖለቲካ ትረካችንን ማቀራረብ የሚያስፈልገው እየተባለ ያለው።


በሁለተኛ ደረጃ፣ መታየት ያለበት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ሽግግር አሳታፊ ነው ወይ? ከትረካው ባለፈ ማየት ያስፈልጋል።


ሰንደቅ፡- (ላቋርጥዎትና) አሳታፊ መድረኮች መኖራቸውን መንግስት በመከራከሪያነት የሚያቀርባቸው አሉ። ለምሳሌ በምርጫ ቦርድ ተመዝግቦ ሕጋዊ ፓርቲ መመስረት እንደሚቻል ያስቀምጣል። የህዝብ መድረኮችም በተለያዩ ቦታዎች እንደሚዘጋጁ ይገልፃል። መከራከሪያዎትን በማሳያ አስደግፈው ቢገልጽልን?


ፕሮፌሰር መድሃኔ፡- መድረኮች በሚባለው ላይ ልዩነት አለ። ኮሚኒኬሽን እና ኢንዶክትሪኔሽን ይለያያል። ኮሚኒኬሽን ከሕዝቡ ጋር መወያየት ነው። ሕዝቡ ሃሳብ ያመነጫል፣ አመራሩም ሃሳብ ያመነጫል፣ ውይይት ይደረጋል። ኢንዶክትሪኔሽን ግን ማጥመቅ ነው።


በአጠቃላይ ግን የኢትዮጵያ የመንግስትነት ቀውስ ከታሪክ አንፃር አልተፈታም። ትልቁ የኢትዮጵያ የመንግስትነት ቀውስ አንድ ቡድን የራሱን ኃይሎች አሰባስቦ ይመስሉኛል የሚላቸውን መርጦ፣ አሰባስቦ የመንግስት ሥልጣን እና ፖለቲካ ኢኮኖሚ የመቆጣጠር ነው። ይህንን አልቀየርነውም፤ መቀየር አለበት። ለዚህ ነው ወደ ቀውስ የምንመጣው፣ የምንገባው።


የመገለል ስሜት ያለው ኃይል በወሳኝ መልኩ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር የለበትም። በሕዝብ፣ በብሔር፣ በፖለቲካ ቡድን ልትገልጸው ትችላለህ፣ ከአንድ አቅጣጫ ኢትዮጵያ ውስጥ ስልጣን ይያዝና የመንግስት ስልጣን ፖሊሲ እና አቅጣጫ ወሳኝ ይሆናል። ይህ መሆን የለበትም። ከየትኛውም አካባቢ ኢትዮጵያ ውስጥ ስልጣን ላይ ሲወጣ፣ ሁሉንም አካባቢዎች ያሳተፈ ሒደት ለመጀመር አልተሞከረም። ኢሕአዴግ ሲገባ ሞክሮት ነበር። አሁንም ቢሆን ከፖለቲካ ጨዋታ ውጪ ነን ያሉት ኃይሎች፣ እስካሁን እንደቀጠሉ ናቸው። ይህንን መቀየር ካልቻለን፣ ሲጀመር ምኑ ነው አብዮታዊነት? አብዮታዊነት ሥርነቀል ለውጥ ማምጣት ነው። የኢትዮጵያ የመንግስትነት ታሪካዊ መዋቅራዊ ችግር፣ ፖለቲካዊ ችግር ነው።


ሁለተኛው የኢትዮጵያ መንግስትነት ቀውስ፣ ነፃ ተቋሞች አለመፍጠር ነው። ሶስተኛው፣ የህግ የበላኝነት አለማስፈን ነው። ሁልጊዜም በአመፅ ነው ሥልጣን የሚያዘው። ይህንን መቀየር አልቻልንም። “አለባብሰው ቢያርሱ፣ በአረም ይመለሱ” እንደሚባለው ነው። ወደዚህ ነው የምንመለሰው። ፖለቲካ ኢኮኖሚው የሚቀየረው የመንግስት ባሃሕሪ እና የስልጣን (የሃይል) ዝምድና (power relation) ሲስተካከል ነው፣ ማስተካከል መቀየር ግን አልቻልንም። የተራዘመ ትግል ቢፈልግም፣ አቅጣጫውን ግን ቁርጠኛ ሆነን አላስቀመጥንም። ይህንን ማድረግ እስካልተቻለ ድረስ፣ መውደቅ እና መነሳት ቀጣይ ናቸው። ተጋላጭነቱም እንደዚሁ ይቀጥላል።


ሰንደቅ፡- አንድ መንግስት አላሳትፍም ብሏል ተብሎ አይተውም። መብት የሚሰጥ ብቻ አይደለም። ከዚህ አንፃር የምሁራን ሚና ምን መሆን አለበት?


ፕሮፌሰር መድሃኔ፡- አዎ መብት የሚሰጥ አይደለም። ሥርዓት የሚፈጠረው በኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ በአንድ ቡድን ወይም አመራር አይደለም። አመራሩ ማድረግ ያለበት በሕገ መንግስቱ ሥር መንቀሳቀስ ነው። ዴሞክራሲን የሚፈጥረው ሕዝቡ እንጂ አመራሩ አይደለም። ከአሁን በኋላ አንድ አመራር ወይም ቡድን ዴሞክራሲ እሰጣለሁ ቢል፣ መስጠትም ቢጀምር አይሰራም። ከላይ የሚሰጥ ዴሞክራሲ ወይም በተወሰኑ ቡድኖች የሚሰጥ ዴሞክራሲ አይሰራም።


ሕወሓት በርሃ ሲወጣ ወጣቶችን አሰልፎ ዴሞክራሲ ፍትህን እናመጣለን ብሎ ነው። አብዛኛው ወጣት ተሰልፎ የታገለው ፍትህ ዴሞክራሲ ይመጣል ብሎ ነው። ግን ዴሞክራሲ እና ፍትህ እናመጣለን የሚለው የተቀደሰ ሃሳብ ሆኖ ሲያበቃ፣ እኛ እናመጣለን ወይም እኛ እንሰጣለን የሚለው አመለካከት ግን ችግር ነው። ከሕዝቡ ነው፣ የምንወስደው ነው የሚባለው። እኛ ሁኔታዎችን እናመቻቻለን፣ ፀረ-ዴሞክራሲ የሆነውን ሥርዓት እንገረስሳለን፣ አሳታፊ ሕገመንግስት፣ ነፃ የሆኑ ተቋሞች እንመሰርታለን። ሕዝቡ እራሱ ነው፣ ዴሞክራሲን ማስፋትም መገደብም የሚችለው።


ሕዝብ ያልደገፈው ነገር የጊዜ ጉዳይ እንጂ ሊቀጥል አይችልም። ስለዚህ፣ ምሁሩ ባለሃብቱ ሲቪሉም ሁሉም እኔ ነኝ ለውጥ ማምጣት የምችለው የሚለውን ስሜት ማዳበር አለበት። ስልጣን ላይ ያለው ኃይልም ቢሆን፣ ሕዝቡ ነው ዴሞክራሲ የሚያመጣው፣ ሕዝቡ ነው ችግሮቹን የሚፈታው፣ ሕዝቡ ነው የሚመራንን፣ ሕዝቡ ነው አቅጣጫ የሚያሳየን ብለው አምነው ቋንቋቸውን መቀየር አለባቸው። ይህ ካልተቀየረ የፖለቲካ ባሕሉም፣ የኢትዮጵያ የመንግስትነት ቀውስን ለመፍታት አልጀመርነውም ማለት ነው። ከሕዝባችን ምክር እና አቅጣጫ እንፈልጋለን ነው፣ መባል ያለበት። የህዝቡን የወሳኝነት ሚና ማስፋት ነው። 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
288 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1034 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us