ለህዝብና ቤት ቆጠራ የተመደበው በጀት በቂ አይደለም

Wednesday, 03 January 2018 16:08

· የቆጠራው ጊዜ ሊራዘም ይችላል

 

 

ለአራተኛው ህዝብና ቤት ቆጠራ የተመደበው በጀት በቂ አለመሆኑን የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ አስታውቁ። የህዝብና ቤት ቆጠራውን ለማከናውን ወደ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የተመደበ መሆኑን ያመለከቱት ዋና ዳይሬክተሩ ይህም የገንዘብ መጠን ከቆጠራው መጀመሪያ እስከ ውጤቱ ይፋ እስከሚሆን ድረስ ያስፈልጋል ተብሎ የተመደበ የገንዘብ መጠን መሆኑን አስታውሰዋል።


ይህ የበጀት መጠን በፌደራል መንግስቱ በኩል የተመደበ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ቢራቱ፤ ገንዘቡ በቂ አለመሆኑን በማመልከት በዚህ ረገድ የክልሎች የገንዘብ ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል። ቆጠራው በያዝነው ዓመት በየካቲት ወር ለማካሄድ የታሰበ ሲሆን አሁን ባለው ዝግጅት ግን ተጨማሪ ጊዜ የሚያስፈልግ በመሆኑ ኤጀንሲው ጊዜው እንዲራዘም ለመንግስት ጥያቄ ያቀረበ መሆኑን አቶ ቢራቱ ጨምረው አመልክተዋል።


እንደ አቶ ቢራቱ ገለፃ እያንዳንዱ የሀገሪቱን ቀበሌና ጎጥ በቆጠራው ለመሸፈን ቆጣሪን ከመመደብና መንገድ መሪን ጭምር እስከማሰማራት ድረስ ብዙ ሊሰራ የሚገባ መሆኑን ያመለከቱት ዋና ዳይሬክተሩ በዚህ በኩል ሲታይ ከአንድ ወር በኋላ ወደ ቆጠራ መግባት አስቸጋሪ መሆኑን ገልፀዋል።


ዋና ዳይሬክተሩ ጨምረውም “ ለቆጠራው የሚደረገው ቅድመ ዝግጅት አስቀድሞ መጠናቀቅ አለበት። በቀበሌ ደረጃ ቀበሌው መንገድ መሪ መድቦ በእያንዳንዱ ጎጥና ሰፈር ሰው በመመድብ ማሰራት መቻል አለበት። ለዚህ ደግሞ ከወረዳና ቀበሌ ኃላፊዎች ጋር በተዋረድ በመነጋገር ሰፊ ሥራ መሰራት መቻል አለበት። አሁን ባለው በብዙ ቦታዎች ይህ ዝግጅት የተካሄደ ቢሆንም የሚቀሩ ቦታዎች አሉ። በመሆኑም በዚህ ሁኔታ ከአንድ ወር በኋላ ቆጠራ ማካሄድ ይቻላል ወይ ለሚለው ጉዳይ አስቸጋሪ ነው” በማለት ጊዜውን የመራዘሙን አስፈላጊነት ገልፀዋል። አክለውም “ በቀበሌና በወረዳ ደረጃ ዝግጅት ሳይደረግ፣ የእያንዳንዱ ቆጣሪና ተቆጣጣሪ ማንነት ተገምግሞ በሚገባ ሳይፈተሸ ወደ ቆጠራ መግባት አደጋ ነው። በመጨረሻም ውጤቱም ላይ ይንፀባረቃል። የበለጠ ችግር የሚመጣው ደግሞ አካባቢውን በማያሳይ መልኩ ውጤቱ ከተገለፀ ፖለቲካዊና ቴክኒካዊ አደጋ ይኖረዋል። ስለዚህ ቆጠራው በዚህ መልኩ ከመካሄዱ በፊት እነዚህ ነገሮች መስተካል አለባቸው” ብለዋል። ይህም ጉዳይ እንዲፈተሽ ጥያቄው ለመንግስት የቀረበ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተው፤ ይህንኑ ጥያቄም ተከትሎ የቆጠራው ቀን ይሸጋሸጋል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑን አቶ ቢራቱ ጨምረው አመልክተዋል።


በኤፌዲሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 108 መሰረት በሀገሪቱ የህዝብ ቆጠራ የሚከናወነው በየአስር ዓመቱ ሲሆን ከዚህ ሶስተኛው ቀደም የህዝብና ቤቶች ቆጠራ የተከናወነው በ1999 ዓ.ም ነበር። በዚህም የጊዜ ሰሌዳ መሰረት አራተኛው ዙር ቆጠራ መከናወን የነበረበት በ2009 ዓ.ም ነበር። የህዝብ ቆጠራ ኮሚሽኑ ለቆጠራው የሚያሰፈልገውን አንድ መቶ ሰማኒያ ሺህ ታብሌቶችን ግዢ በመፈፀም ለቆጣሪዎች ሥልጠና የሰጠ መሆኑ ታውቋል።

 

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
615 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1058 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us