ባህርዳር ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶችን አገኘች

Wednesday, 22 November 2017 12:00

 

በሀገሪቱ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ከሆኑ ከተሞች መካከል አንዷ ባህርዳር ከተማ ናት። ባህርዳር ከተማ ከቱሪስት መዳረሻነቷ ባሻገር በዙሪያዋ በርካታ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ይገኛሉ። በከተማዋ ከሰሞኑ ሁለት ተጨማሪ ግዙፍ ፋብሪካዎችን ተመርቀዋል። እነዚህ ሁለት ፋብሪካዎች የቀለምና የዕምነበረድ ፋብሪካዎች ሲሆኑ ግንባታቸው ተከናውኖ ወደ ሥራ የገቡት ቤአኤካ ጄኔራል ቢዝነስ በተባለ ኩባንያ አማካኝነት ነው።

ፋብሪካዎቹ ኮከብ ቀለም ፋብሪካና ኮከብ እብነበረድ ፋብሪካ በመባል ይታወቃሉ። ሁለቱን ፋብሪካዎች ገንብቶ ወደ ሥራ ለማስገባት በአጠቃላይ ከ 360 ሚሊዮን ብር በላይ ኢንቨስት የተደረገ መሆኑን በዕለቱ በሀላፊዎቹ ከተደረገው ገለፃ መረዳት ችለናል።

 

የፋብሪካዎቹን ግንባታ ለማጠናቀቅም 16 ወራት የፈጀ መሆኑ የተመለከተ ሲሆን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር  አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት ባለፈው እሁድ ህዳር 10 ቀን 2010 ዓ.ም ተመርቀዋል። የኩባንያው ባለቤት አቶ ካሳሁን ምስጋናውን መሬት ለኢንቨስትመንት ከወሰዱ በኋላ በአፋጣኝ ወደ ሥራ በመግባት ከሚታወቁ ጥቂት ባለሀብቶች መካከል አንዱ መሆናቸውን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለዚህም ተግባራቸው ለባለሀብቱ ምስጋናቸውን ቸረዋቸዋል።

 

ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅማቸው ወደ ማምረት ሥራ ሲገቡ ከ5 መቶ በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድልን ሊፈጠሩ የሚችሉ መሆኑ ታውቋል። ከምርት አንፃርም ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ሲገባ በዓመት 25 ሚሊዮን ሊትር ቀለምና 5 መቶ ሺህ ካሬ ሜትር ዕምነበረድ የማምረት አቅም የሚኖራቸው መሆኑ ተመልክቷል። ሁለቱ ፋብሪካዎች እርስ በእርሳቸው ተመጋጋቢ ሆነው እንዲሰሩ የተደረገ ሲሆን፤ በዚህም የቀለም ፋብሪካው 30 በመቶ ግብዓቱን ከዕምነበረድ ተረፈ ምርት እንዲጠቀም ተደርጎ ተገንብቷል። ለኩባንያው የዕብነበረድ ምርት ግብዓት የሚያገለግለው ቋጥኝ የሚገኘው በቤኒሻንጉል ክልል ልዩ ሥሙ ማንኩሽ በተባለ ቦታ ነው።

በፋብሪካው የማምረት ሂደት ውስጥ አልፈው ያለቀላቸው የእብነበረድ ምርቶች የሚሆኑት ነጭ፣ ግራጫ፣ሀምራዊ የእብነበረድ አይነቶች ናቸው። ኩባንያው እነዚህን ምርቶቹን ለወለል ንጣፍ፣ለመስኮት፣ለበር ደጃፍ ለመሳሰሉት የግንባታ ግብአቶች በሚያገለግሉ መልኩ እያዘጋጀ ለተጠቃሚዎች ያቀርባል። በቀለም ምርቱ በኩልም ሱፐር የቤትና የውጭ ግድግዳ ቀለሞችን ማይካ ውስጥና ውጭ ቀለሞችን፣ኳርትዝ ውጭና ውስጥ ቀለሞችን፣የእንጨትና ብረት ዘይት ቀለሞችን፣ቫርኒሽ፣የፈርኒቸር ማጣበቂያና የዝገት መከላከያዎች ያመርታል። ኩባንያው ለጊዜው የቀለም ምርቶቹን እያቀረበ ያለው ለባህርዳር አካባቢ ሲሆን በሂደት ግን የገበያ አድማሱን በማስፋት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ምርቶቹን ለማድረስ እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን ከማርኬቲግ ክፍሉ የተደረገልን ገለፃ ያመለክታል።

 

በባለሀብቱ አሁን ከተገነቡት ሁለት ፋብሪካዎች በተጨማሪ በባህርዳር ከተማ ሌሎች የማምረቻ ኢንዱስትሪዎችንም ለመገንባት ጥናቶች ማጠናቀቃቸው ተመልክቷል። በቀጣይ ይገነባሉ ከተባሉት ፋብሪካዎች መካከልም የግራናይትና  ቴራዞ እንደዚሁም የሴራሚክና የመስታዎት ፋብሪካዎች ይገኙበታል።

 

በቀጣይ በባለሀብቱ ይገነባሉ ተብለው የታሰቡት ፋብሪካዎች ወደ ተግባር ሲገቡ የባለሀብቱን የአማራ ክልል አጠቃላይ የኢንቨስትመንት መጠን ወደ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ያደርገዋል ተብሏል። በዚህም አምስት ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ታስቧል።

 

ባለሀብቱ አቶ ካሳሁን? ለልማት የሚሆነውን መሬት ከመንግስት ከተረከቡ በኋላ በፍጥነት ገንብተው ወደ ማምረት በመግባቱ በኩል በሞዴልነት ሊጠቀሱ የሚገባቸው ባለሀብት ናቸው ተብለው በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ምስጋና ተችሯቸዋል። ከዚህና ከክልሉ የኢንቨስትመንት መዳረሻነት ተፈላጊነት አኳያም ርዕሰ መስተዳድሩ የሚከተለውን ብለዋል፡-

 

“የክልላችንን ባለሀብቶች በተመለከተ በልበ ሙሉነት የምናገረው ክልሉ በልማት ወደፊት እንዲራመድ  እነሱ  የራሳቸው ጉዳይ ሲኖራቸው ብቻ ሳይሆን ስለክልሉ ያዩትንና የሚሰሙትን ችግር ከልብ በመነጨ እንዲሻሻልና እንዲስተካክል በማድረጉ ረገድ ባለቤት ጭምር ሆነው በመንቀሳቀስ ላይ ናቸውና፤ እኛም እናተን ባለሀብቶቻችንን ለማገልገል ሁልጊዜም ከጎናችሁ መሆናችንን ልገልፅላችሁ እወዳለሁ።” በማለት በክልሉ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ በማድረጉ ረገድ የክልሉ ባለሀብቶችና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ሰፊ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን አቶ ገዱ  በሚከተለው መልኩ በመግለፅ ምስጋናቸውን ቸረዋል።

 

“መሬት ለኢንቨስትመንት ሰጥተናቸው ምንም ጊዜ ሳያባክኑ በገቡት ቃል መሰረት ቶሎ ወደ ሥራ ገብተው ወደ ምርት ከተሸጋገሩ በጣም ጥቂት ከሆኑ ባለሀብቶች መካከል አንዱ ናቸው። አማራ ክልል ለተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በኢንቨስትመንት ተፈላጊነቱ እየጨመረ መጥቷል።

 

ኮምቦልቻ፣ደብረ ብርሃን፣ባህርዳር ደብረ ማርቆስ ጎንደር ያለው ኢንቨስትመንት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። በተለይ እንደ ባሀርዳርና ጎንደር ያሉ ቀደም ሲል በቱሪዝሙ የኢኮኖሚ ዘርፍ ይታወቁ የነበሩ ከተሞች አሁን ደግሞ በኢንዱስትሪ ልማት ያላቸው ተፈላጊነት እየጨመረ መጥቷል። በተለይ ደግሞ የአካባቢው ተወላጆችና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በዚህ ረገድ ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ናውና ሊመሰገኑ ይገባል።”

የእነዚህ ኢንቨስትመንቶች ባለቤት የሆነው ቤአኤካ ጄኔራል ቢዝነስ በበርካታ ዘርፈ ብዙ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማራ ሲሆን በ2010 ዓ.ም አጠቃላይ የኢንቨስትመንቱ መጠን 5 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተመልክቷል። በዚህም ድርጅቱ በግብርና፣በማኑፋክቸሪግ፣በኤክስፖርት-ኢምፖርት፣በኮንስትራክሽን እና በማዕድን የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማራ መሆኑን ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

 

በኤክስፖርቱ በኩል ቡና፣የቅባት እህሎችን፣ጥራጥሬን እሴት ጨምሮ በመላክ ስራ ተሰማርቷል። በኮንስትራክሽኑ በኩል  በባቡር እናሀገር አቋራጭ መንገዶች  እንደዚሁም በህንፃ ግንባታዎች በዋና ተቋራጭነትና በንዑስ ተቋራጭነት የሚሰራ ድርጅት መሆኑ ተገጿል።

 

ኩባንያው በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ያሉት ሲሆን በአዲስ አበባ ዙሪያ ታጠቅ ኢንዱስትሪ መንደር በዓመት ከ10 ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይት የማምረት አቅም ያለውን የዘይት ፋብሪካ በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል ተብሏል። ኩባንያው ከዚህም በተጨማሪ በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የፓኪንግና ኬሚካል ፋብሪካዎች ግንባታንም እያካሄደ መሆኑ   ተመልክቷል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
236 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 101 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us