ድብቅ ዕውቀት ወይስ ድብቅ ጥበብ

Wednesday, 11 April 2018 14:46

በጥበቡ በለጠ

 

በአንድ ወቅት ተማሪዎች ሳለን፣ አንድ ጓደኛችን “ጥንቆላም እንደ ጥበብ” በሚል ርዕስ የጥናት ወረቀት ለማዘጋጀት ይፈልጋል። ከዚያም አበረታታነውና ስራውን ጀመረ። በወቅቱም ርዕሰ ጉዳዩ ደስ እንዳለውና ብዙም ያልተዳሰሰ በመሆኑ ስሜቱን እያነሳሳው መሆኑን ሲገልፅልን ሰነባበተ። በኋላ ደግሞ ‘ኧረገኝ! የገባሁበት ጣጣ እንዲህ በቀላሉ የሚወጣበት አይደለም ትንሽ ቆይቼ እኔው እራሴጋ አስጠንቋዮች ሳይመጡ አይቀሩም' እያለ ይናገር ነበር።


ቀናት እየገፉ መጡ። የጓደኛችንም ጥናት ጥልቀትና ስፋት እያገኘ መጣ። የጥናቱን መጠነ-ርዕይ (scop) መወሰን ሁሉ ተሳነው። ከየት ጀምሮ የቱጋ ያቁመው? ችግር ተፈጠረ። ጥንቆላ ሲባል ምን ማለት ነው? የጥንቆላ አይነቶች ብዛትና ልዩታቸውን ፈትሾ ማግኘቱ በራሱ ውጣ ውረድ ያለበት ነው። በቡና ሲኒ አተላ እየተመለከተ ከሚጠነቁለው ጀምሮ አቴቴ፣ ፈጫሳ አዘጋጅቶ ዛሩ ተነስቶ ያዙኝ ልቀቁኝ ብሎ ተወራጭቶ አንተ እንዲህ ነህ፣ አንቺ ወዲያ ነሽ እያለ ከሚናገረው አልፎ ታላላቅ መንግሥታዊ ለውጦችንና እንቅስቃሴዎችን ጨምሮ መፃኢውን ዘመን የሚተነትኑ ጠንቋዮች መኖራቸውን እየደረሰበት መጣ ጓደኛችን። የቱጋ ሄዶ የቱጋ ይቅር? ብቻ በዚያን ወቅት 25 ገጽ የምትሆን ጥናት አቀረበ። ነገር ግን በመፅሐፍ መልክ ለማሳተም በመፈለጉ ዛሬም ድረስ ጥናቱ ተጠናቆ አልቀረበም።


እንግዲህ ይህን ሰፊ ክፍል ነው ትንሽ ለመነካካት የምሞክረው። ጥንቆላ ለምን ተነሳ? ለምን ሽፋን ተሰጠው ብለው ቡራ ከረዩ የሚሉ ወይም የሚከፋቸው ሰዎች ካሉ ብንነጋገርበት ሀጢያት የለውም ነው መልሴ። አብሮን እየኖረ፣ በየአካባቢያችን እየተተገበረ የየዕለት አጀንዳችንም ባይሆን ከልጅ እስከ አዋቂ የሚያውቀው ጉዳይ በመሆኑ እስኪ የምናውቀውን እንጨዋወት ብዬ ነው።


የስነ-ዕምነት ተመራማሪዎች እንደሚገልፁት ከሆነ በዓለም ላይ እምነት የሌለው ሰው ማግኘት አይቻልም ይላሉ። እያንዳንዱ ሰው አማኝ ነው፣ በምንም ነገር ቢሆን ያምናል ሲሉ ይሟገታሉ። በተለይም 'ፓጋን' የሚለውን ቃል ሲያብራሩ ሃይማኖት የሌለው ሰው ማለት አይደለም ብለው ምላሽ ይሰጣሉ። ፓጋን ክርስቲያን፣ ሙስሊም፣ ቡዱሂስት ላይሆን ይችላል። ወጥ የሆነም እምነት የለውም። ግን እንደየሰው እና ባህሪው የሚያምነው ነገር አለ ይላሉ።


የክርስትናው እምነት በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ በመጣበት ዘመን ላይ በአባይ በጠንቋይ ማመን ደግሞ እየከሰመ መሄዱ የሚታወቅ ነው። እንደገና ደግሞ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ብቅ ሲል ሲስፋፋም ኖሯል ጥንቆላ። በተለይም ደግሞ ዓለም በሶሻሊስትና በካፒታሊስት ካምፕ ተከፍላ ስትቀመጥ ሶሻሊስቱ ቡድን ለማንኛውም እምነት በሩን ክፍት ስላላደረገ ክርስትናውም ሆነ ሌላው አምልኮ የተዳከሙበት ወቅት ሆኖ አልፏል። ምክንያቱም የሶሻሊስቱ ቡድን በተጨባጭ ነገሮች አምናለሁ ስለሚልና እምነቶች ደግሞ በሀሳብ ላይ በማተኮራቸው ነው። ዛሬ የሶሻሊስቱ ካምፕ ሲፈራርስ የእምነት ነፃነቶች በሁሉም አካባቢዎች ይፋ ሆነው ታወጁ።


ወደኋላ መለስ ብለን የሀገራችንን ገጽታ በዘመነ ደርግ ላይ ብናየው ለየት ያለ ክስተቶችን ማስታወስ እንችላለን። በደርግ ዘመን ጠንቋይ ቤት የተገኙ ሰዎች ይታሰራሉ። በፖሊስ እንግልት ይደርስባቸዋል። ከፍተኛ ሀጢያትም እንደሰሩ ተደርጐ ይወራ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ጉዳዩ አጉል አምልኮ ተደርጐ ይወሰድ ነበር። የተፅእኖ በትሩ ከመንግስት ብቻ አልነበረም የሚሰነዘረው። እንዲያውም የክርስትናው እምነት ተከታዮችም ዋነኛው የተቃውሞ ኃይሎች ናቸው ጥንቆላ ላይ።


እንዲህ እንዲህ እያለ 1983 ዓ.ም ላይ ተደረሰ። ሌላኛው ያልታሰበ ሀሳብ ብቅ አለ። በወቅቱ በነበረው የሽግግር መንግሥት ላይ ኢትዮጵያ ከዛሬ ጀምሮ የእምነት፣ ሀሳብን የመግለፅ፣ የመሰብሰብ… ነፃነቶች መከበራቸው ታወጀ። የፕሬስ ነፃነት ታወጀ። በወቅቱ ብቅ ያሉት ጋዜጦችና መፅሄቶች የፍቅር ወይም ደግሞ ወሲብን የሚያነቃቁ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ሆኑ። አንዳንዶቹ ልቅ የሆኑ ድርጊቶችና ሀፍረተ ስጋን ሁሉ እስከማሳየት የደረሱ ነበሩ።


በሶሻሊዝም የክልከላ እና የእገዳ ደንቦች ታሽጐ የቆየ የወጣት አእምሮ ምንም አይነት የእድገት ወይም የሽግግር ባህሎችን ሳይለምድ ከወሲቡ ዓለም ጋር ወሬ ጀመረ። የጋዜጦቹ፣ የመፅሄቶቹ የሽያጭ ጣሪያ በሳምንት 50 እና 60 ሺ ቅጂ መድረሱን በሚገባ አስታውሳለሁ። ከዚሁ ጋር ተዳብሎ አንድ ነገርም መጣ። ኮከብ ቆጠራ።


የኮከብ ቆጠራ አምዶች በዝርዝር መቅረብ ጀመሩ። ኤሪስ፣ አኳየርስ፣ ሊዮ፣ ጄሚኒ ወዘተ… እየተጠቀሱ የትውልድ ወርና ቀን ላይ እየተገናዘቡ ትንታኔ ይሰጥ ጀመር። በኮከቡ ትንበያ መሠረት በዚህ ሳምንት ከቤት አትውጣ የሚል ፅሁፍ ካለ የማይወጡ ሰዎች ሁሉ ነበሩ። የትዳር ጓደኛዎን የሚያገኙበት ሣምንት ነው። ስለዚህ ቀይ ልብስ ይልበሱ ወይም አዘወትሩ የሚሉ ፅሁፎች በከዋክብት አምድ ላይ ወጥተዋል። አያሌ ወገኖቻችን የቻይናን አብዮት መስለው ቀይ በቀይ ሆነው በአዲስ አበባ ጉዳናዎች ላይ ፈሰዋል። ስንቶቹ የትዳር አጋሮቻቸውን አግኝተው እንደሆነ አላውቅም።


ኮከብ ቆጠራ ሳይንስ ነው ተብሎ ትንታኔ የሚሰጡ አዋቂዎችም ብቅ ብቅ አሉ። በሰለጠነው ዓለምም በስፋት የሚሰራበት ነው እያሉ ያስተማሩን ነበሩ። በሀገራችንም የእምነት ሰዎች ዘንድ በጥልቀት የሚሰራበት ነው ሲሉ አስረዱን። ሁለት ሰዎች ሊጋቡ በሚወስኑት ጊዜ ኮከብ ቆጣሪ ዘንድ በግላቸው ወይም አንድ ላይ ሆነው ይሄዳሉ። ኮከብ ቆጣሪው የትወልድ ቀንና ወር ይወስዳል። ቀጥሎ የእናት ስም ከነአያት ይቀበላል። እሱ ሳይንስ ነው በሚለው ዘዴ ቃላትንና ፊደላትን እንደ ካርታ ጨዋታ በውዞ፣ ነቃቅሎ፣ በታትኖ እንደገና ገጣጥሞ የወደፊት ዕጣ ፈንታቸውን ያስረዳቸዋል። ጋብቻቸው የተባረከ ወይም ፈራሽ መሆኑን ይነግራቸዋል። አልያም ደግሞ ትወልዳላችሁ ትከብራላችሁ ብሎ ይተነትናል። ካልሆነ ደግሞ አንተ ወይም አንቺ እድሜ የላችሁም ብሎ ከመርዶ ያልተናነሰ ቃል ይበትናል። እነዚህን በመሳሰሉ አገላለጾች የስንቱ ቤት ምድጃ እንደቆመ ወይም እንደፈረሰ ለማወቅ ማጥናት ይጠይቃል።


አንድ ወዳጄ ለእናቱ የትዳር ጓደኛዬ ናት ወደፊት የማገባት እሷ ናት ብሎ እጮኛውን ያስተዋውቃቸዋል። እናትም ያንተን ታላላቆችም ትዳር ያቆምኩት ከኮከብ ቆጣሪ ጋር እየተማከርኩ ነው ብለው ደንበኛቸውጋ ይሄዳሉ። ሲመጡም ለልጃቸው ታላቁን አስደንጋጭ ዜና ይለቁበታል። ከተጋባችሁ ከሁለት አንዳችሁ ትሞታላችሁ። እኔ ደግሞ አንተ እንድትሞትብኝ አልፈልግም። እናም ግንኙነትህን እዚህ ላይ በጥስ ይሉታል። ልጁም አመዱ ቡን አለ። ለስንት ጊዜያት በፍቅርና በደስታ አብሯት የቆየውን እጮኛውን ልቀቅ አሉት። ገና ወደፊት ሊያጣጥመው በዝግጅት ላይ የሚገኘውን ህይወቱን ፍቅረኛውን ትተህ ቁጭ በል አሉት።


እምቢ እማዬ ይሄ ነገር እንዴት ሊሆን ይችላል ብሎ የተቃውሞ ምላሽ ሰጠ። እናት አለቀሱ። ልጄ በጡቴ ይዤሀለሁ። ባጠባሁህ ጡቴ እለምንሀለሁ፤ አትሙትብኝ አሉት። ሀይለኛ ጥያቄ ነው። ምን ያድርግ? ሞትና ፍቅረኛው አንድ ላይ ሆነው እናቱ በሌላ ጐን ቆመው ማንን ይምረጥ? ቢቸግረው አንድ ነገር ላይ ወሰነ። በመጨረሻም ኢትዮጵያን ጥሎ ጠፋ። ዛሬ አሜሪካን ሀገር በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ ነው።


እንዲህ አይነት እምነቶች በየትኛው ጐን ተቀባይነትን ያገኛሉ። የሞቀ ቤት እያፈረሱ ለዘመናት ቆይተዋል። ገንብተዋልም ሊባል ይችላል። ነገር ግን ዘመን እየሰለጠነ ሲሄድ እነርሱም ይከስማሉ የሚሉ የስነ ልቦና ባለሙያዎች አሉ። ሰለጠነ በሚባለው ዓለም ውስጥ እምብዛም አይታዩም ብለው ሃሳብ ይሰጣሉ።


ጥንቆላ ጥበብ ነው ብለው የሚነሱ ደግሞ አሉ። እንዲያውም “ክዋኔውን በተግባር የምናየው እምነት ቢሆን ጥንቆላ ነው” ብለው ትንሽ የንግግር ነፃነት በተገኘበት ጊዜ ሁሉ ብዕራቸውን አሹለው የተነሱ ፀሐፊዎች አሉ።


ለጊዜው ትክክለኛ ቀኑን የማላስታውሰው በ1960ዎቹ ውስጥ በታተመው መነን መጽሄት ላይ ጥንቆላን ብዙ ገሸሽ አናድርገው፤ እንደ ጥበብም እንውሰደው ብሎ አንድ ታዋቂ መጣጥፍ አቅራቢ ሰው ሙግት ይዘው ነበር። ፀሀፊው እንደሚሉት አእምሮአችንን ዝግ አናድረገው፣ የነዚህን የጠንቋዩቹን ችሎትም ማጣጣም መቻል አለብን ይላሉ።


እርሳቸው ሃሳባቸውን ማጠንከሪያ ይሆነኛል ብለው አንድ ምሳሌ ሰጥተዋል። ይህን ምሳሌ ደግሞ ያገኙት እውነተኛ ምንጭ ነው ብለው ከሚያምኑበት ሰው ነው። ጉዳዩን እንዲህ አቅርበውታል።


አንድ ወጣት አንዲትን ሴት ያፈቅራል። ሊቀራረባት ይፈልጋል። ነገር ግን አልሆንለት ይላል። አንዳንዴ ይፈራታል። የልቡን እንዴት ይንገራት። ገና ሲያስበው ልቡ ድለቃዋን ትቀጥላለች። እጁ ላብ በላብ ይሆናል። ታዲያ ከዚህ ስቃይ ይገላግለኝ ብሎ አንድ ጠንቋይ ቤት አዋቂ ቤት ይሄዳል። እየደረሰበት ያለውን ችግር ሁሉ ዝርግፍ አድርጐ ለጠንቋዩ ያስረዳል። ጠንቋዩም ይሄን ሁሉ ከሰማ በኋላ ለወጣቱ መላ ለመዘየድ አንድ የቤት ስራ ይሰጠዋል። ይሄ የቤት ስራም ያቺ ያፈቀራትን ልጅ ፀጉር ከየትም ብሎ ጠንቋዩ ዘንድ እንዲያመጣ፣ ከዚያም ችግሩ ሁሉ እንደሚፈታ ያበስርለታል።


ወጣቱም ደስ ብሎት ከጠንቁዩ ቤት ይወጣል። የታዘዘውንም ጉዳይ ሊፈፅም መንቀሳቀስ ይጀምራል። ያፈቀራትን ልጅ ፁጉር ከየት ያምጣ። ፀጉሯጋ ቢደርስ ኖሮ ጠንቁይ ቤትም ባልሄደ ነበር። ሄዶ ነጭቷት አያመጣ ነገር ወንጀል ነው። እቤቷ አይሄድ ነገር እሱም የሚቻል አልሆን አለ። ፀጉሯ ከየት ይምጣ? ሲጨንቀው ሲጠበብ ጊዜ እሱ ቤት ከተነጠፈው ቁርበት ላይ ያለው” ፀጉር ነጭቶ ወደ ጠንቋዩ ቤት ይሄዳል። ለጠንቋዩም ይሄው ፀጉሯ ብሎ ይሰጠዋል።


ጠንቋዩም ለቀናት ያንን ፀጉር ይዞ ይደግምበታል። አዲስ ነገር ጠፋ። በመጨረሻ ግን ጠንቋዩ ቤት ደጃፍ ፀጉሩ የተነጨበት ቁርበት ተገኘ ተብሎ ተፅፏል።
በርግጥ እንዲህ አይነት ሁኔታዎች ይፈጠራሉ ብሎ ለማመን በጣም አስቸጋሪ ነው። ለመከራከሪያም ተብሎ የሚቀርብ ለዛና ወዝ ያለው ምሳሌም አይደለም።


በማህበረሰባችን ውስጥ ግን ይሄ ጥንቆላ የሚባለው ነገር ስር ሰዶ የቆየ መሆኑን ማንም የሚክደው አይደለም። ጥንቆላ ታላቅ ‘የመንፈስ ልዕልና' ነው የሚሉ ተከራካሪዎች በየጊዜው አጋጥመውኛል። እንዲያውም የፈጠራን ስብዕና ከዚያ ውስጥ ማግኘት ይቻል ነበር ይላሉ። ነገር ግን ጥንቆላን እንደ ነውርና እርኩስ ነገር አፈር ድሜ እያበላነው ስለመጣን ያንን መንፈሳዊ ልዕልና ልናገኝ አልቻልንም በማለት ይሟገታሉ። ምነው በኛ ሀገር ሳይንቲስቶች፣ ፈጣሪዎች ፈላስፋዎች ወዘተ. ጠፉ ሲባሉ እንዲህ አይነት ልዩ ችሎታ ያላቸው ሰዎች አዋቂዎች በማህበረሰቡ ዘንድ ቦታ ስለማይሰጣቸው ነው ብለውኛል። ነገሩ አጠያያቂ ነው።


ይሄ ‘መንፈሳዊ ልዕልና' ሲባል ክርስቲያናዊው አባባል አይደለም። ለነዚህኞቹ የመጣ ነው። ለዚህም ነው በቅንፍ ውስጥ የተቀመጠው። ይሄን መጣጥፍ ለማሰናዳት ስጣደፍ አንዳንድ ጥያቄዎችን ለቅርብ ወዳጆቼ አቅርቤ ነበር።


አንድ በእድሜው ትንሽ ገፋ ያለ ጓደኞዬን ስለ ጠንቁይ የምታውቀው እውነት ነው የምትለው ታሪክ አለ ወይ አልኩት።


“አዎ አለኝ” ብሎ መለሰ።
“ምንድን ነው?” አልኩት።
“የሙት መንፈስን ማነጋገር ታውቃለህ?” አለኝ፡
“አላውቅም”
“የሞተን ሰው የሚያነጋግሩ አሉ”
“በስመ አብ” አልኩት
“እውነቴን ነውኮ” አለኝ ኮስተር ብሎ።
“እንዴት?” አልኩት። መተረክ ጀመረ።


“አንድ የምናውቀው ሰው ሲነጋጋ መንገድ ላይ ሞቶ ተገኘ። የሞተበት ምክንያት ማጅራቱን ተመቶ ነው። ነገር ግን ማን እንደመታው ማረጋገጥ አልተቻለም። ፖሊስ ምርመራውን በየአቅጣጫው መቀጠል ተያያዘው። ተጠርጣሪዎች ሁሉ ተመረመሩ። ይሄ ነው የሚሉ ማስረጃዎች ጠፉ። ቀናት ቀናትን እየወለዱ ሄዱ። አመታትም መጡ። የሟች እናት የልጃቸው ገዳይ ባለመታወቁ ማቅ እንደለበሱ፣ አንዳዘኑ፣ እንዳለቀሱ ቆዩ። ሀዘናቸው እጅጉን ጠና። ታዲያ አንድ ቀን ዘመዳቸው ወሬ ይሰማና ሴትየዋጋ ይመጣል።


‘አክስቴ?'
‘አቤት'
‘የልጃችንን ገዳይ የሚነግርን ሰው አለ'
‘ማነው እሱ?'
‘የሙት መንፈስ የሚያነጋግር አዋቂ ነው'


በዚህ ጊዜ እናት ይደነግጣሉ። ለአመታት ሲያስቡት የነበረውን የልጃቸውን ገዳይ የሚያስረዳቸው ኃይል ካለ በደስታ እንደሚቀበሉት ለዘመዳቸው ይነግሩታል። ከዚያም ተያይዘው እዚያ የሙት መንፈስ ያነጋግራል የሚባልበት ሰው ዘንድ ይሄዳሉ። አካባቢው ገጠራማ እና በእግር ረጅም ርቀት የሚኬድበት ነው። የኋላ ኋላ ደረሱ።


የሟች እናት አሁን ክፉኛ አለቀሱ። ምነው? አላቸው የሙት መንፈስ አናጋሪው፡ የልጄን ገዳይ ማን እንደሆነ አጣሁት። ይሄው እንደተንከራተትኩ ባክኜ አለሁ። እባክዎትን ገዳዩን ይንገሩኝ አሉ። አይዝዎት ያገኙታል ብሎ ተስፋ ሰጣቸው። ጉድ ሊመጣ ነው።


“አንድ ቀን ጠንቁዩ የሟችን እናት ኑ ወደዚህ ይላቸዋል። ከዚያም ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸዋል። ማስጠንቀቂያው ደግሞ እንዲህ ይላል። ዛሬ ከልጅዎ መንፈስ ጋር ይገናኛሉ። የሚያገኙት ጨለማ ቤት ውስጥ ነው። ሲያገኙት ማልቀስ ወይም መጮህ ፈፅሞ አይፈቀድልዎትም። ይህን ካደረጉ መንፈሱ ይሰወራል። ልፋትዎ ሁሉ መና ይቀራል። የልጅዎን መንፈስ ካገኙ የፈለጉትን ነገር ማውራት ይችላሉ። አንጀትዎን ጠበቅ አድርገው ችለው ልጅዎን ያነጋግሩ” አላቸው። ጉዳዩ ያስፈራል።


እንዴት የሞተ ሰው፣ የተቀበረ ሰው መንፈሱ ተንስቶ ሊያወራ ይችላል። ከየትኛው ሳይንስ ወይም ፍልስፍና ጋር እንደሚገናኝ የስነ-ሃይማኖት ጠበብት ሊያስረዱን ይችላሉ። አሁን ግን የሙት መንፈስ አናጋሪውና የሟች እናት ቀጠሮ ሰዓት ደረሰ። ከምሽቱ 6 ሰዓት ሆነ። ሴትየዋን ጥቅጥቅ ያለ ጨለማ ቤት አስገባቸው። አይዞዎት የልጅዎ መንፈስ ሲመጣ ጠንከር ብለው አነጋግሩት ብሎ የመንፈስ መጥሪያ ቃላቱን ያነበንበው ጀመር። ከቆይታ በኋላ ዝም አለ። ፀጥታ ሆነ። በዚያ ፀጥታ ውስጥ እናት ድምፅ ሰሙ።


“እማዬ”
“አቤት ልጄ”
“ለምን ትንከራተቻለሽ?”
“ልጄ ምን ላድርግ? እንዲሁ እንደወጣህ ቀረህ። ማነው አንተን የገደለብኝ? ማነው ልጄን የቀማብኝ? ልጄ ተቃጠልኩ አረርኩ….”
“አይዞሽ ፅኑ ሁኚ። በቃ እድሜ ዘላለም አይኖር። መለያየት ያለ ነው።” አላቸው የልጃቸው ሙት መንፈስ።


“ገዳይክ ማነው ልጄ? ንገረኝ”
“አይዞሽ ገዳዬ ራሱ በቅርቡ ይሞታል። ጐረቤታችን ነው። አሁን ታሟል 15 ቀን አይቆይም” ይላቸዋል። የገዳዩንም ስም ይነግራቸዋል። ግን ወደ በቀል እንዳይገቡም እናቱን ተማፅኖ፣ ያ የሙት መንፈስ ይሰወራል።


ሴትየዋ የልጃቸው የራሱን ድምፅ ነው የሰማሁት የሚሉት። እንዳውም ልጃቸውን እንዳገኙት ሁሉ ነው የሚቆጥሩት። ያ የሙት መንፈስ ስለ ገዳዩ የነገራቸውም ታሪክ እውነት ነበር። ገዳይ የተባለው ሰው ታሞ ተኝቷል። እንደተባለውም 15 ቀን ሳይሞላው ሞተ። የሚገርመው ነገር ሰውዬው በህመም ምክንያት እስትንፋሱ አልወጣ ብላ በምታሰቃየው ወቅት የሰራቸውን ሃጢያቶች ሲናዘዝ ያንን ምስኪን ልጅ አድብቶ መግደሉን ተናግሮ ነበር። ይሄ የማውቀው እውነተኛ ታሪክ ነው ብሎ ወዳጄ አጫወተኝ።


አንዲት የቅርብ ጓደኛዬንም በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ የምታውቀውን እንድትነግረኝ ጠየኳት። ‘አንድ የማውቀው እውነት አለ' አለችኝ። ባክሽ አጫውችኝ አልኳት።


“ዘመኑ በደርግ ጊዜ ነው። ሰውየው የወታደር መኮንን ነው። ከሰሜን ጦር ግንባር አካባቢ ሄዶ ነበር። እናም እዚያ ሞተ ይባላል። መርዶም ለቤተሰቡ ይመጣል። ተረድተው ቁጭ ይላሉ። ወላጆች፣ ሚስት፣ ልጆች። ከወራት በኋላ መንግሥት ለቤተሰቡ የሟችን ጡረታ መቁረጥ ይጀምራል። ቤተሰቡም ጡረታ ይቀበላል። ታዲያ አንድ ቀን ድንገት አዋቂ ጠንቋይ ቤት ይሄዳሉ። ጠንቋዩንም ስለዚሁ የወታደር መኮንን አሟሟት ሁኔታ ይጠይቁታል። ጠንቋዩም፡-


‘አልሞተም' ይላቸዋል።
‘ምን!?' ይላሉ ቤተሰቦች ተጫጩኸው።
‘አይዟችሁ እሱ በህይወት አለ። አልሞተም'


‘እንዴ… ይኸው ሞቷል ተብለን ጡረታውን ሁሉ እየበላን ነው' ይሉታል። ምድር ቀውጢ ትሆናለች። የተስፋ ለቅሶ እንደገና ይራጩ ጀመር።


‘አይዟችሁ፤ ልጃችሁን በህይወት ታገኙታላችሁ። ይመጣል።' ይላቸዋል። ቤተሰቡም የተሰጠውን ተስፋ እውነተኛነት በጉጉት ሲጠብቅ አመት ሁለት አመት አለፈ። ኢህአዴግ ደርግን ጥሎ ስልጣን በሚይዝበት ጊዜ ያ ሞተ የተባለ ሰው ከተሰደደበት ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ከቤተሰቡ ጋር ተቀላቅሏል። ይሄ የማውቀው እውነት ነው” አለችኝ።


እነዚህን ክስተቶች እና ድርጊቶች በመመልከት ጥንቆላ ጥበብ ነው የሚሉት ሰዎች ድምፃቸው ከፍ ብሎ አይሰማ እንጂ አንዳንድ ነፃ ጨዋታ ላይ ሃሳቦቻቸውን ሰንዘር ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ እንዲህ አይነት ገጠመኞች የመኖራቸውን ያህል ደግሞ ውሸታም እና አጭበርባሪ ጠንቋዮች በጣም ብዙ ናቸው። ልጃገረዶችን እየወሰዱ ለሥጋዊ ፍላጐታቸው ማርኪያ በማድረግ ትልልቅ የወንጀል ተግባራትን የሚሠሩ ጠንቋዮች በየስርቻው ተደብቀው ይገኛሉ። መርዝ ቀምመው ባላንጣህን ወይም ባላጋራህን ይህን አጠጣው እያሉ የስንቱን ህይወት ባዶ ያስቀሩ ጠንቋዮች ዛሬም አሉ።


ሰላቢ ሆነው አንዱ ያፈራውን ሀብትና ንብረት ወደ እነሱ እንዲዞር በውድቅት ሌሊት በየሰው ደጃፍ እርቃናቸውን የሚንከባለሉ አሉ እየተባለ ከአመታት በፊት ይወራ ነበር። በመንከባለል የአንዱ ሀብት ወደ ሌላው ሊዘዋወር? እንዴት ይሆናል? ግን ሆኗል ይላሉ። መጨረሻውም አያምርም በማለት ተቃዋሚዎቹ ይገልፃሉ።


ከአንድ ሰው ጋር ቢጣሉ ደግሞ ማታ ላይ የሰውዬው ቤት ቆርቆሮ ላይ የድንጋይ ናዳ ሲወርድ እንዲያድር የሚያደርጉ ጠንቋዮችም አሉ ይባላል። ይሄኛው ደግሞ አንደርቢ በመባል የሚታወቅ ነው። ይሄንንም ብዙዎች ተደርጓል ብለው የሚያምኑበት ነው።


ሌላው የዘመናችን አሳሳች ድርጊት ‘መሲህ' ነን እያሉ የሚመጡት አሳሳቾች ናቸው። አሁን በቅርቡ እንኳን የዛሬ አስር አመት ከናይሮቢ ወጣ ብላ በምትገኝ መንደር ውስጥ ‘እኔ እግዚአብሔር ነኝ፣ እየሱስ ክርስቶስም ልጄ ነው' እያለ የሚዘባርቀው ዋንዮ ዛሬም አለ። ተከታዮችንም እያፈራ ነው። ነገር ግን ዓለም አቀፋዊ ተግሳፅ እና ምክር ለኬኒያውያን እየተላከላቸው ነበር። ዋንዮን ተው በሉት እያሉ። እንዲህ አይነት ሰዎች ደግሞ ስርዓት የለሸ አወናባጆች ናቸው።


ዑጋንዳ ውስጥም ከአመታት በፊት እራስን የማጥፋት ከፍተኛ ሰበካ ተካሄዶ አያሌ ሰዎች ራሳቸውን በአንድ ቤት ውስጥ አስገብተው ያውም ‘የፀሎት ቤት' በሚባልበት ስፍራ ውስጥ ነዳጅ አርከፍክፈው ራሳቸውን አቃጥለዋል። ይሄም ታላቅ ወንጀል ነው።


ይህ ርዕሰ ጉዳይ ሰፊ ነው። የእምነት ጨዋታ ወይም ወሬ አያልቅም። አንድ ቦታ ላይ ካላሰርነው። ብቻ እንደ ሰው ሰከን ብለን ሁሉንም ነገር ማሰብ ይጠበቅብናል። ጭፍን ተቃዋሚዎች ወይም ጭፍን ደጋፊዎች መሆን የለብንም። ጥንቆላ ጥበብ ነው የሚሉት ሀሳባቸው ምንድን ነው ብለን መስማትና መመርመር አለብን። ተሳስተውም ከሆነ በሀሳብ እንሟገታቸው።


አያሌ ገጠመኞቻቸውን ያወጉኝ ሰዎች አሉ። አስገራሚ ሁኔታዎችን ሰምቼ ገረመኝ። በዚህ በጥንቆላ ዙሪያ ድብቅ ገበናዎች ሁሉ ገለጥ ብለው ቃለ መጠይቅ ላደርግላቸው እሺ ያሉኝም ታላላቅ ሰዎች አሉ። ሌላ ጊዜ አንስተን እንጫወታለን።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
7996 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1022 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us