አዲሱ የኢትዮ- ኤርትራ ግንኙነት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች

Wednesday, 11 July 2018 12:51

 

የኢትዮጵያና የኤርትራ የአዲሱ ምዕራፍ ግንኙነት ለሁለቱም ሀገራት ሆነ ለቀጠናው ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች አሉት። ሁለቱ ሀገራት ከተከሰተው የድንበር ጦርነት ማክተም በኋላ ለሁለት አስርት ዓመታት ሰላምም፤ ጦርነትም በሌለበት ሁኔታ ደንበራቸውን እና የግኙነት አውታሮቻቸውን ሙሉ በሙሉ ዘግተው ቆይተዋል። ይህ ሁኔታ በሀለቱም ሀገራት ህዝቦች ላይ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስን ሲያስከትል ቆይቷል። ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ፍፁም በተለየ ሁኔታ የተለየ ምዕራፍ ውስጥ የገባ መሆኑን በግልፅ የሚያሳዩ ጅምሮች እየታዩ ነው። ይህ ሁኔታ የበለጠ ግልፅ የሆነው የሰሞኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ የአስመራ ይፋዊ ጉብኝት ተከትሎ የአስመራ ህዝብ ለዶክተር አቢይ ያሳየው ልዩ አቀባበልና በጉብኝቱ ማጠቃለያ ላይም ሁለቱ ሀገራት በደረሱበት ስምምነት ያ የጦርነት ዘመን ያበቃ መሆኑን በይፋ ማሳወቃቸው ነው።

ይህ ልዩና አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ ለሁለቱ ሀገራት ሊኖረው የሚችለውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ በተመለከተ ከኢኮኖሚ አንፃር የተወሰነ መፈተሹ መልካም ነው።

መከላከያው በኢኮኖሚው ላይ የሚኖረውን ጫና የሚቀንስ መሆኑ

ሁለቱ ሀገራት ባካሄዱት ከባድ ጦርነት ከደረሰባቸው ሰብዓዊ ኪሳራና ማህበራዊ ቀውስ ባሻገር የደረሰባቸው ኢኮኖሚያዊ ክስረትም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ይፋዊ ጦርነቱ ከቆመ በርካታ ዓመታት ቢቆጠሩም ጉዳዩ በሰላም ሥምምነት ያልተቋጨ መሆኑ ሀገራቱ ውጥረት በተሞላበት የጦርነት ድባብ ውስጥ እንዲቆዩ አድርጓቸዋል። ይህ ሁኔታ አንዱ ለሌላው ስጋት ሆኖ እንዲታይ በማድረጉ ሁለቱ ሀገራት ለመከላከያ ይመድቡት የነበረው በጀት ይህንኑ ስጋት ታሳቢ ያደረገ ነበር። ሁኔታውን የበለጠ ውስብስብ ያደረገው ደግሞ የኤርትራ ፖለቲካ ከሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ፖለቲካ ጋር ከመጠላለፍ ባለፈ ሀገራቱ በኤርትራ ምድርና ባህር ዳርቻዎች ወታደራዊ ሠፈር መመስረታቸው ሌላኛው የኢትዮጵያ ፈተና ሆኖ ቆይቷል።

የተባበሩት አረብ ኤሜሬትና የጂሲሲ ሀገራት በአሰብ አካባቢ ወታደራዊ የጦር ሰፈር እየገነቡ ነው የሚለው መረጃ ከመውጣት ባለፈ ከህዳሴው ግድብ ግባታ ጋር በተያያዘ ግብፅም በአካባቢው እያንዣበበች ነው የሚለው ዜና ሲሰራጭ መቆየቱ የኢትዮጵያን የፀጥታ ሥጋት አንሮት ቆይቷል። ይህ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ መንግስትን በትጥቅ ትግል የሚፋለሙ ኃይሎችም ቢሆኑ ዋነኛ ምሽጋቸው የነበረው የኤርትራ መሬት ነበር። በተመሳሳይ መልኩ የኢትዮጵያ መንግስትም ቢሆን የኤርትራ መንግስት ተቃዋሚዎችን በማደራጀትም ሆነ በማገዝ ብሎም የወረራ ሥጋትም ጭምር በመሆን የአካባቢው ውጥረት እንዲንር አድርጎ ቆይቷል። እነዚህ አጠቃላይ ሁኔታዎች የሁለቱን ሀገራት የመከላከያ ወጪ በማናር የሀገራቱ ኢኮኖሚ ላይ ጫና እንዲፈጠር ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ሆኖም የዶክተር አቢይን ይፋዊ ጉብኝት ተከትሎ በተፈረመው የስምምነት ሰነድ ሀገራቱ የ20 ዓመቱ ውጥረትና የጦርነት ደመናን ለማስወግድ ይፋዊ መግባባት ላይ ደርሰዋል። ጦርነቱ ማክተሙንም አወጀዋል። ይህ ሂደት እስከዛሬ በነበረው ሥጋት ለመከላከያና ለፀጥታ ብሎም አንዱ መንግስት ሌላውን ለመጣል ሲያወጣው የነበረው ወጪ ወደ ልማት እንዲዞር የሚያደርገው ይሆናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የሁለቱን ሀገራት አለመግባባት በመጠቀም የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት የሆኑ ሀይሎች አጋጣሚውን ለመጠቀም ጥረት ማድረጋቸውም በአደገኛ ሥጋትነት የሚታይ ነበር። አሁን ባልታሰበ ሁኔታ የተፈጠረው መልካም ግንኙነት እነዚህን ሁሉ ሥጋቶች በማስወገድ ሁለቱ ሀገራት ሙሉ አቅማቸውን ወደ ልማት እንዲያዞሩ የሚያደርግ ይሆናል።

የጦርነት ቀጠናዎች ወደ ሰላም መንደርነት መቀየር

ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ ጦርነት ከገቡ በኋላ ባለፉት 20 ዓመታት የነበረው ዝምታ በድንበር አካባቢ ያሉ የሁለቱን ሀገራት ነዋሪዎች ክፉኛ ጎድቷል። በአካባቢው ካለው የጦርነት ሥጋት ጋር በተያያዘ የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ነዋሪዎች ማንም ከከፈለው መስዋዕትነት በላይ ከፍለዋል። ያለፉት ሁለት አስርት ዓመታት አጠቃላይ ሰላምና ጦርነት አልባ ሂደቶች በሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢዎች ምንም አይነት የልማትና የኢንቨስትመንት ሥራዎች እንዳይሰሩ በማድረጋቸው የአካባቢው ነዋሪዎችን የመልማት መብትና እድል አሳጥቶ ቆይቷል።

በዚህ ሰለባነት ከኢትዮጵያ ይልቅ የበለጠ ተጎጂ የሆነችው ኤርትራ ናት ማለት ይቻላል። ኢትዮጵያ በቆዳ ስፋቷ ከኤርትራ በብዙ እጥፍ የምትበልጥ በመሆኗ ያለፉት ዓመታት የድንበር ውጥረትና ሥጋት የኤርትራን ያህል ጉዳት አድርሶባታል ለማለት ያስቸግራል። አብዛኞቹ ከአስመራ ደቡባዊ አቅጣጫ የሚገኙ የኤርትራ ከተሞች ከጦርነት ቀጠናው ብዙም ያልራቁ መሆናቸው ሰፊው የኤርትራ የቆዳ ሽፋን በጦርነት ደመና ሥር እንዲቆይ አድርጎታል። ሆኖም አሁን የተፈጠረው የሰላም ሂደት የድንበር አካባቢ የሁለቱን ሀገራት ግዛቶች ወደ ልማት መስመር የሚከት ይሆናል።

የድንበር አካባቢ የንግድ ልውውጥ

በዓለማችን ያሉ ጎረቤታማ ሀገራት ድንበር አካበባቢ ህዝቦች የንግድ ልውውጥ ያደርጋሉ። ይህ የንግድ ልውውጥ ከራሱ ከህዝቡ ተፈጥሯዊ ግንኙነት የሚመነጭ እንጂ በመንግስታት ግንኙነት የሚቃኝ አይደለም። ይህም ሁኔታ ለድንበር አካባቢ ህዝቦች ያለው ያለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እጅግ ከፍተኛ ነው። ሆኖም ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የነበረው የኢትዮ-ኤርትራ ውጥረት የአካባቢው ህዝቦችን የዚህ እድል ተጠቃሚ የመሆን እድላቸውን ነፍጎ ቆይቷል።

ይሁንና አሁን በፕሬዝዳንት ኢሳያስና በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የተፈረመው ጦርነትን የማስወገድ ስምምነት ወደ ተግባር ሲወርድ ሁኔታዎችን ወደ በጎነት የሚቀይር ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ይህም የአካባቢውን ህዝቦች ኢኮኖሚያዊ ትስስርና ተጠቃሚነት ወደ ነበረበት የሚመልስ ይሆናል።

የአየር በረራ

የኢትዮጵያና የኤርትራን ጦርነት ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአስመራ በረራውን ካቋረጠ ሁለት አስርት ዓመታትን አስቆጥሯል። በጊዜው ኤርትራ የራሷ አየር መንገድ ያልነበራት መሆኑ በተለይ በኤርትራዊያን በኩል ከባድ ፈተናን ደቅኖ ነበር። ከዚያ በኋላ ፍላይ ዱባይን ጨምሮ የኳታር አየር መንገድ አስመራን አንዱ መዳረሻቸው በማድረግ ሲሰሩ ቆይተዋል። ይሁንና በመሀል ሁለቱም አየር መንገዶች በረራው የማያዋጣ መሆኑን በመግለፅ ያቋረጡበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

የኤርትራ መንግስት የራሱ የአየር መንገድ ቢያቋቁምም አሁን ያለው የበረራና የአቬየሽን ቴክኖሎጂ ተወዳዳሪነት አየር መንገዱ ብዙም ወደፊት እንዳይራመድ አድርጎታል። ይሁንና ሁለቱ ሀገራት መግባባት ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ ከነሀሴ 10 ቀን 2018 ጀምሮ የአስመራ በረራውን የሚጀምር መሆኑ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋዜጣዊ መግለጫ ያመለክታል።

ይህ ሁኔታ ለአየር መንገዱ እንደ አዲስ የገበያ መዳረሻ የሚቆጠር ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ የኤርትራን የአየር በረራ ክፍተት የሚሞላ ይሆናል። የኢትዮ ኤርትራን ጦርነት ተከትሎ የአካባቢው የአየር ቀጠና ከበረራ ውጪ መሆኑ የኢትዮጵያ አየር መንገድን የበረራ ጉዞ አቅጣጫ አሰቀይሮ ቆይቷል። ሆኖም አሁን የሁለቱ ሀገራት ሰላም መመለሱ አየር መንገዱ አዋጪ የሆነውን የበረራ መስመር እንዲከተል የሚያደርገው ይሆናል።

ሀገራዊ ዋጋን ከፍ የሚያደርግ መሆኑ

የኢትዮ ኤርትራ ሰላም የሁለቱን ሀገራት አለም ዓቀፋዊ ዋጋ ከፍ የሚያደርገው ይሆናል። የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሃፊን ጨምሮ፣የአሜሪካ መንግስት ብሎም የተለያዩ መንግስታት የሁለቱን ሀገራት ወደ ሰላም መምጣት በበጎነት ተቀብለውታል። መረጃዎች እንዳመለከቱት ከሆነ በኢትዮጵያ እየተፈጠረ ያለው የውስጥና የውጭ የሰላም አየር ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያቀረበችው ቦንድ ዋጋ እንዲጨምር አድርጎታል። ከዶላር አንፃር የብር ዋጋ ከፍ እያለ እንዲሄድ አድርጎታል። ይህ ሁኔታ በዚህ መልኩ ከቀጠለ የጥቁር ገበያው ዋጋ እንዲቀንስ ስለሚያደርገው የኑሮ ውድነቱን በተወሰነ ደረጃ የሚያቀለው ይሆናል። የውጭ ኢንቨስተሮችም ቢሆኑ በሁለቱ ሀገራት መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ በራስ መተማመን የሚፈጥር ይሆናል።

የአማራጭ ወደብ ጉዳይ

ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ሀገር ከሆነች በኋላ እስከ ጦርነቱ መቀስቀስ ድረስ በመጠነኛ ኪራይ የአሰብ ወደብን ስትገለገል ቆይታለች። ሆኖም የጦርነቱን መፈንዳት ተከትሎ የኢትዮጵያ የገቢ ንግድ ወደ ጂቡቲ ወደብ መዞር ግድ ብሎታል። ሆኖም የጂቡቲ ወደብ አገልግሎት እያደገ ቢሄድም የዋጋውም ሁኔታ እየናረ መሄዱ በኢትዮጵያ የገቢ ሸቀጥ ላይ የዋጋ ንረትን በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ ጫናን ሲፈጥር ቆይቷል።

ይህንንም ሁኔታ ተከትሎ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ወደቦች እስከ ፖርት ሱዳንና የኬኒያው ሞባሳ ድረስ አማራጭ ወደብን ስታፈላለግ ቆይታለች። ሁኔታዎች በሂደት ላይ ቢሆኑም አሁን ከኤርትራ ጋር የተፈጠረው ሰላም በተለይ ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብን በሚገባ እንድትጠቀም የሚያደርጋት ይሆናል። ይህም ኢትዮጵያ በጂቡቲ የተያዘባትን የወደብ ሞኖፖል በመስበር አማራጭ ወደብን እንድትጠቀም የሚያደርጋት ይሆናል። ሆኖም ሁለቱ ሀገራት ለሁለት አስርት ዓመታት ግንኙነቶቻቸውን ያቋረጡ በመሆናቸው መንገዶች ጥገናና ግንባታ ሚያስፈልጋቸው ይሆናል። የአዋሽ፣ኮምቦልቻ፣ ወልደያ ሀራ ገበያ ባቡርን ከኮምቦልቻ ተገንጥሎ ወደ አሰብ ወደብ እንዲገባ ለማድረግ ብዙም ኢንቨስትመንትን የሚጠይቅ አይሆንም። ርቀቱ በጣም አጭር ሲሆን ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ ግን እጅግ ከፍተኛ ነው።

በእርግጥ አሁን ባለው ሁኔታ የአሰብ ወደብ ይዞታ ቢሆን በግልፅ አይታወቅም። ሆንም በአጭር ጊዜም ይሁን በረዥም ጊዜ አሰብ ወደብ ለኢትዮጵያ አገልግሎት የሚሰጥ ከሆነ ለኤርትራ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ፤ለኢትዮጵያም ከጂቡቲ ብቸኛ የወደብ ጥገኝነት የሚያላቅቅ ይሆናል።

Last modified on Wednesday, 11 July 2018 13:42
ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
189 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 604 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us