የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የከፍታ ተግባርና መንፈስ፣ 6ኛው የሐዲስ ዓለማየሁ የባሕል ተቋም ዓመታዊ ዓውደ ጥናት

Wednesday, 13 June 2018 13:01

ገብረክርስቶስ ኃይለሥላሴ

 

በ2004 ዓ.ም. የተቋቋመው የባሕል ጥናት ተቋሙ በዘንድሮው ጉባዔ (ከግንቦት 4 እስከ 5/2010) በዩኒቨርሲቲው አዳራሽ በድምቀትና በተጋጋለ የውይይት መንፈስ ተካሂዷል። የዚህ ዐውደ ጥናት መሪ ሐሳብ “ባሕልና ሥነ-ምግባር በኢትዮጵያ ከየት ወዴት?” የሚል ነበር። ጉዳዩ ደግሞ ለመላው ኢትዮጵያውያን የዘመኑ ዋነኛ የዜግነትና የኃላፊነት አጀንዳ መሆኑ ከልብ ይሰማኛል። በተለይም የወቅቱ የሥነ ምግባር ሁኔታ ማንንም ሰው በገለልተኛነት እንዲመለከት የሚያስችለው አይደለም። የሰው ለሰው፣ የሕብረተሰብ፣ የሥራና የምርት ክፍፍል ግንኙነቶች ከእውንነት ወደ ቀጥተኛ የእያንዳንዱ ሰብዕ የቀን ተቀን የሕይወት ምህዋር ከሆኑ አንስት ሥነ ምግባር (መልካም ግብረ ገብነት) በቀዳሚነት የሚመጣ የሰብአዊነት መለኪያ ነው።

በዓለም ላይ ያሉ ሀገራት የዜጐችን ሥነ-ምግባር (ግብረገብነት) በመገንባት የትውልድ ከትውልድ ቅብብሎሹ በዘመናት ሂደት እያደገና የበለጠ እየተገነባ እንዲሄድ መንግሥት፣ ድርጅቶችና ዋና ዋና የሕዝባዊ ተቋማት ሠፊ ጥረት ማድረጋቸው እሙን ነው። ይህ ዓቢይ ተግባር በኢትዮጵያ ጥረቱ እንኳን ከተቋረጠ ግማሽ ምዕተ ዓመት ተገባዷል። የሂደቱ ባዶነትም ከዘመኑ ለመልካም የሥነ-ምግባር ውድቀት ዳርጐናል። ይህም በእጅጉ ያሳሰበው የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የ6ኛው የሐዲስ ዓለማየሁ ባሕል ጥናት ተቋም ጉባዔ ዋነኛ አጀንዳ “የሥነ-ምግባርንም” ጉዳይ በማንሳት በበርካታ የጥናት ወረቀቶች እንዲቀርብና ሠፊ፣ ጥልቅና በኃላፊነት መንፈስ የታጀበ ውይይት እንዲደረግበት አድርጓል። የባሕል ጥናት ማዕከሉ ከዩኒቨርሲቲው የተሰጠውን የማስተባበር፣ የማዘጋጀትና የመምራት ኃላፊነትም ጥንቅቅ ባለ ተግባር በመወጣቱ ምስጋና የሚቸረው ነው።

በዐውደ ጥናቱ መርሐ-ግብር መሠረት ባሕልና ሥነ-ምግባርን በማስተሳሰር በቅድሚያ የጥናት ወቅት ያቀረቡት ሁለት አንጋፋ ምሁራን ከየራሳቸው ዕውቀት፣ ተሞክሮና አመለካከት አኳያ ኩርጥ ያሉ የመወያያ ሐሳቦችን ፈንጥቀዋል። በመጀመሪያ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ባሕልና ፍልስፍናን በአጭሩ በመገራረፍ በኢትዮጵያ ለሥነ-ምግባር መጓደል ቀዳሚ ምክንያት ያሏቸውን ነጥቦች አስምረውባቸዋል። በምልከታቸው መሠረት ራስን (ማንነትን) ማጣት፣ የተጠሪነት (ኃላፊነት) መጓደል፣ የጥፋትና የተጠያቂነት ጉዳይ ትኩረት አለመስጠት የመሳሰሉትን በአንክሮ ጠቅሰዋል። ሌላው ቀርቶ ሃይ የሚል የንስሐ አባት በተመናመነበትና በዘመኑ የሚወለዱ የክርስትና እምነት ተከታይ ልጆች 95% ስም የሚወጣላቸው የአይሁዳውያን ብቻ መሆኑ ሲታይ ሂደቱ አስጊ መሆኑን ዶ/ር ዳኛቸው ስጋታቸውን ገልፀዋል። የእጓለ ገ/ዮሐንስን “በተዋሕዶ” መክበርን ልብ አድርጐ ማንበብ ጠቃሚ እንደሚሆንም አሳስበዋል።

ጸሐፌ ተውኔት፣ ደራሲና ገጣሚ አያልነህ ሙላቱም ተመሳሳይ ጥናት አቅርበዋል። በእርሳቸው ጥናት መሠረት የሥነ-ምግባር ግንባታ ዋነኛ ተጠሪው ሕዝብ ነው። መንግሥትም ቢሆን የሥነ-ምግባር ጉዳይን በቸልታ ማየቱ አግባብ እማዳልሆነ ገልፀው በአሁኑ ዘመን የሚታየው ሥነ-ምግባር የሙስናና የአስተዳደር ብልሹነት ዋነኛ ካብ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ትውልዱ ሀገሩን አውቆ በመልካም ምግባር በመላበስ ኃላፊነት የሚሸከም ዜጋ ይሆን ዘንድ በምዕራቡም ሆነ በምሥራቁ ያሉ ታላላቅ ምሁራንን ለሥራዎቻችን ዋቢ ማድረግ ብቻውን ተገቢ እንደማይሆንና የሀገራዊ ምሁራንንም ሥራዎች መመርመር ተገቢ እንማሚሆን በአጽንኦት ገልፀዋል።

አስቀድሞ የዘመናዊ ሥርዓተ ትምህርት በሚቀረፅበት ጊዜ የሀገር በቀል ዕውቀትን መሠረት ማድረግ እንደነበረበት አመላክተው ይኸው ዋና ጉዳይ በመላላቱ ለዚህ ዘመን የኩረጃ የምርምር ሥራዎች መብዛት እንደ ምክንያትነት ሊጠቀስ መቻሉን አቶ አያልነህ በዳሰሳቸው አንፀባርቀዋል።

በእርግጥ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥርዓተ-ትምህርት በሚዘጋጅበት ጊዜ መነሻው የሀገር በቀል ዕውቀትና ክህሎት እንዲሆን በእጅጉ አምርረው የታገሉት ክቡር ሐዲስ ዓለማየሁና ክቡር እጓለ ገብረዮሐንስ መሆናቸውን ልብ ማለት ይገባል። በሁለቱም ምሁራን የቀረቡት የጥናት ወረቀቶች በትምህርት ሥርዓቱ ዘርፍ ከፊት ጀምሮ ሲያያዝ የመጣው የኩረጃ ወይም ከሌሎች ሙሉ በሙሉ የመገልበጥ አካሄድ እንዲታረም ተግተው የታገሉትን ሐዲስንና እጓለን ሁነኛ መሠረት አድርገው ማሳየት ቢችሉ ኖሮ መልካም እንደነበር ሳልጠቁም አላልፍም።

በዐውደ ጥናቱ የተነሳውን እጅግ ወቅታዊና አስፈላጊ መራሒ-ቃል በመመርኮዝ በአመዛኙ ወጣት በሆኑ ሌሎች ምሁራንም የተለያዩ ጥናቶች ቀርበው ተደምጠዋል። ሁሉም ጥናቶችና በተለይም ወጣቱ ምሁራን ልብን የሚሞሉ ጠንካሮችና ተስፋን የሚያለመልሙ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። በሐዲስ ዓለማየሁ “ፍቅር እስከ መቃብር” መጽሐፍ ውስጥ በተሳሉት አንዳንድ ገፀ-ባሕርያት የተንፀባረቁት ሥነ-ምግባራዊ ሐሳቦች ለዘመናችንም አስተምህሮ ሊውሉ እንደሚችሉ በዚሁ ጉባዔ የቀረቡ ጥናቶች ያወሳሉ። ለዚች ጽሑፌ ግን በተለይ ሕዝብን የመምራትና የማስተዳደር ኃላፊነት ያለበት ባለሥልጣን ከጊዜ ወደ ጊዜ ሥነ-ምግባሩ የመለወጡንና ያልተገባ ተግባር እንደሚሠራ የፊታውራሪ መሸሻን ባሕርይ በማስታከክ ራሳቸው ደራሲው ሐሳባቸውን የገለፁበትን ነጥብ ጠቅሻለሁ።

“ከሃያና ከሃያ አምስት ዓመት በፊት ይሠሩት የነበረውን ጀብድ፣ ይሠሩት የነበረውን ጀግንነት፣ ትናንት ወይም ዛሬ እንደ ሠሩት እየታደሰና እየተደጋገመ ሲሰሙት ከሃያ ወይም ከሃያ አምስት ዓመት በፊት በነበረው ዘመን የሚኖሩ እየመሰላቸው፣ ያለፈው ሃያ ወይም ሃያ አምስት ዓመት አቅማቸውን ሃያ ወይም ሃያ አምስት ጊዜ የቀነሰው መሆኑን ይረሱታል። አይናቸው የደከመ ጉልበታቸው የላመ ከሰባ ዓመት በላይ የሆናቸው ሽማግሌ መሆናቸውን ብዙ ጊዜ ይረሱታል። በጎልማስነታቸው ስለ ሠሩት የጀግንነት ሥራ ስለ ሠሩት ጀብድ አዝማሪው፣ አቅራሪው፣ ጎበዙ፣ ቆንጆው፣ በየበኩሉ ይዘፍነው የነበረውን፤ ባልቴቱ ሽማግሌው ያወራው የነበረውን፣ እየታደሰ እየተደጋገመ ከቀላዋጮቻቸው አፍ ሲሰሙት፣ በጎልማስነታቸው ዘመን የሚኖሩ እየመሰላቸው ከሰባ ዓመት በላይ የሆነው ሰው፣ የሠላሳ ዓመት ጎልማሳ የሚሠራውን መሥራት የማይችል መሆኑን ይረሱታል።” (ፍቅር እስከ መቃብር ገጽ 256) የዘመናችን ኃላፊዎችና ባለሥልጣናት ይህን ልብ ቢሉት የሚሻል ይሆናል።

በአጠቃላይ የዐውደ ጥናቱ ዝግጅት አቀራረብም ሆነ አካሄድ መልካም ነበር። የዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎች ከፕሬዝደንቱ ጀምሮ ከታደሙት የጉባዔ ተሳታፊዎች ጋር በመሆን አርአያነት ያለው ተግባር አከናውነዋል። የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከግቢው የሚወጣውን የመፀዳጃ ቤቶችና ሌሎች የፍሳሽ ቆሻሻወችን እያጠራ ያለበትን ፕላንት ለጉባዔው ታዳሚዎች አስጐብኝቷል። ይህም ለሌሎች ተቋማት በምሳሌነት ሊጠቀስ ይችላል። ለዩኒቨርሲቲውም አንድ የከፍታ ወይም የስኬት ጉዞ አክሎለታል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
1785 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 966 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us