የታሪካዊ ተውኔቶች አስፈላጊነት፤

Wednesday, 18 April 2018 12:53

 

- ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ እንደ አብነት

 

መብራቱ በላቸው

 

ፈር መያዣ


የታሪክ ልኂቃን ስለ ታሪክ ሲናገሩ፣ “ታሪክ ስለሰው ልጆች እና ማኅበረሰቡ በብዙ ዓመታት ያመጣቸውን ለውጦች እንዲሁም ባለፉት ዓመታት ስለነበሩ ዕድገቶች ያጠናል። ያለው እንዲሻሻል እና ጥሩ ተስፋን ለመገንባት አሁን ያለው ትውልድ ያለፈውን ማወቅ አለበት፤” ሲሉ ያስረዳሉ። ያለፈውን በወጉ የሰነደና ያጠና አገር ደግሞ የወደፊቱን በሥርዓቱ ማየት ይችላል። ታሪካዊ ተውኔት እነዚህን ታሪካዊ ሁነቶች ማሳያና ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፊያ ሁነኛ መንገድ ነው።


ቴዎድሮስ ገብሬ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ በ2003 ባሳተመው የፀጋዬ ገብረመድኅን ታሪካዊ ተውኔቶች መግቢያ 1 ላይ “ታሪካዊ ተውኔት፣ ታሪክ እና ሥነ ጽሑፍ ብለን የምንጠራቸው የሁለት ሙያዎች ማደሪያ ነው። የሁለት ሙያዎች ማደሪያነቱ ለስልቱ ከታሪክና ከሥነ ጽሑፍ ጥበብ የሚከፈሉ መንታ ባሕሪያትን ሲያስገኝለት፤ ባለመንታ ባሕርይነቱ ደግሞ በምላሹ ድርሰቱን ከሁለቱም ዘርፎች የሚሰምሩ መንታ ሙያዎች ይኖሩት ዘንድ ያስችለዋል፤” በማለት የታሪካዊ ተውኔት ከሥነ ጽሑፍና ታሪክ ዘርፎች የተቀናጀና የሰመረ ጥበብ እንደሆነ ያስረዳል። አንድ አገር እነዚህን መንታ ሙያዎች ባግባቡ ተጠቅማ ያላትን ታሪክ በማበልፀግ፣ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ከቻለች ማንነቱን የተረዳና ያወቀ ትውልድ እንዲኖራት ያስችላታል ተብሎ ይታመናል።


ኢትዮጵያ ባለብዙ ታሪክ አገር እንደሆነች ይነገራል። የሚያግባቡንንና የእኛነታችን መገለጫ የሆኑ፣ ለትውልዱ አርዓያነት ያላቸው፣ ለሌላው ዓለምና ለሰው ልጆች ተምሳሌት የሚሆኑ አስደናቂ ትውፊቶችና ታሪክ ባለቤቶች ሆነን እነዚህን ታሪኮችና ትውፊቶች በአግባቡ በሥነ ጽሑፎቻችንና ቲያትሮቻችን ማሳየት ስለምን ተሳነን? ትያትር ቤቶቻችን እንደ ሥማቸው የአገርን ፍቅርና የብሔራዊ ኩራት የሆኑ ሥራዎችን መሥራትና ማሳየት ስለምን ተሳናቸው? የሚሉትን ጥያቄዎች በማንሳት እና ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስን የአንድ ባለታሪክ ተምሳሌት በማድረግ ምን ይሻላል? የሚለውን ለመጠቆም እሞክራለሁ።

 

ታሪካዊ ተውኔት ለምን?


ከትያትር ውልደት ጀምሮ ሲመደረኩ የነበሩ ተውኔቶች በተረትና አፈታሪክ በሚታወቁ ትወናዎች ላይ መሠረት ያደረጉ የአማልክት ታሪኮች ነበሩ። ለዚህም ነው ታሪካዊ ተውኔት ቀደምት የተውኔት ዘርፍ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች የሚናገሩት። ታሪካዊ ተውኔት ታሪክን በፈጠራ ሥራ አጅቦ መተረኪያ አንዱ መንገድ እንጂ በራሱ ታሪክ አይደለም። ይኹን እንጂ ታሪካዊ ተውኔት ትረካውን መሠረት የሚያደርገው በተሠራ ታሪክ ላይ ነው። ነገር ግን የሙያው ባለቤቶች እንደሚያስረዱት “ታሪካዊ ተውኔት መነሻውን ያለፈ ሁነት ላይ መሠረት ስላደረገ ብቻ ታሪካዊ ተውኔት ነው ማለት አይቻልም። ይልቁንስ በዘመኑ ትውልድ ወይም ማኅበረሰቡ ራሱ ታሪክ ናቸው ብሎ ባሰፈራቸው ጉዳዩች ወይም ታሪክ ሠርቷል ብሎ ባመነባቸው ሰዎች ዙሪያ የሚሽከረከር መሆን አለበት። በተጨማሪም ሁነቱ በራሱ ታሪክ ስለመሆኑ ሊረጋገጥ ይገባል፤” በማለት፣ አቶ ተስፋዬ እሸቱ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቲያትር ጥበባት ትምህርት ክፍል በ2000 የሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን በሠሩበት ጥናት ላይ ያስረዳሉ።


በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ታሪክ ተብሎ የተመዘገበን ሁነት መሠረት አድርጎ የሚሠራ ታሪካዊ ተውኔት የራሱ የሆነ ዓላማ ይኖረዋል። ምክንያቱም የሚነግረን አንዳች ዓላማ ያለው ጉዳይ ከሌለው ተመልካችም አይታደምም። ለዚህም ነው ተፈሪ ዓለሙ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ በ2003 ባሳተመው የፀጋዬ ገብረመድኅን ታሪካዊ ተውኔቶች መግቢያ 2 ላይ “…ለዛሬ ዘመን እንዲፈጠር የተጠራው ታሪካዊ ድርጊትም ሆነ ታሪካዊ ሰው ምንም ነገር ላይነግረን አይመጣም። የሚነግረን ወይም የምንጨዋወተው ጉዳይ ከሌለ እኛም አንታደምለትም። በኪናዊ ተውህቦው እያዝናናን ያስቆጨናል፤ ያበሽቀናል፤ ያበረታናል፤ ‹ይኼም ነበር ለካ?!› ያሰኘናል። በዚህም አለ በዚያ ለዛሬ ቁባችን አንዳች የሚለው ነገር አለው፤” በማለት ታሪካዊ ተውኔት ታዳሚው ለሚገኝበት ዘመን ፋይዳ ያለው ነገር የያዘ እንደሆነ በአፅንዖት የሚነግረን።


ተስፋዬ እሸቱ ከላይ በጠቀስኩት ጥናታዊ ጽሑፉ ላይ የተላያዩ የዘርፉ ባለሙያዎች የታሪክ ክስተቶች ደራሲያን ወደ ተውኔት የሚለውጡባቸው ዋነኛ ምክንያታቸውንና በሥራቸው ማስተላለፍ ስለሚፈልጉት መልዕክት ዳሰሳ አድርጓል። በዚህ ዳሰሳ መሠረት ተሻለ አሰፋ በመመረቂያ ጹሑፉቸው “በመረጡት ታሪክ ውስጥ ገድል ሠርተው ያለፉትን ለማስተዋወቅና ከእነርሱ ትምህርት ለመማር፣ ባለፉት የታሪክ ዘመናት ውስጥ የተፈፀሙ ስህተቶች ካሉ በማንሳት በወቅቱ ምን ዓይነት ተፅዕኖ እንዳሳረፉ ለማሳየት፣ ካለፈው ታሪክ በመማር ለመጭው ትውልድ እንደ ምክር እንዲያገለግል፣ ወደፊት ለአገራቸው በጎ ለመሥራት ለሚሹ አዲስና ታዳጊዎች ተሞክሯቸውን ለማካፈል” የሚሉትን እንደ ዋነኛ ምክንያት ያስቀምጣሉ።


ግርማቸው ተ/ሐዋርያት ስለ የአድዋ ታሪካዊ ድራማ ዓላማ ሲያስረዱ “…በታሪክ ላይ በማተኮሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም ወጣቱ ትውልድ በቀድሞ አባቶቹ ጀግንነትና በልባምነታቸው፣ በአርቆ አስተዋይነታቸው እንዲማርና እንዲኮራም ነው።…” ይላሉ። ደራሲ ማሞ ውድነህ በበኩላቸው፣ “እኔ ታሪካዊ ተውኔት የምጽፈው ለሦስት ዋና ዋና ጉዳዩች ነው። መጀመሪያ ታሪክን ለማስተማር ለመዘከር በአንድ ወቅት ታሪካዊ የሆኑ ግለሰቦችን ታሪክ መዝኖ በክብር ማስቀመጥ ሲሆን፤ ሁለተኛ ደረጃ ብሔራዊ ስሜትን ለማጠንከርና አዲሱን ትውልድ በአገር ፍቅር ስሜት ለመሙላት ኢትዮጵያዊነትን ለማስረፅ ሲሆን በሦስተኝነት ለጥበቡ ማለትም ለቲያትሩ አንዳች አበርክቶትና አስተዋጽዖ ለማድረግ” በማለት ታሪካዊ ቲያትር የሚሠሩበትን ምክንያትና ዓላማ ያስቀምጣሉ።


እያንዳንዱ ዘመንና ትውልድ የራሱ ታሪክ አለው። አሁን ያለው ትውልድ ያለፈው ቅጥያ ነው። ያለፈውን በጎም ሆነ ክፉ ታሪክ የታሪክ መዛግብት ቢመዘግቡትም ሙዚቃ፣ ፊልም፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ስዕልና ቲያትር ደግሞ የሰውን ልጅ የፈጠራ ጥበብ በመጠቀም አሁን ላለው ትውልድ እንደየ ዘርፋቸው ይገልጹታል። ታሪካዊ ተውኔትም የቀደሙትን ለማሰብና ለመዘከር ብቻ ሳይሆን ጥበባዊ ለዛ ባለው መልኩ ከታሪክ ለመማር፣ ራስን ለማወቅ፣ በራስ ለመተማመን ባጠቃላይ የት ነበርን? ወዴት መሔድ እንፈልጋለን የሚለውን አመላካች ነው።


አድገዋል፤ በልጽገዋል የሚባሉት አገራትም ከራሳቸው ታሪክ አልፈው መላውን የሰው ልጅ ታሪክ በሥነ ጥበባቸው፣ በፊልሞቻቸው፣ በሥነ ጽሑፎቻቸውና ቲያትሮቻቸው በመጠበብ የሰውን ልጅ ይመረምራሉ። ለታሪክም ትልቅ ቦታ በመስጠት የአሁኑን ዘመን ካለፈው ዘመን አንፃር ይመረምራሉ፣ ወደፊትም ያለውን አርቀው ያዩበታል፣ ያሳዩበታል። ለዚህም ይረዳቸው ዘንድ በታሪክ ትልቅ ሥፍራ ያላቸውን ግለሰቦች የተለያየ ማንነታቸው ይተነትናሉ፣ ይመደረካሉ፣ ይተውናሉ። በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ላይ የተሠሩ ቲያትሮችና ፊልሞችን ብዛትና ዓይነት ማየት ለዚህ በቂ ማሳያ ነው። በአገራችን አንድ ሰው ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ ብቻ በሦስት የተለያዩ ደራሲያንና ወቅቶች፣ በሦስት ቲያትር፣ በአራት እሳቸውን ሆነው የተወኑ ተዋንያን ተሠርተው እናገኛልን። ከዚህም በላይ ለሳቸውም ሆነ ለሌሎች የታሪክ ባለቤቶች በሁሉም የጥበብ ዘርፎች ብዙ ሊሠራላቸው በተገባ ነበር።

 

ታሪካዊ ተውኔቶቻችን ምን ላይ ናቸው?


ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስን እንደ አብነት


በታሪካዊው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር ቤት የተመልካች መግቢያ በር በኩል ወደ ትያትር ቤቱ ሲገቡ የቀደሙ ቲያትሮችን በመጠኑ የሚያስቃኙ ፎቶግራፎች ተለጥፈው ያገኛሉ። ከነዚህ ፎቶግራፎች ውስጥ “ዐፄ ቴዎድሮስን ሆነው የተወኑ” በሚል ርዕስ የመኮንን አበበ፣ የሃይማኖት ዓለሙ፣ የፍቃዱ ተክለ ማሪያም እና የሱራፌል ተካ ፎቶዎች ይገኛሉ። እኒህን ታላቅ ጀግና መሠረት ያደረጉ ሦስት ቲያትሮች ማለትም በግርማቸው ተክለ ሐዋርያት “ቴዎድሮስ ታሪካዊ ድራማ”፣ በፀጋዬ ገብረመድኅን “ቴዎድሮስ” እና በጌትነት እንየው “የቴዎድሮስ ራዕይ” የተሰኙ የመድረክ ሥራዎች ተሠርተው ለመድረክ ቀርበዋል። ከላይ ቲያትር ቤቱ ፎቷቸውን የሰቀለላቸው ተዋንያንም በነዚህ ተውኔቶች ላይ የተወኑ ናቸው።


ተስፋዬ እሸቱ ባቀረበው ጥናት መሠረት አቶ አመረ ይሁን የተባሉ አጥኝ፣ “ቴዎድሮስ በልዩ ልዩ ደራሲያን ዓይን” የተባለውን ጥናታቸውን ጠቅሶ ሲናገር “ዐፄ ቴዎድሮስ በግርማቸው ‹ቴዎድሮስ ታሪካዊ ድራማ› ውስጥ እንደቅርጫ የተበታተነችው ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ከሽፍትነታቸው እስከ በጀግንነት ነግሠው፣ የነበረውን ኋላ ቀር አስተሳሰብ ለመለወጥ ደፋ ቀና ሲሉ ተቀባይ በማጣታቸው ሕልማቸውን እውን ሳያደርጉ ያሳለፉትን ሕይወት መሥመር የሚያሳይ ነው” ይልና ፀጋዬ ገብረመድኅን ‹ቴዎድሮስ› ባለው ተውኔቱ የሚነግረንን ደግሞ እንዲህ ይነግረናል “ዐፄ ቴዎድሮስ የአገራቸውን የአንድነት መንገድ ለመቀየስ ከባድ መስዋዕትነት የከፈሉ፣ በአገሪቱ በተለይም በጎጃም፣ በጎንደር፣ በወሎ፣ በትግራይ አስተዳዳሪዎች ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ በችግር ውስጥ ለነበረው ለታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ተቆርቋሪነታቸውን ያሳዩ፣ በወቅቱም ሆነ አሁን በአርኣያነት ሊጠቀሱ የሚችሉ መሪ” ይላቸዋል።


ብዙዎቹ የትያትር ባለሙያዎች እንደሚስማሙበት የዐፄ ቴዎድሮስ የሕይወት ታሪክ ለድራማና ተውኔት የተመቸ ነው ይላሉ። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም ተፈሪ ዓለሙ በታሪካዊ ተውኔቶች መጽሐፍ መግቢያ ላይ “ከአገራችን ታሪካዊ ስብዕናዎች ውስጥ እንደ ዐፄ ቴዎድሮስ የተጻፈለት፣ የተዘመረለት፣ የተሳለለት ወዘተ. ማንም የለም። እንዲህ ለየዘርፉ የጥበብ ሰዎች የፈጠራ ምናብ የሆነው የቴዎድሮስ አነሳስ የሕይወት ውጣ ውረድ በኋላም አወዳደቅ ድራማቲክ መሆኑም ሊሆን ይችላል፤” ያለው። ምንም እንኳን ታሪካቸው ለተውኔትና ለፈጠራ ሥራ አመች የሆነ ታሪክ ቢሆንም እንደ ሌሎቹ የአገራችን ታሪኮች ሁሉ ትያትር ቤቶቹም ሆኑ ሙያተኞች በበቂ ተርከውታል ማለት ግን አይቻልም።


ለአገራችን ቲያትር ቤቶች ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች ሲናገሩ፣ በቲያትር ቤቶቻችን በሕግና በደንብ የተሰጠ በሚመስል መልኩ ታሪካዊ ተውኔቶች በአስር ዓመት አንዴ ነው የሚሠሩት። ምንም እንኳን ከተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች በተለያዩ ታሪካዊ ሁነቶች ላይ ተመሥርተው ታሪካዊ ተውኔት እንዲሠሩላቸው ጥያቄዎች ቢቀርቡም ከሚመለከታቸው አካላት ግን በቂ ትኩረት እንደማይሰጥ ይናገራሉ። ‹የቴዎድሮስ ራዕይ› ትያትር “በበጀት እጥረት” መውረዱንም እንደ አስረጅ ያቀርባሉ። ‹የቃቄ ውርድወት› ከዐሥር ዓመት አንዴ በብዙ ልፋትና ድካም የመጣች አሁን መድረክ ላይ ያለች ብቸኛ ታሪካዊ ተውኔት ናት።


ሳሙኤል ተስፋዬ በብሔራዊ ቲያትር ‹ሊትራሪ ማኔጀር› ነው። ሳሙኤል ታሪካዊ ትያትሮች ስላላቸው ፋይዳ ሲናገር “ታሪካዊ ትያትሮች የአንድ አገር ሁለንተና የሚንፀባረቅባቸው፣ ለመጭው ትውልድ ስለ አገሩና ስለ ታሪኩ እንዲያውቅ የሚደረግበት ሁነኛ መንገድ ነው” ይላል። ነገር ግን ይላል ሳሙኤል “ይኼን ያህል ትልቅ ፋይዳ ያለውን ነገርና ባለ ብዙ ታሪክ የሆነች አገር በሚባልላት ኢትዮጵያ ውስጥ ለታሪካዊ ቲያትር የሚሰጠው ዋጋና ትኩረት እጅግ አናሳ ነው፤” ይልና በግብፅ አገር በዓባይ ዳርቻ በየዓመቱ ስለሚካሔድ ‹አይዳ ኦፔራ› ሲናገር “ግብፆች በየዓመቱ የሚያካሒዱትና በአሁኑ ሰዓት የቱሪስት መስህብ መሆን የቻለ ‹አይዳ ኦፔራ› የሚባል ትርዒት አላቸው። ይኽ ኦፔራ አይዳ ስለተባለች ሴት ንግሥት የሚተርክ ሲሆን በኢትዮጵያና ግብፅ መካከል በአባይ ወንዝ ምክንያት ስለተካሔደ ጦርነት የሚተርክ ነው። ታሪኩ የኢትዮጵያ ነው። ግብፆች ግን ከመላው ዓለም በመጡ ታዋቂ አቀናባሪዎች ይኼን ታሪክ የራሳቸው አድርገው አስደናቂ የኦፔራ ትርዒት በማደረግ ታሪኩን በራሳቸው መንገድ በየዓመቱ ይዘክራሉ፤” በማለት ምን ያህል ሌሎች ታሪካዊ ተውኔትን ትልቅ ቦታ እንደሚሰጡትና ለብሔራዊ ማንነታቸውና ለኅልውናቸው መሠረት አድርገው እንደሚጠቀሙበት በቁጭት ያስረዳል።


የአገራችን የጥበብ ቤቶች ቋሚና ወጥ የአገራቸውን ታሪክና ትውፊት ነፀብራቅ የሆነ ተቋም ማቆም ቀርቶ ታሪካችንንና ትውፊታችንን የሚያሳዩና ለብሔራዊ ማንነታችን የሚጠቅሙ ረብ ያላቸውን ትዕይንቶች ማቅረብ አልቻሉም። ‹የቴዎድሮስ ራዕይ› ቲያትርን “በጀት የለም” በሚል ሰበብ ከመድረክ መውረዱ አንዱ ለታሪካዊ ተውኔት የምንሰጠው ዋጋ ዝቅተኝነት ማሳያ ነው። እርግጥ ነው ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት ታሪካዊ ተውኔቶች ብዙ የሰው ኃይልና መገልገያ ቁሳቁስ ስለሚጠቀሙ ከፍ ያለ በጀት ይጠይቃሉ። በየትኛውም ዓለም እንደዚህ ዓይነት አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ተውኔቶች በመንግሥት በጀት ድጋፍ ነው ሚንቀሳቀሱት። ‹የአገር ፍቅር እና የብሔራዊ ትያትር ተብለው የተሰየሙ ትያትር ቤቶች የአገርን ፍቅርና የብሔራዊ ማንነት ተልዕኳቸውን ታሪካዊ ቲያትሮችን በበጀት ሥም እየከለከሉ እንዴት ነው የሚወጡት?› ብሎ መጠየቅ ብልሕነት ነው።

 

ምን ይደረግ?


ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ በታሪክ ብዙ የተባለላቸው፣ የአስደናቂ ታሪክ ባለቤት፣ የአልበገር ባይነት ተምሳሌት፣ ዘመናዊትና አንዲት ኢትዮጵያን ለመመሥረት የታተሩ ታላቅ ንጉሥ ነበሩ። እኒህን መልከ ብዙ ጀግና እና የአንድ ሰው ተምሳሌት የሆኑ ንጉሥ መሠረት አድርጎ ድርሰት መጻፍ፣ ስዕል መሳል፣ ትያትር መሥራት የሚያጓጓ ነው። ለዚህም ይመስላል ከሌሎች ታሪኮች በተለየ ብዙ የተባለላቸውና የተተረከላቸው።


ሕይወት እምሻው በማኅበራዊ ድረገጾች ቁምነገር አዘል መጣጥፎችን በማቅረብ ትታወቃለች። በጌትነት እንየው የተደረሰውን ‹የቴዎድሮስ ራዕይ› ቲያትር ከተመለከተች በኋላ የተሰማትን በፌስቡክ ገጽዋ ካሰፈረች በኋላ ዘመኑ ያፈራቸውን ወጣቶች ተመልክታ እንዲህ ብላለች፡- “…በትያትሩ ላይ ያለኝን አስተያየት ለመወሰን በሐሳብ በምንገላታበት ሰዐት፣ ከጀርባዬ ስድስት ሆነው በእቴጌ ተዋበች ሞት የሚሳለቁ፣ በዘመነ መሳፍንት ታሪክ የሚዝናኑ፣ በመቅደላ ስንብት ትዕይንት በሳቅ የሚንተከተኩ ልጆች ይበልጥ ግራ አጋቡኝ። የሮማንቲክ ኮሜዲ ፊልም ውጤቶች ናቸው። እጅ አልሰጥም ብሎ ራሱን ባጠፋ ንጉሡ ታሪክ የሚሳለቅ ‹እጅ ሰጥቶ የጠፋው› ትውልድ አባላት ናቸው፤” በማለት ዘመኑ ያፈራቸውን ወጣቶች ትገልጻለች።


‹ታሪኩን በአግባቡ በትያትሮቹ፤ በፊልሞቹና በሥነ ጽሑፎቹ ለመታደም ያልቻለ ትውልድ መጨረሻው በራሱ ታሪክ መሳለቅ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠለ የዳግማዊ ዐፄ ታድሮስን ሥም የማያውቅ ትውልድ መምጣቱ አይቀሬ ነው። ለዚህም መፍትሔ ያሻዋል። የአገሪቱን ታሪክ መርምሮ ታላላቅ ታሪካዊ ተውኔቶች እንዲሠሩ ቲያትር ቤቶች ከትያትር ደራሲያን ጋር ተቀራርበውና ተነጋግረው መሥራት ይጠበቅባቸዋል› ይላሉ፣ ከቲያትር ቤቶች ጋር ቅርበት ያላቸው አንድ ባለሙያ።


ሳሙኤል ተስፋዬ በመሠረታዊነት ሦስት አካላት ኃላፊነት አለባቸው ይላል። የመጀመሪያው ባለሙያው ነው የሚለው ሳሙኤል “ባለሙያው ሙያው ውስጥ እስካለ ድረስ የአንበሳውን ድረሻ መውሰድ አለበት ባይ ነው። ሌሎች አካላት የቲያትር ጉዳይ ምናልባትም ሁለተኛና ሦስተኛ ጉዳያቸው ነው። በኹለተኛነት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተለይም የዩኒቨርሲቲዎች ቲያትርና ጥበባት ትምህርት ክፍል ለታሪካዊ ተውኔት ትልቅ ትኩረት ሰጥተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ሦስተኛ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ከላይ ከተጠቀሱት ባልተናነሰ ለታሪካዊ ተውኔት ትኩረትና ድጋፍ መስጠት ይገባቸዋል፤” ይላል።


ታሪካችንን ባግባቡ ሰንደንና ተርከን ለቀጣዩ ትውልድ ማድረስ ካልቻልን ተምሳሌት የሚሆኑንን ጀግኖች ብቻ ሳይሆን ማንነታችንን ሊያሳጣን ይችላል። እንደ ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ ያሉ ጀግኖችን በብዙ መልኩ በመተረክ ትውልዱ ሰለቀደሙ አባቶቹ እንዲያውቅ ማድረግ ተቀዳሚ ተግባር ይመስለኛል። የራሳችንን ታሪክ፣ ወግና ባሕል ባግባቡ ሳንተርክና የሚታዩበት ሁኔታ ሳናመቻች ዘመኑ በሚያመጣቸው የሌሎች አገሮች ባሕል ፊልሞች ወጣቱ ቢመሰጥና ቢወሰድ ሊገርመንም ልንፈርድበት አይገባም።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
7695 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 684 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us