ስለ ቋንቋ መበላሸት ትንሽ እናውራ!

Wednesday, 08 March 2017 11:51

 

አንዳንድ ሰዎች በተሳሳተ አነጋገር ላይ እርማት ሲደረግ “ቋንቋ መግባቢያ ስለሆነ ሰው እንደ ፈለገ ቢናገረው ምናለበት” ሲሉ ይሰማሉ። አዎ ቋንቋ መግባቢያ ነው። ነገር ግን መግባቢያነቱ የሚሰምረው በትክክል ሲነገር ወይም ሲጻፍ ብቻ ነው። ስህተት ሆኖ ሲነገር ግን ሌላ ቢቀር ማደናገሩ አይቀርም። አንድ ምሳሌ ልጥቀስ ወሎ ውስጥ በገጠር አካባቢዎች በሁለተኛና በሦስተኛ ሰው (በርስዎና በሳቸው) መካከል የተሳሳተ አነጋገር ይሰማል። እሳቸው መጥተው ነበር ለማለት እሰዎ (እርስዎ) መጥተው ነበር እያሉ ሲያወሩ ይሰማል። ልክ በጎጃም አባባል አልበላሁም ለማለት “አልበልቸም” እንደሚለው አነጋገር መሆኑ ነው። ጎጃምኛው አለመለመዱ ነው እንጅ ስህተት አይመስለኝም። ታዲያ አንድ መንደርኛውን አነጋገር የረሳ ወሎየ ዘመዶቹ ዘንድ (ጋ) ሄዶ ሲጫወት የገጠሬው ዘመዱ “ያንዬ እስዎ ሞተው ሃዘን ላይ ሆነን” ሲለው “እረ ተው ምቸ ሞትኩ እኔ” ሲል ደነገጠ ይባላል። ያ ገጠሬው ሰው ሊል የፈለገው “ያንየ እሳቸው ሞተው ሀዘን ላይ ሆነን” ለማለት ነው። ስለዚህ ቋንቋ በትክክል ካልተነገረ ወይም ካልተጻፈ መግባባት ሳይሆን ማደናገርን ነው የሚፈጥረው-ከላይኛው ምሳሌ እንዳየነው።

ዛሬ የቋንቋ ብልሽት በብዙ መልክ ይታያል። የፈረንጅኛ ቃላት፣ ያውም የተሳሳቱ አባባሎችን ካልጨመሩ ሃሣባቸውን መግለጽ የማይችሉ የሚመስላቸው ሰዎች ብዙ ናቸው። ፋዘር፣ ማዘር፣ ፍሬንድ የሚሉት ቃላት በሰፊው ሲነገሩ ይሰማል። ሽማግሌዎችና አሮጊቶችም ፋዘር፣ ማዘር ሲሉ መሰማት ጀምሯል። ለምን ቢባል “ዘመናዊ” ለመሆን ነዋ! “አባት፣ እናት፣ ጓደኛ ካለ አንድ ሰው ስልጡን እንዳልሆነ ነው የሚታሰበው” አለኝ አንድ ወያላ ሲያብራራልኝ። ለመሆኑ ፋዘር፣ ማዘር የሚባሉት የሰንት ዓመት ሰዎች ናቸው ብዬ ስጠይቀው የሰጠኝ መልስ የሚገርም ነው። “ወንዱን ፋዘር የምንለው ትንሽ ሽበት ካወጣ ወይም ጸጉሩ ከተመለጠ ነው። ሴትዋም ሻሽ ካሠረች ያው ማዘር ነች” አለ እየሳቀ። ወያላዎች ግራንድ ፋዘር (ግራንድፓ) ወይም ግራንድ ማዘር (ግራንድማ) የሚሉትን የእንግሊዝኛ ቃላት ስለማያውቋቸው ያርባ አመትም ሆነ የሰማንያ ዓመት ሰው ያው ፋዘር ነው የሚባለው። ሴትዋም ያው ማዘር ነች። እነኝህ ፋዘር፣ ማዘር፣ ፍሬንድ የሚሉት ቃላት ትርጉሞች በሁሉም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እንደሚገኙ የሚታወቅ ነው። ቁልምጫዊ ዘይቢያቸው ሳይቀር አለ። ለምሳሌ በአማርኛ አባቴ፣ አባብዬ፣ እማማ፣ እማምዬ፣ ጓደኛዬ፣ ጓዴ ወዘተ የሚሉ ቃላት አሉ። የቅርብ ዘመድንና የቤተሰብ አባላትን በቁልምጫ ለመጥራትም ብዙ ቃላት አሉ። ታላቅ ወንድምን፣ ወይንም አጐትንም ሆነ የቅርብ ወንድ ዘመድን፣ ጋሽየ፣ ወንድምዓለም፣ ወንድምጋሼ፣ ጥላዬ ማለት እንደሚቻለው ሁሉ፣ ለሴት እህትም ወይም አክስት፣ እታለም፣ እትአበባ፣ አክስቴ ማለት ይቻላል።

ሌላው በብዛት ስህተት ሲስተናገድበት የሚታየው/የሚሰማው በግዕዝና በአማርኛ እርባታ ላይ ነው። ብዙ ሰዎች በግዕዝ በተረባው ቃል ላይ ቶች፣ ዎች ወይም ኖች በመጨመር የብዙ ብዙ አነጋገር ስህተቶችን ሲፈጽሙ ይሰማሉ። የሚከተሉትን እንመልከት!

የአማርኛ ዕርባታ (ነጠላ-ብዙ)

ሊቅ         ሊቆች

አስተማሪ    አስተማሪዎች

ሕፃን        ሕፃኖች

ቄስ          ቄሶች

መነኩሴ      መነኩሴዎች

ካህን         ካህኖች

ዲያቆን       ዲያቆኖች

ንጉሥ        ንጉሦች

እንስሳ        እንስሶች

ገዳም         ገዳሞች

ጳጳስ          ጳጳሶች

ባህታዊ        ባህታዊዎች

 የግዕዝ ዕርባታ (ብዙ)

ሊቃውንት

መምሕራን

ሕፃናት

ቀሳውስት

መነኮሳት

ካህናት

ዲያቆናት

ነገሥታት

እንስሳት

ገዳማት

ጳጳሳት

ባህታውያን

ጸያፍ ዕርባታ (የብዙ ብዙ)

ሊቃውንቶች

መምሕራኖች

ሕፃናቶች

ቀሳውስቶች

መነኮሳቶች

ካህናቶች

ዲያቆናቶች

ነገሥታቶች

እንስሳቶች

ገዳማቶች

ጳጳሳቶች

ባህታውያኖች

ባሁኑ ጊዜ በጣም ገንኖ የሚታየው ሌላው ስህተት በ ጋ እና ጋር መካከል ያለው ያጠቃቀም ውዥንብር ነው። በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል የተዘጋጀው “አማርኛ መዝገበ ቃላት” እንደሚገልጸው ጋ የሚለው ፊደል “አንድ ነገር የት እንደሚገኝ የሚያመለክት ቃል” ነው። መጽሐፉ ጠረጴዛው፣ እዚያ ነው። ጋር የሚለው ቃል ደግሞ “አብሮ” የሚለውን ሃሣብ የሚገልፅ ነው። ስለዚህ ጋ ዘንድ ሲሆን ጋር ደግሞ አብሮ ማለት ነው። ምሳሌ፣ እኔ ዛሬ ወንድሜ ጋ እሄድና ከሱ ጋር ሄደን ምሳ እንበላለን። ስለዚህ ጋ የሚለው ዘንድ ማለት ሲሆን ጋር የሚለው ቃል ግን አብሮ ማለት ነው። ለምሳሌ ስልክ ተደውሎ የት ነው ያለኸው ሲባል ወንድሜ ጋ ነኝ (ወንድሜ ዘንድ ነኝ) መሆን ነው ያለበት መልሱ። ዛሬ ግን ጋ ለማለት ጋር በማለት ውዥንብር እየተፈጠረ ነው። መጽሐፉ የት ነው ያለው? ብለህ ስትጠይቅ ከበደ ዘንድ ነው ለማለት ከበደ ጋር ነው ይልሃል። ትክክል ያልሆነ አነጋገር ነው። የቃና ቴሌቪዥን ተዋንያን ሳይቀሩ የተሳሳተውን የቋንቋ አገባብ ይዘው ጋ የሚለውን ጋር እያሉ ነው የሚያወሩት። ከአንድ ሰዓት በኋላ ወንድሜ ጋ (ቤት) እሄዳለሁ ለማለት፣ ከአንድ ሰዓት በኋላ ወንድሜ ጋር እሄዳለሁ እየተባለ ነው። ስህተት ነው።

ሌሎች በባዕድ ቋንቋዎች የምንሠራቸው አስቂኝ ስህተቶች አሉ። አንድ ልጅ አባቱ ያልሆነውን ሰው ፋዘር ወይም ዳዲ ብሎ ሊጠራው አይችልም። አንድ ጊዜ አራት ኪሎ አንድ ፈረንጅ ታክሲ ውስጥ ሆኖ ወጣቶች ከበው ገንዘብ ስጠን ለማለት ፋዘር፣ ዳዲ እያሉ ሲያስቸግሩት ደርሼ ገላግየዋለሁ። “ፋዘር ዳዲ ሞኒ ሞኒ” እያሉ በግራና በቀኝ ሲጮሁበት ፈረንጁ ተናዶ I swear I did not father any of these kids (ከነኝህ ልጆች አንዱንም እንዳላስወለድኩ እምላለሁ ነበር ያለው።) ሌላው አስቂኝ ቃል ክላስ የሚለው ነው። ሆቴል ስትገቡ እንግዳ ተቀባዩ ክፍል ይፈልጋሉ ለማለት ድፍረት በተሞላ አነጋገር ክላስ ነው የሚፈልጉት ነው የሚላችሁ። ክላስ ወይም ክላስሩም የመማሪያ ክፍል ነው እንጅ የመኝታ ክፍል አይደለም። የኛም የውጭውም ቋንቋ እንደዚህ ተዘበራርቋል።

በየቀኑ በስህተት የሚነገሩ የውጭ አገር ቋንቋዎችና ቃላት ብዙ ናቸው። አመሰግናለሁ ለማለት ቴንክዩ ወይም ታንክዩ የሚሉ ብዙ አሉ። የቋንቋው ባለቤቶች እንግሊዞች ግን ትክክለኛውን ቃል ለማውጣት ምላስን በላይኛውና በታችኛው ጥርሶቻችን መካከል ብቅ አድርጎ መልሶ ወደ ውስጥ በመሰብሰብ የሚፈጠር ድምፅ ነው ይላሉ። ያን ድምፅ በአማርኛ መጻፍ ባይቻልም ሳንክዩ ለሚለው ቃል ነው የሚቀርበው።

ባሁኑ ጊዜ ቋንቋን ከሚያበላሹ ተቋማት ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት የመገናኛ ብዙሐን ሰራተኞች በተለይ የቴሌቪዥንና የሬድዮ ጋዜጠኞች ናቸው። እጅግ በጣም ጥሩ፣ በጣም ቆንጆ የሚሉትን የአማርኛ ገላጭ ቃላት አሪፍ በሚል የአረብኛ ቃል ለውጠዋቸዋል። አገሩ ሁሉ አሪፍ፣ አሪፍ እያለ ነው። “አሁን ደግሞ “አሪፍ” ሙዚቃ እንጋብዛችኋለን” ማለት የተለመደ የሬድዮ ጣቢያ አነጋገር እየሆነ መጥቷል። ከፈረንጅ ጥገኝነት ወደ አረብ ጥገኝነት በቀላሉ እየተሽጋገርን ይመስላል። ምንም እንኳን ቋንቋ ይወራረሳል፣ ያድጋል ቢባልም የሚወራረሰውም የሚያድገውም የራስ ቋንቋ የማይገልጸውን የሚገልጹ የባዕድ ቃላት ሲገኙና በግልጽ በሥራ ላይ መዋል ሲያስፈልጋቸው ነው። ዛሬ ቀኑ፣ ዓየሩ፣ ጥሩ ነው፣ ቆንጆ ነው፣ ተወዳጅ ነው ወዘተ ለማለት ሁሉም የሚሸፈነው “አሪፍ” በሚለው ቃል ሆኗል። ቃሉ በጣም ከመወደዱ የተነሳ በረጅም ቅላጼ ነው የሚነገረው። ይህ ደግሞ የራሳችንን ቋንቋ ማሳደግ ሳይሆን ለባዕድ ቋንቋ ጥገኛ መሆንና የራስን ቋንቋ ማዳከም ነው። እንድንግባባ እኔም ቃሉን ልዋሰውና አሪፍ የጥገኝነት ባህሪ ነው ልበላችኋ!

ሰርተፊኬት የሚለው ቃል በሰፊው ተለምዶ በሬድዮና በቴሌቪዥን ሲነገር በጽሁፍም ሲቀርብ ይታያል። የቋንቋው ባለቤቶች ሰርቲፊኬት ነው የሚሉት። ስለዚህ እኛ ቃሉን በትክክል ለመጠቀም ወይ ባለቤቶቹ እንደሚሉት ሰርቴፊኬት ማለት አለብን አለዚያም በራሳችን ትርጉም የምስክር ወረቀት ማለቱ ይመረጣል። ሌላው ተመሣሣይ ችግር ያለው ፕረስ የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ነው። ቃሉ ከሕትመት ሥራ ጋር ማለት ከመጫን፣ ከማተም ጋር የተያያዘ ስለሆነ በእንግሊዝኛ ፕረስ የሚለው አነባበብ ይስማማዋል። እኛ ግን ለራሳችን የሚስማማን ፕሬስ ነው በማለት ቃሉን ከትክክለኛው አነጋገር ከፕረስ ወደ ፕሬስ ወስደነዋል። ይህ ድርጊት ምንም ምክንያታዊ አይደለም። አሁንም ሌላው ከትክክለኛ አነጋገር ወደ ተሳሳተ አባባል በልማድ የተወሰደና በስህተት እየተነገረ የምሰማው ኦሎምፒክ የሚለው ቃል ነው። ቃሉ በእንግሊዝኛ OLYMPIC (ኦሊይምፒክ) ነው። የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ለማለት OLYMPIC GAMES ነው የሚባለው። ባንድ ወቅት አንድ የስፖርት ጋዜጠኛ ኦሊይምፒክ የሚለውን ቃል ኦሎምፒክ ብሎ በስህተት አነበበው። ከዚያ ወዲህ እኛ አገር ትክክለኛው አነባበብ ተሽሮ ኦሎምፒክ ሆኖ ቀረ።

ወደ ጣልያንኛ ቋንቋ ደግሞ እንሂድ። በመኪና ላይ ከሁዋላ የሚመጡትን ተሽከርካሪዎች ለመቆጣጠር በግራና ቀኝ ያሉት መስትዋቶች በጣልያንኛ ስፔኪዮ ነው የሚባሉት። ከተጠራጠሩ የጣሊያንኛ ቋንቋን በደምብ የሚያውቅ ሰው ይጠይቁ ወይም የኢጣልያንኛ መዝገበቃላትን ይመልከቱ። በኛ አገር ግን ሕዝቡ በሙሉ ስፖኪዮ ሲል ነው የሚሰማው። ስፖኪዮ አይደለም ስፔክዮ ነው ብለህ ብታርመው ሰው ሁሉ ይስቅብሃል። ብዙዎቻችን ይበልጥ ከሚያውቁ ሰዎች ጠይቀን ከመማር ስህተታችንን ይዘን መኖር የምንመርጥ ይመስላል።

SERIES ተመሣሣይ፣ ተዛማጅ ወይም ተከታታይ ማለት ነው። Series of books ማለት ተከታታይ መጸሕፍት ማለት ነው። በቴሌቪዥን የምንሰማው ማስታወቂያ ግን SERIOUS (ሲሪየስ) of books እየተባለ ነው የሚነበበው። SERIOUS የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ደግሞ ኮስታራ፣ ቁም ነገረኛ፣ ምራቁን የዋጠ ማለት ነው። ሁለቱ የእንግሊዝኛ ቃላት አነባበባቸውም፣ ትርጉማቸውም የተለያየ ነው። አንድ ሰው አነባበቡን በትክክል የማያውቀው የባዕድ ቃል ሲገጥመው በግምት ከማንበብና መሣቂየ ከመሆን ይልቅ ያንን ቋንቋ የሚያውቀውን ሰው ጠይቆ መረዳት ወይም የዚያን ቋንቋ መዝገበ ቃላትን ማየት ያስፈልጋል።

የዘመኑን ቋንቋ በተመለከተ ሌላው አነጋጋሪ ቃል ማለት የሚለው ነው። ማለት ግልጽ ያልሆነን ሃሣብ ለማብራራት፣ ለመግለጽ የምንጠቀምበት ቃል እንደሆነ ለሆሉም ግልጽ ይመስለኛል። አንድን ቃል ከአንድ ቋንቋ ወደ ሌላ ለመተርጎም ይህ ቃል ምን ማለት ነው፣ ይህ ጽንሠ ሃሣብ ምን ማለት ነው ወዘተ እያልን በቃሉ ስንጠቀም ኖረናል። ያሁኑ አዲሱ አጠቃቀም ግን “ማለት ነው” የሚሉትን ሁለት ቃላት ትርጉም የሌላቸው ያደርጋቸዋል። አሁንም በዚህ በተሳሳተ መንገድ በቃሉ እየተኩራሩ የሚጠቀሙት ሕዝብን ማስተማር የማገባቸው የመገናኛ ብዙሐን ሰዎች ናቸው። ያሳዝናል! ጥቂት ምሳሌዎችን ልጥቀስ።

ከዜናው በኋላ ስለ ርዕሰ ጉዳዩ የተዘጋጀውን የትንተና ጽሑፍ እናቀርባለን ማለት ነው። ለዚህ አረፍተ ነገር መጨረሻ ሆነው የገቡት “ማለት ነው” የሚሉት ሁለት ቃላት ለአረፍተ ነገሩ ምንድን ነው የጨመሩለት? “ከዜናው በኋላ ስለ ርዕሰ ጉዳዩ የተዘጋጀውን የትንተና ጽሁፍ እናቀርባለን የሚለው በቂ አይደለም? ለምንድን ነው “ማለት ነው” የተባሉት ሁለት ቃላት የተጨመሩት? ሌላ ምሳሌ፣ ዘንድሮ ትምሕርቴን በደንብ ተከታትዬ የመጀመሪያ ዲግሪየን ከያዝኩ ሥራ ሳልፈልግ በቀጥታ ለሁለተኛ ዲግሪ ማለት ለማስተርስ እመዘገባለሁ ማለት ነው። አሁንም በዚህ አረፍተ ነገር የመጀመሪያው ማለት ትክክል ሲሆን መጨረሻ ላይ የገቡት “ማለት ነው” የሚሉት ሁለት ቃላት ግን ፈጽሞ አስፈላጊ አይደሉም።

የጠቃሽ አመልካች ሥራዋን እንዳታከናውን ተጽዕኖ እየደረሰባት ነው። ስለሆነም አባቴን ለማየት ወደ አገር ቤት እሄዳለሁ በማለት ትክክለኛው አነጋገር ፈንታ አባቴ ለማየት ወደ አገር ቤት እሄዳለሁ ሆኗል የዘመኑ አነጋገር። አባቴን፣ እናቴን፣ አገሬን እወዳለሁ የሚለው ትክክለኛ አነጋገር ቀርቶ አባቴ፣ እናቴ፣ አገሬ እወዳለሁ ሆኗል አሪፉ የዘመኑ አነጋገር። በዉ ካዕብና በው ሳድስ መካከል ያለው ልዩነት እየጠፋ በመሄድ ላይ ነው። በላሁ በማለት ፈንታ በላው እየተባለ ይጻፋል። ለመሆኑ ወዴት እየሄድን ነው? አደግን፣ ሠለጠንን ተባለና ፊደሎቻችንን መለየት ከማንችለበት ደረጃ ደረስን ማለት ነው?

የባዕድ ቋንቋዎችን በትክክል ለማወቅ መሞከርና በትክክል በጥቅም ላይ ማዋል ተገቢ ነው። ከራስ ቋንቋ በላይ (ለዚያውም በተሳሳተ መልኩ) ለባዕድ ቋንቋና ቃላት ጥገኛና ተገዥ መሆን ግን ጤነኛ አስተሳሰብ አይመስለኝም። አመሰግናለሁ።

* አቶ ማዕረጉ በዛብህ አንጋፋ ጋዜጠኛ ሲሆኑ፤ በአሁኑ ወቅት በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ጥናትና ምርምር ክፍል ማኔጂንግ ኤዲተር ናቸው።

Last modified on Wednesday, 08 March 2017 12:04
ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
1031 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1016 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us