የባሕል ሕግ ሥርዓታችን እስከምን?

Wednesday, 23 May 2018 14:27

-    የድራሼ ሕዝቦች የባሕል ሕግ ሥርዓት እንደ መነሻ መድረሻ

መልካሙ ተክሌ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

ጃንሆይ “ለምንወደው ሕዝባችን ይህን ሕገመንግሥት ሰጥተናል” ሲሉ በ1923 ዓመተምሕረት፤ በአልጋ ወራሽነታቸው ዘመን አውሮፓን መጎብኘታቸው ሕገመንግሥት ከነ እንግሊዝ እንዲቀዳ ምክንያት ሆነ።

በቀደሙት ጊዜያት በሀገሪቱ እንደተፃፈ ሕግ ለማጣቀሻ ይውል የነበረው ፍትሐነገሥት ይመስለኛል። ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላ በብዙ የሀገሪቱ ክፍሎች ይበልጥ ተደራሽ የነበረው ኢትዮጵያውያን አነበቡም አላነበበቡም፣ ጻፉም አልፃፉም የየአካባቢው ባሕላዊ ሕግ ሥርዓት ነበር ማለትም ይቻላል- የበለጠ ጥናት ቢጠይቅም።

ሕገመንግሥቱ ከመፃፉ ብዙ መቶ ዓመታት ጀምሮ ያሉት እኒህ ባሕላዊ ሕጎች አሁን በዘመነ ሕገመንግሥትም ይሠራሉ። ዘመናዊነት እና ሕገመንግሥት እንዲሁም አንዳንድ ሃይማኖቶች ቢጫኑአቸውም።

ከተጫነባቸው ደለል በማራገፍ ይህን ይመስላሉ፣ እንዲህ ይጠቅማሉ በማለቱ ውስጥ የኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓቶች ማዕከል የተባለ ድርጅት የበኩሉን አስተዋጽዖ እየተወጣ ለመሆኑ እስካሁን በመስኩ ካደረጋቸው ጥናቶች፣ ካዘጋጃቸው ዐውደ ጥናቶች እና ካሳተማቸው መጻሕፍት መረዳት ይቻላል።

ከእንግዲህ የሀገራችንን ፌደራላዊ ሥርዓትን ለማበልጸግ አውሮፓ አሜሪካን ብቻ የሙጥኝ አንልም የሚለው ማዕከል በጥር 2010ዓ.ም “የድራሼ ወረዳ ሕዝቦች የባሕል ሕግ ሥርዓት”  የሚል ጠብሰቅ ያለ ባለ 549 ገጽ መጽሐፍ ለንባብ አብቅቷል።

የመጽሐፉ አዘጋጅ አብዱልፈታህ አብደላህ እንደሚሉት በአሁኑ ጊዜ የሀገራችን የባሕል ሕግ ሥርዓቶች የመዘንጋት ጋሬጣ ተጋርጦባቸዋል።

ለዚህም ነው ማዕከሉ ከዚህኛው መጽሐፍ በፊት የሌሎች የሀገራችን ብሔረሰቦችን የባሕል ሕጎች በማጥናት መጻሕፍት ያሳተመው እና በዓውደጥናት እንዲሁም መሰል ስልቶች ያስተዋወቀው።

በዚህኛው መጽሐፍ የበርካታ ብሔረሰቦች መገኛ ከሆነው የደቡብ ኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ካሉት የድራሼ፣ የሞስዬ፣ ማሾሌ እና ኩሱሜ ብሔረሰቦች የባሕል ሕግ ሥርዓት ተጠንቶ መጽሐፉ ተዘጋጅቷል።

በመጽሐፉ መጀመርያ የተቃኘው የድራሼ ብሔረሰብ የባሕል ሕግ ሥርዓት ነው። የድራሼ ብሔረሰብ የሚኖረው በድራሼ ወረዳ ነው። የወረዳዋ ዋና ከተማ ጊዶሌ ስትሆን በብሔረሰቡ ተወላጆች አጠራር ከተማዋ ኪቶሌ ነች።

በዳግማዊ ምኒሊክ ዘመን የወረዳዋን አካባቢ ወደ ማዕከላዊ መንግሥት ለመመለስ ንጉሠ ነገሥቱ ያዘመቱት በብዛት የኦሮሞ ወታደሮችን ስለሆነ በአካባቢው የቦታ ስያሜና ቋንቋም ይኸው እየተንጸባረቀ ይመስላል።

የድራሼ ብሔረሰብ የባሕል ሕግ ሥርዓት “ሀልት ሁስ ድራሼ” ይባላል። የብሔረሰቡን ፍትሐብሔርን እና የወንጀል ሕጎች ተመጣጣኝ ሕጎችን ያቀፈ ነው። በ“ሀልት ሁስ ድራሼ” የብሔረሰቡ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔሀብታዊ፣ ማኅበራዊ እና ሌሎች መስተጋብሮችን ለዘመናት መርተውበታል እንደ መጽሐፉ ገለፃ። የዚህ ሕግ መሪ “ዳማ” ይባላል። ንጉሥ እንደ ማለት ነው። ታዲያ መሪ ስለሆነ እንደፈለገ መናገር የሚችል ፈላጭ ቆራጭ አይደለም። ቢናገር ይሳሳታል ተብሎ ስለሚታሰብ የሚናገርለት አፈንጉሥ “ፒሃ” ይባላል።

እኛ በዘመናዊት ኢትዮጵያ የምንኖር ዜጎች ግን የሕግ ብዛኅነትን ከውጪ ሀገራት ስንቀስም ነው የምንታየው- የሀገራችንን ባሕላዊ ሕግ እንዲህ ማጣጣም ስንችል።

ምንም እንኳ የባሕል ሕጉ አካል ነው ለማለት ባልደፍርም በድራሼ የመሬትን እርጥበት የማቆያ ባሕላዊ ሳይንስ እንዳለ በእግረመንገድ ተጠቁሟል። ዝርዝሩን ከመጽሐፉ ገጽ 107-112 ያገኛሉ።

በድራሼ ባልና ሚስት ልጆቻቸው ፊት መጣላት ክልክል ነው። የዚህ ምክንያቱ ምንድነው ብሎ ለጠየቀ ምላሹን በገጽ 117 ያገኛል። ይህን ከየቤተሰባችን አኗኗር እናዛምደውና ድራሼ ምን ያህል እንደመጠቀች እንወቅ። ያለዕድሜ ጋብቻ ክልክል መሆኑን ስንሰማ ምን እንላለን? እንዲህ የተራቀቁ ሥርዓቶች ያሉት የድራሼ ማኅበረሰብ የባሕል ሕግ ሥርዓት አደጋ ላይ ወድቋል- በዘመናዊነት እና በአንዳንድ ሃይማኖቶች።

እንደ ድራሼ ብሔረሰብ የባሕል ሕግ ሥርዓት ሁሉ ዘመን እና ሐይማኖት የተጫነው የሞስዬ ብሔረሰብ ባሕላዊ ሕግ ደግሞ “ዎካቻ” ይባላል። ከድራሼው ጋር የሚያመሳስለውም የሚያለያየውም አለ። በሞስዬ አንድ የጎሳ መሪ በሚመራው ጎሳ ውስጥ ስንት አባወራ እንዳለ ያውቃል። ግብርም በዚሁ መሠረት ይከፈላል። ለሕዝብ እና ቤት ቆጠራ፣ ለግብር ስብሰባ፣ ለሌሎች ወሳኝ ሁነቶች የተመቸ ሥርዓት ነው። በርካታ ጉዳዮች በጎሳው ስለሚፈቱም ፍትሕ ፍለጋ ርቆ መንከራተት ቀንሷል።

የእንደነዚህ አይነት የባሕል ሕጎች ተመራጭነት በሕዝቡ ውስጥ ካላቸው ተቀባይነት እና ሚና ይመነጫል። ለዚህም ነው በጊዶሌ ወረዳ ከሚኖሩት ብሔረሰቦች አብዛኞቹ የየራሳቸው የባሕል ሕግ ያላቸው።

ከነዚህም ብሔረሰቦች አንዱ የማሾሌ ብሔረሰብ ነው። የብሔረሰቡ የባሕል ሕግ “ሙጊሳ” ይባላል። ከድራሼ እና ሞስዬ አንድነትም ልዩነትም አሉት።

ማሾሌዎች በፖለቲካዊ፣ ጎሳዊ እና መደባዊ አደረጃጀቶች እንደተደራጁ በገጽ 336 ተገልጦ ይገኛል። ከዚህ ምን እናገኛለን ከተባለም በተጠቀሱት ገጾች የተጻፈውን ማንበብ የግድ ነው። ካልሆነ የብሔረሰቡን ባሕል ማጥናት አለያም የብሔረሰቡ አባል መሆንን ይጠይቃል።

እዚህ ካሉ የባሕል ሕጎች በአንዱ የሴቶችን ገላ መታጠቢያ ቦታ በግልጽ ወይ በስውር ያየ ወንድ ከባድ ቅጣት እንደሚጣልበት ይደነግጋል።

እንደማሾሌው ሁሉ የኩሱሜ ብሔረሰብ የባሕል ሕግ ሥርዓት “ሙጊሳ” ይባላል። በብሔረሰቡ የሚገኙ ስምንት ጎሳዎች ሲዳኙበት ቆይተዋል- ሃይማኖት፣ የማዕከላዊ መንግሥት መስፋፋት፣ ዘመናዊነት እና ዐረፍተዘመን ቢጫኑትም አሁን።

እዚህ ቀርቦ ይጠየቅልኝ (አኔካስዳ)፣ እቀርባለሁ (ኢንዴሃዳ)፣ አልቀርብም (አንሄኖ)፣ ወዘተ ማለት ይቻላል- በሥርዓቱ። ጥፋተኛ ተመጣጣኝ ቅጣት ተበዳይ ካሳ ያገኛል።

በሌላ በኩል የኩሱሜ ማኅበረሰብ የማገዶ እንጨት ማኅበራዊ ዋስትና አለው። በብሔረሰቡ አጠራር “ነታ” ይባላል። ይህ ማኅበራዊ ዋስትና እንዴት እንደሚከናወን፣ ለነማን እደሚከናወን፣ እነማን እንደሚያከናውኑት መዘርዘር የዚህ ጽሑፍ አላማ አይደለም። ይልቁንስ መጽሐፉን ከመጀመርያ እስከ መጨረሻ ማንበቡ ግን ጠቃሚ ነው። ሲነበብ የተገኘውን ዕውቀት የራስ አድርጎ የተገኘውን ግድፈት ለአዘጋጁ መንገርም ይቻላል።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
5280 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1090 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us