ተመሳሳይ ችግሮችን የሚዘረዝረው የአዲስ አበባ ከተማ የመልካም አስተዳደር ሰነድ

Wednesday, 11 January 2017 14:09

 

በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት በከተማዋ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ አማካኝነት ከሰሞኑ አንድ ሰነድ ይፋ ሆኗል። ሰነዱ “የከተማ መልካም አስተዳደር ንቅናቄ ማቀጣጠያ ሰነድ-2” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። ከዚህ ቀደም ብሎ መሰል ሁሉን አቀፍ ሰነድ ተዘጋጅቶ የነበረ መሆኑንም በማመልከት ይህ ሰነድም ሁለተኛው ሰነድ መሆኑን ያመለክታል።

ሰነዱ በከተማዋ የሚታዩ ችግሮችን በዝርዝር ያስቀምጣል። በመሬት፣ በመኖሪያ  ቤት፣ በትራንስፖርት፣ በኮንስትራክሽን፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በፍትህና በመሳሰሉት ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ይዳስሳል። የተለመዱት ኪራይ ሰብሳቢነት፣ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የህዳሴ ጉዞ፣ ልማታዊ ሰራዊት የሚሉ አገላለፆችን በስፋት ይጠቀማል። ችግሮችንም ውስጣዊና ውጫዊ አድርጎ ይገልፃቸዋል። ሰነዱ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ በገዢው ፓርቲ ሰነዶችም ሆኑ በተለያዩ ጊዜያት የሚዘረዘሩ ችግሮቹን እየደጋገመ ዘርዝሯል። እኛም ሰነዱን በመመልከት ሁለቱን ችግሮች ለይተን በሚከተለው መልኩ አቅርበናቸዋል።

የመሬትና ግንባታ ጉዳይ

  ሰነዱ ከዳሰሳቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች መካከል አንደኛው  ከመሬት ጋር የተያያዘው ጉዳይ ነው። ከተጠቀሱት ችግሮች መካከልም የአገልግሎት ሰጪ ሰራተኞች የተገልጋዩን የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ(ካርታ) በእግድ እንዲመዘገብ ከሚመለከታቸው አካላት የተሰጠን ደብዳቤ ሆን ብሎ የመደበቅና በማህደር ላይ እንዳይታሰር ማድረግ፣ከድላላና ጉዳይ አስፈፃሚ ጋር በስልክና በአካል በመገናኘት የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱን ማበላሸትና በዚህም ያልተገባ ጥቅም ማግኘት አንዱ  ችግር ተደርጎ የሚጠቀስ መሆኑን ይሄው ሰነድ ያመለክታል።

 

ሰነዱ በሰራተኞች በኩል የሚታዩትን ጉልህ ችግሮችንም በተወሰነ ደረጃ አስቀምጧል። ከተዘረዘሩት ችግሮች መካከልም በመንግስት ቢሮና ማቴሪያል የመንግስትን የስራ ሰዓት በመጠቀም የግል ስራን መስራት እንደዚሁም መስክ ነኝ በማለት ከስራ ገበታ መቅረት በዋነኝነት ተጠቅሰዋል። አንዳንድ ሰራተኞች በአገልግሎት አሰጣጥ ሂደትም ለባለጉዳዮች “የፕላን ተቃርኖ አለው፣ መንገድ ይነካዋል፣ የድንበር ክርክር አለበት፣ ማህደሩ አልተገኘምና የመሳሰሉትን ምክንያቶችን ለባለጉዳዮች በመስጠት በማመላለስ ለድርድር የሚጋብዙበት ሁኔታ መኖሩን ሰነዱ ያትታል። የመስክ ስራን የሚሰሩ ሰራተኞች የተሸከርካሪ እጥረትን ምክንያት በማድረግ ተገልጋዮች መኪና ተከራይተው እንዲያመጡ የሚደረግበት ሁኔታ መፈጠሩን ይሄው ሰነድ ያመለክታል።

 

 የሀገሪቱ የህንፃ አዋጅ ደንብና መመሪያ አንድ ህንፃ ከተገነባ በኋላ አገልግሎት መስጠት ከመጀመሩ በፊት የመጠቀሚያ ፈቃድ ማገኝት ያለበት መሆኑን ይደነግጋል። ይህ አሰራር በህንፃ አዋጅ 624/2001 አንቀፅ 18 ቁጥር አንድ እና ሁለት፤ እንደዚሁም አዋጁን ለማስፈፀም በወጣው ደንብ ቁጥር 243/2003 አንቀፅ 16 ላይ በግልፅ ተቀምጦ ይታያል። ይሁንና የሰሞኑ ሰነድ በከተማዋ ግንባታቸው ሳይጠናቀቅ ፈቃድ ወስደው የሚያከራዩ ባለሀብቶች መኖራቸውን ያመለክታል።የመጠቀሚያ ፈቃዶቹም የሚሰጡት ከግንባታ ፈቃድ እውቅና ውጪ መሆኑን  ሰነዱ ያትታል።

 

 አንዱ መንግስት አካል ፈቃድ የሰጠበትን ሌላኛው የመንግስት አካል ወደ ማሸግ ስራ የሚገባበት አሰራር መኖሩን ሰነዱ የሚጠቁም ሲሆን ይሁንና ግንባታቸው ያልተጠናቁ ህንፃዎችን በብዛት የሚከራዩት ባንኮች በመሆናቸው ለማሸግ አስቸጋሪ ሆኖ መገኘቱን ይሄው ሰነድ ቃል በቃል ያስቀምጣል።

 

 የሀገሪቱ ህጎችም ሆኑ የህግ መርህ ግለሰቦችም ሆኑ ህጋዊ ሰውነት ያለው ማንኛውም አካል በህግ ፊት እኩል መሆኑ የህግ መርህ የሚደነግግ ቢሆንም  ይሄው የንቅናቄ “የከተማ የመልካም አስተዳደር ማቀጣጠያ ሰነድ 2” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሰነድ ግን ግንባታቸው ሳይጠናቀቅ አገልግሎት የሚሰጡ ህንፃዎችን ለማሸግ የተቸገረበት ዋነኛ ምክንያት ያላለቁትን ህንፃዎች የሚከራዩት ባንኮች ከመሆናቸው ጋር የተያያዘ መሆኑን ይገልፃል። ችግሩንም ለመቅረፍ የተደረገውን ጥረት በተመለከተ ሰነዱ የሚከተለውን ማብራሪያ ይሰጣል

 

“ግንባታቸው ሳይጠናቀቅ ፈቃድ ወስደው የሚያከራዩና ወደ አገልግሎት የሚገቡ ባለሀብቶች በመኖራቸው በህብረተሰቡ ላይ የሚደርስ ጉዳትን ለመከላከል ቀደም ሲል ለሁሉም ባንኮች ባላለቁ ህንፃዎች ላይ እንዳይከራዩ በደብዳቤ ቢገለፅም ችግሩ ባለመቀረፉ ከሚመለከተው ፈቃድ ሰጭ እና ከፌደራል ጋር በጋራ መስራት እና የመጠቀሚያ ፈቃድ ሳይወስዱ በሚያከራዩ ህንፃዎች የእርምት እርምጃ በመውሰድ ስርዓት ማስያዝ ያስፈልጋል።”

  

የህዝብ ትራንሰፖርት ችግሮች

ሌላኛው በዚህ ሰነድ በመሰረታዊ ችግርነት ከተጠቀሱት ተግዳሮቶች መካከል አንደኛው የከተማዋ ዘርፍ ነው። በአዲስ አበባ ከተማ በህዝብ ትራንስፖርት በኩል ያለው ችግር ሰር የሰደደና እስከዛሬም ድረስ ይህ ነው የሚባል መፍትሄ ያልተገኘለት ጉዳይ ነው። በአቅርቦትና ፍላጎት ካለው ሰፊ ክፍተት ባሻገር ያለውን የትራንስፖርት አቅርቦት በሚገባ ጥቅም ላይ በማዋሉ ረገድ ከአሰራር ጀምሮ መንገድን እስከመሰሉ መሰረተልማቶች ድረስ በርካታ ችግሮች ይታያሉ።

 

የህዝብ ትራንስፖርት አቅርቦትን በተመለከተ አዲስ አበባ ሰማያዊ ሚኒባስ ታክሲዎች፣ የአንበሳ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት፣ ሀይገር ባስ፣ በክልል ታርጋዎች ለከተማዋ አገልግሎት የሚሰጡ በሺ የሚቆጠሩ ሚኒባሶች፣ ቀላል የከተማ ባቡር፣ድጋፍ ሰጪ ቅጥቅጥ አውቶቡሶች፣  እንደዚሁም በመደበኛነት ለመንግስት ሰራተኞችና አልፎ አልፎም ለከተማዋ ነዋሪ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ ያሉትና ፐብሊክ ሰርቪስ  በመባል የሚታወቁት ሰማያዊ አውቶብሶች፣ በቅርቡ ዘርፉን የተቀላቀሉት ሜትር ታክሲዎችና በተለምዶ የኮንትራት ታክሲ በመባል የሚታወቁት አነስተኛ ታክሲዎች አገልግሎት እየሰጡ ቢገኙም ዛሬ በከተማዋ በየትኛውም አቅጣጫ የሚታዩ ረዣዥም የትራንስፖርት ጥበቃ ሰልፎችን መታደግ አልቻሉም።

 

ችግሩ የበለጠ እየተባባሰ ሄዶ በስራ መውጫና መግቢያ የሚታዩት ረዣዥም ሰልፎች በአሁኑ ሰዓት ቀንም ጭምር መታየት ጀምረዋል። በአሁኑ ሰዓት በመሰረታዊነት የሚታየውን የመዲናዋን ሰፊ የትራንስፖርት ፍላጎት ክፍተት በተመለከተ ግን ሰነዱ “የህዝብ ትራንስፖርት እጥረት መኖር” በሚል አንድ አረፍተ ነገር ነው ያለፈው። ከዚህ ውጪም በማስፋፊያ አካባቢዎች የህዝብ ትራንስፖርት ተደራሽነት አለመኖር፣ የአሰራርና አደረጃጀት ችግር፣ የመለዋወጫ አቅርቦት ችግር፣ ታክሲዎች ዞናዊ ስምሪትን ጠብቀው አገልገሎት የማይሰጡበት ሁኔታ መኖር፣ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሠጡ አሽከርካሪዎችን በህጉ መሰረት ከመቅጣት ይልቅ ያልተገባ ጥቅም በመቀበል የጥቅሙ ተጋሪ መሆን በዘርፉ ከተዘረዘሩት ችግሮች መካከል የተጠቀሱት ናቸው።

 

ከዚህ ውጭ ከትራንስፖርት አገልግሎት ጋር በተያያዘ የአሽከርካሪ ተሸከርካሪ አገልግሎት አሰጣጡም በጥናቱ ተዳሷል። ለአሽከርካሪዎች የሚሰጠውን አገልግሎት በተመለከተ በቢሮዎች ጥራት የሌለው የመዝገብ አያያዝ፣ ሲስተም ተበላሽቷል፣እንደዚሁም “ፋይል ጠፍቷል” በማለት ደንበኞችን ማጉላላት፣ ተሸከርካሪዎች አገልግሎት ለውጥ እንደዚሁም ለቦሎ፣ ለታርጋና ሽያጭ የተሟላ መረጃ ሳይቀርብ ወይም በፎርጅድ መረጃ የሚስተናገድበት አሰራር የተስተዋለ መሆኑም በሰነዱ ላይ ተመልክቷል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
620 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us