የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች መግለጫ በምሁራንና ፖለቲከኞች እይታ

Friday, 12 January 2018 17:09

 

በይርጋ አበበ

 

የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከሥራ አስፈፃሚነት የተሰናበቱ ነባር ታጋዮችን ያካተተ ስብሰባ ለ17 ቀናት አካሂዶ ከጨረሰ በኋላ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል። ከፓርቲው መግለጫ ማግስት ደግሞ የግንባሩ አባል ደርጅቶች ሊቃነመናብርት (የኦህዴድ፣ ብአዴን፣ ህወሓት እና ደኢህዴን) ሊቀመንበሮች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ለሁለት የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ብቻ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።


የፓርቲዎቹ አመራሮች ሰፋ የለ ሰዓት የፈጀውን መግለጫ ሲሰጡ ዋንኛ ትኩረታቸው በግንባሩ እና በአባል ፓርቲዎቹ ግንኙነት ላይ ያተኮረ ሲሆን ተጨማሪ አገራዊ ጉዳዮችን የዳሰሰ ነጥብም ታክሎበታል። በተለይ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ከእስር ቤት መፍታት እና ማዕከላዊ የሚባለውን የምርመራ ማዕከል (እንደ አቶ ኃይለማርያም ገለፃ የደርግ ማሰቃያ ቤት) ዘግቶ ሙዚየም ማድረግ የሚሉት የበርካታ የፖለቲካ ምሁራንና መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት የሳቡ ጉዳዮች ሆነዋል።


በእነዚህ ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረት በማድረግ ምሁራን እና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን አነጋግረን ሃሳባቸውን እንዲያካፍሉን አድርገናል። የምሁሩን (ዶ/ር ምህረት አየነው ከፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ) እና ፖለቲከኞቹ (አቶ የሺዋስ አሰፋ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር እና አቶ ሙላቱ ገመቹ የኦፌኮ ም/ሊቀመንበር) የሰጡትን አስተያየት ለአንባቢያን በሚመች መልኩ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

 

የትኞቹ የፖለቲካ እስረኞች?

 

ላለፉት ረጅም ዓመታት ኢህአዴግ “የፖለቲካ እስረኛ የለም” በሚለው አቋሙ ፀንቶ ቆይቶ ነበር። ታህሳስ 25 ቀን 2010 ዓ.ም የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች ሊቃነመናብርት መግለጫ ላይ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ “ለተሻለ ብሔራዊ መግባባት በራሳቸው ጥፋት የታሰሩ የፖለቲካ አመራሮችን እንዲፈቱ እናደርጋለን” ሲሉ ተናግረዋል። የአቶ ኃይለማርያም መግለጫ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም ሆነ አባላት የፖለቲካ እስረኞች መሆናቸውን ባይገልፅም ፖለቲከኞች መታሰራቸውን ግን አመላካች ነው። ለዚህም ሲባል የፓርቲዎቹ አመራሮች ከእስር መፈታትና የተመሰረተባቸው ክስ እንዲቋረጥ መደረግ ለአገራዊ ብሔራዊ መግባባት የተሻለ በር ከፋች እንደሆነ መግለጻቸው ፓርቲው “የፖለቲካ እስረኞች የሉም” ከሚለው አቋሙ ማሻሻያ ማድረጉን ያመለክታል ሲሉ ምሁራኑ ይናገራሉ።


የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዳይሬክተሩ ዶ/ር ምህረት አያሌው እንደሚሉት “መንግሥት የፖለቲካ እስረኞችን በተመለከተ በተለያየ ጊዜ የተለያየ ትርጓሜ ሲሰጠው ቆይቷል። እኔ እስከማውቀው ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ እስረኞች እንደሌሉ ነው፤ የመንግስት አቋም የነበረው። አሁን የፖለቲካ እስረኞች ይፈታሉ ሲባል በመጀመሪያ ደረጃ የትኞቹ ናቸው የሚፈቱት? የሚለውን ማየት ተገቢ ነው። ምክንያቱም ብዙዎቹ የታሰሩት በሽብር ድርጊት ክስ ነው። አሁን አቶ ኃይለማርያም የተናገሩትን ተከትሎ ህዝቡ እየጠበቀ ያለው እነማን ይፈታሉ? እያለ ነው። ሂደቱስ ምን መልክ ይኖረዋል? የሚሉትን ነጥቦች ማየት ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል።


የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ም/ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ በበኩላቸው “በፖለቲካ ሰበብ የታሰሩ ፖለቲከኞች መፈታት የእኛ ብቻ ሳይሆን የህዝቡም ጥያቄ ነበር። የኢህአዴግ አመራሮች እዚህ ውሣኔ ላይ የደረሱት በህዝብ ያለማቋረጥ ተቃውሞ የፈጠሩት ተፅእኖ ውጤት ነው” ሲሉ ኢህአዴግ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ለመፍታት የደረሰበትን ውሳኔ ምክንያት ተናግረዋል። አቶ ሙላቱ አክለውም “በኢህአዴግ አመራር ደረጃ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ከእስር እንፈታለን ተብሎ ሲነገር እኛም ሆነ ህዝቡ ወይም የታሰሩ ፖለቲከኞች ቤተሰብ ተስፋ ያደረግነው ቃል የተገባው ቶሎ እንደሚፈፀም ነበር። ነገር ግን ቃል በተገባው መሠረት ፖለቲከኞቹ እስካሁን አልተፈቱም። ከዚህም የባሰው ደግሞ የእኛ አባላት በዚህ ሳምንት በወለጋ ታስረዋል” ብለዋል። “ከ25 ዓመት በኋላ የፖለቲካ እስረኞች መኖራቸውን ያመነው ኢህአዴግ የህዝብ ቁጣ ገደቡን ጥሶ ስለመጣ ነው” ያሉት አቶ ሙላቱ፤ “ኦፌኮ በስርዓቱ ብዙ የተጎዳ ፓርቲ ነው። ከተወሰንን ዕድለኞች በስተቀር አብዛኛው የፓርቲያችን ስራ አስፈፃሚ አባላት እና እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አባሎቻችን የሚገኙት እስር ቤት ነው። ጽ/ቤቶቻችን ተዘግተዋል” ሲሉ ኦፌኮ ከኢህአዴግ የገጠመውን ፈተና ገልፀዋል።


የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ደግሞ “ቀደም ሲል የፖለቲካ እስረኛ የለም ሲሉ ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ እሰረኛ የለም ማለት ፀሐይ በምስራቅ ትወጣለች የሚለውን ዓለም አቀፍ እውነታ (General truth) መካድ ነው። ቢያንስ የፖለቲካ እስረኛ መኖሩን ማመናቸውና ለመፍታት መወሰናቸውን እየገለፁ መሆኑ ጥሩ ነው። እንዲሁም የቀድሞ ማዕከላዊ እንደሚዘጋም ገልፀዋል። ዝርዝሩን ትተነው እነዚህ ሁለት ውሳኔዎች ተግባራዊ ከሆኑ መልካም ነው ብለን መውሰድ እንችላለን። ነገር ግን ማዕከላዊን ብቻ መዝጋቱ በቂ አይደለም። ምክንያቱም እኔ ራሴ በ2006 ዓ.ም ማዕከላዊ ሳለሁ ስቃይ ደርሶብኛል። እኛ እዚያ እያለን ለበርካታ ቀናት በሌላ የምርመራ ቦታ ምርመራ ሲካሄድባቸው (አካላዊ ጥቃት የተፈፀመባቸው ሲሉ ይገልጿቸዋል) የቆዩ ሰዎች ስቃዩ ደርሶባቸው እኛን ሲቀላቀሉ አይቻለሁ። ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ መቆም ያለበት ስቃይ ነው። ለዚህ ደግሞ ፀረ-ሽብር እና ፀረ-ሽብር ግብረሃይል የተባሉት በአዋጅ ሊፈርሱ ይገባል። ከማዕከላዊ ውጭ ያሉ ማሰቃያ ቤቶች (ምርመራ ክፍሎች) ሊፈርሱ ይገባል” ሲሉ ማዕከላዊ ወደ ሙዚየም እንዲቀየር መወሰኑን አስመልክቶ ሃሳባቸውን ገልፀዋል።


“የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች መፈታት በራሱ እንደ ጅምር ጥሩ ነው” የሚሉት አቶ የሽዋስ፤ “የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት እንደ ዶ/ር መረራ፣ አንዷለም አራጌ እና በቀለ ገርባ ያሉ አመራሮች ከእስር ተፈተው መነጋገር አለባቸው። ሌሎችም እስረኞች ከእስር ወጥተው ስለ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር መስፈን ውይይት ሊያደርጉ ይገባል። ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ሳይኖሩ መነጋገር አይቻልምና። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ሰው ሃሳቡን ስለገለፀ ብቻ እንደማይታሰር ዋስትና ሊሰጠው ይገባል። የፖለቲካ እስረኞች እንደሚፈቱ የተሰጠው ውሳኔ እንደመጀመሪያ ሃሳብ ሲታይ ጥሩ ነው አልን እንጂ ከዚያ በኋላ ብዙ የምንነጋገራቸው ነገሮች አሉ።” ሲሉ ከፖለቲካ እስረኞች መፈታት በኋላም ብዙ የቤት ሥራ እንዳለ ተናግረዋል።

 

ቃል የተገባው ዘግይቷል?


አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች መሪዎች የዛሬ ሳምንት ረቡዕ ረፋዱ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ከእስር እንደሚፈቱ ተናገሩ። ሆኖም እስካሁን ድረስ (ይህ ፅሁፍ እስከተዘጋጀበት ትናንት ምሽት) አንድም የፖለቲካ እስረኛ በምህረት ከማረሚያ ቤት የወጣ የለም። ይህን በተመለከተ ሃሳባቸውን ለሰንደቅ ጋዜጣ የሰጡት ዶ/ር ምህረት አየነው “የተባለው እኮ የእስረኞቹ መፈታት የገና ስጦታ ነበር። ነገር ግን ምንም የተሰራ ነገር የለም። ይህ ደግሞ ህዝብ በመንግስት ላይ እምነት ማጣትን ያስከትላል” ብለዋል።


ዶ/ር ምህረት አክለውም “ልክ እንደ አቶ ኃይለማርያምም ሆነ እንደ ሌሎቹ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት ሁሉ እነዚህ ሰዎችም (የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን) በአገራቸው ፖለቲካ ጉዳይ ላይ የመሳተፍ መብት አላቸው። ይህ ህገ መንግስቱም የሚሰጣቸው መብት ነው። ነገር ግን በፖለቲካ ስለተሳተፉ ለምንድነው ወንጀለኛ የሚሆኑት? አቶ ኃይለማርያም እና አቶ ደመቀ በፖለቲካ ሲሳተፉ ወንጀለኛ ያልሆኑት እነዶ/ር መረራ፣ አንዷለም አራጌ እና በቀለ ገርባ በፖለቲካ ሲሳተፉ ወንጀለኛ የሚሆኑት ኢትዮጵያዊያን አይደሉም እንዴ? የመንግስት ወገን ሲሆን ፖለቲከኛ፤ ተቃዋሚ ሲሆን ወንጀለኛ ነው ማለት እኔ አይገባኝም” ሲሉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን እስር በተመለከተ ሃሳባቸውን ገልጸዋል።


የኦፌኮው ም/ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹም ቃል በተገባው መሠረት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና አባሎች አለመፈታት ቃል የተገባው እንደዘገየ አመላካች ነው ሲሉ ይናገራሉ። አቶ ሙላቱ ሃሳባቸውን ሲያጠናክሩም “አንድ እስረኛ ትፈታለህ ሲባል እያንዳንዷን ሰዓት ነው የሚቆጥረው። ቤተሰብ ይጨነቃል። ይፈታል በተባለው ቀን አለመፈታታቸው የሚያሳየው መዋቅሩ ምን ያህል ደካማ እንደሆነ ነው። ለምሳሌ ከዚህ በፊትም በቀለ ገርባ እንዲፈታ ተወስኖ በራሳቸው ሚዲያ (በመንግስት ሚዲያ) ገልጸው የነበረ ቢሆንም እንደገና እንዲታሰር ነው ያደረጉት። ይህ ደግሞ የሚያሳየው እነዚህ ሰዎች ለሚናገሩት ነገር ምን ያህል ታማኞች ናቸው ወይም እውነተኛ ናቸው? የሚል ጥርጣሬ እንዲነሳ ነው የሚያደርገን። ህዝቡ ውስጥ ያለው ጥርጣሬም ይህ ነው። ምክንያቱም ህዝብ በመንግስት ላይ እምነቱን ካጣ ቆይቷልና።


በሌላ በኩል ደግሞ ጎሮ ላይ ሻምቡ ከተማ በገፍ እያሰሩ ነው። እፈታለሁ ሲል በሌላ በኩል እያሰረ ስናይ የኢህአዴግ መዋቅር እንዴት እንደሆነ ግራ የሚያጋባ መሆኑን ያሳያል። የላይኛው እፈታለሁ ሲል የታችኛው በገፍ እያሰረ ነው። በየቦታው ፀጥታን ለማስከበር የተለቀቀው የታጠቀ ሃይል አነጣጥሮ ተኳሽ ስለሆነ ብዙ ሰው ገድሏል። ይህ አልሞ ተኳሽ ኮማንድ ፖስት ወደ ካምፑ ካልተመለሰ እና የእስሩ አይነት ካልተስተካከለ የኢትዮጵያ ህዝብ አሁንም ኢህአዴግ የተወሰኑ ሰዎችን እፈታለሁ ብሎ ቢፈታም እምነቱን አይሰጠውም። ምክንያቱም የህዝብ ጥያቄ የታወቀ ነው። የሥርዓት ለውጥ ነው የፈለገው” በማለት ተናግረዋል።


“አሁን የማናግርህ የታሰሩ አባሎቻችንን ለመጠየቅ ወደቂሊንጦ እየሄድኩ ሳለ ነው” ብለው መናገር የጀመሩት የሰማያዊ ፓርቲው ሊቀመንበር በበኩላቸው “ኢህአዴግና ህዝቡ ላይገናኙ ተለያይተዋል” ይላሉ። አቶ የሺዋስ ሃሳባቸውን ሲያጎለብቱም “እኔ እስረኛ ሆኜ ችግሩን አይቻለሁ። እስረኛ ትፈታለህ ተብሎ በተባለው ቀን ካልተፈታ ስነልቦናው ይረብሻል። ወዳጅ ዘመድም አብሮ ይረበሻል። ኢህአዴግ ሰሞኑን ያደረገውም በእስረኞቹ ላይ ግፍ ነው የፈፀመው። ይፈታሉ የተባሉት ሰዎች ቶሎ አለመፈታታቸው የድርጅቱን (ኢህአዴግን) አለመታመን አመላካች ነው” ሲሉ ተናግረዋል።


አቶ የሺዋስ አያይዘውም “ኢህአዴግን እኮ ለማሻሻል (Reform ለማድረግ) የማይመቸው ታማኝ አለመሆኑ ነው። ኢህአዴግ እንደድርጅትም ሆነ በውስጡ ያሉትን ሰዎች እንደ ግለሰብ እንተማመናለን የምትላቸው አይደሉም። ይህን ለማድረግ የሞራልም፣ የሃይማኖትም ሆነ የምንም ሃይል የሚይዛቸው አይደሉም። እንደማንኛውም አምባገነን መንግስት ዛሬ የሚያሳድራቸውን ዘዴ ብቻ ነው የሚያስቡት። ይህ ደግሞ እንዳይታመኑ ያደርጋቸዋል። ለምሳሌ ሰሞኑን በተናገሩት ላይም ብንመለከት እስረኞችን ትፈታላችሁ ብለው ባለመፍታታቸው ስቃይ ነው የጨመሩባቸው። መግለጫውን ከመስጠታቸው በፊት የሚፈቱትን አጣርቶ ነበር መናገር የነበረባቸው። ምክንያቱም የሰማዊም፣ የኦፌኮም፣ የመኢአድም ሆነ የቀድሞ አንድነት ፓርቲ አባላት፣ በወልቃይት፣ በኦሮሚያም ሆነ በኮንሶ ጉዳይ የታሰሩት ይታወቃሉ። ይህንን አጣርቶ መወሰን ደግሞ ቀላል ነው። ነገር ግን ይህን ሳያደርጉ መግለጫ በማውጣታቸው የስንት እስረኛ ቤተሰብ እየተሰቃየ እንደሆነ መገመት ቀላል ነው። ለእኛም በየጊዜው የሚደወለው ስልክ የሚያሳየው የችግሩን ስፋት ነው።” በማለት ይፈታሉ ተብለው ቃል የተገቡ እስረኞች አለመፈታታቸው አግባብ አለመሆኑን ተናግረዋል።


የአራቱ ፓርቲዎች ሊቀመናብርት መግለጫ ይዘት


የኦህዴድ፣ ብአዴን፣ ህወሓትና ደኢህዴን ሊቀመንበሮች የሰጡትን “ድንገተኛ” መግለጫ ዶ/ር ምህረት አየነው ሲገልጹት፤ “ያልተሰራ የቤት ሥራ ያመጣው ውጤት ነው” በማለት ነው። ዶ/ር ምህረት ሃሳባቸውን ሲያብራሩም “በአገሪቱ ውስጥ የሆነ የበጎ አድራጎት ህግ አውጥቶ በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ መያዶችን በማፈን ራሱን እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂውማን ራይትስዎች አጋልጠ ሰጠ። የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ደግሞ የአገር ውስጥ ተቺ መገናኛ ብዙሃንን በማግለል ህዝቡን ለማህበራዊ ሚዲያ አጋለጠው፤ እንደ እነ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ አንዷለም አራጌ እና በቀለ ገርባ የመሳሰሉትን ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን በማሳደድ ራሱን ለፅንፈኛ ዲያስፖራ አጋለጠ። እነዚህ ስህተቶች ፓርቲውን ብቻ ሳይሆን አገሪቱንም ወደ ኋላ ጎትተዋታል” ሲሉ በዝርዝር ይናገራሉ። ዶ/ር ምህረት አያይዘውም “አገሪቱ አሁን የምትገኝበት ደረጃ አሳሳቢ ቢሆንም መንግሥት ግን ይህን ያሰበበት አይመስልም” በማለት ገልፀዋል።


አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩላቸው መግለጫውን “ሽሽት የበዛበት” ያሉት ሲሆን ምክንያታቸውን ሲያብራሩም “በመጀመሪያ ለመናገር የመጡበትን ምክንያት ማየት ያስፈልጋል። አባል ድርጅቶቹ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን እና ቅራኔያቸውን መፍታታቸውን ለመግለፅ ነው። እሱ ደግሞ የእኛ ችግር አይደለም። የህዝቡ ችግርም አይደለም። እኔ በበኩሌ ኢህአዴግ ቢፈርስም ደስ ይለኛል። ዋናው የህዝቡ ጥያቄ ይመለስ የሚለው እንጂ የእነሱ ችግር መፈታት አይደለም።


የመግለጫውን ዝርዝር ይዘት ስናየው ደግሞ መጀመሪያ በወረቀት የገለፁት መግለጫ እና ቆይተው የተናገሩት ደግሞ ሌላ ነው። አሁን ሰሞኑን በተከታታይ እየተናገሩ ያሉት ደግሞ ሌላ ነገር ነው። ይህ ጉዳይ በውስጣቸው አለመስማማት መኖሩን ነው የሚያሳየው። ዞሮ ዞሮ የእነሱ ጉዳይ የራሳቸው ነው፤ የእኛ ፓርቲም ሆነ የህዝቡም ጉዳይ አይደለም። የህዝብ ጉዳይ ያቀረበው ጥያቄ ነው። የህዝብ ጥያቄ ደግሞ የሥርዓት ለውጥ ነው። መብራት አምጣልኝ፣ ውሃ ዘርጋልኝ ወይም መልካም አስተዳደር አስፍንልኝ የሚል አይደለም። ምክንያቱም ይህን እንደማያደርግ ላለፉት 27 ዓመታት አይቶታልና። ድርጅቱም በመግለጫው የህዝብን ጥያቄ በተመለከተ የተናገረው የለም። ይህን ለማድረግም አቅም ያለው አይመስለኝም” ብለዋል።


በዚህ ሃሳብ የሚስማሙት አቶ ሙላቱ ገመቹም መግለጫውን “ጊዜያዊ ማምለጫ ነው” ብለውታል። ዘለቄታዊ መፍትሄውን በተመለከተ ሲናገሩም አፈና እንዲቆም፣ ነፃ ሚዲያ፣ ነፃ ፍ/ቤት፣ ነፃ የደህንነት ተቋም ሊገነባ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
140 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1025 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us