ደርዘኛው የአስማማው ኃይሉ "መራ መውጫ" ልቦለድ

Wednesday, 02 May 2018 12:51

 

ግርማ ጌታኹን (ዶ/ር)

 

ደራሲ፤ አስማማው ኃይሉ
ርእስ፤ ከደንቢያ-ጎንደር እስከ ዋሽንግተን ዲሲ
አሳታሚ፤ ደራሲው
ጊዜ እና ቦታ፤ ሂዩስተን፣ ቴክሳስ፣ 2002 ዓ.ም
ገጽ ብዛት፤ 211
ጥራዝ፤ ለስላሳ ልባስ

 

ቀዳሚ ቃል


ይህ ሒሳዊ ዳሰሳ በሚያዝያ 2002 ዓ.ም ለደራሲው በቀረበ ሒሳዊ ተማግቦ (critical feedback) ላይ የተመሠረተ ነው። ተማግቦው የተጻፈው “ከደንቢያ - ጎንደር እስከ ዋሽንግተን ዲሲ” ለንባብ በበቃ በጥቂት ወራት ውስጥ ነበር። እንዲያ በመኾኑም በዚያ ጊዜ ኹነቶች ላይ የቀረቡ አንዳንድ ትዝብቶችን ያካትታል። አስማማው ኃይሉ (ነፍስ ኄር) ዛሬ በሕይወት የሉም። ይህ ሥራቸው ግን ስማቸውን ሲያስጠራ ይኖራል፤ የርሱ ተከታይ የኾነው ቍጥር 2 እና ሌሎች የግጥም እና የታሪክ ድርሰቶቻቸውም እንዲሁ። ተማግቦው ያኔ ለደራሲው ሲቀርብ ልቦለዱ ሕጸጾቹን በሚያስወግድ ኹለተኛ ዝግጅት ይታተም ይኾናል የሚል ተስፋ ነበረኝ። ያ ተስፋ ከአስማማው ኅልፈት ጋር ያለፈ ይመስላል። የተማግቦው ነጥቦች እና አስተያየቶች ግን ልቦለዱን ባነበቡ ሰዎች እና በሌሎችም የዐማርኛ ሥነ-ጽሑፍ አፍቃሪዎች ዘንድ ሐሳብ ቀስቃሽ ይኾናሉ በማለት በሚከተለው ዳሰሳ ቀርበዋል።


አጠቃላይ
ይህ መራ መውጫ (debut) ታሪካዊ ልቦለድ እጅግ አማላይ እና ደርዘኛ ሥራ ኾኖ አግኝቼዋለኹ። ልቦለዱን ደርዘኛ ሥራ ካደረጉልኝ ነጥቦች ውስጥ የታሪኩ አማላይነት እና ርባና፣ የዋናው ገጸ-ባሕርይ (የባለገድሉ) ግዝፈት እና ተአማኒነት እንዲሁም የትረካው ቅልለት እና ቅልጥፍና ተለባሚ (noteworthy) ናቸው።

 

የታሪኩ አማላይነት እና ርባና
“ከደንቢያ-ጎንደር እስከ ዋሽንግተን ዲሲ” (ከዚህ በኋላ “ደ/ጎ/ዋ” እለዋለኹ) በ-ኢሕአፓ-መራሽ ትግል ተሳትፎ ለስደት እና ለግዞት ኑሮ በተዳረገ የአንድ ትውልድ ታሪክ ላይ እያተኰረ፣ የትውልዱን የተናጠል እና የወል የሕይወት ውጣ-ውረዶች ያሥሣል። ታሪኩን በሚጋሩ የትውልዱ አባላት ዘንድ ጐልተው የሚታዩ የአኗኗር፣ የሥነ-ልቦና፣ የወቅታዊ ፖለቲካ አተናተን፣ ወዘተ. ዝንባሌዎች ስለሚታሠሡም መጽሐፉ በኔ-ብጤው አንባቢ ዘንድ የግል እና የማኅበራዊ ሕይወቱ ነጸብራቅ እንደሚኾን ዐስባለኹ። የተጠቀሱት የትውልዱ ዝንባሌዎች በቀሪው የባሕርማዶ ኢትዮጵያዊ ማኅበረሰብ ውስጥ ልባሜ እና ዐዘኔታ (understanding and sympathy) የሚያገኙ አይመስሉም። ይህ ታሪካዊ ልቦለድ በደራሲው የራስ ተመክሮዎች እና አስተውሎዎች የጎለበቱ ስሜታዊ፣ ሥነ-አእምሯዊ እና ባሕሪያዊ አርእስተ-ነገርን በታሪኩ ውስጥ ስለሚቃኝ ስለዚያ ትውልድ ጠለቅ እና ሰፋ ያሉ ግንዛቤዎችን ለአንባቢ ያስጨብጣል ብዬ ዐስባለኹ። ዐሠሣው ምጥን እና ሚዛናዊ በመኾኑም ተአማኒ ነው።


በቅርቡ ዐሥርታት ውስጥ በየካቲቱ አብዮት ዘመን የነበረውን ወጣት ትውልድ በድፍን፣ በ-ኢሕአፓ-መራሽ ትግል የተሳተፈውን ደግሞ በተለይ፣ ሀገር አፍራሽ እና ታሪክ አርካሽ አድርጎ የመውቀስ አንዳንዴም የመኰነን አዝማሚያ ጐልቶ ይታያል። ወቀሳ እና ኵነናው የሚቀነቀነው አብዛኛውን ጊዜ ወይ በዐፄው ሥርዐት ደጋፊዎች፣ አሊያም በደርግ ሥርዐት ተጠቃሚዎች ይመስላል። በርግጥ ከነዚህ ሥርዐቶች ጋር ትውውቅ ባልነበረው፣ የዛሬው ወጣት ትውልድም ውስጥ ዐልፎ ዐልፎ ይኸው ወቀሳ እና ምሬት እንደሚደመጥ ዐስባለኹ። ታዲያ ተወቃሹ ትውልድ ከልጅነት እስከ ዕውቀት የኖረባቸውን ማኅበራዊ ሥርዐቶች ግፍ እና ፍትሕ-አልባነት፣ ከንቱ እምነት እና ኋላቀርነት የሚያሳይ ታሪካዊ የፈጠራ ሥራ ከትልሂት (entertainment) የላቀ ፋይዳ አለው፤ በሥርዐቶቹ ላይ ማመፅ ለምን አማራጭ-የለሽ ተልእኮ እንደነበር ያስገነዝባልና። በዚህ ረገድ ይህ ተአማኒ የውስጥ-ዐወቅ ትረካ ሰፋ እና ጠለቅ ያለ ዐሠሣ ባያደርግም በ“ስለሺ” የልጅነት ባህላዊ ከባቢ እና ከንቱ እምነቶች ላይ ብርሃን በመፈንጠቅ የኵነናውን ከንቱነት በተምሳሌት ያሳየ ይመስለኛል።


የገጸ-ባሕርዩ ግዝፈት
ዋናው ገጸ-ባሕርይ በተለምዶው የዐማርኛ ልቦለድ ውስጥ የሚታይ የመልክ እና የቁመና ገለጻ አልቀረበለትም። መልከ-መልካም ይኹን መልከ-ጥፉ፣ ረዥም ይኹን ዐጭር፣ ኮሳሳ ይኹን ደንዳና፣ ደንሴ ይኹን ተናጣቢ ለአንባቢ በመጀመሪያው ገጾች ላይ በቃል አልተሳለለትም። ስሙ እንኳ አልተሰጠም - የአያቱ ስም እንጂ። ይህ ግን ገጸ-ባሕሪውን ማንነት እና ምንነት አልነፈገውም፤ አንባቢ በፍናፅንስ (preconceived) ሐሳብ ምናቡ እንዳይሸበብ ረዳ እንጂ። የርሱን ምስል እና ሰብእና አንባቢው ከታሪኩ፣ ከገጠመኞቹ እና ለኹነቶች ከሚያያደርገው ዐጸፋ ቀስ-በ-ቀስ እንዲገነባ ዕድል በመስጠቱ ገጸ-ባሕርዩ ግዝፈት እና ውስብስብነት ሊጎናጸፍ የቻለ ይመስለኛል።


“ስለሺ” ከአስተሳሰቡም ኾነ ከምኞቱ ጋር በሚቃረኑ ኹኔታዎች ውስጥ ራሱን ማግኘቱ ለገጸ-ባሕሪው ግዝፈት መልካም መቼት ኾኗል። ይህ ከማርክሳዊ እና ግራ-ዘመም እምነት በፍጹም ያልተላቀቀ ወጣት ቀንደኛ ጠላቱ አድርጎ የታገለው ሀገር እና ሥርዐተ-ማኅበር ተገን ሰጥቶት መኖሩ ምቾት ይነሣዋል፤ ግን የግርመት ምንጭም ይኾነዋል። ብጤዎቹ እና የትግል ጓዶቹ ራሳቸውን ከነጩ ማኅበረሰብ በተቻላቸው መጠን አርቀው እና አግልለው ሲኖሩ፣ እርሱ ግን ስፖንሰር ኾኖ ባመጣው ነጭ ቤተሰብ ውስጥ ፍቅር እና ክብካቤ ሳይጓደልበት ለዓመታት መኖሩን እንታዘባለን። ደግሞም በርእዮትም ኾነ በአኗኗር ምርጫ ከማትጣጣመው ወጣት ሴት ጋር ሲኖር እናየዋለን። እነዚህ ትድረቶቹ (ways of life) ዘለቄታ ባይኖራቸውም፣ እጅግ ብዙ ተመክሮዎች የገበየባቸው ይኾናሉ። በነዚህ መቼቶች ውስጥ ራሱን ሲያገኝ ሕይወት በወጣትነቱ ዘመን እንዳሰበው ግልጽ እና ቀላል ምርጫዎችን የያዘ አይኾንለትም፤ በውስብስብ፣ ጠመዝማዛ እና ተዛናቂ (overlapping) ምርጫዎች የተሞላ እንጂ። በመቼቶቹ ውስጥ የነበረው መስተጋብር የራሱን ከንቱ እምነቶች (prejudices) እና አጕል ግንዛቤዎች (misconceptions) ከላዩ እየቀረፈ እንዲጥል፣ የሌሎችንም እንዲቃወም የሚያስችሉ ልዩ አስተውሎዎችን ያቀርቡለታል።


የፓርከር ቤተሰብ ድፍን ነጭ ነው፤ “ስለሺ” እስከሚዘነቅበት ድረስ (ደንቢያኛ/ጐንደርኛ ዘዬ መዋሴን ልብ ይሏል)። በዚያ ቤተሰብ ውስጥ ግን ባለቤት እና ባልተቤት የኹለቱ ዐበይት የአሜሪካ ፓርቲዎች ደጋፊዎች ኾነው ከትዳራቸው ጐን የፖለቲካ ልዩነቶቻቸውን ጠብቀው ይኖራሉ። የአደንዛዥ ዕፅ ሰለባ ኾና በለጋ ዕድሜዋ ከምትሞተው ልጃቸው ይልቅ ኹለቱ ከ“ስለሺ” ጋር ትርጕም ያለው የልጅ እና የወላጅ ዝምድና ይኖራቸዋል። ይህ ደግሞ እነርሱም ኾነ እርሱ በዕቅድ የፈጠሩት ዝምድና አይኾንም፤ በኺደት የሚገኝ እንጂ። ይህን የመካከለኛ መደብ ዐይነተኛ ነጭ ቤተሰብ - እነዳንኤል እና ሁሴን ከውጭ ዐይተው በዘረኛነት እና በጨቋኝነት የሚፈርጁት ነጭ ቤተሰብ - በአባላቱ ቍጥር ግለወጥ ባሕርያት ያቀፈ፣ የፖለቲካ እና የእምነት ልዩነቶችን አቻችሎ የያዘ ቤተሰባዊ አሐድ (family unit) ኾኖ እናገኘዋለን። ሐዘን እና ደስታ የተፈራረቁበት፣ ውድቀት እና ስኬት የጐበኙት፣ እርጅና እና አደንዛዥ ዕፅ ቀጣይነት የነሡት ቤተሰብ በመኾኑ፣ በቀለም መለያው ብቻ ዘረኛ እና ጨቋኝ አድርጎ ለመፈረጅ አይመችም። ታዲያ ደ/ጎ/ዋ “ስለሺ”ን በዚያ ነጭ ቤተሰብ ውስጥ “ዘንቆ” በማሳየት ነጭ ባልኾ ነው የአሜሪካ ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉትን ከንቱ እምነት፣ አሉታዊ አዝማሚያ እና ግልብጥ ዘረኛነት ያጋልጣል።


ሕይወት እና እውነታ እንዲህ ናቸው። ስለዚህም ነው በአሜሪካ ማኅበረሰባዊ ውስብስብ ውስጥ “ስለሺ” እና ብጤዎቹ ያላቸውን ትድረት በአማላይ ትረካ እየገለጸ እውናዊ ሥዕል የሚያቀርብልንን ደ/ጎ/ዋ ደርዘኛ ሥራ የምለው።

 

አተራረክ
ታሪኩ በጊዜ ቅደም-ተከተል አልቀረበም፤ ወደፊት እና ወደኋላ እየተመላለሰ እንጂ። ይህም አተራረኩን ዘመናዊ እና አማላይ ያደርገዋል። ታሪካዊው ልቦለድ በአንደኛ ሰው (በራስ) ትረካ መቅረቡም ግላዊ እና ውስጣዊ ስሜትን ጠለቅ ባለ ደረጃ ለመዳሰስ ይበልጥ አመችቷል እላለኹ። የ“ስለሺ” ታሪክ በኻያኛዎቹ የዕድሜ ቅጥብ ውስጥ ኾኖ በፍልሰት አሜሪካ ሲደርስ ይጀምራ ል። ስለ ልጅነቱ፣ ስለ አስተዳደጉ፣ ስለ ንሕሰት ዘመኑ ቅጥ- ሰጪዎች (moulders of his formative years) የምናውቀው በምልሰት (flashback) ነው፤ ገጠመኞቹ ዐልፎ ዐልፎ በሚቀሰቅሷቸው ያለፉ ዘመናት ትውስቶቹ ውስጥ። ለስደት እና ፍልሰት ስላበቃውም ምክንያት ለአንባቢ የሚገለጸው ቀስ-በ-ቀስ ነው።


የአተራረኩ ሌላ ዐቢይ አማላይ ታሳቢ በደንቢያ (በጐንደር) ዘዬ እና ፈሊጥ የቀረቡ የእልፍነሽ (የእናቱ) እና ሌሎች “ደንብያውያን” ምልልሶች ወይም ግላዊ መነባንቦች (monologues) ናቸው። የእኒህ ለዛ እና ጥፍጥና አንባቢን (በተለይም ከጐንደር ዐማርኛ ጋር የማይተዋወቅ ከተሜ አንባቢን) አፍነክናኪ ናቸው። የዐማርኛ አፋዊ ቋንቋ ውበት እና ሕብራምነት (colourfulness) በየአካባቢው በሚነገሩ ልይዩ (diverse) ዘዬዎች እና ፈሊጦች ይከሠታሉ። እኒህ ቀበልኛ ዘዬዎች እና ፈሊጦች በጥልቀት እና በምልአት ያልተጠኑ፣ በሥነ-ጽሑፍም ውስጥ እምብዛ ያልተወከሉ በመኾናቸው (1) በዚህ መራ መውጫ ሥራ ውስጥ ተቈጥበው እና በሥሡ ተፈንጥቀው ለሚገኙት ልዩ እኳቴ (appreciation) ይገባቸዋል እላለኹ።


ብዙ ጊዜ ችግር የሚያስከትለው ብሂል-መር (pronunciation-led) አጻጻፍ አግባብ እና ፋይዳ የሚኖረው እኒህን መሰል ቀበልኛ አገላለጾች ሲወክል ነው።
በዘዬ እና ፈሊጥ አጻጻፍ ረገድ የሚታይ ይዘት-ለቀቅነት (inconsistency) እንደ “ኈ” እና “ኰ” ያሉ ፍንጽቅ ቀለማትን (diphthongs) ይመለከታል። በሀገረሰብኛ አባባል ውስጥ ፍንጽቅ ቀለማት እጅግ ገንነው ይደመጣሉ፤ (በጐንደርም ልክ እንደ ሸዋ፣ ወሎ እና ጐጃም)። ለምሳሌ “ጐጃም”፣ “ጐንደር”፣ “ጕልበት”፣ “ጕብል” የሚሉትን ስሞች እንውሰድ። በስሞቹ ውስጥ ያሉት “ጐ” እና “ጕ” በኹሉም ሀገረሰባዊ ዐማርኛ ውስጥ ፍንጽቅ ኾነው ይደመጣሉ። በዚህ ልቦለድ ውስጥ ግን “ጎ” እና “ጉ” ተብለው ተጽፈዋል፣ የዘዬ እና ፈሊጥ አባባል ወካይ ተደርገው በተጻፉበት ቦታዎች ሳይቀር። በተመሳሳይ “ቈዳ”፣ “ቍልፍ”፣ … በከተሜኛ አጻጻፋቸው “ቆዳ”፣ “ቁልፍ”፣ … ተብለው ተሰጥተዋል። በዚህ የተነሣ የፈሊጦች እና ዘዬዎች ጽሑፋዊ ውክልና የተሟላ ሳይኾን ቀርቷል።

 

ጥቂት ስም እና ባሕርይ-ነክ ችግሮች
ከላይ እንደ ተጠቀሰው ዋናው ገጸ-ባሕርይ ስም አልተሰጠውም። ይህ ደግሞ ታስቦበት የተደረገ አይመስልም፤ በዝንጋታ እንጂ። ባለገድሉ ስም-የለሽ መኾኑ (የቤተሰቡ እና የጓዶቹ ስሞች እየተጠቀሱ) ለግዝፈቱ ስሓ ከመኾን የዘለለ ፋይዳ ይኖረው ይኾን? በበኩሌ እጠራጠራለኹ። ወዲህም ስለ ባለገድሉ ለሚደረግ ሥነ-ጽሑፋዊ ተዋሥኦ (literary discourse) ቢያንስ ቅልጥፍናን ይነሣል። በዋሽንግተን ዲሲ እንደከተሙ ጓደኞቹ “ጓዱ” ወይም እንደ ፓርከር ቤተሰብ በአያቱ ስም “ስለሺ” ማለትም አግባብ አይኾንም (በዚህ ተማግቦ ውስጥ የኋለኛውን አጠራር እንዲመቸኝ ብዬ ብጠቀምም)።


ሌላው ስም-ነክ ችግር ባለገድሉ እና የፓርከር ቤተሰብ እርስበርስ የሚጠራሩበት ስሞች ናቸው። ስፖንሰሮቹ እርሱን ከአውሮፕላን ማረፊያ ሲቀበሉ ጀምሮ እስከ ዕለታተ-ሞታቸው ድረስ “ሚስተር ስለሺ” ወይም “ስለሺ” ሲሉት፣ እርሱም ከመጀመሪያ ግንኙነታቸው እስከ መጨረሻው “ሚስተር ፓርከር” እና “ሚሲስ ፓርከር” ይላቸዋል። ይህ ግን ከመቀራረባቸው እና እንደ ወላጅ እና ልጅ ከመዛመዳቸው ጋር ስሙም አይደለም። በተለይ በአሜሪካኖች ወግ-ለቀቅ (informal) ባህል “ልጄ” የሚሉትን እና የቤት ገበናቸውን ያለምንም ገደብ የሚያዋዩትን ወጣት ሲኾን በቅጽል ወይም በቍልምጫ ስም፣ ሳይኾን ደግሞ በተጸውኦ ስም መጥራት ልማድ ይመስለኛል። በዚያው ልክም አሜሪካኖቹ የተወዳጁት/የተዛመዱት ሰው ከቤተሰብ ስም ይልቅ በመጀመሪያ ስማቸው ወይም በሚወድዱት የስማቸው ምኅጻር እንዲጠራቸው ይፈልጋሉ። ታዲያ በመጀመሪያው የግንኙነት ዕለት እንኳ ባይኾን ውሎ ዐድሮ በነዚህ የቤተሰብ አባላት መካከል እንዲህ ያለው ወግ-ለቀቅ አጠራር አለመከሠቱ የአስተውሎ ሕጸጽ ነው።


ሦስተኛ ስም-ነክ ችግር የተምታታ የስም አጠቀቀም ነው። “ስለሺ” ቤተ-መጻሕፍት ውስጥ የሚያገኛቸው የጓደኛው የዳዊት እናት “የከበደ እናት” ተብለዋል፤(ገ. 194)።
ሌላው ምቾት ነሺ ችግር በአሳዛኙ ቤተሰብ ፍጻሜ ላይ የሚከሠት የ“ስለሺ” ድርጊት ነው። የሚስተር ፓርከርን የጣት ቀለበት እና የፓርከሮችን ቤት መክፈቻዎች እወንዝ ውስጥ መጣል፣ አስደንጋጭ እና ግራ አጋቢ ድርጊት ኾኖብኛል። ይህ በብዙ ረገድ ጨዋ እና ቅን ቤተሰብ ባለመታደል የአስከፊ ዕጣ-ፈንታ ሰለባ መኾኑ በገዛ ራሱ እጅግ አሳዛኝ ነው። ታዲያ የቤተሰቡ መሪር ፍጻሜ በቂ እንዳልኾ ነ ኹሉ በ“ስለሺ” ገቢር የመታወስ እና በባለውለታነት የመታሰብ ዕድሉን ማጣት ያለበት አይመስለኝም። አንባቢም ስለ ቤተሰቡ የሚለብመውን የሥርየት ገጽታዎች (redeeming features) አላስፈለጊ በሚያስመስል ድርጊት መቋጨት ፋይዳው አይታየኝም። የዚህ ገቢር እምራ ዊ ጕልኽ ነት (symbolic significance) ምንድነው? የቤተሰቡን አሳዛኝ ፍጻሜ ማግነን? የቤተሰቡ እጅ ዐመድ-አፋሽ መኾኑን ማጕላት? “ስለሺ” ለቁሳዊ ቅርስ ግድ-የለሽ መኾኑን ማሳየት? “ስለሺ” ከነጩ ማኅበረሰብ ጋር የነበረውን ግንኙነቶች ቈርጦ ከሐበሻ ወይም ከጥቍር ብጤዎቹ ጋር መወገኑን ማሳየት? በበኩሌ የትኛውም የእምራዊው ገቢር ማጠየቂያ አሳማኝ የሚኾን አይመስለኝም፤ ከ“ስለሺ” ባሕሪ ያፈነገጠ፣ ኢምክንያታዊ ድርጊት መኾኑን የሚሸፍን አይኾንምና።


ከላይ የተሰጡት አስተያየቶች በባለሙያ ዕውቀት እና ልምድ ላይ የተመረኰዙ፣ ወይም በሥነ-ጽሑፍ ምሁራዊ መመዘኛዎች ተገምግመው በተያዙ ጭብጦች ላይ የቀረቡ ትንታኔዎች አይደሉም፤ እንደ ተራ አንባቢ የተሰቡኝን፣ ትዝብት እና ጥያቄ የቀሰቀሱብኝን የታሪኩ አላባዎች ከብዙ በጥቂቱ ያኰትኩባቸው ነጥቦች እንጂ።

 

ቋንቋ-ነክ ሐተታ
ለዚህ ዳሰሳ መሠረት የኾነው ተማግቦ በቋንቋ-ነክ አብነቶች እና ችግሮች ላይ በማትኰር ዐይነተኛ ተዋፅኦ ያደርጋል። በእላዴ-ቃላት (lexicography) ሙያ የተሰማራኹ ሰው በመኾኔ አብዛኛውን ጊዜ ትኵረቴን የሚስቡ የሥነ-ጽሑፍ አርእስተ-ነገር በቃላት እና አገባብ ዙሪያ የሚነሡ ጕዳዮች ናቸው። እንዲያ በመኾኑም ከዚህ በታች የተሰጡት አጠቃላይ የሐተታ ነጥቦች ስለ ቃላት ፍቺ እና ርባታ፣ ስለአጠቃቀማቸው እና አጻጻፋቸው በመጽሐፉ ውስጥ የታዩ ችግሮችን እና አብነቶችን ይመለከታሉ።


ለፈጠራ ሥነ-ጽሑፍ ኪነታዊ ዕሴት ዐበይት መመዘኛ ከኾኑ ቁምነገሮች ኹለቱ የጽሑፉ ቋንቋ ውበት እና ስብቅልና በመኾናቸው ይህ ዳሰሳ በነርሱ ላይ ተጨማሪ ትኵረት ያደርጋል። በቋንቋ-ነክ ጕዳዮች ዙሪያ የማነሣቸው ነጥቦች እጅግ አብዛኞቹ በዐማርኛ ሥነ-ጽሑፍ ውስጥ ጐልተው እና ተደጋግመው የሚታዩ ናቸው።

 

ተለባሚ ቃላት
በመጀመሪያ ግን ደ/ጎ/ዋ ብዙ ተለባሚ ቃላት እና ብሂሎች ያዘለ በመኾኑ ለኔ-ብጤው አላዲ-ቃላት እና የቋንቋው ተመራማሪ አማላይ ሥራ መኾኑን መግለጽ እወድዳለኹ። የተማግቦው ዐባሪ ሰነድ እኒህን ከመጽሐፉ ውስጥ ለቅሞ በኹለት ንኡሳን አርእስት አስቀምጧቸዋል። ፋይዳቸውን ለዚህ ዳሰሳ አንባቢ ለማሳየት ከቃላቱ እኒህን ልጠቍም - ህ(ሕ)ሉፍ፣ ቅራቦት እና ጥቃሞት።


ህሉፍ (ገ.12) ወይም ሕሉፍ (186) ዐዲስ ቃል ባይኾንም፣ በከተሜ ዐማርኛ እና በሥነ-ጽሑፍ ውስጥ የተለመደ አይደለም። በትግርኛ የዘወትር ቃል የመኾኑን ያኽል በጐንደርም የሚደመጥ ይኾንን? የተሰማ ሀብተ- ሚካኤል እና የደስታ ተክለ-ወልድ መዛግብተ-ቃላት አያካትቱትም። በግእዝ የቃሉ ዐምድ/ኅ-ል-ፍ/ ነውና በሥርውቃላዊ አጻጻፍ “ኅሉፍ” ቢባል ሆሄ ይጠነቅቃል። በዐማርኛ የተለመደ የቃሉ አቻ ማለፊያ ነው። ለማለፊያ መልካም ተማራጭ ይኾናል፤ በተለይ ለሥነ-ግጥም አኹኖ (poetic effect)።


በሌላ በኩል በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙት “ቅራቦት” (ገ. 188) እና “ጥቃሞት” (ገገ. 95፣ 127) ዐዳዲስ ወይም እምብዛ የማይታወቁ ቃላት ይመስላሉ። በደንቢያ እና በሌሎች የጐንደር አውራጆች የሚነገሩ ቀበልኛዎች ይኹኑ ወይም ደራሲው የፈጠሯቸው ቃላት ግልጽ አይደለም። ከዐውደ-አገባባቸው “ቅራቦት” ለአቅርቦት “ጥቃሞት” ደግሞ ለአገልግሎት እና ጠቀሜታ ተማራጭ/ተዋራሽ (alternative/synonym) መኾናቸውን መገመት ይቻላል። ቃላቱ ከ‹ቀረበ› እና ‹ጠቀመ› በቀጥታ የተመሠረቱ ናቸውና ቀልብ ይስባሉ። ‹ፍላጎት› ከ‹ፈለገ› እንደተመሠረተ ደንብ ጠብቀው ቢመሠረቱም በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ይኖራቸው ይኾን?


የደ/ጎ/ዋ ሌላው አማላይ ገጽታ በገጠር ዘዬ እና ለዛ የተከሸኑ ግልጸቶች (expressions) ናቸው። ለቅምሻ ያኽል ጥቂት ላቅርብ። የገድለኛው አባት ልጃቸው በእናቱ ተሞላቅቆ ማደጉን ለመግለጽ እንዲህ ይላሉ፤ “የመጨረሻ ልጀ ነው፤ እናቱ እስከዛሬ አልወለደችውም አርግዛው ነው የምትኖረው። …” (ገ. 25)። ገድለኛው በበኩሉ ልጅ ሳለ የታቦት አገልጋይ እንዲኾን አባቱ ያደረጉትን ጥረት ሲያስታውስ “ከቸንከሩ ተክለሃይማኖት ካህን የተበደሩ ይመስል እኔን ለመክፈል ሲዘጋጁ” (ገ. 95) ይላል ወቀሳ በሚደመጥበት ፍሬ ቃል። እርሱ ብዙ ዓመታት እባሕር ማዶ አሳልፎም የትውልድ አካባቢውን ለዛኛ ንግግር አይዘነጋም። “ፈረንጅም በቅባት ሳያርስ የሰውን ቆዳ እንደሚልጥ...” (ገ. 130) ይለናል፤ ነጮች ሐሜት አያውቁም የሚል የቀድሞ እምነቱን ከንቱነት በመገንዘብ።

 

የከተባ እና የሥርዐተ-ጽሕፈት ችግሮች
አማላዩ የፈጠራ ሥራ እጅግ ብዙ የከተባ ስሕተቶች ይታዩበታል። እንዲያ በመኾኑም ሥራው ታትሞ ከመውጣቱ በፊት የናሙና ዕትም አራሚ (proofreader) ያላየው ያስመስለዋል። በተማግቦው ዐባሪ ውስጥ የተሰጠው ዝርዝር ረዥም ነው። ከዝርዝሩ ርዝማኔ በየገጹ በአማካይ አንድ የከተባ ስሕተት እንደሚገኝ መገመት ያስችላል።


ሌላው ዐቢይ ችግር ከሥርዐተ-ጽሕፈት ይዘት-ለቀቅነት (inconsistency) ጋር የተያያዘ ችግር ነው። ብዙ ቦታዎች ላይ ይህ አጠቃላይ እና መሠረታዊ ችግር በብሂል-መር አጻጻፍ ይከሠታል። ለምሳሌ ሕወኀት (ወይም በዘመናዊ ትግርኛ አጻጻፍ ሕወሓት) የሚባለውን ስመ-ስም (acronym) እንመልከት። ስሙ ሥርዐት ባልተከተለ መንገድ ተጽፎ እናየዋለን (ህወሀት - 131፤ ሕወኅት 107፣ 110፣ 185፤ ኅወሓት -182፣ 183)። ይህ የንባብ እና የትርጕም ውዥንብር እስካላመጣ ችግር የለውም በሚል ማጠየቂያ (justification) ችላ ሊባል አይገባውም። በዘፈቀደ የመጻፍ ባህል ዐማርኛ መደበኛ ሥርዐተ-ጽሕፈት እንዳይኖረው ከማድረግ በቀር ምን ፋይዳ ይኖረዋል?


ብሂል-መር አጻጻፍ የትርጕም አሻሚነት አያስከትልም ማለትም አይቻልም። ሊያስከትል እንደሚችል ከደ/ጎ/ዋ ጥቂት ምሳሌዎችን ማየት ይበቃል። ከድምፀ-ሞክሼ ቃላት “ምሑር”ን፣ ድርብ ቀለም ካላቸው ቃላት ደግሞ “ለቀቀ”ን በአስረጅነት እንመልከት። የመጀመሪያው በቍጥር ርባታው “ምሑራን” ተብሎ ተጽፏል (ገ. 185)፤ የተማሩ የተመራመሩ ሰዎችን ለመግለጽ። “ምሑራን” ግን በቁሙ “ምሕረት ወይም ይቅርታ የተደረገላቸው” ሰዎችን የሚገልጽ ቃል ነው። የተማሩ የተመራመሩ ሰዎችን ለመግልጽ ቃሉ “ምሁራን” ተብሎ መጻፍ ነበረበት። የኹለቱ ቃላት ዐምዶች /ም-ህ-ር/ እና /ም-ሕ-ር/ የፍቺ ልዩነቶችን ያዘሉ በመኾናቸው ሥርው-ቃላዊ አጻጻፍ ሆሄዎቻቸውን ለመጠንቀቅ፣ እንዲያም ሲል እቅጭ ሐሳብን ለማስተላለፍ ያስችላል። ኹለተኛው አስረጅ (“ለቀቀ”) በቦዝ አንቀጽ ሲነገር “ለቅቀን” መኾን ሲገባው “ለቀን” ተብሎ ተጽፏል፤ (ገገ. 7፣ 169)። “ለቀን” ግን በቁሙ ከለቀቀ ይልቅ የቀን (የዕለት) ፍቺ እንዳለው ልብ ይሏል።


ለሥርዐተ-ጽሕፈት መደበኛነት ነፋጊ የምለው ብሂል-መር አጻጻፍ በሥነ-ቃል እና በሥነ-ጽሑፍ መካከል ያሉ ልዩነቶችን በቅጡ ካለመረዳት፣ ድምፀ-ሞክሼ ሆሄያት የሚያዝሏቸውንም የፍቺ ጕልኽ ነቶች (phonemic significance) ካለመገንዘብ የተከተለ ባህል ነው። ከላይ በተሰጠው ምሳሌ ውስጥ በ<ህ> እና ‹ሕ› መካከል ያሉ ታሪካዊ እና ፍቺ-ዐዘል ልዩነቶችን ያለመረዳት ችግር ነው “ምሁር” እና “ምሑር” አንዱ በሌላው ተለዋጭ ቃላት ተደርገው እንዲታዩ የሚያደፋፍረው። ድምፀ-ሞክሼ ሆሄያትን እንገደፍ ማለትም ከዚህ የግንዛቤ ሕጸጽ የሚመነጭ አስተሳሰብ ነው።

 

አጕል እና ዝንኵር አጠቃቀሞች
ደ/ጎ/ዋ በርካታ አጕል እና ዝንኵር አጠቃቀሞች (misuses and abuses) ይታዩበታል። በተማግቦው ዐባሪ ከተዘረዘሩት አላባት ጥቅም ላይ የዋሉ ቃላት እና ሐረጎች የሚከተሉትን እንመልከት።


በገጽ 78 ላይ “ሕብረ ብሔራዊ ጥንቅር” የሚል ሐረግ እናነባለን። ቃል-በ-ቃል ሲተረጐም ሐረጉ “ብሔር-ነክ የቀለሞች ስብጥር” ማለት ነው። እንዲያ በመኾኑም ሐረጉ እምብዛ ስሜት-ሰጭ አይደለም። ደራሲው “ከተለያዩ ዘውጌ ማኅበረሰቦች (ethnic communities) የመጡ አባላትን ያካተተ” ለማለት ግልጸቱን እንደተጠቀሙበት ከዐውደ-አገባቡ መገመት ይቻላል። ግምቱ ትክክል ከኾነ ከ“ሕብረ ብሔራዊ ጥንቅር” ይልቅ “ዘውገይር ስብጥር” (= multiethnic composition) የተሻለ ተማራጭ ይመስለኛል። “ዘውገይር” ከ“ዘውግ” እና “ዕይር” የተበጀ ዐዲስ ስያሜ ነው፤ በዘውግ (ethnicity) ቅይጥ መኾንን፣ (በሌላ አነጋገር የተለያዩ ዘውጌ ማኅበረሰቦች አባላት አሳታፊነትን) በቅጡ የሚገልጽ ቃል ይመስለኛል።


በገጽ 161 ላይ ደግሞ እንደ ረመጥ የሚፋጅ ስሜት ለማለት “ስሜተ-ረመጥን” ጥቅም ላይ ውሎ እናያለን። “ስሜተ-ረመጥ” ግን ቃል-በ-ቃል “የረመጥ ስሜት” ማለት ነው። ረመጥ የራሱ ስሜት የለውምና የጥምር ቃሉ አበጃጀት እንከናም ነው። እንደ ረመጥ የሚፋጅ ስሜትን ዐጠር አድርጎ ለመግለጽ “ረመጣዊ/ረመጥማ ስሜት” ማለት ተገቢ ይኾናል።


በገጽ 120 ላይ የባለገድሉ ሙታን ጓዶች አንጸባራቂ ታሪክ እንደነበራቸው ለመግለጽ “በወርቅ የተኮላ ታሪካቸውን” የሚል ሐረግ እናነባለን። በሐረጉ ውስጥ ያለው “የተኮላ” ግን ተዘንኵሯል። ተኰላ (ከተሜኛውን “ኮ” አለመምረጤን ልብ ይሏል) በቁሙ “ተሰነገለ፤ ተወለወለ፤ እንዲያብረቅረቅ ኾነ” ማለት ነው። እንግዲያስ “በወርቅ የተጻፈ አንጸባራቂ ታሪካቸውን” ማለት ሐሳቡን በእቅጩ ሊገልጽ በቻለ ነበር። ወርቅን ይኰሉታል እንጂ፤ በወርቅ አይኰሉም።


ከነዚህ በተጨማሪ እና በተለይ ሊቀ መጡ የሚገባቸው ደግሞ በአገባብ እና አሰካክ ላይ የሚታዩ ችግሮች ናቸው። ብዛታቸው በዚህ ዳሰሳ ውስጥ በጥቂቱም ቢኾን መካተታቸውን ግድ ይላል። በዚህ ርእሰ-ነገር ላይ ከሚያተኵረው ከዐባሪው ሰነድ አንድ ንኡስ ክፍል የሚከተሉትን በአስረጅነት እንመልከት።


1. ጠጅ፣ አረቄና ጠላ እየጠመቅን … ተለምዶን አስፋፍተናል። (ገ.7)
  1ሀ. ጠጅ እየጣልን፣ አረቄ እያወጣን፣ ጠላ እየጠመቅን … ሱሰኛነትን አስፋፍተናል።
2. ፊቷ ወደ ሳንባነት ይቀየርና (ገ.22)
  2ሀ. የፊቷ ቀለም በለዲ ይኾንና

  2ለ. የፊቷ ቀለም የሳንባ ይመስልና
3. ገላውን ሰዶና ዘና ብሎ የሚዝናናው ተዝናኚ ብዛት (ገ. 83)
  3ሀ. ገላውን ሰድዶ የሚዝናና ታዳሚ ብዛት
4. የቡና ተርቲም … ያንድ ሰሞን ዜና ሆኖ ይባጃል። (ገ. 157)
  4ሀ. በየቡናው ተርቲም … ያንድ ሰሞን ርእሰ-ነገር ይኾናል።

ከላይ ከአንድ እስከ አራት የተሰጡት ዐረፍተ-ነገሮች እና ሐረጎች ከመጽሐፉ የተቀዱ ናቸው፤ ከገጽ ማጣቀሻዎቻቸው ጋር ቀርበዋል። የአገባብ እና የቃላት ምርጫ ችግሮቻቸውን ከግርጌዎቻቸው ከተሰጡት ተማራጮች (1ሀ - 4ሀ) ጋር በማነጻጸር መገንዘብ አያዳግትም። ሦስተኛውን ምሳሌ ቀረብ አድርገን ብናየው የአሰካክ ብቻ ሳይኾን የድግግሞሽ ችግሮቹን እንታዘባለን። ንኡስ ሐረጎችን በያዘው በዚህ ሐረግ ውስጥ “ሰባት ቃላት” ሲኖሩ፣ ሦስቱ የ“ተዝናና” ርባታዎች ናቸው። በዚህ ላይ “ገላውን ሰዶ” የሚለው ቦዛዊ ሐረግ ሲጨመር የድግግሞሹን አለቅጥ መብዛት እንረዳለን፤ እርሱም የመዝናናት ፍቺን ያዘለ ነውና። የአራተኛው ምሳሌ ክፍል የኾነው “ያንድ ሰሞን ዜና ሆኖ ይባጃል” ደግሞ ውስጣዊ አለመመጣጠን ወይም አለመደጋገፍ የሚታይበት ንኡስ ዐረፍተ-ነገር ነው። የተሰጠው ጊዜ “አንድ ሰሞን” ነው። ታዲያ ለሰሞን ቈይታ የሚመጥን ቃል “ሰነበተ” እንጂ “ባጀ” አይደለም። መባጀት የበጋን ቈይታ የሚገልጽ ቃል ነው። በጋን ይባጇል፤ ክረምትን ይከርሟል፤ ሰሞንን ይሰነብቷል። በቃላት ምርጫም ረገድ ከ“ዜና” ይልቅ ርእሰ-ነገር (topic) ለዐውደ-አገባቡ የተሻለ ምርጫ ይመስላል። ዜናን እንደ ትኵስ ወሬ ብንወስደው፣ ብርቅነቱ/ትኵስነቱ የሚሰነባብት አይደለምና።


እኒህን መሰል ችግሮች በአፋዊ ዐማርኛ ውስጥ ዘወትር ይደመጣሉ። በአፋዊ ቋንቋ የሚደመጡትን ያለምንም ማረቂያ በጽሑፍ ቋንቋ ውስጥ መጠቀም ግን ተገቢ አይደለም፤ (ለኪናዊ ፋይዳ ካልኾ ነ በቀር)። ኹለተኛውን ምሳሌ በንግግር መልክ ብናዳምጥ፣ የሰው ፊት ወደ ሳንባ እንደማይቀየር በማወቅ ደራሲው “የፊቷ ቀለም የሳንባ ቀለም እንደመሰለ” ለመግለጽ መፈለጉን እንገምታለን። ግን ደራሲው የኋለኛውን ግልጸት ለመጠቀም ምን የሚያግደው ነገር ነበር? ሐሳብ በንግግር ሲገለጽ ለቃላት ምርጫ፣ ለአገባብ ስኬት ወይም ለሰዋስው ርታታ ፋታ አይገኝ ይኾናል። ያንኑ ሐሳብ በጽሑፍ ለመግለጽ ግን እንዴት ፋታ ይታጣል፣ ያውም ሥነ-ጥበባዊ ዕሴትን ቀዳማው (objective) ለሚያደርግ ሥራ?

 

መደምደሚያ
ደ/ጎ/ዋ በ-ኢሕአፓ-መራሽ ትግል ተሳትፎ ወደ ሰሜን አሜሪካ ስለፈለሰ አንድ ትውልድ ማለፊያ ሥዕል የሚያቀርብ ደርዘኛ ልቦለድ ነው። በ80ኛዎቹ እና በ90ኛዎቹ ጎርጎሮሳዊ ዐሥርታት የዚህ ፈልሶ-መጤ ወገን ትድረት ምን ይመስል እንደነበር ለማሳየት አንድ ሓብሮት (painting) ያቀርብልናል። ፈልሶ-መጤው ከባዕድ ሀገር እና ከዐዲስ ማኅበረሰብ ጋር ለመጣወር ያደረገውን (ወይም ሳያደርግ የቀረውን) ጥረት፣ በትግል ታሪኩ ላይ የተከሠቱ የአተያይ ልዩነቶችን ለማስተናገድ የተጠቀመበትን ዘዴ፣ በልምድ እና በባህል ዳራ ከማይመስሉት ሌሎች የትውልድ ሀገሩ ሰዎች ጋር ለመተሳሰር ያደረገውን ሙከራ፣ ወዘተ. የሚያሳይ ሓብሮት ነው። ባለመታደል ምስሉ እንከን-የለሽ አይደለም፤ በብሩሹ ጥራት ማነስ የተነሣ መስመሮች ደብዝዘው፣ ቀለሞች ተዛልቀው ፍጽምና ነሥተውታልና።


-አበቃ-
22 ግንቦት 2009 ዓ.ም

ዶ/ር ግርማ ጌታኹን በብሪቲሽ አካዳሚ የታተመውን ‹The Gojjam Chronicles› የሚለውን ሥራቸውን ጨምሮ፣ “የጐጃም ትውልድ በሙሉ ከአባይ እስከ አባይ”፣ “የ-ግይጌ ማከያ መዝገበ-ቃላት” እና ሌሎች በርካታ የምርምር ሥራዎችን የጻፉ [እና ያሰናኙ] ባለሙያ ናቸው።
(www.facebook.com/TheBlackLionAfrica)¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
7487 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1053 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us