ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ 798 ተማሪዎችን አስመረቀ

Wednesday, 03 August 2016 14:20

-    የማዕድን እና ሲቪል የመጀመሪያ ተመራቂ ኢንጂነሮችም ይገኙበታል፣

-    ግማሽ የሚጠጉ ተመራቂዎች ሴቶች ናቸው፣

 

ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ለ33 ኛ ጊዜ በዲግሪ እና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ሐምሌ 23 እና 24 ቀን 2008 ዓ.ም በአዲስአበባ እና በአዳማ ልዩ ካምፓስ አስመረቀ።

የሚድሮክ ሊቀመንበር የክብር ዶ/ር ሼህ ሙሐመድ ሁሴን ዓሊ አልዓሙዲ በተገኙበት በአዲስአበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ባለፈው ቅዳሜ ዕለት በተካሄደው የምረቃ ሥነሥርዓት ላይ በጠቅላላው 798 ተማሪዎችን ዩኒቨርሲቲው ያስመረቀ ሲሆን ከዚህ ውስጥ በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በማዕድን ምህንድስና 17 ተማሪዎችን አስመርቋል። በተጨማሪም ለዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ የሆኑ 28 ሲቪል ኢንጂነሮችን በመጀመሪያ ዲግሪ ያስመረቀ ሲሆን ሐምሌ 24 ቀን 2008 ዓ.ም ደግሞ በተመሳሳይ ሁኔታ በአዳማ ልዩ ካምፓስ 108 ተማሪዎችን በዲግሪ መርሃግብር አስመርቋል። በቀጣይ ቅዳሜ ሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም በደሴ ልዩ ካምፓስ 114 ተማሪዎችን እንደሚያስመርቅም ታውቋል። ከጠቅላላ ተመራቂዎች መካከል 48 በመቶ ያህሉ ሴቶች ናቸው።

ተማሪዎቹ  በመደበኛ፣ በማታው መርሀግብር፣ በርቀት ትምህርት የተሰጣቸውን ትምህርት ማለትም በማስተር ኦፍ ቢዝነስ አድምኒስትሬሽን፣ ኤምኤ ዲቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስ፣ ኤምኤ ቢዝነስ ኢኮኖሚክስ እንዲሁም በዲግሪ በአካውንቲንግና ፋይናንስ፣ በኢኮኖሚክስ፣ በማኔጅመንት፣ በማርኬቲንግ፣ ማኔጅመንት፣ በማኔጅመንት  ኢንፎርሜሽን ሳይንስ፣ በኮምፒውተር ሳይንስ፣ በአርክቴክቸር ኤንድ ኽርባን ፕላኒንግ፣ በሲቪል ኢንጂነሪንግ፣ በማይኒንግ ኢንጂነሪንግ፣ በሶሽዎሎጂ፣ በሶሻል አንትሮፖሎጂ፣ በክሊኒካል ነርሲንግ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው።

በተጨማሪም ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥራት ከታች ጀምሮ ለማስጠበቅ የያዘውን የረዥም ጊዜ ራዕይ ለማሳካት ከአጸደ ሕጻናት እስከ መሰናዶ ትምህርት ያለውን አጠቃላይ ትምህርት ለመስጠት ከሶስት ዓመት በፊት በተቋቋመው ዩኒቲ አካዳሚ ሲማሩ የቆዩ ተማሪዎች የቅድመ መደበኛ ትምህርታቸውን አጠናቀው ቅዳሜ ዕለት በሚሊኒየም አዳራሽ ለምረቃ በቅተዋል።

ዩኒቨርሲቲው በ2009 የትምህርት ዘመን በግብርና ዘርፍ ማለትም በእንስሳት እርባታና ቴክኖሎጂ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርትና ቴክኖሎጂ ሥርዓተ ትምህር ቀርጾ በቡራዩ ካምፓስ ለማስተማር መዘጋጀቱን ዶ/ር ብርሃኑ ሲሳይ የዩኒቨርሲቲው ቀዳሚ ምክትል ፕሬዚደንት ይፋ አድርገዋል።

የትምህርት ጥራትን መሰረት ባለው መልኩ ለማስጠበቅ ታስቦ የተከፈተው ዩኒቲ አካዳሚ በ2006 ዓ.ም በአዲስአበባ ገርጂ አካባቢ ከከፈተው የአጸደ ሕጻናት ትምህርት ቤት በተጨማሪ በ2008 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል በአዳማ ከተማ ቅርንጫፍ ከፍቶ በማስተማር ላይ እንደሚገኝ በ2009 ዓ.ም ደግሞ ዩኒቲ አካዳሚ ቁጥር 3 በቀራኒዮ አካባቢ ከፍቶ ተማሪዎችን በመመዝገብ ላይ እንደሚገኝ ዶ/ር ቡቴ ጉቱ የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚደንት አረጋግጠዋል።

የክብር ዶ/ር ሼክ ሙሐመድ ሁሴን ዓሊ አልአሙዲ በሥነሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የተማረ የሰው ኃይል በመፈለግ 25 ዓመታት እንደፈጀ አስታውሰው የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ያገኙትን ዕውቀት ሥራ ላይ በመዋል ለሀገረቻውና ለቤተሰባቸው አለኝታ እንዲሆኑ የአደራ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዶ/ር አረጋ ይርዳው ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ዩኒቨርሲቲው በኳንቲቲ ሳይሆን በኳሊቲ እንደሚያምን ይህንንም ለማረጋገጥ የተማሪዎች ብቃት ከታች ከኬጂ ጀምሮ እስከ 12ኛ ክፍል ማስረጽ እንደሚያስፈልግ፣ ይህንን የረጀም ጊዜ ራዕይ ለማሳካትም ዩኒቲ አካዳሚ ተከፍቶ በመስፋፋት ሒደት ላይ መሆኑን አስረድተዋል። የዩኒቲ የምረቃ ፕሮግራም ከሌሎች ለየት የሚለው የአጸደ ሕጻናት ተማሪዎች አብረው የሚመረቁበት ሥነሥርዓት ማካተቱ ነው ያሉት ዶ/ር አረጋ አንዲት እናት ልጇ በዚህ ዓይነት ሥነሥርዓት ሲመረቅ ደስ ይላታል፣ ለልጆቹም መነሳሳትን ይፈጥራል ብለዋል።

የግብርና ዘርፍ ትምህርት መጀመሩ ምንን ታሳቢ ያደረገ ነው በሚል ለቀረበውም ጥያቄ ሼክ ሙሐመድ በሰጡት አጭር ምላሽ በእርሻው ዘርፍ በየክልሉ ስለገባን የሰለጠነ የሰው ኃይል አፍርተን ሥራውን እንዲረከቡ ለማድረግ ተብሎ የታቀደ ነው። የእርሻ ዘርፉ እየሰፋ መጥቷል፣ ተመራቂ ወጣቶች በዚህ ዘርፍ እየገቡ ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰባቸውን ሊረዱ ይችላሉ ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ዶ/ር አረጋ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ የግብርና ትምህርቱ ሼክ ሙሐመድ አምና በሰጡት መመሪያ መሠረት ተጠንቶ ተከፈተ መሆኑን በመግለጽ የሼክ ሙሐመድ ኩባንያዎች በየጊዜው እየጨመሩና እያደጉ በመሄድ ላይ መሆናቸውን፣ አንዳንድ እንደኤልፎራ ያሉ ኩባንዎች በዘርፉ ብዙ እየሰሩ በመሆኑ ሥራውን ከሥልጠናው ጋር ለማስተሳሰር የትምህርት ክፍሉ መከፈት እንደሚረዳ ጠቁመዋል። ወደፊትም አስፈላጊነቱ እየታየ የኩባንያዎቹን የሰለጠነ የሰው ኃይል ፍላጎት ለማሟላት አዳዲስ የትምህርት ዘርፎች የሚከፈትበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ዶ/ር አረጋ ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲው በትምህርታቸው ብልጫ ያሳዩ ተማሪዎችን የሸለመ ሲሆን በየዓመቱ አርአያነት ባለው ምግባራቸው ለተመረጡ ሶስት ግለሰቦች ማለትም ለቱሪዝም አባት ተብለው የሚታወቁት አቶ ሀብተስላሴ ታፈሰ፣ ለማስታወቂያው ባለሙያ አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ፣ ዶ/ር ፈረደ በፈቃዱ በተባባሪ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የአርክቴክት እና ኸርባን ዴቨሎፕመንት መምህር የሊቀመንበሩን ዋንጫ ከሼክ ሙሐመድ እጅ ተቀብለዋል።¾

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
1079 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1021 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us